ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, August 6, 2023

መሬት ላይ ያለው እውነታ፣ መከላከያ ፋኖ ላይ መተኮስ አይፈልግም።ፋኖም መከላከያ ላይ መተኮስ አይፈልግም።መንግስት ጉዳዩን በሰላም በመፍታት ኢትዮጵያን ከእርስበርስ ጦርነት የማዳን ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት።

=========
ጉዳያችን ምጥን
=========

ጦርነት ውስጣዊ ቁጣ እና ፍትሃዊ የሆነ የመዋጋት ስሜት ይፈልጋል። ከእዚህ በፊትም ለመግለጽ እንደሞከርኩት በአማራ ክልል የተነሳው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ድንገት ደራሽ አይደለም።የእዚህ ዓይነት የትጥቅ ትግል መነሳት በማናቸውም ጊዜ ሊነሳ እንደሚችል ጉዳያችን ላይ የዛሬ 5 ዓመት ከእነምክንያቱ ተጽፎ ነበር። ሊንኩን እዚህ ላይ ተጭነው መመልከት ይችላሉ።

አሁን መሬት ላይ ያለው እውነታ

አሁን መሬት ላይ ያለው ሁኔታ የሚያሳየው መከላከይ ፋኖ ላይ መተኮስ አይፈልግም። ፋኖም መከላከያ ላይ መተኮስ አይፈልግም። ለእዚህ ደግሞ ምክንያቱ ግልጽ ነው። መከላከያ የተዋቀረው በኢትዮጵያዊ ስሜት ነው። ፋኖንም በሀገር አንድነት ትግል ላይ ከህወሃት ጋር ሲያውቀው ኢትዮጵያን ሲያከብር እንጂ የማፍረስ ስሜት አላየበትም። ስለሆነም ከውስጥ የወጣ የጥላቻ ስሜት አብቅሎ አንዱ አንዱ ላይ ለመተኮስ ፈጽሞ የስሜት ጥላቻው በእዚያ ደረጃ የናረ ሁኔታ የለም።ይህ እንደ ሀገር ሲታይ ይህንን ጦርነት የሰው ህይወት ሳይጠፋ፣ንብረት ሳይወድም ለማስቆም የሚቻልበት እድል ትልቅ ነው ማለት ነው።

መንግስት ጉዳዩን በሰላም በመፍታት ኢትዮጵያን ከእርስበርስ ጦርነት የማዳን ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት 

ይህ የእርስበርስ ጦርነት ነው። ውጤቱ ደግሞ በሁሉም ወገን ያለው የኢትዮጵያውያን ሞት የሚያመራው ኢትዮጵያን ይዞ ወደ ሌላ የመከራ ማጥ የሚያመራ ነው። እስካሁን ከደረሰው ጥፋት ሌላ ጥፋት ሳይከተል፣እዚህ ላይ ለማቆም በመጀመርያ ማናቸውንም ግጭት አስቁሞ ወደ መነጋገር መምጣት ያስፈልጋል። ከእዚህ ውጪ መከላከያ በአማራ ክልል ከተሞችን በመቆጣጠሩ ብቻ ድል ብሎ ሊቆጥር አይችልም።አሁንም መከላከያ የኢትዮጵያ ሃብት ነው።መከላከያ ኢትዮጵያን በዘመናዊ ጦርነት ለመከላከል እንጂ ከራሱ ወገን ታጣቂ ጋር ጉልበቱን አድክሞ ሀገርን ለውጭ ወረራ ማጋለጥ ሀላፊነት የሚሰማው ውሳኔ አይደለም። 

ይህ በእንዲህ እያለ በደብረማርቆስ ፖሊስ ኮሌጅ ውጪ እስካሁን ይህ ነው የሚባል የዝርፍያ ሁኔታ በሰሞኑ የአማራ ክልል እየተሰማ አይደለም። ለእዚህ ደግሞ የመረጃ እጥረት ካልሆነ በቀር እየተሰማ ያለው የታጣቂው ኃይል በተቻለ መጠን ለመንግስት እና የግለሰብ ንብረት ጥበቃ ለማድረግ እየሞከረ መሆኑ እንደሆነ እየተሰማ ነው። የደብረማርቆስ ፖሊስ ኮሌጅ ዘረፋ በተመለከተ የአንከር ሚድያ ላይ ቀርቦ የተናገረ አንድ ታጣቂ እንደገለጸው በደብረማርቆስ ፖሊስ ኮሌጅ የደረሰውን እንደሰማ እና ከዝግጅት ማነስ አንዳንድ ሌቦች አይኖሩም ማለት አይደለም በማለት ገልጾታል። ዝርፍያን እና ጸጥታ በተመለከተ የፋኖ ታጣቂዎች በፈለጉት መጠን ጸጥታ ለመጠበቅ ቢሞክሩም በቀጣይ ግን ፈተናዎች አይገጥሙም ማለት አይቻልም። እስካሁን ታጣቂዎች በገቡባቸው አካባቢዎች አካባቢዎች የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጡባቸው አካባቢዎች ቢኖርም የቀጥታ ስልክ ግን በአንዳንድ ቦታዎች ቢያስቸግሩም፣የእዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ዛሬ እንዳረጋገጠውም በባህርዳር የቀጥታ ስልክ፣ውሃ እና መብራት አሁንም አገልግሎት አለ።

አሁን ላለው ወቅታዊ ሁኔታ ብዙ ጭቅጭቅ አያስፈልግም።የፋኖ ታጣቂ እጃቸው የገቡ የመከላከያ አባላት ላይ የደረሰውን ሞት አይደለም፣ መቁሰል እያሳዘናቸው እንደሆነ ዛሬ ዘሐበሻ በቪድዮ አስደግፎ ባቀረበው የአንድ የፋኖ አባል ቃለመጠይቅ አሳይቷል። በሌላ በኩል የአንከር ሚድያ ያነጋገረው የመከላከያ አባልም በተመሳሳይ የፋኖ ታጣቂዎች ለኢትዮጵያ ሲደሙ እንደሚያውቃቸው ገልጾ ፈጽሞ የመውጋት ፍላጎት እንደሌለው ገልጿል። አሁን ጥያቄው አንድ ነው።ተጨማሪ የሰው ህይወት ሳይጠፋ፣መከላከያንም ከህዝብ ጋር ደም ሳይቃባ እና ኢትዮጵያ ወደ የባሰ ግጭት ሳትገፋ፣ መንግስት ጉዳዩን በሰላም በመፍታት ኢትዮጵያን ከእርስበርስ ጦርነት የማዳን ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት።ጉዳዩን በኃይል ለመፍታት መሞከር በምንም መልኩ ኢትዮጵያን አይጠቅማትም።ከህወሓት እና ሸኔ ጋር ተቀምጦ የተነጋገረ መንግስት በአማራ ክልል ከተነሳው ታጣቂና ፋኖ ጋር ለመወያየት የሚያግደው ጉዳይ ምንድን ነው? ከእዚህ ጽሑፍ በፊት እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማወጁ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሃላፊነት በተሰማው መንገድ በአማራ ክልል ለተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ መተግበር የሚገቧቸው ሦስት ተግባራት በሚሉት ሃሳብ ለማቅረብ ተሞክሯል።ይህንን ሊንክ በመጫን ማንበብ ይቻላል።

ለማጠቃለል አሁን ያለው ሁኔታ የሆነ ተአምር ይዞ የሚመጣ መስሎት በስሜት ውስጥ የገባውም ሆነ ብቻ እነእገሌ ይወገዱ እንጂ የሚሉ ሁሉም ጥቅሉን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ከእዚህ በፊት ሃገሪቱ ያለፈችበትን ተመሳሳይ የስሜታዊነት መንገድ ያልተገነዘቡ ኢትዮጵያ በምን ያህል ደረጃ በአካባቢዋ እና በውስጧ ሊያጠፏት የተጠመዱ የፈንጅ ዓይነቶች ካለማወቅ የሚመነጭ ነው።የውስጥ ቁርሾ ይበርዳል።በውስጥ ቁርሾ መከላከያን ማድከም ግን የማይሽር ጠባሳ ለሀገር ጥሎ ይሄዳል። ስለሆነም መከላከያን ማዳን እና አለማዳከም ከፋኖም ሆነ ከመንግስት የሚጠበቅ እኩል ሀገራዊ እና ታሪካዊ ሃላፊነት ነው። ሁለቱም ይህንን ታሪካዊ ሃላፊነት ሊወጡ የሚችሉበት መንገድ ደግሞ ቁጭ ብሎ በመነጋገር ነው።

==================///============






No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...