ፎቶ ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የ2017 ዓም የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ መትከል ብሔራዊ ዘመቻ ሲከፍቱ።
=========
ጉዳያችን ምጥን
========
በእዚህ ጽሑፍ ስር ሶስት ምጥን ርዕሶች ያገኛሉ። እነርሱም
- አመንክም አላመንክም ኢትዮጵያ ተነስታለች ፡
- የአቶ ኢሳያስ አፈወርቅ ወደ አክቲቪስትነት መቀየር እና
- የእነ ''ካፈርኩ አይመልሰኝ'' አክቲቪስቶች ግራ መጋባት።
መንደርደርያ
የኢትዮጵያ ያለፉት ሰባት ዓመታት የለውጥ ሂደት የጎጥ ፖለቲካ በአደባባይ የሚያራምደውን፣የጎጥ ፖለቲካን በኢትዮጵያ ስም ሸፍኖ ሲያራምድ የነበረው እና የባዕዳንን ጥቅም በኢትዮጵያ ውስጥ ተደብቆ የሚያራምደው ሁሉ በጊዜው በጊዜ እየጠለለ መምጣቱን በግልጽ አሳይቷል።ጊዜ፣ተግባር እና ባሕሪ ማን ለኢትዮጵያ እንደቆመ፣ማን ለጥቅሙ ሲጋጋጥ እንደነበር፣ማን ስጋ በተጠበሰበት ሁሉ እያሸተተ ለሆዱ በህዝብ ስም ሲምል እንደነበር የታየበት ጊዜ ነው።
የኢትዮጵያ ልቀት፣ቁልፍነት እና ወሳኝነት በዓለም ጂኦ ፖለቲካ ውስጥ ከመቼውም ጊዜ መጉላት በበቂ መረጃ እና በረጅም ጊዜ የኢትዮጵያንና የምስራቅ አፍሪካን ፖለቲካዊ ሁኔታ በደንብ ላልተረዳ አይገባውም። ችግሩ በለብለብ እና ስሜታዊ የዩቱብ ፎካሪዎች የወቅቱን ሀገራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ጉዳይ ለመረዳት፣ለመተንተን ደፋሮች እንደመረጃ ምንጭ እየወሰደ አዕምሮውን ለሚያጭቅ የኢትዮጵያ ወሳኝ ሆና መውጣት አይገባውም።
ይገርማል! የመቶ ዓመታት ታሪክ ብናወራ ሊያከራክረን ይችላል። ያለፉት ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሂደት ከቀደመው ጋር አያይዞ እና መጪውን አሻግሮ ተረድቶ በበቂ መረጃ መለካት አለመቻል ምን ዓይነት ከዕውቀት ነጻ የመሆን በሽታ ነው? ዩቱብ ላይ እየተሰቀሉ ኢትዮጵያ ላይ መዓት ሲያወርዱ የነበሩ በተናጥል መጮሁን ህዝብ እየነቅ ሲመጣ በቡድን እንጩህ የሚል አዲስ ፈሊጥ የኢትዮጵያን እውነተኛ ገጽታ አይቀይርም።
ኢትዮጵያ ዛሬ አመንክም አላመንክም ተነስታለች።
- ኢትዮጵያ የዘመናዊ ትንሳዔ ጊዜዋ ለመሆኑ ብዙ መለኪያዎችን መመልከት ይቻላል
- ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ የቆዩ ነባር የሚዳሰሱ ታሪካዊ ሃብቶቿን እያደሰች ነው።
- ከብሔራዊ ቤተመንግስት እስከ የጎንደር አብያተ መንግስታት የታደሱት ባለፉት 7 ዓመታት ነው።
- ከጅማ አባ ጅፋር ቤተመንግስት እስከ ብሔራዊ ቲያትር፣ሀገርፍቅር ቲያትር እስከ የአክሱም ሃውልት እድሳት የተከናወነው እና እንቅስቃሴው ይተጀመረው ባለፉት 7 ዓመታት ነው።
- ከመቶ ዓመታት በላ ያስቆጠረችው አዲስ አበባ ከተማ በታሪኳ ባላያችው ደረጃ በዓለም ዘመናዊ ከተሞች የሚያሰልፋት ድንቅ እመርታ ያሳየችው ባለፉት 7 ዓመታት ውስጥ ነው።
- ከመቶ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን በዘመኑ ያልነበረ 80 ሚልዮን ህዝብ በላይ ተደራሽ የሆነው ከእዚህ ውስጥ ከ 43 ሚልዮን በላይ የኢንተርኔት ተደራሽ የሆነው እና በሞባይል ባንኪንግ ትሪልዮን ብር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተንቀሳቀሰው ባለፉት 7 ዓመታት ነው።
- ኢትዮጵያ ከመቶ ሚልዮን በላይ የሚሆን ህዝቧን ለመመገብ ቆርጣ የተነሳችው ብቻ ሳይሆን ምግብ ከውጭ መግዛት ማቆም እንደሚቻልና ከበጋ ክረምት ማምረት ባሕል እንዲሆን እየሰራች ያለው ባለፉት 7 ዓመታት ውስጥ ነው።
- የኢትዮጵያ መከላከያ ከ 1 ሚልዮን በላይ መድረሱ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ስትራቴጂስት የተራቀቁ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ አመራሮች እና መኮንኖች የተሞላው ባለፉት 7 ዓመታት ነው።
- የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአፍሪካ ምርጦቹ ውስጥ ብቻ ሳይሆን የራሱን ትጥቅ በራሱ መንገድ ከማዘመን ባለፈ ይድሮን አምራች የሆነው ባለፉት 7 ዓመታት ነው።
- በአፍሪካ ቀንድ፣በመካከለኛው ምስራቅ እና በዓለም ላይ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ቁልፍነት ከአካባቢ ሀገራት ባለፈ በኃያሉ ሀገራት ዘንድም በጥንቃቄ የሚያዩት እና የኢትዮጵያ ሰላም የብዙዎች የጸጥታቸው ህልውና ጉዳይ መሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ግልጽ የሆነው እና የጎላው ባለፉት 7 ዓመታት ነው።
- ኢትዮጵያ 135 ሚልዮን ሀገር መሆኗ የሰጠው ትርጉም ብዙ ሆኗል። የኢትዮጵያ አብዮት በ1966 ዓም ሲፈነዳ የኢትዮጵያ የህዝብ ቁጥር 30 ሚልዮን ነበር። በወቅቱ የኃያላኑ ፍትጊያ ኢትዮጵያ የያዘችው የህዝብ ቁጥር በራሱ የሚፈጥረው ተጽኖ ከጉዳይ ገብቶ ነበር። በአዲስ አበባ የሩስያ አምባሳደር በወቅቱ ለምን ከሱማሊያ ወደ ኢትዮጵያ ቶሎ እንደዞሩ ሲናገሩ። ''እኛ 30 ሚልዮን ህዝብ ምን ያህል ተጽኖ እንደሚፈጥር ይገባናል።''ነበር ያሉት።
- ዛሬ 135 ሚልዮን ህዝብ ምን ማለት እንደሆነ ማለት ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሯዊው የባሕር በር ማገድ የሚፈጥረው ችግር እራስ ላይ የመተኮስ ያህል መሆኑን ኃያላን መንግስታትም ለመረዳት ብዙ ምርምር አይፈልጉም።
- የውሃ ማማ ኢትዮጵያ ዛሬ በውሃ ማማነት ወሬ ላይ ብቻ አይደለችም ከቀናት በኋላ በዓለም ግዙፍ ከሚባሉት የኤሌክትሪክ ማመንጫ ውስጥ የሚመደበውን የአባይ ግድብ ታስመርቃለች።
- ይህ ግድብ ማለት ብዙ ማለት ነው።ግድቡ ማለት ነዳጅ፣በምስራቅ እና መካከለኛው ምስራቅ ላይ የበላይነት የሚፈጥር ጉልበት እና የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ትንሣዔ አዲስ ምዕራፍ ነው።
- ሌሎች በርካታ ጉዳዮች የኢትዮጵያ መነሳት ዕውን አድርገዋል። ካልገባን ወደፊት እየቆየ ይገባናል። ሌላ ምን ይባላል?
የአቶ ኢሳያስ አፈወርቅ ወደ አክቲቪስትነት መቀየር
- አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ ከ34 ዓመታት በኋላ ጣልያን በቅኝ ግዛት በሰራቸው የድሮ ህንጻዎች ውስጥ የሚኒስቴር መስርያቤታቸውን ብቻ ሳይሆን እራሳቸው እየኖሩ እና ለአስመራ አንድ ለዓይን የሚገባ ህንጻ ሳይሰሩላት እንዲሁ ስለ ጦርነት እያወሩ የአዛውንትነት ዘመናቸውን እየገፉ ነው።
- አቶ ኢሳያስ ከነብረ ባሕሪያቸው በላይ ከሊብያው ጋዳፊ እና ከቀድሞው የግብጹ መሪ ሙባረክ የቆዩ የፖለቲካ ስልት እና የክላሽ ተኩስ ሃሳብ ላይ እያሉ ዓለም የድሮን ቴክኖሎጂ እያለፈ ነው።
- አቶ ኢሳያስ በዘመናቸው ወጣቱን የዓሳ ነባሪ ሲሳይ አድርገው፣ ሌላው ቀርቶ የአስመራ ዩንቨርሲቲ በንጉሱ እና በወታደራዊው መንግስት ዘመን ከነበረበት ደረጃ አውርደው ኤርትራን የዕውቀት አልባ መተራመሻ አድርገዋት ኖረው ዛሬም በመግለጫቸው ስለ የሃገራቸው ልማት ማውራት ትተው በኢትዮጵያ ጉዳይ ይፈተፍታሉ።
- እርጅና የሚያመጣው የራሱ ተጽዕኖ ይኖራል። ሁለት ሰዓት ሙሉ ጋዜጠኞቹ እንቅልፋቸው መጥቶ እስኪንገላጀጁ ድረስ የአዛውንቱን የአቶ ኢሳያስን መግለጫ ሲሰሙ ያሳዝናሉ።
- ከሰሞኑ አቶ ኢሳያስ የኤርትራን የወደፊት የዲሞክራሲ ጉዞ ላይ ለውጥ ያቀርባሉ ሲባል የሚያወሩት ስለ ኢትዮጵያ በቻ መሆኑ አስገራሚ ሆኗል።
- የአቶ ኢሳያስ የሰሞኑ መግለጫ ሲጠቃለል። መግለጫ ከማለት ይልቅ የአቲቪስትነት ሚናቸው የጎላበት ነበር። አክቲቪስትነታቸው ደግሞ ለግብጽም፣ለፋኖም፣ለሸኔም በየደረጃው መሆኑ ያስገርማል።
- መግለጫቸው የአንድ ፖሊሲ አውጪ ቢያንስ የአንድ የፖለቲካ መሪ ደረጃ አያሟላም።
የእነ ''ካፈርኩ አይመልሰኝ'' አክቲቪስቶች ግራ መጋባት።
- ኢትዮጵያ የአንድነትን መንገድ ስትከተል፣መንግስት ስለመተባበር፣የትምህርት ፖሊሲው የሚለያይ እንዳይሆን በሚገባ ይቀረጽ ብሎ ሲሰራ፣ኢትዮጵያ በዘመኗ ያልነበራት የሕጻናት ማስተማርያ ትምሕርትቤቶች ላይ አትኩራ ከስር ለሚመጣው ትውልድ ስትተጋ እና ከተሞቿ ሲዘምኑ በኢትዮጵያ ላይ መዓት ሲያወርዱ የነበሩ የዩቱበር ነጋዴዎች ማፈራቸውን ለመደበቅ ቢጥሩም አልቻሉም።
- አሁን በእዚህ የአክቲቪስት ቡድን ውስጥ የኢትዮጵያ እውነት መደበቅ አልቻለም። ግን አንዴ መስኮት ላይ ወጥቶ መዓት ሲያወራ ስለሰነበተ እያፈራ ብቻውን መውጣት አልቻለም።
- በመሆኑም ሰብሰብ ብለን እንጩህ ምናልባት ህዝብ ቢይምነን ሆኗል ጉዳዩ።
- ነገሩ ''ካፈርኩ አይመልሰኝ '' ነው።
- ማፈር ጤናማነት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ መዓት ስታወርድ ከረምክ።መጨረሻ ሰርቶ አሳየህ አፈርክ። ስታፍር ካፈርኩ አይመልሰኝ ብለህ ተሰብስበህ ያውም የኢትዮጵያን መበታተን ላይ ከሰሩ ጋር እንደ ግሪሳ ተሰብስቦ ውሸት በማውራት አይደለም በኢትዮጵያ ህዝብ በገዛ ቤተሰብህ ትዝብት ላይ ወድቀሃል።
- ካፈርኩ አይመልሰኝ የተም አያደርስም። ይልቁን የተሳሳቱን አርሞ በጋር ለኢትዮጵያ መስራት ብቸኛው አማራጭ ነው። ለእዚህ ደግሞ ከእነካፈርኩ አይመልሰኝ ቡድን በድፍረት ለይቶ ስለ ኢትዮጵያ መመስከር ይፈልጋል። ይሄው ነው።
=====================////============