Thursday, October 30, 2025

''ሙዝ አትብላ! ጦጣዎች ከጫካ ሊመጡ ይችላሉ።'' ዓይነቱ የጀዋር ጊዜው ያለፈበት ትንተና በኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ላይ።

ቀይ ባሕር


  • ዛሬ በዩቱብ አገኘን ብላችሁ በኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ላይ የምትሳለቁ የዘመናችን ባንዳዎች ግዴላችሁም ጊዜ እና ትውልድ ይፈርዳል! እናንተን ብቻ ሳይሆን ልጆቻችሁም ''አባታቸው በዩቱብ ኢትዮጵያ ላይ የተሳለቀ ባንዳ ነበረ።'' የሚል ታሪክ ትታችሁ እንደምትሄዱ አትጠራጠሩ።

ጀዋር በትናንትናው ዕለት በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለቀርቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ አስመልክቶ በተለይ የቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ፣ታሪካዊ፣ስልታዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ የቀይ ባሕር ይገባኛል ጥያቄ በማስመልከት የጻፈው ጽሑፍ ''ውሃ የማይቋጥር '' ብቻ ሳይሆን ምሑራዊ ሽታ የሌለው ነው።

የጀዋር ሃሳብ በአጭሩ ከ130 ሚልዮን በላይ ህዝብ እንዳላት በተባበሩት መንግስታት የተነገረላት ኢትዮጵያ የባሕር በር ይኑረኝ፣ይህ ለሺህ ዓመታት የነበረ እና ባለፉት 30 ዓመታት ገደማ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ሰነድ በሌለበት መንገድ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዴት አጣች የሚለውን ብሔራዊ ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምክርቤት ውስጥ ማንሳታቸው እንደ የጀዋር ፖለቲካ ይህ ጉዳይ ''ሌሎች ወደ ቀይ ባሕር እንዲሳቡ ያደርጋል።''

በመጀመርያ ደረጃ የቀይ ባሕር በዓለማችን ካሉት ቁልፍ ስልታዊ መተላለፊያዎች ውስጥ አንዱ ነው። በዓለም ታሪክ የተነሱ ኃያላንም ሆኑ የአካባቢ ''ግልገል ኃያላን'' ከቀይ ባሕር ላይ ዓይናቸውን የነቀሉበት ጊዜ መቼ ነው? ጀዋር ካልተቸ ላለማደር ምሎ ከሃገር ስለወጣ ዛሬ የጠራውን የጂኦ ፖለቲካ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስለ ቀይባሕር በማንሳታቸው ባዕዳን ተሰበሰቡ ይለናል። ኢትዮጵያ ስለ ቀይባሕር ባታነሳ የግብጽ፣የሳውዲ እና የሌሎች ሀገሮች የጂኦ ፖለቲካ ስልት ሌላ ነበር ማለት ነው?

በእዚሁ የጀዋር ''ውሃ የማይቋጥር'' ወቀሳ ላይ በሱማሊያ የኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ ግብጽን አመጣ፣ ኬንያ እና ጂቡቲም በኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ ከፋቸው። ያስከፋቸው ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የውጭ ፖሊሲ ስህተት አድርጎ ለማቅረብ ሲሞክር ይታያል።

በመጀመርያ ደረጃ የኢትዮጵያ የወደብ እና የባሕር በር ጥያቄ ግልጽ እና ምንም ሽፍንፍን ያልታየበት ነው። ይህ ግልጽ የውጭ ፖሊሲ ጥራት እና ግልጸኝነትን ያሳያል። የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ሱማልያ፣ጂቡቲም ሆነች ኬንያ በኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ አንጻር አንድም ያሰሙት ቅሬታ የለም ብቻ ሳይሆን ሀገራቱ በኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ ዙርያ ከመግባባት አልፈው  ቀድም ብለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያነሱት የአካባቢ ምጣኔ ሃብታዊ ትስስር በተለይ በምስራቅ አፍሪቃ አንጻር ይተነሳውን ሀሳብ እየቆዩ በሚገባ እንዳብላሉት እና እንዳመኑበት ለመረዳት በታላቁ የኢትዮጵያ ግድብ ምረቃ ላይ እራሳቸው ተገኝተው መመረቃቸው ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ የመብራት ትሩፋት በመቋደስ ላይ መሆናቸው አንዱ ማሳያ ነው።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ሳይመለስ ፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሃብታዊም ሆነ ወታደራዊ ሰላም በምስራቅ አፍሪቃ እንደማይሰፍን ጎረቤቶቻችን በሚገባ ይረዳሉ። ለእዚህም ነው የኢትዮጵያ የባሕር በር መመለስ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት ያንቀሳቅሰዋል፣ያሰፋዋል ይህንን ተከትሎ ደግሞ የእነኝህ የጎረቤት ሀገሮች ምጣኔ ሀብት የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆን ሀገራቱ ተረድተዋል። እውነታው ይህ ነው።

የጀዋር ትንተና ለዘለቄታዊ ችግር ኢትዮጵያ የራስ ምታት መድሐኒት እየወሰደች ትቆይ አሁን ስለየባሕር በር ጉዳይ አታንሱ የሚል የጌቶቹን ፕሮፓጋንዳ የማስተጋባት ስራ ነው። ኢትዮጵያን የመውጫ የባሕር በር አያስፈልግሽም ከወጣሽ ሌሎች ይመጣሉ በማለት የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመምከር የሞከረው ጀዋር የበለጠ ሌላ ትዝብት ላይ ወድቋል። ጀዋር በአቶ ኢሣያስ ጉዳይ በግልጽ ሲቃወም ነበር የምናውቀው። ዛሬ ምክር የመሰለች ውስጧ ግን አድርባይነት የተነከረች ምክር ለመምከር መሞከሩ ወዴት ወዴት? የሚያስብል ነው። ጥያቄዎቹ ጀዋር የማንን አጀንዳ  ለማራመድ እየሞከረ ነው? በራሳችን ቋንቋ እየጻፈ ለእኛው የባዕዳንን የመካከለኛው ምስራቅ አንዳንድ ሀገሮችን አጀንዳ ሊነግረን የሚሞክረው በምን ያህል የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመናቅ ቢሞክር ነው? የሚሉት ናቸው። 

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ግልጽ እና የጠራ ነው።አንድ ጂኦፖለቲካ ተንታኝ ነኝ የሚል እንደ ጀዋር የመሰለ ሰው ይህንን ያህል ህዝብን ለማታላለል ሲቃጣ ግን ያሳፍራል። ''ሙዝ አትብላ፣ጦጣዎች ከጫካ ሊመጡ ይችላሉ።'' ዓይነቱ  የጀዋር ጊዜው ያለፈበት ትንተና ዋጋ የሚሰጠው አይደለም። ኢትዮጵያ ባለችበት በመቀመጧ ብቻ ለመክበብ ሲሞክሯት እና ጊዜ ያገኙ ሲመስላቸው ደግሞ ለመውረር ሙከራ ተደርጎባታል። ይህ አዲስ ክስተት አይደለም። የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር መውጣት ከታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ መብቷ ባለፈ የደህንነቷ ዋስትናም ጭምር ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያ ስለራቀች የሚርቁላት፣ስለቀረበች የሚቀርቧት አይደሉም። ሁሉም ጀዋርም ሆነ ዛሬ በዩቱብ አገኘን ብላችሁ በኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ላይ የምትሳለቁ የዘመናችን ባንዳዎች ግዴላችሁም ጊዜ እና ትውልድ ይፈርዳል! እናንተን ብቻ ሳይሆን ልጆቻችሁም ''አባታቸው በዩቱብ ኢትዮጵያ ላይ የተሳለቀ ባንዳ ነበረ።'' የሚል ታሪክ ትታችሁ እንደምትሄዱ አትጠራጠሩ። በፋሽሽት ጣልያን ጊዜ ባንዳ የነበሩና የእነርሱ ልጆች ዛሬ ድረስ ማጠብ ያልቻሉት አሳፋሪ ታሪክ እንዳለ መቼም ለዩቱብ ባንዳ ማስታወስ ለቀባሪው ማርዳት ነው።
=================////=========

''ሙዝ አትብላ! ጦጣዎች ከጫካ ሊመጡ ይችላሉ።'' ዓይነቱ የጀዋር ጊዜው ያለፈበት ትንተና በኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ላይ።

ቀይ ባሕር ዛሬ በዩቱብ አገኘን ብላችሁ በኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ላይ የምትሳለቁ የዘመናችን ባንዳዎች ግዴላችሁም ጊዜ እና ትውልድ ይፈርዳል! እናንተን ብቻ ሳይሆን ልጆቻችሁም ''አባታቸው በዩቱብ ኢትዮጵያ ...