ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, November 6, 2023

የአማራ ክልል ህዝብ የወደቀበትን የመከራ መአት የሚያወራለት አንድም ''ዩቱበር'' አጥቷል። ህዝብ የገባበት ማጥ ሌላ፣ በውጭ ሃገር ሆነው የጥይት ባሩድ የማይሸታቸው የሚያወሩት ሌላ ሆኗል።ስለ የህዝቡ መከራ የሚናገር የለም።ዩቱበሮች ጦርነት ህዝብ የማይጎዳበት አበባ የመበተን ያህል አስመስለው ሲናገሩት ''አጀብ'' ያሰኛል።

ጃናሞራ መሸሃ እርዳታ ሲከፋፈል መስክረም፣2023
  •  ''ከ3 ሚልዮን በላይ ተማሪዎች እስካሁን ትምሕርት ለመጀመር አልተመዘገቡም'' አቶ መኳንንት አደም የክልሉ ምክትል ትምሕርት ኃላፊ፣
  •  ከፍተኛ ረሃብ በክልሉ በተለይ በጃናሞራ መግባቱ ተሰምቷል።የምክር ቤቱ አባል በአቶ ባያብል ሙላቴ የተራቡትን ለመደገፍ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። 
  •  ክልሉ ከአሁኑ ጦርነት በፍጥነት መውጣት ካልቻለ በተጨማሪ የወራት ጦርነት በልማት 60 ዓመታት ወደኋላ ሊቀር ይችላል። 
  • ዝምታው ይሰበር።

============
ጉዳያችን ምጥን
============

 በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነት የክልሉን የንግድ፣ኢንዱስትሪና ማኅበራዊ ተቋማት በከፍተኛ ደረጃ እያሽመደመደ ነው።ከአንድ ወር በፊት ከአንድ ሺህ ሁለት መቶ በላይ ኢንዱስትሪዎች ስራ መስተጓጎሉ የተገለጸ ሲሆን ከትናንት በስቲያ የክልሉ ምክትል ትምሕርት ኃላፊ አቶ መኳንንት አደም እስካሁን ከ3 ሚልዮን በላይ ተማሪዎች የዘንድሮን ትምሕርት ለመማር እስካሁን እንዳልተመዘገቡ ገልጸዋል።ከእዚህ በተጨማሪ ክልሉ የወባ በሽታ አደጋም ተጋርጦበታል።የክልሉ ረሃብ በተመለከተ የተወሰኑ ዜናዎች በመንግስት መገናኛ ብዙኃን ለአንድ ሁለት ቀናት ያህል ከተሰማ በኋላ ስለረሃቡ ብዙም አይሰማም።

ከእዚህ ሁሉ በተለየ በጃናሞር ያለውን የድርቅ ጉዳት ለመደገፍ  በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጃናሞራ ተወካይ አቶ ባያብል ሙላቴ እያስተባበሩ የሚገኙት የቴሌግራም ግሩፕ ላይ በጎ አድራጊዎች የቻሉትን እያደረጉ ይገኛል። የገንዘብ ማሰባሰብያ የባንክ ሂሳብ በጥምረት ማለትም በአቶ ባያብል ሙላቴ፣ፕሮፌሰር ጌታሁን መንግስቱ እና በወ/ሮ እኝሽ ገብሬ እንዲንቀሳቀስ የተደረገ ሲሆን በቴሌግራሙ ገጽ ላይ የተለጠፈው የሂሳብ ቁጥርም ከስር እንደሚከተለው ይታያል።
================================================================
ለጠለምት፣ ጃናሞራና በየዳ ህዝብ ፈጥነን እንድረስት📣

የኢትዮጽያ ንግድ ባንክ ሒሳብ ቁጥር 
1️⃣0️⃣0️⃣0️⃣5️⃣7️⃣9️⃣0️⃣9️⃣3️⃣5️⃣6️⃣4️⃣

በሰሜን ጎንደር ዞን (ጃናሞራ በየዳና ጠለምት) ቆላማ ቀበሌዎች በተከሰተው ድርቅና ርሃብ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖቻችን ድጋፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ ባንክ ሂሳብ ተከፈተ።

የባንክ ሂሳቡ ፈራሚዎች
1.ፕሮፌሰር ጌታሁን መንግስቱ
2.ወ/ሮ እንይሽ ገብሬና
3. አቶ ባያብል ሙላቴ ናቸው

በመሆኑም ለወገን ደራሽ ወገን ነውና በሃገር ውስጥና በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን በሞት አፋፍ የሚገኘውን ወገናችንን ለመታደግ የምንችለውን እንድናደርግ የድጋፍ ጥሪ እናቀርባለን።
=====================================

የተከበሩ አቶ ባያብል ሙላቴ የጃናሞራ ህዝብ ተወካልይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት


ይህ በየምክር ቤት አባል አቶ ባያብል እና የአካባቢው ተወላጆች የተጀመረው የተራቡትን የመርዳት ስራ እጅግ ሊበረታታ የሜገባው እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ሊሳተፉበት የሚገባ ነው።''ጨለማን ሲረግሙ ከመዋል አንድ ሻማ ማብራት '' የሚለውን አባባል በተግባር ያሳየ አርአያነት ያለው ተግባር ነው።
  
የአማራ ክልል ያለው ግጭት በቶሎ መፍትሄ ካላገኘ ክልሉን ወደ የከፋ አደጋ ከመምራት ባለፈ የኢትዮጵያን አንድነት በከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥል ነው። ለእዚህ ደግሞ ዋነኛው ማሳያ የሚሆነን በአጭር ጊዜ ውስጥ የደረሰው ጥፋት ብቻ ሳይሆን ከህዝቡ ብዛት፣የመልክዐ ምድሩ አቀማመጥ የሚያዋስናቸው ክልሎች ብቻ ሳይሆን ከሀገሮች ጋርም መዋሰኑ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ አለው።

አሁን የመንግስት ሚድያዎች ስለ የአማራ ክልል ጦርነት ዕለት ከዕለት ዜና እያሰሙ አይደለም። ስለ ክልሉ ጦርነት እየነገሩን ያሉት ዩቱበሮች ናቸ። ዩቱበሮቹ ግን ስለ የህዝቡ ሰቆቃ አያወሩም። ረሃቡን ደብቀዋል፣የወባ በሽታውን አይናገሩም፣ከሦስት ሚልዮን በላይ ተማሪዎች እንዳልተመዘገቡም አያወሩም።እነርሱ አሽትተውት ስለማያውቁት ባሩድ ከባሕር ማዶ ተቀምጠው እያወሩ፣በፊልም የሚያውቁትን ጦርነት ከአሜሪካ ሆነው በለው፣በለው! እያሉ ያሟሙቃሉ።

ክልሉ እየወረደበት ስላለው የመከራ ዶፍ የሚተነፍስ ዩቱበር የለም። ይህ ክልሉ በጸጥታ ወደ ከፍተኛ ቀውስ የመግባት አደጋ ላይ ነው።''ከትናንት ቢዘገይ ከነገ ይቀደማል '' እና ዛሬም የክልሉ ባለሃብቶች፣ሙሑራን እና የሃይማኖት አባቶች በጋራ ተሰብስበው በነፍጥ የሚመራ ክልል እንዳይሆን እና ያሉት ጥያቄዎች አግባብነት ባለው መልክ ቀርበው በምክክር እና በሰላም እንዲፈታ ጥረት ካላደረጉ ጉዳዩ በባዕዳን እጅ ገብቶ ኢትዮጵያን በከፋ መልኩ ወደ ኋላ 60 ዓመት ሊጎትተው ይችላል።የክልሉ ጉዳይ የሚመለከተው የተወሰኑ ዩቱበሮችን ሊሆን አይገባም። በመከራው ጊዜ የሚያወራለት የሌለው ህዝብ ዓይናችን እያየ አንዳችም ምሑራዊ ውይይት አድርገው ለችግሮች መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ በቀለጠ ፕሮፓጋንዳዊ ስራ ላይ የተጠመዱ ዩቱበሮች መከራውን እንዲደብቁ እና ክልሉን ፍጹም ሲወድም አያየን በመመልከት ወደ የባሰ ጥፋት ሲመሩ ሊሰጣቸው አይገባም። ዝምታው ሊሰበር ይገባል!
===================/////==============


No comments: