ጉዳያችን / Gudayachn
ነሐሴ 25/2009 ዓም (September 1/2017)
ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com
ነሐሴ 25/2009 ዓም (September 1/2017)
ኢትዮጵያ ውስጥ ነገሮች በወራት ሳይሆን በሳምንታት ውስጥ እየተቀየሩ ነው።በአገዛዙ ላይ የተነሳው ተቃውሞ ምኑንም ያህል ግድያ እና እስር ቢከተለውም ሕዝብ በበለጠ የተቃውሞ መንፈስ በገዢው ስርዓት ላይ ያለው ጥላቻ እየባሰ ብቻ ሳይሆን እንደ እሬት እየመረረ መጥቷል።በአንፃሩ ስርዓቱ የግፍ ጡጫ በማብዛት የአገዛዝ ዘመኑን የሚረዝም መስሎት እየታተረ ይገኛል።ከእዚህ ሁሉ ጋር ደግሞ በገዢው ስርዓት ወገን ያሉትም በእራሳቸው የመደናገር፣የመዋለል እና የመባዘን ስሜት ተደባልቆባቸው ምንም እንዳልሆኑ ሁሉ በአሸንዳ ዳንኪራ እራስን ለመደለል ሲሞከር ይስተዋላል። በተቃዋሚው ጎራ በኩል አድፍጦ ከሚሰራው እስከ በአደባባይ የሚፎክረው እያንዳንዱን የሀገር ቤት እንቅስቃሴ በእርሱ እንደተመራ ለመግለፅ መፎካከር ድረስ የሚታዩ ገፅታዎች አሉ።በኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ከጎንደር እና ጎጃም በረሃዎች ያለው የታጣቂ እንቅስቃሴ እስከ ሱማሌ እና ኦሮሞ ድንበር የሚል ስም በተሰጠው ግጭት ገዢው ስርዓት እያፋፋመው እንደሆነ እየተሰማ ነው። የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ከሚታሰበው በላይ እየደከመ ብቻ ሳይሆን እየደቀቀ ነው ለማለት ያስደፍራል።ይህ ደግሞ በመጪው አዲስ ዓመት በባሰ መልኩ እንደሚቀጥል ከግምት በላይ ማስቀመጥ ይቻላል።በቅርቡ በኦሮምያ በተደረገው አድማ ብቻ ብዙ ሺህ ኩንታል ቡና ለውጭ ሀገር ገበያ በወቅቱ መቅረብ አልቻለም።በዐማራ ክልል ከተሞች ለተከታታይ ቀናት የተደረገው የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ እና አድማውን ተከትሎ የተከሰተው የገበያ መቀዛቀዝ የሕዝቡን እና የመንግስትን የእየዕለቱ እንቅስቃሴ አውኮታል።
ከላይ ከተጠቀሱት ክስተቶች በተጨማሪ የስራ ማቆም አድማዎቹን ተከትሎ ሕዝብ ለመንግስት ግብር እንደማይከፍል በግልፅ መናገር ጀምሯል።ሱቃቸውን ዘግተው የተቀመጡ እና በአድማው ተሳተፋችሁ ተብለው ሱቃቸው የታሸገባቸው የትራንስፖርት መኪናቸው ታርጋ ገንዘብ ሳይከፍሉ መውሰድ እንደማይችሉ የተነገራቸው እና ሌላም ተደማምሮ የምጣኔ ሃብቱ በሁሉም መልክ ተቃውሷል።የገበያ ስርዓቱ መቃወስ የምጣኔ ሃብቱን እንዳቃወሰው ሁሉ ሕዝብ ከነበረበት የኑሮ ደረጃ የበለጠ ወደ ታች እንዲወርድ፣ መንግስትም ያለው ገቢ እንዲያሽቆለቁል ምክንያት ሆኗል። ይህ ሁኔታ ከንበረው የፖለቲካ ውጥረት ጋር ተዳምሮ የህዝቡን ማኅበራዊ እንቅስቃሴ አውኮታል። እነኝህ የፖለቲካው ውጥረት፣የምጣኔ ሃብቱ መቃወስ እና የማኅበራዊ ኑሮ መናጋት የህወሓት መንግስትን ወደ አናርኪስት መንግስት ይቀይረዋል።መንግስቱን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም ወደ እዚሁ አደገኛ ደረጃ እንዳያደርሳት ያሰጋል።
አናርኪዝም ህገ ወጥነት የሰፈነበት፣ ህገ ወጥነቱ ለመሰረታዊ የሞራል ህጎችም የማይታዘዝ፣ማንም ጉልበተኛ በዕለቱ ባወጣው መመርያ የሚመራው ስርዓት መገለጫ ነው። በእርግጥ የህወሓት መንግስት ላለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት እነኝህ ጠባዮች አልታዩበትም ማለት አይቻልም። ሆኖም ግን ላለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት የታዩት ህገ ወጥ ፀባዮች በሕዝቡ ሕግ አክባሪነት እና አንገት ደፍቶ የመመታት ፀባይ ተሸፍኖ ቆይቷል። ከእንግዲህ ወዲህ ግን ስርዓቱ የበለጠ ሕግ አክባሪ ለመምሰል ቢሞክርም የሚያመጣው ለውጥ ስለማይኖር የአናርክዝም ፀባዩን ሕዝብ በገሃድ በመንግስት ላይ በመግለፅ ተቃውሞውን ይቀጥላል።ይህ ሁኔታ ደግሞ ወደ አደገኛ መልክ ከመቀየሩ በፊት በሁሉም መንገዶች ተፈትኖ ኢትዮጵያን አሁን ላለችበት አደገኛ ደረጃ ያደረሳትን የህወሓት መራሹን መንግስት በባለአደራ መንግስት መቀየር እና የኢትዮያን ህልውና ማስከበር ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን ይገባል።ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከጦር ሰራዊቱ ጀምሮ የከበደ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት የቤት ስራቸውን በሚገባ መወጣት ይኖርባቸዋል።
ከፈረሱ ጋሪው የቀደመው የአዲስ ዓመቱ መርሃ ግብር
የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ የህወሓት መንደርተኘንት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ውጤት መሆኑ እየታወቀ እና የአድልዎ የጭቆና ደረጃው ቅጥ ባጣበት በእዚህ ወቅት ህወሓት የአዲስ ዓመትን ተሻግሮ የሚነሳው የህዝብ ቁጣ ስላስፈራው ብቻ የአዲስ ዓመት መደለያ መርሃ ግብር ''የከፍታ ዘመን'' በሚል አዲስ ዘመቻ ጀምሯል።ነገሩ '' የቸገረው ምንትስ ይአጌባል አይነት ካልሆነ በቀር በእዚህ አይነት መልክ በዓል ከማክበር በፊት ከህዝብ ጋር መታረቅ በሚገቡ መሰረታዊ ነጥቦች ተስማምቶ መታረቅ ቢቀድም ነገሩ ባማረ ነበር።የመንግስት ቃል አቀባይ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ከትናንት በስቲያ በኢትዮጵያ ለቀጣይ ቀናት እያንዳንዱን ቀን የሕፃናት፣የአረጋውያን፣የንባብ፣የአረንጉአዴ ልማት፣የመከባበር ቀን፣ ወዘተ ተብሎ መሰየሙን እና በልዩ ሁኔታ እንደሚከበሩ አስታውቀዋል።የቀናቱ ስያሜ በራሳቸው የሚስቡ ስሞች ይዘዋል።እነኝህ ቀኖች ላለፉት 26 ዓመታት ሥራ ላይ እንዲውሉ የጠየቁ ወደ እስር ቤት ሲወረወሩ መክረማቸው የታወቀ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የአዲስ ዓመት አከባበሩ መንገድ በእራሱ ''ከፈረሱ ጋሪው ያስቀደመ'' መርሃ ግብር ነው። የእዚህ አይነቱ መርሃ ግብር ልጆቹ እስር ቤት ለሚማቅቁበት ሕዝብ፣ የችርቻሮ ሱቁ ለታሸገባት እናት፣ በስደት ልጆቹ ድንበር አልፈው በረሃ የሚንከራተቱ እና ለናፈቁት አረጋዊ የሚሰጠው ስሜት የለም።
ከአዲስ ዓመቱ መርሃ ግብር በፊት የፖለቲካ መድረኩ ቢፀዳ፣ ሕዝብ የመናገር እና የመፃፍ በመንግስት የሚወከልበት የውክልና ደረጃው በእውነተኛ የዲሞክራሲ መንገድ እንዲሆን የመተማመኛ ሥራ ቢሰራ እና የከሸፈው ደም አፋሳሹ እና ከፋፋዩ የህወሓት ፈድራሊዝም ፖሊሲ በእውነተኛ እና አድሏዊ ባልሆነ የፈድራል ስርዓት መተካቱ ቢቀድም ከህዝብ መተማመኛ በተገኘ ነበር። አሁን ግን '' ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት'' አይነት ሥራ እየተሰራ ነው።
ከአዲስ ዓመቱ መርሃ ግብር በፊት የፖለቲካ መድረኩ ቢፀዳ፣ ሕዝብ የመናገር እና የመፃፍ በመንግስት የሚወከልበት የውክልና ደረጃው በእውነተኛ የዲሞክራሲ መንገድ እንዲሆን የመተማመኛ ሥራ ቢሰራ እና የከሸፈው ደም አፋሳሹ እና ከፋፋዩ የህወሓት ፈድራሊዝም ፖሊሲ በእውነተኛ እና አድሏዊ ባልሆነ የፈድራል ስርዓት መተካቱ ቢቀድም ከህዝብ መተማመኛ በተገኘ ነበር። አሁን ግን '' ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት'' አይነት ሥራ እየተሰራ ነው።
ባጠቃላይ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ደረጃም ከሁሉም አቅጣጫዎች ነገሮችን ለመመዘን ብንሞክር በህወሓት ውስጥ ያለች ኢትዮጵያ ከባለፈው አሳዛኝ የውርደት ዘመኖቻችን በባሰ መንገድ እራሱ ህወሓትም ሆነ ሃገሩ ወደ አናርኪዝም ወይንም የባሰ ስርዓተ አልበኝነት የማምራቱ ሂደት በጣም ሰፊ ነው።አንዳንዶች ህወሓት አንዳንድ ጥገናዊ ለውጥ ካደረገ ነገሮች ሊስተካከሉ ይችልሉ የሚል የፖለቲካ ቂላቂልነት የሚያጠቃቸው ይኖራሉ።ጥገናዊ ለውጥም ሆነ ''የከፍታ ዘመን'' እየተባለ ድግስ ቢዘጋጅ መሰረታዊ የፈድራሊዝም ፅንሰ ሃሳብም ሆነ የፖለቲካ፣ወታደራዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ እና የደህንነት ክፍሉ ሁሉንም ኢትዮጵያ በሚወክሉ የፖለቲካ ኃይሎችም ሆነ ሕዝብ ካልተደለደለ እና የመገናኛ ብዙሃኑ ፍፁም ነፃነት ካልተጎናፀፉ የኢትዮጵያ እድገት የሚያመጣ ለውጥ ይገኛል ብሎ መጠበቅ እራስን መደለል ብቻ ነው። ህወሓት የእራሱም ሆነ የውጭ አማካሪዎች እየቀጠረ የፖለቲካ ትኩሳት የማብረድ የተለያዩ ስልቶችን ሲቀይስ የኖረ ነው።ሕዝብ ግን አሁን ባለበት ደረጃ መልሶ የመታለል አቅም ይኖረዋል ተብሎ አይገመትም።ባጭሩ ሌሎችን መፍትሄዎች ወደጎን ብሎ የእዚህ አይነቱ ድብብቆሽ ጫወታ ላይ ብቻ ህወሓት በማትኮር እጁን ለማፍታታት ከሞከረ ወደ ለየለት የአናርኪዝም ስርዓት መቀየሩ እና የእራሱንም ባለስልጣናት ማዘዝ ወደማይችልበት ከመድረሱም በላይ ሕዝብ በእራሱ መንገድ በሚሄድባቸው እራሱን ከአናርኪስት መንግስት ለመጠበቅ በሚያደርገው እራስን የመከላከል ትንቅንቅ ሃገሩ ባጠቃላይ ወደ አናርኪዝም ደረጃ የመገፋቱ አደጋ ቅርብ ነው።ለእዚህ ነው አሁን ላለው ምስቅልቅል ሁኔታ የጦር ኃይሉ እራሱን አደራጅቶ ሙሰኞች እና ኢትዮጵያን የከዱ ባለስልጣናት ለፍትህ የማቅረብ ግዴታ ከሕዝብ እና የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ተባብሮ የባለ አደራ መንግስት የመመስረት ግዴታ እንደሚኖርበት ተደጋግሞ ለመናገር የሚሞከረው።አናርኪዝምን ለመቅደም ኢትዮጵያን ከህወሓት ማላቀቅ ቸል የሚባል ተግባር አይደለም።
''አሳልፈናል ክፉ ደጉን፣
ቃል ኪዳን አለው (እኛ ኢትዮጵያውያንን ለማለት ነው) እንዳይለየን'' ቴዎድሮስ ካሳሁን
ቃል ኪዳን አለው (እኛ ኢትዮጵያውያንን ለማለት ነው) እንዳይለየን'' ቴዎድሮስ ካሳሁን
ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com
No comments:
Post a Comment