Monday, February 1, 2021

ኢትዮጵያን የመክበብ እና የማዋከብ ሙከራን ለማክሸፍ



ኢትዮጵያ ያለችበትን ቁልፍ አቀማመጥ ብቻ ሳይሆን ከሱዳን እስከ ጂቡቲ ከየመን እስከ ሳውዲ ያለው በረሃማ መሬት ጋር ሲነፃፀር  ምድረ ገነት ነው።እነኝህ በደረቃማ መሬት ላይ ተፈጥሮ ያሰፈረቻቸው አንዳንድ መንግሥታት የአሁኑም ሆነ መጪው  ትውልዳቸውን የሚያጠጡትን ውሃ ለማግኘት ዙርያቸውን ሲያማትሩ ዓይናቸውን የጣሉት ኢትዮጵያ ላይ ነው።ከእነኝህ አማታሪዎች ውስጥ የመካከለኛው ምስራቅ ጋዜጦች እንደ ''አል-አረቢያ'' ያሉት ጋዜጦች የኢትዮጵያን ዓባይ ወንዝ ''የአረቡ ዓለም ወንዝ'' እያሉ ሲፅፉ ትንሽም 'ስቅ!' አላላቸውም።ይሄው ጋዜጣ ባሳለፍነው ክረምት ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ መገደቧ የአረቡን ዓለም ለመቆጣጠር ነው እና የአረብ ሀገሮች በሙሉ ሊነሱ ይገባል  ሲሉ የአረብ ሊግ ቁንጮ መናገራቸውንም አስነብቦናል።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ፍላጎት ግልጥ ነው።ኢትዮጵያ እንድትነሳ አለመፈለግ ብቻ ሳይሆን ከፋፍለው ሊቆጣጠሯት እያለሙ ይቃዣሉ።ይህንን ህልማቸውን ደግሞ ኢትዮጵያ የውስጥ ሁከት የገባች በመሰላቸው ጊዜ ሁሉ እና የዓለምም ሆነ የመካከለኛው ምስራቅ ትኩረት በተደናበረበት ጊዜ  ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ያልሞከሩበት ጊዜ የለም።የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመግባት ቢያንስ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ ብቻ በርካታ ሴራዎችን አሴረዋል። የኢትዮጵያ እና የኤርትራም ሆነ የህወሓት 17 ዓመታት ጦርነት ብንመለከት ከገንዘብ እስከ ቁሳቁስ  ከፍተኛ ድጋፍ ያገኝ የነበረው ከመካከለኛው ምስራቅ እና ሱዳን መንግሥታት ነበር።ለእዚህም ነው ''የኤርትራ ጉዳይ'' የተሰኘው መፅሐፍ ፀሐፊ ክቡር አምባሳደር ዘውዴ ረታ ''የኤርትራን ጉዳይ  እግሩ ኢትዮጵያ ይሁን እንጂ  ራሱ ያለው ውጪ ነው'' ያሉት።ዛሬ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መቀራረብ ያስደነገጣቸው የኢትዮጵያ የቅርብም ሆኑ የሩቅ ጠላቶች ዋና ስጋት ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር የመውጣት ሂደት እና ይህንኑ ባሕርም ሆነ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት የመቆጣጠር ህልማቸው ከንቱ እንደሚሆን ከወዲሁ ስላወቁ አርበትብቷቸዋል።

በሌላ በኩል የአፍሪካ የተፈጥሮ ሐብት መተዳደሪያቸው የሆኑ አደጉ የሚባሉ ሐገሮች የኢትዮጵያ መነሳት እንደ እነርሱ አባባል ''መንሰራራት'' እንደ አንድ ስጋት ይመለከቱታል።ይህ ደግሞ ከሁለት ምክንያቶች ይመነጫል።አንዱ፣ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ምሳሌ ሆና ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች እጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን ለማንኮታኮት እንዳይነሱ ሲሆን።ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ካላቸው የተፈጥሮ ሀብት፣ማዕድናት እና ጅኦ-ፖለቲካዊ ስልት አንፃር የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ወታደራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ሁሉ በእጅ አዙር ለመዘወር ከመፈለጋቸው የተነሳ ነው።ለእዚህም ነው ኢትዮጵያን ለሃያ ሰባት ዓመታት በጎሳ ከፋፍሎ እርስ በእርስ ሲያናክስ አንዳች ያልተናገሩ መንግሥታትም ሆኑ የውጭ መገናኛ ብዙሃን፣የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሚያስደንቅ ፍጥነት ካስወገደው በኃላ ታላቅ ድንጋጤ እንደፈጠረባቸው መደበቅ አልቻሉም።

ይሄውም የስልት መወናበድ እና መደናበር ስለፈጠረባቸው የሚይዙትን እና የሚጨብጡትን አሳጥቷቸው ሲወዛገቡ ታዝበናል።በእዚህም ምክንያት የግፈኛው የቀድሞው ህወሓት ደጋፊዎችም ሆኑ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አሁን ያላቸው ብቸኛ እና ቀሪ አቅም የሐሰት ወሬ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ማሰራጨት ሆኗል።በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሐሰት ዜና የማሰራጨቱን ሥራ እየሰሩ ያሉት ደግሞ በዓለም ላይ ስም አላቸው የሚባሉ ዓለም አቀፍ የዜና ማሰራጫዎች ጭምር እጅግ በሚያሳፍር ሁኔታ ከእውነት የራቁ ዜናዎች ሲያሰራጩ ሰንብተዋል።በእነኝህ የዜና ስርጭቶች ዙርያ የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የዜናዎቹን ሐሰትነት በሚያጋልጥ መንገድ የጥናት ፅሁፎቻቸውን ማቅረብ አለባቸው። ይህ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሐሰት ዜና ኢትዮጵያን የመክበብ ቁጥር አንድ ሙከራ መሆኑን ማወቅ ይገባል።

ሁለተኛው ኢትዮጵያን የመክበብ ግብ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ክልል የገባው የሱዳን ሰራዊት ነው።ሱዳን በቅርቡ በተጣደፈ መልኩ የትራምፕ አስተዳደር በሀገሪቱ ላይ ተጥሎ የነበረውን የዕቀባ መጣል ማንሳቷ ይታወሳል።ይህንን ተከትሎ ከአሜሪካ የገንዘብ ድርጅት ብድር ማግኘቷ እና ከግብፅ ደግሞ የአይዞሽ ባይ ምልክት መታየቱ ነው።ይህ በሱዳን በኩል የታየው ኢትዮጵያን የመክበብ ተግባር መልኩን ቀይሮ ነገ ከኢትዮጵያ ምሥራቅም ሆነ ምዕራብ በሌሎች ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር የሚናበቡ ኃይሎች ተመሳሳይ ከበባ አያደርጉም ብሎ አለማሰብ አይቻልም።ይህ በእንዲህ እያለ የከበባዎቹ ዋና ኃይል አድርገው የሚወስዱት የኢትዮጵያን ውስጣዊ ሰላም ማተራመስ ነው።ኢትዮጵያን ለማተራመስ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ስደተኞችን ሳይቀር ለመጠቀም የኢትዮጵያ ጠላቶች ማቀዳቸው አይቀርም።ኢትዮጵያ ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ወደ ሃያ የሚሆኑ ሀገራት ስደተኞች መጠጊያ ናት።ስደተኞቹ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍል ስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ የህክምና ችግር ፣ ከነበሩበት ሀገር በተለያዩ ጦርነቶች አልፈው ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸው ለአዕምሮ ህመም የተጋለጡ እንዲሁም ጥበቃ የሚያስፈልጋቸውም በከተማ ስደተኝነት ተመዝግበው አዲስ አበባ ይኖራሉ።

ለማጠቃለል ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን የከበባ ሙከራ ለመስበር መንቀሳቀስ አለባቸው።የመጀመርያው የከበባ ሙከራ በዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን የተፈፀመ ነው።ይህንን የሐሰት ዜና በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሚዘሩትን ምሑራን ባገኙት ቀዳዳ ሁሉ ተጠቅመው ምላሽ መስጠት ብቻ ሳይሆን የሕግ ማስከበር ሂደቱ ባይካሄድ ኖሮ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የምስራቅ አፍሪካን በከፍተኛ ደረጃ ሊያበጣብጥ የሚችል ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል የሚያስረዱ በርካታ ፅሁፎች፣ገለጣዎች እና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎች በሰፊው መስራት ያስፈልጋል።በእዚህ በኩል በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ምሑራን መፃፍ በሚገባቸው ያህል ፅፈዋል ማለት አይቻልም።ኢትዮጵያ ያስተማረቻቸው ልጆቿ ለእዚህ ጊዜ ካልሆኗት ለመቼ ሊሆኗት ነው? ኢትዮጵያ በሐሰት ወሬ ይህንን ያህል ከበባ ሲፈፀምባት እንዳላዩ ማየት የት የተማርነው ሙያ ይሆን? በጦር ኃይል በኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ወረራ የፈፀመው የሱዳን ሰራዊት የኢትዮጵያ ጦር ባልተጠበቀ ሰዓት እርምጃ እንደሚወስድበት ሳይታለም የተፈታ ነው። የሐሰት ወረራ የተከፈተባት ኢትዮጵያ ላይ የአፀፋ ምላሽ መስጠት ግን የእንግሊዝኛ ፊደል የቆጠረው ከሀገር ቤት እስከ ባሕር ማዶ የሚኖረው የኢትዮጵያ ምሑር ነው።ስለሆነም ምሑሩ ከትዊተር እስከ ዓለምቀፍ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ከበባ እና የማዋከብ ተግባር  ሰብሮ ለመውጣት ለኢትዮጵያ የሚቆምበት ጊዜ አሁን ነው።ኢትዮጵያ ግን ዛሬም ትጣራለች ምሑሩ የት ነው?
==========////==============
============
ማስታወቂያ 
============
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 

አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 

Friday, January 29, 2021

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን መድረክ "ድምፃችንን ለቤተ ክርስቲያናችን" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ የውይይት መድረክ እሁድ ጥር 23/ 2013ዓም (Sunday January 31/2021 ዓም) በዙም አዘጋጅቷል።

ጉዳያችን/Gudayachn

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን መድረክ "ድምፃችንን ለቤተ ክርስቲያናችን"   በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ የውይይት መድረክ እሁድ ጥር 23/ 2013ዓም   (Sunday January 31/2021 ዓም) በዙም አዘጋጅቷል። በዝግጅቱ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ምዕመናን ስለ ቀጣዩ ምርጫ ምን ያስባሉ? ሚናቸውስ ምንድን ነው ? ለእነዚህና ተመሳሳይ ጉዳዮች የሚነሱበት መርሐግብር እንደሆነ ከመርሃግብሩ ማስታወቂያ ለማወቅ ተችሏል። 

በዝግጅቱ ላይ ምሑራን ገለጣዎች የሚያቀርቡ ሲሆን በሀገር ቤት እና በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናት፣ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና ምዕመናን እንደሚገኙበት ጉዳያችን ተረድታለች።
የስብሰባውን የዙም መግቢያ ኮዱን ከእዚህ በታች ካለው የመርሐግብሩ ፖስተር እና በድምፅ ከተለቀቀው ቪድዮ ላይ ማግኘት ይችላሉ።

============
ማስታወቂያ 
============
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 


Wednesday, January 27, 2021

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ዲና (Dina) በመጪው ቅዳሜ በኖርዌይ ቴሌቭዥን ለመሎዲ ግራንድ ፕሪክስ ውድድር ትቀርባለች።በስልክዎ ድምፅ በመስጠት እንድታሸንፍ ያድርጉ።

Etiopisk-norske, Dina Matheussen, er blant fire artister for Melodi Grand Prix.

በኖርዌይ ነዋሪ የሆነችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ዲና (Dina) ከአዲሱ ነጠላ ዜማዋ ላይ የተወሰደ ፎቶ 


ጉዳያችን/Gudayachn

ዲና ማቴዎስ ትባላለች።ነዋሪነቷ በኖርዌይ የሆነና ትውልደ ኢትዮጵያ የሆነች የ17 ዓመት ወጣት ነች።ገና 12 ዓመት እያለች ነው የዳንስ እና የድምፃዊነት ስራዋን የጀመረችው።ዲና የሙዚቃ ሰው ብቻ አይደለችም።በካራቴ ስልጠና ባለ ጥቁር ቀበቶ ተሸላሚም ድንቅ ወጣት ነች።

በ2014 ዓም እኤአ በኖርዌይ ቲቪ ቻናል 2 ላይ በሚቀርብ የኖርዌይ ታለንት ውድድር ላይ ከፍተኛ አድናቆትን አትርፋ ነበር።በ2017 ዓም በኖርዌይ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን (ኤንአርኮ) የዓመቱ የዳንስ ውድድር ላይም ተሳትፋ ነበር።ባለፈው ዓመት በኖርዌይ አይዶል 2020 ላይ የበዮንሴን "Run the World (Girls)" የተሰኘውን ሙዚቃ በማቅረብ የኖርዌይ አድናቂዎቿን አስደምማለች።በ2019 ዓም በኖርዌይ ብሮድካስት ቴሌቭዥን (ኤንአርኮ) ቻናል 3 ላይ ''አንድ ነን'' ''we are one'' በሚል ያቀረበችው ሙዚቃ ላይ የት መጣ መሰረቷ ኢትዮጵያ መሆኑን በመድረኩ ላይ አሳይታበት ተመልካቾችን ሁሉ አስደንቃለች።

የዲና ተግባራት እነኝህ ብቻ አይደሉም።በእየዓመቱ ወደ ኢትዮጵያ እየሄደች የኦቲዝም እና ልዩ ልዩ ችግር ያለባቸውን ልጆች ለእዚሁ ሥራ ብላ ባጠራቀመችው ገንዘብ ትረዳለች።በያዝነው ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ለተመሳሳይ መልካም ተግባር መሄድ ያልቻለቸው በኮቪድ ወረርሽኝ ሳብያ ነው።አሁንም ግን ኢትዮጵያውያንን ለመርዳት ገንዘብ እያጠራቀመች እንደሆነ እና መርዳቷን እንደምትቀጥል በያዝነው ሳምንትም ባደረገችው ቃለ መጠይቅ ገልጣለች።

ከዲና ጋር ያለፉት ሌሎች አራት አርቲስቶች ካርሰን (Karsten)፣ኤሚ (Emmy) እና ኡለ ሀርዝ (Ole Hartz)
FOTO: JULIA MARIE NAGLESTAD / NRK

ዲና የአሁኑ ቅዳሜ ጥር 22/2013 ዓም (ጃንዋሪ 30/2021ዓም) የኖርዌይ ብሮድካስት ቴሌቭዥን የኖርዌይ ሜሎዲ ግራንድ ፕሪክስ (Norsk Melodi Grand Prix) ውድድር  ከተመረጡት አራቱ ውስጥ ገብታለች።በውድድሩ ሰዓት ዲና እንድታልፍ ኢትዮጵያውያን በስልክ በሚሰጠው ድምፅ በመስጠት ተሳታፊ እንዲሆኑ ተጠይቀዋል።የኖርዌይ ቴሌቭዥን (ኤን አር ኮ -NRK) ''ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ዲናዬ በዘፈኗ ውስጥ የአማርኛ ቃላት እንዲገቡ ያደረገችው መነሻዋ ከኢትዮጵያ መሆኑን ለማመልከት ነው'' በማለት ገልጦታል።

ዲና የቅዳሜውን ውድድር አልፋ ለፍፃሜው ስትደርስ በአውሮፓ ደረጃ ለሚደረገው ዋናው ውድድር ደረሰች ማለት ነው።በእዚህም አንዲት ትውልደ ኢትዮጵያዊት ለአውሮፓ ምርጥ ውስጥ ስትገባ የመጀመርያዋ ያደርጋታል ማለት ነው።በመሆኑም በቅዳሜው ምሽት ውድድር ላይ ኢትዮጵያውያውያን፣ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ኖርወጅያውያን ለዲና በስልካችሁ ድምፅ በመስጠት ኃላፊነታችሁን መወጣት አትዘንጉ።

ከእዚህ በታች ዲና ከሦስት ቀናት በፊት የለቀቀችውን ነጠላ ዜማ ከዩቱቧ ላይ ያለውን ከስር ይመለከቱ።


============
ማስታወቂያ 
============
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 

Tuesday, January 26, 2021

አስደናቂዋ ክብርት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ግብፅ በኢትዮጵያ አንፃር በአፍሪካ ለመቆለፍ የሞከረችውን ዲፕሎማሲ አንድ በአንድ እየተረተሩት ነው።

ክብርት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

ጉዳያችን/Gudayachn 

>> ከጽሁፉ ስር አንድ ወጣት ታንዛንያዊ በክብርት ፕሬዝዳንት ጉብኝት ተደስቶ ጉብኝቱን በቪድዮ ያቀናበረውን ይመልከቱ።

የአንደኛ  እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ሊሴ ገብረማርያም የፈረንሳይኛ ትምህርት ቤት ተምረዋል።በመቀጠለም በፈረንሳይ ሀገር የሚገኘው ሞንትፒለር ዩንቨርስቲ ተምረዋል።ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ከአምባሳደር ዮዲት እምሩ ቀጥለው ሁለተኛ ሴት ኢትዮጵያዊ አምባሳደር ናቸው።በአምባሳደርነት በሴኔጋል መቀመጫቸውን አድርገው የማሊ፣ከፕቨርድ፣ጊኒ ቢሳው፣ጋምብያ እና ጊኒ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል።በጅቡቲ አምባሳደርነታቸው ደግሞ የኢጋድ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል።ከእዚህ በተጨማሪ በፈረንሳይ አምባሳደርነታቸው ደግሞ የመንግሥታቱ ድርጅት የዩኔስኮ ዋና ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል።በናይሮቢ ደግሞ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባንኪሙን ዋና መልክተኛ እና የቢሮ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከፕሬዝዳንትነት ስራዎቻቸው በተጨማሪ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ መታገዝ ባለበት ሁሉ እየተገኙ ክፍተቱን በመሙላት እየሰሩ ያሉት ተግባር ትልቅ ፍሬ እያፈራ ነው።በዲፕሎማሲው የረጅም ጊዜ ልምድ አላቸው የሚባሉት የግብፁ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳማህ ሽኩሪ ከሀገር ሀገር እየዞሩ በኢትዮጵያ ላይ የዲፕሎማሲ ዘመቻ እንዲከፈት ያልረገጡት ምድር የለም።ከእነኝህ ሀገሮች ውስጥ የአፍሪካ ሀገሮች ተጠቃሽ ናቸው።ከእነኝህ ሀገሮች ውስጥ ታንዛንያ እና ኮንጎ ይጠቀሳሉ።በእዚህ በኩል ክብርት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ከኬንያ እስከ ዩጋንዳ፣ከደቡብ አፍሪካ እስከ ፈረንሳይ፣ሰሞኑን ደግሞ ከታንዛንያ እስከ ኮንጎ ድረስ ግብፅ ለመቆለፍ የሞከረችውን የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ በአፍሪካ አንድ በአንድ እየፈቱት ነው።በእርግጥ በአፍሪካ አንፃር ቀድሞም ኢትዮጵያ በአፍሪካውያን ዘንድ ከፍ ያለ ከበሬታ አላት። ይህንን ከበሬታ ግን በአግባቡ ተረድቶ የሚያፋፍመው ጥበበኛ ዲፕሎማት ይፈልግ ነበር።ክብርት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ  ዘውዴ ሰሞኑን በታንዛንያ እና በኮንጎ ያደረጉት ጉብኝት ትልቅ ትኩረት በአፍሪካውያን ወጣቶች ዘንድ ሳይቀር ትኩረት እና ከበሬታ አግኝቷል።

ግብፅ የታንዛንያ እና ኮንጎን ድጋፍ ለማግኘት ስትጥር ሰንብታለች።በታንዛንያ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ሲሆን ኮንጎን ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ ቀጣይ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በመሆኗ ማባበሉ በዝቶ ነበር።የፈረንሳይኛ ተናጋሪ ክብርት ፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ ዛሬ ኮንጎዎችን በፈረንሳይኛ እያናገሩ ከደረሱበት አንዱ ስምምነት ውስጥ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኮንጎ እንዲከፈት የሚለው ይገኝበታል።''ነቢይ በሀገሩ'' ሆኖ ነው እንጂ ክብርት ፕሬዝዳንቷ የሰሩት ዲፕሎማሲያዊ ጀብዱ ትልቅ ከበሬታ የሚያስገኝላቸው ነው።እናመሰግናለን! ክብርት ፕሬዝዳንት ልንላቸው ይገባል።

ከእዚህ በታች የምትመለከቱት ቪድዮ ክብርት ፕሬዝዳንት ሰሞኑን በታንዛያ ያደረጉት ጉብኝት የሚያሳይ ቪድዮ ነው።ቪድዮውን ያዘጋጀው ወጣት ታንዛንያዊ ነው።ምን ይህል በአፍሪካውያን ዘንድ በተስፋ እንደምንጠበቅ አስተማሪ ነው።


============
ማስታወቂያ 
============
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 

Monday, January 25, 2021

የፀጥታ ስጋት የነበረባቸው በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር አዲስ አበባ ተመለሱ።አምባሳደሩ ከካርቱም ወደ ኢትዮጵያ በመኪና ለመግባት ጠይቀው ነበር።


በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ
ጉዳያችን ዜና / Gudayachn News
  • የእስራኤል ደህንነት ሚኒስትር ኤሊ ኮህን (Eli Cohen) ዛሬ ሰኞ ካርቱም ነበሩ። 
በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በካርቱም የፀጥታ ስጋት እንደነበረባቸው እና ወደ ኢትዮጵያ በድንበር በኩል ለመግባት የሱዳንን መንግስት ጠይቀው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።ሆኖም የሱዳን መንግስት በድንበር ውጥረቱ ምክንያት በመኪና ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ለደህንነታቸው ጥሩ አለመሆኑን እንደገለጠላቸው የቱርኩን አናዶል ዜና ወኪልን ጠቅሶ ሚድል ኢስት ሞኒተር ዛሬ ማምሻውን ገልጧል።አምባሳደሩ በአሁኑ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ በሰላም መብረራቸው እና መግባታቸው የሄው ምንጭ የፀጥታ ምንጮቹን መሰረት አድርጎ ገልጧል።

ዜናውን በተመለከተ የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መስርያ ቤት ያለው ነገር የለም።የአምባሳደሩ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እና ካርቱም ለአምባሳደሩ የፀጥታ ስጋት መሆኗ በራሱ ጥያቄ ቢሆንም በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው ግጭት በቶሎ እንዲፋጠን የሚፈልጉ የውጪ ኃይሎችም ሆኑ ከትግራይ ሸሽተው ካርቱም የሚገኙ የቀድሞው ህወሓት ቡድን ደጋፊዎች በአምባሳደሩ ላይ አንዳች ዓይነት ጥቃት ከመፈፀም እንደማይመለሱ መገመት ቀላል ነው።

ኢትዮጵያ የሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር መውረር ምክንያት የሦስተኛ ሀገር እጅ እና በሱዳን በውስጥ ኃይሎች ፉክክር ጭምር የሚከናወን በመሆኑ ጉዳዩ በዲፕሎማሲ እንዲፈታ ጥረት አድርጋለች።ሆኖም ግን ይህ የኢትዮጵያ ትዕግስት አንድ ምሽት ላይ እንደሚያበቃ እና ድንገተኛ ማጥቃት ኢትዮጵያ ልትፈፅም እንደምትችል የብዙዎች ግምት ከመሆን አልፎ በሱዳናውያንም መሃል ከባድ  ፍርሃት ፈጥሯል።

ይህ በእንዲህ እያለ የእስራኤል ደህንነት ሚኒስትር በሱዳን ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ሰኞ ካርቱም መግባታቸው ተሰምቷል።ሚኒስትሩ ከሱዳን መከላከያ ሚኒስትር እና የደህንነት ሹሞች ጋር መነጋገራቸው ለማወቅ የተቻለ ሲሆን።የተነጋገሩበት ጉዳይ ግን ግልጥ አልተደረገም።ሆኖም ሀገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ውጥረት በተመለከተ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ቀላል ነው።ሚኒስትሩ ዛሬ የአንድ ቀን ጉብኝት ካደርጉ በኃላ በተመሳሳይ ቀን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ለማወቅ ተችሏል።

===================
============
ማስታወቂያ 
============
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 

Sunday, January 24, 2021

ሰበር ዜና - በሱዳን ትናንት እና ዛሬ ከፍተኛ ተቃውሞ ሰልፍ ነበር።ሀገሪቱ አዲስ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ያሰጋታል

በካርቱም የእዚህ ሳምንት አመፅ መንገዶች በወጣቶቹ እንዲህ ተዘግቶ ነበር።
Photo = AFP

የጉዳያችን ልዩ ጥንቅር   
======================
በሱዳን ትናንት ቅዳሜ ጥር 15/2013 ዓም ከፍተኛ ተቃውሞ ሰልፍ ነበር።ሰልፈኞቹ በኦምዱርማን አል-አርባይን ጎዳና እና በርካታ ሰፈሮችን በመዘዋወር መንገዶችን ዘግተው ጎማዎችን አቃጥለዋል ፡፡በማዕከላዊ እና ደቡብ ካርቱም ሰሜን አቅራቢያ ባሉ አከባቢዎች ተመሳሳይ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል ፡፡ሰልፈኞቹ በሽግግር መንግስቱ ኢኮኖሚያዊ ዕቅዶች ላይ መፈክሮችን በማሰማት በዳቦ እና በነዳጅ እጥረት የተነሳ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።መንግስት የዳቦ ዱቄት ላይ ድጎማ እያደረገ ቢሆንም ቀውሱ ከመባባሱ በላይ በደርዘን የሚቆጠሩ መጋገርያዎች መክሰራቸው እና ከገበያ ውጪ በመሆናቸው ንግዳቸውን ለመዝጋት መወሰናቸው ነው የተሰማው።

በእዚህ መሰረት የዳቦ መጋገሪያዎች ባለቤቶች  በድጎማ የሚገኘውን ዱቄት ተጠቅመው የሚጋግሩት ዳቦ  ከ 2 ፓውንድ በአንድ ዳቦ ወደ 5 ፓውንድ ለማሳደግ ጥያቄ አቅርበው ነበር ፡፡አመፁ በዛሬው ዕለትም የቀጠለ ሲሆን ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ መርጨቱ ለማወቅ ተችሏል።በእዚህ ተቃውሞ የካርቱም ዋና የደም ስር የተሰኘውን 60ኛው ጎዳና ለትራፊክ ዝግ እንዲሆን ተገዶ ነበር።መንግስት በበኩሉ የሽያጭ ዋጋ በኪሎግራም ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የሚወስን መስፈርት ለመቀየር መወሰኑ ነው የተሰማው፡፡መንግስት በሌላ በኩል በሬስቶራንቶችና በካፍቴሪያዎች ላይ ከተደረገ ሌላ ዘመቻ በተጨማሪ ክብደቱን በትክክል መያዙን ለማረጋገጥ በመዲናዋ መጋገሪያዎች ላይ የክትትል ዘመቻዎች እንደሚያደረግ አስታውቋል፡፡

በሚያዝያ 2020 (እ.ኤ.አ.) የካርቱም መንግስት  በድጎማ የሚገኘውን የዳቦ ዋጋ ከ 1 ፓውንድ በአንድ ዳቦ ወደ 2 ፓውንድ ከፍ ማድረጉ ይታወሳል ፡፡ምንም እንኳን አንዳንድ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎች የወሰደ ቢሆንም የአሁኑ የሱዳን የሽግግር መንግስት የግል ዳቦ ጋጋሪዎች የሚጠቀሙባቸውን ዱቄት ለጋጋሪዎች በቅናሽ ዋጋ እንዲደርስ አሁንም ድጎማ እያደረገ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን መንግስት በመሃል የሚገኙ አቀባባዮች የሚሄዱበትን የሙስና መንገድ መዝጋት እንዳልቻለ ነው የሚነገረው።ይህ በእንዲህ እያለ በሱዳን በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መኖሩ ነው እየተነገረ ያለው። በእዚህ ምክንያት ሀገሪቱ ከውጭ የምታስመጣቸው እቃዎች ላይ የራሱን ተፅኖ ፈጥሯል።አንድ የሁለተኛ ደረጃ ዩኒፎርም የለበሰ ወጣት ለዴይል ሜል በሰጠው ቃል በትምህርት ቤት ለቁርስ የሚሆን ዳቦ ማግኘት አልቻልንም ብሏል።

በ2019 ዓም እኤአ በዳቦ ዋጋ የተነሳው ተቃውሞ ኦማር አልበሽር ከስልጣን እስከመውረድ አድርሶ እንደነበር ይታወሳል።አሁን ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ባለበት ረጅም የዳቦ ሰልፍ ለሰዓታት መቆም ከመብራት መቆራረጥ ጋር ተደምሮ ለሕዝቡ ትልቅ የራስ ምታት ሆኗል።60 ቢልዮን ዶላር ዕዳ ያለባት ሀገር ባለፈው ወር ብቻ የዋጋ ግሽበቷ 269 በመቶ በላይ መድረሱ ሀገሪቱ ወደ ከፍተኛ ቀውስ እየመራት ነው።ይህ በእንዲህ እያለ በቅርቡ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ፀሐፊ ስቴቨን ምኑቺን ወደ አንድ ቢልዮን ዶላር ውዝፍ እዳ ከዓለም ባንክ ለማቅለል አንድ ዓይነት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟ እና ከአሜሪካ አስመጪ እና ላኪ ባንክ ጋር ሌላ የአንድ ቢልዮን ዶላር ስምምነት መፈራረሟ ለማወቅ ተችሏል።በሌላ በኩል የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ መንግስት አሜሪካ ለረጅም ጊዜ በሱዳን ላይ ጥላው የነበረው ሱዳንን በጥቁር መዝገብ ውስጥ ያስገባው እቀባ መነሳቱ ለሱዳን ምጣኔ ሀብት መነቃቃት ይፈጥራል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

በሌላው የሱዳን ክፍል ዳርፉር በእዚህ ሳምንት ውስጥ በተከሰተ አዲስ ግጭት 10 ሕፃናትን ጨምሮ 250 ሰው መገደሉ ተሰምቷል።በእዚሁ ግጭት 100 ሺህ ሰው ከቤቱ የተፈናቀለ ሲሆን ከ3 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ምስራቃዊ ቻድ መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ ያሳያል።የዳርፉር ግጭት በያዝነው አዲስ ሚሊንየም መጀመርያ ዓመቶች ላይ ከተጀመረ ወዲህ ከ300ሺህ በላይ ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን ወደ 2 ነጥብ 5 ሚልዮን ሕዝብ ደግሞ ተፈናቅሏል።

በሱዳን በአሁኑ ጊዜ በተከፋፈለው የጦር ኃይሉ እና በሽግግሩ መንግስት መሃል ያለው ልዩነት ከምንጊዜውም በላይ እያፈጠጠ ነው። የጦር ኃይሉ በራሱ መንገድ የመሄዱ አንዱ ማሳያ የኢትዮጵያን ድንበር መጣሱን የሽግግር መንግስቱ ባለስልጣናት ባይደግፉትም ጦሩ ግን በራሱ መንገድ ሄዷል።አሁን በሱዳን እየሆነ ያለውን አጠቃላይ ሂደት ላይ ሃሳባቸውን እንዲሰጡ ጉዳያችን የጠየቀቻቸው የሱዳን ምሑር ሁለት ስጋት እንዳለባቸው ገልጠዋል።አንደኛው ወገን ለውጡ እራሱ የመጣው አልበሽርን ገለል አድርጎ ሱዳን በአሜሪካ የተጫነበትን ዕቀባ ማስቀረት እና መልሶ የአልበሽር ደጋፊዎች በወታደራዊ መፈንቅል ተመልሰው ወደ ስልጣን እንዲመጡ የማድረግ ዕቅድ ቀድሞውንም ተይዟል የሚሉ ሲሆን።ሌላው ወገን ደግሞ የጦር ኃይሉ መኮንኖች በመካከለኛው ምስራቅ ባላንጣ ሀገሮች አንፃር ስለተቀራመቷቸው በእነኝህ ሀገሮች ሴራም አንፃር በሱዳን አሁን ያለውን የሽግግር መንግስት ለመፈንቀል እንቅስቃሴ እንደሚኖር ጥርጣሬ አላቸው።

ለማጠቃለል ሱዳን በቀውስ ውስጥ የምትንገዳገድ ሀገር ሆናለች።በውስጥ ያለው ቅራኔ በመካከለኛው ምስራቅ የገመድ ጉተታ ውስጥ የጦር ሹማምንቶቿ ገብተዋል።የሽግግር መንግስቱ ደግሞ የምጣኔ ሃብቱን ማረጋጋት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን የዳርፉር ችግር ከማጡ ወደ ድጡ እየሄደ ነው።ይህ በእንዲህ እያለ ሀገሪቱ አሁን ከሚታየው በላይ በግብፅም ሆነ በሌላ የውጭ ኃይል የበለጠ የምትዘወር ሀገር ሆና መቅረቧ ያልተረጋጋ የውጪ ፖሊሲ መኖር ብቻ ሳይሆን፣ከቀልቧ ጋር ያልሆነች ምድር ብትሆን ሊደንቅ አይገባም። የሱዳን ዓይነት አጀንዳ የተሸከመ ሀገር ጠባይ ከእዚህ ያነሰ ሊሆን አይችልም።ከእዚህ ሁሉ ጋር አሁን ያለው የሽግግር መንግስት እየሰከነ መጥቶ የጦር ኃይሉን ከነውጠኛ መኮንኖች አፅድቶ በእዚህ ዓመት ይደረጋል የሚባለው ምርጫ ከተሰካ ሱዳን ወደ አዲስ ዘመን እየተሸጋገረች ነው ማለት ነው።የሱዳን በእዚህ መልክ መረጋጋት ወጥ የሆነ የውጭ ፖሊሲ በተለይ ከምስራቃዊ ጎረቤቶቿ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጋር የሰከነ ግንኙነት እንዲኖራት ያደርጋታል።ከሁሉም በላይ በዓባይ ግድብ ላይ የምታነሳውን በራሷ ጥቅም ላይ የመቆም አባዜ በተላቀቀች ነበር።ሱዳንን ከመፈንቅለ መንግስት ይሰውራት? ወይንስ አይሰውራት? ጥያቄ ነው።ለኢትዮጵያ የሽግግር መንግስቱ ቢረጋጋ እና የጦር መኮንኖቹን ቢቆጣጠር የተሻለ የሚሆን ይመስላል።አሁን የጦር መሪዎቹ የሽግግር መንግስቱን በመናቅ በራሳቸው የሚቦርቁባት ሀገር ሆናለች።እነኝህ መኮንኖች ወደ ስልጣን ቢመጡ ከጥቅሙ ጉዳቱ ለአፍሪካ ቀንድ አይተርፍም ማለት አይቻልም።ምክንያት - ከአሁኑ በባሰ በውጭ ኃይሎች የምትዘወር ምድር መሆኗ ሊብስ ይችላል።
=================