ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, December 22, 2017

"የስኳር ኮርፖሬሽን እና ፕሮጀክቶቹን አስመልክቶ በዋናው ኦዲተር በወጣው ሪፖርት መሰረት አቃቢ ሕግ ክስ እንዲመሰረት ነበር የጠየቅነው እስካሁን ምላሽ የለም።እየጠበቅን ነው" ዋናው ኦዲተር መስርያ ቤት ድጋሚ ማሳሰቢያ።

ጉዳያችን ዜና / Gudayachn News
  
አቶ ገመቹ ዱቢሶ የዋናው ኦዲተር ቢሮ ኃላፊ 
 • መስርያ ቤቱ ለሕዝብ ይፋ ያደረጋቸው 'ጆሮ የሚጠልዙ' የሌብነት እና ዝርክርክ አሰራሮች በመተሃራ፣ወንጂ እና ተንዳሆ ፋብሪካዎች ላይ ያደረሰውን ጉዳት ያጋልጣል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት መንግስታዊ መስርያ ቤቶች የመስርያ ቤቶችን የተዝረከረከ አሰራር የህወሓትን አምባገነናዊ ማሸማቀቅ በማለፍ በድፍረት ሙስናዎችን ለሕዝብ ይፋ በማድረግ በአቶ ገመቹ ዱቢሶ የሚመራው የዋናው ኦዲተር መስርያቤት አርአያነት ያለው ሥራ ሰርቷል። መስርያ ቤቱ የስኳር ኮርፖሬሽን በአቶ አባይ ፀሐዬ እየተመራ የደረሰበትን ክስረት ለሕዝብ በዝርዝር እና የኦዲት ሕግ እና ስርዓት በጠበቀ መልኩ በማቅረብ እና ሰነዱንም ለክስ በሚቀርብ መልኩ በማስረጃ አስደግፎ በመያዝ በኩልም ብዙ እርቀት እንደሄደ ይነገራል።
ይህም ሃገራዊ ኃላፊነት በሚሰማቸው የመስርያ ቤቱ ኃላፊ እና ሰራተኞቹ ብርቱ ትጋት እንደሆነ ይነገራል።

መስርያ ቤቱ በዛሬው እለት ታህሳስ 13፣2010 ዓም በዋና ኦዲተር ቢሮ ኃላፊው አቶ ገመቹ ዱቢሶ አማካይነት ለሸገር ራድዮ በሰጠው መግለጫ አቶ ገመቹ ዱቢሶ "  "የስኳር ኮርፖሬሽን እና ፕሮጀክቶቹን አስመልክቶ በዋናው ኦዲተር በወጣው ሪፖርት መሰረት አቃቢ ሕግ ክስ እንዲመስረት ነበር የጠየቅነው እስካሁን ምላሽ የለም።እየጠበቅን ነው" ማለታቸው ተሰምቷል።

መስርያ ቤቱ ለሕዝብ ይፋ ያደረጋቸው ስኳር ፋብሪካዎች ጋር የተያያዙ የሌብነት እና ዝርክርክ አሰራሮች 

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለው
ስኳር  እጥረት አቶ መለስ እና ኃይለማርያም እንደሚሉት ሕዝብ በብዛት ስኳር ስለተጠቀመ ነው የሚለው ተረት ተረት ፀሐይ የሞቀው ውሸት መሆኑን ይህንን ሪፖርት የተመለከተ ሰው በቀላሉ መረዳት ይችላል። በእዚህ በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ተባባሪ ሹማምንት በተመራ የዝርፍያ እና ዝርክርክ ተግባር በኢትዮጵያ ላይ የደረሰው የጥፋት መጠን ሪፖርቱ በገለጠው የገንዘብ መጠን ብቻ ይወሰናል ብሎ መገመት ፈፅሞ እንደማይቻል መረዳት ይገባል።ከእዚህ በታች የዋናው ኦዲተር ቢሮ ያወጣው ሪፖርት በሶስቱ ፋብሪካዎች ብቻ ላይ የተጠቀሰው ዋና ዋናው ብቻ ተዘርዝሯል።

የተንዳሆ ፋብሪካን በተመለከተ 

 • የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ አፈጻጸምን አስመልክቶ ዓመታዊ የግርድፍ መሬት፣ የውሃ ገብ መሬት ርክክብና የሸንኮራ አገዳ ተከላ እቅዶች አለመሳካታቸው፣ የፋብሪካው ግንባታና ተከላ በ6 ዓመት የዘገየ ፕሮጀክት ሆኗል፣ ለፋብሪካው በአማካሪነት ከተቀጠረው ድርጅት ጋር የተገባው ውል ለ7 አመታት መራዘሙና ይህም ወደ 9.5 ሚልየን ብር ጭማሪ (713.4%) እንዲከፈል ማድረጉ፣ ለ499 ቤቶች ግንባታ ከ300 በላይ ለሆኑ ተቋራጮች ካለውል ስራ መሰጠቱ፣
 • በእዚሁ ፋብሪካ በርካታ ማሽነሪዎች ለብልሽት መዳረጋቸው፣ በማስከተልም በህወሓት ጀነራሎች የሚመራው ብረታ ብረት ኮርፖሬሽን ጋር 44 ሚልዮን ብር የሚያወጣ ለማሽነሪ መግዣ  ውል ቢፈራረምም ብረታ ብረት ኮርፖሬሽን ማሽኖቹን ሳይሰራ ከአንድ ዓመት በላይ ስለሆነ የሀገር ንብረት እንደባከነ ገልጧል፣
 • ለፋብሪካው የቲሹ ካልቸር ሥራ በሚል የተመደበው በጀትም ሆነ የወጣው ወጪ ተደብቆ እስካሁን ግልጥ አልተደረገም፣
 • ፋብሪካው ወደ ሥራ ባለመግባቱ ከ300 ሄክታር በላይ ላይ የተተከለው የሽንኮራ አገዳ ወደ ምርት ሳይቀየር እንዲገለበጥ  መደረጉ፣1349 ሄክታር ላይ የነበረ ቀደም ብሎ የደረሰ ሸንኮራ አገዳም ወደ ምርት መግባት ባለመቻሉ እንዲጣል መደረጉ እና ይህ ከፍተኛ ብክነት መሆኑ፣ 
የመተሐራ ፋብሪካን በተመለከተ 
 • የኢታኖል ፕላንት ግንባታና ተከላ ጨረታ ሂደትን የሚያሳይ ሰነድ አለመገኘቱ፤ ለግንባታና ተከላ ከተመደበው መነሻ የኮንትራት ዋጋ በላይ በብልጫ ለተፈጸመው የብር 33,859,495.41 ክፍያ ምክንያቱን የሚገልጽ የውል ማስረጃ አልተገኘም፣
 • የእንፋሎት ሀይል ማቅረብ ባለመቻሉ ከምርት ሊገኝ የሚቻል ከ68,6 ሚልየን ብር በላይ መታጣቱ እንዲሁም በግብዓትነት ሊውል የሚችል  ብር 39,193,770 የሚያወጣ ሞላሰስ መባከኑ ብሎም ብር 3,915,328.10 የሚያወጣ ከተሽከርካሪዎች ነዳጅ ጋር የሚቀላቀል 412,139.8 ሊትር ኢታኖልና ለተለያዩ የመጠጥ ኢንዱስትሪዎች በግብዓትነት የሚሸጥ ብር 2,559,388.99 የሚያወጣ 176,631.4 ሊትር ረክቲፉይድ ስፕሪት አልኮል ባለመመረቱ በድምሩ ብር 6,474,717.09 ሀገሪቱ እንድታጣ መደረጉን ደርሶበታል፣
 • በውል አፈጻጸምና ግዥ በኩል ከስኳር ኮርፖሬሽኑ ግዥ አፈፃፀም መመሪያ ውጪ ግዥ በመፈፀሙ ፋብሪካው ያልተገባ ተጨማሪ ወጪዎች እንዳወጣና በውል ያልታሰሩ ግዥዎችን እንደፈጸመም ተገልጾ በአብነት ለሥራ ላይ አደጋ መከላከያ አልባሳት ተጨማሪ ብር 168,834.89 ለሠራተኞች ዩኒፎርም ግዥ ደግሞ ብር 437,368.75 ተጨማሪ ወጪ ለሁለት አቅራቢዎች እንደከፈለ ተጠቅሷል፡፣
 • የእንፋሎት ሀይል ለማመንጨት የሚያስፈልገውን ውሃ እንዲያጣራ በብር 1,906,362 ለፋብሪካው ተገዝቶ ከህንድ የመጣና ሌሎች ልዩ ልዩ ክፍያዎች ተፈጽመውለት የተተከለ መሳሪያ ፋብሪካው ከሚጠቀምበት ነባር ቴክኖሎጂ ጋር ባለመግጠሙ ምክንያት ከሁለት ዓመታት በላይ አገልግሎት ሳይሰጥ መቀመጡ ለከፍተኛ ኪሳራ አስከትሏል፣
 • በተደረገው የነዳጅ ቆጠራ 3,224.86 ሊትር ፔትሮሊየም እና 8,304.95 ሊትር ዲዝል ከካርድ ባላንስ ጋር ሲነፃፀር አንሶ ተገኝቷል መልስ የሚሰጥ የለም 
 • በሁለት መርከብ ከውጭ ሀገር ተጭኖ ከመጣ ስኳር ውስጥ 3,777 ኩንታል የተበላሸ በመሆኑ ትክክለኛ ማስረጃ ባልተገኘለት መንገድ መቀበሩና ካሳ ያልተጠየቀበት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ (ዘግይቶ በወጣ ሌላ ምንጭ ተቀበረ የተባለው ውሸት መሆኑ እየተገለጠ ነው።ከእዚህ ይልቅ ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ በኃላ ሳይበላሽ እንደተበላሸ ተደርጎ እና እንደተቀበረ የተገለጠው ውሸት መሆኑ እና በድብቅ ገበያ ላይ መሸጡ የሰሞኑ ትኩስ ሆኗል)፣
የወንጂ ስኳር ፋብሪካ በተመለከተ 
 • የስኳር ፋብሪካ ማስፋፊያ የመነሻ ውል ስምምነት ላይ የፋብሪካው መጠናቀቂያ ጊዜ አለመገለጹ በተጨማሪም የፋብሪካ ግንባታና ተከላ ስራውን በአማካሪነት የተከታተለው ኩባንያ ውል ማጠናቀቂያ ጊዜ ለ8 ጊዜ እየተራዘመ ለ9 ዓመታት በመዘግየቱ ከመነሻ ኮንትራት ዋጋው በላይ ዩሮ 4,648,860  (150,190,992.82 ብር) አለአግባብ ተጨማሪ ክፍያ ለኩባንያው መከፈሉን ኦዲቱ አመልክቷል፣
 • የሸንኮራ አገዳ እርሻ ልማት ለማከናወን የመስኖ ግድብና አውታር ግንባታ የወለንጪቲ ቦፋ መስኖ ፕሮጀክት በ3 ዓመት ለማጠናቀቅ ውል ቢገባም ለ2 ዓመት ከ2 ወር ከመራዘሙ በላይ ስራዎቹ በተቀመጠላቸው ጊዜ ባለመጠናቀቃቸው ውሉ 4 ጊዜ የታደሰ በመሆኑ በድምሩ ብር 30,489,214 ከመነሻ ዋጋ ተጨማሪ ክፍያ መፈጸሙ ተገልጿል፣
 • ጂቡቲ ወደብ ተከማችተው የሚገኙ የፋብሪካ እቃዎችን በተመለከተ በፋብሪካው ለኮርፖሬሽኑ የቀረቡ የድጋፍ ጥያቄዎች አለመመለሳቸው፤ ከሞጆ ደረቅ ወደብ ለሚመጡ ዕቃዎች የገንዘብ ጥያቄን አስመልክቶ ብር 22,019,678.78 መከፈል ባለመቻሉ የመወረሻ ጊዜያቸው የተቃረበ 9 ዕቃዎችን በወቅቱ ባለማንሳት ለመጋዘን ኪራይ ብር 393,231.33 መከፈሉ ተመልክቷል፡፣
 • በንብረት አያያዝ በኩል እ.ኤ.አ በ2014/2015 በጀት ዓመት 124 ቀላል እና 41 ከባድ ተሽከርካሪዎች፤ እ.ኤ.አ በ2015/2016 በጀት ዓመት ደግሞ 172 ቀላልና 21 ከባድ ተሽከርካሪዎች በንብረት ቆጠራ ወቅት አለመገኘታቸው እና እነኝህ መኪናዎች የት እንዳሉ ማንም መልስ መስጠት አለመቻሉ፣
ባጠቃላይ የኦዲት ሪፖርቱ በገንዘብ በኩል የደረሰው ጥፋት ላይ ቢያተኩርም በእራሱ በኮርፖሬሽኑ ቀደም ብሎ ለማስፋፍያ በሚል ኢትዮጵያ ከ70 ቢልዮን ብር በላይ መበደሯ እና እስካሁን አንድም ፋብሪካ ወደ ሥራ አለመግባቱ መገለጡ ይታወቃል።ይህ በእንዲህ እያለ ነው ዛሬ ታህሳስ 13፣2010 ዓም የዋናው ኦዲተር ሥራ አስኪያጅ አቶ ገመቹ ከላይ የተጠቀሱት ጉድዮች በሕግ እንዲጣሩ ከማስረጃ ጋር ለአቃቢ ሕግ የላክን ቢሆንም እስካሁን መስርያቤቶቹም ሆኑ አቃቢ ሕግ ምላሽ አልሰጠም።ይልቁንም በባሰ ሁኔታ ችግሮች እየቀጠሉ መሆኑን ይገልጣሉ። ከእዚህ በተጨማሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ80 ሚልዮን ብር በላይ መፈረም ያለበት ኃላፊ ሳይፈርም ወጪ መደረጉን የኦዲት መስሪያ ቤቱ ቢገልጥም እስካሁን ምላሽ አለመሰጠቱን ዜናው ያብራራል።የኢትዮጵያ የሙስና እና የባለስልጣናቱ የዘረፋ ደረጃ ከምንገምተው በላይ ነው።የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት ቅሌት በትንሹ ምን ያህል የሰፋ ምዝበራ እንደሚደረግ የሚያሳይ አንዱ ናሙና ነው።በእዚህ መልኩ በእያንዳንዱ ሴክተር ውስጥ ያለውን የዘረፋ ጥልቀት ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ ይቻላል።የኦዲት መስሪያ ቤት ለእያንዳንዱ ክሶቹ በቂ በሰነድ የተያዘ ማስረጃ እንዳለው እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ የኦዲት ምርመራ ደረጃ መስራቱን አክሎ ገልጧል። 

ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...