ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, January 28, 2016

ለትዕቢት እና ጎጣዊ ስሜት ሕመምተኞች አልቅሱ! (የጉዳያችን ልዩ ማስታወሻ)


foto: http://hearinghealthmatters.org/ 

የሰው ልጅ በኖረበት ዘመን ሁሉ ሁለት ነገሮች ቀንደኛ ፈተናዎቹ ናቸው።እነርሱም ትዕቢት እና ጎጠኝነት ናቸው።ትዕቢት ከእኔ በላይ ማን አለ? የሚል  ስሜት እና ሌላውን ዝቅ አድርጎ የመመልከት አባዜ ሲሆን  የጎጠኝነት  ስሜት ደግሞ ''ሰው ሁሉ ለምን እኛ መንደር አልተወለደም'' መሰል የአስተሳሰብ ድህነት ነው።በሌላ በኩል ጎጠኘንት ከእራስ ወዳድነት አልፎ ሌላን መጥላት መለያው ያደርጋል።

የአንድ ሕዝብ እና የአንድ ግለሰብ ባህርያት የጋራ መገናኛ ድልድይ አላቸው።ሁለቱም መከራ ይሸከማሉ።ሁለቱም የሌሎችን የትቢት አንቡላ በላያቸው ላይ ሲራገፍ እንዳላዩ ሆነው ለተወሰነ ጊዜ ያልፋሉ።ሁለቱም  የጎጣዊ ስሜት ውስጣቸውን እንደምስጥ ለቦረቦራቸው ሁሉ እያዘኑ አሁንም ለጥቂት ጊዜ ይታገሳሉ።

 አንድ ግለሰብ ትዕቢትን እና ጎጥን መጠየፉ በእራሱ የትዕቢተኞች እና የጎጣዊ ስሜት አራማጆች ሰለባ እንዳይሆን ዋስትና አይሆነውም። ትዕቢት እና ጎጥን የማምለክ በሽታዎች ደግሞ የሚገለጡበት አንድ አይነተኛ መንገድ አለ።ይሄውም በንቀት ነው። ጎጠኞች በቅርብም ሆነ በሩቅ የሚያውቁትን ከመንደራቸው ውጭ የሆነውን ሁሉ በጣም ይንቃሉ።በአደባባይ ጎጠኛ እንዳልሆኑ ለመታየት ግን ይታትራሉ።ጎጠኞች ሁል ጊዜ ከበታቻቸው ሆኖ ለማየት የቀን እና የሌት ህልማቸው ነው።ከጎጣቸው ውጭ የሆነ ሰው ሰርቶ ቢያገኝ ይነዳቸዋል። ተምሮ መልካም ደረጃ ላይ ቢደርስ አይፈልጉም። ሆኖም ግን ይህንን እኩይ ስሜታቸውን ውጠው በጎ የመከሩ መስለው መቅረብ ደግሞ ይችሉበታል።አፋቸው ማር ነው።ከንፈራቸውን በየጊዜው ለሚያሳዝነውም ለማያሳዝነውም እሰው ፊት በመምጠጥ አዛኝ ቡቡ መምሰል ይችሉበታል። ዘወር ብለው ግን ከጎጣቸው ጋር ገጥመው ሰው ሁሉ የእነርሱ ጠላት ስለሚመስላቸው የተንኮል መረባቸውን ሲያደሩ ስትመለክቱ ትገረማላችሁ።

መፅሐፍ ''ትዕቢት ውድቀትን ይቀድማል'' እንደሚል ከጎጣቸው ውጭ የሆነ ሰው ምን ቢወዳጃቸው እና ሊዛመዳቸው ቢፈልግ ከእርሱ አንዳች ጥፋት እና ክፉ ቃል ቢያጡበት የእርሱ ጥፋት ይመስል ''እናቱ ለምን እኛ መንደር መጥታ አልወለድችውም'' መሰል ጥላቻ በተግባራቸው ውስጥ ሁሉ ታዩባቸዋላችሁ።ስለዚህ ከጎጣቸው ውቼ የሆነውን ሰው አሁንም ምኑንም ያክል ሊወዳጅ ቢፈልግ  አንዳች ጥፋት ሳያገኙበት የጎጥ ህመማቸው ቀስፎ ስለሚይዛቸው ብቻ ያገሉታል፣ይርቁታል፣ ወይንም ግንኙነታቸው ከጎጣቸው እና የእኔ ከሚሉት ወይንም ከሚሏት ጋር ብቻ ያደርጋሉ። በእዚህ ጊዜ  ግን የተገለለው ጎጠኞችን በበጎዎች አስገብቶ ማየት የለበትም። ሌሎች የሚያውቃቸው ደጋጎቹን እያሰበ እራሱን ማፅናናት የግድ ይለዋል። የጎጠኞች የንቀትን ልክ ስርዓት ለማስያዝ እልሁን  መፈታተኑ አይቀርም። ሆኖም ደጋጎቹን ያየ እና መልካም እና በጎ ህሊና ያላቸው ሌሎቹን  ያየባቸውን በጎ ዘመኖች ያስባል።ሁለት ፀጉር እና እድሜ ካላስተማራቸው ጋር መልሶ መጎጠጥ በእራሱ በሽታ መሆኑን መረዳት የግድ ይላል።

በጎጥ በሽታ የተለከፉ እራሳቸውን የደጎች መጨረሻ አድርገው ለመሳል ይሞክራሉ።ሆኖም ግን እንደ አይን ብሌን ከህሊናቸው ጋር የተሰፋው የዘር ቡቶቶ እያደናቀፈ ስለሚጥላቸው ደጋግመው ሊወዳጃቸው የቀረበውን በጥላቻ እሾህ አዕምሮውን እየጨቀጨቁ ሲወጉ ህሊና ቢስነታቸው ለእራሳቸውም አይታወቃቸውም። በመጀመርያ ህሊና ከጎጥ ይልቅ ሰው መሆን ማመንን ይጠይቃል።ህሊና በበሰበሰ አስተሳሰብ ከታጀለ የጎጥ ቂም እና ''እናቱ ለምን እኛ መንደር አልወለደችውም '' መሰል የተደናበረ አስተሳሰብ ወጥቶ ሰው የተባለ ፍጡርን  በማየት ብቻ ማዘንን ይጠይቃል። ህሊና የእራስ ጎጥ ሁል ጊዜ ልክ ነውን ሳይሆን ማመዛዘን እና ግፍ መፍራትን ይፈልጋል።

ሌላው የጎጥ በሽተኞች አስገራሚ ባህሪ እድሜ የሚባል ትምህርት ቤት ፈፅሞ አያስተምራቸውም።እነርሱ እዚህ እድሜ ለመድረስ የተለያዩ  በጎጥም በምንም የማይመስሏቸው ሰዎች ባደረጉላቸው በጎነት  መሆኑን እረስተው ዛሬ ላይ ሆነው የጥላቻ መርዛቸውን ''የኛ አይደለም'' ባሉት ላይ ለመትከል  እንደ ቀትር እባብ ሲቅለበለቡ መመልከት መጨረሻቸውን ለማየት ያስናፍቃል። 

ባጭሩ ጎጥ አምላኪዎች የግለሰብም ሆነ የህዝብ ፀር ናቸው።ግፋቸው ለዘለዓለም ነዋሪ አይደለም።ለሕዝብ እና ለግለሰብ ያላቸው የንቀት ደረጃ በድቡሽት ላይ እንደተሰራ ቤት ሲፈርስ እራሳቸው የታሪክ ምስክር ይሆናሉ።በጥላቻ የገነቡት ከንቱ ስብዕና እራሳቸውን እንደምስጥ ቦርቡሮ ወና መቃብር ያደርጋቸዋል። አንዲት ቀን ከጎጣቸው ውጭ ለሆነ ሰው ለተባለ ግለሰብ በጎ ማድረግ ሳይሆን በትዕቢት መወጠር የተለማመደ ከንቱ እነሱነታቸው የሸረሪት ድር ማድርያ ይሆናል። እግዚአብሔር ለትዕቢተኞች እና ለጎጠኞች ጥብቅና ቆሞ አያውቅም።ትዕቢተኞች እና ጎጠኞች እርስ በርሳቸው ''አይዞህ፣አይዞሽ'' በመባባል የሰሩትን የግፍ ግፍ ለመሸፋፈን ይሞክሩ ይሆናል።ሊዛመዳቸው በቀረበው ሕዝብ እና ግለሰብ ላይ የሰሩትን ኃጢአት ለማጠብ የሚሆን ጠብታ ውሃ ግን ማመንጨት አይችሉም።እግዚአብሔር ለጎጠኞች እና ትዕቢተኞች የሚከፍለው የቁጣ የደሞዝ ቀን እንደ ንስር እየበረረ ይመጣል።    

ጉዳያችን GUDAYACHN
ጥር 20/2008 ዓም (ጃንዋሪ 29/2016)

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...