Pages

Pages

Wednesday, January 15, 2025

የግሪክ አቴንሱ ''ኢትዮጵያዊው'' አውርቶ አዳሪው ''ዲያቆን'' እና ከጥንትም የኢትዮጵያ ጠላት የሆነው የ''አውርቶ አደር'' ማንነት



=============
የጉዳያችን ማስታወሻ
=============

ከጥንትም የኢትዮጵያ ጠላት የሆነው ''አውርቶ አደር'' ማንነት 

የኢትዮጵያ የታሪክ ስብራት ዋነኛዎቹ ምክንያቶች አውርቶ አደሮች ናቸው።ይህ አደር የሚለው የአማርኛችን ቃል ከፊት አንድ ቃል እያስከተለ ''አደር'' የሚለውን ቃል ብዙ ፍቺ ያሰጠዋል። ወቶአደር(ወታደር)፣ላብአደር፣ ሰርቶአደር፣ወዝአደር የሚሉትን ቃላት እናውቃቸዋለን። በስማቸው ያልጠራናቸው እና መጥራትም የሚገባን ''አውርቶአደር'' የሚባሉትን ነው።

ኢትዮጵያን ወደፊት ለማስፈንጠር የተጉቱ የቀደሙ የኢትዮጵያ ነገስታት፣ምሑራን፣ሃሳብ አመንጪ ዜጎችን ሁሉ አላሰራ ያለ አፉን በነጠላ ሸፍኖ አንዳች ፍሬ ነገር ሳይሰራ እያልጎመጎመ ሲያወራ ውሎ የሚያድረው አውርቶ አደር ነው። አፄ ቴዎድሮስ ከዘመናቸው ቀድመው የሚያስቡ መሪ ነበሩ።ሌላው ቀርቶ መጪው የሀገር መከላከያ በዘመናዊ መሳርያ ካልታገዘ ሃገር መጠበቅ አዳጋች መሆኑን ስላወቁ መድፍ እንዲሰራላቸው ትዕዛዝ ሲሰጡ፣አውርቶ አደር ያወራ ነበር።

ዳግማዊ ምንሊክ አውርቶ አደር ሳይሆኑ ሰርቶ አደር ነበሩ።ከዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ እስከ የትራንስፖርት ስራ፣ከአካባቢ ጥበቃ እስከ ዘመናዊ ጦር ማደራጀት፣ከስልክ እና መኪና ማስመጣት እስከ አብያተክርስቲያናት ግንባታ ሰርቶ አደር ነበሩ። አውርቶ አደሩ ግን በዘመናቸው ሰላም የነሳቸው ጊዜ በቀላሉ የሚቆጠር አልነበረም። በእያንዳንዱ ስራቸው አውርቶ አደር እየገባ ለሀገራቸው የሚሰሩትን ለማደናቀፍ ሲያወራ ውሎ ሲያወራ ያድር ነበር። ዳግማዊ ምንሊክ መኪና አስመጥተው የመጀመርያው ነጂ ሲሆኑ፣ሊገዝቱ የቃጡ ነበሩ። ሲኒማ ቤት ከፍተው ለሕዝብ ሲያሳዩ አውርቶ አደር ''የሰይጣን ቤት'' ብሎ ሲያወራ ዋለ። መጪው የታያቸው ዳግማዊ ምንሊክና እቴጌ ጣይቱ የመጀመርያውን ዘመናዊ ሆቴል ጣይቱ ከፍተው ንጉሱና ንግስቲቱ እየገቡ ሰውን ለማለማመድ ሲሞክሩ አውርቶ አደሩ ሴት እንዴት ሆቴል ገብታ ትበላለች? እያለ ይሳለቅ ነበር። አውርቶ አደር በየዘመኑ ነበር። በዘመናችንም ጨምሮ።

አሁን ባለንበት ዘመን አውርቶ አደር እንደቀድሞው አፉን በኩታ ሸፍኖ የሚንሾካሾክ ወይንም ጠላና ጠጅ ቀኑን ሙሉ እየጠጣ ሲያወራ የሚውል አይደለም። የማኅበራዊ ሚድያ ላይ ተጥዶ ለኢትዮጵያም ለወገኑም አንድ ሳይሰራለት ብቻ ሳይሆን የሚሰሩትን ሲያብጠለጥል ሲሳለቅ የሚውል  በአውርቶ አደርነቱ ደግሞ ዩቱብና ሌሎች የማኅበራዊ ሚድያ ተቋማት ገንዘብ ስጡኝ እያለ ሲማጸን የሚኖር ነው።

የዘመናችን አውርቶ አደር ከተማ ጸዳ፣መብራት ተተከለ ሲባል ሰርቶ አደሩ በሰራው የሚነቅፍበትን ሲያስብ ያድራል። የአድዋ ሙዜም ሊሰራ ነው ሲባል፣ የምንሊክን ሃውልትን ሊነቅሉት ነው ይላል፣ ይሄው አውርቶ አደር።ሃውልቱም ደምቆ ያልነበረ ሙዜም ተሰርቶ ሲያልቅ ደግሞ ሙዜም ከሚሰራ ይልና ሌላ ትረካ ይጀምራል።አውርቶ አደር ስራው አውርቶ ማደር ብቻ ስለሆነ ማመስገን ብሎ ነገር አያውቅም። ሌላው ቀርቶ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያልታደሰው የብሔራዊ ቤተመንግስ ሲታደስ፣ሸረሪት ያደራባቸው የሀገር ቅርሶች በወጉ ሲቀመጡ፣የሳይንስ ሙዜም ሲሰራ፣ግዙፍ ብሔራዊ መጻሕፍት ቤት ተሰርቶ ሲያልቅ፣የብሔራዊ መዛግብት መረጃ ማዕከል ሲሰራ፣የስቶክ ኤክስቸንጅ ማዕከል ስራ ሲጀምር፣የጎንደር አብያተ መንግስታት ታድሰው ከተማው ሲደምቅ ሳይቀር አውርቶ አደር አይኑን እያሸ ይመጣል። ያው እንደለመደው ለማውራት።

የዘመናችን አውርቶ አደሮች ምሳሌ እንጥቀስ ብንል እጅግ ብዙ ናቸው።ከአክቲቪስት ጀዋርን ብንወስድ አንዲት ጉድጓድ ውሃ ላላስቆፈረለት እና አንዲት ብርጭቆ ውሃ እንዲጠጣ ያላደረገውን የኦሮሞ ወንድሞቻችንን በአውርቶ አደርነት ነግዶ ጨርሶ አሁን በኢትዮጵያ ስም አውርቶ ለማደር እየሞከረ ነው። አውርቶ አደሮች እንዲህ ናቸው። ከአንዱ ጎራ ወደ ሌላ ለመዝለል ችግር የለባቸውም።በዩቱብ በአማራ ክልል ህዝብ የሚነግዱት አውርቶ አደሮች ለህዝቡ አንድ ቀን አንዲት ሳንቲም ልከው የአንድ ትምህርት ቤት መገልገያ የሚሆን አንዲት ቾክ አልላኩለትም። በስሙ አውርተው እያደሩ ግን በዩቱብ የልጆቻቸውን የትምሕርት ቤት ወጪ ይሸፍናሉ። የኢትዮጵያ ጉዳይ በሰርቶ አደሮች እና በአውርቶ አደሮች መሃል የሚደረግ ፍልምያ ነው። ህዝብ አውርቶ አደሮችን እየለየ ብቻ ሳይሆን እያራገፈ እና በስሜ አትነግዱ፣ከጫንቃዬ ውረዱ እያለ ነው።የኢትዮጵያ ሀገራዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ችግር ፈጣሪዎች አውርቶ አዳሪዎች ናቸው።በእዚህ ዘመን ''አውርቶ አደሮች'' እና ''ሰርቶ አደሮች'' ተለይተዋል።


=================////============

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን እዚህ ላይ ይስጡ