Sunday, May 20, 2012

ጋዜጠኛ አበበ ገላው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እና ሂላሪ ክሊንተን

ሰኔ 11፣2011 ዓም የ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን አዲስ አበባ በሚገኘው የ አፍሪካ ህብረት ተገኝተው  40 ደቂቃ የፈጀ ንግግር አድርገው ነበር።በንግግራቸው ላይ የ አዲሱ ትውልድን ፍላጎት መስማት አስፈላጊ መሆኑን  እና ሁሉም የ አፍሪካ መሪዎች ቸል እንዳይሉት የመከሩበት ነበር።
ንግግራቸውን በጀመሩ በ ስድስተኛው ደቂቃ ላይ ታድያ የ አዳራሹ መብራት ጠፋ። ቀሪውን ንግግር በድንግዝግዝ መብራት ማንበብ ነበረባቸው። ይህን የሚያህል ትልቅ አዳራሽ ጀነረተር እንደሚኖረው ማንም አይጠራጠርም። የነበረው መብራት ግን (በፊልሙ እንደሚታየው) በግማሽ የተለቀቀ ይመስል ነበር።

 ሂላሪ ክሊንተን  ስለ አፍሪካ ዲሞክራሲ መናገር ሲጀምሩ መብራት በመጥፋቱ የ ኢትዮዽያ መንግስት የ መብራት ሃይል መስርያ ቤት ያልተጻፈ ህግ እንደሚያዘው ''ማስጠንቀቅያ ሳይሰጥ መብራት ማጥፋት ህገ-መብራት ሃይላችን ያዛል''ሊል እንደሚችል የመገመቱን ያህል ባለፈው የ ጂ 8 ጉባዔ ላይ ለ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የ ጋዜጠኛ አበበ ገላው'' ነጻነት!ነጻነት! የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ! አቶ መለስ አምባገነን ናቸው!'' ለሚሉት ድምጾች የ አሜሪካ መንግስት ምላሽ ''የ አሜሪካ ህገ መንግስት ሃሳቡን እንዲገልጽ ይፈቅድለታል ''እንዳለ ለአበበ ፖሊሶቹ ባሳዩት ትህትና አሁንም ይገመታል ።
በሚቀጥለው ቀን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ  በጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ውስጥ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሲነጋገሩ  ከውጭ እንግዳ መቀበያ ክፍል ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ስለነበር ጋዜጠኞች በጉጉት ሲጠባበቁ ነበር። ሆኖም ከንግግራቸው በኋላ በ ሹሉክታ በር ሄዱ።ለምክንያቱ እስካሁን ድረስ  በቂ መልስ የተሰጠ አይመስለኝም። እናም ሂላሪ  አዲስ አበባን ደስ ብሏቸው እንዳለቀቁ ሁሉ አቶ መለስም ዋሽግተንን እንዲሁ።
ጉዳዩ በዲፕሎማሲ ቋንቋ አንድ ለ አንድ ነው እንዴ?
 የ አበበን ሃሳብ በሚጋሩት ዘንድ የማስደሰቱን ያህል የ መለስ አድናቂዎችን በ እጅጉ አናዷል። ቁም ነገሩ ግን ያ አደለም። ወደድንም ጠላንም ግን ለ ኦባማ ጉዳዩ ያን ያህል አያናድዳቸውም። ምክንያቱም ሃሳብን መግለጽ አደለም የተናደደ ጋዜጠኛ  ጫማ የተወረወረበት መሪ ያላት ሃገር ነች- አሜሪካ። የሃገሪቱ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች በ ቀድሞው የ አሜሪካ ፕሬዝዳንት ቡሽ  ላይ ስለተወረወረው ጫማ ከ ኮሜዲ ፊልም ጀምሮ ትልቅ ውይይት አድርገውበታል።

 ወደ እኛ ሃገር ሲመጣ ግን' ተደፈርን' የሚል ስሜት ይዞ ዛቻ እና ማስፈራራት ይጎርፋል። እዚህ ላይ ነው ፈተና ያለው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ካሰቡት ወይንም ጉዳዩን ካዩበት እይታ በተለየ እና በላይ 'እኛ ነን የተነካን' ብሎ መናደድ ግን ተገቢ አደለም።  ሁኔታውን በ በቀል እና በ ዛቻ ከመግለጽ በእርጋታ ''ማንም መቶ ከ መቶ ትክክል  የሚባል የለም ስሕተት ምን ላይ ተሰርቷል? ጥፋስ የቱ ላይ ነው ያለው?'' እያሉ መወያየት እና ለወደፊቱ እንደ ሃገር የሚጠቅመን የቱ ነው? ብሎ ማሰብ ነው ጠቃሚው ነጥብ  ።' አንድ ጎል ገባብኝ እኔ ደግሞ ሌላ ጎል  ላግባ' እየተባለ የሚታሰብ ስሌት ህዝብን የሚያጠፋ መሆኑን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ማለቅያ የሌለው ያልሰለጠነ ፖለቲካ መገለጫ ሆኖ እንዳይቀር ማሰብ ያስፈልጋል።  ሃሳቦችን በሃሳብነታቸው ላይ መወያየት ግለሰቦቹ (አቶ መለስም ሆኑ አቶ አበበ)  የ ሃሳቡ ተሳታፊዎች ምናልባትም አመንጪዎች መሆናቸው እንደ ገለሰብ በእነርሱ ላይ ብቻ እንዲተኮር ሳይሆን ከእነርሱ ጋር ባሉት ሃሳቦች ላይ መከራከር፣ መነጋገር የ ስልጡን ህዝብ መለያ ነው።


አሁን የተያዘው ግን በሃሳቦች ላይ ከመከራከር ይልቅ በግለሰቦች ላይ ማተኮር ያስመስላል።እናም ግለሰቦችን ትተን ሃሳቦች ላይ መወያየት ብልህነት ነው። አበበም መለስን ሳይሆን ሃሳባቸውን  የመቃወም መብት እንዲኖረው መለስ እና አድናቂዎቻቸውም አበበን ሳይሆን ሃሳቡን ላይ ብቻ ቢያተኩሩ መልካም ነው።ከእዚህ ውጭ ግን 'እኔ ነኝ የተነካሁት' የሚል አስተሳሰብ ከ አፍንጫ እስከ ከንፈር የሚደርስ የጠባብ የሚለው ቃል ቢያንሰው የ ''ጥብቆ'' አስተሳሰብ ነው።እና 'እንሰራለታለን'  በሚል ሃሳብ ከመታጠር በነጥቦቹ ላይ አተኩሮ መወያየት አሁንም ያልለመድነው ግን ልንለምደው የሚገባን ቁም ነገር ነው ።
አበበም 'እንደግለሰብ ከ መለስ ጋር ጸብ የለኝም ሃሳባቸውን ግን እቃወማለሁ' የሚሉት ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞች ቢሰራ። እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን በግለሰቦቹ ላይ ብቻ መተኮሩ ትልልቅ ሃሳቦች ተረስተው ጉዳዩ አበበ መለስን እንዲህ አላቸው የሚለው ምን ያህል ጉዳዩን የ ግለሰቦች ጉዳይ አርገው ሊይሽከረክሩት ለሚፈልጉ ሰዎች ከ ግለሰብ ወደ ቡድን ከዚያም በላይ ለማሳደግ ሲያንደረድሩት ይታያችሁ። እናም ሃሳቦቹ ይጉሉ ይነገሩ።
ግለሰቦቹን ስናስታውስ ከመገለጫ ሃሳቦቻቸው ጋር እንጂ ለብቻቸው አናንሳቸው። አበበ ሃሳቡን እዚህ ስብሰባ ላይ ባይገልጽ ኖሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩን  የት አግኝቶ ሃሳቡን ሊገልጽ ይችል ነበር? እሳቸውስ ምን ያህል ግልጽ የውይይት ሃሳቦችን ከፉም ለሙም የሚሰሙበት መድረክ አዘጋጅተው (ቢያንስ ኤምባሲዎቹ አመቻችተው) ያውቃሉ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለውይይት መነሻነት የማይሆኑበት ምን ምክንያት አለ?  አሜሪካኖች ፕሬዝዳንት ቡሽ ላይ ጫማ ስለወረወረው እና ስለተወረወረበት ሰው ሳይሆን ስለ ጉዳዩ እንዲፈጠር ምክንያት ስለሆነው ስለ ኢራቅ ጦርነት ተወያዩ ቀጥለው ፕሬዝዳንት ኦባማን መርጠው ሰራዊታቸውን ከ ኢራቅ አወጡ።ይህ ሸጋ ሃሳብ ነው።

አበቃሁ
ጌታቸው
 ኦስሎ

Post a Comment

GUDAYACHN BLOG started on August 28/2011 ኢሜይል አድራሻዎን በመሙላት ጽሁፎቹን መከታተል ይችላሉ/Follow by Email

በብዛት የተነበቡ/Popular Posts

ጉዳያችን በፌስ ቡክ ገፅ / GUDAYACHN ON FACE BOOK

https://www.facebook.com/gudayachn/?pnref=story