ጉዳያችን ማሳሰቢያ!
የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ከስሜት በፀዳ ነገር ግን የቆረጠ እና የጠራ መስመር እንዲይዝ ማድረግ ተገቢ ነው።በመሆኑም በቂ መረጃዎችን ማድረስ እና ጉዳዮች መያዝ ያለባቸውን መንገድ መጠቆም አስፈላጊ ነው።
ፈጣን ውሰኔ፣አረዳድ እና ዕይታ የሚሹት ጉዳዮች
2) የሕወሃትን ምርጫ ለማየት ሄዱ ስለተባሉ ጋዜጠኞች፣እና የውጭ ሀገር ዜጎች በተመለከተ (ውሳኔ የሚፈልግ)
3) ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ (ዕይታ እና አረዳድ የሚፈልግ )
=======================
1) ውጪ ጉዳይ ያሉ የፅንፈኞቹ መረብ (ውሳኔ የሚፈልግ)
==========================
ከለውጡ ሂደት ጀምሮ በኢትዮጵያ ያሉ መስርያቤቶች የአሰራር እና የመዋቅር ለውጥ እያደረጉ እንደሆነ ተነግሯል።አንዳንዶቹ መስርያቤቶች ጋር ጥሩ እየሄደ ነው ሲባል አንዳንዶቹ ጋር የሚቀረው ሂደት እንዳለው ይነገራል።ለውጥ የሚለው አካሄድን በመጠቀም አብረው ተሳፍረው ከሚያበላሹት ውስጥ ዋነኞቹ የፅንፍ ኃይሎች ናቸው።የፅንፍ ኃይሎች እንደ አሜባ እንዲወሯቸው ከተደረጉት የመንግስት መስርያቤቶች ውስጥ በተለይ ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ወደ ውጭ ጉዳይ ከመምጣታቸው በፊት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ያሉ ክፍሎች እና በውጭ ሀገር ያሉ ኤምባሲዎች ናቸው።
በእነኝህ የስራ ቦታዎች ውስጥ ኢትዮጵያን እንደሀገር የሚጠሉ ሰዎች የተሰገሰጉባቸው የስራ መደቦች እና ኤምባሲዎች መብዛታቸውን የዲያስፖራው ማኅበርሰብም ሆነ ተግባራቸው በግልጥ እያሳየ ነው።ይህ ጉዳይ አደገኛ ጉዳይ ነው።የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መስርያ ቤትም ሆነ ኤምባሲዎቹ የሀገር ስስ ከሆኑ አካሎች ውስጥ የሚመደብ እና ከፍተኛ የሰው ኃይል ብቃት፣ሃገርን መውደድ እና ከምንም ዓይነት የሙስና አሰራር የፀዳ ስብዕና ይጠይቃል።የኤምባሲ ሠራተኛም ሆነ አምባሳደር ኤምባሲው ማለት የሀገሩ ምድር በመሆኗ የሚመጣውን ማናቸውም ጉዳይ እስከሞት ተጋፍጦ የሀገሩን ክብር የማስከበር የሞራል ልዕልና ሊኖረው ይገባል።የአሜሪካ ኤምባሲ በኢራን ተማሪዎች በታገተ ጊዜ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ያሳዩት የአሜሪካዊ ሃገራዊ ፍቅር እስካሁን ድረስ ይጠቀሳል።
በኢትዮጵያ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት የሚደነቁ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰራተኞችም ሆኑ አምባሳደሮች ጥቂት እንዲሆኑ ያደረገው የካድሬ አመላመል እና ጎሳን መሰረት ያደረገ አመዳደብ እና ዕድገት መኖሩ ነው።አሁን ደግሞ ሁኔታው ወደ አደገኛ መስመር እየሄደ ፅንፈኛ የኦነግ ሸኔ አቀንቃኞች እና አድናቂዎች የሚጠሏትን ኢትዮጵያን የሚወክሉ መስለው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥም ሆነ በቅን የሚያገለግሉ ኢትዮጵያዊነታቸው የሚያከብሩትን ሲያሸማቅቁ እና ተገቢ ስራቸውን እንዳይሰሩ ሲያደርጉ እየታዩ ነው።ስለሆነም ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነው የፅንፈኞች መረብ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከኤምባሲዎች በሙሉ መበጣጠስ አለበት።
2) የህወሓትን ምርጫ ለማየት ሄዱ ስለተባሉ ጋዜጠኞች፣እና የውጭ ሀገር ዜጎች በተመለከተ (ውሳኔ የሚፈልግ)
የህወሓትን ምርጫ ለመታዘብ ወደ መቀሌ ሊሄዱ ሲሉ ከቦሌ አየር መንገድ ትናንት የውጭ ሀገር ጋዜጠኞች እና የዓለም አቀፍ ድርጅት ሰራተኞች መያዛቸው ተሰምቷል።ይህንን ያደረጉ የውጭ ሀገር ጋዜጠኞች የሀገሪቱ ሕግ አውጪ አካል የፌድሬሽን ምክር ቤት ቅዳሜ ነሐሴ 30/2012 ዓም በህወሓት የሚደረገው ምርጫ ህገ ወጥ ምርጫ መሆኑን ለመጨረሻ ጊዜ ያሳለፈው ውሳኔ እያወቁ ወደ መቀሌ ለመሄድ መሞከራቸው ከታወቀ ወንጀል ብቻ ሳይሆን የሚሰሩበትን የዜና አገልግሎትን ብቻ ሳይሆን የሚሰሩበትን ድርጅት ሕጋዊ አሰራር ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው።ሙከራው በአንድ ሀገር የውስጥ ጉዳይ የመግባት ጉዳይም ነው።ስለሆነም ይህ ጉዳይ ተጣርቶ ከፈቃድ መሰረዝ እስከ ወደ ሀገር እንዳይገቡ የሚያግድ ውሳኔ ከመንግስት ይጠበቃል።የድርጊቱ ሂደት በውስጥ ጉዳይ የመግባት እና የሀገሪቱን ሕግ አለማክበር የሚታይበት ግልፅ አካሄድ ነው።
3) ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ (ዕይታ እና አረዳድ የሚፈልግ )
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን በተመለከተ በማኅበራዊ ሚድያ አልፎ አልፎ የሚታዩ ነቀፋዎች እየተመለከትን ነው።በእርግጥ ከእዚህ በፊትም ጨዋነት ከጎደለው እስከ በሆነ ባልሆነው የጥላቻ ፅሁፎች በየማኅበራዊ ሚድያው የሚለጥፉ አሉ።አንድ ሰው የተሰማውን ጨዋነት በተላበሰ መንገድ ሃሳቡን መግለጥ መብቱ ነው።ነገር ግን ኢትዮጵያን እንወዳለን ለምንለው ነው ይህንን መልዕክት ማስተላለፍ የምፈልገው።ኢትዮጵያን የሚጠሉ የአክራሪ ፅንፍ ኃይሎች እና የጎሳ ፖለቲካ ለማራመድ የሚፈልጉ የሌላው ገመድ ጎታቾች ጧት ማታ ጠቅላይ ዓቢይን ሲያጥላሉ ቢውሉ ኢትዮጵያን ማለታቸው እንዳልተመቻቸው መረዳት እንዴት ያቅተናል?
ሁሉም ሊያውቀው የሚገባው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን የምናደንቀው ኢትዮጵያን በማለታቸው ነው።የፓርላማ ንግግራቸውን ከአርባ ጊዜ በላይ ኢትዮጵያ! በሚል ንግግር ካጀቡበት ቀን ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ያሳዩትን የኢትዮጵያዊነት ሂደት ማበረታታት ኢትዮጵያን ከምንል ሁሉ ይጠበቃል።የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አስተዳደር ያልተቆጣጠራቸው የመንግስት የስራ ቦታዎች አሉ ወይ? አንዱን ሲነካው ሌላው ይተረተራል በሚል ያቆዩት ጉዳይ አለ ወይ? አጠቃላይ ማዕቀፉ እና አካሄዳቸው ኢትዮጵያዊ ነው ወይ? ብሎ ነገሮችን በሚገባ መመርመር ኢትዮጵያን ከሚለው ሁሉ ይጠበቃል።
ሌላው የሕዝብ ትኩረት ለመሳብም ሆነ አዲስ የትሕትና መንገድ ለማሳየት እራሳቸውን ከሊስትሮ እስከ ትራፊክ እየሆኑ የሚያሳዩትን አንዳንዶች ''አታለለን''ወዘተ እያሉ ከፅንፍ ኃይሎች ጋር አብረው በማኅበራዊ ሚድያ ላይ ሲፅፉ እያየን ነው።ቢያንስ ይህንን የትህትና መስመራቸውን ማድነቅ ኢትዮጵያዊ መስመራቸውን ማገዝ ነገር ግን የሕግ፣የኢትዮጵያን ማኅበራዊ መሰረት እና ታሪካዊ ዳራ ባላናገ መልኩ ሀገሪቱ እንድትሄድ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንጂ ኢትዮጵያን ያለ ሰው ከማበረታታት ይልቅ የነቀፋ ሃሳብ መሰንዘር ትክክል አይደለም።
ዛሬም ሆነ ነገ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን የምናበረታታቸው የበለጠ ለኢትዮጵያ እንዲሰሩ ነው እንጂ የስሜታዊነት ጉዳይ አይደለም።በእርግጥ ከፅንፍ እና ከጎሳ ስሜታቸው አንፃር ጧት ማታ የሚነቅፉት የቆሙበት መሰመር ስለሆነ እና ዓቢይ የእነርሱን ፀረ-ኢትዮጵያዊ መንገድ እንዳለተቀበላቸው ስላወቁ መሆኑን ማወቁ ቀላል ነው።ባጭሩ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን ያለ ማንንም ሰው አብረነው ልንቆም ይገባል።ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት መስመር ያልወጡ ኢትዮጵያን በእዚሁ መስመር ለማስገባት እየጣሩ ያሉ ሰው ናቸው።
መልካም አዲስ ዓመት!
No comments:
Post a Comment