ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, August 18, 2022

በግሪክ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የቤተመንግስትንም ሆነ የቤተክህነትን አፋጣኝ መፍትሔዎች ይፈልጋሉ።

ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ እጃቸውን ከፍ አድርገው ሊቀበላቸው የወጣውን ሕዝብ ሰላምታ ሲያቀርቡ
 1947 ዓም


በእዚህ ጽሑፍ ሥር የሚከተሉት ንዑስ ርዕሶች ያገኛሉ።
  • ኢትዮጵያና ግሪክ
  • የወጣቷ ኢትዮጵያዊት እናት ጭንቀት በግሪክ፣
  • በግሪክ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የችግሮቻቸው መፍትሔዎች እራሳቸው ኢትዮጵያውያኑ ጋር እና አዲስ አበባ ቤተመንግስትም ነው
  • ከቤተክህነት የሚጠበቀው አፋጣኝ መፍትሔ
==============
ጉዳያችን ልዩ ሪፖርታዥ
==============

ኢትዮጵያና ግሪክ

ኢትዮጵያና ግሪክ ወደኋላ ከአምስት ሺህ ዓመታት በላይ ታሪክ ያላቸው ጥንታውያን አገሮች ውስጥ በቀዳሚነት ከሚቀመጡት ውስጥ ናቸው።800 ዓዓ አካባቢ የኖረው የግሪክ ባለቅኔ ሆሜር ኢትዮጵያን በጽሑፉ ከትቧታል። በግሪክ አይቲዮፕያ የጠይም ሰው መገለጫ ነው። ኢትዮጵያ እና ግሪክ የጥንቱ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን  ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ስላላቸው ብቻ ሳይሆን በቀላሉ የማይቦረቦር ክፍለ ዘመናትን በኩራት የተሻገረ ባሕል ባለቤቶች ናቸው።ከእዚህ በዘለለ ወደ የጥንቱ የዓለም ታሪክ ስንሄድ ኢትዮጵያ በቀይባህር ላይ ባላት የበላይነት፣ግሪክ ደግሞ በሜዴትራንያን ባህር ላይ ባላት ስልታዊ ወሳኝ አቀማመጥ አንጻር ከንግድ ግንኙነት በላይ ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው ጉልህ ነበር።

በዘመናዊዋ ኢትዮጵያ በቀዳማዊ  አጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ኢትዮጵያ እና ግሪክ ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ የተሸጋገረበት ነበር።ንጉሱ በ1947 ዓም ግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ ሲገቡ የአቴንስ ሕዝብ በከፍተኛ ቁጥር በአደባባይ ወጥቶ ተቀብሏቸዋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጸረ ፋሽሽት ትግል አኩሪ ገድል የፈጸመው የግሪክ ህዝብ በአውሮፓ ደርሶ እንደነበረው ጦርነቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1945 ዓም እንደተጠናቀቀ ረሃብ ገብቶ ነበር። በእዚህ ጊዜ ታድያ አፄ ኃይለሥላሴ አቴንስ ከተማ ተገኝተው ቁጥሩ ብዙ የሆነ የቁም ከብት ገዝተው ህዝቡን በአደባባይ ስጋ አብልተዋል። ይህ ሥጋ ህዝቡን ያበሉበት ቦታ አሁን ድረስ አቢሲንያ አደባባይ ይባላል።የእዚህ ጽሑፍ አዘጋጅም ቦታው ድረስ ሄዶ በአደባባዩ ዙርያ ያሉ ባለሱቆችን ለምን የአቢሲንያ አደባባይ ተባለ ብሎ ሲጠይቃቸው ይህንኑ ንጉሱ የሰሩት የቸርነት ሥራ አስታውሰው ነግረውታል። 

ግሪኮች በንጉሡ ጊዜ በተለይ ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ በመኖር በንግድ፣በመምህርነት፣በግንባታ እና በተለያዩ ሙያዎች ተሰማርተው ለኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።እዚህ ላይ የሱፐርማርኬት ባለቤቱ እና ከቤቴ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተለይቶኝ አያውቅም ያለው አቶ ባምቢስን ማስታወስ ይቻላል።ይህ ሁሉ ሆኖ በአሁኑ ጊዜ ግን ኢትዮጵያውያን እና ግሪካውያን ግንኙነት ላይ በጣም የጠለቀ ግንኙነት አይታይም።አዳዲሶቹ የሁለቱ አገሮች ትውልዶች በሚገባ መተዋወቅ እንዲችሉ የባሕል ልውውጥ እና የንግድ ግንኙነታቸውን ማሳደግ አለባቸው።

ዛሬ ላይ የወጣቷ ኢትዮጵያዊት እናት ጭንቀት በግሪክ

ግሪክ በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩባት ይነገራል።ኢትዮጵያውያን ወደ ግሪክ የሚመጡት ባብዛኛው በስደተኝነት ሲሆን የሚገቡበት አቅጣጫ በሦስት መንገድ ነው። እነርሱም በቀጥታ በአይሮፕላን ከአዲስ አበባ፣በቱርክ እና በሊብያ በኩል እንዲሁም ከመካከለኛው ምሥራቅ በኩል ነው።ግሪካውያን ኢትዮጵያውያንን ይወዳሉ፣ያመሰግናሉ።ኢትዮጵያውያን ጥሩዎች እና ታማኞች ናቸው የሚለው አባባል ከታክሲ ነጂ እስከ የላይኛው የሃብት ደረጃ ያሉ ግሪካውያን ይመሰክራሉ።

የስደተኞቹን ሁኔታ ለመግለጽ የእዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የተመለከተውን እንዳለ ማቅረቡ ለአንባቢ ስዕሉን ይሰጣል።

እድሜዋ ገና ሓያዎቹ መጀመርያ ያለች ወጣት ነች።በተደላደለ ኑሮ ላይ እንደነበረች ታስታውቃለች።ግሪክ በሆነ አጋጣሚ ስደት ብላ ከአገሯ እንደወጣች ነው የነገረችኝ።ሁለት ልጆቿን የወለደችው ግሪክ ነው። ቋሚ ሥራ እንዳትሰራ ልጆቿን የምታውልበት ያስፈልጋታል።ስለሆነም መሥራት ከሚገባት በታች ለመሥራት ተገዳለች።ከቤተክርስቲያን ወጥታ ሁለቱ ልጆቿ ቤተክርስቲያኑ በር ላይ ሲጫወቱ ፍዝዝ ብላ ታያቸዋለች።ልጆቹ የእናታቸው ሃሳብ እና ጭንቀት አይገባቸውም።እናት በግሪክ ያላት ጊዜያዊ ፈቃድ ስለሆነ ነገ የእርሷም ሆነ የልጆቿ ዕጣ ያሳስባታል። ከእዚህ ሁሉ በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ ልጆቿ ትምሕርት መጀመር ባለባቸው ጊዜ ላይጀምሩ ይችላሉ።ምክንያቱም ፈቃድ የሌለው ወላጅ ልጆቹን ሲያስመዘግብ የሕጋዊነት ፍቃድ አብሮ ይታያል።ይህ ሁኔታ ከአንዱ ትምሕርት ቤት ወደሌላው ይለያያል።አንዳንዱ ጋር ያጠብቃሉ።ሌላው ጋር ሊላላ ይችላል። ወታቷ እናት ልጆቿ ሲጫወቱ ፈዛ የምታስበው ይህንን ሁሉ ነው።

ከእዚህ በተለየ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሰርተው የሚኖሩ እና ከእርሳቸው አልፈው ለቤተሰብም የሚደጉሙ ናቸው።አብዛኛዎቹ የአዲሱ ትውልድ አካል የሆኑ እና ትኩስ አምራች ኃይል ናቸው።ከቤተክርስቲያን እስከ የእርስ በርስ መተሳሰባቸው፣የተቸገሩትን የመርዳት እና የመተባበር አቅማቸው እና ማኅበራዊ ኑሯቸው የሚያስደንቅ ነው።ከሥራ በኋላ ያላቸው የማኅበራዊ ኑሮ ግንኙነታቸው እና በጋራ በደስታ የመገናኘታቸው ሁኔታ ሁሉ አስደናቂ ነው።

በግሪክ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የችግሮቻቸው መፍትሔዎች እራሳቸው ኢትዮጵያውያኑ ጋር እና አዲስ አበባ ቤተመንግስትም ነው

በግሪክ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ካሉባቸው ችግሮች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ እና መፍትሔዎቻቸው 

ችግሮቹ  
  • በሚገባ አለመደራጀት፣
  • የጋራ መገናኛ ሚድያ አለመኖር፣
  • የስደተኞቹን የፈቃድ አሰጣጥ እና በአውሮፓ ሕብረት ሕግ የተሰጣቸው መብት ለግሪክ መንግስት አቅርቦ የሚያስረዳ የሕግ ባለሙያ ማጣት፣
  • በዓለም አቀፍ ሕግ መማር የማንኛውም ሰው መብት ሆኖ ሳለ አንዳንድ ትምሕርትቤቶች ፍቃድ የሌላቸው ወላጆች ልጆች ትምሕርት ቤት ለማስመዝገብ የሚያዩት ፈተናዎች፣
  • መሰረታዊ የገንዘብ አያይዝ ስልጠና አለማግኘት።ከእዚህ ጋር ኢትዮጵያውያኑ ሰርተው የሚያገኙትን ገንዘብ ምን ዓይነት አዋጭ እና አትራፊ ነገር ላይ ማዋል እንዳለባቸው ምክር ይፈልጋሉ።
መፍትሔዎቹ 

1/የኢትዮጵያ መንግስት ክፍተኛ ልዩ ልዑክ ወደ ግሪክ ልኮ ከግሪክ መንግስት ጋር በሚከተሉት ወሳኝ ነጥቦች ላይ ከሚመለከታቸው ባለስልጣናት ጋር መነጋገር አለበት።እነርሱም 
                i / የኢትዮጵያውያን የስደተኛ ወረቀቶቻቸው ሲያድሱላቸው እንዲቀላጠፍ እና የኢትዮጵያውያንን ጉዳይ የግሪክ መንግስት በልዩ ሁኔታ እንዲታይ ታሪካዊ ግንኙነታችንን ጠቅሶ እንዲሻሻል ማስደረግ ይቻላል።የግሪክ ሕዝብ ኢትዮጵያውያንን በጣም ነው የሚረዳው።ነገር ግን በመንግስት በኩል ያሉ ቢሮክራሲዎች እንዲሻሻሉ እና ኢትዮጵያውያኖች ለግሪክ ኢኮኖሚ የሚያደርጉትን አስተዋጾ እንዲጨምር ማግባባት ይቻላል።

                ii / ፍቃድ የሌላቸው ወላጆች ልጆቻቸው በቀላሉ ትምህርት ቤት የመግባታቸው ሂደት ቢሮክራሲው እንዳያደናቅፍ የኢትዮጵያ መንግስት በግልጽ ከግሪክ መንግስት ጋር መነጋገር አለበት።ይህ ዓለም አቀፍ መብት ከመሆኑ አንጻር ኢትዮጵያም ግሪክም ትምህርት ለሁሉም አስገዳጅ ዓለም አቀፍ ሕግ ፈራሚ ናቸው።

2/ የኢትዮጵያ መንግስት ልዑካንን ልኮ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ማነጋገር አለበት።ልዑኩ ከኢትዮጵያውያኑ ምን ድጋፍ እንደሚፈልጉ፣ወደ አገር ቤት መመለስ የሚፈልጉ ካሉ ለመመለስ ድጋፍ የሚደረግበት መንገድ ማመላከት ያስፈልጋል።

3/ የኢትዮጵያ መንግስት ከግሪክ ጋር ያለውን የባሕል ልምድ ልውውጥ ማጠናከር አለበት።ግሪክ በባሕል የበለጸገ አገር ነች። የኢትዮጵያ የባሕል ልዑካን ወደ ግሪክ እየመጡ ግሪካውያንንም ወደ ኢትዮጵያ እየሄዱ ሁለቱ ህዝቦች የሚተዋወቁበትን መንገድ መክፈቱ ለረጅም ጊዜ በሁለቱ አገሮች ያለውን ግንኙነት ቢያጠናክርም በግሪክ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በግሪካውያን ዘንድ ባሕላቸውን እንዲያስተዋውቁ እና በኩራት እንዲሄዱ የማድረግ ፋይዳው ከፍተኛ ነው።

4/ ኢትዮጵያውያን በሚገባ መደራጀት አለባቸው። የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በከፍተኛ ደረጃ መጠናከር ያስፈልገዋል። ለእዚህም ከአደረጃጀት እስከ ዘመኑን የዋጀ መዋቅር አሰራሮችን ማዘመን እና እያንዳንዱ ኢትዮጵያውያንን በቀላሉ በቴክኖሎጂ ተደራሽ በሆነ መልኩ የመድረስ አቅም ማስፋት ያስፈልጋል።ካልተደራጁ በቀላሉ መጠቃት ይመጣል።ኢትዮጵያውያን ከሚሰሩባቸው ቦታዎች የሚነሱ ክርክሮች፣በደሎች ቢኖሩ በቀላሉ ኮሚኒቲያቸው የሕግ ክፍል አብሯቸው እንዲቆም ማድረግ ይቻላል። 

ከቤተክህነት የሚጠበቀው አፋጣኝ መፍትሔ

በግሪክ አንዱ እና የብዙ ኢትዮጵያውያንን አዕምሮ የሚፈትነው ጉዳይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲንከባለሉ የመጡት ችግሮች የህዝቡን ማኅበራዊ ግንኙነት እስከማወክ መድረሳቸው እና መንግስትም ሆነ ቤተክህነት በጥብቅ ተከታትለው አፋጣኝ መፍትሔ እንዲወሰድ ማድረግ አለባቸው። በሥራ የደከመ ኢትዮጵያዊ በሰንበት ከአምላኩ የሚገናኝበት የሰላም ቦታ ይፈልጋል።የቤተክርስቲያን አንዳንድ ችግሮች ቀኖናዊ እና ስርዓታዊ በመሆናቸው ግሪክ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚፈቱት ሳይሆን የግድ ቤተክሕነት ጊዜ ሳይሰጥ መፍትሄ መስጠት የሚገባቸው ናቸው።በእዚህ ጉዳይ ዝርዝር ሁኔታ ላይ ጉዳያችን ወደፊት ችግሩ በቶሎ ካልተፈታ እንደ አስፈላጊነቱ በዝርዝር ትመለስበታለች።ሆኖም ግን መፍትሄው በቶሎ ከመጣ ለታሪክ መዝገብ ይቀመጣል።

በአቴንስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከቤተክርስቲያንነቷ ጋር አብሮ የሚታየው ኢትዮጵያን በግሪክ የምትወክል ትልቅ ተቋም ነች። ትልቅ ተቋም እንድትሆን ደግሞ ከመንፈሳዊ አገልግሎቷ በተጨማሪ ለግሪካውያን ትልቅ ፋይዳ ያለው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አንጻር ብዙ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ ኢትዮጵያን የማስጠራት አቅም አላት።

በግሪክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አንጻር ቤተክህነት ሁለት ጉዳዮች ላይ አትኩሮ መስራት አለበት

1/ የመልካም ተግባቦት ( Good Communication) ያለው አገልጋይ እንጂ የመልካም ተግባቦት ችግር ያለበት አገልጋይ ወደ ውጭ አለመላክ

የተግባቦት ክህሎት (Communication Skill) አማርኛ መናገር፣ግዕዝ መቻል ወይንም እንግሊዝኛ የማቀላጠፍ ጉዳይ አይደለም።የምዕመኑን ባሕላዊ ዕሴት፣ከተሜነት ወይንም ከገጠር የመጣ፣ከሩቅ ምስራቅ የመጣች እህት ወይንም ከአዲስ አበባ የመጣች ምዕመን ሁሉ ልዩ አቀራረብ ይፈልጋሉ።ልዩ የተግባቦት ክህሎት እና የመረዳት አቅም ይፈልጋል። እንደ ክርስቶስ ዝቅ ብሎ ለትንሽ ለትልቁ መታዘዝ እና የወጣቱንም ሆነ የአረጋውያንን ችግር ወርዶ ጠይቆ መርዳት እና አንደበትን ከክፉ አነጋገር ሁሉ ማቀብ ይፈልጋል። ህዝብ ተግባቦት ሲያጣ ተስፋ ይቆርጣል፣የሚሰጠው ክብር ይቀንስበታል።

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በተለይ ወደ ውጭ የምትልካቸው አገልጋዮች በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ከሁሉም የአገሪቱ ክፍል ከመምጣቱ አንጻር ብቻ ሳይሆን ያለውን ነባራዊ አካባቢያዊ ሁኔታ የመተንተን አቅም እንዲኖራቸው ልዩ የተግባቦት እና ሌሎች ተጨማሪ ስልጠናዎች ቤተክርስቲያን ሰጥታ መላክ አለባት።ይህ በውጭ አገሮች ያሉ ችግሮች ሁሉ መገለጫ ነው ባይባልም አንዱ ቀላል የሚመስለን ነገር ግን ቋጥኝ የሚያህል ችግር የሚያመጣው የተግባቦት ክህሎት ማነስ ነው።

2/  የቅዱስ ሲኖዶስ አካል ከአገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጋር ወደ ግሪክ መምጣት እና ችግሮቹን ፈትቶ የመሄዱ አስፈላጊነት 

የግሪክ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ችግር የመልካም ተግባቦት ጉድለት ጉዳይ ብቻ አይደለም።ጳጳሳት ከአገልጋይ ካህናት ጋር በር ዘግተው ቀኖናዊ ጉዳዮችን መርምረው ውሳኔያቸውን ከቤተክርስቲያኒቱ ፍትሕ መንፈሳዊ አንጻር መርምረው ውሳኔያቸውን ለምዕመኑ ማስታወቅ አለባቸው። እዚህ ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ልዑክ ከአገረ ስብከቱ ጳጳስ ጋር ወይንም የአገረ ስብከቱ ጳጳስ በቤተክርስቲያን ቀኖና መሰረት የሚወስኑት ውሳኔ የመቅደሱ ጉዳይ ነው። ምዕመናን ከመቅደስ ውስጥ ስላለው አገልግሎት ስለ ማዕጠንቱ፣ስለ አቀዳደሱ ወዘተ ሃሳብ የመስጠት መብት የላቸውም።ይህ ስልጣነ ክሕነት ይጠይቃል። የቅዱስ ሲኖዶስ ልዑክ ጉዳዮቹን ለምዕመናን የማይነገሩ ካሕናት ብቻ የሚያውቋቸው ጉዳዮች ከቤተክርስቲያኒቱ ህግ አንጻር መርምረው ለሚወስኑት ውሳኔ ድንጋይ አንስቶ ይህን ካልወሰናችሁ፣ይህንን ለምን ወሰናችሁ ካለ ይህ መቅደስ ውስጥ ገብቶ ስለ ማዕጠንቱ እና ቅዳሴው ልናገር የማለት ያህል ነው።

ስለሆነም ለምን እንደተወሰኑ አደባባይ የማወጡ ጉዳዮች ላይ አባቶች በር ዘግተው ተወቃቅሰው የሚወስኑት ውሳኔ ስላለ የምዕመኑ ድርሻ አባቶቹን ተቀብሎ ውሳኔዎቹ የመቀበል እና ቤተክርስቲያኑን የማገልገል ድርሻ ነው። ይህ የቤተክርስቲያን ሥርዓት ነው።በመቅደሱ የውስጥ ጉዳይ ምዕመናን በማያውቁት ጉዳይ አይገቡም። ምዕመናን የማይረዱት ጉዳይ አባቶች ይተዛዘናሉ።የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አባቶች ስልጣነ ክህነት አክብሮ ውሳኔዎችን አክብሮ መሄዱ ጥያቄዎች ሲኖሩ በጨዋነት ማቅረብ እንጂ በተረበሸ እና ስሜታዊ በሆነ መልኩ አባቶች ፊት መቅረብ አይገባውም። 

ያለፉት ሁሉ ትምህርት ሆነው ያልፋሉ።ለምን ሆኑ ብሎ መቆጨቱ አሁን አይጠቅምም።ለእግዚአብሔር ቤት የቀና የሚመስለው በስሜት ብዙ ነገሮች አድርጎ ይሆናል።እግዚአብሔር ልብን ስለሚመረምር ከእግዚአብሔር ቤት ቅናት አንጻር ያደረገው መሆኑን እግዚአብሔር ስለሚመረምር፣ላለፈው ንስሃ ገብቶ ለመጪው ጊዜ ቤተክርስቲያንን የበለጠ ለመካስ መነሳት ነው ቁም ነገሩ። ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲወገር በሉት እያለ የወጋሪዎቹን ልብስ ይጠብቅ የነበረው የበፊት ስሙ ሳውል በኋላ የእግዚአብሔር ምርጥ ዕቃ የሆነው ቅዱስ ጳውሎስ ነበር። እግዚአብሔር ቅዱስ ጳውሎስ ለእግዚአብሔር እቀናለሁ ብሎ ካለማወቅ እንዳደረገው ልቡን ያውቅ ስለነበር ወደ ቀናው መንገድ መርቶ የቤተክርስቲያን ብርሓን ቅዱስ ጳውሎስ ተብሏል። ስለሆነም ያለፈው ሁሉ በስህተት የነበሩ ንግግሮች፣በጉልበት የተፈጸሙ ድርጊቶች ሁሉ ለቤተክርስቲያን ቅናት ነገር ግን በማይገባ መንገድ የተፈጸመ ቢሆንም ለእዛ ንስሃ ገብቶ ለመጪው መልካም አገልግሎት መትጋት ነው አሁን የሚያስፈልገውል።

ለማጠቃለል ግሪክ አገሩም ህዝቡም ሰው ወዳጅ ነው።በእዚህ ደግ እና ሩህሩህ ህዝብ መሃል የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ትኩረት ከመንግስት ይፈልጋሉ። ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ችግሮች ላይ የመንግስት ትኩረት ያለው ባብዛኛው በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉት ላይ ነው።በእርግጥ በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ወገኖቻችን ትኩረት ያስፈልጋል።ግሪክ ያሉ ኢትዮጵያውያንም በቀላል ዲፕሎማሲያዊ ንግግር ከግሪክ ጋር በማድረግ ብዙ ከባድ ጉዳዮች ሊፈቱ ይችላሉ።በመሆኑም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዝርዝር ጉዳዮች አጥንቶ በቶሎ መድረስ አለበት። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ችግር የመፍታቱን ጉዳይ ቤተክህነት በኩል በቶሎ መፈጸም አለበት።እዚህ ላይ ከእዚ በፊት የተወሰኑ ውሳኔዎች አሉ ከተባለም እነርሱ ተግባራዊ እንዳይሆን የገጠሙ ችግሮች ምክንያትነት መርምሮ ማየት አስፈላጊ ነው።በግሪክ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የቤተመንግስት እና የቤተክህነት አፋጣኝ ድጋፍ ይፈልጋሉ።
=================///==========

ከእዚህ በታች ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ በ1947 ዓም አቴንስ፣ግሪክ ለጉብኝት ሲገቡ የአቴንስ ነዋሪ ያደረገላቸውን የሞቀ አቀባበል የሚያሳይ አጭር ቪድዮ ይመልከቱ።




No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...