Thursday, May 29, 2014

ሐገራችንን እንወቅ ''ቅዱስ ያሬድ የጉባኤያት አባት'' (ቪድዮ)

የቅዳስ ያሬድ  አባቱ አብድዩ /ይስሐቅ/ እናቱ ክርስቲና /ታውክልያ/ ይባላሉ፡፡የትውልድ ሥፍራው አከሱም ነው፡፡ የተወለደው በ505 ዓ.ም/  ሚያዝያ 5 ቀን  ሲሆን በተወለደ በ7 ዓመቱ ወላጅ አባቱ ስለሞተ እናቱ የአክሱም ጽዮን መምህር ለነበረው ለአጎቱ ለጌዴዎን እያስተማረ እንዲያሳድገው ሰጠችው፡፡

ቅዱስ ያሬድ የኢትዮጵያውያን ሀብት ብቻ ሳይሆን መላው ዓለምን ከእግዚአብሔር በተሰጠው ፀጋ ያጣፈጠ ትልቅ ሊቅ ነው።ዓመታዊው በዓል በያዝነው ወር ግንቦት 11 ይውላል።የማኅበረ ቅዱሳን ሳምንታዊ ቴሌቭዥን የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ስለ ቅዱስ ያሬድ የተናገሩትን እንዲህ አቅርቦታል።



ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG

Wednesday, May 28, 2014

ኢህአዲግ ከ70 ዓመት በፊት በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመን በተገነባ ስታዲዮም ውስጥ ሆኖ ግንቦት 20 እያከበረ ኢትዮጵያ አድጋለች ይላል።ለዘንድሮው በዓል ክብረ በዓል በመላ ሀገሪቱ ከግማሽ ቢልዮን (500 ሚልዮን) ብር በላይ ወጪ እንደሆነ እየተነገረ ነው።



በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ለማወቅ ብዙ ምርምር የሚጠይቅ አይደለም።ህዝቡ የመሰረታዊ ፍጆታዎችን የመግዛት አቅሙ ተዳክሟል።ቀድሞ እናት ልጇን እንጀራ በሽሮ ብቻ ማብላቷ ያሳስባት ነበር።ዛሬ ይህ ዘመን በተለይ በከተሞች አካባቢ በቁጥርም ከፍተኛ በሆነው ሕዝብ ዘንድ ችግሩ ከፍቶ ዳቦ ገዝቶ ማብላት ከባድ ሸክም ሆኗል።አብዛኛው ሕዝብ ስለ ዳቦ ብቻ አይደለም ጭንቀቱ።የሚጠጣ ውሃም ነው። በአዲስ አበባ ብቻ ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጋ ሕዝብ የሚናፍቀው እና ለማግኘት የሚታትርበት አንዱ ተግባሩ ሆኗል የውሃ ነገር።ውሃ ፍለጋ ጀርካል ይዘው የሚንከራተቱ ሕፃናት እና እናቶችን ማየት የተለመደ ነው።በአዲስ አበባ ብቻ አደለም ሐረር፣ድሬዳዋ፣ሐዋሳ እና በርካታ ከተሞች የውሃ እጥረት ላይ ናቸው።

ይህ  ከሰው ልጅ መሰረታዊ ፍጆታ አንፃር ብቻ የምናየው ኢህአዲግ/ወያኔ 23 ዓመት ሙሉ ሊያስተካክለው ያልቻለውን ጉዳይ ጠቀስኩ እንጂ ባለፉት 23 ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያ በፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብት  ዘርፍ ሁሉ ወደ አደገኛ መንገድ እያመራች ነው።እርግጥ ነው ከስርዓቱ በመጠቀማቸው የሀገራቸውን ችግር እና የሌላውን እሪታ ላለመስማት የወሰኑ ወገኖች የሚሉት በተቃራኒው ነው።እውነታው ግን  ከእነርሱ አስተሳሰብ ብዙ የራቀ ነው።

ፖለቲካው 

- ፖለቲካው በጥቂት በጎሳ የሚያምኑ ኢትዮጵያዊነትን በሚያጥላሉ እና የጎሳ ግጭትን ለመለኮስ እስከ 20 ሚልዮን ብር አውጥተው የእጅ እና የጡት ሃውልት በሚሰሩ ጉድ አመራር ስር ነው፣
- ፖለቲካው ለኢህአዲግ/ወያኔ ማጎብደድ እና መልመጥመጥን ብቻ እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠ እና በዙርያው ተስፋ ቢስ ግን ለገንዘብ እና ለጥቅም ባደገደጉ አድር ባዮች ተከቧል፣
- ፖለቲካው ዲሞክራሲ ላይ እየተሳለቁ እና እያፌዙ በሚናገሩ የተቀመጡበትን የህዝብ ትከሻ በዘነጉ ባለግዜዎች ተተራምሷል፣
- ፖለቲካው በአንድ ወቅት በጠበንጃ ስልጣን በያዙ ኃይሎች ስር ወድቆ ለዘላለም ገዢዎች እኛ ነን ብለው እራሳቸውን በሾሙ ሹመኞች ተይዟል።

ምጣኔ ሃብቱ - 

- ምጣኔ ሃብቱ  አቅጣጫውን የማያውቅ በፖለቲካው እና በጎሳቸው ስም በተሰበሰቡ ግለሰቦች ፍላጎት እንጂ በሀገር ራዕይ እና እድገት መሰረት አይመራም፣
- ምጣኔ ሃብቱ ከ70 በመቶ በላይ በስርዓቱ ስር በተደራጁ ኩባንያዎች የሚሽከረከር እና ሀብት ለማጋበስ ባሰፈሰፉ የውጭ ጥቅመኞቹ እየታገዘ በአስፈሪ እና አደገኛ ኃይሎች እየተሽከረከረ ነው።
- ምጣኔ ሃብቱ ሙስና የገንዘብ ብቸኛ ምንጫቸው የሁኑ ግለሰቦች ኢንቨስተር ተብለው የሚጠሩበት ነው፣
- ምጣኔ ሃብቱ ብሔራዊ ባንክ የተጭበረበረ ወርቅ ከመግዛት አንስቶ እስከ ግምሩክ ኃላፊ ድረስ በሀብት የሚ ምነሸነሹበት ተቋማት ሆኗል።

ኢትዮጵያ ከምንገምተው በላይ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነች

ኢህአዲግ ኢትዮጵያን የዛሬ 23 ዓመት ከነበረችበት ከፍ አደረኩ እያለ ቢናገርም ዕውነታው ኢትዮጵያ ከምንገምተው በላይ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነች።ከምጣኔ ሃብቱ እና ከፖለቲካው የተገለለው ሕዝብ ምሬቱ ገፍቶ የሚወስደው ጫፍ ለማወቅ ይከብዳል።የእዚህ ዓይነቱ ምሬት የኃይል እርምጃም ስለማይቀርለት ከትናንቱ ይልቅ መጪው አስፈሪ እንዲሆን አድርጎታል።

የዘንድሮው ግንቦት 20 እንደባለፈው ሁሉ ካለፈው ይልቅ መጪውን አስፈሪ አድርጎታል።ሃያ ሶስት ዓመት ደቡብ ኮርያ እና ብራዚል የድሃ ህዝባቸውን ቁጥር ቀንሰው ሀብት በፍትሃዊነት እንዲከፋፈል ያደረጉበት እረጅም የተባለ ብዙ ታምር የሚሰራባቸው ዓመታት ናቸው።በኢትዮጵያ ደግሞ  23 ዓመታት ሀብት የተወሰኑ ቡድኖች ውስጥ የተሰበሰበበት፣ ከአስር ሺዎች ወደ መቶ ሺህ ሕፃናት የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑባቸው ዓመታት ናቸው።ህንፃ እና መንገድ መስራት ሕዝብ ማስተዳደር አደለም።የአረና አባል አቶ አሰግደ እንዳሉት ''መንገድ መስራት አስደናቂ ነገር አደለም።ጣልያን በአምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ቆይታው ከስድስት ሺ ኪ ሜትር በላይ መንገድ ሰርቷል።ይህንን ማድረጉ ፋሽሽታዊ ስራው ይቀጥል አያስብልም።

 የሆነው ሆኖ ኢህአዲግ ከ70 ዓመት በፊት በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመን በተገነባ ስታዲዮም ውስጥ ሆኖ ግንቦት ሃያን እያከበረ ኢትዮጵያ አድጋለች ይላል።ከየቀበሌው እና ትምህርት ቤቶች በልፈፋ አዲስ አበባ ስታድዮም ውስጥ ለተሰበሰበው ሕዝብ አቶ ኃይለማርያም ሲናገሩ ''በምግብ እራሳችንን ችለናል'' ሲሉ ተደምጠዋል።''የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም'' እና ይችን ንግግር በመጪው የእህል መሰብሰብያ ወቅት ላይ እንደማይደግሙት እራሳቸውም ያውቁታል።እንዳፋቸው ቢሆንልን ጥሩ ነበር።እውነታውን እርሳቸው የቤተ መንግስት እንጀራ ከሚበሉት ይልቅ የሚያውቀው ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።

ለዘንድሮው በዓል ክብረ በዓል በመላ ሀገሪቱ ከግማሽ ቢልዮን (500 ሚልዮን) ብር በላይ ወጪ እንደሆነ እየተነገረ ነው።የግማሽ ቢልዮን ብር ብክነትን አስቡ እና በውሃ ጥም የሚንከራተቱ የከተማ እና የገጠር ነዋሪዎችን አስቡ።ስንቱ በእዚህ ገንዘብ ንፁህ ውሃ ባገኘበት ነበር። ስንት ገበሬ ከባህላዊ የበሬ አስተራረስ ወደተሻሻለ የትራክተር ማረሻ በተሻገረበት ነበር።ከሃያ ሶስት ዓመታት በኃላም በበሬ እያረስን ነው።ከ 23 ዓመታት በኃላም  ኢህአዲግ/ወያኔ ከ70 ዓመት በፊት በተሰራ ስታድዮም ውስጥ ሆኖ አደጋችሁ እያለ መፎከሩ  የጤና ይሆን?

ጉዳያችን
ግንቦት 20/2006 ዓም/ ሜይ 28/2014

  

Monday, May 26, 2014

ኦስሎ ትጣራለች (ማስታወቂያ)



  • በሰሜን አሜሪካ፣ጀርመን፣እንግሊዝ፣ፈረንሳይ እና ሌሎች ሀገሮች በሚገኙ ከተሞች ውስጥ ታይቷል፣
  • ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ጎብኝቶታል፣
  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋኅዶ ቤ/ክርስቲያን የቅዱሳን ገዳማት ያሳለፉት ታሪክ፣ምንነት፣አሁን ያሉበት ሁኔታ እና በመጪው ዘመን እንዴት መያዝ እና ማልማት እንደሚገባ አቅጣጫ ያሳያል፣
  • የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በኢትዮጵያ የነበረበትን ሂደት እና ስራው የተጀመረ ግን ደግሞ አዲስ እና ልዩ በስብከተ ወንጌል ላይ የተቀረፀ ፕሮጀክት ያስተዋውቃል፣
  • በዓይነቱ ልዩ አውደ ጥናት ይቀርብበታል፣
  • የምዕመናንን እና የሰው ልጅ ቅርስ አክባሪዎች ሁሉ ድርሻቸው ምን እንደሆነ ያሳያል፣
  • እነኝህን እና ሌሎች ተጨማሪ መረጃዎችን የሚያገኙት በአንድ ስፍራ ነው።ማኅበረ ቅዱሳን በኦስሎ ባዘጋጀው ዓውደ ርዕይ እና አውደ ጥናት ውስጥ።


ቀን - ከሰኔ 6 እስከ 8/2006 ዓም (ጁን 13-15/2014)

ቦታ - ማየሽትዋ ሺርክ፣ሺርከን ቫየን 84፣ኦስሎ   

         (Majorstuen   Kirke,Kirkefeien 84,Oslo)


ማሳሰብያ - በመርሐ ግብሩ ላይ ለመገኘት ሃይማኖት፣ሀገር፣እና ሌላ ምንም አይነት ገደቦች አይጣሉበትም።ማንም ፈቃደኛ የሆነ ሁሉ መገኘት ይችላል።ለምሳሌ ኖርዌጅያንም ከታዳሚዎቹ ውስጥ ናቸው።

Friday, May 23, 2014

በሕግ አምላክ! የኢትዮጵያን ታሪክ የቆነፀላችሁበት እና ያደበዘዛቹበት አቀራረብ ይስተካከል።የመንግስት የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ድረ-ገፅን ይመለከታል።




'ስለ ኢትዮጵያ' በሚለው ስር ''ታሪክ''  አምድ ላይ 'የመንግስት የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች' ድረ-ገፅን ኢትዮጵያን ያቀለለ ወረድ ሲል ደግሞ ያጣመመ የታሪክ አቀራረብ ይታይበታል።
ለመጨረሻ ጊዜ ድረ ገፁ የታረመው በ 2011 ዓም እ አ አቆጣጠር ነው ይላል ከድረ-ገፁ ላይ የሚነበበው የቀን ፅሁፍ።ያኔ አቶ በረከት አርመው አሳልፈውት ከሆነ ዛሬ በታሪክ ባለሙያዎች እንደገና መታየት አለበት።ድረ-ገፁ ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቅበት አገላለፅ 'ውስጠ ወይራ' ነች።

ይህ ገፅ ማለት ለውጭ ሃገራት ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርጉት ማናቸውም ግንኙነት በተለይ በሚድያ ዘርፍ ላሉት እንደ ዋና በር የሚታይ ነው።ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ጋዜጠኞች መሙላት የሚገባቸው ፎርም ሁሉ የሚገኘው በእዚሁ ገፅ ላይ ነው።ስለ ሀገራችን በውጭ ሃገራት የትምህርት ተቋማት ሁሉ ''ኦፊሻል''  የመንግስት ድረ-ገፅ ስለሆነ የተፃፈው ሁሉ ለማጣቀሻነት ሊቀርብ ይችላል ማለት ነው።ለእዚህ ነው ድረ-ገፁ የሚለው ነገር ሁሉ አነሰም በዛ አዲስ ለሚወለዱትም ሆነ ለውጭ ሀገር ዜጎች የሚሰጠው ፋይዳ የበዛብኝ እና ኢትዮጵያዊ አቀራረቡ የኮሰሰብኝ።

እነኝህን አንብቡ እና ቁንፅልነቱን እና የትኩረት አቅጣጫውን ታዘቡ።የመጀመርያዎቹ መንግሥታት በሚለው ስር እንዲህ ይላል።

''የመጀመሪያዎቹ መንግስታት''
''በ፰፻ ዓመተ ዓለም አካባቢ ደአማት የሚባል መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያና ኤርትራ ተቋቋመ በሰሜን ኢትዮጵያ የምትገኘው የሀ የደአማት ዋና ከተማ ነበረች። በየመን የሚኖሩት ሳባውያን በደአማት ላይ ተፅዕኖ እንደነበራቸው የሚታመን ሲሆን ይህ ተፅዕኖ ምን ያህል እንደሆነ ግን በእርግጥ አይታወቅም። ወደ ፬፻ ዓመተ ዓለም አካባቢ የደአማት መንግስት ከስልጣን ሲወድቅ በትናንሽ መንግስቶች ተተካ። ከነዚህ ትናንሽ መንግስቶች አንዱ አክሱም ሲሆን አካባቢውን እንደገና በአንድነት ለመግዛት ችሎ ነበር።''
በኢትዮጵያ እና ''በኤርትራ ተቋቋመ'' ሲል በወቅቱ ኤርትራ የምትባል ሀገር መች ነበረች? ብላችሁ ብትጠይቁ ልክ ብላችኃል። ታሪክ በወቅቱ በነበሩት የቦታ ሁኔታዎች ወይንም ደግሞ  ''አሁን ኤርትራ ተብላ በምትጠራው'' ብሎ መፃፍ አንድ ነገር ነው። ''በኢትዮጵያ እና በኤርትራ'' የሚለው አፃፃፍ ግን ፈፅሞ ስህተት ነው።

በሌላ በኩል ንግስት ሳባም ሆነች ሳባውያን እንዲሁም የሳባ ፅሁፍ መነሻው ኢትዮጵያ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳናል።''የሳባ ታሪክ ከየመን ይነሳል'' የሚሉ የታሪክ መሰረት የሌላቸው ፅሁፎች የሚነዙት ከየመን ነው።መቀመጫዋም ኢትዮጵያ መሆኑ ተፅኖ የነበረው ከኢትዮጵያ ሳባ ነው እንጂ ከየመን አይደለም።

በስድስተኛው ክ/ዘመን የቅዱስ ያሬድ ታሪክን ቀጥሎም የመሐመድ ቤተሰቦች ወደ ኢትዮጵያ መምጣትን እና በ12ኛው ክ/ዘመን የነበረው የቅዱስ ላሊበላ ታሪክን በሙሉ ይዘል እና  15ኛው ክ/ዘመን ላይ እንዲህ ይላል -''

በ፲፭ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ ኢትዮጵያ ከአክሱም ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአውሮፓ ጋር ግንኙነት ጀመረች'' ይላል።
ኢትዮጵያ ከአክሱም መንግስት መውደቅ በኃላ ከውጭ ሃገራት ጋር የነበራት ሌሎች ግንኙነቶች አልነበሩም?

ይቀጥላል -----

አፄ ቴዎድሮስ መውደቅ ምክንያቱን ሲናገር ''የሰሜን አሮሞዎችና ትግሬዎች አመፅና የግብፆች ተደጋጋሚ ድንበር መጣስ የአፄ ቴዎድሮስ ስልጣን እንዲዳከም አደረጉት።''
እዚህ ላይ ፀሐፊው ወይንም አራሚው  በአራዳ ልጆች አባባል ''እራሱን አስፎገረ'' ተመልከቱ ''በዘር የተቃኘች ማሲንቆ'' ስትመታ።ለአፄ ቴዎድሮስ መውደቅ ምክንያቱ የዘር ጉዳይ ነው? እርግጥ ነው እንግሊዞችን እየመሩ መቅደላ ድረስ በማምጣት በኃላ አፄ ዮሐንስ ተብለው የነገሱት (በቀድሞ ስማቸው ደጃች በዝብዝ ካሳ) ይሁኑ እንጂ አፄ ቴዎድሮስን ከዳር ሃገሩ ሕዝብ አጠገባቸው ያለው የመሃል ሀገር ሕዝብ ብዙ ችግር ፈጥሮአል።ለመሆኑ ''የሰሜን ኦሮሞ'' የሚባል በኢትዮጵያ ታሪክ አለ?

ዝቅ ስትሉ ኢትዮጵያ በእንግሊዝ እና በአርበኞች ጣልያንን እንዳሸነፈች ይናገር እና ግን ጣልያን ስታሳዝነው ፈፅሞ እዚህ ቦታ የመግባቱ ፋይዳ እስከማይገባችሁ ድረስ ጣልያኖች እንዴት ሽምቅ ይዋጉ ነበር ለማለት እንዲህ ያላል - ''ግን እስከ 1943 እ.ኤ.አ. ድረስ አንዳንድ ጣልያኖች በደፈጣ ያለ ስኬት ይዋጉ ነበር።'' ጉዳዩ ውግያ ነው ከድል በኃላ አንዳንድ ተባራሪ ጣልያን እንደሚኖር ይታወቃል። ታሪክ ላይ ግን መክተብ እና ሽምቅ ይዋጉ እንደነበር ለመፃፍ መዋተቱ የኢትዮጵያን ድል ማድረግ ላያደበዝዘው የመጨነቁ  ፋይዳው ምንድነው?

ይቀጥላል----

የሱማሌ ጦርነትን ''የኡጋዴን ጦርነት'' ይላል ድረ-ገፁ።በእዚህ ጦርነት ከ 300 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ሚሊሻ ከአባት ጡረተኛ ጋር ዘምተው የሀገራቸውን ድንበር ማስከበራቸውን አንዳች ነገር ሳይተነፍስ ሙሉ በሙሉ በውጭ ኃይል ኢትዮጵያ እንዳሸነፈች ሊነግረን ይሞክራል።ሌላውን ዋሹን ግን ይህንን ታሪክ የሚነግሩን አባቶች ዛሬም በሕይወት አሉ እና አትዋሹን፣ታሪኩን አታደብዝዙ።
አዎን የውጭ እርዳታ ነበር የኩባ ወታደሮችም ተራድተውናል ግን ''የኢትዮጵያ መንግስት'' የተባለ የቃል አቀባዩ ቢሮ የፃፈው የኢትዮጵያ ታሪክ ሙሉ በሙሉ የሀገሩ ሰማዕታትን ክዶ በውጭ ኃይል ነው ያሸነፍነው ብሎ መፃፍ ምን አይነት ሞራላዊ ሥራ ነው?
 ስለ ሱማሌ ወረራ ድረ-ገፁ የፃፈው ይህንን እና ይህንን ብቻ ነው።
''በ1977 እ.ኤ.አ. ሶማሊያ ኦጋዴንን በመውረሯ የኦጋዴን ጦርነት ተነሳ። በሶቪየት ሕብረት፣ ኩባ፣ ደቡብ የመን፣ ምስራቅ ጀርመንና ሰሜን ኮሪያ የመሳሪያ እርዳታ እንዲሁም ወደ 15 ሺህ በሚቆጠሩ የኩባ ወታደሮች ድጋፍ አማካኝነት ደርግ ኦጋዴንን እንደገና መቆጣጠር ቻለ።''
በመሰረቱ ጦርነቱ የደርግ ጦርነት አይደለም።የኢትዮጵያ ጦርነት ነው።15 ሺህ የኩባ ወታደርን ለመጥቀስ የተጋ ብእር ምነው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሚሊሻዎችን እረሳብን?

ድረ - ገፁ የኢትዮጵያን ታሪክ ''የቅርብ ጊዜ'' በሚል ስር ማጉላት የፈለገው ዋናውን አላማውን የሚያመላክት ነው። ልብ በሉ የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ ይልና የሚናገረው ስለ ኤርትራ ነው። እንዳለ ላስነብባችሁ።

''በቅርብ ጊዜ''

''በ1993 እ.ኤ.አ. በተካሄደውና የተባበሩት መንግሥታት በታዘበው ሕዝበ ድምፅ፣ ከ99 ከመቶ በላይ የሚሆነው የኤርትራ ሕዝብና በውጭ ሀገር የነበሩ ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ መገንጠልን መርጠዋል። በሜይ 24፣ 1993 እ.ኤ.አ. ኤርትራ ከኢትዮጵያ ነፃነቷን አወጀች።
በሜይ 1998 እ.ኤ.አ. የድንበር ውዝግብ እስከ ጁን 2000 እ.ኤ.አ. ወደቀጠለው የኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት አምርቶአል። ይህ ጦርነት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን ጎድቶአል''

 እዚህ ላይ የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ  የኤርትራ ከኢትዮጵያ መነጠል ከተፈፀመ ከ20 ዓመት በኃላ በ 2011 ዓም እ አ አቆጣጠር ለመጨረሻ ጊዜ የታረመው እና የኢትዮጵያን ታሪክ የፃፈው የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ድረ-ገፅ የሚነግረን ሌላ ነው።99% ከኢትዮጵያ መነጠላቸውን ለመተረክ ከመሮጥ ለምን የታሪኩን መነሻ አትነግሩንም?
በመንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ ገብተው የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያጣምሙትን ማጋለጥ ይገባል።ታሪካችን በኢትዮጵያውያን ይፃፍ!

ጉዳያችን 
ግንቦት 15/2006 ዓም/ሜይ 23/2014 

ኤርትራ 23 የመከራ እና የፍዳ ዓመታት - አቶ ኢሳያስ በኤርትራውያን ''በነጠላ ጫማ የገባ ሌላ ደርግ'' የሚል ስም ተሰጥቷቸዋል።በሺህ ለሚቆጠሩ በግፍ ለታሰሩ ማሳያ የሆነችው ከአስር ዓመት በላይ ካለፍርድ በኤርትራ እስር ቤት የምትማቅቀው አስቴር ዮሐንስ ማን ነች? (ቪድዮ)

ኤርትራ የዛሬ 23 ዓመት ከኢትዮጵያ መነጠሏ ቢነገርም አዲስ የመከራ እና የስቃይ ዘመን እንጂ ለሕዝቡ አንዳች ለውጥ አለማግኘቱ የአደባባይ ምስጢር ነው። ቀድሞውንም ቢሆን የመገንጠል እና የብሔር ጥያቄን የችግሮች ሁሉ መፍትሄ አድርጎ የሚወስደው የአቶ ኢሳይስ እና አቶ መለስ የተሳሳተ የፖለቲካ እይታ ዛሬም ድረስ ለብዙ ሺዎች ስደት፣እስር እና ጉስቁልና ምክንያት ሆኗል። ጥቂት የስርዓቱ አቀንቃኞች ግን ዛሬም አስመራ እና አዲስ አበባ ላይ የግንቦት ወር በዓል ለማክበር ሽር ጉድ እያሉ ነው።

ፀጥ ለጥ አድርገው ለመግዛት የሚያስቡት አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ ከደርዘን በላይ የሚሆኑ አብረዋቸው በረሃ የነበሩ ወዳጆቻቸውን እና  ሌሎች ሺዎችን በእስር ቤት አጉረው፣ በመቶ ሺዎችን ደግሞ በሊብያ፣በግብፅ፣በሱዳን እና በየመን ሀገር ጥለው እንዲሄዱ አድርገው፣ዛሬም የግንቦት 16 በዓል ሊያከብሩ አስመራ ላይ ሽር ጉድ እያሉ ነው።የኤርትራ እናቶች ግን አንድ ኩንታል ጤፍ 10 ሺህ ናቅፋ እየከፈሉ ልጆቻቸውን መመገብ አቅቷቸው ተቀምጠዋል።

በደርግ ዘመን ሻብያ አስመራን  በከበበት፣ህወሓት ትግራይን ከመላው ኢትዮጵያ ነጥሎ በያዘበት 1982 ዓም ምንም አይነት የመንገድ ትራንስፖርት ከመሃል ሀገር ወደ አስመራ ለመውሰድ የማይቻልበት ሁኔታ ነበር። የአስመራ ሕዝብ ግን ከመሰረታዊ የኑሮ ሸቀጥ ጀምሮ እስከ ጤፍ እና ልዩ ልዩ ጥራጥሬ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደሌሎች ሃገራት የሚያደርገውን ካርጎ በረራ እየሰረዘ  የአቅርቦት ዋጋው አስመራ ላይ  ከአዲስ አበባ ብዙም የተለየ እንዳይሆን ለማድረግ ትልቅ ወጪ የጠየቀ ሥራ ይሰራ እንደነበር በወቅቱ በአየር መንገዱ ሰራተኛ የተናገሩትን አስታውሳለሁ።ይህ ደግሞ የአንድ መንግስት ግዴታ ነው እና ደርግ አሁን አስመራ ካለው የኑሮ ውድነት በማይገናኝ መልኩ አቅርቦቱን በቀበሌ እንዲዳረስ ያደርግ ነበር። ዛሬ አቶ ኢሳያስ ይህንን ማድረግ አልቻሉም።የስሕተታቸው መሸፈኛ ማሰር፣መግደል እና ማሰደድ ሆኗል።
ዛሬ በኤርትራ መፃኢው ምን እንደሆነ የማያውቅ ግን በገዥው እንደ ህዝቡ አጠራር ''በነጠላ ጫማ የገባው ሌላው ደርግ'' አማካይነት ማንነቱን ያጣው ሕዝብ ዛሬም የሰሚ ያለህ እያለ ነው።ለእዚህ ሁሉ አብነት እናንሳ አስቴርን። በሺህ ለሚቆጠሩ በግፍ ለታሰሩ ማሳያ የሆነችው  ከአስር ዓመት በላይ ካለፍርድ በኤርትራ እስር ቤት የምትማቅቀው አስቴር ዮሐንስ ማን ነች? ቪድዮውን ይከታተሉ።



ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG

Thursday, May 22, 2014

ይሻል መጣ ብዬ ምርኩዝ አስጨበጨ መንገድ ያሳየሁት፣ ለካ ሌላም አይደል 'ደርጉ'ን ኖሯል እና 'ኢህአዲግ' ነው ያልኩት።




ይሻል መጣ ብዬ ምርኩዝ አስጨበጨ መንገድ ያሳየሁት፣
ለካ ሌላም አይደል 'ደርጉን' ኖሯል እና 'ኢህአዲግ' ነው ያልኩት። የደርግ እና የኢህአዲግ መመሳሰል ታወሰኝ እና  የኢትዮጵያ ገበሬ ምን ብሎ ያስብ ይሆን? እያልኩ ሳስብ የመጣልኝ ግጥም ነው።

በ 1967 ዓም የንጉሱን ስርዓት ከስልጣን ሲወርዱ በትረ መንግስቱን የተረከበው ደርግ የኢትዮጵያ ሰራዊት አካል በመሆኑ እና በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና አንድነት ላይ የማይደራደር ቢሆንም በአገዛዙ አምባገነንነት ኢህአዲግ ደርግን ተስተካክሎታል ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ ረቀቅ ባሉ ተንኮሎች ''ደርግ የዋህ አልነበር እንዴ!'' የሚሉ ድምፆች እንዲበራከቱ እያደረገ ነው። በደምሳሳው ስንመለከተው አይመስልም።ወደ ዝርዝር ነገሮች ስንገባ ግን ኢህአዲግ በትክክል የደርግ አምባገነናዊ አገዛዝ ግልባጭነቱ ፍንትው ብሎ ይታየናል።
እስኪ እነኝህን ነጥቦች እንመልከት -

ደርግ ስልጣን ለሕዝብ እመልሳለሁ ብሎ ምሎ ተገዝቶ መልሶ መለዮውን እያወለቀ ስልጣኑን ያዘ።''ሕዝባዊ መንግስት አሁኑኑ'' ያሉትን ገደለ። ኢህአዲግም ስልጣንን ለሕዝብ እሰጣለሁ ብሎ ምርጫ አደረገ ተሸነፈ።''ድምፃችን ተሰረቀ'' ብለው አደባባይ የወጡትን አያሌዎችን በአደባባይ ገደለ።

ደርግ ልማቱ እየተፋጠነ ነው።''እየተዋጋን እናመርታለን'' ይል ነበር። ኢህአዲግም ''እድገታችን ሁለት አሃዝ ነው '' ፀረ ሰላም ኃይሎችን በአንድ በኩል እየተዋጋን ምርታማነትን እንጨምራለን'' ይላል።

ደርግ ሕዝቡን በዘር ሳይለይ አኢወማ (አብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበር)፣አኢሴማ (አብዮታዊት ኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር) እና ኢገማ (ኢትዮጵያ ገበሬዎች ማኅበር) እያለ ያደራጅ ነበር።
ኢህአዲግ/ወያኔ ረቀቅ አደረገው። በቋንቋ እየሰነጠቀ አማራ፣ኦሮሞ፣ትግሬ፣ሱማሌ እያለ አደራጀው። የኢህአዲግ የከፋ የሚያደርገው  ማህበራትን ሳይሆን የፖለቲካ ድርጅቶችን ነው በጎሳ የሚያደራጀው።

ደርግ በአዲስ አበባ ዙርያ ያሉ ጤፍ አምራች ገበሬዎች ምርታቸውን በአህያ ጭነው አዲስ አበባ ወፍጮ ቤቶች ድረስ አምጥተው እንዲሸጡ ይፈቅድ ነበር (ጅንአድ ከገበሬው መግዛቱን ሳንዘነጋ)። ኢህአዲግ ገበሬዎቹ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ማገድ ብቻ አይደለም ከመሬታቸው ካለ በቂ ካሳ (ይሰመርበት ካለ በቂ ካሳ) ልቀቁ አለ።

ደርግ የብሔር በሄረሰቦች ኢንስቲትዩት መስርቶ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦችን ባህል፣ወግ፣ ቋንቋ በምሁራን እንዲጠኑ ያደርግ ነበር።ኢህአዲግ ብሔር ብሔረሰቦች በዓመት አንዴ ሞቅ ያለ ዘፈን እየከፈተ በቲቪ እንዲደንሱ በማድረግ እና አብዝቶ ስለነሱ በማውራት ደርግን አስንቆታል።

ደርግ የድሀውን ሕዝብ የኑሮ ችግር ለመደገፍ በእየቀበሌው ከክብሪት ጀምሮ እሰክ ኩንታል ጤፍ እና የተማሪዎች ደብተር ሳይቀር በቅናሽ ዋጋ እንዲዳረስ ያደርግ ነበር። ኢህአዲግ በዘመኑ የኑሮ ውድነቱ ጣርያ ደርሶም እራሱ ''ኑሮ ተወደደ'' ብሎ መናገር የሚያሳስር መሆኑን በተግባር አሳየ።(ባለፈው ሰሞን ኑሮ ከበደን ያሉ ሴቶች የደረሰባቸውን ማሰብ በቂ ነው)

ደርግ አንድ ሰው ከቦታ ወደ ቦታ ሲሄድ ስሙ እና ፎቶው ያለበት መታወቅያ እንዲይዝ ያስገድድ ነበር። ኢህአዲግ ግን ስምና ፎቶ ብቻ ሳይሆን 'ብሔር' የሚል ጨምሮ ሕዝቡን ለያየው።

ደርግ አዋጅ ሲያወጣ አዋጁን ለምሳሌ የሰዓት እላፊ፣የመሰብሰብ ነፃነት ወዘተ ሲያግድ በራድዮ እና በቲቪ እንዲነገር ለጋዜጠኞች ይሰጥ ነበር።ኢህአዲግ እራሳቸው አቶ መለስ ''ከዛሬ ጀምሮ ከቤት ውጭ የሚደረግ ስብሰባ ተቃውሞ በሕግ ተከለክሏል'' ብለው ሲናገሩ አሰማን።(ግንቦት 7/1997 ዓም አቶ መለስ በምርጫ ሲሸነፉ ያወጁትን አዋጅ አስታውሱ)።

ደርግ የኢትዮጵያ ዳር ድንበርን ሳያስደፍር ሲጠብቅ ኖረ።ኢህአዲግ ከባህር በር እስከ ኢትዮ-ሱዳን ድንበር ድረስ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ ሰጠ።

ደርግ ሕዝብ ሁሉ ማንበብ እና መፃፍ መቻል አለበት ብሎ የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ጀመረ።ኢህአዲግ ሕዝብ ሁሉ እስከ ቤተሰብ ወርዶ አንድ ለ አምስት መጠርነፍ (እንደ እርሱ አጠራር መደራጀት) አለበት ብሎ አንዱ ሌላውን እንዲሰልል አደረገ።

ደርግ ባለስልጣናቱ ከስልጣን እስኪወርዱ ድረስ ብዙዎቹ ባለስልጣናት እና የጦር መሪዎች በመንግስት ቤት ውስጥ እንዲኖሩ አደረገ። ኢህአዲግ ባለስልጣናቱ ሁለት እና ሶስት ቪላ እና መኪና እንደ ግምሩክ ባለሥልጣኑ ያሉት ደግሞ አልጋቸው ስር  'የፎረክስ' ቢሮ እስኪመስል ድረስ በሺህ የሚቆጠሩ የውጭ ምንዛሪዎች የሚይዙ ሆኑ።

ደርግ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁትን በሙሉ ኃላፊነት ወስዶ ሥራ ይቀጥር ነበር። ኢህአዲግ ዩንቨርስቲ የጨረሱ ተማሪዎችን ሲመርቅ ገና ከዩንቨርስቲ እያሉ የስነ ልቦና ዘመቻ ይከፍትባቸዋል።ከምረቃ በኃላ ኮብል ስቶን እንደሚሰሩ ያረዳቸዋል። (አቶ ጁነዲን የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ሆነው ለአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተመራቂዎች የተናገሩትን እናስታውስ)።

ደርግ መብራት፣ውሃ እና ስልክ ከመቋረጡ በፊት በራድዮ እና በቲቪ ለምን፣መቼ እና ለምን ያህል ሰዓት እንደሚቋረጥ ይገልፅና ደንበኞቹን ከባድ ይቅርታ ይጠይቅ ነበር። ኢህአዲግ መብራት እና ውሃ ለሰዓታት አይደለም ለቀናት  ሲቆም ይቅርታ ሲያልፍም አይነካው። ለምሳሌ አዲስ አበባ አንድ ሚልዮን ህዝቧ ውሃ አለመኖሩ ብዙ አስጊ የሚባል አለመሆኑን የገለፁት የኢህአዲግ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው።''ውሃ የማያገኘው ሕዝብ 25% ብቻ ነው'' ነበር ያሉት አቶ ኃይለማርያም ለጋዜጠኞች ሲመልሱ።

ደርግ ሕዝብ በግዳጅ ሰልፍ እንዲወጣ ያደርግ ነበር። ኢህአዲግ ሕዝብ ከኖረበት ቦታ ተባሮ እንዲወጣ በባለስልጣናቱ ሲደረግ እንዳለየ ለመምሰል እንደ አቶ መለስ ስለምፈናቀሉት ወገኖች ሲጠየቁ  ደግሞ ነዋሬውን ''ድሮም ሞፈር ሰበር ነው'' ሲሉ ተናገሩ።(እዚህ ላይ ከጉርዳ ፈርዳ፣ሐረር ጋምቤላ እና ሌሎች ቦታዎች የተፈናቀሉትን አስቡ።)

እንዲህ እንዲህ እያልን ደርግ ተመልሶ በከፋ አገዛዙ መመለሱን እና በአንዳንዶቹማ ይብሱን ደርግ የተሻለባቸው ሁኔታዎች እንደነበሩ ብዙ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል።

ይሻል መጣ ብዬ ምርኩዝ አስጨበጨ መንገድ ያሳየሁት፣
ለካ ሌላም አይደል ደርጉን ኖሯል እና  'ኢህአዲግ' ነው ያልኩት።

ጉዳያችን
ግንቦት 11/2006 ዓም 

ወቅታዊው እና መጪው የኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ምጣኔሃብታዊ እና ማኅበራዊ ሁኔታ በሶስት ርዕሶች ማጠቃለል ይቻላል።

  ፎቶ ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የ2017 ዓም የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ መትከል ብሔራዊ ዘመቻ ሲከፍቱ። ========= ጉዳያችን ምጥን ======== በእዚህ ጽሑፍ ስር ሶስት ምጥን ርዕሶች ያገኛሉ። እነርሱም  አ...