ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, October 24, 2016

በፈሰሰው የኢትዮጵያውያን ደም ላይ ተረማምዶ የሚመሠረት የሕወሓት የተቀባባ ካቢኔ ለኢትዮጵያ ´´ኢንፌክሽን´´ ያለበት ቁስል ነው (የጉዳያችን ማስታወሻ)



ኢትዮጵያ  በለውጥ ማዕበል ውስጥ ነች።ከለውጥ መለስ መፍትሄ የላትም።ማንም የመሰለውን ትንታኔ ሊሰጥ ይችላል።ይህ ግን በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ አይቀይረውም።የኢትዮጵያ ሕዝብ በቴሌቭዥን መስኮት ላይ የሚያያቸውን ሰዎች ለውጥ ሳይሆን የኢትዮጵያ እንደ ሀገር መቀየር እና የማኅበረሰብ ሽግግር ይፈልጋል።ይህ ሽግግር ደግሞ በተቀባባ የሕወሓት መሠረትነት ሳይሆን ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የሚያቆም፣ ሁሉንም በእኩልነት የሚያሳትፍ እና የሕወሓትም ሆነ የማንም የበላይነት የማይታይበት መንግስት ማቆምን ያለመ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ሕወሓት የተቀባባ መንግስት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማሳየት ሽር ጉድ እያለ ነው። ዛሬ ጥቅምት 14፣2009 ዓም የመጀመርያው የተቀባባ ካቢኔ ለኦሮምያ ተበርክቷል።የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የኦሮምያ ምክርቤት አዲስ ካቢኔ እና የክልሉ ፕሬዝዳንት መሾሙ ተነግሯል።ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ከአንድ ሺህ  በላይ ኢትዮጵያውያን ከተገደሉ እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከታሰሩ በኃላ ይልቁንም መሰረታዊው የሕወሓት የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያውያን ጫንቃ ላይ በአዋጅ ስም ይበልጥ በተጫነበት ሰዓት የተቀባባ ካቢኔ በመመስረት የኢትዮጵያውያንን ጥያቄ መልሻለሁ ብሎ መመፃደቅ የሚያስከትለው አደጋ ቀላል አይደለም።

´´አሳማ ሊፒስቲክ ብትቀባ አሳማነቷን አትቀይረውም´´ የሚባለው የፈረንጆቹ አባባል ሕወሓት ለኢትዮጵያ ሕዝብ መደለያ ሊያቀርብ ያሰበውን  የተቀባባ ካቢኔ በሚገባ ይገልፀዋል።ሕወሓት ከኃላ ሆኖ በማሽከርከር የነበረ የጎሳ ፖለቲካውን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በባሰ መልኩ ኢንድጭን መፍቀድ በፈሰሰው የኢትዮጵያውያን ደም ላይ መረማመድ ነው።ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ መሰረታዊ የፖለቲካ ችግር ምንም አይነት መፍትሄ አይሰጥም። ይልቁንም ቆይቶ ለባሰ ችግር ኢትዮጵያን የሚዳርግ
´´የኢንፌክሽን´´ቁስል ማለት ነው ይቻላል።በኢንፌክሽን የተመታ ቁስል ስር የሰደደ እና በቀላሉ የማይድን ይልቁንም የሰውነት መቆረጥ ድረስ የሚያደርስ አደጋ ያለው ነው።

ሕወሓት ለገጠመው የህዝብ ተቃውሞ ማስታገሻ ክኒን አድርጎ ያቀረበው የካቢኔ አባላትን መቀየር ነው።ለእዚህም እንዲረዳው ታማኝ ተቃዋሚዎች እና በከፍተኛ ትምህርት ቋማት አካባቢ ያሉ ለስርዓቱ የሚቀርቡ ግለሰቦችን ጊዚያዊ ክኒን ሁኑኝ እያለ እየተማፀነ ነው።ይህ የሕወሓት መሰረታዊ ባህሪ ነው። ባለፉት ታሪኩም ስልጣኑ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ ´´ከፀሐይ በታች የማንደራደርበት ጉዳይ የለም´´ የሚል የማባባያ ቃላት ተጠቅሞ ለማለፍ ይሞክራል።በ1997 ዓም ከቅንጅት ጋር አቶ መለስ ሲደራደሩ ወቅቱን በዘዴ ለማለፍ ብቻ አልመው እንደነበረ በማስከተል የቅንጅት አመራሮችን በሙሉ እስር ቤት ሲያስገቡ ታይቷል። ኢትዮጵያ ከገባችበት የጎሳ አጣብቂኝ ተላቃ በሰላማዊ መንገድ ወደ ሽግግር መንገድ ብትመጣ የማይወድ የለም።ሆኖም ግን ይህ በሕወሓት ዘመን ይሆናል ብሎ ማመን እራስን ማታለል ነው።ለእዚህ ሁለት ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል። 

የመጀመርያው ምክንያት ሕወሓት እንደ ሌላው ሀገር ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን የመሰረቱት ሳይሆን የአንድ ክልል ሰዎች ብቻ የመሰረቱት ነው።እነኝህ ግለሰቦች ደግሞ ስልጣናቸውን መጠበቅያ አጥር አድርገው የሚከተሉት ጎሰኝነትን ማራገብ እና ስልጣንን በጠበንጃ አስገድዶ መጠበቅ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ሕወሓት ለአርባ ዓመታት የሰራቸው በሀገር ውስጥም ሆነ  በውጭ ሃገራት ከባድ ወንጀሎች አሉ።ስለሆነም ከስልጣን ከወረድኩ በእነኝህ ወንጀሎች እጠየቃለሁ ብሎ ስለሚያስብ ስልጣኑን የህዝብ ደም እያፈሰሰ ማቆየትን ይመርጣል።

እንደመደምደምያ በእዚህ ሁሉ መካከል የዘውግ ተቃዋሚም ሆነ በኢትዮጵያዊነት ስር የተጠለሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ወሳኝ ደረጃ መድረሳቸውን ማወቅ አለባቸው። ወቅቱ በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ እያተኮሩ ከመተባበር የሚሸሹበት ሳይሆን በግልፅ የጋራ የማግባቢያ ማታገያ አጀንዳ ቀርፆ ወደ ተግባር መሄድ አለባቸው።ወደ እዚህ ህብረት ለመግባት ፈቃደኛ ያልሆኑትንም በመጠበቅ ሌላ አመታትን ማባከን በሕዝብ ስቃይ መቀለድ ነው።አሁን የፖለቲካ ድርጅቶች መሰረታዊ የፍልስፍና መርህ ነጥሮ የሚወጣበት እና በሕዝብ የሚደገፉ እና የማይደገፉ መሆናቸው መለየት አለባቸው።በአላማ እና በአስተሳሰብ አንድ የሆኑት  ሰፊ መሰረት ይዘው ሕዝብ የሚያታግሉበት ወቅት ነው። ከእዚህ በዘለለ በዓላማ ከተለዩት ጋር የጎንዮሽ ንትርክን ባለማድረግ ነገር ግን ግልፅ የሆነ የመስመር ልዩነትን ለሕዝብ ግልፅ በማድረግ እና ፍርዱን ለሕዝብ በመተው ትግሉን መግፋት  ብቸኛው አማራጭ ነው።


ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...