ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, July 17, 2017

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በአውሮፓ ለመጀመርያ ጊዜ ሲመተ ጵጵስና አካሄደች።የኦስሎ ቅዱስ ገብርኤል አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የጵጵስና ማዕረግ ተሹመዋል።


ሲመተ ጵጵስና ከተከናወነ በኃላ (ፎቶ ጉዳያችን)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን  በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገሮች ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ሀገር ተወላጆች የምትሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።ይህ አገልግሎት በተለይ በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በተለየ መልክ እና እጅግ ወሳኝ የሆነ ገፅታ አለው። ከሀገሩ በርቀት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ማለት የመንፈሳዊ ሕይወታቸው መሪ ብቻ ሳትሆን የባህል፣ማንነት እና ስነልቦናዊ ፋይዳ ሁሉ የሚገለጥባት ልዩ አካሉ ነች።ከእዚህ ሁሉ የአገልግሎት ፋይዳ ጋር እንግዲህ የአገልጋይ ካህናት ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደ አንድ ቁልፍ ተቋም እና የምእመናንን ሕይወት በመንፈሳዊ እና ዓለማዊ ሕይወት ዙርያ የመምራት አቅም፣ አሻጋሪ ርዕይ እና ብቁ ትውልድ የማፍራት ሥራ ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ በሚኖራት ብቃት ያላቸው አገልጋይ ካህናት ይወሰናል። 

ቤተ ክርስቲያኒቱ ካሏት መሰረታዊ ባህርያት ውስጥ አንድነት እና ሐዋርያዊ መሠረትነት ላለፉት ሃያ አምስት አመታት በፈተና ላይ መውደቃቸው ይታወቃል።ለእዚህም ዋነኛ ምክንያቱ አሁን ስልጣን ላይ የሚገኘው መንግስት የነበሩትን ፓትርያርክ መርቆርዮስ ከሀገር እንዲወጡ ግፊት ካደረገ በኃላ ፓትርያርኩ በሕይወት እያሉ የአቡነ ጳውሎስ ፓትርያሪክነት መሰየም ነው።ችግሩ ከተፈጠረ በኃላም በውጭ እና በሀገር ቤት  ያሉ ብፁዓን አባቶች መካከል  ንግግር ተደርጎ ችግሩን ለመፍታት የተደረጉ ሙከራዎች  የሚፈለገውን ውጤት አላስገኙም።ለእዚህ በዋናነት የሚጠቀሰው ምክንያት ለአንድነቱ በጎ ፍቃድ ብቻ ሳይሆን በሁሉም መስክ በታማኝነት ለመስራት ፈፅሞ ምልክትም ያላሳየው በስልጣን ላይ የሚገኘው መንግስት  አንዱ እና ተጠቃሽ ነው። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ሀገር በስደት የሚገኘው ሲኖዶስ ብፁዓን አባቶች አህጉረ ስብከቶቹ ከሚያስፈልጋቸው አገልጋይ ጳጳሳት አንፃር ተጨማሪ ጳጳሳትን ከቆሞሳት መካከል እየመረጡ ለጵጵስና ማዕረግ እያበቁ ይገኛሉ።ከአገልግሎቱ አንፃር የቆሞሳት ለጵጵስና ማዕረግ መብቃት ቤተ ክርስቲያን እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ እግዚአብሔር እንደፈቀደ የሚቀጥል መንፈሳዊ ተግባር ነው።የሁሉም ምእመናንም ሆነ የሁሉም ብፁዓን አባቶች ምኞት እና ፀሎት ግን አሁንም ቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነቷን መልሳ የምታጠናክርበት ቀን እንዲቀርብ ነው። ይህ እስኪሆን ድረስ ግን በአባቶች መካከል የቀኖና እና ስርዓት ጉዳይ እንጂ የመሰረተ ሃይማኖት (ዶግማዊ)  ልዩነት ካለመኖሩ አንፃር ቤተ ክርስቲያን አሁን ያሉባትን ችግሮች የመፍታት አቅሟ አሁንም ትልቅ መሆኑን መረዳት ይቻልል።

በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውጭም ሆነ በሀገር ቤት የሚገኙ አባቶች በጋራ በመቆም አርአያነት ያላቸው እንቅስቃሴዎች እየታዩ ናቸው። እነኝህ እንቅስቃሴዎችም በተሃድሶ ጉዳይ ላይ እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች ናቸው።በያዝነው ዓመት ብቻ በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ያሉ አባቶች በሲኖዶስ ስብሰባዎች ላይ በመግለጫ ደረጃ በጋራ ያስነበቡት ዓቢይ ጉዳይ የቤተ ክርስቲያኒቱን መሰረተ ዕምነት መፃረር ላይ የሚገኘው በተሃድሶ እንቅስቃሴ ላይ ያሳዩት ግልጥ መመሪያ ነው። በስደት የሚገኙ አባቶች በቅርቡ በተደረገው የሲኖዶስ ስብሰባ ላይም ሆነ ባሳለፍነው ሳምንት በስዊድን ፣ ስቶኮልም በተደረገው ሃያኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አውሮፓ መንፈሳዊ ጉባኤ ፍፃሜ ላይ በወጣ መግለጫ በተሃድሶ እንቅስቃሴ ላይ ሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት እራሳቸውን መጠበቅ እና ምእመናንን ማስተማር ተገቢ መሆኑን አፅኖት በመስጠት አሳስቧል። 

የመጀመርያው ሲመተ ጵጵስና በአውሮፓ 

ከላይ የተጠቀሱት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ነባራዊ እና ወቅታዊ ሁኔታ ለመንደርደርያነት ከቀረበ ባሳለፍነው ሳምንት ማለትም ሐምሌ 9፣2009 ዓም በአውሮፓ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመርያ ጊዜ ሲመተ ጵጵስና ማካሄዷን ወደ ሚገልጠው ዜና እንለፍ።በጵጵስና የተሾሙት አባት የቀድሞ ስማቸው መላከ ብስራት ቆሞስ አባ ሀብተየሱስ ለገሰ ሲሆኑ የጵጵስና ስማቸው አቡነ ሕርያቆስ ተብለው በስደት የሚገኙት ብፁዓን አባቶች በተገኙበት ፀሎት ተሹመዋል።ከእሁዱ የሹመት መርሃግብር በፊት በ2008 ዓም አቡነ ሕርያቆስ የቀደመ አገልግሎት እና ለጵጵስና ማዕረግ ብቁ መሆናቸው በውጭ ለሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በአቡነ መርቆርዮስ ሰብሳቢነት ጉዳዩ  የቀረበ እና ብፁዓን አባቶችም ጉዳዩን መርምረው ለጵጵስና ከታጩት ስምንት አባቶች መካከል አንዱ መሆናቸው እና ከስምንቱ መካከል ስድስቱ ጥቅምት 23፣2009 ዓም በኦሀዮ መድሃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን አባቶች ምልዓተ ጉባኤ ሲሾሙ በቪዛ ምክንያት በቦታው ተገኝተው መሾም ያልቻሉት አቡነ ሕርያቆስ (የቀድሞው መላከ ብስራት ቆሞስ አባ ሀብተየሱስ ለገሰ) ባሉበት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ  መልካም ፍቃድ እና ብፁዓን አባቶች ምርጫ ባሉበት እንዲሾሙ ቋሚ ሲኖዶስ ብፁዓን አባቶችን ልኮ እንዲከናወን ምልዓተ ጉባኤው ውሳኔ አሳልፎ ነበር። በእዚሁም መሰረት ቋሚ ሲኖድስ የምልዓተ ጉባኤው ውሳኔ መሰረት መጋቢት 5፣ 2009 ዓም ባደረገው ስብሰባ ሿሚ ሊቃነ ጳጳሳትን በመመደብ  ሹመቱ ሐምሌ 9፣2009 ዓም በብፁዕ አቡነ ኤልያስ መንበረ ጵጵስና በሚገኝበት በስቶኮልም ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን እንዲከናወን  በመጋቢት 20፣ 2009 ዓም ለሿሚ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ለአቡነ ኤልያስ እና ስቶኮልም ለሚገኘው ደብረ ሰላም መድሃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በፃፈው ደብዳቤ ማሳወቁን ለማወቅ ተችሏል። በመሆኑም አቡነ ሕርያቆስ መቀመጫቸውን በኦስሎ፣ኖርዌይ አድርገው የአቡነ ኤልያስ ልዩ ረዳት በመሆን ተሹመዋል።


አቡነ ሕርያቆስ ከጵጵስና ሹመት በኃላ ከዲያቆን ናትናኤል እና ዲያቆን ሳሙኤል ጋር 

አቡነ ሕርያቆስ  (ከጵጵስና በፊት በነበራቸው ስማቸው መላከ ብስራት ቆሞስ አባ ሀብተየሱስ) ማን ናቸው?

ልደት 

ጥቅምት 5፣1968 ዓም ከአባታቸው ከአቶ ለገሰ አዛናው እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ጥሩ ወርቅ ከበደ በኢትዮጵያ ስማዳ ወረዳ ተወለዱ።

ትምህርት 
እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በተወለዱበት በደብረ ቅዱሳን ዱቄ እየሱስ ከአባ ተፈራ ፀጋው ፊደለ ሐዋርያ፣ ውርድ ንባብና አምስቱ አዕማደ ምስጢርን ከአባ አሳየ ጎሹ በቃል ልዑል ሰምራ በዓታ፣ ዳዊት እና ቅዳሴ ከአባ ይሄይስ ካሳ በቅዱስ ወይራዬ ቅዱስ ገብርኤል ተምረዋል።ከእዚህ በተጨማሪ የሚከተሉትን ትምህርቶች በሚገባ አጠናቀዋል።እነርሱም -

1/ ዜማ 
ከየኔታ ይትባረክ እና ከየኔታ ኪነ ጥበብ ዓለማየሁ በአንጎት ማርያም ተምረዋል።

2/ ቅኔ 
በስማዳ ስመጥር ከሆነው ደብር ቃጨና ኢየሱስ ከየኔታ ዓለሙ፣ እንዲሁም ወደ ምስራቅ ጎጃም ተሻግረው በደጀን ጊዮርጊስ ከየኔታ ናቃቸው ዲበ ኩሉ ተምረዋል።

3/ አቋቋም 
በአጋጥ ሩፋኤል ከየኔታ ተመቸ እና በደብረ ኤልያስ ከየኔታ ወልደ ሚካኤል እና የክብረ በዓላትን እና መዝሙራትን አሰላ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ከሊቀ ጉባኤ ጽጌ አክሊሉ ተምረዋል።

3/ ትርጓሜ
ውዳሴ ማርያም፣ ቅዳሴ ማርያም፣ኪዳን፣ትምህርተ ኅቡዓት እና ባሕረ  ሀሳብ የትርጓሜ መምህር ከነበሩት የኔታ ፍስሃ (አበባው) በመቱ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ተምረዋል።

4/ ኮርሶች 
- በመቱ ፈለገ ሕይወት የካህናት ማሰልጠኛ የሶስት ወራት ኮርስ ወስደዋል፣
- አዲስ አበባ በሚገኘው በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ኮሌጅ የአንድ ዓመት ኮርስ ተከታትለዋል።

5/ ማስተርስ፣ ባችለር ዲግሪዎች  እና ዲፕሎማ 
ደቡብ አፍሪካ፣ ጆሃንስበርግ  በሚገኘው ወርልድ ሃርቨስት ቴዎሎጂ ኮሌጅ (World Harvest Theological College _ WHT)  የማስተርስ ዲግሪ በክርስቲያን አመራር (Christian leadership)፣ የባችለር ዲግሪ በነገረ መለኮት (Bachelor of Divinity) እና ዲፕሎማ በመፅሐፍ ቅዱስ ጥናት( Diploma in biblical studies) ተምረው ተመርቀዋል።

6/ክህነት 
- በ1983 ዓም ዲቁና ከብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣
- በ1991 ዓም ምንኩስና እና ቁምስና ከአቡነ ፊሊጶስ መቱ፣ኤልባቦር ደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል 

7/ አገልግሎት 
- ከመጋቢት 1989 እስከ የካቲት 1990 ዓም በኢልባቦር ሃገረ ስብከት እና በደሌ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በመሪ ጌትነት፣
- ከ1990 እስከ 1993 ዓም ወደ ሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ከፍተኛ ኮሌጅ ለተጨማሪ ትምህርት እስከተላኩበት ድረስ የኢልባቦር ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ የብፁዕ አቡነ ፊልጶስ አቡነ ቀሲስ በመሆን እና በመቱ የደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል መንበረ ጵጵስና ረዳት መሪ ጌታ በመሆን አገልግለዋል።
- ከ2001 እስከ 2005 ዓም በአቡነ ኤልያስ መልካም ፍቃድ የዩጋንዳ መካነ ሰላም መድሃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፣
- ከ2005 እስከ 2015 ዓም በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ፅርሐ አርያም ስላሴ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ኃላፊ ሆነው ለአስር አመታት አገልግለዋል።
- ከ2007 ዓም ጀምሮ የኦስሎ ቅዱስ ገብርኤል አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሆነው በጵጵስና እስከተሾሙበት ሐምሌ 9፣2009 ዓም ድረስ አስተዳዳሪ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን በጵጵስና ማዕረግ ከተሾሙም በኃላ የኦስሎ ቅዱስ ገብርኤል አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነታቸው የሚቀጥሉ መሆናቸው ሲታወቅ በተጨማሪ የአቡነ ኤልያስ ልዩ ረዳት በመሆን ያገለግላሉ።

በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ እና በአቡነ መርቆርዮስ ፍቃድ መሰረት በአቡነ ሕርያቆስ ሲመተ ጵጵስና ላይ ስቶኮልም፣ ስዊድን መድሃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ከአቡነ ኤልያስ ጋር  በተጨማሪ ተገኝተው ሹመቱን የፈፀሙት ብፁዓን አባቶች የሚከተሉት ናቸው። እነርሱም - 
1ኛ/ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል የምዕራብ ካናዳ ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ ምክትል ዋና ፀሐፊ፣

2ኛ/ አቡነ ዲሜጥሮስ የምስራቅ ካናዳ ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣

3ኛ/ አቡነ ቴዎፍሎስ የካሊፎርኒያ ሃገረ ስብከት ረዳት ሊቀጳጳስ እና የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣

4ኛ/ አቡነ ማርቆስ የዋሽንግተን ሲያትል እና የፖርትላንድ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ናቸው።



ፎቶ - በሃያኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ የአውሮፓ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ከብፁአን አባቶች ጋር አቡነ ኤልያስ ሲናገሩ

በመጨረሻም አቡነ ሕርያቆስ ከላይ ቀደም ብሎ ከተጠቀሱት ተግባራት በተጨማሪ በደቡብ አፍሪካ እስከ ክህነት ድረስ ያደረሷቸው ወጣቶችን በማስተማር አርአያነት ያለው ተግባር ፈፅመዋል። በኦስሎ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንም ማገልገል ከጀመሩ ገና ሁለተኛ አመታቸው ቢሆንም የአብነት ትምህርት መርሃ ግብር በመክፈት፣የቤተ ክርስቲያኗ የአገልግሎት መዋቅር እንዲሰፋ በማድረግ እና ሁሉንም ምእመናን በአባታዊ ፍቅር በማቅረብ እየሰጡት ካለው አገልግሎት በተጨማሪ የአብነት ትምህርት ዘወትር አርብ በአካል እየሰጡ ሲሆን የያይዝነውን ክረምት ሁለት ወሮች ደግሞ በእየቀኑ ለሶስት ሰዓታት እየተገኙ ትምህርት እየሰጡ ሲሆን በእዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥም አራት ዲያቆናትን ኦስሎ ላይ አፍርተዋል። ለአቡነ ሕርያቆስ እረጅም እድሜ እና መልካም የአገልግሎት ዘመን እንመኛለን።







ጉምህርትዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...