ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, August 27, 2020

''እንዴት አንድ ሰው ፈጣሪዬ ብሎ በሚጠራው ፈጣሪው የተፈጠረ ብሎ የሚያምነውን ሰው በዕምነት ስላልመሰለው ብቻ በፈጣሪው ሥም ያርዳል?'' - አቶ ዓለማየሁ ብርሃኑ ከባሌ እና ከአርሲ ጉብኝታቸው ባለፈው ሳምንት እንደተመለሱ ለጉዳያችን የተሰማቸውን ፅፈዋል።ሙሉውን ያንብቡ።

አቶ ዓለማየሁ ብርሃኑ

እኔ ባደግሁበት አካባቢ በልጅነት አዕምሮአችን እየሰማን ያደግነው አባቶቻችን ነገ ለሚያደርጉት ነገር ሲቀጣጠሩ በጠዋት ለመገናኘት የቀጠሮ ሠዓት የሚያደርጉት "ጠዋት አላህ ወአክበር ሲል" እንነሳ ይባባሉ ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር እንደዛሬው ሰዓት ባልነበረበት በዚያ ዘመን ጠዋት ክርስቲያን አባቶቻችን ወደ ቤተ ክርስቲናቸው ለመሄድም የመስጊዱን አዛን ቀስቅሶ እንደሚያበረታታ 'በጎ ቀስቃሽ' ይጠቀሙበት ነበር።ምክንያቱም አንዱ የአንዱን እምነት አክብሮ የሚኖርበት የፍቅር ዘመን ስለነበር፡፡
ታዲያ! በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች ከእስልምና እምነት ተከታይ አብሮ አደግ ጓደኞቻችን ትርጓሜውን ስንጠይቅ 'ኣላህ ታላቅ ነው' ማለት እንደሆነ ይነግሩን ነበር፡፡ ይህ ቃል እንግዲህ ለጨዋዎቹ የእስልምና አማኞች ክብር ያለው ቃል እንደሆነ ከትርጓሜው መረዳት ይቻላል፤ ለክርስቲያኑም ከላይ እንደጠቀስኩት ይህ ቃል በጎ ቃል ሆኖ ኖሯል፡፡ዛሬም ኢትዮጵያውያን ተከባብረው በሚኖሩበት ቦታ ሁሉ ከመስጊድም ሆነ ከአብያተ ክርስቲያናት የሚወጡ የማንቂያ ድምፆች እንደተከበሩ አሉ ይህ ቃል ግን ዛሬ በምሥራቅ ኦሮሚያ ላሉ ክርስቲያኖች የሰቀቀን ቃል ሆኗል። ክርስቲያኖችን በአደባባይ የሚገድሉ በእስልምና ስም የሚንቀሳቀሱ እና የንፁሃንን ደም የሚያፈሱ ይህንኑ ''አላህ ወአክበር'' የሚሉትን ቃላት እየተጠቀሙ ነው።
በሰኔ 23 እና 24/2012 ዓም በአምስቱ የኦሮሚያ ዞኖች በአካባቢው በሚገኙ የዕምነቱ ተከታይ ነን በሚሉ የመንግስት ባለሥልጣናትና ፖሊሶች ድጋፍ በተደረገው ክርስቲያኖችን የማጥፋት ዘመቻ ላይ ይህ ቃል እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በሰፊው በሥራ ላይ ውሏል። ግን ለበጎ ተግባር ሳይሆን አብሮ የኖረን ህዝብ ንብረት ለማውደምና ለመስረቅ በተለይም ደግሞ ዕምነት የሌለው ሰው እንኳን ያደርገዋል ተብሎ የማይገመት አሰቃቂ ግድያን በወንድም ላይ ለመፈፀም ነው፡፡ እኔም በባሌና አርሲ የደረሰውን ጉዳት ለማየት ባለፈው ሳምንት ከሄደው ቡድን ጋር ተጉዤ ነበርና ከተጎጂዎቹ በአካል ተገኝተን በሰማነው መሠረት ሰው በህይወቱ እያለ እጅ ሲቆርጡ ዓይን ሲያወጡ፣ አጋርፋ ላይ የአእምሮ ዝግመት ያለበትን ወጣት ጭንቅላቱን ቀጥቅጠው በማጅራቱ ሲያርዱትና መሰል አስነዋሪ ተግባራትን ሲፈፅሙ ሁሉ "አላህ ወአክበር" እያሉ እንደነበር ከጉዳቱ የተረፉት ሃዘን በተሞላ አንደበት ተርከውልናል ፡፡
ይህ ነገር አዲስ አይደለም ሠዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከክርስቲያኑ ሃጫሉ ሞት ጋር ያያይዙታል። ነገር ግን ይኼ ታቅዶ የተሰራ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ከአስር ዓመት በፊትም በጅማ ዙርያ በሻሻ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንም በተመሳሳይ እልቂት ሲፈፀም ይሄው ቃል እየተጠራ ነበር።በቅርቡ በጥቅምት/2012 ዓም ተመሳሳይ ድርጊት በተፈፀመበት እና ከ80 በላይ ንፁሃን ሕይወት በጠፋበት እልቂት ወቅትም ይሄው ቃላት የተደጋገመ መፈክር ሆኗል፡፡ የድሮ አልቃሽ አባቷ ሞቶባት በዓመቱ ባሏ ለሞተባት ሴት ስታላቅስ "ያምናን ቀን አማሁት ላፌ ለከት የለው፤ መጣ የዘንድሮው እጅ እግር የሌለው፡፡" አለች አሉ፡፡ እኛም ታዲያ 'ከካቻምናም አምና ከአምናውም ዘንድሮ፤ እያስጠላኝ መጣ የዚች ዓለም ኑሮ' እንድንል በክርስቲያንነታችን እየተገፋን ነው፡፡ እንዴት አንድ ሰው ፈጣሪዬ ብሎ በሚጠራው ፈጣሪው የተፈጠረ ብሎ የሚያምነውን ሰው በዕምነት ስላልመሰለው ብቻ በፈጣሪው ሥም ያርዳል? እንዲህ ዓይነት የዕምነት አስተምህሮ አለ ብሎ መቀበል በዕውነቱ ይከብዳል። በተለይ ጠላትህን ውደድ በሚል አስተምህሮ ለተገራው ከአዕምሮ በላይ ነው፤ ግን ደግሞ እየሆነ ያለው ዕውነታ ይህ ነው፡፡
እዚህ ላይ ታዲያ የኔ ጥያቄ በተለይ ለዕውነተኞቹ የእስልምና አማኞች በርዕሱ ላይ እንደጠቀስኩት 'አላሁ አክበር' ትርጉሙ ተለወጠ እንዴ? የሚል ነው፡፡ እኔ ይወክሏችኋል ብዬ ባላምንም እናንተም በምታመልኩበት አምላካችሁ ሥም ነውና እየተገደልን ያለነው ለምን ዝም አላችሁ? አምናችሁበት በውስጣችሁ ደስ እያላችሁ? ወይንስ ከናንተው ወገን ያለሃፍረት 'እዚህም ቤት እሳት አለ' በሚል ዓይነት ማስፈራሪያ የምናስጮኸው አናጣም ብለው ሊያስፈራሩን የሚሹት ሠዎች እናንተም ላይ የሚያሳድሩት ስውር ደባ ይኖራቸው ይሆን? በእርግጥ ኃይማኖትን የተረዱ ጥቂት ዕውነተኛ ኡስታዞችና ህሊናቸውን ለዕውነት አስገዝተው ስለዕውነት ድርጊቱን በማውገዝ በፊት ለፊት በግላቸው ያወገዙትን ዋጋ ማሳጣት አልፈልግም፡፡ በሌላም በኩል በሱማሌ ክልል ደርሦ በነበረው ጥቃት በይፋ ድርጊቱን በማውገዝና ይቅርታ በመጠየቅ በጋራ ለማቋቋም ጥረት ያደረጉትን የክልሉን ፕሬዝዳንት ሙስጠፌንና የሶማሌ ሙስሊም የሃገር ሽማግሌዎች ዓይነት ሠዎች ባሉበት ሃገር ከዚህ ትምህርት መውሰድ ሲገባ ዛሬም 'አምላክ ታላቅ ነው' እያሉ አምላክ የፈጠረውን በማረድ ለማባረር መሞከር መጨረሻው ላያምር ይችላልና ቆም ብለን ብናስብበት ጥሩ ነው፡

እንደኔ ግን እነኚህ ሠዎች ለክርስትና ብቻ ሳይሆን ሳያምኑበት የሚያምኑበት አስመስለው ዓላማቸውን ማራመጃ ላደረጉት ለእስልምናም ውሎ አድሮ አደጋነታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም በጋራ ሊያወግዘው የሚገባ ሃይማኖት ተኮር እኩይ ተግባር ነው፡፡ ይህ ሲባል የሚያቅራቸው የመንግስት ሹማምንትም ለዕውነታው ዕውቅና ሰጥተውና ይፋ ይቅርታ ጠይቀው ለመፍትሔው አብሮ መስራት ይሻላል እንጂ የሐይማኖት አይደለምና ዕውነትን አትናገሩ ብሎ ሚዲያዎችን ለማገት መጣሩ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ቤተክርስቲያን በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት 'ለምጣዱ ሲባል…' በሚለው ሃገራዊ ብሂል መሠረት ብዙ መከራዎችን ዋጥ አድርጋ መታገሷን ታሪክ ይመዘግበዋል፡፡ አሁንም ይልቅ የደህንነት ሥጋት ያለባቸውን የዴራ ወረዳ ክርስቲኖች ቤት ንብረታቸው መውደሙ እየታወቀ ከተጠለሉበት ቤተ ክርስቲን ያለምንም ዝግጅት እንዲወጡ የሚያስገድዱ የወረዳ ሹማምንት ዕውነት ለመንግስት ጥሩ ሥም እየሰሩ ነው? ወይስ ያላለቀ ተልዕኮ ያላቸው ሠዎች ዛሬም ይኖሩ ይሆን? አሁንም የኦሮምያ ክልል ይህንን ፈትሾ ለዜጎች የደህንነት ዋስትና የመስጠት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡
አምላክ እንደአባቶቻችን በፍቅር የምንኖርበትን ጊዜ ያምጣልን፡፡
ዓለማየሁ ብርሃኑ ነኝ

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...