ጉዳያችን - GUDAYACHN
ጉዳያችን - በጉዳያችን ሚድያ፣ኮምኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት የሚዘጋጅ ሲሆን ከ2003 ዓም ጀምሮ በድረ-ገፅ ላይ የነበረ በአሁኑ ጊዜ ከአንድ ሚልዮን በላይ ጎብኚዎች ያሉት ገፅ ነው። Gudayachn is prepared by Gudayachn Multimedia, Communication and Consultant Organization. It has been online since 2011. Currently, Gudayachn is being visited by over One-million readers from all over the world.
Friday, December 5, 2025
Friday, November 28, 2025
Tuesday, November 18, 2025
በጎ ኅሊና የማጣት ችግር እንደ ሀገር ሊጎዳን ይችላል። በጎ ኅሊና ላይ ይተኮር!!! @Εthiopia @positivity
https://www.youtube.com/watch?v=Tq8Nu9U8CjE
Thursday, October 30, 2025
''ሙዝ አትብላ! ጦጣዎች ከጫካ ሊመጡ ይችላሉ።'' ዓይነቱ የጀዋር ጊዜው ያለፈበት ትንተና በኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ላይ።
- ዛሬ በዩቱብ አገኘን ብላችሁ በኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ላይ የምትሳለቁ የዘመናችን ባንዳዎች ግዴላችሁም ጊዜ እና ትውልድ ይፈርዳል! እናንተን ብቻ ሳይሆን ልጆቻችሁም ''አባታቸው በዩቱብ ኢትዮጵያ ላይ የተሳለቀ ባንዳ ነበረ።'' የሚል ታሪክ ትታችሁ እንደምትሄዱ አትጠራጠሩ።
ጀዋር በትናንትናው ዕለት በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለቀርቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ አስመልክቶ በተለይ የቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ፣ታሪካዊ፣ስልታዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ የቀይ ባሕር ይገባኛል ጥያቄ በማስመልከት የጻፈው ጽሑፍ ''ውሃ የማይቋጥር '' ብቻ ሳይሆን ምሑራዊ ሽታ የሌለው ነው።
የጀዋር ሃሳብ በአጭሩ ከ130 ሚልዮን በላይ ህዝብ እንዳላት በተባበሩት መንግስታት የተነገረላት ኢትዮጵያ የባሕር በር ይኑረኝ፣ይህ ለሺህ ዓመታት የነበረ እና ባለፉት 30 ዓመታት ገደማ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ሰነድ በሌለበት መንገድ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዴት አጣች የሚለውን ብሔራዊ ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምክርቤት ውስጥ ማንሳታቸው እንደ የጀዋር ፖለቲካ ይህ ጉዳይ ''ሌሎች ወደ ቀይ ባሕር እንዲሳቡ ያደርጋል።''
በመጀመርያ ደረጃ የቀይ ባሕር በዓለማችን ካሉት ቁልፍ ስልታዊ መተላለፊያዎች ውስጥ አንዱ ነው። በዓለም ታሪክ የተነሱ ኃያላንም ሆኑ የአካባቢ ''ግልገል ኃያላን'' ከቀይ ባሕር ላይ ዓይናቸውን የነቀሉበት ጊዜ መቼ ነው? ጀዋር ካልተቸ ላለማደር ምሎ ከሃገር ስለወጣ ዛሬ የጠራውን የጂኦ ፖለቲካ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስለ ቀይባሕር በማንሳታቸው ባዕዳን ተሰበሰቡ ይለናል። ኢትዮጵያ ስለ ቀይባሕር ባታነሳ የግብጽ፣የሳውዲ እና የሌሎች ሀገሮች የጂኦ ፖለቲካ ስልት ሌላ ነበር ማለት ነው?
በእዚሁ የጀዋር ''ውሃ የማይቋጥር'' ወቀሳ ላይ በሱማሊያ የኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ ግብጽን አመጣ፣ ኬንያ እና ጂቡቲም በኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ ከፋቸው። ያስከፋቸው ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የውጭ ፖሊሲ ስህተት አድርጎ ለማቅረብ ሲሞክር ይታያል።
በመጀመርያ ደረጃ የኢትዮጵያ የወደብ እና የባሕር በር ጥያቄ ግልጽ እና ምንም ሽፍንፍን ያልታየበት ነው። ይህ ግልጽ የውጭ ፖሊሲ ጥራት እና ግልጸኝነትን ያሳያል። የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ሱማልያ፣ጂቡቲም ሆነች ኬንያ በኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ አንጻር አንድም ያሰሙት ቅሬታ የለም ብቻ ሳይሆን ሀገራቱ በኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ ዙርያ ከመግባባት አልፈው ቀድም ብለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያነሱት የአካባቢ ምጣኔ ሃብታዊ ትስስር በተለይ በምስራቅ አፍሪቃ አንጻር ይተነሳውን ሀሳብ እየቆዩ በሚገባ እንዳብላሉት እና እንዳመኑበት ለመረዳት በታላቁ የኢትዮጵያ ግድብ ምረቃ ላይ እራሳቸው ተገኝተው መመረቃቸው ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ የመብራት ትሩፋት በመቋደስ ላይ መሆናቸው አንዱ ማሳያ ነው።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ሳይመለስ ፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሃብታዊም ሆነ ወታደራዊ ሰላም በምስራቅ አፍሪቃ እንደማይሰፍን ጎረቤቶቻችን በሚገባ ይረዳሉ። ለእዚህም ነው የኢትዮጵያ የባሕር በር መመለስ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት ያንቀሳቅሰዋል፣ያሰፋዋል ይህንን ተከትሎ ደግሞ የእነኝህ የጎረቤት ሀገሮች ምጣኔ ሀብት የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆን ሀገራቱ ተረድተዋል። እውነታው ይህ ነው።
የጀዋር ትንተና ለዘለቄታዊ ችግር ኢትዮጵያ የራስ ምታት መድሐኒት እየወሰደች ትቆይ አሁን ስለየባሕር በር ጉዳይ አታንሱ የሚል የጌቶቹን ፕሮፓጋንዳ የማስተጋባት ስራ ነው። ኢትዮጵያን የመውጫ የባሕር በር አያስፈልግሽም ከወጣሽ ሌሎች ይመጣሉ በማለት የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመምከር የሞከረው ጀዋር የበለጠ ሌላ ትዝብት ላይ ወድቋል። ጀዋር በአቶ ኢሣያስ ጉዳይ በግልጽ ሲቃወም ነበር የምናውቀው። ዛሬ ምክር የመሰለች ውስጧ ግን አድርባይነት የተነከረች ምክር ለመምከር መሞከሩ ወዴት ወዴት? የሚያስብል ነው። ጥያቄዎቹ ጀዋር የማንን አጀንዳ ለማራመድ እየሞከረ ነው? በራሳችን ቋንቋ እየጻፈ ለእኛው የባዕዳንን የመካከለኛው ምስራቅ አንዳንድ ሀገሮችን አጀንዳ ሊነግረን የሚሞክረው በምን ያህል የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመናቅ ቢሞክር ነው? የሚሉት ናቸው።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ግልጽ እና የጠራ ነው።አንድ ጂኦፖለቲካ ተንታኝ ነኝ የሚል እንደ ጀዋር የመሰለ ሰው ይህንን ያህል ህዝብን ለማታላለል ሲቃጣ ግን ያሳፍራል። ''ሙዝ አትብላ፣ጦጣዎች ከጫካ ሊመጡ ይችላሉ።'' ዓይነቱ የጀዋር ጊዜው ያለፈበት ትንተና ዋጋ የሚሰጠው አይደለም። ኢትዮጵያ ባለችበት በመቀመጧ ብቻ ለመክበብ ሲሞክሯት እና ጊዜ ያገኙ ሲመስላቸው ደግሞ ለመውረር ሙከራ ተደርጎባታል። ይህ አዲስ ክስተት አይደለም። የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር መውጣት ከታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ መብቷ ባለፈ የደህንነቷ ዋስትናም ጭምር ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያ ስለራቀች የሚርቁላት፣ስለቀረበች የሚቀርቧት አይደሉም። ሁሉም ጀዋርም ሆነ ዛሬ በዩቱብ አገኘን ብላችሁ በኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ላይ የምትሳለቁ የዘመናችን ባንዳዎች ግዴላችሁም ጊዜ እና ትውልድ ይፈርዳል! እናንተን ብቻ ሳይሆን ልጆቻችሁም ''አባታቸው በዩቱብ ኢትዮጵያ ላይ የተሳለቀ ባንዳ ነበረ።'' የሚል ታሪክ ትታችሁ እንደምትሄዱ አትጠራጠሩ። በፋሽሽት ጣልያን ጊዜ ባንዳ የነበሩና የእነርሱ ልጆች ዛሬ ድረስ ማጠብ ያልቻሉት አሳፋሪ ታሪክ እንዳለ መቼም ለዩቱብ ባንዳ ማስታወስ ለቀባሪው ማርዳት ነው።
=================////=========
Saturday, July 26, 2025
ወቅታዊው እና መጪው የኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ምጣኔሃብታዊ እና ማኅበራዊ ሁኔታ በሶስት ርዕሶች ማጠቃለል ይቻላል።
ፎቶ ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የ2017 ዓም የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ መትከል ብሔራዊ ዘመቻ ሲከፍቱ።
=========
ጉዳያችን ምጥን
========
በእዚህ ጽሑፍ ስር ሶስት ምጥን ርዕሶች ያገኛሉ። እነርሱም
- አመንክም አላመንክም ኢትዮጵያ ተነስታለች ፡
- የአቶ ኢሳያስ አፈወርቅ ወደ አክቲቪስትነት መቀየር እና
- የእነ ''ካፈርኩ አይመልሰኝ'' አክቲቪስቶች ግራ መጋባት።
መንደርደርያ
የኢትዮጵያ ያለፉት ሰባት ዓመታት የለውጥ ሂደት የጎጥ ፖለቲካ በአደባባይ የሚያራምደውን፣የጎጥ ፖለቲካን በኢትዮጵያ ስም ሸፍኖ ሲያራምድ የነበረው እና የባዕዳንን ጥቅም በኢትዮጵያ ውስጥ ተደብቆ የሚያራምደው ሁሉ በጊዜው በጊዜ እየጠለለ መምጣቱን በግልጽ አሳይቷል።ጊዜ፣ተግባር እና ባሕሪ ማን ለኢትዮጵያ እንደቆመ፣ማን ለጥቅሙ ሲጋጋጥ እንደነበር፣ማን ስጋ በተጠበሰበት ሁሉ እያሸተተ ለሆዱ በህዝብ ስም ሲምል እንደነበር የታየበት ጊዜ ነው።
የኢትዮጵያ ልቀት፣ቁልፍነት እና ወሳኝነት በዓለም ጂኦ ፖለቲካ ውስጥ ከመቼውም ጊዜ መጉላት በበቂ መረጃ እና በረጅም ጊዜ የኢትዮጵያንና የምስራቅ አፍሪካን ፖለቲካዊ ሁኔታ በደንብ ላልተረዳ አይገባውም። ችግሩ በለብለብ እና ስሜታዊ የዩቱብ ፎካሪዎች የወቅቱን ሀገራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ጉዳይ ለመረዳት፣ለመተንተን ደፋሮች እንደመረጃ ምንጭ እየወሰደ አዕምሮውን ለሚያጭቅ የኢትዮጵያ ወሳኝ ሆና መውጣት አይገባውም።
ይገርማል! የመቶ ዓመታት ታሪክ ብናወራ ሊያከራክረን ይችላል። ያለፉት ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሂደት ከቀደመው ጋር አያይዞ እና መጪውን አሻግሮ ተረድቶ በበቂ መረጃ መለካት አለመቻል ምን ዓይነት ከዕውቀት ነጻ የመሆን በሽታ ነው? ዩቱብ ላይ እየተሰቀሉ ኢትዮጵያ ላይ መዓት ሲያወርዱ የነበሩ በተናጥል መጮሁን ህዝብ እየነቅ ሲመጣ በቡድን እንጩህ የሚል አዲስ ፈሊጥ የኢትዮጵያን እውነተኛ ገጽታ አይቀይርም።
ኢትዮጵያ ዛሬ አመንክም አላመንክም ተነስታለች።
- ኢትዮጵያ የዘመናዊ ትንሳዔ ጊዜዋ ለመሆኑ ብዙ መለኪያዎችን መመልከት ይቻላል
- ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ የቆዩ ነባር የሚዳሰሱ ታሪካዊ ሃብቶቿን እያደሰች ነው።
- ከብሔራዊ ቤተመንግስት እስከ የጎንደር አብያተ መንግስታት የታደሱት ባለፉት 7 ዓመታት ነው።
- ከጅማ አባ ጅፋር ቤተመንግስት እስከ ብሔራዊ ቲያትር፣ሀገርፍቅር ቲያትር እስከ የአክሱም ሃውልት እድሳት የተከናወነው እና እንቅስቃሴው ይተጀመረው ባለፉት 7 ዓመታት ነው።
- ከመቶ ዓመታት በላ ያስቆጠረችው አዲስ አበባ ከተማ በታሪኳ ባላያችው ደረጃ በዓለም ዘመናዊ ከተሞች የሚያሰልፋት ድንቅ እመርታ ያሳየችው ባለፉት 7 ዓመታት ውስጥ ነው።
- ከመቶ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን በዘመኑ ያልነበረ 80 ሚልዮን ህዝብ በላይ ተደራሽ የሆነው ከእዚህ ውስጥ ከ 43 ሚልዮን በላይ የኢንተርኔት ተደራሽ የሆነው እና በሞባይል ባንኪንግ ትሪልዮን ብር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተንቀሳቀሰው ባለፉት 7 ዓመታት ነው።
- ኢትዮጵያ ከመቶ ሚልዮን በላይ የሚሆን ህዝቧን ለመመገብ ቆርጣ የተነሳችው ብቻ ሳይሆን ምግብ ከውጭ መግዛት ማቆም እንደሚቻልና ከበጋ ክረምት ማምረት ባሕል እንዲሆን እየሰራች ያለው ባለፉት 7 ዓመታት ውስጥ ነው።
- የኢትዮጵያ መከላከያ ከ 1 ሚልዮን በላይ መድረሱ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ስትራቴጂስት የተራቀቁ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ አመራሮች እና መኮንኖች የተሞላው ባለፉት 7 ዓመታት ነው።
- የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአፍሪካ ምርጦቹ ውስጥ ብቻ ሳይሆን የራሱን ትጥቅ በራሱ መንገድ ከማዘመን ባለፈ ይድሮን አምራች የሆነው ባለፉት 7 ዓመታት ነው።
- በአፍሪካ ቀንድ፣በመካከለኛው ምስራቅ እና በዓለም ላይ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ቁልፍነት ከአካባቢ ሀገራት ባለፈ በኃያሉ ሀገራት ዘንድም በጥንቃቄ የሚያዩት እና የኢትዮጵያ ሰላም የብዙዎች የጸጥታቸው ህልውና ጉዳይ መሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ግልጽ የሆነው እና የጎላው ባለፉት 7 ዓመታት ነው።
- ኢትዮጵያ 135 ሚልዮን ሀገር መሆኗ የሰጠው ትርጉም ብዙ ሆኗል። የኢትዮጵያ አብዮት በ1966 ዓም ሲፈነዳ የኢትዮጵያ የህዝብ ቁጥር 30 ሚልዮን ነበር። በወቅቱ የኃያላኑ ፍትጊያ ኢትዮጵያ የያዘችው የህዝብ ቁጥር በራሱ የሚፈጥረው ተጽኖ ከጉዳይ ገብቶ ነበር። በአዲስ አበባ የሩስያ አምባሳደር በወቅቱ ለምን ከሱማሊያ ወደ ኢትዮጵያ ቶሎ እንደዞሩ ሲናገሩ። ''እኛ 30 ሚልዮን ህዝብ ምን ያህል ተጽኖ እንደሚፈጥር ይገባናል።''ነበር ያሉት።
- ዛሬ 135 ሚልዮን ህዝብ ምን ማለት እንደሆነ ማለት ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሯዊው የባሕር በር ማገድ የሚፈጥረው ችግር እራስ ላይ የመተኮስ ያህል መሆኑን ኃያላን መንግስታትም ለመረዳት ብዙ ምርምር አይፈልጉም።
- የውሃ ማማ ኢትዮጵያ ዛሬ በውሃ ማማነት ወሬ ላይ ብቻ አይደለችም ከቀናት በኋላ በዓለም ግዙፍ ከሚባሉት የኤሌክትሪክ ማመንጫ ውስጥ የሚመደበውን የአባይ ግድብ ታስመርቃለች።
- ይህ ግድብ ማለት ብዙ ማለት ነው።ግድቡ ማለት ነዳጅ፣በምስራቅ እና መካከለኛው ምስራቅ ላይ የበላይነት የሚፈጥር ጉልበት እና የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ትንሣዔ አዲስ ምዕራፍ ነው።
- ሌሎች በርካታ ጉዳዮች የኢትዮጵያ መነሳት ዕውን አድርገዋል። ካልገባን ወደፊት እየቆየ ይገባናል። ሌላ ምን ይባላል?
የአቶ ኢሳያስ አፈወርቅ ወደ አክቲቪስትነት መቀየር
- አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ ከ34 ዓመታት በኋላ ጣልያን በቅኝ ግዛት በሰራቸው የድሮ ህንጻዎች ውስጥ የሚኒስቴር መስርያቤታቸውን ብቻ ሳይሆን እራሳቸው እየኖሩ እና ለአስመራ አንድ ለዓይን የሚገባ ህንጻ ሳይሰሩላት እንዲሁ ስለ ጦርነት እያወሩ የአዛውንትነት ዘመናቸውን እየገፉ ነው።
- አቶ ኢሳያስ ከነብረ ባሕሪያቸው በላይ ከሊብያው ጋዳፊ እና ከቀድሞው የግብጹ መሪ ሙባረክ የቆዩ የፖለቲካ ስልት እና የክላሽ ተኩስ ሃሳብ ላይ እያሉ ዓለም የድሮን ቴክኖሎጂ እያለፈ ነው።
- አቶ ኢሳያስ በዘመናቸው ወጣቱን የዓሳ ነባሪ ሲሳይ አድርገው፣ ሌላው ቀርቶ የአስመራ ዩንቨርሲቲ በንጉሱ እና በወታደራዊው መንግስት ዘመን ከነበረበት ደረጃ አውርደው ኤርትራን የዕውቀት አልባ መተራመሻ አድርገዋት ኖረው ዛሬም በመግለጫቸው ስለ የሃገራቸው ልማት ማውራት ትተው በኢትዮጵያ ጉዳይ ይፈተፍታሉ።
- እርጅና የሚያመጣው የራሱ ተጽዕኖ ይኖራል። ሁለት ሰዓት ሙሉ ጋዜጠኞቹ እንቅልፋቸው መጥቶ እስኪንገላጀጁ ድረስ የአዛውንቱን የአቶ ኢሳያስን መግለጫ ሲሰሙ ያሳዝናሉ።
- ከሰሞኑ አቶ ኢሳያስ የኤርትራን የወደፊት የዲሞክራሲ ጉዞ ላይ ለውጥ ያቀርባሉ ሲባል የሚያወሩት ስለ ኢትዮጵያ በቻ መሆኑ አስገራሚ ሆኗል።
- የአቶ ኢሳያስ የሰሞኑ መግለጫ ሲጠቃለል። መግለጫ ከማለት ይልቅ የአቲቪስትነት ሚናቸው የጎላበት ነበር። አክቲቪስትነታቸው ደግሞ ለግብጽም፣ለፋኖም፣ለሸኔም በየደረጃው መሆኑ ያስገርማል።
- መግለጫቸው የአንድ ፖሊሲ አውጪ ቢያንስ የአንድ የፖለቲካ መሪ ደረጃ አያሟላም።
የእነ ''ካፈርኩ አይመልሰኝ'' አክቲቪስቶች ግራ መጋባት።
- ኢትዮጵያ የአንድነትን መንገድ ስትከተል፣መንግስት ስለመተባበር፣የትምህርት ፖሊሲው የሚለያይ እንዳይሆን በሚገባ ይቀረጽ ብሎ ሲሰራ፣ኢትዮጵያ በዘመኗ ያልነበራት የሕጻናት ማስተማርያ ትምሕርትቤቶች ላይ አትኩራ ከስር ለሚመጣው ትውልድ ስትተጋ እና ከተሞቿ ሲዘምኑ በኢትዮጵያ ላይ መዓት ሲያወርዱ የነበሩ የዩቱበር ነጋዴዎች ማፈራቸውን ለመደበቅ ቢጥሩም አልቻሉም።
- አሁን በእዚህ የአክቲቪስት ቡድን ውስጥ የኢትዮጵያ እውነት መደበቅ አልቻለም። ግን አንዴ መስኮት ላይ ወጥቶ መዓት ሲያወራ ስለሰነበተ እያፈራ ብቻውን መውጣት አልቻለም።
- በመሆኑም ሰብሰብ ብለን እንጩህ ምናልባት ህዝብ ቢይምነን ሆኗል ጉዳዩ።
- ነገሩ ''ካፈርኩ አይመልሰኝ '' ነው።
- ማፈር ጤናማነት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ መዓት ስታወርድ ከረምክ።መጨረሻ ሰርቶ አሳየህ አፈርክ። ስታፍር ካፈርኩ አይመልሰኝ ብለህ ተሰብስበህ ያውም የኢትዮጵያን መበታተን ላይ ከሰሩ ጋር እንደ ግሪሳ ተሰብስቦ ውሸት በማውራት አይደለም በኢትዮጵያ ህዝብ በገዛ ቤተሰብህ ትዝብት ላይ ወድቀሃል።
- ካፈርኩ አይመልሰኝ የተም አያደርስም። ይልቁን የተሳሳቱን አርሞ በጋር ለኢትዮጵያ መስራት ብቸኛው አማራጭ ነው። ለእዚህ ደግሞ ከእነካፈርኩ አይመልሰኝ ቡድን በድፍረት ለይቶ ስለ ኢትዮጵያ መመስከር ይፈልጋል። ይሄው ነው።
=====================////============
Saturday, June 7, 2025
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሰሞኑ ቃለ መጠይቅ ( አራቱም ክፍል ቃለ መጠይቅ ቪድዮ እዚህ ያገኛሉ)
የኢትዮጵያ የ20ኛውና የ21ኛው ክ/ዘመን ትውልድ ሲታገልለት የነበረው አንዱና ቀዳሚው ጉዳይ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማት ጉዳይ ነው። ጠ/ሚ/ር ዐቢይ በእዚህ ሳምንት ለኢቢሲ የሰጡት ባለ አራት ክፍል ቃለ መጠይቅ ማድመጥ እና የኢትዮጵያን ርዕይ መጋራት የሁሉም ባለ በጎ ሕሊና ዜጋ ግዴታ ነው። ድንቅ ማብራርያ፣ርዕይ እና የሥራ ውጤት ሁሉ በቃለ መጠይቁ በሚገባ ተብራርቷል።
ክፍል 1
ክፍል 2
ክፍል 3
ክፍል 4
===================////===============
Saturday, May 31, 2025
አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ የኢትዮጵያን የቀይ ባሕር ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ዓለም አቀፋዊ የቀይ ባሕርን በሙሉ መብትነት የመጠቀም ጥያቄ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን የአንድ ክልል ጥያቄ አድርገው ለማቅረብ የሞከሩበት መንገድ በራሳቸው ላይ የመተኮስ አደገኛ አካሄድ ነው።
=========
ጉዳያችን ምጥን
=========
አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ በአፍሪካ ውስጥ በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ ከተነሱት የዓለማችን አምባገነኖች የሚመደቡ ብቻ ሳይሆኑ በእነኝህ ዓመታት የተነሱ አምባገነኖች የቀዝቃዛው ጦርነት ውጤቶች ስለሆኑ የተካኑበት ጉዳይ አንድ እና አንድ ነው።ይሄውም በ20ኛው ክ/ዘመን ያረጀው እና ያፈጀው ግጭት፣ሴራ፣እና ጦርነትን ብቻ አራግቦ ስልጣን ማቆየት ነው። አቶ ኢሳያስ የሊብያውን ሙሐመድ ጋዳፊ ከሚያደንቁ መሪ አንዱ ነበሩ። ጋዳፊ ከስልጣን ሲወገዱ ቀኝ እጃቸው የተቆረጠ ያህል በሃዘን መጎዳታቸውን የሚያውቋቸው ይናገራሉ።
አቶ ኢሳያስ የ20ኛውን ክ/ዘመን የሴራ ፖለቲካ በ21ኛው ክ/ዘመን የዲጂታል እና የአርቴፍሻል ኢንተለጀንስ ዘመን ላይ ዓለም የፖለቲካውን፣የምጣኔ ሃብቱንም ሆነ የወታደራዊውን ዓለም በምን ያህል ፍጥነት እንደቀየረው እና ዓለም የሚሰራበት አሰራር እንዳልገባቸው ብቻ ሳይሆን በጣም እንደከበዳቸው ለማወቅ ብዙ ሊቅ መሆን አይፈልግም።
በአቶ ኢሳያስ እና በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መሃከል ያለው የዕውቀት፣ነገሮችን በፍጥነት የመረዳት እና የመጪውን ዘመን በሚገባ የመተንበይ አቅም የሰማይና የምድር ያህል ብቻ እርቀት ያለው አይደለም። ዶ/ር ዐቢይ የብዙ ክህሎቶች ባለቤት መሆናቸው ብቻ አይደለም፣አንባቢነታቸው እና ነገሮችን በፍጥነት የመረዳት እና ችግርን ወደ መልካም የመቀየር ክህሎትም ብቻ አይደለም። ዶ/ር ዐቢይ ብቁ አማካሪዎች ከማቅረብ እና ከእነርሱም የመማር ክህሎታቸው ሁል ጊዜ እጥፍ እርምጃ እንዲቀድሙ ያደርጋቸዋል።
የአፍሪካ መሪዎች አንዱ ችግር ብቁ አማካሪ አለማቅረብ እና አዋቂ አለመስማት ነው። ዶ/ር ዐቢይ በእዚህ በኩል ችግር የለባቸውም።ከአርበኞች ግንቦት 7 ፕሮፌሰር ብርሐኑ ነጋን፣ከአብን የአይቲ ባለሙያ፣ከቀድሞ የኦነግ ሰዎች በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ሌላው ቀርቶ ህወሐትን ሲያገለግሉ የነበሩትን የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ አማካሪ አድርገው የኢትዮጵያን ሥራ ለመስራት ዶ/ር ዐቢይ ልቀታቸውን አሳይተዋል። አቶ ኢሳያስ ዶ/ር ዐቢይ ያሉበት የልቀት ደረጃ ለመድረስ ከአሁን በኋላ ሌላ የ34 ዓመታት ቢጨመርላቸውም ሊደርሱበት ፈጽሞ አይችሉም። ይህ ተራ ትንበያ አይደለም። ይልቁንም አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር የባሕር በር ከሦስት አስር ዓመታት በላይ ይዘው ለኤርትራ ሕዝብ ብልፅግና ሳይሆን አንድ የረባ ህንጻ አስመራ ላይ አልቀየሩም። በንጉሱና በወታደራዊ ዘመን የተሰሩና የታደሱ ስታድዮም ላይ ዘንድሮም የኤርትራ 34ኛ ዓመት በዓል ብሎ የማክበር ያህል የሚያሳፍር ጉዳይ ምን አለ?
አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ በዘመናቸው ሁለት ትውልድ ከኤርትራ ተሰዶ በደርዘን የሜዴትራንያን ባሕር የዓሳ ነባሪ ''ሲሳይ '' ሲሆን እና በሊብያ በረሃዎች ሲንከራተት ማየት እንዴት ህሊና ይሰብራል?
ከ34 ዓመታት በኋላም አቶ ኢሳያስ በዘንድሮ ''የነፃነት በዓል '' ብለው ቀድሞ በኢትዮጵያ የተገነባው ስታድዮም ውስጥ ባደረጉት ንግግር አዲስ የኢትዮጵያን ህዝብ በጎሳ ለማጋጨት ያለመ ንግግር አድርገዋል።|
አቶ ኢሳያስ በእዚሁ በግንቦት 16፣2017 ዓም ባደረጉት ንግግር ላይ የኢትዮጵያን የቀይ ባሕር ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ዓለም አቀፋዊ የቀይ ባሕርን በሙሉ መብትነት የመጠቀም ጥያቄ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን የአንድ ክልል ጥያቄ አድርገው ለማቅረብ የሞከሩበት መንገድ በራስ ላይ የመተኮስ አደገኛ አካሄድ አሳይተዋል።ይህ ንግግራቸው የተስፋ መቁረጥ ንግግር መሆኑን አስረግጦ መንገር ግን ስህተት አይሆንም። ሰው ተስፋ ሲቆርጥ የሚያደርገው የማይቧጠጥ ነገር ይቧጥጣል።
አቶ ኢሳያስ በእዚሁ ንግግራቸው ላይ እንዲህ ማለታቸው ተስምቷል፡ ፟
"ሊያቀርቡ የሚፈልጓቸው ምክንያቶች ብዙ ናቸው። የውሃ ጉዳይ፣ አባይ እና ቀይ ባሕር፣ የባሕር በር ማግኘት፣ የኦሮሞ ሕዝብን የማይወክል የኦሮሙማ አስተሳሰብ፣ የኩሽ እና የሴም ግጭት፣ የአፋር ሕዝብ እና መሬትን ለዚህ አጀንዳ መጠቀም እንዲሁም ጦርነት በሰፊው መቀስቀስ"
በእዚህ ንግግራቸው አቶ ኢሳያስ የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን ስለ ዓባይ ግድብ እና የቀይባሕር ጉዳይ የሚያነሳው አንድ ክልል ነው የሚል ፌዝ አዘል ንግግር ነው። ስለ ኩሽና የሴም ጉዳይ ሲያነሱም የተስፋ መቁረጥ ልኩ የመጨረሻ የጎሳ ካርድ በኢትዮጵያ ላይ ለመምዘዝ የመውተርተር ጉዳይ ነው። አቶ ኢሳያስ ግን ይህ መንገድ እንደማያዋጣቸው በትክክል ያውቁታል። በብዙ ዕውቀት ቢጎዱ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጠንቅቆ በማወቅ ግን ጉድለት ያለባቸው አይመስልም። የኢትዮጵያ ህዝብ በዓባይ እና በቀይባሕር ጉዳይ እንደማይደራደር ብቻ ሳይሆን ማንም መንግስት ጋር በእነኝህ ቁልፍ የህልውናው ጉዳይ ላይ አብሮ ይቆማል። እንዴት በቅጽበት አንድነቱን እንደሚፈጥር እና እንደግስላ ተቆጥቶ እንደሚቆም በሚገባ ያውቁታል።
ለማጠቃለል አቶ ኢሳያስ የቀይባሕር ጉዳይ የአንድ ክልል ጥያቄ እንዳልሆነ እርስዎም ጠንቅቀው ያውቁታል።የኢትዮጵያ ህዝብ ሲወድ ይንከባከባል፣ ከዚያም አልፎ ''ኢሱ! ኢሱ!'' ይላል።ሁሉን እረስቶ ማለት ነው። ሊከፋፍሉት ሲሞክሩ ግን ቢያንስ በምፅዋ በቀይባሕር ውስጥ ለኢትዮጵያ (ኤርትራን ጨምሮ) የተሰዉትን ልጆቹን ያስታውሳል።ይቆጣል። አሁን አቶ ኢሳያስ የኢትዮጵያን ሕዝብ አስቆጥተዋል። በዘር ለመከፋፈል የተጠቀሙበት ንግግር አቶ ኢሳያስ ኢትዮጵያን በዘር የመከፋፈል ሴራ ውስጥ የለሁበትም በማለት ከእዚህ በፊት እየማሉ የተናገሩትን ሁሉ ሃሰት መሆኑን ያረጋገጠ ነው። ''የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም '' እንዲሉ።ባጭሩ አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያሰሙት ከፋፋይ እና ጎሰኛ ንግግር መልሶ ወደራሳቸው ላይ እንደሚባርቅ እረስተውታል።
====================////=============
Subscribe to:
Comments (Atom)
-
The Ethiopian herald News Paper August 20 , 2020 BY STAFF REPORTER Addis Ababa ************************** (EPA) ADDIS ABABA - Over sixty-mil...
-
Gudayachn Report August 14,2020 Senior Hydrologists and water resource Engineers webinar presentation and discussions on creating awareness ...
-
ከመንግሥቱ ጎበዜ ሉንድ ዩንቨርስቲ፣ ስዊድን አፄ ምኒልክ አዋጅን ካስነገሩ በኋላ በአዲስ አበባ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተገኝተው የተሳሉት ስዕለት “አምላከ ቅ/ጊዮርጊስ ድሉን ቢሰጠኝ ይህን የ...