ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, June 16, 2012

የአምባገነንነት ዲግሪው ስንት ነው?

ይህንን ጽሁፍ ስጽፍ በኖርዌይ ቲቪ(NRK 1)  ኦስሎ ''ቀዩ ቤት'' የኖቤል ሽልማት መቀበያ አዳራሽ በቀጥታ የሚተላለፍ ፕሮግራም የበርማዋን ዲሞክራሲ ታጋይ አዉንግ ሳንሱኪ ሃያ አመታት በፊት ተሸልማ የነበረውን የኖቤል ሽልማት ሳቢያ (እስር ቤት በመክረሟ በወቅቱ ሽልማቱን ለመውሰድም ሆነ ንግ ግር ለማድረግ ባለመቻልዋ) ንግግር ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነበረች።
አውንግ ሳንሱኪ :-
 • ሰኔ 19/1945 እኤአ በርማ ተወለዱ፤
 •  1990 ዓም እኤአ በተደረገው ብሔራዊ ምርጫ በሊቀመንበርነት በሚመሩት ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ሊግ ሰማንያ ዘጠኝ ከመቶ በማሸነፍ ተመረጡ።ነገር ግን አምባገነኑ የበርማ መንግስት ቁም እስር ፈርዶባቸው ነበር እና የዲሞክራሲው ጭላንጭል ቶሎ ከሰመ፤
 • ሀምሌ 20 ፣1989 እስከ ህዳር 13 ፣2010 ሃያ አንድ አመታት ያህል በእስር ቆዩ፤
 • በእስር ላይ ሳሉ  በ1991 ዓም  ኖቤል ሽልማት፣በ1992ዓም   ህንድ ጃዋላ ኔህሩ ዓለም አቀፍ ሽልማት እና በ2007 ዓም  ካናዳ ክብር ዜግነት አግኝተዋል፤
ዛሬ ሰኔ 16/2012 እኤአ የዛሬ 20 ዓመት ማድረግ የነበረባቸውን ንግግር እያደረጉ ነው። አውንግ ሳንሱኪ አምባገነንነት ሰለባ ተምሳሌት ናቸው። አንድ ወቅት ላይ ዳኛ ቡርቱካን ሜዴቅሳ ''በትግል ህይወትዋ ሁሉ ምሳሌ የሚሆንሽ ማነው? ''ስትባል አውንግ ሳንሱኪ ማለትዋን እና በእያንዳንዱ የፈተና ቀናት የምታስታውሰው አውንግ ሳንሱኪ መሆኑን ፤ በእርሷ ላይ የደረሰውን ስታስብ ብርታት እንደምታገኝ መናገሯን አስታውሳለሁ።

  ብርቱካን ከ እስር እንደተፈታች ለ ሮይተር ጋዜጠኛ በ መኪና መስታወት ስር ስትናገር


የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ስለ ዳኛ እና ዲሞክራሲ ታጋይ ብርቱካን ለማውሳት ሳይሆን አምባገነንነትን እና አደጋውን ምን ያህል ከገመትነው በላይ በደቀነው ችግር ላይ ትንሽ ለመሰንዘር ነው።

አምባገነንነት ምንድን ነው?
ዊኪፒድያ  አምባገነንነትን ''የ አንድ ሰው ወይንም የተወሰኑ ቡድሮች ፈላጭ ቆራጭ አስተዳደር፤ በዘመናዊ ትርጉም ደግሞ ህገመንግስት፣ለ ማህበረሰባዊ ህጎች ሁሉ የማይገዛ የመንግስት አስተዳደር''  ነው ይላል::(http://en.wikipedia.org/wiki/Dictatorship)
አምባገነንነት አስገራሚ ባህሪው   የደነገጋቸውን ህጎች ተግባራዊ የሚያደርጋቸው እራሱ የተመቹት ጊዜ ብቻ መሆኑ ነው። ኢትዮዽያ ስለ አምባገነንነት አደጋው እና ሃገር ህልውና ላይ ያዘለውን የጥፋት መዓት የምንረዳበት ደረጃ ያንስብኛል። እዚህም ይመስለኛል ሰዎች ''የባሰ አታምጣ'' የሚል ብሂል እየደጋገሙ ነገን  ማየት በተሳነ አዕምሮ መኖርን የሚመርጡት። የበርማዋ አውንግ ሳንሱኪም ሆኑ ዳኛ ብርቱካን ሜደቅሳ የባሰ አታምጣ ብለው በሙያቸው እያገለገሉ ሲጠሩዋቸው'' አቤት'' ሲልኩዋቸው ''ወዴት'' እያሉ መኖርን ሳያውቁበት ቀርተው አይደለም።የነገው አደጋ ፍንትው ብሎ ቢታያቸው እንጂ።
የአምባገነኖች የሃገር አመራር ዘይቤ አንድ እርምጃ ወደፊት ሶስት እርምጃ ወደ ኋላ
 • በ አምባገነን ስርዓት ስር የሚተዳደር ሃገር መንገድ ይሰራ ይሆናል ነገር ግን በመንገዱ ላይ የሚሔደው በፍርሃት የተሸበበ እና የተከዘ ህዝብ ነው፤
 • በ አምባገነን ስርዓት ስር የሚተዳደር ሃገር ዩንቨርሲቲ ይከፍት ይሆናል:: ነገር ግን ስለምን መመራመር፤ ስለምን ማውራት፤ወዘተ እንዳለባቸው የሚነገራቸው ብቻ ሳይሆኑ የቱን ማንበብ ፤የቱን አለማንበብ፤ እንደሚገባቸው የተወሰነላቸው ምሁራን የሞሉበት ተቋም ይሆናል፤
 • በ አምባገነን ስርዓት ስር የሚተዳደር ሃገር የተረጋጋ፣ሁሉ ነገር አልጋ በ አልጋ የሆነ ህዝቡ ከዝምታው የተነሳ ሃገሩ ሰላማዊ ነው ሊባል ይችል ይሆናል። ሰላም የሆነው ጎዳናው ነው እንጂ የህዝቡ አዕምሮ አይደለም። ሰላምም ሆነ ጦርነት  የሚፈጠረው  በሰው አዕምሮ ነው  የሚባለው ለእዚህ ነው።ምንም ያክል ልማት ቢሰራ ነገን ዋስትና ያልሰጠ ልማት እንደኖረ መቁጠር የሚከብደው ለእዚህ ነው። ለእዚህም ምሳሌ የምትሆነን ሊብያ ነች። ሊብያ ከ 1980 ዎቹ ማለቅያ ጀምሮ በ አለም ላይ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ከፍተኛ ከሆኑት ሃገሮች ተርታ ትመደባለች።በ እዚህም መሰረት ከጣልያን፣ሲንጋፖር እና ደቡብ ኮርያ ጋር በተስተካከለ እና አንዳንድ ጊዜም በተሻለ ሁኔታ መሆንዋ ሲተረክላት ነበር። (http://en.wikipedia.org/wiki/Libya#Economy) የ ጋዳፊ አምባገነንነት ግን የ ህዝቡ በ ኑሮ መደላደሉ ሊያዘናጋው አልቻለም። ነጻነት፣ዲሞክራሲ፣ እንደሰው የማሰብ መብት ከሁሉ ልቀው ተነሱ። ለእዚህ ነው ዛሬም ስለ ልማት ብቻ በማውራት ሃገር ከ አምባገነንነት ሳትላቀቅ ታድጋለች ብለው ለሚናገሩ ሁሉ ማስረጃችን ከ ጓሮ አለ እና ለ አስተማማኝ እድገት ዲሞክራሲ፣የ ህግ የበላይነት እና ከ ዘረኝነት የጸዳ ፖሊሲ እና ስርዓት መቅደም አለባቸው የሚባለው።
 ለመሆኑ የ አምባገነንነት ዲግሪው ስንት ነው?
 •  የ ሰማንያ ሚልዮን ህዝብ ይወክላል ብለው ባቆሙት ምክር ቤት ውስጥ  99.6% ፐርሰንት አሸነፍኩ ማለት?
 • የትኛውም መንግስት ከ አንድ ሺህ አመት በላይ ያልደፈሩትን የዋልድባን ገዳም ደፍሮ ስኳር ፋብሪካ መገንባት እና የገዳሙን አካባቢ ወደ ከተማነት መቀየር?
 • የሰለጠነው ዓለም በነጻ የፈቀደውን የ ኢንተርኔት አገልግሎት ስካይፒን ጨምሮ ማገድ?
 • በጋዜጣም፣በኢንተርኔትም፣በቀልድም (አቤ ቶክቻውን ቀልዶች ያስቡ) አትውቀሱኝ እኔ ትክክል ነኝ ማለት?
 • በንግግር በጽሁፍ የተቃወሙትን አሸባሪ ብሎ ወደ እስር ቤት መላክ?
 • ቤልጅየምን ያህል መሬት ለ ውጭ ሃገር ባለ ሃብት ይሸጣል ማለት?
 • መምህራን የደሞዝ ጭማሪ ሲጠይቁ ድሮም ችሎታ የሌላቸው ነበሩ ማለት?
ዛሬ ሃገራችን የገጠማት ችግር አሳሳቢ የሚያደርገው የ አምባገነንነት አሰራር መስፈን ብቻ አይደለም:: የ አምባገነንነት ዲግሪው የጋለ መሆን ነው እንጂ። መቸም ይህን አባባል የሚያስተባብል ይኖራል ለማለት ይከብደኛል ምክንያቱም ይህንን ስዬ አብርሃምም፣አረጋዊ በርሔም፣ገብሩ አስራትም፣ፕሬዝዳንት ነጋሶም ያረጋገጡት ሃቅ ነው።ምናልባት የ አምባገነንነቱን ዲግሪ አለኩልንም ሌላ ጥያቄ ሊሆን ይችላል። ግን ግን ከ ስዬ አብርሃም በላይ ኢህአዲግ ነኝ ማለት ትንሽ ይከብዳል።እርሱ ቢያንስ የ አምባገነንነትን አደጋ  ነግሮናል።ዳኛ ብርቱካንም ስዬ አብርሃን በዳኛነቷ ነጻ ለቃ  ተፈትናበታለች። አውንግ ሳንሱኪ ደግሞ የ አምባገነኖችን ሰው በላነት  ለዓለም ህዝብ አሳስባለች። ጆሮ ያለው ይስማ!

ለመሆኑ የ አምባገነንነት ዲግሪው ስንት ነው?

በዛሬው የ ኦስሎ የ አውንግ ሳንሱኪ አቀባበል እና ንግግር እነሆ:-


ዛሬ 16/6/2012 ዓ.ም .እኤአ  በኦስሎ የ አውንግ ሳንሱኪ አቀባበል እና ንግግር

ጌታቸው በቀለ
ኦስሎ

2 comments:

Anonymous said...

Thank you thank you thank you for updating us!

S.K said...

Tiru akerareb new gin ye Birtukanin nigigir bitichemirbet tiru neber. But it is short and fruitfull.thank you Gech.