ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, January 12, 2023

የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር በቋንቋ ዙርያ ያሳለፈው ውሳኔ አረብኛን ሲያካትት ከኢትዮጵያ አልፎ በአውሮፓና ካናዳ ዩንቨርሲቲዎች የሚሰጠውን የግዕዝ ቋንቋ በስርዓተ ትምሕርቱ ውስጥ አለማካተቱ ታሪካዊ ስህተት ብቻ ሳይሆን በደል ነው። አሁንም ማረም አለበት።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በቋንቋ ጉዳይ ውሳኔ የሰጠበት ስብሰባ
 (ፎቶ ፋና ብሮድካስቲንግ)
  • ፖሊሲ ሕዝብ ያድናልም፣ይገድላልም። 
  • ግዕዝ በትምሕርት ቤቶች እንዲሰጥ ህዝብ መጠየቅ አለበት።
  •  መንግስትም ምላሽ መስጠት አለበት። 
=======
ጉዳያችን
=======
የአዲስ አበባ ክልል አስተዳደር ካቢኔ በአዲስ አበባ የሚገኙ ተማሪዎች የሚማሩትን የቋንቋ ዓይነት በተመለከተ ውሳኔ ማሳለፉ ዛሬ ተነግሯል። ዜናውን አስመልክቶ ፋና ብሮድካስቲንግ እንዲህ ዘግቦታል።

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባካሄደው በ2ኛ አመት 8ኛ መደበኛ ስብሰባው ከብዝሃ ቋንቋ ካሪኩለም ጋር በተያያዘ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

ካቢኔውም በመደበኛው ስብሰባ የብዝሃ የቋንቋ ስርዓተ ትምህርትን አስመልክቶ የኮተቤ ትምህርት ዩንቨርሲቲ ሲያስጠናው የቆየውን አዲሱን ካሪኩለም አስመልክቶ የተወያየ ሲሆን ዩንቨርሲቲው ባስጠናው ጥናት ዙርያ ሰፋ ያለ የተለያዩ የህዝብ ( የተማሪ ወላጆችን ጨምሮ) ምክክሮችና ውይይቶች ሲካሄዱበት ቆይቶ በዛሬው እለት በጥናቱ በቀረቡት ምክረ ሃሳቦች ዙርያ ውሳኔውን አሳርፏል፡፡

በዚህም መሰረት፡-

1ኛ:- በአዲሱ ስርዐተ ትምህርት ጥናት መሰረት በአፋን ኦሮሞ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ለሚማሩ ተማሪዎች አማርኛ እንደ ተጨማሪ (ሁለተኛ ) ቋንቋ እንዲሰጥ

2ኛ:- በአማርኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ለሚማሩ ተማሪዎች ደግሞ አፋን ኦሮሞ እንደ ተጨማሪ (ሁለተኛ )ቋንቋ እንዲሰጥ

3ኛ:- ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ በሁሉንም የከተማው ትምህርት ቤቶች ሁሉንም የትምህርት አይነቶችን በእንግሊዘኛ መማር እንዲችሉ እንዲደረግ

4ኛ:- ለ9ኛ እና 10ኛ ክፍል ተማሪዎች አረብኛና ፈረንሳይኛ በሃይስኩል ደረጃ አማራጭ ትምህርት ሆኖ እንዲቀጥል፡፡

5ኛ:- የቅድመ አንደኛ ደረጃ የትምህርት መጀመሪያ እድሜ ከ4 ዓመት እንዲሆን

6ኛ:- በአዲሱ የስርዓተ-ትምህርት ማዕቀፍ መሰረት 11ኛ እና 12ኛ ክፍል የስራ እና ቴክኒክ ትምህርት በተለያዩ አመራጮች እንደሚማሩ በሚያስቀምጠዉ መስረትና ከፍተኛ ሀብት የሚፈልግ በመሆኑ ከቴክኒክና ሞያ ኮሌጆች በክላሰተር በቅንጅት እንዲሰጥና በተጠናው ጥናት መሰርት ወደ ግንባታ እንዲገባ እንዲደረግ

7ኛ:- የግል ት/ቤቶችን የመፅሐፍት እጥረት ለመቅረፍ በሽያጭ ለማቅረብ ለመጽሓፍት ህትመት የተዘዋዋሪ ፈንድ 250 ሚሊየን ብር ተጨማሪ በጀት እንዲፈቀድ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ ከኦሮምያ ክልል ለኦሮምኛ ቋንቋ ማስተማርያነት በውሰት ተወስዶ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው ስርአተ ትምህርት በአዲሱ ስርዐት ትምህርት የሚተካ ይሆናል። ይላል ዜናው።


የካቢኔው ውሳኔ ተማሪዎች የተለያዩ ቋንቋዎች እንዲማሩ መደረጉ ባልከፋ።ችግሩ ግን ኢትዮጵያውያን ስለራሳቸው ታሪክ፣ሳይንስ፣ሃይማኖት፣ፍልስፍና፣አስተዳደር እና ሕግ ጭምር የተጻፉ መጻህፍትን እንዳይመረምሩ የግዕዝ ቋንቋ እንዲማሩ አለማድረጉ ታሪካዊ ስህተት ብቻ ሳይሆን በደል ነው።አረብኛ የሃይማኖት ቋንቋ ብቻ እንዳልሆነ ሁሉ፣የግዕዝ ቋንቋ የሃይማኖት ቋንቋ ብቻ አይደለም። ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም ታሪክ የሚገኝበት ጥልቅ ምስጢር ያለው እና ኢትዮጵያውያን በዓለም ላይ የነበራቸው ኃያልነት ሁሉ የተደበቀበት ነው።የአውሮፓ እና አሜሪካ ተመራማሪዎች በግዕዝ የተጻፉ መጻሕፍትን እያጋዙ የወሰዱት ከመድሃኒት እስከ የጠፈር ምርምር በርካታ ጽሑፎች ስላገኙበት ነው።


የግዕዝ ቋንቋ በአሁኑ ጊዜ በጀርመን፣ካናዳ፣አሜሪካና ሩስያ ዩንቨርሲቲዎች እየተሰጠ ነው።ባለቤቷ ኢትዮጵያ ግን በትምሕርት ቤቶቿ መስጠት አቅቷታል።የግዕዝ ትምህርት ለተማሪዎች ለመስጠት የመምሕራን ችግር ፈጽሞ የለም።ሆኖም ግን የአረብኛና ፈረንሳይኛ መምህራን ለማግኘት ኢትዮጵያ ከውጭ መምህራንን መቅጠር ያስፈልጋታል። ቋንቋ መማር ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የሕዝብ አቅም በምጣኔ ሃብትም ሆነ በማኅበራዊ ግንኙነቱ ያጠናክረዋል እንጂ አይጎዳም።ነገር ግን ግዕዝን የሚያህል የራስን ቅርስ አጥፍቶ እና ትውልድ እንዳይማረው አድርጎ መሄድ ታሪካዊ ስህተት ብቻ ሳይሆን በደል ነው። ፖሊሲ ህዝብ ይገድላልም ያድናልም። የግዕዝ ትምህርት በትምሕርትቤቶች አለመስጠት ኢትዮጵያውያን ታሪካቸውን እንዳያውቁ እና የነበራቸውን ሃገር በቀል ዕውቀት ለራሳቸው እንዳይጠቀሙ ከማድረግ ባለፈ ለዓለም በኩራት ስለራሳቸው እንዳይናገሩ የማድረግ እኩይ ተግባር ነው።ግዕዝ በትምሕርት ቤቶች እንዲሰጥ ህዝብ መጠየቅ አለበት። መንግስትም ምላሽ መስጠት አለበት። 

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...