ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, November 14, 2023

በአጼ ቴዎድሮስ፣ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴና ኮ/ል መንግስቱ ላይ የሰራነውን የመሪዎቻችንን በጎ ሀሳብ የመጎተት ክፉ ባሕል በጠ/ሚ/ር ዐቢይ ላይ አንደግምም!


ፎቶ - አጼ ቴዎድሮስ፣አጼ ኃይለስላሴ፣ኮ/ል መንግስቱና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
  • ዛሬ አጼ ቴዎድሮስ፣ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ፣ ኮ/ል መንግስቱ እያልን ስንጣራ መሪዎቹን ክነበረ ህልማቸው በየዘመናቸው ያልጎተትን  ጨዋዎች እንመስላለን።
============
ጉዳያችን ምጥን
============

የመሪዎቻችንን በጎ ሀሳብ ጎታቾቹ እኛ!

ኢትዮጵያ በታሪኳ ድንቅ መሪዎች መርተዋታል። የመሪዎቿን አስደናቂነት እኛ ከጻፍነው በላይ በየዘመኑ ''ሰለጠኑ'' ከሚባሉ ሀገሮች የመጡ ጸሐፊዎች የጻፉት እና አድንቀው የገለጡበት መንገድ ይበልጣል። ድንቅ የተባሉ መሪዎቻችንን ርዕይ በመጎተት ወደፊት እንዳይሄዱ በማድረግ ግን የሚያክለን የለም።

አጼ ቴዎድሮስ

አጼ ቴዎድሮስ በቀድሞ ስማቸው ካሣ፣ከቋራ ምዕራብ ጎንደር ተነስተው የኢትዮጵያ ንጉሰነገስት ለመሆን ሲነሱ አንዱና ዋናው ዓላማቸው  በዘመኑ በዘመነ መሳፍንት ታውካ የነበረችው ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ እና ወደ የቀደመ ክብሯ መመለስ መሆኑን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ መናገራቸውን የታሪክ ድርሳናት ያሳዩናል። ንጉሱ ከነገሱ በኋላ በወረራ ውስጥ ያለች ኢየሩሳሌምን ገና ነጻ ያወጣሉ ተብሎ ይነገርላቸውም ነበር። ይህንንም አዝማሪ ሳይቀር
 '' ካሳ ብሎ ፈረስ ካሳ ብሎ ስም፣
    ዓርብ፣ዓርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም።''

እያለ የሚያበረታታቸው የመኖሩን ያህል፣ ሌት ተቀን እጁን በአፉ ላይ አድርጎ ሲያማ የሚውልም ነበር። ንጉሱ አይቻልም የሚሉት ነገር የለም።ኢትዮጵያ ከመላው ዓለም ጋር የነበራት ግንኙነት ከ16ኛው ክ/ዘመን በኋላ በጣም በተዳከመበት ዘመን የነበሩት ንጉስ ከአውሮፓ የሚመጡ ጥቂት ሰዎች ጋር በጥልቅ በመወያየት ስለ ቴክኖሎጂ በመረዳታቸው ሴቫስቶቮል የተሰኘ መድፍ ለማሰራት ጥረት ያደርጉ መሪ ናቸው። እኝህ የኢትዮጵያን አንድነት ከዘመነ መሳፍንት በኋላ ለመመለስ ህይወታቸውን ሰጥተው የታገሉ መሪ፣ኢትዮጵያን ከዘመኑ የቅኝ ገዢዎች በደከሙበት የአንድነት ትግል መሰረት የጣሉ እና ኢትዮጵያን ለማሻገር ቀን ከሌሊት ያለሙ መሪ በመጨረሻ ላይ እኛ ጎታቾቹ እንግሊዞች ሲወሯቸው መቅደላ ላይ ብቻቸውን አጋፍጠን፣ እራሳቸውን እንዲሰዉ ከማድረግ በላይ ልጃቸውና ባለቤታቸው ታግታ ስትወሰድ ያጀብን መሆናችንን ማሰብ አለብን። በወቅቱ ከንጉሱ በኢትዮጵያ ላይ ከነበራቸው ህልም ይልቅ የመንደር ቂጣ መጉደል ከትልቅ ነገር ወስደው በንጉሱ መሞት ላይ የፈነደቁ ነበሩ። የእኛ ታሪክ ለኢትዮጵያ ህልም የነበራቸውን መሪዎች እግር መጎተት የነበረ አሳፋሪ ታሪካችን ነው።

አጼ ኃይለሥላሴ 

አጼ ኃይለሥላሴን እግር የመጎተት ሥራ የተጀመረው ገና አባታቸው ራስ መኮንን የአጼ ምንሊክ ባለሟል ሆነው ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ የጀመረ ነው።አጼ ኃይለስላሴ ከአልጋወራሽነት ዘመናቸው በኋላ የጣልያን ጦር ተሸንፎ እንደወጣ የገጠማቸው የእግር ጉተታ ይህ ነው የሚባል አይደለም። ንጉሱ በሱዳን፣በኦሜድላ በኩል ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ጎጃም ላይ ከነበሩት አርበኞች ውስጥ በላይ ዘለቀ አንዱ ነበር። ንጉሱ በጎጃም በተዘጋጀ የእንኳን ደህና መጡ ሰልፍ ላይ አርበኞች በንጉሱ ፊት ሰላምታ እያቀረቡ ሲያልፉ በላይ ዘለቀ ግን የንቀት መልክ አሳይቶ ማለፉን ይህንን ታሪክ የሚያውቁ አባት የነገሩትን የእዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ሰምቷል። ከእዚህ በኋላ ንጉሱ በክብር አስጠርተው ደጋግመው በላይ ዘለቀን አነጋግረውታል። በአንድ ወቅት ንጉሱ ምናልባት በትምሕርት ብዙ አለመግፋቱ ይሆናል እኛ የምናየው የኢትዮጵያ አደጋ ለእርሱ ያልታየው አሁንም ለመሸፈት ያስባል የሚል ዜና ንጉሱ ደርሷቸው በነጻ ወደ ትምሕርት ቤት ከመግባትና የማዕረግ እና የ ሀገር ሹመት የትኛውን እንደሚመርጥ ለበላይ ዘለቀ እስከማቅረብ ንጉሱ ደርሰው ነበር።

ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ኢትዮጵያን ለማሳደግ ጊዜ አትሯቸው ይሮጣሉ። በሌላ በኩል ግን የገበሬ አመጽ አንድ ጊዜ ከጎጃም፣ሌላ ጊዜ ከባሌ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከትግራይ ቀዳማዊ ወያኔ የተነሱ የገበሬ አመጾች ኢትዮጵያን ወደ ዘመናዊ ምዕራፍ ለማሻገር የገጠሟቸው የእግር ጉተታ ፈተናዎች ነበሩ።ንጉሱ በቀረ ዘመናቸው እነኛን ሁሉ የእግር ጉተታዎች አልፈው በእርጅና ዘመናቸው ቀድመው የስልጣን ወንበሩን ሳያስተካክሉ ቢቀሩም በመጨረሻ በተነሳው አብዮት ግን መፍትሄ እንዲሆን የመርማሪ ኮሚሽን ተቋቁሞ ነገሩን በህግ ለመምራት ቢያስቡም፣ወታደሩም መፈንቅል በአራተኛ ክ/ጦር ተሰብስቦ እያደረገ መሆኑን እየሰሙ እና የክብር ዘበኛ ሄደን እንዋጋ ቢላቸውም ''ተዉ! እኛው ያስተማርናቸው ናቸው '' ለክፉ አይጥሉም በሚል ቤተመንግስታቸው ተቀምጠው ቢጠብቁም፣ በመጨረሻ እኛ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ እና ለዓለም ድንቅ ሥራ የሰሩ መሪ ክብራቸውን ያዋረድን መስሎን በቮልስዋገን መኪና ጭነን ከመሳለቅ ባለፈ ህይወታቸው እንዲያልፍ አድርገን እና የቀሩ 60 ባለስልጣኖችን እና ለኢትዮጵያ መልካም የሰሩ ልጆቿን በአንድ ቅዳሜ ምሽት ገድለን  አብዮት ተካሄደ ብለን የፎከርን የአሳፋሪ ታሪክ ባለቤትም ነን። የመሪዎቻችንን እግር መጎተት የነበረ ክፉ ባህላችን ነው።

ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም 

ኮ/ል መንግስቱ የንጉሱን መንግስት ተክተው ''ታሪካ የጣለብን አደራ ነው '' በሚል የወታደራዊ ደርግ እየመሩ ኢትዮጵያን መሩ። ኮ/ል መንግስቱ በመጀመርያ የስልጣን ዘመናቸው ኢትዮጵያ በተለይ ከሱማልያ ለገጠማት ወረራ ያደረጉትን ጥሪ ህዝብ ሰምቶ ኢትዮጵያን ታድጓል።በመቀጠል ከኮ/ል መንግስት የአስተዳደር ግድፈት እንዳለ ሆኖ ነገር ግን የደርግ መንግስት በመራቸው በሦስት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ አድምቶ ቢሰራበት ኖሮ እና ከእግር ጉተታ ብንድን ኖሮ ኢትዮጵያን በብዙ መንገድ እናሳድጋት ነበር። ይሄውም የደርግ መንግስት ያቀዳቸው የሰፈራ እና መንደር ምስረታ ( የመለስተኛ ከተሞች ፈጠራ)፣ የመሰረተ ትምሕርት ዘመቻ እና የኢትዮጵያ በቀይባሕር ላይ ያላት ታሪካዊ ባለቤትነት የሚሉት ይጠቀሳሉ። ሆኖም ግን በእነኝህ ቁልፍ ዳዮች ላይ ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በመደረጉ የመንግስት ተቀያያሪነትን ተገንዝቦ የልማት ፕሮጋራሞቹን ግን ወደፊት ይዞ  ከመሄድ ይልቅ በማጥላላት ላይ ውለን አደርን። ውጤቱ ግን ኢትዮጵያ ከረሃብ ያልተላቀቀች ብቻ ሳይሆን የነበራትን ወደብ ያጣች ሀገር ሆነች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ 

በያዝነው 21ኛው ክ/ዘመን መጀመርያ ላይ ኢትዮጵያ ባለችበት የለውጥ ሂደት ላይ ኢትዮጵያን የመምራት ዕድል ያገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአስተዳደራቸው ሂደት ላይ የቱንም ያህል ጥያቄ ያለው ሰው ቢኖር መጠየቁ እና ይህ ይስተካከል፣ ይህ ይታረም ማለቱ እና በምክንያታዊ መንገድ መሞገት በራሱ ጥፋት አይደለም። ይልቁንም ከሴራ አስተሳሰብ በራቀ መንገድ ሙያዊ ሙገታ እና እንዲስተካከል በሰላማዊ መንገድ መታገሉ ሊኖር የሚገባው ነው። ከእዚህ ባለፈ ዛሬም እየደገምነው ያለው የነበረ ክፉ ባሕላችን ግን አሁንም በዩቱበሮች እና የነገን ሳይሆን የዛሬን ከከንፈር እስከ አፍንጫ ብቻ የሚያይ አስተሳሰብ ይዘን ግዙፍ የሆኑ እና ትውልድ አሻጋሪ የሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሀሳቦች ላይ ቁጭ ብሎ አቃቂር በማውጣት ከአጼ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የተሰራውን የእግር ጉተታ እኩይ ተግባር ለመድገም የሚደረገው እሽቅድምድም ሌላ አሳፋሪ የታሪካችን አካል እንዳይሆን ሁሉም ይህ ክፉ ታሪክ እንዳይደገም ለኢትዮጵያ ልዕልና ሲል ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዘመን ተሻጋሪ ሀሳቦች ጋር አብሮ መቆም ተገቢ ነው።ስለ የኢትዮጵያ የባሕር በር ሲነሳ የኢትዮጵያን እንጀራ በልቶ እንዳላደገ ሰው ሀሳቡን ችላ ማለት፣ ኢትዮጵያን በአረንጓዴ ተክል እናልብሳት ሲባል የሚያሾፍ፣ የከተማ ወንዞችን እናልማ ሲባል አቃቂር የሚያወጣ፣ መጻሕፍት ቤት ሙዜየም ሲሰራ ለማቃለል የሚጣደፍ ይህ ሁሉ እግር ጎታችነት ብቻ ሳይሆን የነበረ እኩይ ባሕላችንን የመድገም ሙከራ ነው።ኢትዮጵያውያን አንጸባራቂ ታሪክ ያለንን ያህል የመልካም እና ብሩህ አዕምሮ መሪዎቻችን ለሀገራቸው ያላቸውን መልካም ርዕይ ለማኮሰስ የምንሮጠው ሩጫ እና የእግር ጉተታ አሳፋሪ ነው።የመሪዎች መልካም ርዕይ ትውልድ ተሻጋሪዎች እንጂ የአንድ መንግስት ዕድሜ የሚኖራቸው አይደለም። ስለሆነም ከመሪዎች መልካም ርዕይ ጎን መቆም እና ትውልድ ተሻጋሪ ስራዎች ላይ ሁሉ መተባበር ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን ማወቅ አለብን።


ለመጠቅለል፣ በአጼ ቴዎድሮስ፣ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴና ኮ/ል መንግስቱ ላይ የሰራነውን የመሪዎቻችንን በጎ ሀሳብ የመጎተት ክፉ ባሕል በጠ/ሚ/ር ዐቢይ ላይ አንደግምም። ኢትዮጵያ እንደቀደሙት ዘመናት አትታለልም። ትውልዱም ካለፈው ስህተት በብዙተምሯል።ከዘመን እና ትውልድ አሻጋሪ የመሪዎች ሀሳብን በማንም የባዕዳን እና የባዕዳን ቁራሽ ተመጽዋች እግር ጎታች ሀሳብ አንቀይረውም።
=====================/////===============

No comments:

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሃራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሐራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)