ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, July 21, 2019

ለኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት አደገኛው ፖለቲካዊው ተግዳሮት ብቻ አይደለም። (ጉዳያችን ልዩ ትኩረት)

ጉዳያችን / Gudayachn
ሐምሌ 14/2011 ዓም ( ጁላይ 21/2019 ዓም)

~ የጎሳ ግጭቶች በቀጥታ እያመሩ ያሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ  አብያተ ክርስቲያናትን  ወደ ማቃጠል እና አገልጋይ ካህናትን ወደ መግደል ነው።ይህ ደግሞ ለዓመታት በሌሎች የተሰጡት የዕምነት ትምህርቶች ውስጥ የተቀየጠ ጎሳዊ እና ፖለቲካዊ  የተደባለቁ ጉዳዮች እንደነበሩ አመላካች ነው።

~ የኢትዮጵያን ሁኔታ ስንመለከት ከፖለቲካው እና ወታደራዊ ሁኔታዎች አንፃር ብቻ የምንረዳ፣ፖለቲካው እና ወታደራዊ ሁኔታዎች የሚዘወሩበት ሌሎች ጉዳዮች የሌሉ ያህል ተዘንግተዋል።

~ የጎሳ ፖለቲካው ጡዘት የሚዘወረው በምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች እየታከከ መሆኑ አንዱ ማሳያ ይሄው የደቡብ ኢትዮጵያ ጉዳይ ነው። 
===============================

ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ተቆጣጥሮ የነበረው ህወሓት መሩ የኢህአዴግ ስርዓት በሕዝባዊ እንቅስቃሴ ግፊት በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ በተነሳ የለውጥ የማቀንቀን ሂደት ድርጅቱ ተገፍቶ እና አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ዶ/ር ዓቢይ አህመድን ወደ ጠቅላይ ሚንስትርነቱ ቦታ ለማምጣት ተገዷል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጋቢት 24/2010 ዓም በፓርላማ ካደረጉት ንግግር ወዲህ የሀገሪቱ የፖለቲካ ውጥረት መርገብ ብቻ ሳይሆን በባህር ማዶም ሆነ በኤርትራ የነበሩ በርካታ የተቃውሞ አደረጃጀቶች ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል። 

እነኝህ ሁሉ ሂደቶች ለአንድ ዓመት ሁኔታዎች ካበረዱ በኃላ መሰረታዊው የሀገሪቱ ችግሮች በራሳቸው እያፈጠጡ መጥተዋል።እነኝህ መሰረታዊ ችግሮች በቀደሙ ዓመታት ፖለቲካዊ ብቻ ተደርገው ይወሱ ስለነበር።የፖለቲካ ለውጡ ሁሉንም ይፈታል የሚል የተሳሳተ ዕሳቤ የያዘው ኢትዮጵያዊ በተለይ ምሁራንም ጭምር ቀላል አይደሉም። በተለይ በምሁራኑ ዘንድ ፖለቲካውን ብቻ የመመልከት እና ሌሎች ወሳኝ የሀገሪቱ ጉዳዮች የመርሳት አባዜ የተጠናወተው ቀላል አይደለም።ይህም በመሆኑ ከለውጡ ሂደት ጋር በተያያዘ የሚነሱት ጉዳዮች በሙሉ ፖለቲካዊ ስለሆኑ ዜጎች ለመፍትሄ ሲያስቡ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ከመሆን እና ከመመስረት ያለፈ ሊሆን አልቻለም።

በኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የመንግስት ስሪት ሂደትም ሆነ የታሪክ አፃፃፍ ልማድ የቤተመንግስቱን መንግስታዊ በተለይ አስተዳደራዊ እና ወታደራዊ ታሪኮች ብቻ ላይ የተመሰረቱ ሰለሆኑ የኢትዮጵያን ሁኔታ ስንመለከት ከፖለቲካው እና ወታደራዊ ሁኔታዎች አንፃር ብቻ የምንረዳ፣ፖለቲካው እና ወታደራዊ ሁኔታዎች የሚዘወሩበት ሌሎች ጉዳዮች የሌሉ ያህል ተዘንግተዋል።

ባለፈው አንድ ዓመት ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ለለውጥ መነሳቱን ካሳወቀ ወዲህ በርካታ ለአመታት የተጮሁባቸው በተለይ የእስረኞች አያያዝ፣የመፃፍ እና የነፃ ጋዜጦች መውጣት፣አሳሪ የነበሩ ደንቦችን በማሽሻል፣ እና ባጠቃላይ የፖለቲካ ውጥረቱን ከማርገብ አንፃር ትልቅ ሥራ ተሰርቷል።ይህ ብቻ አይደለም የኢትዮጵያ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፍ ሚና ከለውጡ ሂደት መጀመር በፊት ከነበረበት አንፃር ሲታይ የተሻለ ተደማጭነት የማግኘቷ ሁኔታ ሁሉ አመርቂ ናቸው።የሰሜንም ሆነ የደቡብ ሱዳን ችግሮች ኢትዮጵያ ቀድሞ በነበረችበት ደካማ ዲፕሎማሲያዊ ተደማጭነት ደረጃ ሆና ቢሆን ኖሮ የበርካታ መካከለኛው ምስራቅ እና ምዕራባውያን ሳይቀሩ በኢትዮጵያ ጎረቤቶች ጉዳይ እጃቸውን እንዲያስገቡ ዕድል በሰጣቸው ነበር። 

ለለውጡ ሂደት የፖለቲካ ጡዘቱን የጨመሩት ሁለቱ ወሳኝ ጉዳዮች ከፖለቲካው እኩል መፍትሄ ይሻሉ።

የለውጥ ሂደቱ ፖለቲካዊ መፍትሄ መፈለጉ ጥያቄ ውስጥ አይገባም።እዚህ ላይ ለውጥ የሚለውን ቃል ከመተርጎም አንፃር ለውጡን ፍኖተ ካርታ በሌለበት ሁኔታ እንዴት እንለካው? መዋቅራዊ ለውጥ በሌለበት ሂደት እንዴት እንተምነው? የሚሉ ጥያቄዎች አሁንም በብዙዎች አዕምሮ የሚመላለስ ጉዳይ መሆኑ ሳይረሳ  ከአንድ መቶ በላይ ተቃዋሚ ድርጅት በሚርመሰመስበት ሀገር መንግስት ፍኖተ ካርታ ተወያይቶ ማዘጋጀት ይችል ነበር ወይ የሚለውንም መሰረታዊ ጥያቄ መዘንጋት አይገባም።ይህ ማለት እንደ አከራካሪ ነጥብ ለማንሳት እንጂ  በእዚህ ምክንያት ፍኖተ ካርታ በእዚህ ሳብያ ሊኖር አይገባም ወደሚል ድምዳሜ ይወስዳል ማለት አይደለም።

ኢትዮጵያ ላለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን የፖለቲካውን ሜዳ በጎሳዊ ስሜት የመቃኘት እና የህዝብ የእርስ በርስ ግንኙነቱን ወደ አደገኛ መስመር የመሩት ሁለቱ ቁልፍ ጉዳዮች ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሁኔታዎች ናቸው። እዚህ ላይ ለጎሳ ፖለቲካ የፖለቲካ አመራሩ ተጠያቂ አይደለም እያልኩ አይደለም።የፖለቲካ አመራሩ ፖሊሲ ከማውጣት እና ወታደራዊ ኃይሉን ከመያዙ አንፃር እነዚህ ሁለቱንም ማለትም ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሁኔታዎች ያገናዘበ አመራር ከመስጠት ይልቅ ወደ አንድ ጎሳ ያደላ የጥቅም ሽምያ ውስጥ በመግባቱ ችግሩን አናረው ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ወደ አደገኛ መስመር ከቷት ዘወር አለ። አሁን ያለው የለውጥ ሂደት ይህንን  ውጥንቅጥ ሁኔታ ላይ የተቀመጠ የለውጥ ሂደት ነው። ሁለቱ ቁልፍ ጉዳዮች ማለትም ማኅበራዊው እና ምጣኔ ሃብታዊ ሁነቶች በውስጣቸው በርካታ ዘርፎች ቢኖራቸውም ለእዚህ ፅሁፍ አደጋው ፖለቲካዊ ብቻ አለመሆኑን ለማሳየት ከማኅበራዊ እና ከምጣኔ ሃብታዊ ሁኔታዎች አንዳንድ ነጥቦች ብቻ አነሳለሁ። 

የምጣኔ ሃብታዊው ጉዳይ እና የጎሳ ፖለቲካ ችግር።

ብዙውን ጊዜ የጎሳ ፖለቲካ ሲነሳ የሚወሳው የጎሳ ፖለቲካ ስለሚያቀነቅኑ ድርጅቶች እና ግለሰቦች እንጂ የጎሳውን ፖለቲካ እንዲያቀነቅኑ የህዝብ ጆሮ የገዙበት የምጣኔ ሀብት ጉዳይ አይነሳም።የጎሳ ፖለቲካ በራሱ መዘውር የለውም አንዱ መዘወሪያው  የምጣኔ ሀብት ችሮታ እንደሚያስከትል ለወጣቱ ስለሚሰብክ ነው።''ክልል መሆንህ የሚያመጣው ፀጋ አለ'' ከሚለው ስብከት ስር ሥራ ታገኛለህ፣ከሌላ አካባቢ የመጣ የስራ ዕድልህን አይወስድም፣ የምክር ቤት አባል ትሆናለህ፣የክልልህ ካቢኔ አባል ትሆናለህ፣ እና የመሳሰሉ ማባበያዎች ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ናቸው።በርካታ ወጣት ከዩንቨርስቲ ተመርቆ ሥራ ባላገኘበት ሁኔታ ብቸኛ አማራጩ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቅኖ ሥራ መያዝ ሆኖ ከታየው የጎሳ ፖለቲካው መሰረታዊ አንቀሳቃሽ ምጣኔ ሃብታዊ ጥያቄዎች እንጂ ፖለቲካዊ ብቻ ሊሆኑ አይችሉም። 

ከምጣኔ ሃብቱ ጋር በዋና መሠረትነት የሚነሳው የመሬት ጉዳይ አለ።መሬት ውሱን ሀብት ነው።በአንፃሩ ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት ቁጥር ከዘጠና አምስት ሚልዮን በላይ እንደሆነች ይገመታል።በሀገራችን ያሉ የጎሳ ፖለቲካዊ ግጭቶች ዋና መሰረታቸው ምጣኔ ሃብታዊ ነው።የወልቃይት ችግር መሰረቱ ፖለቲካዊ ይምሰል እንጂ የምዘውረው ምጣኔ ሃብታዊ ጥያቄ ነው። 

የወልቃይት መሬት የቅባት እህል ከሚመረትባቸው የኢትዮጵያ ግዛቶች ቀላል ያልተባለ ድርሻ ያለው እና ባብዛኛው ለውጭ ንግድ የሚቀርብ ምርት የሚመረትበት ነው። ከእዚህ በተጨማሪ ቦታው የሰሜን ጎንደርን፣የኤርትራን፣የሱዳንን እና የትግራይን አካባቢዎች በጋራ የሚያቃልል ከመሆኑ አንፃር እና ለሱዳን ወደብ ገበያ ቅርብ ከመሆኑ አንፃር ምጣኔ ሃብታዊ ስልታዊ መሬትነቱ ቀላል አያደርገውም።ከእዚህ ሁሉ በላይ በአካባቢው ካለው ሞቃት አየር በተቃራኒ የመረብ ወንዝ ምድሩን የተለየ ብቸኛ አማራጭ የውሃ ምንጩ ነው። እነኝህ ሁሉ ድምሮች የወልቃይት ጉዳይን ፖለቲካዊ ጎሳዊ ቃና ሰጥቶት ያነታርካል።ቀድመው የነበሩትን ነዋሪዎች ለማፈናቀል በህወሓት በኩል በርካታ የተንኮል ስራዎች እየተሰሩ በሰላም ምጣኔ ሃብታዊ ሂደቱን ሲያስኬድ የነበረው ሕዝብ ወደ ግጭት እንዲያመራ አደረገው። ይህ ማለት የችግሩ መዘውር ምጣኔ ሃብቱ ላይ እንዳለ አመላካች ነው።

በሌላ በኩል በደቡብ ኢትዮጵያ ያለው የጎሳ ፖለቲካ ጡዘት መመልከት ይቻላል።የደቡብ ኢትዮጵያ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚለየው በከፍተኛ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ መምጣት እና በርካታ ሕዝብ ያልሰፈረባቸው ቦታዎች ቢኖሩም በርካታ ሕዝብ በተወሰኑ ቦታዎች ተጣቦ በመኖር (population density) የሚኖርበት መሆኑ ነው። ይህ የህዝብ ቁጥር መጨመር እና ተጣቦ በተወሰኑ ቦታዎች የመኖር ሁኔታ የመሬት ጥበት እና የስራ አጥ መብዛት አስከትሏል።በሌላ መልኩ ደግሞ ለጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች ለስራ ማጣቱም ሆነ ለችግሩ መንስኤ ከክፍለዘመን በላይ በቦታው የኖሩ ሰዎችን እንደምክንያት እየጠቀሱ ሕዝብ ለማጋጨት ተመችቷቸዋል።ስለሆነም የጎሳ ፖለቲካው ጡዘት የሚዘወረው በምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች እየታከከ መሆኑ አንዱ ማሳያ ይሄው የደቡብ ኢትዮጵያ ጉዳይ ነው።የህዝብ ስፍረት መጣበብ በደቡብ ኢትዮጵያ የዛሬ ስድስት ዓመት የነበረውን ሁኔታ ከስር ካለው ካርታ ላይ ብንመለከት ከፍተኛው የህዝብ ስፍረት መጣበብ የሚታየው በደቡባዊ ኢትዮጵያ መሆኑን እንመለከታለን።ይህ ማለት ግን ሕዝብ ሊሰፍርባቸው የሚችሉ ሰፊ ቦታዎች በደቡባዊ ኢትዮጵያ የሉም ማለት ግን አይደለም።የጎሳው ፖለቲካ በዛው በደቡብ ውስጥ ላለው ህዝብም በበርካታ የጎሳ ክልል ስለለየው ሌላው ጋር ሄዶ እንዳይሰራ እንቅፋት እየሆነ እንደመጣ አመላካች ነው።

Large Cities and Population Density in Ethiopia 

በኢትዮጵያ ትልልቅ ከተሞች እና ሕዝብ በብዛት የሰፈረባቸው ቦታዎች  

 Source: EASE 2000/01, Central Statistical Agency 

(Copy from A Sub-National Hunger index for Ethiopia Assessing programs in Region level Out comes by  Emily Schmidt and Paul Dorosh)



የማኅበራዊ ጉዳይ እና የጎሳ ፖለቲካ ጡዘት 

ቀድም ብሎ እንደጠቀስኩት በእዚህ ፅሁፍ ስር የሚነሳው ሁሉንም የምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ዘርፎች አይደለም። ከማኅበራዊ ዘርፍ ውስጥ ከኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የቀደመም ሆነ የአሁኑ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ሚና የሚጫወተው የሃይማኖት ጉዳይ ላይ ለማትኮር ይሞከራል።ኢትዮጵያ በረጅም ጊዜ ታሪክ ውስጥም ሆነ በያዝነው 21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ የሃይማኖት ሚና በአብዛኛው ህዝቧ የዕለት ከዕለት ሕይወት አንፃር ያለው ተፅኖ ቀላል አይደለም።ሃይማኖት ከአምልኮት ሂደቱ በተጨማሪ የህዝቡ ስነ ልቦናዊ ሁኔታ ሁሉ ከሃይማኖታዊ እሳቤዎች ውጪ ማድረግ አይቻልም።

በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ የሚገኘው አብዛኛው ሕዝብ መንግስታዊ ስሪቶችንም ከእዚሁ አንፃር እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸውን ይከታተላል።በሃይማኖት ምክንያት ለክቶ ያለውን መንግስት ሊያጥላላ ወይን ሊያወድስ ይችላል። በእርግጥ አሁን ባለንበት ዘመን ህዝቡ መንግስት ጭልጥ ብሎ የአንዱ ሃይማኖት አቀንቃኝ መሆኑን አይፈልገውም።ከእዚህ ይልቅ ሚዛናዊ የሆነ እና የሁሉንም ዕሴቶች የሚያከብር መንግስት መሆን እንዳለበት የሚያምን ትውልድ ነው። ለእዚህ ደግሞ ከደርግ ዘመን ጀምሮ የነበረው ሃይማኖት አልባ መንግሥታት የጣሉበት አንዳች ተፅኖ የለም ማለት አይቻልም። ይህ ማለት ግን ሃይማኖት አልባ መንግስት ሕዝብ ባይጥለው መለኮት ስለማይወደው እግዚአብሔርን የሚፈራ መንግስት መሆኑ አስፈላጊ መሆኑን ያምናል።  

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማኅበራዊ ዘርፍ በሆነው በሃይማኖት አንፃር በኢትዮጵያ እየተለወጡ ያሉ ጉዳዮች አሉ። እነርሱም : -

  • በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች የጎሳ ፖለቲካ መጠግያ ማድረጋቸው፣
  • ካልታወቁ የዓረብ ሀገሮች የሚተላለፉ ፅንፈኛ እስልምና ቅስቀሳዎች በሳተላይት ዲሽ ኢትዮጵያ ውስጥ መታየት መቻላቸው እና አንዳንድ ወጣቶችን ማማለላቸው፣
  • ወጣቶች ወደ ዕምነት ቦታዎች በብዛት መምጣት መጀመራቸው፣
  • የሃይማኖት ተቅዋማት ዘመኑን የዋጀ አስተዳደራዊ ስርዓት አለመዘርጋታቸው  
  • መንግስት ላለፉት አርባ ዓመታት የሃይማኖት ተቅዋማትን የመደገፍ አዝማምያ ከማሳየት ይልቅ ለማዳከም ብዙ ርቀት መሄዱ እና 
  • የምዕራብ ሚሽነሪዎች በክርስትና ስም በብዛት ወደ ኢትዮጵያ መጉረፍ የፈጠረው አዲስ ፖለቲካዊ እና አካባቢያዊ ስሜቶች የሚሉት ይጠቀሳሉ።
ሃይማኖታዊ ጉዳይን በተመለከተ ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ብቻ የቅርብ የኢትዮጵያ ክስተቶች አይደሉም።ሆኖም ግን ከጎሳ ፖለቲካ ጡዘቱ አንፃር ሃይማኖት ምን አስተዋፅኦ አደረገ የሚል መሰረታዊ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ከላይ የተፈጠሩት የቅርብ ክስተቶች (ላለፉት ሰላሳ ዓመታት) በራሳቸው የፈጠሩት ክፍተት ቀላል አይደለም። ለምሳሌ የጎሳ ፖለቲካ አደረጃጀቶች የሃይማኖት ፅንፍ እንዲይዙ የተደረጉበት አንዱ ምክንያት የሌላውን ሃይማኖት የሚከተሉ የእገሌ ጎሳ ናቸው በሚል በጥናት ላይ ያልተመሰረተ የጅምላ ፍረጃ አንዱ ነው። እዚህ ላይ የሐጂ ጃዋር የአንድ ወቅት በአሜሪካ ለተሰበሰቡ ኢትዮጵያውያን ያደረገው ንግግር ላይ  የኦሮሞ ብሄርተኝነትን ከእስልምና ጋር ብቻ ለማያያዝ የሞከረበት ንግግር መመልከት ብቻ በቂ ነው። በእዚህ ''ኦሮሞ ማለት እስላም ነው'' በሚል ትርክት የተሞላው የአክትቪስት ሐጂ ጃዋር ንግግር ላይ (ንግግሩን ይህንን በመጫን መመልከት ይችላሉ) የጎሳ ፖለቲካን እንዴት ከሃይማኖት ጋር በመለወስ ለመቀስቀሻነት እንደተጠቀመበት መረዳት ይቻላል።

በደቡብ ኢትዮጵያ እና በምዕራብ ወለጋ  እየተፈጠረ ያለው የጎሳ ፖለቲካ ቅኝቱ ሃይማኖታዊ ሽታ የለውም ማለት አይቻልም።በርግጥ ጉዳዩ ፈጦ በሚድያ ደረጃ አይውጣ እንጂ ወደ ደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍል እና ወደ ምዕራባዊው ወለጋ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ሲጎርፉ የነበሩት ሚሽነሪዎች የአካባቢውን የህዝብ ስነ ልቦና ቀደም ብሎ ከነበረው የጠበቀ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዕምነት ስርዓት በተቃረነ መልክ መሄድ እና የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ''የእነ እገሌ ነች'' የሚለው ትርክት አዲስ በተከፈቱት የሚሽነሪ አዳራሾች ውስጥ አልተተረኩም ማለት አይቻልም።

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከአካባቢው ተወላጆች በብዛት አገልጋዮችን ለማፍራት ከሄደችበት ፍጥነት በበለጠ የሚሽነሪዎቹ የሃይማኖት ድርጅቶች ስለሄዱ የሚሽነሪዎቹ የዕምነት ድርጅቶች የበለጠ ለአካባቢው ነዋሪ የሚቆረቆሩ ተደርገው መቅረብ ጀመሩ። በእርግጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከደቡብም ሆነ ከምዕራብ ወለጋ አገልጋዮችን በዘመኗ አላፈራችም ማለት አይደለም። በርካታ አገልጋዮቿ እስከ ሊቀ ጳጳስ ደረጃ ደርሰዋል።ሆኖም ግን የቤተ ክርስቲያኒቱ የትምህርት ጊዜ ከሚፈልገው ረዘም ያሉ ዓመታት እና የሚጠይቀው የመምህራን እውቀት አንፃር ሲታይ የምሽነሪዎቹ በአጫጭር ኮርስ ለአገልጋይ የሚያመጧቸው የአካባቢው ተወላጆች በብዛት እየጨመሩ መጡ። 

እዚህ ላይ ማወቅ የሚገባን ሕዝብ የመረጠውን ሃይማኖት የመከተል መብቱ የተጠበቀ ነው።ሃይማኖት በራሱ የፀጥታም ሆነ የልዩነት መፍጠርያ ምክንያት መሆን የለበትም።በኢትዮጵያ ግን እየያዘ ያለው አዲስ መልክም ነው።የጎሳ ግጭቶች በቀጥታ እያመሩ ያሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ወደ ማቃጠል እና አገልጋይ ካህናትን ወደ መግደል ነው።ይህ ደግሞ ለዓመታት በሌሎች የተሰጡት የዕምነት ትምህርቶች ውስጥ የተቀየጠ ጎሳዊ እና ፖለቲካዊ ቅይጥ ጉዳዮች እንደነበሩ አመላካች ነው።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በጅማ፣በጅጅጋ፣በኦሮምያ ክልል ውስጥ እና በያዝነው ሳምንት ከአምስት በላይ አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸው የተነገረበት ከሲዳሞ የክልል ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተነሳው ግርግር ብቻ ብንመለከት የኢትዮጵያ የፖለቲካው መዘውር ማኅበራዊው ውስጥ እንዳለም እንመለከታለን።

ለማጠቃለል የኢትዮጵያ አከራካሪው የለውጥ ሂደት በብዙ ምሁራን አንፃር እየታየ ያለው ከፖለቲካዊ መልኩ ብቻ ነው። ለጎሳ ፖለቲካ ችግር መፍትሄ ሲታሰብ የሚነሳው የፖለቲካ ጎኑ ብቻ እንጂ ከማኅበራዊ እየተቀየረ የመጣው የሃይማኖታዊ ጉዳይ እና ከምጣኔ ሃብቱ የመሬት ይዞታ ጉዳይ፣የስራ ዕድል እጦት እና የህዝብ ቁጥር መጨመር አንፃር ያለው ግዙፍ ጉዳይ ተዘንግቷል።የለውጥ ሂደቱ ትልቁ እንቅፋት የፖለቲካው ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳይ ነው።ለመፍትሄነት ብዙው ሰው መንግስት ይህንን ቢያደርግ፣ይህንን ባያደርግ የሚለው የቃላት ምልልስ ላይ ተጠምዷል።በርግጥ መንግስት ከፖሊሲ አውጪነት ባለፈ ነገሮች ከግለሰቦች እና ከቡድኞች በተሻለ መልኩ በተቀለለ መልክ (bird eye view) የማየት እና መረጃ የማግኘት አቅም ቢኖረውም ከፖለቲካው ባለፈ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ላይ እያንዳንዱ ግለሰብ፣ስብስብ፣የሃይማኖት ተቅዋም፣በውጭ እና በሀገር ቤት የሚኖር ምሁር ሁሉ ሚናውን ማሳነስ የለበትም።

በመፍትሄነት - ይህ ለውጥ ተመልሶ የተወሰኑ የፅንፍ ኃይሎች እጅ እንዳይገባ አቅጣጫ ብዙ (multidimensional) መፍትሄዎች ከሁሉም ወገን ይጠበቃል።በተለይ መንግስት የለውጥ ሂደቱን ከአሁን በኃላ በነበረበት ሂደት የመሄድ አቅሙ እያነሰ መምጣቱን ብቻ ሳይሆን ህወሓት መራሹ የቀድሞው ኢህአዴግ ቢሮክራሲ የለውጡን ሂደት ይዞ የመሄድ ስነ ልቦናዊ አቅም የሌላቸውን የማራገፍ ስራውን በቶሎ ጀምሮ በአዲስ የሰው ኃይል ካልቀየረ እና እራሱ ኢህአዴግም ከመፍረስ ያላነሰ ለውጥ ካላደረገ ለውጡ አደጋ ላይ መሆኑን ማወቅ አለበት።ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፈው አንድ ዓመትም ሆነ ቀደም ብሎ ለነበሩ ግጭቶች እና የህዝብ መፈናቀሎች ዋነኛ ተዋናይ የኢህአዴግ ቢሮክራሲ እና ታጣቂ ሚሊሻ ለመሆኑ የቅርብ ጊዜ እውነታ ነው።ስለሆነም ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ዋስትና ላይ ያተኮረ የለውጥ ሂደት ማንቀሳቀስ ይህም ወደ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመራ የተጠና ስልታዊ ዕቅድ ይዞ መቅረብ ከመንግስት ይጠበቃል።


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments: