ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, May 30, 2018

የትግራይ ሕዝብ ብቸኛ ጠላት የህወሓት አዛውንት መሪዎች ናቸው

በእዚህ ፅሁፍ ውስጥ : -

  • አዛውንቶቹ የሴራ ፖለቲካ ባለቤቶች የትግራይን ሕዝብ ከቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚለዩባቸው ሁለት መንገዶች እና 
  • የጀብሃ ዘፋኝ በኃላ ሻብያን ሸሽታ በስደት ባለፈው ሳምንት ያረፈችው ፀሐይ ባራኪ (ፀሐይቱ) በጆሲ ኢን ዘ ሃውስ የተቀናበረው ዜማ (ኦድዮ) ያገኛሉ።

ጉዳያችን / Gudayachn 
ግንቦት 23/2010 ዓም (ሜይ 31/2018 ዓም)

ነሐሴ 18፣2004 ዓም ፍኖተ ነፃነት በተሰኘው ጋዜጣ በዳሰሳ ዓምድ ስር በዞን ዘጠኝ ፀሐፊዎች የቀረበው ፅሁፍ ላይ የህወሓት አነሳስን ስገልጥ የሕወሓት ወላጅ ከሆነው  መስራች አባላት አንዱ ከሆኑት አረጋዊ በርኸ The Origin of The Tigray People’s Liberation Front በሚለው ጥናታቸው ላይ ያሰፈሩትን መነሻ ያደርጋል።አቶ አረጋዊ በእዚሁ ፅሁፋቸው ህወሓት አፈጣጠሩ ሲጀምር መጀመሪያ ትግራዋይ የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ሕብረት ተብሎ እንደተፈጠረ ይነግሩናል፡፡ የህብረቱ አባላት ከሆኑት ውስጥ መለስ፣ ተክሌ እና አባይ ፀሃዬ የዩንቨርስቲ ተማሪዎቹን ማኅበር  አርታኤ ቡድን ይመሩ ነበር፡፡ የኅብረቱ ዋነኛ ዓላማ ለትግራይ ሕዝቦች ፖለቲካዊ ንቃት ማጎናፀፍ ብቻ ስለነበር፣ ከዚያ የተሻለ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዲችል በሚል “ማህበር ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ” (ማገብት) ተወለደ፡፡ ማገብት  የህወሓት ወላጅ አባት እንደሆነ ያብራራሉ፡፡

ማገብት ህወሓት ከመመስረቱ በፊት ከኅግሓኤ (ሕዝባዊ ግምባር ሓርነት ኤርትራ) ጋር የሥራ ግንኙነት መስርቶ ነበር፡፡ (ስሙም ከዚያው የተገኘ ይመስላል፡፡) መለስ ከህወሓት፣ ጥቂት ቀደምት አባላት አንዱ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ መጽሐፍት እንደሚተርኩት መለስ ዜናዊ እና አቦይ ስብሓት የህወሓት መስራቾች ሳይሆኑ፣ ከተመሰረተ ጥቂት ወራት በኋላ ትግሉን የተቀላቀሉ መሆናቸውን A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975- 1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopia በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ አረጋዊ በርኸ ጽፈዋል፡፡

አዛውንቶቹ የሴራ ፖለቲካ ባለቤቶች የትግራይን ሕዝብ ከቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚለዩባቸው ሁለት መንገዶች 

ህወሓት ከተመሰረተ በኃላ የመጀመርያ የጅራፍ በትሩን ያሳረፈው የኢድዩ እና የፊውዳል ርዝራዦች ናችሁ እያለ የትግራይ አዛውንቶችን እና እናቶችን ወደ ማጎርያ ከመላክ እስከ ግድያ እና ለስደት የዳረገ ድርጅት ነው።በእዚህም ሳብያ ላለፉት አርባ ዓመታት ሙሉ የትግራይ አንድ ትውልድ ጨርሶ በህወሓት ቅኝት ብቻ የተቃኘ አንድ ትውልድ ፈጥሯል። ይህ በህወሓት ቅኝት የተፈጠረው ትውልድ የተቀረፀበት አንዱ እና ዋነኛው ባሕሪ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ትግራይን እና የትግራይ ተወላጆችን በጠላትነት እንደሚመለከት አድርጎ መሳል እና የዐማራ ተወላጅ ዋነኛ ጠላት ነው የሚል ትርክት በማስቀመጥ (በ1967 ዓም ባወጣው ማነፈስቶ ላይ እንዳስቀመጠው) ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ አባቶቹ ተፈጅተው የተረፈው ትውልድ ሌላውን ኢትዮጵያዊ የሚፈራ አድርጎ ቀርፆታል።

ይህ ሌላውን ኢትዮጵያዊ እንዲፈራ ተደርጎ የተቀረፀው ትውልድ የፍራቻ እና የማራራቅ ስራው የሚሰራው እና የሚቀመመው በአዛውንቶቹ የህወሓት አመራር ነው። ላለፉት አርባ ዓመታት በተንኮል እና የሴራ ፖለቲካ የተካኑት አዛውንት የህወሓት አመራሮች ላለፉት አርባ አመታት ውስጥ የመጣውን ትውልድ ስሜቱን ከወጣትነቱ ጀምሮ የመጠቀሙባቸው ሁለት መንገዶች በማስደንበር እና በማጋጨት ነው።የማስደንበር ስራው የሚከናወነው ተከታታይ የፕሮፓጋንዳ ሥራ በስብሰባዎች፣በፅሁፎቻቸው እና በመገናኛ ብዙሃን ሲሆን።ተደጋግሞ በመናገር ብዛት ይህንን ትውልድ ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል የትግራይ ጠላት እንደሆነ ይህንን ጠላት ካሉት ለመታደግ ደግሞ የህወሓት አዛውንቶቹ አመራር ብቸኛ ጠባቂዎቻቸው እንደሆኑ እንዲሰማቸው አእምሯቸውን የመቆጣጠር ሥራ ለአመታት ሲሰሩ ኖረዋል።


ከማስደንበር ስራው በተጨማሪ የህወሓት አዛውንት አመራሮች የትግራይ ሕዝብ የመጨረሻ ምሽጋቸው እና ምሰሷቸው መሆኑን በማመን የትግራይ ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ ጋር ግልጥ የሆነ ግጭት ውስጥ እንዲገባ ያደርጉታል።  እነኝህ ግጭቶች ለአዛውንቱ አመራር ሆን ተብለው የሚፈጠሩ እና የትግራይ ሕዝብ ሁል ጊዜ ሰግቶ እንዲኖር የሚያደርግበት አይነተኛ መሳርያ ሆነው አገልግለውታል። ለእዚህ አብነት የሚሆኑትን ምሳሌዎች ማንሳት ይቻላል።በ1997 ዓም ምርጫ ቅስቀሳ ላይ ህወሓት ''ኢንተርሃምዌ'' የምትለዋን ቃል የተጠቀመበት በመጀመርያ ደረጃ የትግራይን ሕዝብ ለማስደንበርያነት ነው።በቀጣይ ቀናትም የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የጎረቤት ፀብ ሳይቀር ስም እየጠቀሰ በመገናኛ ብዙሃን መጠቀስ የማይገባው ፀያፍ ዜናዎችን ሲሰራ ሰንብቷል። በቅርቡ ደግሞ በወልዲያ ከተማ እና በአዲስ አበባ ከተሞች የተደረጉ በእግር ኳስ ጫወታ ሳብያ የተፈጠሩ ግጭቶች ብዙ ሰው የሚያስበው በጫወታው መሃል የተነሱ ግጭቶች አድርጎ እንጂ ከጀርባ የትግራይን ሕዝብ ለማስደንበር የሴራ ፖለቲከኞች አዛውንት የህወሓት አመራሮችን ፈፅሞ አላሰባቸውም።ሆኖም ግን በወልዲያ በፒክ አፕ መኪና ተጭነው ጫወታው ከመደረጉ በፊት ከተማዋን እየዞሩ ጠብ የሚጭር ቃላት የሚያወጡ ወጣቶችን ከትግራይ ይዞ መጥቶ ከዋዜማ ጀምሮ ሕዝቡን ለፀብ ያዘጋጁ እነማን ናቸው? በአዲስ አበባው የወልዋሎ የአዲግራት ዩንቨርስቲ ቡድን ጋር የተፈጠሩ ፀቦች ተራ ግጭቶች ናቸው? እስከ ዳኛውን መልበሻ ክፍል ድረስ እየመጡ ከጫወታው በፊት የተደረጉ ነገር የመቆስቆስ ስራዎች በኃላም አሰልጣኙ በቀዳሚነት የተሳተፈበት ግጭት ሜዳ ላይ ብቻ በተፈጠረ የስሜት መጋል የተከሰተ ከሆነ ጥሩ ነው።ሆኖም ግን ቅንብሩ አይመስልም።ከእዚህ በተለየ ህወሓት የማስደንበር ሌላ ተግባሩን የሚፈፅመው እንደ የግል ንብረቱ የሚመለከተውን የትግራይ ሕዝብ በድንገት ከቦታችሁ ተነስታችሁ ለቃችሁ ወደ ትግራይ ኑ! እያለ ከጎንደር እስከ ደቡብ ያሉ የትግራይ ተወላጆችን በሚስጥር የሚያውቀው ሊከሰት የሚችል ግጭት አለ የሚል የተሳሳተ መልዕክት እየላከ የማስደንበር ተግባር መፈፀሙን ባለፉት ሁለት ዓመታት የታዘብነው ጉዳይ ነው።እዚህ ላይ በውጭ ሀገር የሚገኙ የትግራይ ልማት ማኅበራት አመራር የተቆጣጠሩ ግለሰቦች ተመሳሳይ የማስደንበር እና የማጋጨት ሥራ በትግራይ ተወላጆች ላይ እንደሚሰሩ የአደባባይ ምስጢር መሆኑን ሳንዘነጋ ነው።

ይህንን ሁሉ የግጭት እና የማስደነበር ሥራ ሲሰራ አስተሳሰቡን በአዛውንቶቹ የተንኮል መረብ ቁጥጥር ስር የወደቀው ሌላው የትግራይ ተወላጅ ነገሮችን አጢኖ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ተባብሮ ከመስራት ይልቅ በትግራይ ልማት ማኅበር በኩል የመጣ ብጣሽ ወረቀት መልዕክት ማመኑ ምን ያህል በሚገባ እያገናዘበ እንዳልሆነ እና በአዛውንቶቹ የሚሰራበትን ተንኮል እንዳላየ ሲያልፈው ይታያል።ይህ ግብ ውሎ አድሮ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን ማወቁ ነው ቁምነገሩ።አንዳንዶች ህወሓት ባይመጣ ኖሮ ትግራይ ከተሞቿ ፎቅ ሊኖራቸው እንደማይችል ያስባሉ።ሆኖም ግን ሃያ ሰባት ዓመት ማለት ቀላል ጊዜ አይደለም።እነ ሐዋሳ፣ሻሸመኔ እና አዳማ ከተሞች ያደጉት በጊዜ ሂደት መሆኑን መዘንጋት የለብንም።ህወሓት ባይመጣም አሁን ትግራይ ያለው ልማት እንደሌሎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች ቢያንስ የመሰረተ ልማት እና የከተሞች መስፋት አይደርሳትም ብሎ ማሰብ አይቻልም።የህወሓት አዛውንቶች ኖሩም አልኖሩም ትግራይ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የመልማት ሂደቷ አይቆምም።አንዳንዶች የትግራይ ተወላጆች ህወሓት ቤተ መንግስት ከሌለ ትግራይ ልማት የማታይ አድርገው የሚያስቡ አሉ።ሆኖም የሕግ የበላይነት እና እኩል ተጠቃሚነት ጋር ዲሞክራሲያዊ ሂደቱ ከተስተካከለ የትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ይልቁንም ከታሰበው በላይ የማደግ እድሉ ትልቅ ነው።የህወሓት አዛውንት መሪዎች ግን አሁንም የትግራይን ሕዝብ ሊያሞኙ ይሞክራሉ።

የተንኮል ፖለቲካ ባለቤቶች አዛውንቶቹ ገለል ማለት አለባቸው

ህወሓት ከሁለት ዓመት በፊት መደበኛ ስብሰባውን ሲያደርግ አዛውንቶቹን አመራሮች ለማስወገድ እና ለውጥ ለማምጣት (ምን አይነት ለውጥ እንዳሰቡ አልታወቀም) ወጣቶቹ እና ጎልማሶቹ ከፍተኛ ርብርብ አድርገው ነበር።ሆኖም የአዛውንቱ ክፍል አሁንም በድንገት ደርሶ ወንበሩን ያዘው።በእዚህም አቶ አባይ ወልዱ የመጨረሻ ድምፅ የተሰጠባቸው በአስረኛ ደረጃ የተመረጡ ቢሆኑም ወደላይ መጥተው የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት በመሆን ከወልቃይት እስከ ወልድያ የትግራይን ሕዝብ ከቀረው ወንድሙ ጋር በድንበር አጋጭተው ገበያም እንዳይደራረስ እያደረጉት ነው።አንድ አመራር ለሕዝቡ የሚያስብ ከሆነ ዘለቄታ የህዝብ ግንኙነት ላይ እንጂ ጊዜያዊ  ግንኙነት ላይ ብቻ ሊያልም አይችልም። የህወሓት አዛውንት አመራሮች ግን የነበረውን የህዝብ ግንኙነት ሲያደበዝዙ ሲታይ የትግራይ ሕዝብ ዋና ጠላት ይሄ የአዛውንቶቹ አመራር መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል።

ባጠቃላይ ለትግራይ ሕዝብ ቀዳሚ ጠላቱ የህወሓት አዛውንት አመራሮች መሆናቸውን ማወቅ አለበት።ሕዝቡን የሚወድ አመራር  ሕዝቡን ከህዝብ አያጋጭም።ይልቁንም ለዘለቄታ አብሮ የሚኖርበትን መንገድ ሲፈልግ ይታያል።በህወሓት አዛውንቶች እና አፈቀላጤዎቻቸው ዘንድ የሚታየው ግን ከእዚህ የተለየ ነው።በመድረክ ንግግሮቻቸው የሚያቃቅር እና ሁሉን ነገር በኃይል እንዲፈታ ሲነግሩት ይሰማሉ።በመጋጨት እንጀራ እንደሚገኝ ይመክሩታል።እነርሱ በመጡበት መንገድ ብቻ መፍትሄ እንዳለ በሃያ አንደኛው ክ/ዘመን ላይ ተቀምጠው ይመክሩታል።ስልጣን ላይ ከወጡ ሩብ ክፍለ ዘመን እንዳለፈ እና በእነኝህ ዘመናት ውስጥ በርካታ ነገሮች መቀየሩን እረስተውታል።በተጨማሪም ከእነርሱ ውጭ ህዝቡ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ይነዙለታል። ይህ ሁሉ ግን ተራ ፈጠራ ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮ ሲኖር ያለፉት ሃይ ሰባት አመታት የመጀመርያው አይደለም።አሁን ያለው መፍትሄ አንድ ነው።ይሄውም ለዘመናት በላዩ ላይ ሆነው ያረጃ የማርክስ ርዕዮት የጫኑበትን  የአዛውንቶች አመራር ላይ መነሳት እና ከሁሉም ሕዝብ ጋር አብሮ የሚያኖር አመራር ማምጣት እና እራሱን ከሴራ ፖለቲካ ነፃ ማውጣት አለበት። ለእዚህም ትክክለኛ ጊዜው አሁን ነው።

 ባለፈው ሳምንት ከእዚህ ዓለም በ79 ዓመቷ በሞት የተለየችው  የፀሐይቱ (ፀሐይ ባራኪ) ዜማ (ኦድዮ)
(ፀሐይ ባራኪ ለጀብሃ  ዜማዎች ታዜም እንደነበር እና በኃላ ነገር አለሙን ትታ በተቀመጠችበት በ1983 ዓም ሻብያ አስመራን ሲቆጣጠር በሱዳን በኩል ወደ ኔዘርላንድ ተሰዳ ባለፈው ሳምንት ሕይወቷ እስካለፈ ድረስ በስደት ኖራለች። ፀሐይ ባራኪን የአሁኑ ትውልድ አናውቃትም።ምናልባት ባለፈው ሳምንት እረፍቷ ሲሰማ በተነገረው ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ያወቅናት የአሁኑ ትውልድ አካሎች ብዙ ነን።ፀሐይ በ1960ዎቹ በአዲስ አበባ ከአንጋፋ ዘፋኞች ጋር ሙዚቃዎቿ ይሰሙ እንደነበር ይነገራል።)


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Sunday, May 27, 2018

የሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፈድሬሽን ደንብ በሕዝብ የማይስተካከልበት ምን ምክንያት አለ? (የጉዳያችን ማስታወሻ)


ጉዳያችን/Gudayacn
ግንቦት 20/2010 ዓም (ሜይ 28/2018 ዓም)


የሰሜን አሜሪካ ስፖርት ፈድሬሽን ሕግ በራሱ መከለስ እንዳለበት በእዚህ ሳምንት መጨረሻ የተነሳው ጉዳይ በእራሱ አመላካች ነው። የሰሜን አሜሪካ ስፖርት ፈድሬሽን የሚጋብዛቸውን እንግዶች የፖለቲካ ተሳትፎ የጎላ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሕጉ ይከለክል ከነበረ (የሕጉን ትክክለኛ ቅጅ ስላላገኘሁት ሆኖም ከእዚህ በፊት በሚጋበዙ እንግዶች ዙርያ የተነሱ ሃሳቦችን መሰረት በማድረግ) ይህ ሕግ አሁን ላይ ይሰራል ወይ? ብሎ የመጠየቂያ ጌዜው አሁን ነው ማለት ነው።ሕግ ከወቅቱ ጋር እየታየ ይስተካከላል፣ ይከለሳል።ወሳኙ ጠቅላላ ጉባኤው ነው።ምናልባት ይህ ሕግ የውስጥ ንዑስ ሕግ እንጂ ፈድሬሽኑ በአሜሪካ ሕግ የሚመዘገብበት ዋናው ሕግ አንቀፅ ውስጥ ስለማይሆን የውስጥ ደንቡን ተከትሎ መስተካከል ይችላል ማለት ነው።


በሌላ በኩል ደግሞ ቀደም ብሎ የወጣው ሕግ የፖለቲካ ተሳትፎን እያጤነ ይለይ ከነበረ በወቅቱ አስፈላጊ ነበር ቢባልም ሃሳቡ ግን ትክክል ነው ማለት አይደለም።ስፖርት በፖለቲካ አመለካከትም ሆነ አስተሳሰብ ክብደት እና ቅለት እየታየ ተጋባዥ እንግዳ መጋበዝ በእራሱ የአዲሱን ወጣት የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያቀጭጭ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን የስፖርትን አምስቱን መሰረታዊ መርሆዎች ጋር  ላለመጣጣሙ  እማኝ ማቅረብ አይቻልም።የቀደሙ የኢትዮጵያ መሪዎች አፄ ኃይለስላሴም ሆኑ ኮለኔል መንግስቱ በስፖርት በዓላት ላይ እየተገኙ ወጣቶችን ያበረታቱ ነበር።ይህ ተፈጥሯዊ አሰራር ነው።አንድ ሰው በፖለቲካ መስመሩ ብቻ የኢትዮጵያን የጋራ ዕሴት በተቃረነ መልኩ እስካልቆመ ድረስ የስፖርት በዓሎች ላይ በክብር እንግድነት የመገኘት መብቱ ሊገሰስ አይገባም።

ስለሆነም የሰሜን አሜሪካ ስፖርት ፈድሬሽን አሁን ላይ ሆኖ እራሱን ሲመለከተው  ያለፈው ሕጉ ችግር ነበረበት  ማለት ነው። በእርግጥ በወቅቱ ለነበሩት የፖለቲካ ትኩሳቶች ላለመንገላታት  ጠቅመው ይሆናል።በአንድ ወቅት ከነበረ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተዛመደ መልክ የወጣ ሕግ ግን ሁል ጊዜ ትክክል ነው ማለት አይቻልም።አሁን አዲስ ትውልድ መጥቷል።ዘመን እየነጎደ ነው።ልዩነት ከማስፋት የማጥበብ አስፈላጊነት ላይ የሚያጠነጥኑ አስተሳሰቦች እና ኢትዮጵያዊነት  በልዩነት አንድነት የሚለው አስተሳሰብ ከመቼውም ጊዜ የጎሳ አስተሳሰብን መተካት እንዳለበት ከፍ ያለ እምነት በሕዝብ ዘንድ ይንፀባረቃል።ይሄው ሃሳብ ደግሞ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይም እየተስተጋባ ነው።


እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን ስለ ሕጉ እያወራን ያለው ዛሬ ዶክተር ዓብይ ዋሽንግተን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ለሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፈድሬሽን ዳላስ ላይ በሚደረገው የዘንድሮ  በዓል ላይ እንድገኝ ፍቀዱልኝ ብለው የመጠየቃቸው  ምክንያት ስለሆነ  እና ይህንን ለመርዳት መውጫ የመፈለግ መላ አይደለም።ይልቁን ጥያቄው በእራሱ የሕጉን መከለስ አስፈላጊነት አመላከተ እንጂ።ሲሆን ክስተት ሳይፈጠር ቀድሞ መጪውን አስቦ ሕግ ማስተካከል ተገቢ ነበር።ሆኖም ሁል ጊዜ ይህ አይሳካም እና ክስተቱ የሕጉ መስተካከል አስፈላጊነትን አሳየ ማለቱ ይቀላል።


ጠቅላይ ሚንሰተር ዶ/ር ዐብይ ዘንድሮ በሚደረገው የሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓ እግር ኳስ ውድድር ላይ መገኘት በሚለው ሀሳብ ሰዎች የተለያየ ሀሳብ ሊኖራቸው ይችላል::ይህ ማለት መከፋፈል ማለት አይደለም::የተለያዩ ሀሳቦች ከማንሸራሸር ያለፈ ስም አይሰጠውም::ሀገራዊ ለውጥ በግለሰቦች ልቦና ተመላልሶ በህብረተሰብ ውስጥ አድጎ የሚተገበር ድርጊት ነው::የስፖርት ፌድሬሽኖቹ ህግ በተመለከተ ዶ/ር ዐብይ መጋበዝ ላይ አሳሪ አይመስለኝም::አሳሪ ስላልሆነም ነው አንዳንድ ግለሰቦች ላይ አከራካሪ ሲሆን የነበረው:: አሳሪ ሕግ ሆኖ ቢሆን ኖሮ አንቀፅ ጠቅሶ ይቆም ነበር።ከእዚህ በፊት በነበሩ ሂደቶች ግን (የብርቱካን ሜደቅሳ ማስታወስ ይቻላል) የሕጉን ትርጉም ለማስረዳት የአሜሪካ ድምፅ ራድዮ ሳይቀር ሲያወያይ ነበር።ምክንያቱም አንዳንዶቹ ግለሰቦች የምከለከሉበት የፖለቲካ አስተሳሰባቸው መሰረት ማድረጉ ያልተዋጠላቸው በርካታ ወገኖች ስለነበሩ ነው። ይህ በእራሱ ክፉ ነገር አይደለም።ለንትርክም አይጋብዝም።ሆኖም ግን ሕግ በረጅም ጊዜም የሚያረጅ ከመሆኑ አንፃር ትናንት የነበረው አሰራር ዛሬ ላይ የትናንቱን አይነት ጥያቄ ይዞ መጥቷል።ባለቤቱ ሕዝብ ደግሞ እንዲስተካከል የምፈልገው ሕግ በሙሉ ሕግ ሆኖ ይኖራል።ይህ በዲሞክራሲያዊ አሰራሮች ላይ የተመሰረቱ አደረጃጀቶች ሁሉ የሚከተሉት ነው።


ዶ/ር ዐብይ ተጨማሪ እርምጃዎች መውሰድ የበለጠ አስፈላጊ መሆኑን ባምንም::ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተቃዋሚ እስከ ውጭ ነዋሪ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድረስ የጎላ ተቃውሞ ካለመኖሩ አንጻር እና የእርሱ በበዓሉ ላይ መገኘት ከሀገራዊ ፋይዳ አንጻር የአውሮፓም ሆነ የአሜሪካ ፌድሬሽኖቹ ቢፈቅዱ ትልቅ ጥቅም አለው:: ከእዚህ አትራፊ ደግሞ ኢትዮጵያ ብቻ ነች:: አንዳንዶች የአሜሪካ ምክር ቤት ወደ ሕግ መውሰኛው የመራውን የሰብዓዊ መብት ሕግ ለማስቀየር ነው እና ሌሎች መላ ምቶችን ይሰጣሉ። ይህ ግን ከእዚህ ጋር አይገናኝም።ሕጉ እንዲፀድቅ የሚጠይቅ ሕዝብ ነው እንጂ መንግስት አይደለም።ከእዚህ ይልቅ በርካታ ሕዝብ በስታድዮሙ መታደሙ የኢትዮጵያዊነት አመክንዮ በምን ያህል በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው ለአሜሪካኖችም ሆነ ለእራሳችን የምንገልጥበት መልካም አጋጣሚ ነው። ይህ ካልተፈቀደ ዶ/ር ዓብይ የጎሳ ፖለቲካ የሚያቀነቅኑ ጋር ሄደው ንግግር ያድርጉ? በነገራችን ላይ ቀላል የማይባል በብዙ አስር ሺዎች የሚቆጠር በውጭ የተወለደ እና በጉዲ ፈቻ የመጣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ አለ:: ይህ ትውልድ ኢትዮጵያዊነት የጠማው የሌላ ሀገር ዜጎች በሀገራቸው የፖለቲካ ህይወት ውስጥ ሲሳተፉ÷የመሪዎቻቸው ርዕይ በአደባባይ ሲያዳምጡ በቅናት እና በቁጭት የሚኖሩ ናቸው::ስለሆነም የፖለቲካ ሜዳውንም ሆነ እንዲህ አንዳንዴ እንደ ዶ/ር ዐብይ አይነት ሰዎች ስለኢትዮጵያ ሲናገሩ ቢሰሙ በውስጣቸው የሚሰንቁት በጎ ነገር ቀላል አይደለም::ስለሆነም የእዚህ ዐይነት መድረክ ምን ማለት እንደሆነ ካልተረዳን ከባድ ነው::

ይህ ማለት ሕጉን ለማስተካከልም ሆነ ዶ/ር ዓብይን በአሜሪካም ሆነ አውሮፓ የሚደረጉት የስፖርት ፈድሬሽን ጫወታዎች  ላይ እንዲገኙ ፔትሽን ሕዝብ ማሰባሰብ ይችላል።በፔትሺኑ አማካይነት በልዩ ሁኔታ ኢትዮጵያዊነትን በማጉላት የጎሳ ፖለቲካን ሶስት መቶ ስልሳ ዲግሪ ያዞሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር በክብር እንግድነት መጥራቱ ምንም የሚያመጣው ጉዳት የለውም።በብሔራዊ ደረጃ የተጎዳውን ኢትዮጵያዊነት በእዚህ ደረጃ በማንሳት በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል በአንድነት መኖር የበለጠ ነው ብሎ መስበኩ ብቻ ያመጣው ስነ ልቦናዊ ልዕልና በእራሱ በክብር እንግድነት ያስጋብዛል።

ለማጠቃለል  የስፖርት ፈድሬሽኑ ለውሳኔው ከተቸገረ በቀላሉ በኦንላይን ሕዝብ ድምፅ እንዲሰጥበት ፔቲሽን ክፍት አድርጎ ማስወሰን ይችላል።የእዚህ አይነት ሃሳቦች ሲነሱ የምንደናገጥ እና የምንሰጋ እንደምንኖር አስባለሁ።ምክንያቱም ለውጥ መኖር በእራሱ የሚያጠፋ መስሎ ማሰብ ተፈጥሯዊ ስጋት ነው።ሆኖም ግን የሚያስደነግጥ ጉዳይ የለውም።ለውጡ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ግን የስፖርት ፈድሬሽኑ የደረሰበትን የእድገት ደረጃ አመላካች ነው።የእዚህ አይነቱን የለውጥ ሂደት ዛሬ ባይደረግ ነገም የማይቀር ነው። ለማጠቃለል የሰላሳምስተኛውን የኢትዮጵያውያን ስፖርት ውድድር በዳላስ ማስታወቂያ  በድምፅ የሰራው ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ በማኅበራዊ ድረ ገፁ ላይ የዶ/ር ዓብይ በበዓሉ ለመታደም መጠየቅን አስመልክቶ የፃፈውን በመጥቀስ ፅሁፌን እገታልሁ። ዓለምነህ እንዲህ ይላል ህዝባቸውን ለማግኘት ፍቀዱልኝ ልገኝ ብለው መጠየቃቸው  (ዶ/ር ዓብይን ነው) በዜግነታችን የሚያከብረን እኩል ተነጋግሮን ተደማምጦን መፍትሄ ለማበጀት የሚሻ መሪ አያደርገውምን "

የዘንድሮው በዓል ማስታወቂያ ቪድዮ 


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Sunday, May 20, 2018

'' ንቃት፣ትጋት እና ቅንነት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ወሳኝ ናቸው'' አቡነ ሕርያቆስ በኖርዌይ የመካነ ቅዱሳን ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለ ሐይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ እና የአቡነ ኤልያስ ረዳት አገልጋዮችን ሲሸልሙ የተናገሩት (ቪድዮ)

ጉዳያችን/Gudayachn
ግንቦት 12/2010 ዓም (ሜይ 20/2018 ዓም)

  • የኖርዌይ መካነ ቅዱሳን ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለ ሐይማኖት ቤተ ክርስቲያን የህንፃ አሰሪ ኮሚቴ አሰራር ናሙና ለሌሎች አጥብያ አብያተ ክርስቲያናት መልካም ናሙና (model) አሰራሮች ስላሉት ከመዋቅር እስከ ስብሰባ አመራር እና ስራዎች ሂደት አንድ ወጥ የሆነ ባለ ጥቂት ገፆች ዝርዝር ማስታወሻ በአነስተኛ መፅሐፍ መልክ ለየትኛውም አጥብያ እንዲረዳ በታሰበ መልክ እንዲያዘጋጁ በእዚህ አጋጣሚ አደራ ማለት እንፈልጋለን።

በኖርዌይ የመካነ ቅዱሳን ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለ ሐይማኖት ቤተ ክርስቲያን አዲስ የገዛችውን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አድሳ እና አስባርካ ግንቦት 11/2010 ዓም ታቦታቱን አስገብታለች።በኖርዌይ የኢትዮያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  አገልግሎት ስትሰጥ ከ15 ዓመታት  በላይ ብታስቆጥርም የራሷ ህንፃ ቤተ ክርስቲያን አልነበራትም።ሆኖም ላለፉት ሶስት ዓመታት በተለየ መልክ  የምእመናንን ተሳትፎ ባጎለበተ መልኩ በተደረገው እንቅስቃሴ እና የአቡነ ሕርያቆስ ለአገልግሎት ወደ ኖርዌይ መምጣት፣የእርሳቸው መልካም አስተዳደር፣አመራር እና ጸሎት፣ከሁሉም ቀደም ብሎ ደግሞ የአቡነ ኤልያስ የረጅም ዓመታት ክትትል፣አባታዊ ምክር እና ጸሎት ሁሉ ታግዞ  መንፈሳዊ አገልግሎቱን የበለጠ የሰመረ ከማድረጉም በላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ የራሷ ህንፃ እስከመግዛት እና ውስጡን በአዲስ መልካ አድሳ በሊቃነ ጳጳሳት አስባርካ ለመግባት ችላለች።


ይህ በእንዲህ እያለ ግንቦት 12/2010 ዓም ለቤተ ክርስቲያን ህንፃ ግዢ የበኩላቸውን ያገለገሉ ወንድሞች እና እህቶችንን እና ታዳጊ ወጣት ዲያቆናትን አቡነ ኤልያስ እና አቡነ ሚካኤል በተገኙበት በአቡነ ሕርያቆስ አቅራቢነት ከሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ጋር መክረው እንዲሸለሙ አድርገዋል። የሽልማቱን ቪድዮዎች ከእዚህ በታች በክፍል አንድ እና ሁለት ይመልከቱ።የእዚህ አይነቱ አገልግሎት ለሌሎች አጥብያዎች ትምህርት እንደሚሆን አያጠራጥርም።የኖርዌይ መካነ ቅዱሳን ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለ ሐይማኖት ቤተ ክርስቲያን የህንፃ አሰሪ ኮሚቴ አሰራር ናሙና ለሌሎች አጥብያ አብያተ ክርስቲያናት መልካም ናሙና (model) አሰራሮች ስላሉት ከመዋቅር እስከ ስብሰባ አመራር እና ስራዎች ሂደት አንድ ወጥ የሆነ ባለ ጥቂት ገፆች ዝርዝር ማስታወሻ በአነስተኛ መፅሐፍ መልክ ለየትኛውም አጥብያ እንዲረዳ በታሰበ መልክ እንዲያዘጋጁ በእዚህ አጋጣሚ አደራ ማለት እንፈልጋለን።የእዚህ አይነቱ በፅሁፍ የሚቀመጡ አሰራሮች ወደፊት እየዳበሩ ሄደው ለቤተ ክርስቲያናችን አሰራር ማንዋል ደረጃ ሊጠቅሙ ይችላሉ።ምክንያቱም የችግሮች መፍትሄዎች የሚገኙት ከተጨባጭ የአሰራር ሂደት ውስጥ ከሚያጋጥሙ መሰናክሎች እና እነኛን መሰናክሎች እንዴት እንደተፈቱ ለሌሎች በጽሁፍ በማስቀመጥ ነው።  

ክፍል አንድ  
ቪድዮ በጉዳያችን
ቪድዮ በጉዳያችን

 ክፍል ሁለት  



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Tuesday, May 15, 2018

በኢ/ኦ/ተ/ የኖርዌይ ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለሐይማኖት ቤተ ክርስቲያን አዲስ የገዛችውን ህንፃ ቤተ ክርስቲያን በእዚህ ሳምንት በሶስት ጳጳሳት ታስባርካለች።ዝርዝር የበዓሉ መርሐግብር ወጥቷል።



ጉዳያችን / Gudayachn
ግንቦት 8/2010 ዓም (ሜይ 16/2018 ዓም)

  • ዘማሪ ይልማን ጨምሮ ከልዩ ልዩ የዓለም ክፍል ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይገኛሉ፣
  • ከኖርዌይ መንግስት ልዩ ልዩ ቢሮ ኃላፊዎች ይገኛሉ።
  • ከቤተ ክርስቲያን ቡራኬ በተጨማሪ በዓለ ንግስም አለ።
  • ሰማይ ተከፈተ (መዝሙር ከጽሁፉ መጨረሻ ያድምጡ) 

የኖርዌይ ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለሐይማኖት ቤተ ክርስቲያን አዲስ የተገዛው ህንፃ ቤተ ክርስቲያን በእዚህ ሳምንት በሶስት ጳጳሳት ማለትም በአቡነ ኤልያስ፣ አቡነ ሚካኤል እና አቡነ ሕርያቆስ ታስባርካለች።በቤተ ክርስቲያኒቱ ድረ ገፅ ላይ የወጣው መረጃ  እንደሚያሳየው ከግንቦት 10 እስከ 12/2010 ዓም የቤተ ክርስቲያን ቡራኬ አስታኮ ከሚኖረው ልዩ ጉባኤ  በተጨማሪ ግንቦት 12 የሚከበረው የአቡነ ተክለ ኃይማኖት ዓመታዊ በዓል (ፍልሰተ አፅም)  እሁድ ብፁዓን አባቶች በተገኙበት ታቦታት ከመንበራቸው ተነስተው ዑደት እንደሚያደርጉ እና በዓለ ንግሥ መኖሩ ተጠቅሷል።

በእዚሁ የሶስት ቀናት ጉባኤ እና አዲስ ቤተ ክርስቲያን ቡራኬ ከብፁዓን ጳጳሳት በተጨማሪ ዘማሪ ይልማ ኃይሉ ከአሜሪካ፣ መላከ ሕይወት ቀሲስ ጌጡ ከስዊድን፣መጋቢ ሐዲስ ቀሲስ አባተ ከእንግሊዝ፣ መላከ ኃይል ቀሲስ ታደሰ ከጉቶቦሪ ስዊድን እና ሌሎች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ ሲሆን ጥሪ የተደረገላቸው ከኖርዌይ ቤተ ክርስቲያን እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የኖርዌይ መንግስት ቢሮ ልዩ ልዩ ክፍል ኃላፊዎች  በእሁዱ መርሃ ግብር ላይ እንደሚገኙ እና በኖርዌይ ቋንቋ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣አገልግሎት እና ማኅበራዊ ሱታፌ ማብራርያ ይሰጣቸዋል።

በሌላ በኩል ከቤተክርስቲያኒቱ የአይቲ ክፍል ለመረዳት እንደተቻለው በሶስቱ ቀናት የሚኖረው መርሐ ግብር በቤተ ክርስቲያኒቱ የፌስ ቡክ ገፅ (የፌስ ቡክ ገፁን ለመክፈት ይህን ይጫኑ) በቀጥታ ስርጭት እንደሚሸፈን ለማወቅ ተችሏል። ከእዚህ በታች ከቤተ ክርስቲያኒቱ ድረ ገፅ (ድረ ገፁን ለመክፈት እዚህ  ይጫኑ) የተገኘው የሶስቱ ቀኖች መርሐ ግብሮች ማጠቃለያ  ይመልከቱ።

መዝሙር ሰማይ ተከፈተ (ያድምጡ)



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Monday, May 14, 2018

ከ40 ዓመታት በላይ የዘለቀው የኢትዮጵያ የለውጥ እንቅስቃሴ ጥሩ ማሳረጊያ ያለማግኘቱ ለምን ይሆን? (ኦድዮ)

ሸገር ኤፍ ኤም ራድዮ ''መንግስት እና ዲሞክራሲ፣ዘመናዊነት፣ ዝመና እና ልማት'' በሚሉ ፅንሰ ሐሳቦች ዙርያ ሸገር ካፈ በተሰኘ ሳምንታዊ መርሐግብር ተወዳጇ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ምሁራንን የምታወያይበት ተከታታይ ዝግጅት ዘወትር ዕሁድ ረፋድ ላይ እየተላለፈ ነው።ከእዚህ በታች ባለፈው ዕሁድ ግንቦት 5፣2010 ዓም የተላለፈውን ያድምጡ።

ምንጭ :- ሸገር ኤፍ ኤም ራድዮ ዩቱብ



ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

Wednesday, May 9, 2018

ሰሚ ያጣው የአማራ ዘርን የማፅዳት እኩይ ተግባር ፍትሃዊ የተባለ ጦርነት ሊያስነሳ ይችላል። Ignorance of Ethnic cleansing on Amhara nationality in Ethiopia can follow a new unrest in the country.

ጉዳያችን / Gudayachn
ግንቦት 1/2010 ዓም (ሜይ 10/2018)

በእዚህ ፅሁፍ ውስጥ :- 

  •  አማራ በመባል ብቻ የተባረሩ ኢትዮያውያን ላይ የተሰራ ዜና በኢትዮያ ቴሌቭዥን (ቪድዮ)፣
  • ባህር ዳር የሚገኘው የአማራ ብዙሃን መገናኛ ቴሌቭዥን ዘገባ (ቪድዮ) ፣
  • የአሜሪካ ራድዮ ጣብያ ዘገባ (ኦድዮ) እና 
  • የቀበሌ ሊቀመንበር ሰዎች አማራ በመሆናቸው ብቻ ለቀው እንዲወጡ ያዘዘበት ደብዳቤ ቅጅ ተያይዟል። 

በኢትዮጵያ አማራ በመሆናቸው ብቻ ከሁለት ትውልድ በላይ የኖሩበትን ቀዬ ለቀው እንዲባረሩ የተደረጉ በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።ከጉርዳፈርዳ እስከ ኢልባቦር፣ ከሐረር እስከ ጅጅጋ፣ከቤንሻንጉል እስከ ሰሜን ጎንደር ወልቃይት አማራ ናችሁ ተብለው በአደባባይ እየተነገራቸው በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተመፅዋች ሲሆኑ፣የከተማ ጎዳና ተዳዳሪ ሲሆኑ እና እርጉዞች ሳይቀሩ ጫካ እየወለዱ የሚቀምሱት እያጡ ሲሞቱ የኢትዮጵያ ሕግም ሆነ በሔራዊ እየተባለ የሚነገርለት የጦር ሰራዊት እንዲሁም በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ አንዳች ነገር ሲያደርግ አልታየም።

ችግሩ ከአቶ መለስ ዘመን ጀምሮ ከፓርላማ እስከ ወረዳ ስብሰባ፣ከኢቲቪ እስከ ኢሳት ቴሌቭዥን ከአሜሪካ እስከ ጀርመን ራድዮ ሁሉም በተመሳሳይ የደረሰውን የዘር ማፅዳት እኩይ ተግባር ዘግበውታል።ሆኖም ግን የአራት ኪሎ ባለስልጣናት አንዳች እርምጃ ሲወስዱ አልታየም።ይልቁንም በህዝባዊ አመፅ ወቅት ስለጠፋ ንብረት በእየመድረኩ በዲስኩር ሲያደምቁ ማየት ተለምዷል።ጉዳዩ አሁን እጅግ የመረረ ደረጃ ደርሷል።በተለይ ታች ያለው ሕዝብ ዘንድ የመጨረሻ የሚባል ደረጃ እንደደረሰ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። የአማራ ተወላጆች እንደ ቤንሻንጉል ከመሳሰሉት ቦታዎች ሲባረሩ ጉዳዩ የሃይማኖት ጥላቻ መነሻ እንደሆነ እየታየም ነው።የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ መሆናቸው ብቻ እንዳሰደዳቸው ብዙ መረጃዎች መጥቀስ ይቻላል።በክልል ስልጣን ላይ የሚገኙት የፅንፈኛ እምነት አራማጅ ከሆኑ የመጀመርያ ኢላማቸው አማራ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ ላይ ነው።

የአማራ ተወላጆች ከቀያቸው እንዲወጡ ተደረጉ የሚል ዜና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ሲወራ እንደ አንድ ቀላል ዜና የዜናው አንባቢውም ሆነ ሰሚው እንደ ቀላል ጉዳይ ሰምቶ ከንፈር የሚመጠውም ሆነ እንዳልሰማ የሚያልፈው እኩል የጆሮ ጠገብ አይነት ዜና ሆኗል።ሆኖም ግን እታች ያለው የተጎዳው ሕዝብ መሃል የፈጠረው ምሬት እና በቀላሉ የማይሽር የማኅበራዊ ቀውስ ነገ ለምትኖረው ኢትዮያ ብቻ ሳይሆን በቅርብ ለሚኖር ማናቸው የጦርነት አደጋ ቅርብ ነው።አንድ ሕዝብ ህገ መንግሥቱም፣ሠራዊቱም መገናኛ ብዙሃኑም፣የሃይማኖት አካላትም ሆነ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በዘሩ ብቻ ተለይቶ መጠቃቱ እያወቁ ዝም ካሉት በመጨረሻ ''በችግር ጊዜ ከወንድም በላይ ነች'' የሚላትን ጠብመንዣውን ይዞ ይነሳል።በእዚህ መሃል የሚወጣ መሪ ደግሞ እስከ ምድር ጫፍ ድረስ ማንንም እየጠረገ የሚያስኬድ የብሶት ማስታገሻ አቅም ይኖረዋል።

የአማራ ተወላጅ በኢትዮጵያ የነፃነት ታሪክም ሆነ የነፃነት ትግል ውስጥ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር አብሮ የወደቀ የተነሳ፣ በቅኝ ገዢ ኃይሎች በተለየ መጠቃት አለበት ተብሎ አዋጅ የወጣበት ሕዝብ ለመሆኑ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።ፋሽሽት ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረበት ዘመን በዋናነት በትኩረት የሰራው ተግባር ቢኖር የጎሳ ልዩነት ለመፍጠር መሞከር ነበር።

ለማጠቃለል ከእዚህ በታች የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን፣ኢሳት ቴሌቭዥን፣የአሜሪካ ድምፅ አማርኛ አገልግሎት እና ባህርዳር የሚገኘው ክልላዊ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ሁሉም በአማራነት ሰዎች እየተለዩ መባረራቸውን በማስረጃ እያስደገፉ ዜናውን አቅርበዋል።ሆኖም ግን መፍትሄ የሚሰጥ አካል የለም።ይህ መፍትሄ የማጣት ችግር ከአራት ኪሎ ቤተ መንግስት ብቻ ሳይሆን የሕዝቡን መንገላታት የሚመለከተው ስደተኞቹን የሚቀበለው የባህርዳር ከተማ ህዝብን ጨምሮ የክልሉ ባለስልጣኖች ጨምሮ የሚጠበቀውን ያህል እንቅስቃሴ አላደረጉም።ይህ ሁሉ ሲደመር ፍትሃዊ ያለውን ጦርነት ሕዝቡ በማናቸውም ሰዓት ቢያውጅ ድንገት ደራሽ ሊባል አይችልም። ለሁሉም መፍትሄው ግን አሁንም በሕግ እና በሥርዓት የምትመራ ኢትዮጵያን ማምጣት የግድ አስፈላጊ ነው።ይህ ማለት ከእዚህ በፊት ለተገፉት ካሳ ሰጥቶ መልሶ ማስፈር እና ሕዝብ በማባረር የተሳተፉትን ለፍርድ ማቅረብ ሁሉ ይጨምራል።
ከእዚህ በታች አማራ በመባል ብቻ የተባረሩ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ዓለም አቀፍ እና ብሔራዊ የዜና ማሰራጫዎች የተላለፉ ዜናዎች በናሙናነት ተመልከቱ።
Ethiopian National Television report on Amhara Nationality Ethnic cleansing in Ethiopia (video)
የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ግንቦት 8/2018 እኤአ ያስተላለፈው

Amhara Mass Medea report on Amhara cleansing report from Bahir Dar city

ባህርዳር ከተማ የሚገኘው የአማራ ክልል መንግስት  ቴሌቭዥን በግንቦት 7/2018 እኤአ ያስተላለፈው 


Voice of America Amharic service report  on Amhara cleansing on May 2,2018
የአሜሪካ ድምፅ ራድዮ የአማርኛው አገልግሎት ግንቦት 2/2018 እኤአ የዘገበው 

ESAT  News on Amhara nationality ethnic cleansing (report from Washington DC)
ኢሳት ቴሌቭዥን ከሁለት ዓመት በፊት የዘገበው 



አማራ በመሆናቸው ብቻ ለቀው እንዲወጡ በቀበሌ ሊቀመንበር መጋቢት 10/2010 ዓም የበሎ ዴዴሣ  ቀበሌ መስተዳደር ዴዴሣ የተለጠፈ ደብዳቤ
Benishangule local authority public notice on Amhara nationality to leave their permanent place with in the region. The Federal government did not take any action for such ethnic cleansing public notice.

የበሎ ዴዴሣ  ቀበሌ መስተዳደር
ዴዴሣ

ቀን 16/7/2010 ዓም 

ማሳሰቢያ:_ ለበሎ ዴዴሣ  የአማራ ነዋሪዎች በሙሉ

ይኸውም የአማራ ተወላጆች ለሆናችሁ በሙሉ እስከ መጋቢት 30/7/2010 ዓም ድረስ ወይም እስከ ሚያዝያ 10/8/2010 ዓም ሀብታችሁን ሆነ ንብረታችሁን ሸጣችሁ ሆነ አርዳችሁ  የማትወጡ ከሆነ   ግን  በሕግ ተገዳችሁ  እየታሰራችሁ  ወዳችሁ ሳይሆን  በግድ  ተገዳችሁ  በህግ የምትወጡ መሆኑን  እስከተሰጠው  ጊዜ ገደብ  ካልወጣችሁ  በሚደርስባችሁ ችግር  የቀበሌው መስተዳደር ተጠያቂ አለመሆኑን  በዚህ ደብዳቤ መግለፃችን  እናስታውቃለን

ምንጭ : - ጌታቸው መታፈርያ 




ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Friday, May 4, 2018

ሰበር ዜና - በውጭ እና በሀገር ቤት ባሉ የኢ/ኦ/ተ/ ቤ/ክርስቲያን አባቶች መሃል አዲስ ንግግር ሊጀመር ነው

ሰበር ዜና - ጉዳያችን (ኦድዮ) በሀገር ቤት እና በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል አዲስ ንግግር ሊጀመር ነው።
ዜናውን ለማዳመጥ ይህንን ይጫኑ።https://www.youtube.com/watch?v=NKAtDq5-WMw&feature=youtu.be

ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

በሚጠበቀው እና በሚሆነው መካከል ያለው ልዩነት ዜሮ ካልሆነ የእርስ በርስ ጦርነት ያሰጋናል። (Expectation - Actual= 0)።(የጉዳያችን ማሳሰቢያ)

ጉዳያችን / Gudayacn
ሚያዝያ 26/2010 ዓም (May 4/2018 ዓም)
---------------------------------
ከላይ የተሰጠው  ርዕስ የተጋነነ የሚመስለው ካለ እንዳልተጋነነ ቢረዳው ደስ ይለኛል።ይህ የግል አስተያየቴ ነው።አጉል ትንቢት ግን አይደለም።ዶ/ር ዓብይ  በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየሙ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ውጥረት ላይ ደርሶ የነበረው የሀገሪቱ የፖለቲካ ውጥረት የረገበ የመሰለው በአጭር ዕይታ ተስፋ ከንግግራቸው ብዙዎች በመሰነቃቸው ነው።ይህ ተስፋ እና እንዲሆን የሚጠበቀው እና የሚሆነው መካከል ልዩነት ከተፈጠረ ከፍተኛ አደጋ እስከ እርስ በርስ ጦርነት የሚያስነሳ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ  ሁኔታ በኢትዮጵያ ሊፈጠር ይችላል።ዶ/ር ዓብይ በፍጥነት እየተዘዋወሩ ንግግር ማድረጋቸው፣ሕዝብ ብሶቱን ሲናገር ማድመጥ በእራሱ የፈጠረው በጎ ተፅኖ አለ። ይህ ተፅኖ ግን በጣም ጊዜያዊ እንጂ ዘለቂታዊ አይደለም።ዘለቂታ የሚሆነው በሚጠበቀው እና በሚሆነው መካከል ያለው ልዩነት ዜሮ ከሆነ ብቻ ነው (Expectation - Actual= 0)

ችግሩ 
====
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሕግ አስፈፃሚው በህወሓት ስር፣ሕግ አውጭው በተከፋፈለ ሁኔታ እና የተፅኖ መጠናቸው ያልለየው ዶ/ር ዓብይ ደግሞ የትኛው ጋር እንደሆነ የማስፈፀም አቅማቸው ገና አልታየም። ይህ እጅግ አደገኛ ሁኔታ ይመስለኛል።ዶ/ር ዓብይ በጎ ህሊና አሳይተዋል።ኢትዮጵያ እንዴት ብትሄድ ሃሳባቸውን አካፍለዋል።በልካም  ነው።ይህ ማለት ሕዝብ ከመንግስት የሚፈልገውን የለውጥ ፍላጎት አፅንተውታል ማለት ነው። አሁን ችግሩ በሚጠበቀው እና በሚሆነው መካከል ልዩነት በታየ ቁጥር ባልተጠበቀ መልኩ ግጭት ሊፈጠር ይችላል።የሚጠበቀው  ለውጥ እንዳይደረግ በዋናነት ያለው እንቅፋት አሁንም የሴራ ፖለቲካ የተለያየ የጥቅም ፍላጎት ያላቸው አካሎችን የማነሳሳት እና ቅራኔዎችን የማስፋት ተግባር በአናንድ ፅንፈኛ የህወሓት አካላት እየተፈፀመ ስለሆነ ነው።

መፍትሄው
======
ለኢትዮጵያ መጪ መፍትሄ ዋናው እና ዋናው ዋስትና ሁሉንም አካል ያሳተፈ የሽግግር መንግስት ወደ መመስረት ሂደት መግባት እና መጪ የምርጫ ሁኔታን ማመቻቸት አስፈላጊ ነው። ይህ ማለት አሁን ያለውን የሲቪልም ሆነ የወታደራዊ መዋቅር ማፈራረስ ሳያስፈልግ ሆኖም ግን አሰራሩም ሆነ የሰው ኃይሉ በጎሳ  ላይ የተመሰረተ ግንኙነቱን ማጥፋት እና ኢትዮጵያዊ አቅሙን መገንባት ማለት ነው።ሁሉን ያሳተፈ ሽግግር መንግስት ለመመስረት ዶ/ር አብይ አሁኑኑ መስራት ያለባቸው ሰባት  ዋነኛ ተግባራት የሚመስሉኝ እነኝህ ይመሳሉኛል። እነርሱም
1ኛ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በፍጥነት ማንሳት፣
2ኛ) የሽብርተኝነት ሕጉን መሻር፣
3ኛ) ሁሉን ያሳተፈ የሽግግር ምክር ቤት መመስረት እና ፍኖተ ካርታውን፣እቅዱን በግልጥ ማስቀመጥ፣
4ኛ) የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት መስጠት፣
5ኛ) የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞችን በሙሉ መፍታት ።
6ኛ) የሕግ የበላይነት ብቻ እና ብቻ የእያንዳንዳንዱ ግለሰብ ዋስትና መሆኑን በሚገባ ማሳየት ይህንንም ተከትሎ በግል፣በሕቡ እየተደራጁ ሕዝቡን የሚያስፈራሩ የህወሓት ፅንፈኛ ክፍሎችን የሚገታ ሕግ ማውጣት እና አሰራሩም ግልጥ ማድረግ፣
7ኛ) የሲቪክ ድርጅቶች፣የሙያ ማኅበራት እና ዜጎች የመደራጀት መብታቸውን ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ
የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።

ማጠቃለያ 
=======
ለማጠቃለል አሁን ባለው ሁኔታ ተስፋ ያልቆረጡ ፅንፈኛ የህወሓት አካላት ወደ ለውጥ የሚሄደውን የለውጥ ኃይል የመገዳደር እጅግ አደገኛ አካሄድ እያሳዩ ነው።ይህ ሁኔታ ዶ/ር ዓብይን የሚያስወቅስ አድርገው በማሰብ በጣም የብልጣብልጥነት ሥራ እየሰሩ እንዳሉ ለአድናቂዎች በመንገር እጅግ ወደ አደገኛ መንገድ ሕዝቡን እና ኢትዮጵያን እየመሯት ነው።ግጭቶች በእየቦታው እየፈነዱ ነው፣ምጣኔ ሃብቱ መንኮታኮቱን ቀጥሏል።የስራ አጡ ብዛት ጨምሯል፣የህዝብ ቁጥር እያደገ ነው፣የጎሳ ቁርሾው ለውጥ ካጣ ሊባባስ ይችላል፣ ይህ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ግጭትም ሊያስከትል ይችላል።ስለሆነም ሕዝብ ከሚጠብቀው ለውጥ ያነሰ ሳይሆን ከጠበቀው በላይ በመሄድ ብቻ ነው ሀገር ማረጋጋት የሚቻለው።
ዶ/ር  ዐብይ ያላቸው አንድ ምርጫ ብቻ ነው።ለውጡን ሕዝብ በሚጠብቀው መጠን ወይንም ከጠበቀው በላይ እንዲሄድ ማድረግ ካልቻሉ የችግሩ ፈጣሪዎችን በግልጥ ለሕዝብ መንገር።ከእዚህ ባነሰ ችግር የሆነውን የኢትዮጵያን ጉዳይ ነካክተው መተው አደጋ አለው።ቆሻሻ ከነካኩት የበለጠ ይሸታል።ከነካኩ ማስተካከል ይፈልጋል።ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ ልትቀጥል አትችልም።ለውጡ በዘገየ ቁጥር ወደ እርስ በርስ ጦርነት የማምራት አደጋው ይጨምራል። ይህ ተራ ግምት አይደለም።ከግምት በላይ ነው።ለለውጡ ህወሓት ከልብ፣ከልብ ቢያስብበት እና ከለውጥ ያነሰ ነገር ሁሉ የበለጠ አደጋ መሆኑን ከልብ ማመን አሁንም በጣም ይጠበቅበታል።ልመናም ጭምር ነው። ይህንን የምለው የሚመጣው አደጋ ከአሁኑ የከፋ መሆኑን በእርግጠኝነት ማወቅ ስለሚቻል ነው።''ሰይጣንን አንድ ቀን ቢገለጥ ኖሮ ሰው ሁሉ ልመንን ይል ነበር'' እንዳሉት አባት ለለውጥ ካለመዘጋጀት የተነሳ ወደፊት የሚመጣው አደጋ እጅግ የከፋ ነው።ዛሬ ግን በፍጥነት ወደ ቀና ለውጥ መምጣት ብልህነት ነው። ዶ/ር ዓብይም ከእዚህ በኃላ ምንም ደቂቃ ባያጠፉ እና ፍፁም የሆነው ለውጥ ሁሉን ያሳተፈ አካል ምስረታ ላይ ዋስትናው ላይ አሁኑኑ ሥራ ወደመጀመር ቢሄዱ ጥሩ ነው።



ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

Wednesday, May 2, 2018

በኖርዌይ፣ኦስሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የገዛችውን ህንፃ ቤተ ክርስቲያን ልታስባርክ ነው።የሶስት ቀናት ልዩ መንፈሳዊ ጉባኤም አዘጋጅታለች።

ጉዳያችን / Gudayachn
ሚያዝያ 25/2010 ዓም (ሜይ 4/2018 ዓም)

በኖርዌይ፣ኦስሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ከስድስት ወራት በፊት ከፍተኛ ውድድር ከተካሄደበት ጨረታ በኃላ በእግዚአብሔር ፈቃድ  ህንፃ ቤተ ክርስቲያን መግዛቷ ይታወቃል።ህንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ቀድሞም በቤተ ክርስቲያንነት ኖርዌይ ስትጠቀምበት የነበረ ሲሆን ህንፃው በ1900 ዓም እ ኤ አ የተመሰረተ እና  በአሁኑ ሰዓት ህንፃው  ውስጣዊ ክፍሎቹ ላይ አንዳንድ መጠነኛ የፅዳት እና የጥገና ስራዎች እየተሰሩ ነው።
በመሆኑም የህንፃው የውስጥ ክፍል ፀድቶ እና ተስተካክሎ ግንቦት 11/2010 ዓም (ሜይ 19፣ 2018 ዓም) ህንፃ ቤተ ክርስቲያኑ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እንደሚባረክ ለማወቅ ተችሏል። 

ከእዚህ በተጨማሪ የቅዳሴ ቤቱን ቡራኬ አስታካ ቤተክርስቲያኒቱ የሶስት ቀናት ልዩ መንፈሳዊ ጉባኤም  አዘጋጅታለች። ስለሆነም ጉባኤው ከዓርብ ግንቦት 10 እስከ ግንቦት 12/2010 ዓም (ሜይ 18 እስከ 20/2018 ዓም) የሚቆይ ሲሆን ቅዳሜ ግንቦት 11 (ሜይ 19) የቤተ ክርስቲያን ቡራኬ በብፁዓን ጳጳሳት እንደሚከናወን እና እሁድ ቅዳሴ እና በዓለ ንግሥ እንደሚኖር ለማወቅ ተችሏል። በቤተ ክርስቲያኑ ቡራኬ ላይ እስካሁን አቡነ ሚካኤል እና አቡነ ኤልያስ የሚገኙ ሲሆን መንበራቸው ኦስሎ ላይ የሆነው አቡነ ሕርያቆስ የኖርዌይ፣ኦስሎ ቅዱስ ገብርኤል አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ እና የአቡነ ኤልያስ ልዩ ረዳት ከብፁዓን አባቶች ጳጳሳት ጋር በቡራኬው ላይ የሚገኙ እና አባቶችን በሀገረ ስብከታቸው የሚያስተናግዱ መሆናቸውን ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።(ስለ አቡነ ሕርያቆስ የቀደሙ አገልግሎቶች ለማንበብ ይህንን ይጫኑ)።

በቤተ ክርስቲያኒቱ ቡራኬ ክብረ በዓል ላይ ከብፁዓን ጳጳሳት በተጨማሪ መላከ ሕይወት ቀሲስ ጌጡን እና ዘማሪ ይልማ ኃይሉን ጨምሮ ሰባክያነ ወንጌል እና ካህናት እንዲሁም ከልዩ ልዩ የአውሮፓ እና ኖርዌይ ክፍል የሚመጡ ምዕመናን እንደሚታደሙ ለማወቅ ተችሏል።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በዘንድሮ ዓመት ብቻ በአውሮፓ ውስጥ በሚገኙ አራት ሀገሮች ማለትም እንግሊዝ፣ጀርማን፣ኖርዌይ እና ግሪክ የእራሷን ህንፃ ቤተክርስቲያን ገዝታለች።

ከእዚህ በታች የኦስሎ ኖርዌይ ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አዲስ የተገዛው ህንፃ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በእዚህ ሳምንት ስያፀዱ የሚያሳዩ ፎቶዎች ይመልከቱ።


ህንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ከዋና የኦስሎ ከተማ እንብርት በቅርብ እርቀት የሚገኝ ሲሆን የተሰራው በ1900 ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ነበር። 

 የቤተ ክርስቲያኑን የውስጥ ክፍል ምዕመናን በፅዳት ላይ ሚያዝያ 23/2010 ዓም (ፎቶ ጉዳያችን)
አቡነ ሕርያቆስ አዲሱ ቤተ ክርስቲያን ፅዳት እና እድሳት ሲከታተሉ ሚያዝያ 23/2010 ዓም (ፎቶ ጉዳያችን)





ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com