ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, June 29, 2017

የተቃወሰ መንግስት ምልክቱ እራሱን ወደ 'አናርኪዝም' ማሸጋገሩ ነው - የኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ ጉዳይ ይመለከታል


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 


ጉዳያችን/ Gudayachn
ሰኔ 23/2009 ዓም (ጁን 30/2017 ዓም)
++++++++++++++++++++
በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ታሪክ የኢትዮጵያ ባንኮች ከሌሎች የአፍሪካ በተለይ ከሣሃራ በታች ካሉት ሀገሮች በተለየ ጥሩ ተአማኒነትን በሌላው ዓለም አትርፈዋል።ለምሳሌ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደርግ ዘመን ማለትም ኢትዮጵያ ከቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ጋር ወዳጅ ሆና ሳለም ሳይቀር የምዕራብ ባንኮች በ"ሌተር ኦፍ ክረዲት" የላኪ እና የአስመጪ ሰነዶች ላይ በሚፈፀሙ ክፍያዎች ታማኝነቱ የተመሰከረለት ነው።ለምሳሌ የአሜሪካው "ሲቲ ባንክ" እና የእንግሊዙ "ስታንዳርድ ቻርተር" የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰነዶች ላይ እምነታቸው ከፍ ያለ ነው።ለእዚህ ደግሞ ምክንያቱ የስርቆት አደጋዎች በብዛት የማይታዩበት፣ለቀረቡለት የክፍያ ሰነዶች በወቅቱ መክፈሉ እና ለእረጅም ጊዜ በባንኩ የዓለም አቀፍ ባንክ አገልግሎት ክፍል (International Banking Division) ላይ የሰሩት ኃላፊዎች የገነቡት ዓለም አቀፍ ስብዕናም ጭምር ነው።ይህ ማለት ታማኝነቱ በአንድ ጀንበር የተገንባ ሳይሆን የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ከቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ጊዜ ጀምሮ የገነባው ብቁ እና ታማኝ የሰው ኃይል ውጤትም ጭምር ነው። በእርግጥ ደርግ የሆነ ወቅት ላይ በሙያው በቂ ስልጠና የሌላቸውን አስገብቶ እንደነበር እና ይህም ለባንኩ የስራ ጥራት ላይ የእራሱን አስተዋፅኦ ማድረጉን የሚናገሩ አሉ። ይህም ሆኖ ግን በታማኝ የሰው ኃይል እና ስራን በማክበር አይታማም።

በእዚህ ፅሁፍ ማንሳት የፈለኩት ግን ይህንን አይደለም።ስለ የባንኮቻችን በቀውስ ላይ ያለው መንግስት አናርክዝም ወይንም ስርዓት አልበኝነት ሰላባ ስለመሆን ነው።በአሁኑ ጊዜ የግል ባንኮችን ጨምሮ 18 ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ።ይህ በራሱ ጥሩ ነገር ነው። ሆኖም ግን የባንክ ቁጥር መደርደሩ ሳይሆን አጠቃላይ የባንክ ኢንዱስትሪው ለኢንዱስትሪው ስነ-ምግባር እና የንግድ ሕግ ተገዢ ነው ወይ? የሚለው ጉዳይ ወሳኝ ነው።አንድ ባንክ ከሁሉም በላይ በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪ ብቻ ሳይሆን በውጭ ሀገር ተመሳሳይ የገንዘብ ድርጅቶች ዘንድም ታማኝ የሚያደርገው ለደንበኞቹ ያለው ዋጋ ነው።ደንበኞቹ ማለት ደግሞ ገንዘብ ያስቀመጡ እና የምበደሩ የሀገር ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ በውጭ ያሉ ባንኮች እራሳቸው ደንበኛ ባንኮች ይባላሉ።ይህ ማለት የውጭ ባንኮችም ደንበኞቻችን ናቸው ማለት ነው።ባንክ ባንክ ለመባል ትንሹ የሚጠበቅበት እና ለምንም ድርድር የማይቀርበው ጉዳይ ደንበኞች ያስቀመጡትን ገንዘብ በፈለጉ ጊዜ መክፈል መቻሉ ነው።ይህ የባንክ ሀ! ሁ! ነው።ይህንን ማድረግ ያልቻለ ባንክ ባንክ አይባልም።ይህ ሃገራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ግዴታ ነው። የብሔራዊ ባንክ ካሉበት ትልልቅ ሃገራዊ ምጣኔ ሃብታዊ ኃላፊነቶች ውስጥ ትንሹ እና ለድርድር የማይቀርበው የቁጥጥር ቀዳሚ ስራው ውስጥ የንግድ ባንኮች ደንበኞቻቸው ገንዘባቸውን ሲፈልጉ መልሰው  የመክፈል አቅም ሳይኖራቸው ተበዳሪ አገኘን ብለው  ያላቸውን ሁሉ አበድረው ደንበኞች ገንዘባቸውን እንዳያጡ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ነው። ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ታሪክ ውስጥ ጥያቄ ሆኖ አያውቅም። በእዚህ በአሁኑ ዘመን ግን አንድ ሰው በፈለገበት ሰዓት ባንክ ሄዶ ገንዘቡን ለማውጣት ሲፈልግ " ሲስተሙ ችግር አለበት ወይንም ዛሬ ሲስተም የለም" እየተባለ መመለስ የተለመደ ነው። ይህ አይነቱ መልስ በባንኮች ታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ በደርግም ሆነ በሃይለስላሴ ዘመን ተደረገ ሲባል አልሰማሁም።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 'ሲስተሙ አይሰራም' በሚል ምክንያት ደሞዝ ወደ ሂሳባቸው የገባ ሰራተኞች ደሞዛቸውን ሳይወስዱ ከሶስት ቀናት በላይ ይመላለሳሉ።የንግድ ውል ተዋውለው ገንዘቡን መክፈል የሚፈልጉ ነጋዴዎች ባንካቸው ገንዘቡን መክፈል ሳይችል ለሳምንት ልዘገዩ ይችላሉ አልያም ደንበኞች ያስቀመጡትን ገንዘብ ለማውጣት ለቀናት በእዚሁ ሲስተም በሚል ሰበብ ይመላለሳሉ። እዚህ ላይ ሲስተም ተብሎ የሚነገረው በኢትዮጵያ ቴሌኮምኒኬሽን ብቸኛ አቅራቢነት የሚሰጠው የኢንተርኔት አገልግሎት ነው።ቴሌን የሚመሩት የኮማንድ ፖስቱም አለቆች ናቸው እና እነርሱ ስለ ንግድ ሕግ፣ ስለ ባንኮች ለደንበኞቻቸው የገቡት ቃልም ሆነ የኢትዮጵያ ባንኮች ለዓለም አቀፍ ባንኮች የገቡት የንግድ ሰነዶች ጉዳይ ሁሉ በወሬ ይሆናል የሚያውቁት። 'ዛሬ ኢንተርነቱን ዝጋው አየሩ ጥሩ አደለም' ካሉ መዝጋት ነው።እዚህ ላይ የባንኮች ለክፍያቸው ታማኝ አለመሆን ያለውን ሌላውን ጣጣ ጉዳያቸው አይደለም። አናርክዝም ወይንም ስርዓት አለበኝነት ማለት ይህ ነው።በሕግ የማይመራ የተቃወሰ መንግስት። በውጪ እና ገቢ ንግዶች ዙርያ ያሉ ክፍያ የሚጠብቁ ዓለም አቀፍ የባንክ የክፍያ መጠየቂያ ሰነዶች ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልጉ እና የክፍያ ሂደቱም ከተባለለት ጊዜ ከፍ ወይም ዝቅ ሳይል መሆን እንዳለበት ይታወቃል። 

አንድ አስመጪ ወይንም ላኪ  እቃው ወደ ሚላክበት ሀገርም ሆነ እቃው ከሚመጣበት ሀገር ያሉ ባንኮች ገንዘባቸው እንዲከፈላቸው የሚፈልጉበት የጊዜ ገደብ በሌተር ኦፍ ክረዲቱ ላይ የተጠቀሰ እና ገዢ እና ሻጭ በገቡበት የውል ሰነድ መሰረት ነው። በሁለቱ ገዢ እና ሻጭ መካከል ከፍተኛ ታማኝ ተብለው የሚያቀባብሉት ደግሞ ኢትዮጵያ ያለው ባንክ እና ውጭ ሀገር ያለው ባንኮች ናቸው። ልብ በሉ። የኢትዮጵያ ቴሌ ሲስተም መዝጋት ስንት የክፍያ ሰነዶች ለቀናት እንዲቀመጡ እና የውጭ ሀገር ባንኮች በእዚህ ሳብያ ስንት ወለድ እንደጠየቁባቸው በእየባንኩ ቤት ያላችሁ መስክሩ።በእዚህ ሳብያ የሚደርሰው ኪሳራ የወለድ ብቻ አይደለም።ወለዱ ቢደመር ኢትዮጵያ በቴሌ እና የኮማንድ ፖስት አለቆቹ ሳብያ ምን ያህል እንደከሰረች መለስተኛ የዳሰሳ ጥናት ቢደረግ አስደንጋጭ እንደሚሆን ለማወቅ ሊቅ መሆን አይጠበቅም። ከእዚህ ሁሉ በላይ ያለው ኪሳራ ግን የኢትዮጵያን መልካም ስም እንዲጠበቅ አድረገው በዓለም አቀፍ ባንኮች ውስጥ ከሁሉም አፍሪካ ሀገሮች በተሻለ ታማኞች የተባሉት የኢትዮጵያ ባንኮችን ስም እንደሚያጎድፍ እና እየቆየም ወደ ጥቁር ዝርዝር መዝገብ እንደሚያስገባን ማወቅ አለብን። 

ለማጠቃለል እነ አባይ ፀሐዬ የቦርድ አባል ሆነው የመሩት የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ የስርዓቱ "አናርክዝም" ወይንም ስርዓት አልበኝነት ሰለባ መሆኑ ሌላው የኢትዮጵያ የወቅቱ ህመም ነው።በየትም ሀገር አልፎ አልፎ የሲስተም መቆራረጥ ሊያጋጥም ይችላል። የኢትዮጵያ ግን ኢንተርኔት የሚዘጋው በተደጋጋሚ ያውም በኮማንድ ፖስቱ አለቆች መሆኑን ሲታሰብ እና እያመጣ ያለው ቀውስ ሲታይ የተቃወሰ መንግስት ምልክት መሆኑ በግልፅ አመላካች ነው።በንግዱ ሕግ እና ስነ-ምግባር መሰረት ቴሌ ለባንኮች አገልግሎቱን ሲሰጥ ውል ገብቷል።ባንኮች ደግሞ ለደንበኞቻቸው አገልግሎታቸውን ሲያቀርቡ ውል ገብተዋል።ቴሌ የገባው ውል አገልግሎቱን ሳያቆም ለማቅረብ ሲሆን ባንኮቹም በበኩላቸው ለሚሰጡት አገልግሎት ምንም አይነት መቆራረጥ ሳይኖር ለማገልገል ነው። ስለሆነም በእዚህ የንግድ ትስስር መሃል አንዱ ውሉን ባያሟላ ሌላው ለሚደርስበት ኪሳራ ተጠያቂ ነው።ኪሳራ የደረሰበትም በፍርድ ቤት ቀርቦ ከሶ ካሳ ማግኘት ይችላል። ይህ የአምባገነን መንግስት መኖር እና አለመኖር ጉዳይ አይደለም።በደርግ ዘመን በትክክል ይቻላል።በደርግ ዘመን የነበረው የመብራት ኃይል እና የውሃ ፍሳሽ አገልግሎቶች በእለተ እሁድ የሚሰጡት አገልግሎት የሚቆም ከሆነ ቀድመው ከሶስት ቀናት በፊት በራድዮ እና ቴሌቭዥን እንዲናገሩ የንግድ ውል ሕጉ ያዛቸዋል። ከደንበኛው ጋር ውል ሲገቡ አገልግሎቱን ላያቆሙ ካቆሙ ግን ቀድመው ሊያሳውቁ ነው። ይህ ቀላል የንግድ ውል ሕግ በተቃወሰው የሕውሓት መንግስት ውስጥ አይሰራም። መብራት እና ውሃ እንደሚቆም ሳይነገር ለቀናት መጥፋት የጅመረው በአናኪዝም ወይንም ስርዓት አለበኛው የሕወሓት መንግስት ነው እንጂ በደርግም ሆነ በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ  ዘመን ማስታወቂያ ሳይነገር ውሃ እና መብራት አይቆምም።ምናልባት ከዋናው ጣቢያ ሳይሆን በመንገድ ላይ በደረሰ አደጋ አገልግሎቱ ካልቆመ ማለት ነው።በዘመነ ሕወሓት ግን ውሃ እና መብራት ለሳምንት ሲጠፋ ማስጠንቀቂያ የሚባል ነገር የለም። ይህንን ነው ስርዓት አልበኝነት ወይንም አናርክዝም የነገሰበት መንግስት የምለው። የዶ/ር ደብረፅዮን መስርያቤት ለባንኮች የሚሰጠውን የኢንተርኔት አገልግሎት በማቆሙ መክፈል ያለበት በሚልዮን ምናልባትም በብልዮን የሚቆጠር ብር አለበት።ባንኮችም ለደንበኞቻቸው መስጠት የሚገባቸውን አገልግሎት በወቅቱ ባለመስጠታቸው ደንበኞቻቸው በንግድ ስራቸው ላይ ለደረሰባቸው ኪሳራ በፍርድ ቤት ከሰው የመጠየቅ መብት አለባቸው።ይህንን ስናገር በዛሬዋ የተቃወሰ መንግስት ውስጥ ስለ ሕልም እንደማወራ እንደምትገምቱ አውቃለሁ።እንደዚህ አይነት ግምት ላይ እንድንደርስ ያደረገን ግን እራሱ አናርክዝም የሰፈነበት ስርዓት ነው። ቢያንስ ግን መሆን ያለበትን እያወቅን እየሆነ ባለው መናደድ ከቻልን ለነገ መስተካከል ያለበትን ከአሁኑ እያወቅን መጣን ማለት ነው።


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Tuesday, June 27, 2017

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የኢትዮጵያ ምድር ላይ ልዩ ጥቅም አለው! የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ የሕወሓት ሀገር ከፋፋይ ቀጣይ አጀንዳ አካል ነው (የጉዳያችን ማስታወሻ)

ጉዳያችን / Gudayacnhn
ሰኔ 21/2009 ዓም (ጁን 28፣2017)
++++++++++++++++++++
ዛሬ ሰኔ 20፣2009 ዓም የሕወሓት ሚኒስትሮች ምክር ቤት የኦሮምያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ የሚኖራት ጥቅም በሚል ርዕስ ውሳኔ ማሳለፉ እና የሕወሓት ኢህአዴግ  99% አሸነፍኩ ወዳለበት ምክር ቤት እንደሚመራ ተነግሯል። ጉዳዩ ልዩ መብት የሰጠ የመሰለው ካለ እርሱ ከ26 አመታት በኃላም ገና ፖለቲካ ሀ ሁ እያለ እንደሆነ መረዳት ያለበት ይመስለኛል።

1/ ልዩ ጥቅም የሁሉም ኢትዮጵያዊ መብት አይደለም እንዴ?

ልዩ ጥቅም የሚለው አባባል በእራሱ የመከፋፈል አላማ ያነገበ አባባል ነው።አንድ ሰው ልዩ ጥቅም ለማግኘት ዋናው መሰረት ሊሆን የሚገባው በኢትዮጵያዊነቱ ነው እንጂ የታሪክ የበላይነት ወይንም የዘር መሰረቱ ወይንም የተለየ አነጋገር በመናገሩን መሰረት አድርጎ የሚሰጥ ከሆነ መከፋፈል ነው።ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የኢትዮጵያ ምድር ላይ ልዩ ጥቅም ሊኖረው ይገባል። ልዩ የሚያደርገው ደግሞ ከኢትዮጵያ ምድር በመውጣቱ ነው።ከጃፓን ወይንም ብራዚል የመጣ ሰው የማይኖረው ልዩ ጥቅም ኢትዮጵያዊ ሊኖረው ይገባል።ይህ ማለት ኦሮሞው አዲስ አበባ ላይ በኢትዮጵያዊነቱ ልዩ ጥቅም እንደሚኖረው ሁሉ አዲስ አበቤውም በኦሮምያ ላይ ልዩ ጥቅም አለው።ኦሮሞው በመቀሌ ላይ ልዩ ጥቅም እንደሚኖረው ሁሉ የአክሱሙም ሰው በኦሮምያ ላይ ልዩ ጥቅም አለው።የወለጋው ገበሬ በጎንደር ላይ ልዩ ጥቅም እንዳለው የራስ ዳሽን ገበሬም በነቀምት ላይ ልዩ ጥቅም አለው።ይህ ሁሉ ልዩ ጥቅም የሚመነጨው እንደ ህወሓት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በከፋፋይ አጀንዳ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት ሙሉ መብት ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጋ እና መሬት በሁሉም የኢትዮጵያ መሬት ላይ ልዩ ጥቅም አለው።የኦሮምያ ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ የሚለው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ  በእራሱ ከፋፋይ የሆነው  የስርዓቱ አጀንዳ ቀጣይ ምዕራፍ ነው።

2/ የውሃ ፍሳሽ አገልግሎት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሰጥ አገልግሎት አይደለም እንዴ?

 "የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት በአዲስ አበባ ዙርያ ላሉ የኦሮምያ ክልሎች ያካተተ ይሆናል" ይላል ከአዋጁ አካል ውስጥ አንዱ።አሁንም ውሃ የማግኘት ልዩ መብት የሁሉም ኢትዮጵያዊ መብት ነው።ይህ አዋጅ ባይወጣ ኖሮ በኢትዮጵያዊነቱ በአዲስ አበባ ዙርያ ያሉ የኦሮምያ ክልሎች የውኃ አገልግሎት ላያገኙ ነበር? የውኃ ፍሳሽ አገልግሎት ለማግኘት የልዩ ጥቅም አዋጅ ባይወጣ ኖሮ በኢትዮጵያውነታቸው የማግኘት መብት የላቸውም ነበር? ይህ በእራሱ ከፋፋይ አቀራረብ ነው።በአዲስ አበባ ዙርያ ያለ የኦሮሞ ሕዝብ ውሃ ለማግኘት ልዩ አዋጅ መጠበቅ ነው ያለበት ወይንስ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያገኘው መብት ነው መሆን ያለበት? ለአዲስ አበባ ውሃ ፍሳሽ አገልግሎት ወጪ የሚሸፈነው  ቀረጥ  ከኦሮምያ የሚመጣ ገንዘብም ጭምር መሆኑን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊያረሳሳን ነው ? እናስ የአዲስ አበባ ዙርያ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ገና ለገና ከአዲስ አበባ ሕዝብ ጋር አብሮ ይነሳብኛል ልከፋፍለው በሚል እሳቤ ውሃ በልዩ ጥቅም አዋጅ መሰረት ይዘረጋልሃል የሚል አዋጅ ረቂቅ አንድ ሐሙስ የቀረው እና የታመመ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ካልሆነ ማን ያወጣዋል?   

3/ የጤና አገልግሎትስ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መብት አይደለም እንዴ?

በአዋጁ ረቂቅ ላይ "አዲስ አበባ ወይም ፊንፊኔ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ በመሆኗ በከተማዋ የሚሰጠው የጤና አገልግሎት በከተማዋ ዙሪያ ያሉ የክልሉ ተወላጆችን ታሳቢ ያደረገ ይሆናል" ይላል። የጤና አገልግሎት የኢትዮጵያዊነት ልዩ ጥቅም ነው።ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍልል ቢኖር የጤና አገልግሎት የማግኘት መብቱ ነው።በእዚህ ረቂቅ ላይ አዲስ አበባ እና ኦሮምያ የተለያዩ ሀገሮች ይመስል በአዲስ አበባ የሚሰጠው የጤና አገልግሎት በከተማዋ ዙርያ ያሉ የክልሉ ተወላጆች ታሳቢ ያደርጋል ሲል ዛሬ ተነስቶ ልዩ ጥቅም የሰጠ አስመስሎ ሕዝብ የመከፋፈል አላማ ለማሳካት ብቻ የተገለፀ ነው።

4/ የአዲስ አበባ ሕዝብ እና የኦሮምያን ሕዝብ ከህወሓት በበለጠ ይተዋወቃል  

በእዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ የአዲስ አበባ ስም በፊንፊኔ፣የከተማዋ አንዳንድ ቦታዎች እና አደባባዮች በኦሮምያ ታሪክ ይቀየራሉ የሚል ሃሳብ የያዙ አረፍተ ነገሮች እንዲሁም ኦሮምኛ ከአማርኛ ጋር የስራ መጠቀምያ ይሆናል ይላል።ኦሮምኛ የስራ መጠቀምያ መሆኑ አማርኛ እስካልገባው ድረስ ኦሮምያ የተወለደ ኢትዮጵያዊ በኦሮምኛ አገልግሎት ማግኘቱ ሙሉ መብቱ ነው።ዛሬ ህወሓት እንደ ልዩ ጥቅም አድርጎ ማቅረቡ ነው የማይመቸው። ይህ እንዴት ልዩ ሆኖ ይቀርባል? ኢትዮጵያዊ መብቱ በሚለው ስር የሚገባ ነው።አንድ የጋምቤላ ተወላጅ አዲስ አበባ መጥቶ አማርኛ ካልገባው በጋምቤላ አነጋገር አገልግሎት የማግኘት መብቱ ኢትዮጵያዊነቱ ያጎናፀፈው መብት ነው እንጂ ልዩ መብት ሊባል ያችልም። ሕወሓት ለመከፋፈል ስትፈልግ ልዩ መብት ብላ ትርክት መጀመሯ አስቂኝ ነው። የአዲስ አበባ ስያሜ መቀየር እና የከተማዋን ታሪካዊ ቦታ ከመቀየር አንፃር የተነሳው አገላለጥ በእራሱ የተደናበሩ ሰዎች ያወጡት ረቂቅ አዋጅ ነው። በመጀመርያ ደረጃ በአዲስ አበባ ውስጥ የተሰጡት ስሞችም ሆኑ የአዲስ አበባ የእራሷ ስያሜ እውን ታሪካዊ አመጣጥ የሌለው ባዶ ትርክት ከነበረ የታሪክ ሰዎች ይንገሩን እና እንመን።በሐሰት ታሪክ ግን የትም ሀገር ስም አይቀየርም። ይህንን ልሞክር የሚል ካለ የመስቀል አደባባይ እና የአብዮት አደባባይ ስያሜን ማስታወስ ነው።በሕልም እና በስሜት ሕዝብ ያጋጭልኛል ከሚል እሳቤ ብቻ ሕወሓት ይህንን ማሰቧን እራሱ የኦሮሞ ሕዝብ እና የአዲስ አበባ ነዋሪ ጠንቅቆ ይረዳል።

ባጠቃላይ ልዩ ጥቅም በሚል ቡልኮ የተሸፈነው የህወሓት ሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቂቅ አዋጅ አዲስ አበባ እና ኦሮምያን የተለያዩ ሀገር በማስመስል የአዲስ አበባ እና ዙርያዋን ያሉት የኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ግንኙነት ኢትዮጵያዊ የሆነ የጋራ እሴት ሳይሆን የጥቅም ግንኙነት ብቻ ያላቸው  አስመስሎ የማቅረብ ሙከራ ነው።መንግስት የተባለ አካል የመጀመርያ ስራው ዜጎቹን በእኩልነት የማስተዳደር፣ሕግ የማውጣት እና የማስፈፀም አቅሙን የማስመስከር  መሆን ይገባው ነበር።ከእዚህ ውጭ አንዱን አስነስቶ በእዚህ አካባቢ ልዩ ጥቅም አለህ።አንተኛው ግን በምትኖርበት ከተማ ከእርሱ ያነሰ ጥቅም ነው የምታገኘው የሚሉ አባባሎች በእራሳቸው ህዝብን ለመከፋፈል የሚደረጉ አጀንዳዎች የማስቀጠል ሥራ አካል ካልሆኑ ሌላ ሊሆኑ አይችሉም። አዲስ አበባ እና ኦሮምኛ ተናጋሪውን ኢትዮጵያዊ ለመከፋፈል አትሞክሩ።ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የኢትዮጵያ ምድር ላይ ልዩ ጥቅም ሊኖረው ይገባል። ሕዝብ የምታገለውም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊነቱ እኩል ልዩ ጥቅም እንዲኖረው ነው።

ይህንን ፅሁፍ የምደመድመው አንድ የኦሮሞ ማኅበረሰብ አክቲቪስት በተናገረው ንግግር ነው። አባበሉ አሁን ሕወሓት እየዳከረበት ካለው የመከፋፈል ከንቱ ሥራ ፍሬ እንደሌለው በሚገባ ያሳየ ነው። አክትቪስቱ ያለው እንዲህ ነበር
"ሕወሓት የኦሮሞ ማሕበረሰብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ያለውን ማኅበራዊ፣ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ትስስር በመቶዎች በሚቆጠሩ  ዓመታት ውስጥ ያለፈ እና ጠንካራ የደም ትስስር መሆኑን ህወሓት በደንብ ያወቀው አይመስለኝም።እነርሱ ራቅ ካለ አካባቢ ስለመጡ የእዚህ አይነቱ ጠንካራ ግንኙነት ታሪክ በደንብ የገባቸው አልመሰለኝም።የኦሮሞ ሕብረተስብ አሁን ሕወሓት እለያይበታለሁ እያለ የሚያቀርባቸው አጀንዳዎችን የመለያያ አጀንዳዎች እንደማይሆኑ ጥንት በሰራቸው ስርዓቶች ካፈረሳቸው ቆይቷል።ሕወሓት ትልቅ የመረጃ ክፍተት ላይ እንዳለ መረዳት አለብን" ነበር ያለው። 



ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Thursday, June 22, 2017

ስምንት ሚልዮን ሕዝብ በረሃብ የሞት አፋፍ ላይ ባለበት ሁኔታ የጅቡቲ ወደብ በፀጥታ ምክንያት አገልግሎቱ የመታጎል አደጋ ተጋርጦበታል (ጉዳያችን ዜና)

ፍጥጫ - አቶ ኢሳያስ እና ኢስማኤል ኦመር ጉሌህ 

አቶ ጆን ግራም (Mr. John Graham) የሕፃናት አድን ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር በተጨነቀ ስሜት ውስጥ ሆነው ለፕሬስ ቲቪ ይህንን የተናገሩት የትናንትናዋ ጀንበር ሳትጠልቅ ነበር።ጆን ግራም እንዲህ ነበር ያሉት -

    " የሕይወት አድን የምግብ እርዳታው ሊቆም ይችላል። በአንድ ወር ውስጥ ያለው የምግብ ክምችት ያልቃል።ከዝያ ምን እንደሚሆን አሁን መገመት አንችልም " (ፕሬስ ቲቪ፣ ሰኔ 15፣2009ዓም )
"We're looking at the food pipeline actually breaking, so the food is running out in about a month's time," John Graham, country director for Save the Children, said, adding, “After that, we don't know what's going to happen." 
እንደ ቴሌቭዥን ጣቢያው የዛሬ ሰኔ 15፣2009 ዓም ዘገባ በሱማሌ ክልል ድርቁ በተባባሰበት አካባቢ በትንሹ ወደ ግማሽ ሚልዮን የሚጠጋ ሕዝብ ቀየውን ትቶ ተሰዷል።የፕሬስ ቴሌቭዥን የኢትዮጵያ አደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሽን ኃላፊ አቶ ምትኩ ካሳን ጠቅሶ እንደዘገበው ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የለገሰው እርዳታ አነስተኛ መሆኑን ማማረራቸውን ይገልፃል።

በተባበሩት መንግስት የዓለም ምግብ ድርጅት (FAO) ገለጣ መሰረት ረሃብ ዋነኛ መሰረቱ ድርቅ ብቻ ሳይሆን የመንግሥታት መልካም ያልሆነ አስተዳደር ውጤት መሆኑን በማያሻማ መንገድ ይገልጣል። ከእዚህ በተጨማሪ ረሃብ የሚከተለው የፀጥታ መደፍረስ መሆኑን ይሄው የዓለም የምግብ ድርጅት ሲገልጥ  "በየትኛውም የዓለማችን ክፍል  ረሃብ የፀጥታ ስጋት ነው "  "Hunger anywhere threatens peace everywhere" (FAO Summit, June, 2002) ይላል። 

በኢትዮጵያ አሁን የተንሰራፋው አድሏዊ ስርዓት እና በዕውቀት ላይ ያልተመሰረተ ነገር ግን በሙስና እና ብልሹ አሰራር የተተበተበው የሕወሓት አገዛዝ ከሩብ ክ/ዘመን በኃላም የኢትዮጵያን የእርሻ ምርት አንዲት ስንዝር ሳያራምድ ይልቁንም የኢትዮጵያን ለም መሬት ለአረብ ቱጃር በመቸብቸብ ዛሬም የስምንት ሚልዮን ሕዝብ ርሃብተኛ የያዘች ሀገር ሆና ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ እርዳታው ዘገየ የምትል ሀገር ሆናለች።ይህ እንግዲህ አዲሱ የፈረንጆች 21ኛው ክፍለ ዘመን (ሚሊንየም) ከገባ ከ17 ዓመታት በኃላም መሆኑ ነው ህመሙ።


ከሁሉም የሚዘገንነው ጉዳይ ደግሞ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እና ራድዮ ድርቁን ከሚገመተው በላይ ደብቀውታል።ሕዝብ ተረባርቦ ወገኖቹን እንዳያድን መረጃው መደበቁ አሁንም በገሃድ እየታየ ነው።የበልግ ዝናብ በብዙ ቦታዎች ላይ በበቂ አለመገኘቱ እና በጎጃም የተነሳውን የአንበጣ መንጋ ትልቅ ስጋት ሆኖ እየታየ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ለመከላከል አሁንም  ምንም አለማድረጉ የህዝቡን ችግር አባብሶታል።የህዝብን መራብ መደበቅ በእራሱ ከሰብአዊ መብት ጥሰት በላይ በዓለም አቀፍ ሕግም የሚያስጠይቅ መሆን እንዳለበት በርካታ አካላት ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወቃል።በላቲን አሜሪካ እና ሩቅ ምስራቅ አገሮች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ረሃብ የደበቁ መንግስታቶቻቸውን ለፍርድ ቤት እያቀረቡ ማስፈረዳቸው የሚታወቅ  ነው። 

በዓለም ምግብ ድርጅት ማብራርያ መሰረት የርሃብ ምክንያቶች በርካታ መሆናቸውን እና በዋናነት ግን ስድስት መሆናቸውን ይገልፃል። በቅድምያ ፅሁፉ በመግቢያነት የሚይስቀምጠው ነጥብ ''ዓለም ለ7 ቢልዮን የዓለማችን ሕዝብ በቂ ምርት ያመርታል'' በማለት ይጀምርና ስድስቱን በአንድ ሀገር ላይ ርሃብ የሚከሰትባቸውን ምክንያቶችን ይዘረዝራል። እነርሱም : - ድህነት (Poverty trap)፣በእርሻ ላይ በቂ መዋለ ንዋይ አለመመደብ ( Lack of investment in agriculture)፣ የአየር ንብረት ለውጥ 
( Climate and Weather)፣ ጦርነት እና የህዝብ ከስፍራው መፈናቀል (War and displacement)፣ ያልተረጋጋ የምግብ ገበያ ( Unstable Market)፣ የተረፈ ምግብ ብክነት ( Food Wastage)።

የኢትዮጵያን የአሁኑን የርሃብ ችግር የሚያባብሰው አንዱ ጉዳይ በአንድ ወር ውስጥ የመካከለኛው ምስራቅ ግለት ከጨመረ እና በጅቡቲ እና በኤርትራ መካከል ግጭት ከተነሳ የኢትዮጵያ ብቸኛ ወደብ ጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የእርዳታ እህል ብቻ ሳይሆን ነዳጅ ጨምሮ ምንም አይነት ሸቀጥ ላይገባ ይችላል።በሱዳን በኩል ይገባ የነበረው የነዳጅ ምርት በአሁኑ ጊዜ አካባቢው በአማፅያን ኃይሎች በመያዙ ሕወሓት የሱዳን መኪናዎችንም ጭምር መከላከል እንዳልቻለ ይታወቃል።በመጪው ሁለት የክረምት ወራት ደግሞ አማፅያኑ የበለጠ ቦታዎችን ለመያዝ አመቺ ሁኔታ ከወንዝ መሙላት እና ሳሮች ተራሮችን ከመሸፈናቸው አንፃር የሕወሓት ሰራዊት በአብዛኛው ይዞታዎቹን እንደሚያጣ መገመት ይችላል።ምክንያቱም በመካናይዝድ ጦር የተሻለ አቅም የሚኖረው ሕወሓት በክረምት ወራት መንቀሳቀስ ስለማይችል ነው።

ይህ በእንዲህ እያለ ኤርትራ ሰሜናዊ ጅቡቲ የሚገኘውን ራስ ዱሜራ ተራራማ ቦታ ኳታር 400 የሚሆኑ ወታደሮቿን ማንሳቷን ተከትሎ መቆጣጠሯ የወቅቱ ሌላው አዲስ ክስተት ነው።ኳታር ስፍራውን የለቀቀችበት እለት ማለትም እኤአ ሰኔ 12 እና 13/2017 ዓም  ሲሆን ኤርትራ ስፍራውን የያዘችውም በተመሳሳይ ሁለት ቀናት መሆኑን የጅቡቲ መንግስት ገልጧል።ይህንኑም  ተከትሎ ቀጣዩ ግጭት ኢትዮጵያ የጅቡቲን ወደብ የመጠቀም አቅሟን በእጅጉ ሊፈታተን የሚችል ሁኔታ እንደሚሆን ተገምቷል።ይህ ማለት ኢትዮጵያ ለአፋጣኝ የምግብ ዕርዳታ ብቻ ሳይሆን የጦር መሳርያ ለማስገባትም የጅቡቲ ወደብ ማለት ብዙ ማለት መሆኑ የታወቀ ነው።

በሕውሃት አስተዳደር ወቅት ኢትዮጵያን ከአካባቢው ሀገሮች በስልታዊ የተፈላጊነቷን ደረጃ ዝቅ እንድትል ካደረጋት አንዱ እና ዋናው ጉዳይ የአቶ መለስ ዜናዊ አስተዳደር ኢትዮጵያ ካለ ወደብ መኖር እንደምትችል በመግለፅ ጉዳዩን ማድበስበሳቸው መሆኑ ይታወሳል። በእርግጥ እዚህ ላይ የሚነሳው ጉዳይ ኢትዮጵያ ወደ ጦርነት መግባት ነበረባት ወይ? የሚል ጥያቄ እንደሚነሳ ይታወቃል። ሆኖም ግን የአቶ መለስ ሕወሓት የወደብ ጉዳይን ወደተራዘመ የመደራደርያ አጀንዳነት ማቅረብ ሲችሉ እና አንዳንድ የአሜሪካ ባለስልጣናትም ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት የመሆኗ ዓለም አቀፍ ሕግ እንደሚፈቅድላት ይሄውም 90 ሚልዮን ሕዝብ በ20 ኪሜ ርቀት ካለወደብ ሊቀመጥ አይችልም የሚለው መከራከርያ ጎልቶ የወጣ ግዙፍ ሃሳብ ነበር።የወደብ ጉዳይ የሕወሓት የኢትዮጵያን ሕዝብ ማማለያ ካርድ ከሆነ ሰንብቷል።ሕወሓት ውጥረት ውስጥ በሚሆንበት ወቅት የወደብ ጉዳይን እንደ ሰሞኑ ጀኔራል ፃድቃን "ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታል" የሚል አረፍተ ነገር የመሰለ የወቅታዊ ካርድ መዘዛ አንዱ አካል ነው።



የጅቡቲ ወደብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሳድ ኦማር ጉለህ 
M. SAAD OMAR GUELPH

ባጠቃላይ ሕወሓት የመዳከሙ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን የበለጠ አደጋ ላይ የጣለ ቡድን ለመሆኑ አንዱ መገለጫ ሆኖ እየቀረበ ያለው ብቸኛ የኢትዮጵያ ገቢ እና ወጪ መስመር የሆነው የጅቡቲን ወደብ መከላከል የማይችል መሆኑን አስመስክሯል።የጅቡቲ ወደብ በአንድ መለስተኛ ሮኬት ተኩስ ጠቅላላ ወደቡ የመድን ሽፋን ዋስትና ሊያጣ እንደሚችል እና የዱባይ ኩባንያ በኮንትራት የሚያስተዳድረው የጅቡቲ ወደብ በማንኛውም ጊዜ በፀጥታ ችግር ሳቢያ አገልግሎቱ ሊቆም እንደሚችል አመላካች ነው። የሃያ ስድስት አመታት የሕወሓት አመራር ኢትዮጵያውያ ወደብ አልባ ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት ሀገር ጅቡቲም የምትጠቀምበትን ወደብ መከላከል የማትችል ሀገር ደረጃ አድርሷታል። ይህ የሕወሓት የስልጣን ጥማት እና እጅግ የጠበበ የጎሳ ፖለቲካ ይህንንም ተከትሎ የፍትህ እና ዲሞክራሲ ጥያቄ የሚጠይቁ ኢትዮጵያውያንን የመግደል፣ማሰር እና ማሰደድ ተግባር  ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ያማዳከም ደረጃው ከሚገመተው በላይ ነው።ለእዚህም ነው ኢትዮጵያን ለማዳን ሕወሓት ስልጣኑን መልቀቁ እና የሽግግር መንግስት መመስረት ብቸኛ ወቅታዊ ሃገራዊ ጥሪ ሆኖ የሚቀርበው።

ጉዳያችን GUDAYACHN

www.gudayachn.com


ማጣቀሻዎች 

- ፕሬስ ቲቪ http://217.218.67.231/Detail/2017/06/22/526188/Ethiopi-UN-Warder-Save-the-Children

- የዓለም ምግብ ድርጅት (ዜሮ ሀንገር)   http://www1.wfp.org/zero-hunger 

- የዓለም ምግብ ድርጅት 2002 ጉባኤ   http://www.fao.org/worldfoodsummit/msd/Y6808e.htm
-


Saturday, June 17, 2017

አገራዊ ንቅናቄው የአገራችንን የፖለቲካ ችግር የሚመጥን መፍትሄ ለመፈለግ ጠቃሚ ነው - ፕ/ብርሃኑ ነጋ።የኢትዮጵያ ጉዳይ ከልብ ያሳስበኛል - አቶ ሌንጮ ለታ


በፅሞና መመካከር - ፕሮፌስር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ ሌንጮ ኦስሎ ጉባኤ (ፎቶ ጉዳያችን)


ጉዳያችን ሪፖርታዥ 
ሰኔ 10፣2009 ዓም 
==============
የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ ቅዳሜ ሰኔ 10፣2009 ዓም በኦስሎ፣ኖርዌይ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ጉባኤ ሁለት ከፍተኛ ኃላፊዎችን ጋብዞ ጉባኤ አካሂዶ ነበር።ይሄው በኦስሎ የቀይ መስቀል ዋና መስርያ ቤት አዳራሽ የተካሄደው ጉባኤ ላይ ከ200 ሰው በላይ የታደመበት ነበር።በጉባኤው ላይ የተጋበዙት የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ ነበሩ።

የዝግጅቱን መክፈቻ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ ሰብሳቢ አቶ ይበልጣል ጋሹ በንግግር ከተከፈተ በኃላ  የመጀመርያ ተናጋሪ የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታ ነበሩ።
አቶ ሌንጮ "ተቀምጨ እንዳልናገር አጭር ነኝ" በሚል ቀልድ አዘል ንግግር ተሰብሳቢውን ፈገግ ካስደረጉ በኃላ የመተባበር አስፈላጊነት ላይ አፅኖት ሰጥተው ተናግረዋል።በመቀጠልም " በ1966 ዓም ንጉሱ ከስልጣን ሲወርዱ እርሳቸው ይወረዱ እንጂ መጪው ጊዜ የተሻለ እንደሆነ በጣም ተስፋ አድርገን ነበር። ካሉ በኃላ ሆኖም ግን ደርግ መጣ ብለዋል።

አቶ ሌንጮ አያይዘውም ደርግ ሲመጣ ከደርግ የባሰ ሊመጣ አይችልም ብለን ስናስብ የባሰ መጣ።ሆኖም ግን ማሰብ የሚገባን ደርግ ሲገድል በቀጥታ `የፍየል ወጠጤ` እያለ ነበር።ስለሆነም የገደለውን ቁጥር መገመት ይቻላል።የአሁኖቹ ግን በስውር ነው።በስውር ያሰሩት፣የገደሉት እና የሰወሩት ሕዝብ ቁጥር አሁን መናገር አንችልም። ምክንያቱም ሁሉን በድብቅ ነው የሚያደርጉት" ካሉ በኃላ ስለመጭዋ ኢትዮጵያ ማሰብ እንደሚገባ እና እርሳችውንም የሚያሳስባቸው ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።ለዚህም የሱማሌ፣ደቡብ ሱዳን ጉዳይ እያነሱ በሰፊው ለማብራራት ሞክረዋል። አቶ ሌንጮ ኢትዮጵያ እስካሁን እንደ ሀገር እንድትቆይ ካደረጋት ጉዳይ ውስጥ ቀዳሚው ያሉት የህዝቡ ጨዋነት መሆኑን ሲናገሩ እንዲህ አሉ - "ኢትዮጵያን እስካሁን ጠብቆ ያኖራት የህዝቧ ጨዋነት እንጂ የመሪዎቿ ብቃት አይደልም" ነበር ያሉት።በመቀጠልም አቶ ሌንጮ አሁን ያለው መንግስትም ሆነ ተቃዋሚዎች እንዲሁም ሕዝቡም ትኩረት የማይሰጠው ጉዳይ የህዝብ ቁጥር መጨመር እና እርሱን ተያይዞ የሚመጣው የአካባቢ ብክለት፣ የማህበራዊ ኑሮ መዳከም እና የህዝብ ኑሮ ማሽቆልቆል ዋነኞቹ ችግሮች ውስጥ እንደሚካተት አብራርተዋል።

ከጉባኤው ተሳታፊዎች በከፊል 


በመቀጠል ንግግር ያደርጉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ነበሩ።ፕሮፌሰሩ ንግግራቸውን የጀመሩት ሶስት ነገሮችን በቅድምያ ካላወቅን ነገን ለማወቅ ያስቸግረናል በሚል መነሻ ነጥቦች ነበር። እነርሱም : -

1/ አሁን የገጠመን ባላንጣ (የወያኔ ስርዓት) ብሔራዊ ጥቅም የሚባል ነገር የማያውቅ፣ ስርዓቱ ስልጣኑን የማያስጠብቅበት ሁኔታ ከተፈጠረ ሁሉ ነገር እንዲወድም የሚሰራ ስርዓት መሆኑን፣

2/ የሀገራችን ፖለቲካ  በብዙ ምክንያቶች ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ያለ መሆኑ እና 

3/ የህዝባችን የሞራል ደረጃ እየወረደ መምጣቱ የሚሉት መሆናቸውን አብራርተዋል።

ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮች የአገር አድን ንቅናቄው መፍትሄ መሆኑን ለማመላከት ንቅናቄው እንዴት ችግሮች ይፈታሉ ብሎ እንደሚሰራ አብራርተዋል።

ለመሆኑ የአገር አድን ንቅናቄው ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች የሚሰጣቸው ስልታዊ ምንድን ናቸው? በሚል በጥያቄ ንግግራቸውን የቀጠሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ንቅናቄው በሚከተሉት ስልታዊ መንገድ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር የመፍታት አቅም እንዳለው አብራርተዋል።

1/ በሚደረጉ የንቅናቄው ውይይቶች መጥራት የሚጎዳላቸው የሃጋራችን የፖለቲካ ችግሮች እንዲጠሩ በማድረግ፣ 

2/ በውይይቱ ሂደት መስማማት።በሂደቱ ላይ ከተስማማን በውጤቱ ላይ መስማማት መጨረሻ የሚመጣ ጉዳይ ነው። አሁን የውይይቱ ሂደት ዲሞክራሲያዊ መሆኑ ላይ መስማማት እና ውጤቱን ደግሞ ሕዝብ እንዲወስን መተው ነው።

በዲሞክራሲ ሂደት ላይ ከተስማማን በሌሎች ጉዳዮች ላይ ልዩነት አይኖርም ማለት አይደለም።ለምሳሌ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ እና በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ የግድ ላንስማማ እንችላለን። ሆኖም  ግን የቀሪ ልዩነታችን መፍቻ ዲሞክራሲያዊ አፈታትን ስለመረጥን ብዥታ አይኖርም  ማለት ነው።

ለጨረታ የቀረበው እና ከበርገን ከተማ የመጡ የጉባኤ ታዳሚዎች በ16 ሺህ የኖርዌይ ክሮነር የወሰዱት ስዕል 

ከእዚህ በተጨማሪ የጋራ ንቅናቄው ምን እያደረገ ነው? ለሚሉ ጥያቄዎች  ፕሮፌሰር ብርሃኑ ሲያስረዱ አገራዊ ንቅናቄው - 

ሀ) ዋና ጉዳዮች ላይ ማትኮር መቻሉ ፣

ለ) ሌሎች ድርጅቶችን እያሰባሰበ ወደ አንድ ነጥብ ማምጣት ላይ እየሰራ መሆኑ፣

ሐ) ድርጅቶችን ማቀፉ የትግሉን መልክአ ምድራዊ ሽፋን ማስፋቱ እና አገራዊ ቅርፅ መያዙ፣ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው። 

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ከላይ የተጠቀሱትን ሶስት የንቅናቄው ተግባራት በምሳሌ ካስረዱ በኃላ የወያኔን ውድቀት ለማፋጠን የሚያስፈልጉ ሶስት አበይት ጉዳዮችን ጠቅሰዋል። እነርሱም -

1ኛ) የጠራ መንገድ በትግሉ ሂደት መያዝ፣

2ኛ) መሬት የያዘ ትግል ማካሄድ እና 

3ኛ) ወያኔ ያዳከመብንን ሞራላዊ ልዕልና መልሰን መገንባት እና ማምጣት የሚሉ ናቸው።

ከላይ የተጠቀሱት ሶስት አበይት ጉዳዮች ውስጥ የሞራል ልዕልናችንን መልሰን መገንባት የእረጅም ጊዜ ስራችን መሆን ያለበት ሲሆን ቀሪዎቹ ሁለቱ ግን በፍጥነት የሚሰሩ እና አሁን እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች መሆናቸውን አውስተዋል።

በእዚሁ ጉባኤ ላይ ከነበሩት የፕሮፌሰር ብርሃኑ እና አቶ ሌንጮ ንግግሮች በተጨማሪ የጥያቄ እና መልስ መርሃ ግብር ነበር።በጥያቄ ከተነሱት ውስጥ አሁን ያለነው ወጣቶች በወያኔ ዘመን ያደግን ስለሆነ ስለ ጎጥ እየሰማን ስላደግን ኢትዮጵያዊ ስሜታችን ሳይጎዳ ለመጠበቅ ምን ማድረግ ´አለብን? የሚል የነበረ ሲሆን አቶ ሌንጮ ሲመልሱ - 

"በኢትዮጵያ ታሪክ ማንም ንጉስ ከእዚህ ብሔር የመጣሁ ነኝ ብሎ አያውቅም።በኢትዮጵያም  ጨቋኝ  የሚባል ብሔር የለም።የጨቆነ ከአንድ ብሔር የወጣ ቡድን ቢሆን ይህ ቡድን ብሄሩን ይወክላል ማለት አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።" ብለዋል።በመጨረሻም አቶ ሌንጮ " እኔ ኦሮሞም ኢትዮጵያዊም መሆን እፈልጋለሁ።" ብለዋል። በማስከተልም ፕሮፌሰር ብርሃኑ ኢትዮጵያዊነት ከኢትዮጵያዊው ወጣት ትውልድ ውስጥ ወጥቷል የሚል ፈፅሞ ግምት እንደሌላቸው እና ለእዚህም በርካታ  ማስረጃዎች መኖራቸውን አብነት እየጠቀሱ አስረድተዋል።

በመጨረሻም በዋናነት የፕሮፌሰር ብርሃኑን እና አቶ ሌንጮ ለታን ንግግር፣ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎች መመለስ፣የገቢ ማሰባሰቢያ ጨረታ የተካሄደበት ጉባኤ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ እንግዶችን በክብር በመሸኘት ተፈፅሟል።ባጠቃላይ በእዚህ ጉባኤ ላይ የታየው ከፍተኛ ዲስፕሊን፣የሰዓት አጠቃቀም እና የመድረክ መስተንግዶ ሁሉ የተዋጣለት እና ደረጃውን የጠበቀ መሆን የጉባኤውን ተሳታፊዎችንም ሆነ እንግዶችን ያስደሰተ ተግባር ሆኖ አምሽቷል። 


ጉዳያችን GUDAYACHN

 www.gudayachn.com

Friday, June 16, 2017

ሰበር ዜና - አዲስ አበባ የሚለውን ስም እና የጎዳናዎቿን ስም ለመቀየር በሕወሓት የሚታዘዘው የኢህአዴግ ምክር ቤት ዛሬ ስብሰባ ይቀመጣል



ሃያ አባላት እንደቀሩት የሚነገረው በሕወሓት የሚታዘዘው የኢህአዴግ ምክር ቤት ዛሬ ሰኔ 10፣2009 ዓም የአዲስ አበባን ስም ወደ ፊንፊኔ ለመቀየር፣የአዲስ አበባ ጎዳና ስሞችን በኦሮሞ ታሪክ ስሞች ለመቀየር፣የአዲስ አበባን የስራ ቋንቋ ኦሮምኛ ለማድረግ፣የኦሮምኛ ተናጋሪዎች አዲስ አበባ ላይ መሬት ካለ ሊዝ እንዲወስዱ ለመፍቀድ እና በአዲስ አበባ ውስጥ ያሉ ሁሉም መስሪያ ቤቶች ሥራ አስኪያጆች በኦሮሞ ተወላጆች ለመቀየር በሚሉ የውሳኔ ሃሳብ አጀንዳዎች ላይ እንደሚመክር ለማወቅ ተችሏል። ዜናውን ከአስተማማኝ ምንጭ መገኘቱን የኢሳት ራድዮ እና ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ በእየፊናቸው ሰኔ 9፣2009 ዓም ምሽት ገልጠዋል።

ሕወሓት አዲስ የመነታረኪያ አጀንዳ ለመሃል ሀገር ለመስጠት እና በዐማራ ክልል የተነሳበትን ብረት ያነሳ ሕዝባዊ ኃይል ለመዋጋት ያቀደ ይመስላል።አሁን በአዲስ አበባ ላይ ሊወሰድ ነው የተባለው እርምጃ ውሎ አድሮ እራሱ ሕወሓትን ጠልፎ እንደሚጥለው ለማወቅ ብዙ ውስብስብ ጉዳዮችን ማሰብ አያስፈልግም።

ከእዚህ በታች አለምነህ ዋሴ ጉዳዩን አስመልክቶ የለቀቀውን ዜና ያዳምጡ።



ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

Monday, June 12, 2017

አርበኞች ግንቦት 7 ለመጀመርያ ጊዜ አዲስ አበባ ላይ ጥቃት መፈፀሙን ገለጠ

Patriotic-Ginbot 7 Movement for Unity and Democracy attacks TPLF´s secret torching house and armament store in Addis Ababa 

የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ለመጀመርያ ጊዜ አዲስ አበባ ከተማ  ውስጥ በሚገኝ የስርዓቱ የሚስጥር ማዕከል ላይ ጥቃት መፈፀሙን አስታወቀ።ጥቃቱ የተፈፀመው የቀድሞው ናዝሬት አውቶብስ ተራ አጠጋብ በሚገኝ የሕወሓት ድብቅ ማሰቃያ እና የመሳርያ ማከማቻ ላይ መሆኑን ይገልጣል።ይህ በአዲስ አበባ የድርጅቱ ሴል በኩል መፈፀሙ የተገለጠው ጥቃት የሚስጥር ማሰቃያ ቤቱንም ሆነ የመሳርያ ግምጃ ቤቱን ሙሉ በሙሉ እንዳወደመው እና ውድመቱ በቶሎ ሳይጠፋ መቆየቱን እና የአዲስ አበባ ህዝብም ለሰዓታት እንዲመለከተው መደርጉን ዜናው ያብራራል።

ድርጅቱ ለኢሳት ራድዮ እና ቴሌቭዥን ዛሬ ሰኔ 5፣2009 ዓም በላከው ዜና ላይ መለቀቁን ለማወቅ ተችሏል።ከእዚህ በተጨማሪ ድርጅቱ በሰሜን ጎንደር የተለያዩ ቦታዎች በስርዓቱ ወታደራዊ ኃይል ላይ ጥቃት መፈፀሙን እና ከስልሳ በላይ እስረኞችን ማስለቀቁን ገልጦ ነበር።ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሕወሓት በኩል የአርበኞች ግንቦት 7 ታጣቂዎች በፈቃዳቸው ወደ መንግስት እጃቸውን ሰጡ የሚል ዜናም የተለቀቀው ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ነበር።

በሌላ በኩል የመንግስት የአርበኞች ግንቦት 7 ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጡ የሚለው ዜና ድርጅቱ ጥቃት የመፈፀሙ አፀፋ ፕሮፓጋንዳ ሆኖ መቅረቡ በትክክልም አንድ አይነት ግጭት መኖሩን አመላካች ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው።የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ላለፉት ሁለት የሳምንታት መጨረሻዎች በሰሜን አሜሪካ እና ካናዳ በተዘጋጁ ሕዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ንግግር ማድረጋቸው ሲታወቅ በያዝነው ሳምንት ቅዳሜ ሰኔ 10 ኦስሎ ኖርዌይ፣ ሰኔ 11 ደግሞ በስዊዘርላን ተመሳሳይ ሕዝባዊ ስብሰባዎች ላይ እንደሚገኙ ከድርጅቱ የወጡ ዘገባዎች ጠቁመዋል።

ከእዚህ በታች አባይ ሚድያ ላይ የአዲስ አበባውን ጥቃት አስመልክቶ የወጣው ዜና ነው። 





ጉዳያችን GUDAYACHN

 www.gudayachn.com