ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, April 30, 2014

ለሀገራቸው የተሰዉ በርካታ ጀግና ኢትዮጵያውያንን ያፈራችው አምቦ እያነባች ነው።

ለቪኦኤ የአማርኛው አገልግሎት የአይን እማኞችን እንደገለፁት

- ቁጥሩ ያልታወቀ ሰው ተገድሏል፣

- አንድ ባንክ ተቃጥሏል፣

- ሶስት ህንፃዎች ተቃጥለዋል፣

- ብዙ ቤተሰብ ተበታትኖ ከቤት ወጥቶ ይገኛል።

ኢሳት የአይን እማኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው ደግሞ በተማሪዎቹ ላይ እና ህዝቡ ላይ ሲተኩሱ የነበሩት የመንግስት ወታደሮች አልመው የሚተኩሱ ''ስናይፐሮች'' ነበሩ ብሏል።

እጅግ አሳዛኝ ተግባር።ኢህአዲግ በትክክል ሀገር ማስተዳደር አለመቻሉን መግለፅ ያለበት ጊዜ ላይ ነው።ሕይወታቸው ላለፉት ሁሉ እረፍተ ነፍስን ይስጥልን ለቤተሰብ መፅናናንትን። ለሀገራቸው የተሰዉ ጀግና ኢትዮጵያውያንን ያፈራችው አምቦ እያነባች ነው። በኢህአዲግ የሚታዘዙት የመገናኛ ብዙሃን ዝምታ አሳፋሪ ነው።ኢትዮጵያ ልጆቿ በሰበብ አስባቡ እየረገፉባት ነው።



ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG

Tuesday, April 29, 2014

''የፈሪ ዱላው አስር'' ኢህአዲግ ፈርቷል።ለመሆኑ ኢህአዲግ ያሰራቸው ምንም አይነት ድብቅ አላማ የሌላቸው የዞን ዘጠኝ ጦማርያን እና ጋዜጠኞች እነማን ናቸው?



ፍርሃት የማያሰራው ነገር የለም።ኢህአዲግ በከፍተኛ የፍርሃት ማጥ ውስጥ ነው።ሁሉንም ይፈራል።አይዞህ አትፍራ ቢሉትም የሚችል አይመስልም።በሕዝብ ላይ የሰራቸው ሕዝብ የሚያውቃቸው እና የማያውቃቸው ብዙ ድብቅ ስራዎች ስላሉት የመፍራት ደረጃው ከዕለት ወደ ዕለት እየባሰበት እንጂ እየተሻለው አልሄደም። የሚደግፉትም ልያፅናኑት አልቻሉም።ከሚገባው በላይ ፍርሃት ሲያንቀጠቅጠው ሲመለከቱ እነርሱም ይብሱን ፈሩ።ብዙ የስርዓቱ ደጋፊዎች እና በሀብት የደለደሉቱ ሀገር ጥለው እየወጡ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።ይህ ደግሞ ሌላው የፍርሃት ገፅታ ነው።

የዞን ዘጠኝ ጦማርያን እና ሌሎች ሰሞኑን የተያዙት ጋዜጠኞች ምንም የተደበቀ አጀንዳ የሌላቸው ግን ህገ መንግስቱ ላይ የሰፈረው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ይከበር ያሉ በእዚህም መስረት የሕገ መንግስቱን አንቀፅ እየጠቀሱ የሃሳብ የመግለፅ መብታቸውን የተጠቀሙ፣የሚሰሩት በመንግስት መስርያቤቶች የሆነ፣የሚፅፉት አይደለም ምን በልተው ከማን ጋር ውለው እንዳደሩ መንግስት ብቻ ሳይሆን ሕዝብ የሚያውቃቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው።ከእዚህ በፊት በሃሳብ የሞገቱትን ሁሉ ''ህገ መንግስቱን እና ስርዓቱን ለመናድ የተንቀሳቀሱ'' እያለ ሲያስራቸው የነበረው መንግስት ዛሬ እራሱ ህገ መንግስቱን አክብረው ሕግ እየጠቀሱ የፃፉትን በ20 ዎቹ እድሜዎች ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን ''ሃገርን በውጭ ከሚኖር ድርጅት ጋር ተመሳጥረው ሊያሸብሩ'' እያለ ፌዝ አይሉት ቀልድ መሰል ክስ አቅርቦ ማዕከላዊ እስር ቤት አስገባቸው።ምንም አይነት ወንጀል እንደሌለባቸው እራሱ ኢህአዲግ ያውቀዋል።ግፍ መስራት የማይሰለቸው እና በፍርሃት የተዋጠ መሆኑ ግን የእዚህ አይነቱን ተግባር እንዲቀጥልበት አድርጎታል።

''የፈሪ ዱላው አስር'' እንዲሉ የኢህአዲግ አባላት ማታ ኢቲቪ ዜና ላይ የግብፅ፣የየመንን በቅርቡ ደግሞ የዩክረንን የህዝብ ንቅናቄ እያዩ በሰላም መተኛት አልቻሉም።ያ ቀፎው እንደተነካ ንብ የሚተመው ሕዝብ አንድ ቀን እኛም ላይ ይነሳል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል።ለእዚህም ማስረጃው ኢቲቪ ባለፈው ሰሞን ያሳየው የዩክሬንን አመፅ የተመለከተ ፊልም መጥቀሱ ይበቃል።ፍርሃታቸውን ደግሞ እነ ሚሚ ስብሃቱ ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ ገብቶ እንደሚንዘፈዘፍ ሰው እየተንቀጠቀጡ ሲናገሩ ሕዝብ ታዝቦ ''ወይ ፍርሃት'' ብሏል።ግንቦት 20 ስመጣ ጀግና እንደነበሩ ከሃያ ዓመት በፊት የነበሩ አሮጌ ታንኮች ያሳየናል።መለስ ብለው ደግሞ በፈስ ቡክ እና በጡመራ ፈራን ይላሉ።አጀብ ነው።

ኢህአዲግ ፈራሁ ብሎ ያሰራቸው ንፁሃን ጦማርያን እና ጋዜጠኞች እነማን ናቸው? የወጣቶቹን የስራ መስክ ግልፅነት እና ሙያ ተመልክታችሁ ፍረዱ።ለፈሪዎችም እዘኑላቸው።

1/ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ
ለተባበሩት መንግሥታት ዜና አገልግሎት ኢሪን ለረጅም ጊዜ የሰራ የእንግሊዝኛው 'ፎርቹን' ጋዜጣ አምደኛ እና ዘጋቢ

2/ ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ
  አዲስ ጉዳይ መፅሄት ከፍተኛ ኤዲተር
3/ ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ
በአካባቢ ጥበቃ የሰለጠነች በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እና በቀድሞው 'እንቢልታ' ጋዜጣ ዘጋቢ
4/ በፍቃዱ ኃይሉ
የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ፣ብሎገር እና ቅድስት ማርያም ዩንቨርስቲ በሙያው የሚሰራ
5/ አቤል ዋበላ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ የአየር መንገዱ 'ግራውንድ ቴክኒሻን' 
6/ ማህሌት ፋንታሁን
የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምሩቅ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሰራተኛ
7/ አጥናፍ ብርሃኔ
የ25 ዓመት ወጣት በፌስ ቡክ ሃሳቡን የሚገልፅ በብሎጉ ላይ ሃሳቡን የገለፀ
8/ ናትናኤል
የ 26 ዓመት ወጣት የኢኮኖሚ ባለሙያ፣'የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር' አባል
9/ ዘላለም ክብረት
የሕግ ባለሙያ፣ማስተርሱን ከሰራ ገና ሳምንታት የሆነው በአምቦ ዩንቨርስቲ የሕግ ትምህርት መምህር ናቸው።

ምንጭ - ከጦማርያኑ ውስጥ በውጭ ሀገር የሚገኙት እንዳልካቸው እና ሶልያና ለቪኦኤ የአማርኛው አገልግሎት ሚያዝያ 20/2006 ዓም ከሰጡት መግለጫ የተገኘ።

ጉዳያችን
ሚያዝያ 21/2006 ዓም

Sunday, April 27, 2014

የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን መተግበር ሌላ፣ ኦሮምኛ ተናጋሪ ገበሬዎችን በግፍ ከመሬታቸው መንቀል ሌላ ፣ኦሮምኛ ተናጋሪ ገበሬዎችም ከኢትዮጵያ ሌላ ሀገር የላቸውም።

አዲስ አበባ ዙርያ ገበሬዎች በእርሻ ላይ 

አዲስ አበባ ከ 3.5 ሚልዮን ሕዝብ በላይ ውሎ ያድርባታል።ከተማዋ አሁን ካላት የህዝብ ብዛት በላይ እንደምትጨምር ሳይታለም የተፈታ ነው።ገጠር ወደ ከተማነት እየተቀየረ ይመጣል እንጂ ከተማ ወደ ገጠርነት ሊቀየር አይችልም።ዕድገት ባለፈ ታሪኩ ያስመሰከረው ይህንኑ ነው።

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማን ለማስፋፋት ከተያዘው ማስተር ፕላን አንፃር ከተማዋ በኢህአዲግ አከላለል መሰረት ከ 'ኦሮምያ' ክልል መሬት ለመውሰድ በነበረው ሂደት ውስጥ በርካታ ገበሬዎች መሬታቸውን እንደሚለቁ በመታወቁ ተቃውሞዎች በክልሉ ቢሮዎች እና ከዩንቨርስቲ ተማሪዎች ተሰምቷል።

በመሰረቱ ኦሮምኛ ተናጋሪ ገበሬዎች ሌላ ሀገር የላቸውም።ተወልደው ያደጉባት አፈር ፈጭተው ውሃ ተራጭተው ያደጉባት መሬት ኢትዮጵያ ነች።ከቀያቸው ''ተነሱ!'' የሚል ቀጭን ትእዛዝ ማስተላለፍ በራሱ ሃሳፊነት የጎደለው ተግባር ነው።አንድ ሰው ከመሬቱ ለመነሳት ቢያንስ ከሁለት አንዱ መስፈርቶች መሟላት አለባቸው።
አንደኛው በፈቃዱ ወደ ሚፈልገው ቦታ ሲሄድ እና ሌላው ከለመደው ቦታ ለመሄድ የበለጠ ጥቅም የሚያስገኘለት ክፍያ ሲሰጠው ነው።ከእዚህ ውጭ  በዜግነትም ሆነ ለሀገር በማሰብ በምንም በማይበልጠው ሃብታም ቦታው መወሰድ አለበት ማለት በእራሱ የአስተሳሰብ ድህነት ነው።ለኢትዮጵያ ሀብታምም ሆነ ድሃ እኩል አይን ሊታዩ ይገባል።ሀብታሙ መሬቱን ከፈለገ ድሃውን የሚያማልል ልዩ ጥቅም በህጋዊ ሰነድ አረጋግጦ መስጠት አለበት።በከተሞች የቀድሞ ይዞታ የሆኑ ቦታዎች ሲወሰዱ መሆን ያለበትም ይህ ነበር። እየሆነ ያለው ግን ሀብታሙ  ወደድሃው ሲመጣ የመንግስትን ጡንቻ ይዞ መሆኑ ነው ጉዳቱ።

በአዲስ አበባ ዙርያ ያሉ የኦሮምኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን ለዘመናት ከኖሩበት ቦታ ሊወረወሩ አይገባም።የሚነሱ ከሆነ በሚያማልል ጥቅም እነርሱም አምነውበት ከሆነ ብቻ መሆን ይገባዋል።በአንድ ወቅት ከከተማ እርቆ የነበረ ቦታቸው  ከተማው ሲለጠጥ ደረሰባቸው እና የመሬታቸውን ተፈላጊነት አናረው።ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።የመሬታቸው ዋጋ ሲጨምር ጉልበተኛ ተገቢውን ክፍያ በሚያማልል መልክ ሳይሰጣቸው ፈድራል ፖሊስ ይዞ እያስፈራሩ አርቆ ማስፈር ምን አይነት ፍትሃዊነት ሊሆን ይችላል? ይህንኑ ጉዳይ የተቃወሙ የዩንቨርስቲ ተማሪዎችን መደብደብ እና ማሰርስ ምን ያህል የዜጎች የመጠየቅ መሰረታዊ መብትን መጋፋት ነው? ማናቸውም ፕሮጀክቶች በቅድምያ ከፕሮጀክቶቹ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ ማሳመን ይጠይቃል።ከእዚህ ውጭ ከጋምቤላ እስከ ቡራዩ  እና አምቦ መስመር የፕሮጀክቶች ግልፅነት የማነስ ጥያቄን እና በቂ ምላሽ የመስጠት አቅም ማነስን  በፌድራል ፖሊስ የመፍታት አባዜ እጅግ አደገኛ አካሂያድ ነው።

እዚህ ላይ የማስተር ፕላኑን ትግበራ ከንፁሃን ገበሬዎች መፈናቀል ጋር በተያየዘ እንጂ አዲስ አበባ እራሷ ''የምንስትሶ'' ነች እና ማስተር ፕላኑ የማስፋፋት ትግበራ ሊያዝ አይገባም የሚሉት የተሳሳተ እና ደካማ አስተሳሰብ እንደሆነ እረዳለሁ።''ገብረ ጉራቻ የምንትስ ደብረብርሃን የእገሌ'' ስለሆነ በሚል ስሌት የገበረዎቹን መፈናቀል የሚቃወሙ በራሳቸው የተሳሳተ ተምኔት ገብተው የምስኪን የኦሮምኛ ተናጋሪ ወገኖቻችንን ችግር ለሕዝቡ እንዳይደርስ ያደረጉበት ብሎም ከቀሪው ሕብረተሰብ ጋር በመጋጨት እና በማጋጨት የሚደክሙ መኖራቸው ይታወቃል።ይህ እንግዲህ ቀላሉን ጉዳይ  በአጉሊ መነፀር ለማየት እስከሚያዳግት ድረስ ያጠበቡበት የጥበት ደረጃ ተቀባይነት ሊያገኝ አይችልም።

ጉዳዩን ያነሱ ተማሪዎችም ይፈቱ! ፕሮጀክቶችም ህዝብን አሳታፊ እና የህዝቡን ይሁንታ ሳያገኙ አይተግበሩ።

ጉዳያችን
ሚያዝያ 19/2006 ዓም


Saturday, April 26, 2014

'' 'ቁርጥ ቀን ባይመጣ ሁሉም ጀግና ነበር' በላዬ ላይ የተሰካውን የአምባገነኖች እና የጎሰኞች እሾህ እሁድ ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ ላይ በመገኘት ማራገፍ እጀምራለሁ'' አዲስ አበባ የምትኖር ወጣት የተናገረችው።(የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ)


ኢትዮጵያ በየዘመኗ የሚቀልዱባት አምባገነኖች ቁራኛ መሆኗ ልጆቿ ዓለም ከደረሰበት የስልጣኔ ደረጃ እንዳይደርሱ እንቅፋት እንደሆናቸው ብዙ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል።ላለፉት 23 ዓመታት የኖረው ትውልድ አምባገነንነትን ብቻ ሳይሆን በጉልበት የተጫኑ ጎሰኝነት፣ውርደት፣ስደት፣ቅጥ ያጣ ሙሰኝነት፣የተጣመመ ታሪክ መጋት፣የብሔራዊ ሉዓላዊነት ሆን ተብሎ መዋረድን ሁሉ አስተናግዷል።

አምባገነኑ የኢህአዲግ/ወያኔ መንግስት ቅጥ ያጣ የመንደር ፖለቲካውን ህገ መንግስት በሚል ቃል ሸፍኖ በነፃ ሃሳባቸውን የገለፁትን ሁሉ ''ህገ መንግስት የጣሱ'' ሲል እንዳልነበር ''ህገ መንግስቱ ይከበር'' ብለው ከሕገ መንግስቱ አንቀፅ እየጠቀሱ የመፃፍ፣የመናገር እና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶች ይከበሩ'' ያሉት 'የዞን ዘጠኝ'  ጦማርያንን ትናንት ሚያዝያ 17/2006 ዓም ቤት ለቤት እያሸበረ ከእስር ቤት ማጎሩን ለማወቅ ተችሏል።ዛሬ ሚያዝያ 18/2006 ዓም የጦማርያኑ ድረ-ገፅ እንደጠቆመው ስድስቱ ታሳሪዎች ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስን ጨምሮ ማዕከላዊ እስር ቤት እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

በሌላ በኩል ሰማያዊ ፓርቲ ለሚያዝያ 19/2006 ዓም የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ በተያዘለት መርሃግብር መሰረት እንደሚደረግ እና ዝግጅቱ መጠናቀቁን ፓርቲው በድረ-ገፁ እና በፌስ ቡክ በለቀቀው ተከታታትይ ዘገባ ለማወቅ ተችሏል።

ይህ ትውልድ አምባገነንነትን የምሸከምበት፣ ሃገሩ ወደ እንጦሮጦስ ስትወርድ እየተመለከተ ጥቂቶች ''ሀገር ሰላም ነው፣እያደግን ነው'' እያሉ የሀገርን ሀብት ሲምነሸነሹበት የሚመለከትበት ዘመን በትክክል አብቅቷል።ቢያንስ በዝምታ የተሸበበ አንደበት መከፈት እንዳለበት እና ኢትዮጵያዊነት ቃል ኪዳኑን የሚያድስበት ጊዜ ላይ መሆናችንን ለማወቅ ይቻላል።

ዛሬ አዲስ አበባ አንድ ወዳጄ ታክሲ ውስጥ የወቅቱን የጎሳ ፖለቲካ እየኮነነች ካለምንም ፍርሃት ስትናገር የነበረች ወጣትን የሰማ ወያላ ''የምትይው ይገባኛል ግን መርሳት የሌለብሽ ብዙ ሸቤ አሉ'' ብሎ ሲመልስላት ከታክሲው ስትወርድ የሰጠችውን የመጨረሻ መልስ ከትቦ ላከልኝ።''ወጣቱ የደረሰበትን ደረጃ ተመልከት አምባገነኖችን የሚሸከሙ ጫንቃዎች የአገልግሎት ዘመናቸውን ጨርሰዋል።'' ካለ በኃላ ወዳጄ ወጣቷ ያለችውን እንዲህ ያስቀምጠዋል- '' 'ቁርጥ ቀን ባይመጣ ሁሉም ጀግና ነበር' በላዬ ላይ የተሰካውን የአምባገነኖች እና የጎሰኞች እሾህ እሁድ ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ ላይ በመገኘት ማራገፍ እጀምራለሁ''  

ጉዳያችን 
ሚያዝያ 18/2006 ዓም 




Thursday, April 24, 2014

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ዛሬ ባቀረቡት ሪፖርት ያስገረሙኝ April 24, 2014 at 12:05pm



ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የዘጠኝ ወር ሪፖርት ለምክርቤት ዛሬ ሐሙስ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት አቅርበው ጨረሱ።ከቤቴ ጀምሮ ትራንስፖርት እየሄድኩ በሞባይሌ ከአዲስ አበባ ኤፍ ኤም ላይ እየተከታተልኩ ነበር።ብዙ የሚባሉ ነገሮች ነበሩት።ነገር ግን ሁሉንም ለማንሳት ጊዜ የለኝም።ከእነኝህ ውስጥ ግን ያስገረሙኝን ብቻ ላንሳ።ቀድመው ወደስልጣን ሲመጡ የፎከሩበት ሙስናን አድበስብሰው ማለፋቸው አንዱ ነው።የዋናው ኦዲተር መስርያቤት ''ሀገር ተዘረፈ ለኢትዮጵያ ድረሱላት'' የሚል ሪፖርት ለምክርቤቱ ካቀረበ ዛሬ ሁለተኛ ቀኑ ነው።ሪፖርተር ጋዜጣም ዘግቦታል።ጉዳዩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦዲተር መስርያቤቱ ምን ያህል ነፃነት እንዳለው እያደነቁ በመንገር ሊሸውዱን መሞከራቸው አስገርሞኛል።እንደሳቸው ቀጥታ አባባል ''ማሳጅ'' ያልተደረገ ሪፖርት በማለት ጠርተውታል።የሪፖርቱን ታማኝነት በሌላ በኩል አረጋገጡ ማለት ነው። ሆኖም በጠራራ ፀሐይ አሰራር እና መመርያ ያልገደባቸው ሌቦች እንዴት ሀገር እንደሚዘርፉ እና የችግሩ ምንጭ እራሱ የመንግስታቸው እና የኢህአዲግ የሰው ኃይል በሙስና የተጨማለቀ መሆኑን ግን ለመንገር አልደፈሩም።

ሌላው ብድር የተበደርነው ''አበዳርዎቻችን ስለሚያምኑን ነው'' የሚል አባባል መጠቀማቸው ነው።እውን ጠቅላይ ሚኒስትር አሁን ባለንበት ዓለም ሃገራት ብድር የሚሰጡት ተበዳሪው ሀገር የመክፈል አቅም አለው በሚል ብቻ ነው? ለእዚህ ነው አበዳሪ ሃገራት ብድር ለሕንድ ከመስጠት ይልቅ ለመካከለኛው አፍሪካ ብድር የሚፀድቀው? የብድር ዓላማ አንዱ የመመለስ ዕድሉ ቢሆንም ሌላው የሃገራትን ፖሊሲ እጅ መጠምዘዣ መሳርያ ስለሆነም ጭምር ነው።አቶ ኃይለማርያም እየነገሩን ያሉት  ''የመመለስ አቅማችን ስላደገ ብቻ ነው'' የሚለው አባባላቸው አይዋጥልኝም።ይልቁን ከ 5 ቢልዮን ዶላር በላይ ብድር ተበድረን ለምን ለሙሰኛ እና ለሌባ ሲሳይ እንደሚደረግ ቢነግሩን ደስ ይል ነበር። መድበለ ፓርቲ በተመለከተ ያሉት ''ልብ ውልቅ'' ነው።ያደክማል።

''ኢንቨስተር የሀገር ሉዓላዊነትን አይነካም በተለይ በጋምቤላ የእዚህ አይነቱ አደጋ የለም''ላሉት።ኢንቨስተር በእራሱ ጠላት አይደለም ግን የሉአላዊነት አደጋ የመሆን አጋጣሚዎች ግን አሉ።በተለይ ኢንቨስተር ተቀባዩ ሀገር እና መንግስት እንደ እኛ በሙስና የተጨማለቀ ከሆነ የከፋ ነው።ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ ኢንቨስተሮቹ መሬት ብቻ ሳይሆን ወንዞችን የግላቸው እያደረጉ ከመሆናቸው አንፃር ብቻ ስናየው ብዙ ነገሮች ይከሰቱልናል።ሲመጡም ውሃ ከሀገራቸው በሃይላንድ እያመጡ ልያጠጡ አይደለም የመጡት ወንዞቻችን እና ዝናማችንን ነው የፈለጉት።ኢንቨስተር የሀገር ሉዓላዊነትን የመዳፈር አጋጣሚ መኖሩን ለማየት ወደ ኃላ ታሪክ ቢመለከቱ አሰብ ላይ ጣልያን እግሯን የተከለችው ከአንድ ሱልጣን በገዛችው ቁራሽ መሬት (በኢንቨስተር ስም) መሆኑን ከእርስዎ አይሰወረም። ለመሆኑ 'የልማት ጥናት' ትምህርት እራሱ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች multi-national corporations (MNC) በሀገሮች የውስጥ ጉዳይ እየገቡ ለብዙ ሃገራት የፀጥታ ችግር መሆናቸውን ያስተምር የለም እንዴ? በእዚህ ዙርያ በዓለማችን በርካታ ድርሳናት ለመፃፋቸው ጠቅላይ ሚኒስትራችን አላነበቡም? በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረ ቀጥሎ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነ ሰው የአንዲት ሀገር ሉዓላዊነት አደጋዎች የመምጫ አቅጣጫዎችን አያውቅም ብሎ ማለት ይከብዳል።ግን ሃገሩ ኢትዮጵያ ሆነ እና ጠያቂ ጠፋ።

የኢትዮጵያ ብድር ቅጥ ያጣ መሆኑን እና በሕገ ወጥ መንገድ ምን ያህል ገንዘብ ከሀገር እንደወጣ ይህንን ሊንክ ከፍተው ያንብቡ http://gudayachn.blogspot.no/2014/04/2001-2005-156-1117-165.html 

ጉዳያችን 
ሚያዝያ 16/2006 ዓም 

Tuesday, April 22, 2014

ማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቭዥን የአየር ሰዓት ስርጭቱን ወደ 24 ሰዓት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገለጠ።ወደፊት የራሱ የቴሌቭዥን ጣቢያ እንደሚያስፈልገውም ተጠቆመ።

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤ/ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቭዥን ስርጭት የጀመረበትን አንደኛ ዓመት አከበረ።የካቲት 30/2006 ዓም ይህንኑ በዓል ባከበረበት ወቅት የማኅበሩ የሚድያ ክፍል ኃላፊ ዲያቆን ዶ/ር መርሻ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ ማኅበሩ የቴሌቭዥን ስርጭቱን ወደ 24 ሰዓት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ከመግለፃቸውም በላይ የእራሱ የቴሌቭዥን ጣብያ መኖር አስፈላጊነትን አስምረውበታል።

ዜናውን የማኅበሩ ጋዜጣ 'ስምዐ ፅድቅ' ጋዜጣ በመጋቢት/2006  የዘገበውን ከእዚህ በታች ይመልከቱ።




Thursday, April 17, 2014

ሰበር ዜና - በኢትዮጵያ በግብረ ሰዶማዊነት ጉዳይ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ተቃውሞ፣ሊደረግ የነበረው ፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ሰልፍ መቅረት፣ የመንግስት ሁኔታውን አቅልሎ ለማየት የሚያደርገው ሙከራ ለ2007ዓም ምርጫ ለምዕራባውያን የቀረበ ማባበያ ይሆንን?



ፎቶ ደብረ አሚን አቡነ ተ/ኃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አዲስ አበባ መርካቶ (ፎቶ ከማ/ቅ/ መልቲ ሚድያ የተገኘ) 

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የግብረ ሰዶም ጉዳይ ከማኅበራዊ የቀውስ ጉዳይ ወደ ዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ ጉዳይ እየተሸጋገረ መምጣቱ ይታወቃል።ድርጊቱን የሚደግፉት ምዕራባውያን የኃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ ጥያቄዎችን ወደጎን በመተው  ''ከሰው ልጆች መብት'' ጋር ብቻ በማያይዝ ሃገራት ፀረ-ግብረ ሰዶማዊነት ሕግ እንዳያፀድቁ ካፀደቁም እንዳይተገብሩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅኖ ለመፍጠር ሲሞክሩ ተስተውሏል።

ግብረ ሰዶማዊነትን ፖለቲካዊ መልክ አላብሳ ሀገሮችን የመጎንተያ መሳርያ ካደረጉት ሃገራት ውስጥ ለምሳሌ አሜሪካ ሩስያን እና  በርካታ የአፍሪካ ሃገራት ዑጋንዳ እና ናይጄሪያን ጨምሮ ያወጡትን ፀረ-ግብረ ሰዶማዊነት ሕግ ስትኮንን መሰንበቷ ይታወቃል።በተለይ የዑጋንዳው መሪ ዩዌሪ ሙሰቨኒ  ''አውሮፓውያን በፖለቲካ ጉዳያችን እንደገባችሁ በማኅበራዊ እና ባህላዊ ጉዳያችን አትግቡብን'' በሚል ኃይለ ቃል  ፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ሕጉን ጋዜጠኞች ጠርተው በአደባባይ መፈረማቸው  ይታወሳል።

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ በጉዳዩ ላይ ጠንካራ ተቃውሞ የሚያሰማ አንድም የኢህአዲግ ባለስልጣን እስካሁን አልተሰማም።ይህ ብቻ አይደለም  በርካታ አፍሪካውያን በጠቅላይ ሚኒስትራቸው ደረጃ በተቃውሞ መግለጫ ሲሰጡበት ሁለቱን የዓለም ታላላቅ ኃይማኖቶች በመቀበል ከዓለም ቀደምት የሆነች ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ምንም አለማለቷ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን አፍሪካውያንን ያሳዘነ ጉዳይ ነው።

ይልቁንም ከዓመት በፊት በአዲስ አበባ በተደረገ አንድ የዓለም አቀፍ የጤና ጉባኤ አስታከው ከተለያዩ ሃገራት የተውጣጡ ግብረ ሰዶማውያን በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ስብሰባ ሊያደርጉ ነው የሚለው ዜና እንደተሰማ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከማስቆጣቱም በላይ የሃይማኖት አባቶች ተሰብስበው የተቃውሞ መግለጫ ለማውጣት በዝግጅት ላይ እንዳሉ በወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የነበሩት የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የሃይማኖት አባቶችን ሰብስበው ተቃውሞ እንዳያወጡ ተፅኖ ማድረጋቸው እና ስብሰባው አዲስ አበባ ላይ ሊደረግ መቻሉ ይታወቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን አዲስ አበባ ላይ ግብረ ሰዶማዊነትን በመቃወም ሊደረግ የነበረው ሰልፍ መቅረቱ እየተሰማ ነው ።ሰልፉ በአዲስ አበባ ወጣቶች ''ፎረም'' እና ''ወይንዬ'' በተሰኘ የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን የምዕ  መናን  ማኅበር አማካይነት እንደሚካሄድ ሲነገር ነበር።ሰልፉ የሚደረግ ለመሆኑ እና ፈቃድ ከመንግስት ያገኘ መሆኑን አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በመግለጫው ላይ ያረጋገጠ ከመሆኑም በላይ ዕሁድ ሚያዝያ 19/2006 ዓም ሊደረግ መታሰቡን ከመንግስት ፈቃድ ማግኘቱን መግለጫው ስያብራራ '' ሚያዝያ 26/2014 ዓም የሚደረገው ሰልፍ ''ፀረ-ግብረ ሰዶማዊነት ሲሆን ሰልፉ በአዲስ አበባ እንዲደረግ ከመንግስት ማረጋገጫ አግኝቷል''  ይላል።

ዘግይተው የወጡ ዘገባዎች ደግሞ ሰልፉ እንደማይደረግ እና መንግስት ያላዘጋጀው ሰልፍ መሆኑን ይገልፃሉ።ቀድሞውንም መንግስት ያዘጋጀው ሰልፍ ነው የሚለው ግምት ያሰጠው ''የአዲስ አበባ ወጣቶች ፎረም'' በኢህአዲግ የሚደገፍ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንጂ መንግስት እስካሁን በግልፅ ጉዳዩን አምርሮ ሲቃወም አልተሰማም።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተ/ቤተክርስቲያን ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ለቪኦኤ የአማርኛው አገልግሎት ላይ በተሰማ የ 2006 ዓም የትንሣኤ መልካም ምኞት መግለጫ ላይ ግብረ ሰዶማዊነትን በእጅጉ ኮንነው መግለጫ ሰጥተዋል።በመግለጫቸው ላይም “በአገራችን ላይ ልማትና ዕድገት ሳይሆን መቅሰፍትና ውርደት እንዳያስከትልብን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ግብረ-ሰዶምን በፅናት መመከት አለበት” ብለዋል።

ባጠቃላይ የግብረ ሰዶማዊነት ጉዳይ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀድማ መናገር የሚገባት ሆና ሳለ በተገቢ መንገድ መንግስቷ አለመናገሩ ብዙ አፍሪካውያን ያሳዘነ ጉዳይ እንደሆነ በሚሰማበት ወቅት ይደረጋል የተባለው ሰልፍ እርግጠኝነት አለመታወቁ እና መንግስት ተገቢውን ድጋፍ አለማድረጉ ብዙ ኢትዮጵያውያንን መንግስት ከምዕራባውያን የሚያገኘው እርጥባን እንዳይቀርበት ብሎ የሚያደርገው ነው ሲሉ ይተቻሉ።በተጨማሪም ጉዳዩን ለ 2007 ዓም ምርጫ ከምዕራባውያን ለማግኘት የሚፈልገውን ድጋፍ ማግኛ ካርድ ያደርገው ይሆን እንዴ? የብዙዎች ጥያቄ ነው።

ጉዳያችን
ሚያዝያ 10/2006 ዓም 

Wednesday, April 16, 2014

Friday, April 11, 2014

የኢትዮጵያ የውጭ ብድር በ 2001 እና በ 2005 ዓም መካከል ባሉት ዓመታት ብቻ በ156 % ወደ 11.17 ቢልዮን ዶላር ማደጉን ያሳያል በተቃራኒው ''ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ 16.5 ቢልዮን ዶላር ከሀገር ወጣ''


ኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት በለየለት የገንዘብ ዘረፋ ላይ መሰማራታቸውን እራሱ መንግስትም ያመነው ጉዳይ ነው።አንዳንድ ባለሥልጣናቱንም ዘብጥያ ማውረዱ ይታወቃል።ሆኖም የኢትዮጵያ አንጡራ ሃብት በቢልዮን የሚቆጠር ዶላር አሁንም እየተመነዘረ መውጣቱ የዓለም ዓቀፍ ጥናቶች አመላክተዋል።የሚገርመው ነገር ግን እንደተጠበቀው የሙስና ዘመቻ ሲባል የነበረው የውሃ ሽታ ሆኖ መቅረቱ ነው።አሁን የሙስና ኮሚሽን መኖሩን የሚያስታውሱት ምናልባት በለጋሃር በኩል ሲያልፉ ህንፃውን ከተመለከቱ ብቻ ነው።

ጥቂቶች በናጠጡበት፣ ሙስና ከሃይማኖት ድርጅት እስከ ቁንጮ ባለስልጣናት የተካኑበት ተግባር ነው። ጉዳዩ የበለጠ የእያንዳንዱን ሰው ትኩረት የሚሻ መሆኑን የምንረዳው ሀገሪቱ በገፍ ከውጭ ከሚቀርበው እርዳታ በተጨማሪ በከፍተኛ መጠን እየገባችበት ያለው የብድር ዕዳ ነው።በአግባቡ በፓርላማ የማይመከርባቸው፣ ፓርላማ ላይም ቢነሳ ሁሉም አጨብጭቦ የሚወጣበት ፓርላማ ከመሆኑ አንፃር ብድሩን የሚያፀድቀው አካል ምን ያህል ኃላፊነት እየተሰማው ነው? የሚለው ሌላው አጠያያቂ ጉዳይ ነው።ዕዳው ለልጅ ልጅ የሚቀመጥ እየተቀመጠልን መሆኑን አለመዘንጋት ጠቃሚ ነው።

የኢትዮጵያ የገንዘብ እና ኤኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ድረ-ገፅ እንደሚያመለክተው በ 2001 እና በ 2005 ዓም መካከል ባሉት ዓመታት ብቻ  የኢትዮጵያ የውጭ ብድር በ 156 % ማደጉን ያሳያል።ይሄውም በ 2001 ዓም 4.35 ቢልዮን የነበረው ብድር በአምስት ዓመታት ውስጥ ወደ 11.17 ቢልዮን ዶላር መመንደጉን ያሳያል።ባጠቃላይ የቅሌት መዝገባችን ወደ 16.11 ቢልዮን ዶላር ደርሷል። አብዛኞቹ በመንግስት የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ዋና ምንጫቸው የውጭ ብድር ነው።ብድር አትራፊ ለሆኑ አዋጭ ፕሮጀክቶች ከሆነ ሙሉ በሙሉ አይወቀስም ነገር ግን ተበድሮ ለሙስና እና ለጥቂቶች ኪስ ማድለብያ ሲሆን ወንጀሉን ያከብደዋል።

ትናንት ሚያዝያ 2/2006 ዓም የ ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ባቀረበው የአምስት ዓመት ትራንስፎርሜሽን ክንውን ላይ ከተባለው ግብ ኢትዮጵያ መድረስ አለመቻሏን አምኗል። የምክር ቤቱ ብቸኛ ተቃዋሚ አቶ ግርማ ''ቀድሞውንም ዕቅዱ በአግባቡ ያልታሰበበት ለመሆኑ አሁን ላለበት ውጤት መብቃቱ በራሱ ምስክር ነው'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ከፖሊሲ ችግር በተጨማሪ ቅጥ ያጡ የኢህአዲግ ባለስልጣናት ሙስና ዋነኛው ምክንያት ለመሆኑ አያጠራጥርም። ከእነርሱ ጋር አብረው የሚዘርፉ ግን ሀገሪቱ አድጋለች እያሉ ሪፖርት ለማውጣት የሚሽቀዳደሙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን እዚህ ላይ መዘንጋት አይገባም።

 ከላይ መግስት እራሱ  ያመነውን የብድር መጠን ካወሳን ቀጥለን ለሙስናው ማስረጃ ባለፈው ዓመት ግንቦት ላይ መሰረቱን ዋሽግተን ላይ ያደረገው ''ግሎባል ፋይናንስ እንተግርቲ'' ከኢትዮጵያ  ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ 16.5 ቢልዮን ዶላር ከሀገር ወጣ ይላል።(Ethiopia lost 16.5 Billion to illegal smuggling of cash out of the country in 10 years) ለትውልድ ከሚቀመጥ ብድር ላይ ከተሞች ሲብለጨለጩ እናይ ይሆናል።ግን ሀገሪቱ ከተበደረችው መጠን አንፃር እየተሰራ ነው ወይ? ስንል ትልቅ ጥያቄ ይጭራል። ጥያቄውን ይህንን ያህል ብድር የተበደረች ሀገር ዋና ከተማዋ ነዋሪ ከ25% በላይ የሚሆነው ውኃ ማግኘት አልቻለችም ይህም ቁጥሩ ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጋ ሕዝብ ነው ስንባልስ?።

ጉዳያችን
ሚያዝያ/2006 ዓም  

Monday, April 7, 2014

''ከአያያዝ ይቀደዳል፣ከአነጋገር ይፈረዳል'' አሁንም ጥያቄው የኢህአዲግ/ወያኔ መንግስት የአባይን ግድብ ከልቡ ይፈልገዋልወይ? የሚለው ነው።(የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ)

ዓባይ 

በአባይ ላይ የሚገነባው ታላቁ ''የህዳሴ ግድብ'' ከተጠናቀቀ እና መሰራት ከተቻለ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ አትሆንም የሚል ዕምነት የለኝም። የአካሄድ፣ቀድሞ ሳይታቀድ  የፕሮጀክቱ በድንገተኝነት መገለፅ፣የህዝብ ዲፕሎማሲ አመራሩ፣ከፖለቲካዊ ፍጆታ አውጥቶ የህዝቡ የማድረግ ሂደቱ ወዘተ ላይ አሁን በዝርዝር አልገባበትም።

 እኔን እየሞገተኝ ያለው ጥያቄ ኢህአዲግ/ወያኔ ከልቡ ነው ወይ 'አባይ አባይ' የሚለው? የሚለው ጥያቄ ነው።

ለሁሉም እስኪ እነኝህ ጥያቄዎች እንመልከት እና የእራሳችንን ፍርድ እንስጥ  -

 የአባይ ግድብ የኢትዮጵያ ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን መንግስት ካመነ - 

- ለምንድነው በሀገር ውስጥ ያለውን የውስጥ ፖለቲካ ለማላላት ፍቃደኝነት የማያሳየው?

- ለምንድነው እለት ከእለት ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ጋር ሲጋጭ፣ምሁራንን ስያሸሽ፣ሃይማኖትን ለመቆጣጠር ሲባዝን የሚታየው?

 - የአባይ ጉዳይ ትልቅ የዲፕሎማሲ ንቅናቄ የሚጠይቅ በተለይ የዲያስፖራውን ድጋፍ የሚፈልግ መሆኑ ይታወቃል።የዲያስፖራው ጥያቄ ደግሞ ግድቡ  አይገንባ አይደለም።ይልቁን የሰብአዊ መብት አያያዝ፣እኩል ተሳታፊነት፣ተጠቃሚነት እና የጎሳ ፖለቲካ በሃገር ዓቀፍ ፖለቲካ ይቀየር የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።የአባይ ግድብ ቀዳሚ አጀንዳዬ ነው ካለ መንግስት ለምን እነኝህን ጥያቄዎች መመለስ አልፈለገም?

-  በግድቡ ሳብያ ከውጭ የሚመጣው ተፅኖ ቀላል አለመሆኑ እየታወቀ። የውጭው ተፅኖ ደግሞ ከሀገር ውስጥ የልዩነት መስፋት ጋር ኢትዮጵያን ትልቅ አደጋ ላይ እንደምጥላት እየታወቀ ለምንድነው ዲፕሎማሲው በደካማ እና ለስራው ብዙ ልምድ በሌላቸው ሰዎች እንዲመራ የሚያደርገው? (የዲፕሎማሲ ሥራ እራሱን የቻለ ሙያ ነው የ ጤና ሙያ ያጠና ሰው ዲፕሎማሲው ላይ አምጥቶ ማሰራት ማለት ምን ማለት ነው?)

 - የአባይ ጉዳይ የኢትዮጵያ ቀዳሚ አጀንዳ ከሆነ መንግስት ለምንድነው ኢትዮጵያውያንን አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ በሚለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው?

- ለግድቡ የገንዘብ ድጋፍ ትኩረት የሚሰጥ ከሆነ -
        - ለምንድነው ለአንድ ሃውልት አሩሲ ውስጥ 20 ሚልዮን ብር የሚያወጣው? ለምንድነው ለአንድ ባለሥልጣኑ   መታከምያ ከሰላሳ ሚልዮን ብር በላይ የሚያወጣው?
        - ለምንድነው በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር በውጭ የሚኖረውን ዲያስፖራ ለመሰለያ የሚጠቅሙ ሶፍት ዌሮችን ለመግዛት የሚያወጣው?

- የአባይ ጉዳይ የኢትዮጵያ ቀዳሚ አጀንዳ ከሆነ ለምንድነው ግብፅ ከደርዘን በማያንሱ ሃገራት እየዞረች የዲፕሎማሲ ዘመቻ ስታደርግ መንግስት ጉዳዩን ለማስረዳት ልዑካንን በየሃገራቱ መላክ ያልፈለገው?

ባጠቃላይ የአባይ ጉዳይ ትልቁ የኢህአዲግ/ወያኔ የትኩረት ጉዳይ የሚመስላቸው ትንሽ ሳይሳሳቱ የቀሩ አይመስለኝም።የመንግስት ትልቁ ጉዳይ አይመስለኝም።ትልቁ ጉዳይ ቢሆንማ ኖሮ የሀገር ውስጥ ፖለቲካውን ለማረም በተነሳ ነበር።ግን ይህንን አላደረገም። በትክክል ለሀገር የሚያስብ መንግስት ለአባይ ግድብ የሚከፍለው ትንሽ መስዋዕትነት (መስዋዕትነት ከተባለ) የሀገር ውስጥ ፖለቲካውን በፍጥነት አሻሽሎ ብሔራዊ ህብረት እና እንድነትን ማጠናከር ነው።

በመሆኑም መንግስት ይህንን ለማድረግ ፍቃደኛ ባልሆነበት ሁኔታ የሚያመላክተው አንድ ነገር ግድቡን መፈለግን አይደለም።ግድቡን መጀመር ከፍተኛ ገንዘብ ማሰባሰብ፣በተሰበሰበው ገንዘብ በሚሰጡ የፕሮጀክት ስራዎች ''የእህት'' ኩባንያዎችን አቅም ማፈርጠም፣ተደናቂነትን ሀገር ውስጥ ማግኘት፣ለረጅም ጊዜ የስልጣን ገበያ የሕዝብን ሃሳብ ወጥሮ ይዞ ማቆየት የኢህአዲግ ትልቁ አጀንዳው ይመስላል። ''ከአያያዝ ይቀደዳል፣ከአነጋገር ይፈረዳል'' አሁንም ጥያቄው የኢህአዲግ/ወያኔ መንግስት የአባይን ግድብ ከልቡ ይፈልገዋል ወይ? የሚለው ነው።

ጉዳያችን
መጋቢት 2/2006 ዓም 

Friday, April 4, 2014

ሰበር ዜና - ኢህአዲግ/ወያኔ የኖርዌይ ዜግነት ያለውን ትውልደ ኢትዮጵያዊ የቀድሞ የጋምቤላ ክልል አስተዳዳሪ ኦኬሎ ኦቻላን ከደቡብ ሱዳን ጋር በመተባበር ጠልፎ ወደ ኢትዮጵያ በመውሰዱ ከኖርዌይ መንግስት ጋር ዲፕሎማሳዊ ፍጥጫ ውስጥ ገብቷል።ኢህአዲግ/ወያኔን ''ድንበር ተሻጋሪ አሸባሪ'' ለመሆኑ ይህ በቂ ማስረጃ ነው የሚሉ አሉ።





የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዝዳንት ኦኬሎ ኦቻላን  በታህሳስ/1996 ዓም (ዲሴምበር 13/2003 እ አ አቆጣጠር) በጋምቤላ በተፈፀመው ጭፍጨፋ ወቅት ከሀገር መውጣታቸው እና በተለያዩ ሃገራት ከኖሩ በኃላ ወደ ኖርዌይ በመምጣት ዜግነት ማግኘታቸው ይታወቃል።

ሐሙስ መጋቢት 25/2006 ዓም ከ 150 ዓመት በላይ በሕትመቱ ዓለም መቆየቱ የሚነገርለት የኖርዌይ ቁጥር አንድ ተነባቢ ጋዜጣ ''አፍተን ፖስተን'' ''ትውልደ ኢትዮጵያዊው ኖርዌጃዊ ከደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ካለፈቃዱ ተወሰደ''  በሚል አርዕስት ስር ባስነበበው ዘገባ  ስር ጋዜጣው ዜናውን ሲቀጥል '' የሰብአዊ መብት አክቲቪስት'' በማለት የጠራቸውን አቶ ኦከሎ ኦቻላ  በደቡብ ሱዳን መንግስት ባለስልጣኖች አጋዥነት  ወደ ኢትዮጵያ ተወስደው እንዲታሰሩ መደረጋቸውን እና ኖርዌይ ጉዳዩን አዲስ አበባ በሚገኘው ኢምባሲዋ እየተከታተለች መሆኗን ጋዜጣው ያብራራል።

ሚስተር ስቫየን ሚቸልሰን የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኮምንኬሽን ጉዳዮች አማካሪ ስለ ጉዳዩ የሚከተለውን ብለዋል ''He confirmed that Aquai (ኦኬሎ) is a Norwegian citizen and that UD is familiar with the matter . The Norwegian Embassy in Addis Ababa now assisting Aquai''

''Han bekrefter at Aquai er norsk statsborger og at UD er kjent med saken. Den norske ambassaden i Addis Abeba bistår nå Aquai, opplyser Michelsen, som ikke ønsker å si noe mer om saken.''

'' ኦኮሌ የኖርዌይ ዜግነት ያለው ግለሰብ ነው።የኖርዌይ የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ (UD) የእርሱን ጉዳይ በሚገባ ያውቀዋል።አዲስ አበባ የሚገኘው የኖርዌይ ኤምባሲ ለኦኬሎ ድጋፍ እያደረገ ነው''  ሲሉ  ባጭሩ ማብራራታቸውን ጋዜጣው ያትታል።

በመጨረሻም ጋዜጣው ኦኬሎ በሰብአዊ መብት ጥሰት በደረሰባት ጋምቤላ በነበረው ችግር መሰደዳቸውን ገልጦ የደቡብ ሱዳን የፀጥታ ኃይሎች ግለሰቡን ከደቡብ ሱዳን እና ዑጋንዳ ድንበር መካከል መወሰዳቸውን ያብራራል።

ጉዳዩን  እዚህ ኖርዌይ ውስጥ የተመለከቱ ተንታኞች ኢህአዲግ/ወያኔን ''ድንበር ተሻጋሪ አሸባሪ'' ለመሆኑ  በቂ ማስረጃ  መሆኑን ይስማማሉ።
በእርግጥም ነገሩን ስናጤነውም ኖርዌይ በጋምቤላ ጉዳይ የመግባት እድሏን በሰፊው የሚከፍትላት ከመሆኑም በላይ ዜጋዋን በነፃ በማስለቀቁ ሂደት ላይ ከኢህአዲግ/ወያኔ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በፍጥነት ሊያሽቆለቁል  እንደሚችል ብዙዎች ያምናሉ።
ኢህአዲግ/ወይኔ እጅግ ከሚፈራቸው እና  ''ስስ ብልቶቹ'' ተብለው ከሚጠቀሱት ጉዳዮች አንዱ የጋምቤላው እልቂት ሳብያ በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት የመከሰስ እድሉ ሰፊ የመሆኑ እውነታ መሆኑ ይታወቃል።

ጉዳያችን
መጋቢት 26/2006 ዓም
ኦስሎ፣ኖርዌይ

የ ''አፍተን ፖስተን'' ጋዜጣ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ያወጣውን ዘገባ ዕትም ከእዚህ በታች ይመልከቱ

Norsk-etiopier utlevert fra Sør-Sudan til Etiopia

NTB

Oppdatert: 03.apr. 2014 17:20

Den norske statsborgeren og menneskerettsaktivisten Okelo Ochala Aquai sitter fengslet i Etiopia etter at sørsudanske myndigheter skal ha pågrepet og deretter utlevert ham. UD er orientert om saken.
- Vi yter konsulær bistand, opplyser kommunikasjonsrådgiver Svein Michelsen i Utenriksdepartementet til NTB.

Han bekrefter at Aquai er norsk statsborger og at UD er kjent med saken. Den norske ambassaden i Addis Abeba bistår nå Aquai, opplyser Michelsen, som ikke ønsker å si noe mer om saken.

Okelo Aquai er tidligere president i den urolige Gambella-regionen i Etiopia. Han kom til Norge som flyktning etter at han skal ha avslørt menneskerettighetsbrudd begått av etiopiske myndigheter i Gambella.

Det er uvisst hvorfor Aquai er pågrepet. Men ifølge opplysninger NTB har fått, ble han tatt av sørsudanske sikkerhetsstyrker på grensen mellom Sør-Sudan og Uganda. Han skal ha sittet fengslet i den sørsudanske hovedstaden Juba før han ble utlevert til Etiopia.

Det er ikke kjent hvorfor Aquai var i området.

LES OGSÅ: Bygger opp ny overvåkingstat i Afrika

Etiopia har lenge vært kritisert for manglende respekt for demokrati og menneskerettigheter og for å slå stadig hardere ned på opposisjonen. De siste årene er en rekke av landets ledende opposisjonelle og journalister satt i fengsel.

ምንጭ - http://www.aftenposten.no/nyheter/uriks/Norsk-etiopier-utlevert-fra-Sor-Sudan-til-Etiopia-7525988.html#.Uz84dL9Iwds

Thursday, April 3, 2014

''ዋቃዮ ቁልቁሉ'' በማኅበረ ቅዱሳን Ethiopian Orthodox Mezmur in Afan Oromo - Waqayo Qulqulu - Mahibere Kidusan

ማኅበረ ቅዱሳን ኦርቶዶክሳዊ መዝሙሮችን በሀገራችን ልዩ ልዩ ቋንቋዎች በሲዲ እያዘጋጀ እንደሚያሰራጭ ይታወቃል።ለምሳሌ በኦሮምኛ፣በትግርኛ እና በሌሎች የሃገራችን ቋንቋዎች የመዝሙር ልዑኩ በሄዱበት የአገልግሎት ቦታዎች ሁሉ ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ያቀርባሉ።ይህ በማኅበሩ መዘምራን ከተዘጋጀው እና በሲዲ ከታተመው የኦሮምኛ መዝሙራት ውስጥ አንዱ ነው።

''ዋቃዮ ቁልቁሉ'' በማኅበረ  ቅዱሳን