በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡
- ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ?
- የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመረጡ?
- የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እነማን ናቸው? የትምሕርት ዝግጅታቸውና ልምዳቸውስ?
- የኮሚሽኑ ርዕይ፣ተልዕኮ፣ዓላማው እና መርሆዎቹ ምንድን ናቸው?
- የኮሚሽኑ ተግባርና ኃላፊነቶቹ ምንድን ናቸው?
- የኮሚሽኑ ምክርቤት ተግባርና ሥልጣን ምን ምን ናቸው?
- የምክክር ኮሚሽኑን የኢትዮጵያ ደህንነት እና ሰላም አንዱ እና ዋናው መፍትሄ አድርጎ መውሰድ ይቻላል?
- የውይይት ሰነዶች ከውይይት በኋላ ምን ይሆናሉ?
መነሻ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዴት ተመሰረተ?
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ርዕይ፣ተልዕኮ፣ዓላማው እና መርሆዎቹ ምንድን ናቸው?
ርዕይ
የኮሚሽኑ ርዕይ እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ተፈጥሮ ማየት ነው፡፡
በኢትዮጵያ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ ፣ በተለዩ አጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ ምክሮችን በማካሄድ፣ ምክረ ሀሳቦችን በማቅረብ እና ለተግባራዊነቱም የመከታተያ ስርዓ በመዘርጋት ለሀገራዊ መግባባት ምቹ ሁኔታ መፍጠር፡፡
- በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተጠሩ ልዩነቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በመለት እና ውይይቶቹ የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት ምክክር እንዲደረግባቸው ማመቻቸት፤
- የሚካሄዱት ሀገራዊ ምክክሮች አካታች፣ ብቃት ባለውና ገለልተኛ በሆነ አካል የሚመሩ፣ የአለመግባባት መንስዔዎችን በትክክል በሚዳስስ አጀንዳ የሚያተኩሩ፣ ግልፅ በሆነ የአሠራር ሥርዓት የሚመሩ እና የምክክሮቹን ውጤቶች ለማስፈፀም የሚያስችል ዕቅድ ያላቸው እንዲሆኑ በማድረግ ውጤታማ የሆኑ ሀገራዊ የምክክር ሂደት ተግባራዊ ማድረግ፤
- የሚካሄዱት ሀገራዊ ምክክሮች በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እንዲሁም በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል፣ መተማመን የሰፈነበትና አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር በሚያስችል አግባብ ውይይቶቹ እንዲካሄዱ ሥርዓት መዘርጋት፤
- ከምክክሮቹ የተገኙ የመፍትሔ ምክረ ሃሳቦች በሥራ ላይ እንዲውሉ ድጋፍ በማድረግ በዜጎች መካከል እንዲሁም በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመን የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲገነባ ማስቻል፤
- ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ለማዳበር እና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምቹ መደላድል መፍጠር፤
- ወቅታዊ ችግሮች ዘላቂ በሆነ መንገድ ተፈተው አስተማማኝ ሰላም የሚረጋገጥበትን የፖለቲካ እና የማኅበራዊ መደላድል ማመቻቸት፤
- ለአገራዊ መግባባት እና ጠንካራ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ጽኑ መሠረት መጣል ናቸው።
የምምክር ኮሚሽኑ ተግባርና ኃላፊነቶች
- ምክክሮችን የሚያመቻቹና ሚያስፈጽሙ፣ የተለያዩ ጥናቶችን የሚያካሂዱ እና ምክረ ሃሳቦችን የሚያመነጩ ኮሚቴዎችን እና የባለሙያ ቡድኖችን ያቋቁማል፤
- ከዚህ በፊት በመንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት የተደረጉ ሀገራዊ የምክክር ሂደቶችን እና የተገኙ ውጤቶችን ያጠናል፣ በቀጣይ ለሚያካሂዳቸው ሀገራዊ ውይይቶች በግብዓትነት ይጠቀማል፤
- በተለያዩ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉትን ልዩነቶች በጥናት፣ በሕዝባዊ ውይይቶች ወይም ሌሎች አግባብነት ያላቸውን መንገዶች በመጠቀም ይለያል፤
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አቀጽ (፫) መሰረት በተገለፁት ዘዴዎች የለያቸውን ጉዳዮች መሰረት በማድረግ የምክክር አጀንዳዎችን ይቀርፃል፣ ምክክር እንዲደረግባቸው ያመቻቻል፣ ምክክሮችን እና ውይይቶችን ያሳልጣል፤
- ከመላ ሀገሪቱ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እና አካላትን የሚወክል ተሳታፉዎች የሚሳተፍባቸው፣ ሀገራዊ መግባባት ለማምጣት የሚያስችሉ የተለያዩ የምክክር ስብሰባዎችን በፌደራል እና በክልሎች ደረጃ እንዲካሄዱ ያመቻቻል፤
- በሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ ተሳታፉዎችን ግልፅ በሆኑ መሥፈርቶች እና የአሠራር ሥርዓት መሠረት ይለያል፣ በምክክሮች ላይ እንዲሳተፉ ያደርጋል፤ ይህን የተመለከተ ዝርዝር መመሪያ ያወጣል፤
- ምክክሮቹ በኮሚሽነሮች ወይም የኮሚሸነሮች ምክር ቤት በሚሰይማቸው አወያዮች አማካኝነት እንዲመሩ ያደርጋል፤ በአወያይነት የሚመድባቸዉ ሰዎችም በተቻለ መጠን በዚህ ሕግ አንቀጽ ፲፫ ላይ የተመለከቱትን ለኮሚሽነርነት የሚያበቁ መስፈርቶችን የሚያሟሉ መሆናቸዉን ያረጋግጣል፤
- በምክክር ሂደቶች የሚደረጉ ምክክሮችን ቃለ ጉባዔ የሚዙ፣ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችን የሚያጠናቅሩ እና አደራጅተው ለኮሚሽነሮች ምክር ቤት የሚያቀርቡ ባለሙያዎችን ይመድባል፤
- የጽህፈት ቤቱን የውስጥ የአሠራር ሥርዓት፣ የምክክር አጀንዳዎች ወይም አርዕስት የሚመረጡበትን የሚመለከት፣ በሀገራዊ ውይይቶች ላይ የሚሳተፉ አካላት የሚለዩበትን ሥርዓት ለመዘጋትና መሰል ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችሉ ውስጠ ደንቦችን እና መመሪያዎችን ያወጣል፣ በሥራ ላይ ያውላል፤
- የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ አጀንዳዎችን፣ የምክክሮቹን ሂደት፣ በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን እንዲሁም ምክረ ሃሳቦቹ በተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉበትን ሥልት የሚገልጽ ሰነድ በማዘጋጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለአስፈጻሚ አካሉ እና ሌሎች የሚመለከታቸዉ የመንግስት አካላት ያቀርባል፤ ለሕዝብም ይፋ ያደርጋል፤
- መንግሥት ከሀገራዊ ውይይቶች የሚገኙ ምክረ ሃሳቦችን በተግባር ላይ ለማዋል እንዲችል ግልፅ እና ተጨባጭ የሆነ ዕቅድ እንዲዘጋጅ አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋል፤
- የምክረ ሃሳቦቹን አፈፃፀም መከታተል የሚያስችል ሥርዓት ይዘረጋል፤ ዓላማውን ለማስፈፀም የሚያስፈልጉ ሌሎች ተግባራትን ያከናውናል።
የኮሚሽኑ ምክርቤት ተግባርና ሥልጣን
- የሕዝብ ምክክር የሚደረግባቸውን አጀንዳዎች በዝርዝር በመፈተሽ ምክክር እንዲደረግባቸው መወሰን፤
- በኮሚቴዎች ተዘጋጅተው የሚቀርቡ እና በሕዝባዊ ውይይቶች የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን በዝርዝር በመፈተሸ እና በማጠናቀር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአስፈፃሚ አካላትና ሌሎች የሚመለከታቸዉ የመንግሥት አካላት እንዲቀርብ ማፅደቅ፤
- የጽህፈት ቤቱን ዓመታዊ በጀትና ዕቅድ መርምሮ የማፅደቅ፤
- የጽህፈት ቤቱን አጠቃላይ ሪፖርት መርምሮ የማፅደቅ፤
- አስፈላጊ ኮሚቴዎችን የማቋቋም፤
- በክልሎች የጽህፈት ቤቱን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች እንዲቋቋሙ የመወሰን፤
- የጽህፈት ቤቱን የኦዲት ግኝት መርምሮ የማፅደቅ፤
- የምክር ቤቱ ዋና ኮሚሽነርና ምክትል ዋና ኮሚሽነር በተመሳሳይ ጊዜ በሥራ ገበታቸው ላይ ለተከታታይ አስር ቀናት ካልተገኙ ከአባላቶቹ መካከል ጊዜያዊ ሰብሳቢ የመምረጥ፤
- የጽህፈት ቤቱን መዋቅራዊ አደረጃጀት የማፅደቅ፤
- የጽህፈት ቤቱን ኃላፊ ሹመት የማፅደቅ፤
- አዋጁን ለማስፈፀም የሚያስፈልጉ መመሪያዎችን የማውጣት፤
- የኮሚሽነሮች የሥነ ምግባር መመሪያ የማውጣት፤
- የጽህፈት ቤቱን የመተዳደሪያ ደንብ የማውጣት፤
የምክክር ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ደህንነት እና ሰላም አንዱ እና ዋናው መፍትሄ አድርጎ መውሰድ ይቻላል?
የዛሬ ሦስት ዓመታት በታኅሳስ አጋማሽ ላይ የእዚህ ዓይነት ተቋም አስፈላጊነት ላይ ውይይት በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ‹‹ሰላም፣ ደኅንነት፣ ዲፕሎማሲና ልማት በኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ ምን ይደረግ?›› በሚል ርዕስ ምሁራንን ያካተተ የፓናል ውይይት ተደርጎ ነበር።በእዚሁ ውይይት ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም መምህርና ‹‹ብሔራዊ ደኅንነት በኢትዮጵያ›› በሚል የጥናት ርዕስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እየሠሩ ያሉት አቶ ዮናስ ታሪኩ ‹‹ደኅንነት›› በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ በተለይ ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ‹‹የማንን ደኅንነት እናስጠብቅ›› የሚለው ላይ አለመግባባት መኖሩንና በዚህም ምንክያት የአገሪቱ ደኅንነት ፍትጊያ ውስጥ መግባቱን መናገራቸው ተዘግቧል።
በእርሳቸው ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ እንደተገለጠው የሃገረ መንግስቱ መጠበቅ የቡድን መብት መጠበቅ ለምሳሌ በቋንቋ እና ማንንነት ላይ ያለው ከለላ ትኩረት እንዲሰጠው የሚፈልጉ የመኖራቸውን ያህል በተቃራኒው ሃገረ መንግስቱ መጠበቅ ላይ ኢትዮጵያዊነትን በሚገባ ይዞ መጓዝ እንዳለበት አጥብቀው የሚያሳስቡ እንዳሉ ገልጠዋል። አቶ ዮናስ ማብራርያቸውን በመቀጠል የሁለቱ ቡድኖች ሃሳብ እርስ በርስ የሚጋጩ አስመስሎ በማቅረብ ችግር የመፍጠር ሁኔታ መሆኑን ገልጠው ይህ ግን ወደ ግጭት ሊያመራ እንደማይገባ አብራርተዋል።ይህ እና ሌሎች ጥናቶች የሚያሳዩት የምክክር ኮሚሽን ተግባር ለኢትዮጵያ የደኅንነት እና ሰላም አንዱ እና ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ነው።|
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገራዊ ደረጃ የማያግባቡ አጀንዳዎችን መርጦ በሰነድነት አዘጋጅቶ ለውይይት የሚያቀርብ አና የሚቋጩትን በመቋጨት ያልተቋጩትን ደግሞ በውይይት እንዲፈቱ የማድረግ ትልቅ ሀገራዊ አደራ ተቀብሏል። ሌላው እና የኮሚሽኑ ትውልድ ተሻጋሪ መሆኑን የሚያሳየው የኮሚሽኑ ተግባር ደግሞ የውይይት ሰነዶቹ ሂደት ጭምር ለቀጣይ ትውልድ መማርያ እንዲሆኑ በሚገባ በሰነድነት ሰንዶ ለብሄራዊ ቤተ መዛግብት የሚያስረክብ ሲሆን፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሰነዶቹን በፈለገ ጊዜ ለመመልከት እንዲችል ሁኔታዎች የሚመቻቹ መሆናቸው ነው።
የመረጃ ምንጮች ፡
- ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ድረ ገጽ
- ጉዳያችን ስለኮሚሽኑ ከሦስት ዓመት በፊት የጻፈችው
.png)