ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, May 17, 2017

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያን የማዳን ኃላፊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየገዘፈ መጥቷል። (የጉዳያችን ማስታወሻ)



 "ጆሮን የተከለው አይሰማምን? ዓይንን የሠራው አያይምን? አሕዛብንስ የሚገሥጸው፥ ለሰውም እውቀት የሚያስተምረው እርሱ አይዘልፍምን? የሰዎች አሳብ ከንቱ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ያውቃል" መዝሙር 94፣ 9

ሁከት በዝቷል፣ጨዋነት ጠፍቷል፣ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ በጎሳ እንዲከፋፈሉ ሆነው በእራሷ በመገናኛ ብዙሃኗ እኩይ የክፍፍል ወሬ እየተነዛባት ነው።ትውልዱ በአራቱም አቅጣጫ እየተሰደደ ነው።ሰርቆ ህንፃ ያቆመ የሚደነቅባት፣ለፍቶ ሰርቶ የሚያድረው የሚናቅበት፣ሹማምንቷ የሀገሪቱን ገንዘብ በጠራራ ፀሐይ ይዘው ሲወጡ ከለንደን እስከ ታይላንድ አየር መንገዶች ላይ የሚያዙበት፣መሪ ተብሎ የተቀመጠው ሰው በቴሌቭዥን ሕፃናት ሳይቀሩ ሲያዩት ውሸት የሚያወራው የተባለበት፣ስታድዮም ውስጥ አብሮ ለመጫወት አንተ ከእዚህኛው ክልል አንተ ከእዝያ ማዶ ነህ እየታባባለ የሚቧቀስበት፣ ባለስልጣናቱ ሁሉ መድረክ ላይ ወጥተው ከኢትዮጵያውነታቸው ይልቅ ከእዚህ ዘር ነኝ የመጣሁት የሚባባሉበት፣ኢትዮጵያ ሴት ልጆቿ ከወላጆቻቸው ጋር ወግ ማዕረግ በማየቻቸው የአፍላ ወጣትነት ጊዜያቸው ለአረብ ሀገር የፈተና ሥራ ፍዳ የሚያዩበት፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ሌሎች የእምነት አካላት ሁሉ በቀጥታ በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የተሾሙበት፣ ሕዝብ ሃዘን ላይ የሚገኝበት ወቅት ነው።

ይህ ብቻ አይደለም ወቅቱ ዓለም የኢትዮጵያን አካሄድ በጥንቃቄ እያየ እየተሳቀቀ እና ግራ እየተጋባ ያለበት ወቅት ነው። ወዲህ አዋጅ ያወጀበት ሕዝብ ላይ እልቂት የሚፈፅመው ስርዓት በእውር ድንብር አካሄድ ያገኘውን እያሰረ እና እየገደለ ልጆቿን እያሰቃየ በሌላ በኩል ኢትዮጵያን በባዕዳን ስትከበብ ሁሉ ምንም እንዳልሆነ ከማታለል በላይ የኢትዮጵያን ህልውና ከሚፈታተኑ ሁሉ ጋር ግንባር እየፈጠረ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጦርነት ያወጀበት ነው።በሕወሓት እና ሱዳን መካከል የተደረገው ስምምነት ክርስቲያኑን ሕዝብ በመግደል እና በመጨረስ አላማ ላይ ያለመ ነው።ኢትዮጵያውያን ከውስጥ እሳት ከውጭ ረመጥ ሆኖባቸው መከራቸው እየባሰ ነው።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ሌሎች የእምነት አካላት ሁሉ ከላይ በተጠቀሰው ፈተና ውስጥ የተዋጡ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው።በኢትየጵያ ቤተ ክርስቲያን አንፃርም እነኝህ ፈተናዎች እና የስርዓቱ ቤተ ክርስቲያኒቱን የማጎስቆል እና የማዳከም ተከታታይ ሥራ ላለፉት 25 ዓመታት ተሰርቷል።ባለፉት 25 ዓመታት የስርዓቱ ዕቅድ ቤተ ክርስቲያኒቱን አሁን ካለችበት ደረጃ በበለጠ መልኩ መቆጣጠር እና ማዳከም ቢሆንም የተሸረበውን እኩይ ዕቅድ ስርዓቱ በፈለገው ደረጃ ሙሉ በሙሉ ሄዶለታል ማለት አይቻልም። ለእዚህም ማስረጃው የምዕመኑ መጠንከር እና የበለጠ ቤተ ክርስቲያኑን በቅርብ ማወቁ ነው።ይህም ሆኖ ግን ከላይ ያለው መዋቅር ንቁ እንዳይሆን ብቻ ሳይሆን በሙስና እና ብልሹ ተግባራት ሲታመስ ሕግ አስከባሪ ነኝ የሚለው ስርዓት አንድም እገዛ ሳያደርግ ይልቁንም ለሕገ ወጦች የፖሊስ ኃይል ሁሉ እየመደበ ቤተ ክርስቲያኒቱ አሁን ላለችበት ደረጃ አድርሷታል። 

የሙስናውን ደረጃም በቅርቡ አቡነ ማቴዎስ ለሸገር ራድዮ እንደተናገሩት " ሁኔታው ከአቅም በላይ ሆኗል" ብለዋል። ከአቅም በላይ የሆነ ነገር በእግዚአብሔር በምታምን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፈፅሞ ቦታ ባይኖረውም እርሳቸው ግን ብለውታል።በተለይ ይህ ፅሁፍ በሚፃፍበት ሰዓት በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአሜሪካ እና አዲስ አበባ የግንቦት ርክበ ካህናት የሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ናቸው። በውጭ በአቡነ መርቆርዮስ በአገር ውስጥ በአቡነ ማትያስ ሰብሳቢነት። ይህ በእራሱ እንደ ሀገር አንዱ ስብራታችን ነው።የዘመናችን ቁስል ነው።ይህንን ቁስል ለልጆቻችን ሳይተላለፍ እንዴት ማጠገግ እና ማሻር ይቻላል? የሚለው በእያንዳንዱ ምእመን እና አባቶች ላይ የወደቀ ሸክም ነው።ይህ ሁሉ የሆነብን ይህ ስርዓት በጎሳ ላይ የተመሰረተ መከራ በላያችን ላይ ከጫነብን ጊዜ ጀምሮ ነው።እዳው ግን ይሄው እሳክሁን ቤተ ክርስቲያኒቱን እና ሀገሪቱን እያንገላታት ነው።የሚገርመው የቤተ ክርስቲያንን መከፋፈል በፅኑ ስርዓቱ እንደሚደግፈው ለመረዳት ላለፉት 25 ዓመታት ችግሩን እንደ ችግር አይቶ ለመፍታት ስንዝር ያህል የሄደበት ሂደት አለመኖሩን መመልከቱ በእራሱ በቂ ነው።ይልቁንም አባቶች በእራሳቸው ወደ ውይይት መድረክ ሲቀርቡ (የዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ውይይትን ያስታውሷል) እነ አቦይ ስብሐት ተነስተው "መሰቀል አለባቸው" እና ሌሎችም አባባሎች በመናገር የቀድሞው ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስን የተናገሩትን እንዲያጥፉ በማስፈራራት ጭምር ኢትዮጵያ የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች ለሁለት እንዲከፈሉ ከወትሮውም የሰሩ መሆናቸውን ዳግም አስመስክረዋል።

የኢትዮጵያ ጥሪ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን 

አሁን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን እየተጣራች ነው።አንቺ ከሰማያዊ አምላክ ጋር ገፅ ለገፅ የተነጋገሩብሽ  ቤተ ክርስቲያን ልጆቼ በዘር እየከፋፈለ የሚያፋጅ መንግስት ሲያምሰኝ ዝም አትበይ። ልጆቼ በእየእሥር ቤቱ ተወርውረው እየማቀቁ እና በጎጥ እየተለዩ እየተሰደቡ ነው እና ከሕዝቡ ጋር አብረሽ አልቅሺ። ዋልድባን የሚያህል ለመላው ዓለም የሚፀልዩ የተሰወሩ አባቶች ፀጋ የሰፈነበት ገዳም ያሉ አባቶች ሲሰደዱ እና ሲገረፉ ካህናቶችሽ ማቅ ለብሰው ያልቅሱ።እንባቸው በሕዝብ ፊት ይታይ።የሃይማኖት ሰው ሃዘን እግዚአብሔርን ከዙፋኑ ይጠራዋል።የአዳም እንባ መድኃኔአለምን ከዙፋኑ እንደሳበው። የእኔ ነገር እንዲህ ሕፃን አዋቂውን አስጨንቆት ሕዝቤ ይህ መንግስት እንደ ሩዋንዳ ሊያባላን ነው እያለ በጭንቀት ላይ ሆኖ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሆይ!  ከጳጳሳቶችሽ  ከስር ባሉ ካህናቶችሽ እና ምእመናን ጋር በአደባባይ አልቅሺ።ማልቀስ ሲከለክሉሽ  ካህናቱ ቢታሰሩ ይሻላቸዋል።የኢትዮጵያ እንባ መሬቱን እያራሰው የሲቃ ድምፅ አለምን ሳይቀር እያስተከዘ በሕዝብ መሃል ከመኖር ከታሰሩት ጋር መታሰር ይሻላል። እርግጥ ነው የዕለቱም ሆነ የሳምንታቱ ፀሎት፣ቅዳሴ እና ምልጃ ሁሉ እንደሚያግዘኝ አውቃለሁ።የአሁኑ ወቅት ግን ከእዚህ የበዛ ድምፅ ወደሰማይ ማሰማት የሚሻበት ወቅት ነው። እስከዛሬ በለሆሳስ ከነበረ ፀሎቱ አሁን በእንባ እና የምድርን ዳር በሚንጥ እንዲሁም ወደ እግዚአብሔር በበለጠ በመጮህ መሆን አለበት። እስከዛሬ ትንሽ ትንሽ በመራብ ከነበረ አሁን የበለጠ በመጦም መሆን አለበት።እስከዛሬ ልጆቼ በጎሳ እየከፋፈለ የሚያባላቸውን ስርዓት በፍርሃትም ሆነ በአርምሞ ዝም በማለት ከነበረ አሁን በግልጥ አደባባይ ወጥቶ በመናገር እና ልጆቼን ከጥፋት በማዳን መሆን አለበት።

በእዚህ ሰዓት ምእመን ጳጳሱን የሚጠብቅበት፣ዲያቆኑ ቄሱን የሚጠብቅበት ወቅት አይደለም።ምዕመኑም ዲያቆኑን የሚጠብቅበት አይደለም።ኢትዮጵያን በዘር ፍጅት ውስጥ ለመክተት የመጨረሻ አማራጭ አድርጎ ስርዓቱ ወስኗል።ወንጀልን ለመሸፈን በእርስ በርስ የዘር ፍጅት አስነስቶ በሕዝብ ደም ታጥቦ አቅጣጫ ለማስቀየር።ለእዚህ ብዙ ምልክቶች ታይተዋል።በሱማሌ እና ኦሮሞ፣በአፋር እና ትግራይ፣በአፋር እና አማራ፣ወዘተ ግጭቶች የተነሱት በስርዓቱ አነሳሽነት መሆኑ ግልጥ ሆኗል።በቅርቡ በመቀሌ ስታድዮም የተነሳው የባህርዳር ከነማ እና የመቀሌ አቻው መሃል የተነሳውን ብንመለከት ችግሩ ስርዓቱን ያሳሰበው ሳይሆን ይልቁንም በትዕቢት  መመልከትን መርጧል። የትግራይ ፖሊስ አዛዥ ለጀርመን ድምፅ ራድዮ ሲመልሱ "ምን አገባችሁ" የሚል ምላሽ ነበር።ይህንን የሰሙ የስርዓቱ ደጋፊዎች እሰይ ደግ አደርጉ የሚል ምላሽ የሰጡ ሲኖሩ ሌሎች ጉዳዩ ያሳሰባቸው አሉ።ይህ ሁሉ የሚያሳየን መጪው ጊዜ ኢትዮጵያውያንን በመጪው ጊዜያት ህዝብን ሊያፋጅ የተዘጋጀ ሕዝብ እርስ በርስ እንዲታረቅ ምንም ጥረት የማያደርግ ይልቁንም እራሱ የፀብ ጫሪ መንግስት እንዳለን ካወቅን ሰንብተናል።በእዚህ ጊዜ የጎሳ ፖለቲካን አውግዘው ኢትይጵያውያንን የህብረት መንገድ የሚያሳዩ የሃይማኖት አርበኞች በመብራት ይፈለጋሉ።ይህንን የማያደርግ ሃይማኖተኛ ነኝ ብሎ ልናገር ከቶ አይችልም።ኢትዮጵያ የኢትዮያ ቤተ ክርስቲያንን ስትጣራ ከጳጳስ እስከ ተራ ምእመን ያለህ ሃይማኖት አለኝ የምትል ሁሉ ሕዝቤን ፍቅር እና አንድነትን እያስተማራችሁ ከተደገሰብኝ የእልቂት ድግስ አድኑኝ እያለች ነው።በሃይማኖት በኢትዮጵያ ላይ የተደገሰውን የእልቂት አዋጅ እንጋፈጥ።በሃይማኖት የተነሳን የሚችለው ምድራዊ ኃይል የለም።ሃይማኖት ብረቱን ያቀልጣል፣ተራራን ይንዳል፣ጨለማውን ይገፈዋልና።

አረሳት ኢትዮጵያን በዘማሪ ይልማ ኃይሉ 







ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...