የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ ይመስለኛል በቀድሞ መስርያ ቤቴ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አብሮኝ ይሰራ የነበረ እና የመንፈሳዊ ወንድሜ የሆነ ወዳጄ ሰርጉ መቀሌ ላይ ነበር።ሙሽሪት አባት እና እናቷ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ነበሩ።መቀሌን ከእዚህ በፊት ወደ አክሱም ፅዮን መንፈሳዊ ጉዞ ስንሄድ መቀሌ ጊዮርጊስ ስናርፍ በማደር እንጂ በውል አላውቃትም ነበር።ከተማዋን ለእዚህ ወዳጀ ሰርግ በሄድኩበት ወቅት በቆየሁባቸው ሁለት ቀናት ውስጥ ግን የአፄ ዮሐንስ ቤተ መንግስትን እና በመቀሌ የማኅበረ ቅዱሳን ማዕከል ፅህፈት ቤት ለማየት ዕድሉ ገጥሞች ነበር።መቀሌ የሚገኘው የማኅበረ ቅዱሳን ፅህፈት ቤት የነበሩት እና መቀሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ያሉ ወንድሞች እና እህቶች ትሕትና እስከመቼም አይረሳኝም።
በተለይ ወደ አክሱም ፅዮን በሁለት የተለያዩ ጊዜያት ከመንፈሳውያን ሰራተኞች ጋር ጉዞ በሄድንበት ወቅት አዳራችን መቀሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ ነበር። የመቀሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰንበት ትምሕርት ቤት አባላት ትህትና ከአዕምሮዬ አይጠፋም። በመንፈሳዊ ጉዞው የነበሩትን ከአንድ መቶ ሃያ የማያንሱትን መንገደኞች በሙሉ እግር አጥበው፣ለእያንዳንዳችን ነጠላ ጫማ እና ፍራሽ ከቤታቸው ሰብስበው አምጥተው፣እራት አብልተው እና ለሚቀጥለው ቀን ጉዞ ስንቅ የሚሆነን እኛ ተኝተን እነርሱ ሌሊቱን ሲሰሩ አድረው የሚሸኙን እነኝሁ የመቀሌ መንፈሳውያን ወጣቶች ነበሩ።
ወደሰርጉ አጋጣሚ ልመልሳችሁ
እድምተኞች በታደሙበት ሆቴል፣በሰርጉ ምሽት እራት ላይ ከአዲስ አበባ ድረስ አብረውን የሄዱት አባት ለሃያ ደቂቃዎች ያህል ትምህርት አስተምረው ሲጨርሱ ከታዳሚው አንድ ሰው ተነሱ እና በትግሪኛ መናገር ጀመሩ።እጅግ መቆጣታቸው በንግግራቸው መሃል እንባ እና ሳግ ሲተናነቃቸው ያስታውቃል።በመሃል ትግርኛውን ገታ አድርገው በሚጣፍጥ አማርኛ ቀጠሉ ከንግግራቸው መሃከል የማስታውሰው ''ወንድሞቻችን እንደገባኝ ከአዲስ አበባ ነው የመጣችሁት። የመቀሌ ህዝብም ተቸግሯል።አሰሙልን! ንገሩልን! ቤተ ክህነት ያሉት ሰዎች ምን እየሰሩ ነው? እየሾሙ የሚልኩት ላይ ጥያቄ አለን።ቅሬታ አለን ስንል ስም ይለጥፉብናል ።መናፍቅ እና ተሃድሶ ከቤተ ክህነት ይውጣልን!አያምታቱን! ንገሩልን! ሃይማኖታችን እየተዋረደች ነው'' እጃቸውን እያወራጩ ነበር የሚናገሩት። የሰርጉ ታዳሚ በሃዘን ከንፈሩን መጠጠ።ሙሽራው እና አብረውን የሄዱት አባት ከአዲስ አበባ መምጣታቸው ብቻ ቤተ ክህነት የሚሰማቸው መስሏቸዋል።እኛ ከአዲስ አበባ መምጣታችን ብቻ ለቤተ ክህነት የቀረብን አድርገውናል።ቆይቶ የሙሽሪት ወላጅ እንዳስረዱን የተናገሩት አዛውንት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ሰብሳቢ በከተማዋም ውስጥ ከቀድሞ መንግስት ጀምሮ የታወቁ እና የተከበሩ አዛውንት መሆናቸው ነገሩን።
ተመሳሳይ ጉዳይ አክሱም ፅዮን አጋጥሞኛል። አክሱም ፅዮን ለመጀመርያ ጊዜ መንፈሳዊ ጉዞ ስሄድ ወደ ስልሳ የምንጠጋ መንገደኞች በአንድ አውቶብስ ተሳፍረን ነበር ከአዲስ አበባ የተነሳነው። አክሱም ፅዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያንን፣የአክሱም ሃውልት፣የቅዱስ ያሬድ ቃለ ሙራድ? የተቀበለበት ቦታ እና የንግሥት ሳባ ቤተ መንግስትን ያየሁበት አጋጣሚ ነበር።በአንድ መኪና የመጣው መንገደኛ በሙሉ የሚያድረው ከቤተክርስቲያኑ አጠገብ ከሚገኝ የእንግዶች ማረፍያ ጠበብ ያለ አዳራሽ ነበር።
በምሳ፣በእራት እና በቁርስ ሰዓት ለመንገደኞች ውሃ ማምጣት ኃላፊነት ከተሰጣቸው ውስጥ ነበርኩ። በመሆኑም በቀን ጊዜ ወደ አስር ደቂቃ የሚያስኬድ ሬስቱራንት መሄድ እና ውሃውን በባሊ ማምጣት ነበረብን። በእዚህ መሃል ነበር ውሃ በነፃ እንድንወስድ የፈቀደልን የሬስቱራንት ባለቤት ጋር መግባባት የቻልነው።ግለሰቡ አዲስ አበባ የኖረ የአክሱም ሰው ነበር።በንግግራችን መሃል ታድያ ባብዛኛው የምናተኩረው በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ዙርያ ነበር።ግለሰቡ ከንግግሮቹ ሁሉ ጎልቶ የሚወጣው የቤተ ክህነቱ በሙሰኞች እና ከሃይማኖታዊ ምግባር እና ቀኖና በወጡ አገልጋዮች የበላይነት መመራቱ እንደሚያሳዝነው ነበር።ሁሉን ማውራቱ እዚህ ላይ ባይጠቅምም ከነገረን ውስጥ የሚገረመው ግን የአክሱም ከተማ ምዕመናን በቅርሳቸው ጥበቃ ላይ የሚፈሩት ከባዕዳን እኩል ቤተ ክህነቱ ውስጥ ያሉ እንደ እርሱ አጠራር ''ዘራፊ እና ቀማኛዎችን'' መሆኑን ሲነግረን ሁላችንም በድንጋጤ የተያየንበት ወቅት ነበር።
እነኝህ ሁለት አጋጣሚዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በቤተ ክህነት ውስጥ ሆነው የሚያምሱት እና ማኅበረ ቅዱሳን ላይ እጃቸውን የሚቀስሩቱ ለሃይማኖቱ ክብር ባለው በትግራይ ሕዝብ ታንቅረው የተተፉ ለመሆናቸው እማኝ የሆንኩባቸው አጋጣሚዎች ሆነው አልፈዋል።ዛሬ የማስታወሻ ደብተሬን እንዳነሳ ያደረገኝ ሰሞኑን የተያዘው አዲሱ የቤተ ክህነት አማሳኞች እና የማኅበረ ቅዱሳንን አገልግሎት ቦታ የለየ አስመስሎ የሚያቀርብ ፅሁፍ በማየቴ ነው።በዛሬው እለት በወጣው ፅሁፍ ላይ ''የአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ገዳምን ስም ማኅበረ ቅዱሳን ለማንሳት ይፀየፋል'' የሚል ሙሉ በሙሉ በውሸት የተለወሱ አረፍተ ነገሮች ይነበባሉ።የሚገርመው ነገር ገዳሙ ተረስቶ እና የሚያስበው አጥቶ በብዙ ድካም እና መንገላታት ከቦታው ደርሶ ለገዳሙ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት ቀርፆ ለገዳሙ ያስረከበ ማኅበረ ቅዱሳን መሆኑን ፀሐፌው አለማወቃቸው ምን ያህል በመረጃ ዘመን ከመረጃ የራቁ መሆናቸውን አመላክቶኛል።አልያም ሃይማኖትን ለማመስ ከአማሾች ጋር የተባበሩም መሰሉኝ። ለሁሉም ማኅበረ ቅዱሳን በምን አይነት ፈተና ወደ አባ ሰላማ ገዳም ተጉዞ ፕሮጀክት እንደቀረፀ እና እንደተገበረ ይህንን ማያይዣ በመክፈት ፊልሙን ይመልከቱ እና ይታዘቡ።
ጉዳያችን
ጥቅምት 11/2007 ዓም (ኦክቶበር 21/2014)
No comments:
Post a Comment