ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, July 30, 2012

የኢትዮዽያ ጉዳይ በማን እጅ ነው? (አጭር ትረካ)

¨ወቸው ጉድ ሰማዩ እንዴት ጠቁሯል ጃል!¨ አሉ አባ እንጦስ አንገታቸውን ወደ ሰማይ አቅንተው።
¨አዎን አባቴ ክረምት አይደል ወቅቱ ያውም ወርሃ ሃምሌ¨ ራማ መለሰ እርሱም እንደ እሳቸው አንገቱን ቀና አርጎ በ አንድ እጁ ግን የ አባን እጅ እንደያዘ።
¨በል ልጄ ወደ ገዳማችን እንሂድ ተነስ¨ ቀጠሉ አባ እንጦስ በግራ እጃቸው ወተት የመሰለ ጺማቸውን ዳበስ እያደረጉ ¨ለመሆኑ ስንት ሰዓት ነው እንግዶቹ የመጣሉ ያልከኝ?¨
¨ዘጠኝ ሰዓት ነው አባቴ¨ መለሰ ራማ አባ የተቀመጡበትን አጎዛ መጠቅለል ጀመረ።
¨የቀትር ጸሎት እንደፈጸምኩ ታስገባቸዋለህ¨ አሉ አባ አሻግረው ገዳማቸውን እያዩ ከ ራማ ጎን በፍጥነት መራመድ ይዘዋል።

ራማ የ አባ እንጦስ ረድእ (በ እለት እለት ኑሮ የሚያገለግላቸው) ከሆነ እነሆ አምስት አመታት አልፈዋል።እርሱን ለመምከር ወይንም ለማስተማር ካልሆነ ብዙ ሲናገሩ የማያውቃቸው አባ ዛሬ እንግዶች ይመጣሉ ብሎ ከነገራቸው ወዲህ በተለየ መልክ ትኩረት ሰጥተው ሰዓቱን ሲጠይቁት አሁን ሶስተኛ ጊዜ ነው።
¨ ዛሬ ስለሚመጡት እንግዶች የተለየ ነገር መኖሩን አባ ቢያውቁ ነው እንጂ እንደዚህ አበክረው አይጠይቁም ነበር።¨ አለ ለራሱ በሃሳቡ።
አባ ለዋዛ ፈዛዛ ንግግር ፈጽሞ ቦታ የላቸውም።ብዙ ያዳምጣሉ።አስፈላጊ ነው ብለው ካላመኑ በቀር ባብዛኛው ትንሽ ይናገራሉ።
ራማ ይህን ሁሉ የ አባን ባህሪ፣መንፈሳዊነት፣አስተዋይነት ሁሉ ሲያወጣ ሲያወርድ።
¨በመጀመርያ ተግባር ቤት ገብተን ንፍሮውን አይተን እንመለስ¨ ሲሉ አባ እንደመባነን አደረገው እና ¨ደረስን እንዴ?¨ ብሎ ቀና ቢል የገዳማቸው መግቢያ ላይ ያለው ትልቅ የ እንጨት መስቀል ለካ ከፊቱ መሆኑን አስተዋለ።
ቀጠለናም ¨ይተዉ አባቴ እርስዎ ወደ ጸሎት ይግቡ እኔ አይቸው ልመለስ።ወዲያውም እንጨት ከፈለገ ቆስቁሸው እመለሳለሁ¨ አለ።
¨የለም ልጄ አንተ ለእንግዶቹ ውሃው እንዲቀዘቅዝ እንስራው ውስጥ ቀድተህ አዘጋጀው¨ ብለው አባ ወደ ተግባር ቤት መንገድ ጀመሩ።
የ አባ እንጦስ ገዳምን ድፍን ኢትዮዽያ አይደለም ከብዙ የ አለማችን ክፍሎች ብዙ ሰዎች እየመጡ ልመናቸው ተሰምቶ፣ችግራቸው ተቃሎ ተመልሰዋል።
በ ራማ ዘንድ የ ዛሬ እንግዶች ከ እዚህ ቀደም እንደነበሩት እንደሚሆን ቅንጣት ታክል አልተጠራጠረም-ገዳሙን ለመሳለም የሚመጡ አልያም ለመጎብኘት የሚመጡ የባህር ማዶ ሰዎች::

ከ ቀኑ ዘጠኝ ሰዓት እንግዶቹ ወደ ገዳሙ መግባት ጀመሩ። ራማ የ እንግዶቹን ብዛት የገመተው እስከ ሰባት ሰው  ነበር። ሆኖም ግን ቁጥራቸው ከ ሁለት መቶ በላይ ሆነው ስለተገኙ የ አባ እንጦስ ትንሽ ክፍል ፈጽማ የምትበቃ ባለመሆንዋ ከገዳሙ መግብያ በስተቀኝ በኩል ባለው መስክ ላይ እንዲቀመጡ ሆነ።
¨አባቴ ይህን ያህል ህዝብ ይመጣል ብለው ገምተዋል? እኔ እኮ የገመትኩት ቢበዛ አንድ አምስት፣ሰባት ሰው ነበር።¨ አለ ራማ አባ እንግዶቹን መስቀል ሲያሳልሙ ወደ ጆሯቸው ጠጋ ብሎ።
አባ እንግዶቹ መስቀል ከተሳለሙ በሁዋላ ራማ አጎዛ ካነጠፈላቸው ወንበር ላይ ቁጭ አሉ።ጸጥታ ሰፈነ።¨አባም ዝም መጽሃፉም ዝም¨ አለ ራማ በሆዱ ከ አባ ስር ካለችው ድንጋይ ላይ ቁጭ ብሎ ማስተዋል ጀመረ።
ከእንግዶቹ አንድ አዛውንት ተነሱና-
¨እንዴት ነው ነገሩ ያንን ሁሉ ሃገር ተጉዘን የመጣነው ለዝምታ ነው እንዴ?¨ አሉና ንግ ግራቸውን ቀጠሉ።
¨እኔ እስከተረዳሁት ድረስ እዚህ ያለነው ሁላችን አንዳችን ካንዳችን አንተዋወቅም። ሆኖም ግን ሁላችንም አንድ ጥያቄ እየሞገተን ነው። መቸም በ አካል ባንተዋወቅም እዚህ ያለው ህዝብ አባታችን ግማሻችን ኢህአዲጎች፣የቀረነው ሚያዝያ ነው ማን ሰባት ነበር እእእ... ¨ ሲሉ ሽማግለው  ¨ግንቦት ሰባት¨ አለ አንዱ' የ ግንቦት ሰባት' አባል ቆጣ ብሎ የድርጅቱ ስም ቶሎ አለመጠራቱ አናዶታል።¨በነገራችን ላይ ኢህአዴጎች በሉ አባቴ  `ዲ`አይደለም `ዴ` `ዴሞክራሲ` ማለት ነው።¨ አለ አንድ የ ኢህአዲግ አባል ተነስቶ¨
 ¨ድንቄም ዲሞክራሲ¨ አለ አንድ የ 'ኦነግ' አባል በተቀመጠበት። ¨አመድ በዱቄት ይስቃል ሁልሽም ከረፈደ መጥተሽ ደሞ¨ አለ አንድ የ 'ኢህአፓ' አባል ነኝ ያሉ ሸምገል ያሉ ሰው።
የቆሙት ሽማግሌ ቀጠሉ ¨ቆዩ ቆዩ ለስም አጠራሬ ይቅርታ አድርጉልኝ። ታገሱኝ አንድ ጊዜ አይዟችሁ አመት አላወራም¨ ብለው ጋቢያቸውን አስተካከሉ እና ቀጠሉ።
¨....እና በ አካል ባንተዋወቅም በ ቡድን በ ቡድን ግን እንተዋወቃለን።ቀድም ብየ ከ ጠራሁልዎት በተጨማሪ ከ ሃያ በላይ የምንሆን ቡድኖች  አንድ የሚያደርጉን ብዙ ነገሮች አሉ ከ እነዚህም ውስጥ ዲሞክራሲ ይቅርታ ዴሞክራሲ¨ ብለው ወደ ኢህአዲጉ ሰው መልከት አሉና ቀጠሉ
 ¨ አንደኛ ዴሞክራሲን መሽቶ እስኪነጋ የምንሰብክ ነን፥
ሁለተኛ ያለፉት የኢዮዽያ መንግስታት በሙሉ ችግር ነበረባቸው ብለን  እናስባለን ብቻ ሳይሆን ክፉውን ትተን ምን በጎ ነገሮች መያዝ አለብን ብለን አስበን አናውቅም፥
ሶስተኛ ጥርት ያለ ህዝቡ የሚፈልገው ያመነበት ራዕይ የለንም ምናልባት ራዕይ ያለው ገዳም ብቻ ስለሚመስለን ይሁን አይታወቅም¨ ሲሉ ሽማግሌው ተሰብሳቢው ሁሉ ሳቀ አባ እንዳቀረቀሩ በሃዘን ይሰማሉ። ሽማግሌው ሳቁ ሲገታ ቀጠሉና ¨እንደ እዚህ አንዳንዴ በመሳቅም አንድ ነን¨ ሲሉ ሽማግሌው ሌላ ሳቅ ተከተለ።አባ አሁንም እንዳቀረቀሩ ዝም አሉ።
ሽማግሌው ቀጠሉ -

¨አራተኛው ለህዝቡ በ እየቀኑ አዳዲስ ተስፋ በመስጠት አንድ ነን፥
አምስተኛው  ሁሉ ነገር ለእኛ ሚስጥር ነው ኮመዲናው፣በሩ፣ውሃው፣ወንበሩ ሁሉ ነገር ሚስጥር ነው እያልን ከባለቤቱ ከ ህዝቡ ስንደብቅ ሲያውቅብን; ስንደብቅ ሲያውቅብን አለን።
ስድስተኛው  ሁላችንም እራሳችንን የሃገር መሪ አርገን ደምድመናል። ሁሉ መሪ ነው ስልዎት አባቴ በ ቀልድ እንዳያዩብኝ።ርዕስ አንቀጻችን የሚወጣው የቡድናችን መሪ የ ሃገር መሪ እንደሆነ ደምድሞ ነው። በ እርግጥ ይህ አባዜ ዛሬ በ ሃገሩ የፖለቲካ ጉዳይ የሚጽፍ ሁሉ እራሱን መጀመርያ የሃገር መሪ አድርጎ ወይንም ቢያንስ የሚሰራው ሁሉ ወደ መሪነት እንዲያደርሰው በማሰብ እንጂ የ እኔ ድርሻ እስከ እዚህ ድረስ ነው ድርሻዬ ልወጣ የሚል ሰው እንዲያንስ አስተዋጾ አድርገናል ብየ አስባለሁ። የመጨረሻው አንድ የሚያደርገን ሁላችንም የኢትዮዽያን ሚስጥር የት እንደሆነ የማናውቅ መሆናችን ነው።ወደ ልዩነታችን ስንመጣ¨ ሲሉ  ሽማግሌው   የ ሻብያ ወኪል ነኝ ያለ ሰው ተነሳ እና
¨አቦይ ስርዓት ግበር ይህ ጉዳይ 'ሻብያን' እና 'ሻብያውያንን' አይመለከትም።¨ ብሎ ሳይጨርስ ከፊቱ ተቀምጦ የነበረ ሰው ተነሳና ¨እኔ የ 'አዲስቱ' ኤርትራ ዲሞክራሳዊ ድርጅት ነኝ 'ስርዓት ግበር' የምትል  ልክ አደለህም:: ''እያነቡ እስክስታ'' አለ ዘፋኙ የምን መደባብቅ ነው ኤርትራ ወጣቱ ቀድሞ ለጦርነት አሁን ለስደት አይደል እንዴ የተዳረገው?¨ ተናጋሪው ¨ሻብያን አይመለከትም¨ወዳለው ወጣት ዞረ እና እንዳፈጠጠ ቀረ።የተፈጠጠበት ወጣት ድምጹን ዝቅ አድርጎ ¨ወይ ጉድ ዘንድሮ የመጣብን ጣጣ!!'' አለ ግራ በተጋባ ስሜት::
ሽማግሌው ¨የምን ሰው ንግ ግሩን ሳይፈጽም ማቋረጥ ነው።ታገሱ እንጂ ከ እግዚአብሄር ቤት መጥተንም አንታገስም እንዴ? ተዉ ደግ አደለም እንዳንቀሰፍ። እዚህ የመጣነው 'እግዚአብሄር ስለኛ ምን ይላል?'  ብለን ለማወቅ ነው።አባቶችን አንጩህባቸው። ይህ የዝምታ ቦታ ነው።እባካችሁ የታመሙትን፣የሞቱትን እንመልከት እንጂ።ስንት ስንንቀጠቀጥላቸው የነበሩት አሁን የት ነው ያሉት?ተዉ እንጂ ወደ ልቦናችን እንመለስ። አስረሳች ሁኝ የት ላይ ነበር ያቆምኩት ¨ ሲሉ አንዱ ከ ዶቦቢካ ብሄረሰብ ፓርቲ ነኝ ያለ ¨አንድነታችንን ነግረውን ወደ ልዩነታችን ሊነግሩን ነበር¨አለ።
¨አዎ ልዩነታችን ሃገር ያወቀው ነው። አንድነቱን ላውሳ የመጨረሻው አንድነታችን ጥርት ያለ ያለፈውን የ ሃገሪቱን ማንነት፣ታሪክ፣እሷነት ተመልክተን ህዝቡን የሚመራ ከፈረንጅ ያልተቀዳ በራሳችን ልናዳብረው የምንችለው የፖለቲካ ራዕይ ካለመኖር ይመነጫል። እያንዳንዱን ብነቅሰው ምን ዋጋ አለው።ይልቅ የአንድነቱ ምንጫችን የሚያጠነጥንበትን አዙሪት ማውሳቱ ይሻላል ብየ ነው። እና አሁን የመጣነው አባታችን አባ እንጦስ እግዚአብሄር የሚላችሁን ይነግሯችኋል ብለውን ነው።¨ አሉና ሽማግሌው ሲቀመጡ ጭብጨባ ተከተላቸው።

ራማ ጆሮውን ያዘ ተጨብጭቦ አይደለም ድምጽን ከፍ ተደርጎ የማይወራበት ገዳም ውስጥ ጭብጨባ ሲሰማበት በእጅጉ አናደደው። አባ ግን እንዳቀረቀሩ ሁሉን ሰሙና ተነሱ።በመስቀላቸው ዙርያውን ባረኩ እና በ ለሆሳስ መጸለይ ጀመሩ።የተቀመጡት ሁሉም ተነሱ።በጸሎት መሃል ግን አንዱ ካንዱ ቀስ እያለ በነገር በ ለሆሳስ እያወራ መጎነታተል ጀመረ።
¨አንተም ወደ እግዚአብሄር ቤት መጣህ? ገዳሙ ላይ ፋብሪካ ልስራ ስትል አልነበርክም እንዴ?¨ ይላል አንዱ።
¨አንተ ዝም በል! እኔ ወረቀቱን አልፈርምም ብዬ የፈረሙት ሌላ ናቸው።እሳቸውም አሁን የሉምየት እንዳሉም አልታወቀም ¨ ሌላው ይመልሳል።
¨አንተ ፓትርያሪኩን አስመራ ላይ በቁም አስረህ ህክምና እንዳያገኙ ከልክለህ እዚህ ደግሞ ምን ልታረግ መጣህ?¨ አንዱ ጀመረ ነገር።
¨እኔን ደግሞ አንተ ልትወቅስ ነው? አንተ አለህ አይደል እንዴ የተሾሙበት ነው እያልክ ከሸራተን እስከ ክራውን ሲደገስ አብረህ እየበላህ ቤተ ክርስቲያን ስትዘረፍ እንዳላየህ ሆነህ:: ተው እንጂ! ብዙ አታናግረኝ¨ መለሰ ተጠያቂው።
¨እስኪ ዝም በሉ አሁን ጸሎት እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው¨ ሌላው መለሰ።
አባ እንጦስ ጸሎታቸውን ሲጨርሱ ፊታቸውን ወደ እንግዶቻቸው መለሱ። ፊታቸው በ እንባ እንየታጠበ ነው።

ቀጠሉ እና ¨እኔ ስለ ምድራዊ መንግስት እንድነግራችሁ አትፈልጉ። ግን እግዚአብሄር ምን እንዳለን ንገረን ነው ያላችሁኝ? አሁን እግዚአብሄር ለ እናንተ ምንም ነግሯችሁ አያውቅም? ¨ አባ ጠየቁ።
¨ፈጽሞ፣በፍጹም¨ ሁሉም እየተቀባበሉ መለሱ።
¨ልጆቼ `እግዚኣብሄር ባንድም በሌላም ይናገራል ሰው ግን አያስተውልም` ይላል  ኢዮብ።የምሰሩት ስራ አንድ ፍሬ የሌለው ለትውልድ የሚቆይ የማይሆንላችሁ ለምንድን ነው?ለምን ህዝብን የሚያጽናና ቃል ጠፋባችሁ? ሃገሪቱስ ለምን አዙሪት ችግር ውስጥ ትገባለች? ለምን መሰላችሁ በመጀመርያ ኢትዮዽያ ከ እግዚአብሄር ሌላ ዕጣ ክፍል የላትም።ግን የ እግዚአብሄርን ቃል በ መገናኛ ብዙሃን እንኳን ለመጥራት የሰነፈች ሃገር ነች። ራማ ይነግረኛል።ባለፈው የ ጋናውን ፕሬዝዳንት የተኩት ሰው በምክር ቤታቸው ሲምሉ በመጨረሻ ያሉት `'ይህን ሁሉ እንድሰራ እግዚአብሄር ይርዳኝ ነው' ያሉት። ኦባማ ምርጫቸውን አሸንፈው የመጀመርያውን እራት ሲበሉ ቀጥታ ለሃገሪቱ ህዝብ በቴሌቭዥን መስኮት እየተላለፈ የ ጸሎት መርሃግብር ነበር ያደረጉት።ምንም እንኳን በእምነት ብንለያይም መላው አለም ለ አፉ እንኳን ያልዘነጋውን አምላክ እኛ በ አደባባይ ለመጥራት አፈርን።አምላክን በማወቅ ቀድመን በ አደባባይ እንደ ስርዓታችን ለማመስገን ዳገት ሆነብን።ሌላ የምለው የለም። ሁላችሁም ግን በ አምላክ ዘንድ እኩል ናችሁ። ስራች ሁ ነው የሚለያችሁ።እግዚአብሄር ፓርቲ የለውም፣ የወንዝ ልጅ የሚባል የለውም፣ሰውን በ ፖለቲካው አይለይም።በ ስራው እና ለ ት ዛዙን በመስራት እና ባለመስራት መሃል ግን ይለያል።ይቀጣል። አንድ ግን ሁል ጊዜ መዘንጋት የሌለባች ሁ ነገር አለ። ሁላች ሁም ሟች ናችሁ።ከተማርንበት ሁሉ ነገር አስተማሪ ነው።ዛፉ፣ውሃው፣ተራራው ሁሉ አስተማሪ ነው።
ከ አርባ አመት ወዲህ የመጣ ትውልድ ሁሉን ዘነጋው እንጂ አባቶቻች ሁ በ አስተዳደር ጉዳይ ሁሉ በጸሎት አስቡን በለው ቢችሉ በገዳሙ ተገኝተው ጸልየው ባይችሉ መባውን ልከው ከ እግዚአብሄር ጋር ይገናኙ ነበር።እናንተ ግን አለምን የሚያንቀጠቅጥ፣የሚያደኸይ፣የሚያበለጽግ አምላክ በመካከላች ሁ ሆኖ ወርቅ ላይ ተቀምጣች ሁ ሳትጠቀሙበት ቀራችሁ አሁንም ከትናንት ቢዘገይ ከነገ ይቀደማል። በስራችሁ ሁሉ እግዚአብሄርን አስቀድሙ። አሁንም `'እግዚአብሄር በ አንድም በሌላም ይናገራል ሰው ግን አያስተውልም' እናንተን ምክንያት አርጎ ነው እንጂ የኢትዮዽያ ጉዳይ በእግዚአብሄር እጅ ነው።።ይብቃኝ::አባ እንባቸው ይብሱን መውረድ ጀመረ። ከ እዚህ የተረፈውን በጸሎት ከ አምላክ ጋር ልነጋገር::¨

ዝምታ ሰፈነ:: ሁሉ ወደ እራሱ ተመለሰ። የ እግዚአብሄርን ነገር ቅድምያ ሰጥቶ ያሰበም ሆነ የጠየቀ አለመኖሩ የተረዳ ሆነ።ሁሉም ስራው ሁሉ ከፊቱ ላይ መጣበት። የሌላውን ስህተት ለመንቀስ ቅድሚያ ከ እግዚአብሄር ጋር ተነጋግሮ እርሱን አውቆ መሆን እንዳለበት ተገለጠ።ችላ የተባለው የ እግዚአብሄር ቤት ጉዳይም በተለይ ለኢትዮዽያ የፈተናው ሁሉ ምንጭ መሆኑን የተጠራጠረ የለም።
 አባ ተሰናብተው ወደ ባዕታቸው ገቡ።ቅድም አባ ነበሩ ያቀረቀሩት አሁን እንግዶቹ ሁሉ አቀረቀሩ።በራሳቸው እና በ እግዚአብሄር መካከል ያለው ጉዳይ መታየት እንዳለበት አሰቡ።
 እግዚአብሄርም የእነርሱንም ሆነ የ ህዝቡን ወደ እርሱ መመለስ ሲጠብቅ መሸም ነጋም ሌላ ሁለተኛ ቀን ሆነ።
ጌታቸው በቀለ
ኦስሎ

1 comment:

Anonymous said...

እንዲህ የምንመካከርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ግን ለ ፈጣሪ ምን ይሳነዋል?