ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, April 20, 2024

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።


በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል
ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ

  • ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል 
  • ''ስኩዌር ዋን'' ህወሓት ወደ ቀደመ ፕሮፓጋንዳውና የጦርነት ገንዘብ ማሰባሰቡ ተመልሷል።
  • ህወሓት ለአራተኛ ጊዜ ''አደገኛ ወጥ እረግጧል'' 

========
ጉዳያችን
========

''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል 

ከተፈረመ ዓመት ያለፈው የፕሪቶርያ ውል ህወሓት እንደፈለገ እየተረጎመ እና እያብጠለጠለ፣ መንግስት አንድ ጊዜ የህወሓትን ትጥቅ አስፈታሁ፣ዛሬ ይህን ያህል ከባድ መሳርያ ተረከብኩ እያለ በቴሌቭዥን እያሳየ፣ ቆየት ብሎ ደግሞ ህወሓት ትጥቅ አልፈታሁም እያለ ሲደነፋ ስንሰማ ውሉ ዓመት አልፎት ሌላ  ዓመቱን ተያይዞታል።

ባለፈው ዓመት ውስጥ ህወሓት በሚልዮን የሚቆጠር የትግራይ ሕዝብ አስፈጅቶ፣ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ኮሚሽን ባወጣው አዲስ ጥናት ደግሞ ከአንድ ሚልዮን በላይ የትግራይ ተወላጅ ልጆች በእዚች ሰዓትም ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸው ታውቋል። ይህ በእንዲህ እያለ ከፕሪቶርያው ውል ወዲህ የትግራይ ክልል በቢልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከማዕከላዊ መንግስት ማግኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የትግራይ ተወላጆችን በቢሯቸው አዳራሽ ሲያነጋግሩ ሲነግሩን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ከጎናቸው አስቀምጠው ምስክር ይዘው ነበር። ይህ ገንዘብ ግን ለትግራይ ህዝብ አንድ ሚልዮን ልጆቹን ወደ ትምሕርት ቤት ለመስደድም ሆነ ከደረሰበት ጉስቁልና ለማገገም አልረዳውም። ይልቁንም ህወሓት ከህዝቡ ጉሮሮ የነጠቀውን ምግብ ለትታጣቂው እያበላ ሰሜን ወሎን መወረሩን የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ መገናኛዎች ከነገሩን ቀናት ተቆጠሩ።

እንደ ቢቢሲ አማርኛ የዛሬ ቅዳሜ ሚያዝያ 12፣2016 ዓም (እኤአ ሚያዝያ 20፣2024 ዓም) ዘገባ  በወረራው ሳብያ አስር ሺዎች ተፈናቅለዋል። ዘገባው እንዲህ ይነበባል ፡ 

''ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ከትግራይ ኃይሎች በተደረጉ የተኩስ ልውውጦች አለመረጋጋት ውስጥ የገቡት ስድስቱ የራያ ወረዳ እና ከተማ አስተዳደሮች፤ በአማራ ክልል መንግሥት ስር በተመሠረቱላቸው መዋቅሮች ስር መተዳደር ማቆማቸውን አራት የወረዳዎቹ አመራሮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የትግራይ ኃይሎች በተለይም የገጠር ቀበሌዎችን መቆጣጠራቸውን የዛታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሳሁን መኮንን እና የወፍላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍሰሐ ሞላ ገልፀዋል። ይህንን ተከትሎም የሁለቱ ወረዳዎች አመራሮች እና ነዋሪዎች ከማክሰኞ ዕለት ጀምሮ ወደ አጎራባች አካባቢዎች መሸሻቸውን ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አምስት የኮረም እና አላማጣ ከተማዎች ነዋሪዎች በሰሜን ወሎ ዞን በሚገኙት ቆቦ እና ወልዲያ ከተሞች እንዲሁም ሰቆጣ ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስር በሚገኙት ሰቆጣ ከተማ እና ሐሙሲት ቀበሌ መጠለላቸውን ገልጸዋል።

ተፈናቃዮቹ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከእነዚህ አካባቢዎች መጠለላቸውን ተናግረው፤ የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ በበኩላቸው 30 ሺህ ገደማ የራያ አካባቢ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አስረድተዋል።'' የቢቢሲ ዘገባ መጨረሻ።

''ስኩዌር ዋን'' ህወሓት ወደ ቀደመ ፕሮፓጋንዳውና የጦርነት ገንዘብ ማሰባሰቡ ተመልሷል።

የህወሓትን ወረራ አስመልክቶ የውጭ ሚድያዎች በለሆሳስ እየተናገሩ ነው።በለሆሳስ ያልኩበት ምክንያት የህወሓት ውል ጥሶ ብቻ ሳይሆን ከአንድሚልዮን ህዝብ እልቂት በኋላም መልሶ ለስልጣኑ ወደ ጦርነት አረንቋ ለመግባት የሚያደርገውን መላላጥ ለመውቀስ ሲሽኮረመሙ ብቻ ሳይሆን በሚገባ እና በሚወቅስ መልክ የጻፈ አላጋጠመኝም። ይህ የደንባራው እና የራሱን ጥቅም ብቻ ከሚያነፈንፈው የባዕዳን የሚድያ ፖሊሲ የሚመነጭ ምግባር የለሽ የአለቆቻቸውን አስተያየት እና አቅጣጫ ከመጠበቅ የመጣ እንጂ የህወሓት ድርጊት እጅግ ግዙፍ እና ሌላ ወንጀል በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመበት ተግባር መሆኑ ጠፍቷቸው አይደለም። 

ባትሰባ ሰይፉ የኒውዮርክ ዩንቨርስቲ የሕዝብ አስተዳደር ማስተርስ ተመራቂ ነች። ዛሬ ''ሞደርን ዲፕሎማሲ ዶት ኢዩ''ላይ  የፕሪቶርያ ውል መክሸፍን በገለጸችበት ጽሑፍ ጉዳዩ የሕገመንግስታዊ ቀውስ መሆኑን፣ትግራይ በቂ እርዳታ በመንግስት ቢሮክራሲ አለማግኘቷንና ሌላው ቀርቶ በህወሓት በራሱ የተዘረፈውን የዕርዳታ እህል ህወሓትን ለመውቀስ ወደ ሌላ በመቀሰር ለማብራራት ሞክራለች። ባትሰባ ሰይፉ በእዚሁ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በጻፈችው እና ''The Fractured Reality After the Pretoria Peace Agreement'' የሚል ርዕስ የሰጠችው ጽሑፍ ውስጥ የፕሪቶርያው ውል ሦስት ምሰሶዎች እንደነበሩት ታብራራለች። እነርሱም ፡ የሰብዓዊ ርዳታ ተደራሽነት፣ሕገመንግስታዊ ስርዓት ማስከበር እና ሰብዓዊ መብት የሚሉ ሲሆኑ የህገመንግስታዊ ስርዓትን እንደ እርሷ አገላለጽ ''የአማራ ክልል ኃይሎች እና የኤርትራ ወረራ'' የፕሪቶርያን ውል ዋጋ እንዳሳጣው ለማሳየት በእዚሁ ጽሑፏ የውጪውን ዓለም ለማታለል ተጠቅማበታለች። በእዚህ ሁሉ ገለጻ ውስጥ ግን ህወሓት ሰሜን ወሎን ውርሮ በአስር ሺዎች ማፈናቀሉን፣ ትጥቅ እፈታለሁ ብሎ ዛሬም ክላሽ እየወዘወዙ የአማራ ክልልን የሚወሩ በሺህ የሚቆጠሩ ታጣቂዎች ለፕሪቶርያ ውል መፍረስ ምክንያት እንደሆነ ማብራራ አልሞከረችም። 

ይህ ጽሑፍ የሕወሃት ፕሮፓጋንዳ ማሽን መልሶ ዓለምን ለማታለል ለመጋጋጥ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት መጀመሩን ያሳያል። በሌላ በኩል በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካ ህወሓት የዲያስፖራ ክንፉ ገንዘብ እንዲያዋጣ መጎትጎት ይዟል። ለምሳሌ በጣልያን የሚኖሩ የዲያስፖራ ክንፉ ገንዘብ የሚያዋጡበትን መርሐግብር ቀርጾ በፖስተር ማሰራጨት ጀምሯል።ዛሬ በወጡ ዘገባዎች ደግሞ ህወሓት በሰሜን ወሎ የገጠር ወረዳዎች ግልጽ ዘረፋ ላይ እንደተሰማራ ከስፍራው በቀጥታ የሚመጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ህወሓት ለአራተኛ ጊዜ ''አደገኛ ወጥ እረግጧል'' 

ህወሓት ለአራተኛ ጊዜ ''አደገኛ ወጥ እረግጧል''። የአሁኑ አረጋገጥ ካለፈው ተሞክሮ ተምሮ በተለየ ስልት እንደሚሆን መገመት ቀላል ነው። አቶ ጌታቸው ረዳ አዲስ አበባ ሆኖ ስለ ሰላም እያወራ፣ ታደሰ ወረደ ከትግራይ ሆኖ ከመንግስት ጋር ተነጋግረን ነው እያለ የሚያምታቱበት አዲስ ታክቲክ ይዘው መምጣታቸውን ሕጻን ልጅም ይረዳዋል። በህወሓት ውስጥ የሰላም ፈላጊና የጦርነት ናፋቂ ሁለት አንጃ ካለ አንዱ አንዱን አስሮ ያሳየን እና እንመነው። ከእዚህ ውጪ ''በዕቃ ዕቃ ጨዋታ'' የኢትዮጵያን ሕዝብ ዳግም ማደናገር አይቻልም። የትግራይ ሕዝብ በሚልዮን የሚቆጠር ልጆቹን ቀብሮ ዛሬም ህወሓት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሲያጋጨው ተቅምጦ የሚመለከተው ከሆነ ሌላ አደገኛ የታሪክ ስብራት ምናልባትም ክልሉ የሚበተንበት አደጋ ውስጥ እንደሚገባ መረዳት አለበት። በእዚሁ በጉዳያችን ላይ ለዓመታት በህወሓት አመራር በትግራይ ይደርሳል ህዝብ መቃወም አለበት እያልን ስንጮህ የሰማ አልነበረም።ዛሪ የትግራይ ህዝብ የደረሰበትም ሆነ የሆነው ግን ያኔ የተናገርነው ነው።ዛሬ የሚነገረውም ሰሚ ካላገኘ ነገ በህዝቡ ላይ የበለጠ መከራ ህወሓት ይዞ እንደሚመጣ ለማወቅ ነቢይ መሆን አይጠይቅም።

በመጨረሻው መጨረሻ ግን ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።ህወሓት ትጥቅ መፍታት አለበት። ይህ የፕሪቶርያው ውል አካል ካልሆነ ይነገርን።አልያም የፕሪቶርያውን ውል ህወሓት እንዳፈረሰ የመንግስት የፖለቲካውም ሆነ የወታደራዊው አመራር በግልጽ ይንገረን።

==================///=============



 






Saturday, March 16, 2024

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።



Monday, February 19, 2024

የኢትዮጵያ ድንቅ መስተንግዶ ዳግም የተመሰከረበት የአፍሪካ ኅብረት 37ኛ የመሪዎች ጉብዔ ዛሬ ሰኞ ተጠናቀቀ።ኢትዮጵያን የሚመጥነው የኢትዮጵያ መስተንግዶ በቪድዮ።

በእዚህ ሊንክ ስር ፡ 
  • መሪዎቹ የተወያዩባቸው አራቱ አጀንዳዎች ምን ነበሩ? (አጀንዳዎቹ በአጭሩ ተዘርዝረዋል)
  • እድሳቱ በቅርቡ የተጠናቀቀው ብሔራዊ ቤተመንግስት የተደረገው የራት ግብዣ የእንግዶች አቀባባል (ቪድዮ ይመልከቱ)
  • የአዲስ አበባ ከተማ ቸርችል ጎዳና የሰሞኑ የምሽት ገጽታ እንደወረደ (ቪድዮ ይመልከቱ)
=============

የአፍሪካ ኅብረት 37ኛ የመሪዎች ጉባዔ አራቱ አጀንዳዎች፡ 

1. የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት የዘንድሮ የፈረንጆች ዓመት የትምህርት ዘመን ተብሎ መሰየሙን ተከትሎ የኅብረቱ ጉባኤ በአህጉሪቱ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ለማረጋገጥ ሊሰሩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ መክሯል። የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፤ በአፍሪካ በተለይም ከሰሃራ በታች በሚገኘው የአህጉሪቱ ቀጣና በዓለም የትምህርት ተደራሽነት ካልተረጋገጠበት አከባቢ ቀዳሚ ነው። ለአብነትም አጠቃላይ በአህጉሪቱ ከሚገኙ እድሜያቸው ከ15 እስከ 17 የመሆኑ ታዳጊ ወጣቶች 60 በመቶ የሚሆኑት ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው። ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ታዳጊዎች ቁጥርም አጅግ ከፍተኛ ነው። ብቂ መምህራን የማሰማራት እንዲሁም አህጉሪቱን ለመለወጥ የሚያስችሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፉ የተግባር ትምህርቶች ተደራሽነትም ከሚፈለገው በታቸ ነው።

2. አህጉራዊ ምጣኔ ኃብታዊ ትስስር የአፍሪካን ከውጭ የፋይናንስ ጥገኝነት ለማላቀቅና ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊና ምጣኔ ኃብታው ችግሮችን ለመቅረፍ የውስጥ አቅምን አሟጦ መጠቀም በተመለከተ ውይይት ተደርጓል። በዚህ ረገድ በተለይም ትልቅ ግምት የተሰጠው አሁን በሙከራ ደረጃ ላይ የሚገኘው አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የእስካሁኑ ሂደትና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ምክክር ተደርጓል። ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ በአህጉሪቱ 30 ሚለየን ሰዎችን ከድኅነት የማውጣት እንዲሁም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር በ2035 በአፍሪካ ገቢን በ7 በመቶ እንደሚጨምር ተስፋ የተጣለበት ይኸው የንግድ ቀጣና በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገባ አገራት ከታሪፍና ከሌሎች የንግድ ሂደት ጋር ያሉ ውስብስብ አሰራሮችን እንዲያስወግዱ አቅጣጫ ላይ መክሯል።

3. አፍሪካ በዓለም መድረክ ያላት ሥፍራ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ተቋማት ያላትን ውክልና ተገቢውን ሥፍራ እንድትይዝ በተለይም በመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ያላትን ውክልና በተመለከተ ለበርካታ ዓመታት ስትጠይቅ ቆይታለች። ይህንን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትም የአፍሪካን ፍላጎት ያገናዘበ ቁመና ሊኖረው ይገባል የሚለውም አጀንዳ የዘንድሮው ጉባኤ አጀንዳ ነበር ። አፍሪካ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን መድረኮች ጋር በተለይም አሁን አፍሪካ የቡድን 20 አገራት አባል መሆኗን ተከትሎ እንዲሁም ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ እየገነነ ከመጣው ከብሪክስ ጋር ባላትና ሊኖራት በሚችለው ግንኙነት ዙሪያም ምክክር ተደርጎበታል። በተለይም አፍሪካ እንደ ተጨማሪ የቡድን 20 አባልነቷ፤ ምን ይዛ ልትሄድና ልታመጣ ትችላለች እንዲሁም አባልነቷን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለበርካታ ዓመታት ተፈልጎ የታጣውን ውክልና ለመካስ ወይም የአህጉሪቱን ድምጽ ይበልጥ ለማሰማት በሚቻልባቸው ምቹ ሁኔታዎች ዙሪያ ምክክር ተደርጓል።

4. የሠላምና ደኅንነት ተግዳሮቶችና መፍትሄያቸው የመሪዎቹ ጉባኤ ዘንድሮም በአፍሪካ የጸጥታ ችግሮች ዙርያ ምክክር አድርጓል። አህጉሪቱን ከድኅረ -ነጻነት በኋላ በእጅጉ እየፈተኑ ከሚገኙ ከነገረ ፖለቲካዊ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚውን ሥፍራየሚይዘው የጸጥታ መደፍረስ ነው። ሽብርተኝነት፣ ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ የሥልጣን መቆናጠጥ፣ ግጭቶችና ከምርጫ ጋር የተያያዙ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ሌሎች መሰል ቸግሮች አሁንም ለአፍሪካ ፈተና ሆነው ቀጥለዋል። እነዚህ የፖለቲካ ቀውሶች አህጉሪቱ በየትኛውም ማኅበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ መስክ ወደፊት ፈቅ እንዳትል ካደረጓት ምክንያቶ ዋነኛው መሆኑን ነው የተለያዩ ጥናቶች የሚያሳዩት። እነዚህን ግጭቶች ባሉበት ለማቆምና ሌሎችም በቀጣይ እንዳይከሰቱ በተለይም የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል (ውይይት) ብቸኛ አማራጭ ለማድረግ ኅብረቱ ከዚህ ቀደም የጀመራቸውን ሥራዎችና ሌሎች ተግባራትን ለማጠናከር በሚያስቸሉ ጉዳዮች ላይ መሪዎቹ ውይይት አድርገዋል፣የመፍትሄ አቅጣጫዎችም ስብሰባው አስቀምጧል።

እድሳቱ በቅርቡ የተጠናቀቀው ብሔራዊ ቤተመንግስት የተደረገው የራት ግብዣ የእንግዶች አቀባባል (ቪድዮ)


የአዲስ አበባ ከተማ ቸርችል ጎዳና የሰሞኑ የምሽት ገጽታ እንደወረደ (ቪድዮ)

ቪድዮው የሚጀምረው ከፒያሳ የአድዋ ድል መታሰብያ ሙዜም ዙርያ ነው።

ለጽሑፉና ቪድዮዎች ምንጮች ፡  

  • ENA
  • FBC
  • J.Walking Tour

Tuesday, January 23, 2024

ኢጃት ማን ነው? እንዴት ተመሰረተ? (ቪድዮ)

  • በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምሕርትቤቶች ማደራጃ መምርያ ስር መዝግባ ዕውቅና ሰጥታዋለች።

  • ከክፍሎቹ ውስጥ ሦስቱ ፡የመዝሙር ክፍሉ ጃን ያሬድ  ሰሞኑን የአዕላፋት ዝማሬን ያቀረበው ሲሆን ሁለተኛው ጃን አጋፋሪ የዝግጅቶች አስተባብሪ ነው።ሦስተኛው ጃን ምኩራብ የሚድያ ክፍል ነው።

  • ኢጃት ሐያሁለት ፕሮጀክቶች ይዞ እየሰራ ነው።

  • ዋና ዓላማው በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገለገልና የሚያገለግል ትውልድ ማፍራት ዓላማው የሆነውን የኢጃትን መልካም ሥራውን ለማጣጣል '' የክርስቶስ የሆኑትን ሊሳደብ አውሬው አፉን ከፈተ'' ተብሎ  በመጽሐፍ ላይ እንደተጻፈ በባሕር ማዶ ሆኖ በኢጃት ውጥን ስራዎች ላይ ሊሳለቅ የሞከረውን ከሰሞኑ ታዝበናል።

    በጎ ሥራ የሚሰራ ትውልድን ሁልጊዜ እናበረታታ!





Thursday, January 11, 2024

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲን እጅግ ዘመናዊ በሆነ አቀራረብ የተዘጋጀው ዐውደ ርዕይ ዛሬ አዲስ አበባ በሳይንስ ሙዝየም ተከፍቷል (ቪድዮውን ይመልከቱ)

  • ዐውደ ርዕዩ ከንግስት ሳባ ጀምሮ ያለውን የኢትዮጵያ የውጪ ግንኙነት ያሳያል።
  • ኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መስርያቤትን ስራ ካስጀመረች 116 ዓመታት እንደሆናት ዐውደ ርዕዩ ያሳያል።
  • በዛሬው መክፈቻ ስነስርዓት ላይ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገሮች አምባሳደሮች ጨምሮ፣ከተልያየ ዓለም የመጡ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።
  • ዐውደ ርዕዩ ከሁለት ሳምንታት በላይ ክፍት ሆኖ ይቆያል።በቀጣይ ቀናት በአዲስ አበባ ነዋሪ እና የዓለም ዓቀፍ ኮሚኒቲ ይጎበኛል ተብሎ ይጠበቃል።
  • በቅርቡ በአዲስ አበባ እንደሚደረግ የሚጠበቀው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ የሚገኙ የሀገራት መሪዎች፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ዓለም ዓቀፍ ጋዜጠኞች እንደሚጎበኙት ይጠበቃል።
ቀን ጥር 2፣2016 ዓም


ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...