ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, February 13, 2018

ኢትዮጵያ ከአሁን በኃላ ከነፃነት ውጭ አንድም ቀን መቆየት አትችልም።የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ሃገራዊ ወይንም ብሔራዊ ጥያቄ ላይ ያተኮሩ አድርጎ መነሳት ይገባል። (የጉዳያችን ማሳሰቢያ)



 በእዚህ ፅሁፍ ስር የሚከተሉት ሃሳቦች በአጭር ንዑስ ርዕሶች ስር ተነስተዋል።እነርሱም : -
  • ከህወሓት በኃላ ኢትዮጵያን የመቅረፅ አቅም ያላቸው ሶስቱ ኃይሎች እነማን ናቸው?
  • የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ሃገራዊ  ወይንም ብሔራዊ ጥያቄ ላይ ያተኮሩ አድርጎ መነሳት ይገባል
  • በኦሮምያ ያለው እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉት ሁለቱ  አስተሳሰቦች 
  • “ኧረ አምሳለ” በገጣሚት ምልእቲ ኪሮስ (ቪድዮ)

የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት ሩብ ክፍለዘመን በህወሓት የጎሳ ፖለቲካ ተጭኖባት፣ ህዝቧ እርስ በርሱ እንዲከፋፈል በሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን ሳይቀር በርካታ ደባዎች ተሰርቶበታል።ይህ ሁሉ ደባ ተሰርቶበትም ግን ህዝቡ ዛሬም ባገኘው መንገድ ሁሉ ለነፃነቱ እየተዋደቀ ነው።

ለነፃነቱ የሚዋደቀው በተለይ አዲሱ ትውልድ እጅግ አስደማሚ እና አስደናቂ ሂደቶችን እየሄደ በብዙ የምጣኔ ሀብት ድቀት፣የመገደል እና የመታሰር ፈተና ውስጥ እያለፈ ዛሬም ድምፁን ከፍ አድርጎ ለነፃነቱ እየታገለ መሆኑን በተግባር አሳይቷል።ለእዚህም በኦሮምያ፣ዐማራ እና ሌሎች ቦታዎች የታዩት የትግል ሂደቶች ሁሉ መጥቀስ ይቻላል።ሆኖም ግን እስካሁን የሚደረጉት ትግሎች ሁሉ በህወሓት ከስልጣን መውረድ ላይ ቢስማማም ሃገራዊ የጋራ አጀንዳ ላይ አተኩሮ የሚደረጉ ትግሎች እየተቀነቀኑ ያሉት በሁሉም ዘንድ አይደለም።

በኦሮምያ ያለው እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉት ሁለቱ  አስተሳሰቦች


በኦሮምያ ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ በሁለት ክፍል ከፍሎ መመልከት ይቻላል።እነርሱም : -

 ሀ) በኢትዮጵያዊነት እና የግዛት አንድነት ጉዳይ ጥብቅ አመለካከት ያላቸው

በእዚህ ክፍል ያለው አብዛኛው የኦሮም ሕዝብ ከደመነፍሱ እስከ ተግባራዊ ሃሳቡ ድረስ በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ ጥልቅ ስሜት ህዝቡ ውስጥ አለ።አንዳንዶች ባለፈው 26 ዓመታት በኦሮምያ ትውልዱ ተቀይሯል ብለው ይናገራሉ።ይህ ግን ከሕብረተሰብ አቀያየር ሂደት በራቀ መልክ የሚደመድሙት የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። ለእዚህ ማስረጃ የሚሆኑ ነጥቦች ማንሳት ይቻላል።

የመጀመርያው ማስረጃ የኦሮምያ ክልል በእራሱ የያዘው የህብረተሰብ ክፍል የቅርብ ታሪክ መመልከት በቂ ነው።በኦሮምያ ክልል ውስጥ አሁን በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙት ወጣቶች የተቀረፁት እና እየሰሙ ያደጉት ለኢትዮጵያ አንድነት ለአመታት ሲፋለሙ የነበሩ የቀድሞ ጦር ሰራዊት አባላት (አሁን በእርግና እድሜ የሚገኙ) ጭምር ነው። ኦሮምያ በቀደሙት የኢትዮጵያ ሰራዊት ከከፍተኛ ማዕረግ እስከ ተራ ወታደር ትልቅ ተሳትፎ ነበራት።በእያንዳንዱ የኦሮምያ መንደር ውስጥ የቀድሞ ሰራዊት አባላት፣በቀድሞ ስርዓቶች በከፍተኛ የኑሮ ደረጃ የነበሩ እና በዘመነ ህወሓት ወቅት ከብሄራዊ ጥቅሞች ሁሉ የተገፉ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚነግሩት ህወሓት ያመጣው ድህነት እንጂ ኢትዮጵያ ያመጣችው ድህነት አይደለም በማለት ነው።ለእዚህ አብነት የሚሆነን የአምቦ እና የቢሸፍቱ ከተሞች ናቸው።እነኝህ ከተሞች በርካታ የጦር ሰራዊት መኮንኖች መኖርያ ከተሞች ናቸው።ልጆቻቸው ዛሬ ደርሰው የኢትዮጵያ አንድነት ጠላቶች ናቸው ብሎ የሚያስብ ነገሮችን ጠለቅ አድርጎ ማየት የተሳነው ነው።

በሁለተኛ ደረጃ ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት እና የግዛት አንድነት በኦሮምያ ውስጥ ለመኖሩ ማሳያው ህዝቡ ከቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ያለው ጠንካራ ማሕበራዊ ትስስር  ነው።ማኅበራዊ ትስስር ውስጥ አንዱ ሃይማኖት ነው።በኦሮምያ ከአስር ሚልዮን የሚበልጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ መሆኑ መጥቀሱ በእራሱ አንዱ የትስስር ማሳያ ነው።ይህ ትስስር ከገበያ እስከ ቤተሰባዊ ትልቅ ታሪካዊ ትስስር ያለው ነው።እነኝህ ሁለት የትስስር አይነቶች ለመግለጥ ያስፈለገው በቀላሉ ነገሮች ለማስረዳት እንጂ ወደ ጠለቀው የኢትዮጵያዊነት ትስስር ስንገባ በርካታ ታሪካዊ እና የማይበጠስ የደም ትስስር ያለው ሕዝብ ነው።ኢትዮጵያን ከኦሮሞ ሕዝብ ውጭ ማሰብ አይቻልም።ስለሆነም ለኢትዮያዊነት ለመመስከር ከኦሮሞ ማኅበረሰብ በላይ ሌላ ሊመጣ አይችልም።አቶ ለማ መገርሳ የኦሮምያ የወቅቱ ፕሬዝዳንትም የመሰከሩት ይህንኑ ነው።አሁን የምናምነው በሚናገሩት ነው።የተናገሩትም '' የኢትዮጵያ አንድነት ከአህያ ቆዳ የተሰራ አይደለም ጅብ ስጮህ የሚፈራርስ።ኢትዮጵያን የገነቡት አባቶቻችን ናቸው" ነው ያሉት።ይህ ማለት በእዚህ በኩል የሚቀርበው ስጋት በጣም የተጋነነ እና ሚዛኑ የሚደፋ አይደለም ለማለት ነው።ይህ ማለት ግን በኦሮምያ ስም የሚነግዱ አልተፈጠሩም ማለት አይደለም።

 ለ) በኢትዮጵያዊነት እና አንድነት ጉዳይ ለዘብተኛ አመለካከት ያላቸው ቡድኖች

በኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ለዘብተኛ እና ቅድምያ ለክልሉ ብቻ በመስጠት የፖለቲካ ግብ መምታት ይቻላል የሚለው አስተተሳሰብ በውስጡ ሁለት አይነት ኃይሎች በአንድነት ተባብረውበት ይታያል።እነርሱም የኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ከወያኔ በኃላ የሚነሳ ጉዳይ ነው ቅድምያ ወያኔ መውረድ ላይ እናተኩር የሚሉ እና ወያኔ ከወረደም በኃላ የኢትዮጵያ አንድነት ብሎ ነገር አይታሰብም "ሰባብረን እንሰራታለን" ባዮች ናቸው።ሆኖም ግን ከቁጥር አንፃር በኢትዮጵያ አንደነት ላይ አሉታዊ ስሜት ይዘው የሚሄዱት ከቁጥር አንፃርም ሆነ ከህዝብ ድጋፍ አንፃር ቁጥራቸው ብዙ አይደለም።ሆኖም ግን በአደረጃጀት እና ድብቅ አጀንዳቸውን አቆይተው የህዝቡን ስሜት አይተው ለመንቀሳቀስ ያደፈጡ ናቸው ማለት ይቻላል። ይህንን እውነታ ከህዝብ ደብቆ መሄድ ፈፅሞ አይቻልም።እውነታው አለ ሆኖም ግን የህዝብ ሃሳብ አሉታዊውን አስተሳሰብ እንደሚሞርደው ማመን ይቻላል።

የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ሃገራዊ  ወይንም ብሔራዊ ጥያቄ ላይ ያተኮሩ አድርጎ መነሳት ይገባል


አሁን ቀዳሚው ጉዳይ የነፃነት ጥያቄ ነው።ኢትዮጵያ ከአሁን በኃላ ከነፃነት ውጭ አንድም ቀን መቆየት አትችልም።ሕዝብ ከበቂ በላይ ታግሷል።ከበቂ በላይ ተገድሏል፣ታስሯል፣ክብሩ በባዕዳን ተዋርዷል፣ሀብት ንብረቱ ተዘርፏል፣የበይ ተመልካች ሆኗል።ከእዚህ በኃላ በእዚህ አይነት ሁኔታ ወደፊት የመቀጠል አቅም ያለው የለም።የነፃነት ቀን ነገ አይደለም።ዛሬ! ነው።


በነፃነት ጥያቄ ሂደቱ ውስጥ ሁለት አበይት ነጥቦች አስፈላጊ ናቸው።ከላይ የተጠቀሱት በተለይ በኦሮምያ ክልል ውስጥ ከሚታየው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አንፃር መታየት የሚገባቸው ሁለት ነጥቦች ጥያቄዎችን ብሔራዊ አጀንዳ ማድረግ እና የፖለቲካ ምህዳሩን ክልላዊ ሳይሆን ብሔራዊ ወይንም ሀገር አቀፋዊ ማድረግ የሚሉት ናቸው። ከቅርብ አመታት ወዲህ ባለው ትግል ውስጥ ቀዳሚ አጀንዳዎችን ብሔራዊ ወይንም ሃገራዊ አድርጎ አለማቅረብ  አርዝሞታል።ለሀገራዊ አጀንዳዎች ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከዳር የመነሳት አቅማቸው ቀላል አይደለም።ከላይ ከተጠቀሱት ለዘብተኛ አመለካከት ያላቸው ጥያቄዎችን ከኦሮምያ አንፃር ብቻ በመቃኘት እና በማጥበብ ሌላው ኢትዮጵያጵያዊ በርቀት እንዲመለከት እና ሌላ መስመር እንዲከተል ያደረጉበት ሂደት ያስከፈለው የሰው እና የጊዜ ሀብት ቀላል አይደለም። ከአሁን በኃላ ይህንን ስህተት ማረም ተገቢ ነው። በእርግጥ ሁለት እውነታዎችን መካድ አይቻልም።አንዱ በኦሮምያ በኩል በተለያየ አስተሳሰብ ውስጥም ቢሆኑ በተቀናጀ መልክ መዋቅር በመፍጠር እና ቄሮ በሚል ግንኙነት የተፈጠረው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ለሰላማዊ ትግል አንዱ ምሳሌ ሆኗል።ይህ አንዱ የኢትዮጵያ አቅም ነው።

በሌላ በኩል በዐማራ ክልል ውስጥ ከፍተኛ የትጥቅ ትግል ለማካሄድ የሚችል የታጠቀ እና በበረሃ እና በከተማ አድፍጦ ያለ ኃይል አለ።ይህ ኃይል ከአቅም አንፃር እስካሁን በሰሜን ጎንደር እና በሱዳን ድንበር እንዲሁም በኤርትራ ሳይቀር ይገኛል።ይህ ኃይል ምንም ቢዘገይ በኢትዮጵያ መጪ የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ የሚናቅ አይደለም።እንደ ኢትዮጵያ ላለ ስልጣን በጠብ መንጃ ብቻ ለሚፈራረቅባት ሀገር እና እንደ ህወሓት በኃይል ብቻ ለሚያምን ቡድን በዐማራ ክልል ያለው ሕዝብ ባብዛኛው ጦረኛ የሆነ ባህሉ በእራሱ በአግባቡ ከተያዘ በጎ ነገር ይዞ መምጣት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በበጎ ለማይመለከቱ ሁሉ አንዱ እና አይነተኛ ኃይል ነው። ለኢትዮጵያ ሰራዊትም ከደጀን እስከ ግንባር አጋዥ ነው።

ከህወሓት በኃላ ኢትዮጵያን የመቅረፅ አቅም ያላቸው ሶስቱ ኃይሎች እነማን ናቸው?


ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ኃይሎች ማለትም በኦሮምያ ያለው የቄሮ እንቅስቃሴ እና በዐማራ ያለው የፋኖ ታጣቂ ኃይሎች በአግባቡ በበሳል የፖለቲካ አመራር መመራር አለባቸው።ይህ ነው እንግዲህ ኢትዮጵያን ወደ ቀጣይ ትውልድ በክብር የማስተላለፉ ፈታኝ ሥራ የሚሆነው።ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ብለን ብንጠይቅ ከኢትዮጵያ አንፃር የሶስት  ወሳኝ አካላት መናበብ እና ቆርጦ መነሳት ያስፈልጋል።እነርሱም በሳል የፖለቲካ፣ምጣኔ ሀብት እና ማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና በሳል የሚድያ ሰዎች ናቸው።

እነኝህ ሶስቱ የኢትዮጵያን ሕዝብ መጪ አቅጣጫ የመቅረፅ አቅም አላቸው። የፖለቲካ፣ምጣኔ ሀብት እና ማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያዎች የፖለቲካ ድርጅቶችን ወደ ኅብረት የማምጣት እና የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት በጠበቀ መልኩ የፖለቲካ መስመሩን የመቅረፅ ሚና ይኖራቸዋል።የሃይማኖት መሪዎች በቅድምያ የጎደፈ መልካቸውን በመልካም መቀየር እና ከሕዝቡ ጋር መሆናቸውን ማሳየት በመቀጠልም የህዝቡን እርስ በርስ ትስስር ማጥበቅ ይጠበቅባቸዋል።የሚድያ ሰዎች ደግሞ ሁሉም አካላት ከህዝብ ያፈነገጠ እና ኢትዮጵያን የሚጎዳ ተግባራት ሲሰሩ በፍጥነት ለሕዝብ ትክክለኛውን መረጃ መስጠት እና የሕዝብ አመለካከት ኢትዮጵያዊ በሆነ እና የእርስ በርስ ፍቅሩን በሚያጠነክር መስመር ላይ እንዲሄድ ፈር ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል።

ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ያለበት ደረጃ ለነፃነት ፍሬ ሊያሳይ በሚችል መስመር ላይ ነው።ለነፃነት ቀጠሮ ከሰጠ ግን የተደገሰለትን የመከፋፈል መርዝ ለመጠጣት የመዘጋጀት ያህል አደገኛ ነው።ሕዝብ ከህወሓት አገዛዝ መውጣት አለበት።በመቀጠል እራሱን የቻለ ሌላ ምዕራፍ ይኖራል።ይህ ምዕራፍ ግን በህወሓት ውስጥ በመኖር ከሚደርስበት አደጋ ጋር የሚመጣጠን ፈፅሞ ሊሆን አይችልም።በእርግጥ ከላይ የተጠቀሱት የምሁራን፣የሃይማኖት መሪዎች እና የሚድያ ሰዎች ትጋት እጅግ  እጅግ አስፈላጊ ነው።

“ኧረ አምሳለ” ግጥም በገጣሚት ምልእቲ ኪሮስ (ቪድዮ)



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...