ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, September 21, 2023

''አክቲቪዝም ከጆርናሊዝም'' የደባለቀባቸው ዩቱበሮች በአማራ ክልል የሚፈሰው የመከላከያ እና የአማራ ክልል ህዝብ ደም አልታያቸው ብሏል። በኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ሊባሉ ይገባል።


  • የሰው ደም እየፈሰሰ መከላከያና የአማራ ክልል ታጣቂ ኃይል አይነጋገር የሚሉት በውጪ ሀገር ሶፋ ላይ የተቀመጡት መሆናቸውን ልብ ይሏል።
  • የሰላም ንግግሮችን ለማጣጣል የሚሞክሩትን አጥብቀን መቃወም ኢትዮጵያዊ የውዴታ ግዴታችን ነው።
============
ጉዳያችን 
============

ኢትዮጵያ በወንድማማቾች ጦርነት ስትታመስ 50 ሙሉ ዓመት ዘንድሮ ይሞላታል። የኢትዮጵያ አብዮት በ1966 ዓም ከፈነዳ እነሆ በያዝነው 2016 ዓም 50 ዓመት ይሞላዋል።የወቅቱን ለውጥ ተከትሎ ከተነሳው የቀይሽብር እና ነጭ ሽብር ፍጅት ጀምሮ ከሻብያ እና በኋላ የእርሱ ውላጅ የሆነው ህወሓት ጋር ለ17 ዓመታት የተደረገው ጦርነት መቶ ሺዎችን ገብሮ የሃገሪቱን አንጡራ ሃብት በልቶ፣በጣት የሚቆጠሩ ስደተኞች የነበሯት ኢትዮጵያ ልጆቿ እንደጨው በመላው ዓለም ተዘርተው የወታደራዊ መንግስት ወድቆ የጎሳ ፖለቲካ የሚያቀነቅነው የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ሌላ የመከራ ምዕራፍ በኢትዮጵያ ላይ ከፈተ።

በ27 ዓመቱ የጎሳ ፖለቲካ የኢትዮጵያ ልጆች ስደት ከአውሮፓና አሜሪካ እንዲሁም ጎረቤት የአፍሪካ ሀገሮች ወደ መካከለኛው ምስራቅ የኢትዮጵያ የነገ ተስፋ የሆኑ ወጣት ልጆች የስደት ዘመን ሆነ። ከግማሽ ሚልዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ባብዛኛው ወጣት ሴት እህቶቻችን በመካከለኛው ምስራቅ ብቻ ተበተኑ፣ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት ባለ 120 ሚልዮን ህዝብ ሆነች። ይህ ሁሉ ጥፋት ከውጭ ብቻ የተሴረ የሴራ ውጤት ብቻ አይደለም። የእኛው በጥቅምና በስልጣን ያበዱ ፖለቲከኞቻችን የተደናበረ የፖለቲካ አዙሪት ውጤትም ነው።

ባለፉት 5 ዓመታትም የኢትዮጵያ የጸጥታ ሁኔታ ችግር ተባብሶ የጎሳ ፖለቲካው የበለጠ አገንግኖ ወጥቶ የክልሎች የግጦሽ ቦታ እና ትንንሽ መንደሮች የእኔ ነው የእኔ ነው ተራ ንትርክ ሁሉ እስከ ሚልዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የሚያፈናቅል፣ሺዎችን የሚያሰድድ እና ወደ የበለጠ ድህነት የሚከት ሆነ። ኢትዮጵያ የተሻለ መንገድ ለመያዝ ስትታትር አዳዲስ ግጭቶች እየተፈለፈሉ እና ፖለቲከኞቻችን ደግሞ ዘለው እያቦኩት (እነርሱን እሳቱ አይነካቸውም) ህዝቡን ለበለጠ መከራ እየማገዱ ሀገሪቱን የሽብር ምድር ለማድረግ ከላይ ታች እያሉ ነው።

መንግስት በሌላ በኩል የቆረጠ አቋም እና ወጥ የሆነ አሰራር እና የጸጥታ መዋቅር እንደመመስረት በየክልሉ ያሉ የጎሳ አደረጃጀቶች እና ታጣቂዎች ከወለጋ እስከ ቤኒሻንጉል ከጌድዮ እስከ ቦረና ህዝብ ሲያፈናቅሉና ከተሞች ሲያወድሙ የመረረ እርምጃ ከመውሰድ ጋር የተለየ እና አዲስ አቅጣጫ ማስቀመጥ ስለተሳነው ኢትዮጵያ በጎበዝ አለቃ የምትመራ ሀገር እስክትመስል ድረስ ከአንዱ የሀገሪቱ ክፍል ወደ አንዱ የሀገሪቱ ክፍል መሄድ እንደ ትልቅ ዕድል እንዲቆጠር ሆኗል።

ወደወቅታዊው የሀገራችን ሁኔታ ስንመጣ በአማራ ክልል እና በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ከፍተኛ ቅቡልነት የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት በኦሮምያ ክልል ያለው የብልጽግና የቀድሞው ኦህዴድና በውስጡ የተሰገሰገው የኦነግ ሸኔ ቡድን ባራመዱት የጎሳ ፖለቲካ እና የማንአለብኝነት ጥቃት በተለይ የአማራ ተወላጆች በሆኑት የወለጋ እና ሌሎች ቦታዎች ላይ የፈጸሙት ግፍ አሁን በአማራ ክልል ለተነሳው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ሆኗል።በእዚህም በብሄርተኝነት የመቀስቀስ ስራው ለብሄርተኞች አመቺ ሆኖላቸዋል።  

''አክቲቪዝም ከጆርናሊዝም'' የደባለቀባቸው ዩቱበሮች በአማራ ክልል የሚፈሰው የመከላከያ እና የክልሉ ህዝብ ደም አልታያቸው ብሏል። በኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ሊባሉ ይገባል።

በአማራ ክልል የተነሳው ቁጣ በኦሮምያ ክልል አክራሪ ቡድኖች የፈጸሙት ጥላቻን የተሞላ የግፍ ውጤት መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል።ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይሏን በራሷ ህዝብ ፈጅታ ሌላ የታሪክ ጠባሳ ይቀመጥ ማለት አይደለም። መንግስት በውስጡ ያሉትን በኦሮሞ ስም የሚነግዱትን አክራሪ ብሔርተኞች ማስወጣት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ወደ የለየለት የእርስበርስ ጦርነት የሚከተውን የጎሳ ፖለቲካ እና አደረጃጀት በሕግ የማገድ ውሳኔ ድረስ ካልሄደ ነገሮች ከተበላሹ በኋላ እና ሁሉም ነፍጥ ካነሳ በኋላ ''እንደ 1966ቱ የእንዳልካቸው ካቢኔ '' በኋላ ከረፈደ የጎሳ ፖለቲካ ታግዷል ወዘተ ቢሉት አይሰራም። ሁሉም መከወን ያለበት በጊዜው ነው።

ከእዚህ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ያለው በመከላከያና በአማራ ክልል ታጣቂ (ፋኖ) መሃከል ያለው ግጭት በምንም መልኩ መቆም ያለበትና ያሉት ጉዳዮች ሁሉ ወደ ንግግር መምጣት አለባቸው። ይህ የመነጋገር ጉዳይ ሲነሳ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉት አክቲቪዝም ከጆርናሊዝም የተደባለቀባቸው ዩቱበሮች ናቸው። እነኝህ ዩቱበሮች ከውጭ ሆነው ''እስከ መጨረሻው ተጫረሱ'' ዓይነት መልዕክት ብቻ ሳይሆን ወደ ንግግር ይመጣ ሲባል ''ይሄ ባንዳ፣የአማራ ጠላት '' እያሉ ከምሁራን እስከ የሃይማኖት አባቶች በመሳደብ እና በማሸማቀቅ ሰው ለሀገሩ ያለውን ሃሳብ በነጻነት እንዳይሰጥ ከሽብር ያላነሰ ተግባር እየፈጸሙበት ነው። የዛሬ 50 ዓመት በኢትዮጵያ የነበረው ቀይ ሽብር ብቻ አልነበረም።የወቅቱ መንግስት ተቃዋሚዎችም ነጭ ብለው የሚጠሩት ሽብር ነበራቸው። በወቅቱ ሁሉም ለሚሰራው ለራሱ እና ለደጋፊዎቹ '' እንደ ቅዱስ ስራ '' እየተወሰደ ይሞከሻሹበት ነበር። ዛሬም በ21ኛው ክ/ዘመን ተቀምጦ '' ብልጽግና የሆነውን በሙሉ ፍጀው፣በለው'' የሚባልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል። በሌላ በኩል የፋኖ ታጣቂ ብቻ ሳይሆን ለፋኖ የምትደግፉ ናችሁ እየተባሉ ዜጎች ፍዳቸውን እያዩ ነው። ሁሉም እንደየቀይ ሽብር ዘመን የራሱን ያሞግሳል። የአሁኑን የከፋ የሚያደርገው ለአቅመ ጋዜጠኝነት ያልደረሰ ሁሉ ለዩቱብ ክፍያ ብሎ ሀገር ወዳድ መስሎ ግጭቶጭ እንዲጠመቁ ቀን ሙሉ ላይ ታች ሲል መዋሉ ነው። በወንድማማቾች መሃክል ያለ የደም ወሬ በማዛመት ከዩቱብ የተገኘ ገንዘብ ለቤተሰብስ ጤና ይሆናል? ይህንን በጊዜ የምናየው ነው። ዩቱበሮች ስለየምስኪኑ ገበሬ ቁስል አውሮፓና አሜሪካ ተቀምጠው ሊሰማቸው አልቻለም። የእነርሱ ልጆች ትምህርት ቤት እየሄዱ ሃገር ቤት ያለው የገበሬው ልጅ ህይወት ግን ገና አልተሰማቸውም። ይልቁንም ''ከመከላከያ ጋር አንዳች ንግግር ታደርኛ'' እያሉ የማሸማቀቅ እኩይ ተግባራቸውን ቀጥለውበታል። 

ኢትዮጵያ ከእዚህ በላይ የምትሸከመው የጦርነት ትከሻ የላትም። 50 ዓመታት ያህል ደም ፈሶባታል።መንግስት በኦሮምያ ክልል ያለው ጽንፍ የረገጠ አስተሳሰብና የዕብሪት አካሄዶችን አደብ ማስገዛት ብቻ ሳይሆን የጎሳ ፖለቲካውን የሚያከስም የህግ ማዕቀፍ በቶሎ አውጥቶ ስራ ላይ ማዋል አለበት። በአማራ ክልል ያሉት ታጣቂ የፋኖ አባላትም ከመከላከያ ጋር በቶሎ እርቅ ፈጽሞ እና በክልሉ ሰላም እንዲመጣ በመነጋገር የጋራ ኢትዮጵያን ለመጠበቅ መነሳት አለባቸው። ህዝብ ሁሉንም እየታዘበ ነው።ታዝቦ ታዝቦ ለሰላም አልቆም ያለው ማናቸውም ኃይል ላይ ማለትም መንግስት ላይም ሆነ በአማራ ክልል ያለው ታጣቂ ላይ ድንገት ይነሳል። ከእዚህ ሁሉ በፊት ሁሉም አደብ የመግዣ ጊዜው አሁን ነው። የኢትዮጵያ ገበሬ ደግሞ ከፖለቲከኛው በተሻለ መንግስት ምን ማለት እንደሆነ ያውቃል። የመንግስት ድንበር ይፍረስ የሚል አይደለም። ከመጠን ያለፈ የሕግ መጣስ ያስቆጣዋል። ይህ ቁጣ ግን የታጠፈው ሕግ ተመልሶ ሲዘረጋ ይመለሳል።

ባጠቃላይ የባዕዳን ጣልቃ ያልገባበት የመነጋገር እና ኢትዮጵያ ከገባችበት የፖለቲካ ቅርቃር የሚያውጣ የመፍትሄ መንገድ ከመንግስትም ከፋኖም ይጠበቃል። አሜሪካን አውሮፓ ቁጭ ብለው መንግስት ለመገልበጥ ነው መሄድ ያለብህ የሚለው ስብከት ኢትዮጵያን ወደ መበተን ደረጃ የሚያደርስ አደገኛ አካሄድ ስለሆነ ጆሮ ሊሰጠው የሚገባ አይደለም። መንግስት ይቀየራል።የሚቀየረው ግን በጦርነት ክልልን በማውደም አይደለም። ትግል ሲያስፈልግ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሰላማዊ ትግሎች መንገዶች አሉ።ከእዚህ ባለፈ የምርጫ ሰሌዳን ተከትሎ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ የሚፈልገውን በመምረጥና ድምጹ እንዲከበር በመታገል ወደ የሚፈለገው ለውጥ መምጣት ይቻላል።ቢያንስ በ21ኛው ክ/ዘመን መንግስት ባልሰለጠነ መንገድ በማውረድ ሀገር ከመበተን መታደግ የሁሉም ግዴታ መሆኑን ማወቅ አለብን።ከእዚህ ጋር የሰላም ንግግሮችን ለማጣጣል የሚሞክሩትን አጥብቀን መቃወም ኢትዮጵያዊ የውዴታ ግዴታችን ነው።

+++++++++++++++++++++++++++++


No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...