Thursday, April 28, 2022

ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ቡድኖች የየዋህ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞችን የእምነት ስሜት ቆስቁሰው ወደ ግጭት ሊመሩን ሲሞክሩ ልንታለል አይገባም።

ኢትዮጵያውያን ታዳጊ ሙስሊም እና ክርስቲያን አዲስ አበባ ሙዚየም በር ላይ 
Photo = Adam Jones
  • በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ወደ ውጭ የፈረጠጠው ''የሸኔ የውስጥ አርበኛ'' ከሽብርተኛው የህወሃት ቡድን ጋር ከፈረጠጠባቸው አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ ሃገሮች ውስጥ ሆኖ የሰሞኑን በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እና ሙስሊም ወገኖቻችን መሃከል ግጭት እንዲፈጠር ሲያስተባብር ነበር።
===============
ጉዳያችን / Gudayachn
===============

በኢትዮጵያ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ለማጋጨት ሙከራ ሲደረግ ዛሬ አዲስ አይደለም።ለ27 ዓመታት ህወሃት ኢትዮጵያን ሲመራ ሆን ብሎ የሃይማኖት ግጭቶች እንዲነሱ ሰርቷል። ክርስቲያኖች የጥምቀት በዓል ሊያከብሩ አንድ ቀን ሲቀራቸው ሙስሊሞችን የደገፈ የመሰለ መግለጫ ሲወጣ፣ የሙስሊም ወገኖቻችን ድምጻችን ይሰማ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የሙስሊም መንግስት ይመስረት እያሉ ነው የሚል የሃሰት ወሬ በክርስቲያኖች መሃከል ይዘራ ነበር።ህዝብ ከህዝብ ጋር የሚነጋገርበት የራሱ ልዩ ቋንቋ ስላለው ይህ ሁሉ ከንቱ ሙከራ ሆኖ አልፏል።

ሰሞኑን መንግስት በሸኔ ላይ የጀመረው በድሮን የታገዘ መጠነ ሰፊ ዘመቻ በራሱ በመንግስት ውስጥ ሆነው የሸኔን እና የሸኔ መመታት የህወሃት አንዱ ክንፍ መመታት መሆኑ ያስበረገጋቸው ሁሉ አንድ ዓይነት ግርግር ካልፈጠሩ በቀር የውድቀታቸው መጨረሻ እንደሆነ ገባቸው። በእዚህ ደግሞ ከውጭ ያሉ የባዕዳን አዝማቾቻቸው ጭምር የውስጥ ተላላኪዎቻቸው ላይ የሚወሰደው እርምጃ አስደንግጧቸው ከርሟል።ባዕዳኑ በከፍተኛ ደረጃ ኢትዮጵያን ከማወክ ባለፈ ይበትንልናል ብለው በቅደም ተከተል ያስቀመጡት ቀዳሚው ሽብርተኛው ህወሃት ሲሆን በማስከተል የቤንሻንጉል እና የኦነግ ሸኔ እንቅስቃሴዎች ናቸው። ህወሃት በህዝብ ክንድ ተመትቶ ወደ ጎሬው ሲገባ በሎጀስቲክ እና በምክርም ጭምር ከተረፈው የህወሃት ቡድን ጋር አቀናጅተው ኢትዮጵያን ለማወክ ተስፋ ያደረጉበት ሽኔ ከበርካታ ቦታዎች ሰሞኑን በመከላከያ ሰራዊት እየተመታ ሲጠራረግ አንዳንድ የቡድኑ ደጋፊዎች ወደ ውጭ ሃገር መፈርጠጣቸው የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም።

ይህ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ወደ ውጭ የፈረጠጠው የሸኔ የውስጥ አርበኛ ከሽብርተኛው የህወሃት ቡድን ጋር ከፈረጠጠባቸው አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ ሃገሮች ውስጥ ሆኖ የሰሞኑን በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እና ሙስሊም ወገኖቻችን መሃከል ግጭት እንዲፈጠር ሲያስተባብር ነበር።ለግጭቱ የገንዘብ ድጋፍ የተገኘውም ሆነ በየዋሃን እምነታቸውን በሚያከብሩ ክርስቲያን እና ሙስሊም ወገኖቻችን መሃከል የተደራጁ በወገናቸው ደም የሚነግዱ ተከፋዮች መዋቅራቸውን አንዳንድ የክልል ባለስልጣናት ቢሮ ውስጥ ሁሉ በገንዘብ ኃይል ለመዘርጋት የሞከሩ ሲሆን የሰሞኑ የጎንደርም ሆነ የዛሬው በወራቢ የደረሱት ጥቃቶች የእነኝህ ተከፋዮች ስውር እንቅስቃሴ ውጤቶች ናቸው።በጎንደር ባብዛኛው ሙስሊም ወገኖቻችን ሲጠቁ፣በወራቢ ደግሞ ክርስቲያን ወገኖቻችን ተጠቅተዋል። በሁለቱም ቦታዎች ቤተክርስቲያን እና መስጊድ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። የጥቃቱ አነሳሾችም ሆኑ ጥቃት አድራሾቹ ላይ መንግስት ግልጽ በሆነ መንገድ ለፍርድ ማቅረብ እና ቅጣታቸውም ህዝብ አስተማሪ መሆን ይገባዋል።

በሙስሊም ወገኖቻችን መሃከል ሆነው ክርስቲያኖችን የሚያስቆጡ ድርጊቶች መፈጸም፣ በክርስቲያን ወገኖቻችን መሃከል ሆነው ሙስሊም ወገኖቻችንን የሚያበሰጭ እና የሚያጋጭ ተግባር እንዲፈጸም ማድረግ እና በሚያስገኙት የደም ማስፈሰስ ስፋት እና ጥልቀት እየታየ በልዩ ልዩ መንገዶች የሚከፈላቸው የራሳችን ወገኖች ተልዕኮ የሰሞኑ ክስተት ውጤት ነው። ድርጊቱን ደግሞ የኢትዮጵያ ባላንጣ የሆኑ የቅርብ ሃገሮች በስለላ መዋቅሮቻቸው ከጀርባ የሚደግፉት እና ያገኙትን ቀዳዳዎች ሁሉ በመጠቀም የማባባስ ስራዎች ላይ ተጠምደው ከርመዋል። ተከፋይ አጋጮች መሬት ላይ የሚሰሩት ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ ሚድያ የሚያጣሉ እና አንዳንዶቹ በክርስቲያንም ሆነ በሙስሊም ስም ዩቱበር እና ፌስቡክ ከፍተው ሁለቱም ላይ የሚያጋጩ ጽሑፎች እየለጠፉ ሕዝቡን ለማባላት የሚጥሩ ናቸው። ለእዚህ ነው ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ዝም ብለው የነበሩ በክርስቲያንም ሆነ በሙስሊም ወገኖቻችን የሚታወቁ ተከፋይ የሃይማኖቱ አስተማሪ ተብዬዎች ቁስል እየፈለጉ እና ያሉ መለስተኛ አለመግባባቶችን እያሳበጡ ለመቀስቀስ ከየጠፉበት ብቅ እያሉ መሆናቸውን መመልከቱ በቂ ማስረጃ ነው።እነኝህ ተከፋዮች መምሕራን ተብዬዎች በመገናኛ ብዙኃን የተሰሙ መለስተኛ ግጭቶች የሕዝቡን ስሜት እንዲነኩ አድርገው እየጮሁ እና ስሜት እንዲኮረኩር አድርገው በመንገር አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ ስልታዊ በሆነ መንገድ ይቀሰቅሳሉ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የተንኮል ዓይነቶቹን መለየት አለበት። መሬት ላይ ያለው እውነታ የጽንፍ አስተሳሰቦች አሉ።ሆኖም ግን ብዙኃኑ ክርስቲያንም ሆነ ሙስሊም ወገናችን በየራሱ ውስጥ ያሉትን የጽንፍ አስተሳሰብ አራማጆች ፈጽሞ አይቀበላቸውም።ይልቁንም ከሁሉም የመንፈሳዊ አገልግሎቶች ከጽንፍ ባለፈ የፖለቲካ አስተሳሰብ አራማጆችን በቻለው አያቀርብም፣ይከላከላል።ሆኖም ግን እነኝህ ተከፋይ አጋጮች ትንሽ የመግቢያ ቀዳዳ የሚያገኙት መለስተኛ ግጭቶች ታይተው የህዝብ ስሜታዊነት በሚያይልበት እና እነርሱም የጥላቻ ቅስቀሳቸውን በሚያቀጣጥሉበት ጊዜ ነው።ባጭሩ ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ቡድኖች የየዋህ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞችን የእምነት ስሜት ቆስቁሰው ወደ ግጭት ለመምራት ሲሞክሩ ልንታለል አይገባም።ከአንደኛው ክ/ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ የኖረው ክርስትናም ሆነ ከ6ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ ያለው የእስልምና እምነቶች ዛሬ በተከፋይ የፖለቲካ ከሳሪዎች እንደእንግዳ አይተያዩም።እንንቃ!
=================////==============

Tuesday, April 26, 2022

በዩክሬን ግጭት ሳቢያ ዘንድሮ የዓለም ምጣኔ 3.6 በመቶ ብቻ ያድጋል።የኢትዮጵያ ግን ዘንድሮ 3.8 በመቶ ሲያድግ በመጪው ዓመት ደግሞ በ 5.7 በመቶ ያድጋል ሲል አይኤምኤፍ አስታወቀ።

The Ethiopian economy will grow by 3.6% in 2022. By next year it will go up to 5.7% - IMF

በየሁለት ዓመቱ በሚያወጣው የዓለም ኢኮኖሚ ምልከታ ሪፖርት የኢትዮጵያን የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት (ጂዲፒ) ትንበያ ሳያካትት ያለፈው የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ)፣ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚያንሰራራበት ዕድል መኖሩን አስታወቀ፡፡

አይኤምኤፍ የሩሲያና የዩክሬይን ጦርነት የዓለምን ኢኮኖሚያዊ ማገገም ወደኋላ እንደሚመልሰው ባብራራበት አዲሱ ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እ.ኤ.አ በ2022 3.8 በመቶ ያድጋል ሲል ተንብዮ፣ በመጪው ዓመት ደግሞ ይህ ቁጥር ወደ 5.7 በመቶ ከፍ ይላል ብሏል፡፡ 

በጥቅምት ወር ይፋ ተድርጎ በነበረው የድርጅቱ ትንበያ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍጋኒስታን፣ ሊባኖስ፣ ሊቢያና ሶሪያ የተያዘውን የአውሮፓውያን ዓመት ጨምሮ ለቀጣይ አምስት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚኖራቸውን አጠቃላይ አገራዊ ምርት ዕድገት መተንበይ አለመቻሉን አስታውቆ ነበር።

ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚ በዋናነት የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከመከሰቱ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሽቆልቆል እንደሚገጥማቸው መተንበዩ አይዘነጋም፡፡ ኢትዮጵያ በትንበያው ያልተካተተችው በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ አገራዊ የምርት ዕድገት ሒደቱን ማመላከት አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነ መግለጹ ይታወሳል፡፡

ባለፈው ሳምንት ይፋ በተደረገው ሪፖርት መሰረት በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ንረት እኤአ በ2021 ከነበረበት  26.8% ወደ 34.5% እንደሚያድግ የተተነበየ ሲሆን፣ነገር ግን ይህ አኃዝ እ.ኤ.አ በ2023 ወደ 30.5 በመቶ ዝቅ የማለት ዕድል አለው ተብሏል፡፡

የሩሲያና የዩክሬይን ጦርነት የዓለም ምጣኔ ሀብትንእኤአ 2021 ከነበረው 6.1%  ዕድገት 2022 ወደ 3.6% ሊያወርደው እንደሚችል በሪፖርቱ ተመላክቷል። ይህ ደግሞ ጦርነቱ የውጪ ንግድ እንቅስቃሴዎችን በማስተጓጎል፣ የነዳጅና የምግብ ዋጋ ንረት በማስከተሉ እንደሆነ ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

ከሰሃራ በታች የሚገኙት ነዳጅ አቅራቢ አገሮች በአማካይ 3.4 በመቶ እንደሚያድጉ የተተነበየ ሲሆን፣ መካከለኛ ገቢ እንዳለቸው የሚነገርላቸው የአፍሪካ አገሮች ደግሞ በአማካይ 3.3 በመቶ እንደሚያድጉ ይጠበቃል፡፡

ዝቅተኛ ኢኮኖሚ አላቸው የተባሉት አገሮች በአማካይ ሊያድጉ ይችላሉ የተባለበት አኃዝ 4.8 በመቶ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 6.4 በመቶ፣ ኬንያ 5.7 በመቶ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከ4.7 አስከ 4.9 በመቶ የሚመዘገብ ዕድገት እንደሚስመዘግቡ ሲጠበቅ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ 3.8 በመቶ እንደምታድግ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዕድገት የዝቅተኛ ገቢ አላቸው ተብሎ ከተቀመጡት የአፍሪካ አገሮች ዝቅ ብሎ ቢገኝም፣ የነዳጅ ላኪ አገሮች ዝርዝር ውስጥ ከሚገኙት ናይጄሪያ፣ አንጎላና ጋቦን፣ እንዲሁም መካከለኛ ገቢ ካላቸው እንደ ደቡብ አፍሪካና ዛምቢያ ከመሳሰሉ አገሮች ብልጫ እንዳለው የአይኤምኤፍ ሪፖርት ትንበያ ያሳያል፡፡

የተራዘመ ጦርነት፣ ድርቅና ሰፊ የፀጥታ ችግር ውስጥ እንደምትገኝ በሚገለጸው ኢትዮጵያ ትንበያው ተስፋ የሚያሰንቅ ቢሆንም፣ አገሪቱ ብዙ ሥራዎች ማከናወን እንደሚገባት አመላካች እንደሆነ ሪፖርቱን የተመለከቱ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አስታውቀዋል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይ በሪፖርቱ ላይ ባቀረቡት አጭር ጽሑፍ እንዳመለከቱት፣ዓለም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ተዳክሞ የነበረውን ኢኮኖሚ እንዲያገግም የማድረግ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ነገር ግን የሩስያና የዩክሬይን ጦርነት ነገሮችን ለውጦታል ብለዋል፡፡

አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ የዕድገት ትንበያ የሠራው የተጀመሩ ሥራዎችን፣ እንዲሁም ሪፖርቶችን መሠረት አደርጎ ነው የሚለውን ከግንዛቤ እንደወሰደ ይታመናል ያሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ በተጨማሪም በአገሪቱ ውስጥ የግብርና ምርታማነት እንደሚያድግ፣ የውጪ ንግድ አማራጮች እንደሚሰፉ፣ ለዓለም ገበያ ክፍት መሆን  የጀመሩት ሥራዎችና የህዳሴ ግድብ የኃይል ምንጭ ጅማሮ ከግምት ውስጥ የገቡ ጉዳዮች ይሆናሉ የሚል እምነት እንዳለቸው አቶ ዋሲሁን ጠቁመዋል፡፡

የዜናው ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ ሚያዝያ 24፣2022 ዓም እኤአ ዕትም ነው።

https://ethiopianreporter.com/article/25300

====================/////=========

Tuesday, April 19, 2022

ኦነግ ሸኔ ከኦሮምያ ክልል በቶሎ ካልተወገደ ፋኖ መላው የአማራ ክልልን ሊቆጣጠር ይችላል።ሸኔ በኦሮምያ ፋኖ በአማራ ተሰማርተው ኢትዮጵያ የጦር አበጋዞች አገር እንዳያደርጓት ጥንቃቄ ያስፈልጋል።

ፋኖ፣ፋኖን ከ50 ዓመታት በፊት ያዜመው ድምጻዊ  ካሣ ተሰማ 
  • አሁን ያለንበት ከስጋቱ ሁሉ በጣም ጧት ላይ ነን።ሆኖም ግን አስፈላጊው ስራ በመንግስትም ሆነ በህዝብ በትብብር ካልተሰራ ቀትርም ምሽትም ይመጣል።
===============
ጉዳያችን / Gudayachn
===============
አገር ከብሔራዊ የጦር ኃይሏ ውጭ ምንም ዓይነት አደረጃጀት ቢኖረው ሌላ በሺህ የሚቆጠር የጦር ኃይል እንዲንቀሳቀስ የማንም አገር ሕግ አይፈቅድም።የማንኛውም መንግስት አንዱና ዋናው ግዴታውም ሰላም እና ጸጥታ ማስከበር ነው።ጸጥታን ማስከበር ድህነት በተስፋፋበት፣የምጣኔ ሃብቱ በተጎሳቆለበት ሁኔታ በራሱ ከባድ ፈተና አለበት።ምክንያቱም በቀላል የጥቅማጥቅም ድለላ ወጣቶችን በቀላሉ ወደ ጥፋት መንገድ መምራት የሚችል ከባቢያዊ ሁኔታ ይፈጥራል።ኢትዮጵያ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሕዝቧ ወጣት ነው።ይህ ኃይል ደግሞ ከሥራ ማጣት ችግሩ ጋር ተዳምሮ ብቸኛ የሥራ መስክ ጠብመንጃ አንግቦ መንቀሳቀስ እንዳይሆን ያሰጋል።

ኦነግ ሸኔ መንግስት ባለበት ሃገር አንድ ጊዜ ከሱማሌ አዋሳኝ መንደሮች፣ካለፈው እሁድ ጀምሮ ደግሞ በሸዋ ሮቢት ዙርያ ጥቃት ከፍቷል። እዚህ ላይ የሰሜን ሸዋ የመንግስት ተጠሪዎች በተለይ በሸዋ ሮቢት ዙርያ ዳግም የተከፈተው ጥቃት በግለሰቦች ግጭት የተነሳ እንደነበር ቢገልጹም ሁኔታው ግን እንደዛ እንዳልሆነ ለማወቅ ብዙም ምርምር አይጠይቅም።የኢትዮጵያ ከተሞች በኦነግ ሸኔ በተፈናቀሉ ስዱዳን እየተጣበቡ ነው። ደብረብርሃን ለእዚህ ጥሩ ምሳሌ ነች። ደብረብርሃን በኦነግ ሸኔ በሰሜን ሸዋ ባደረሳቸው ጥቃቶች ብቻ ሳይሆን በወለጋ ባደረሰው ጥቃትም የተፈናቀሉ ደብረ ብርሃን ከተማ ከትመዋል። 

የኦነግ ሸኔ በቶሎ አለመጥፋት አሁን ባሉት አነስተኛ ከተሞች የሚደረግ ጥቃት ብቻ አይሆንም መዘዙ። በቀጥታ ወደ የለየለት የከተማ የሽብር ቡድን እራሱን አያደራጅም ማለት አይቻልም።ለእዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቱ የሸኔ የገንዘብ፣የስንቅ እና ትጥቅ ምንጭ በስልጣን ላይ ያሉ የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት እና የጸጥታ ጉዳይ ኃላፊዎች ጭምር መሆኑ ነው። መንግስት ባሉት የጸጥታ መዋቅሩ በሚገባ የሕዝቡን የጸጥታ እና ደህንነት በሚገባ ካላስጠበቀ ሕዝብ ከውስጡ የወጡትን ፋኖ እንዲጠብቀው እና ኢመደበኛ በሆነ መልክ ሁሌም እንዲኖር ይፈልጋል።በእዚህ መሃል ደግሞ በቅንነት የቆመው የፋኖ አባል  ቀድሞ ባላሰበው መንገድ ሊገፋ ይችላል።

ጉዳዩ አደገኛ ነው። ፋኖ በተለይ በኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ያለው ታሪካዊ ዳራ እና በታሪክም ለኢትዮጵያ ነጻነት የፋሺሽት ጣልያንን ከኢትዮጵያ ማስወጣት ጀምሮ የተጻፈ ታሪክ አለው።በስሙ ሲዘፈንለት፣ግጥም ሲገጠምለት እና የራሱ ሕዝባዊ ቅርጽ ያለው ታሪክ አለው። በቅርቡ ከህወሃት ጋር በተደረገው ጦርነትም የአማራ ክልልን ከኢትዮጵያ መከላከያ ጋር በአንድነት አኩሪ ታሪክ ሰርቷል። ይህ በራሱ የጠለቀ ማኅበራዊ መሰረት እንዳለው በቀላሉ መረዳት ይቻላል።

በሌላ በኩል ኦነግ ሸኔ የኦነግ ጽንሰሃሳብ ውሉደ ውሉድ ወይንም ውላጅ ነው።ጽንሰ ሃሳቡ የጠራ የፖለቲካ ግብ አይኑረው እንጂ ጧት ማታ የሚያዜመው አማራውን፣ነፍጠኛውን ማጥፋት እና የኦሮምያ መንግስት መመስረት የሚሉት ሃሳቦች የት እንደሚያደርሱ ሳያውቅ የሚናውዝ እሳቤ ባለቤት ነው። የመናወዙ ዲግሪ ለመረዳት የኦሮምያ ክልልን ያሏትን የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች ሳይቀር የሚያወድመው ይሄው የኦነግ ውላጅ የሆነ ሃሳብ የተሸከመው ሸኔ ነው። 

ሸኔ በቀጥታ ፋሺዝም ነው። ፋኖ የቀደመ ታሪኩም ሆነ አሁን ያለበት ደረጃ ሕዝብ ተከላካይ ነው። ፋኖ በቀድሞ ታሪኩ ሂደቱ ግልጽ ነው። ይሄውም ጦርነት ሲመጣ ሴት ወንድ ሳይል ይዘምታል፣የሃገር ሰላም አስተካክሎ ተመልሶ ገበሬው ወደ ግብርና ሰራተኛው ወደ ስራው ይመለሳል።አበቃ! አሁን ባለንበት ጊዜ ሽብርተኛው ህወሃት ገና ከትግራይ ህዝብም ጫንቃ ላይ ገና አልተነቀለም፣ኦነግ ሸኔም በዘር ላይ በተመሰረተ የጥላቻ ወረራ ገና አልቆመም።ስለሆነም ፋኖ የቤቱ እና የልጆቹ ጉዳይ ካላስገደደው በግንባር ጥቂት ጊዜ መቆየቱ ጉዳት የለውም። ይህም ግን ያለው ውስጣዊ አመራር ወደ ሌላ አደገኛ መንገድ እንዳይመሩት ጥንቃቄ አያስፈልገውም ማለት አይደለም።ምክንያቱም የአገር ቀዳሚ መርሁ አንድ መከላከያ ሰራዊት ነውና።

በእዚህ ሁሉ መሃል ኦነግ ሸኔ ካልጠፋ ግን ፋኖ ወደ ቤቱ የመመለስ እድሉ ላይኖር ይችላል ብቻ ሳይሆን በሂደት የአማራ ክልልን በሙሉ የመቆጣጠር ሁኔታዎች አይፈጠርም ማለት አይቻልም።ለእዚህ ደግሞ ዋናው መሰረታዊ አመላካች ጉዳይ ህዝብ ከመደበኛ ሰራዊቱ ባላነሰ ባንዳንድ ቦታዎች ፋኖ በበለጠ ሁኔታ ይጠብቀኛል የሚል ሕዝብ እየተፈጠረ መሆኑ ነው። በእዚህ አስተሳሰብ ደግሞ በህዝቡ ላይ ልንፈርድበት ምንም ዓይነት ሞራላዊ ሁኔታ አይኖርም።ምክያቱም መንግስት የሰላም እና የጸጥታ መጠበቅ ስራውን በሚገባ መወጣቱን ማሳየት ብቸኛው አማራጭ ነውና።

ለማጠቃለል ኦነግ ሸኔ ከኦሮምያ ክልል በቶሎ ካልተወገደ ፋኖ መላው የአማራ ክልልን ሊቆጣጠር ይችላል።ሸኔ በኦሮምያ ፋኖ በአማራ ተሰማርተው ኢትዮጵያ የጦር አበጋዞች አገር እንዳትሆን ያሰጋል።አሁን ያለንበት ከስጋቱ ሁሉ በጣም ጧት ላይ ነን።ሆኖም ግን አስፈላጊው ስራ በመንግስትም ሆነ በህዝብ በትብብር ካልተሰራ ቀትርም ምሽትም ይመጣል።ለእዚህ ሁሉ መፍትሄው ችግሮቻችንን በሚገባ መረዳት ነው። የኦነግ ሸኔ አረመኔያዊ ተግባርን ከአማራ ክልል እና ከሱማሌ ክልል ባልተናነሰ በኦሮምያ ክልልም ይታወቃል። ይህ ሁኔታ ግን ወደፊት እንዳለ ላይቀጥል ይችላል። ለምሳሌ ኦነግ ሸኔ ፋታ ተሰጥቶት ከኖረ ፋኖ አገንግኖ ወጥቶ ከሸኔ የመከላከል ብቸኛ አውራ ሆኖ ለመውጣት ታሪክ በራሱ ይገፋዋል። ይህ ደግሞ ከላይ በርዕሱ እንደተገለጸው ኢትዮጵያ የጦር አበጋዞች አገር እንዳትሆን ያሰጋል።ለእዚህም ዛሬ የሚሰራው አገራዊ የጋራ ስራ ወሳኝ ነው። በእዚህ ስራ ደግሞ መተማመን የሚፈጥር አሰራሮች መንግስት በሁሉም መስክ ማስፈን፣ኦነግ ሸኔ ላይ የሚደረገው ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠሉ ፋይዳው ብዙ ነው።
============////============


Monday, April 18, 2022

በአማራ ክልል የጽንፍ እንቅስቃሴ? በአማራ ክልል ታዳጊዎችን ለጽንፍ ተግባር ለማሰማራት ስልጠና ተጀምሯል።ኦፌኮ ከሸኔ የጸዳ አይደለም የሚሉ ድምጾች ተበራክተዋል።ሽብርተኛው ህወሓት ሱዳን ውስጥ ስደተኛ ህጻናትን ለመመልመል እየተንቀሳቀሰ ነው።

በአማራ ክልል ታዳጊዎችን ለጽንፍ ተግባር የሚመለምሉ አሉ።

===============
ጉዳያችን / Gudayachn
===============

ጽንፈኝነት ዘር የለውም። የእገሌ ጎሳ ሲሰራው ስህተት እና ወንጀል፣የእንቶኔ ጎሳ ሲሰራው ትክክል ሊሆን አይችልም። ነጩን ነጭ፣ጥቁሩን ጥቁር ብሎ ኢትዮጵያዊነት ከሁሉም አቅጣጫ ገንኖ እንዲወጣ ማድረግ በምንም ዓይነት ድርድር ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም።ኢትዮጵያ ዘመናትን ተሻግራ ዛሬ ላይ የደረሰችው በጎሳቸው እያሰሉ ፍትሕ የማይሰጡ እውነተኛ መሪዎች ስለነበሯት ነበር። ህዝብን ወደ እልቂት የሚመራ ማናቸውም ዓይነት ተግባር ከየትኛውም ጎሳ ቢመጣ ኢትዮጵያን የሚል በሙሉ ሊቃወመው የሚገባ ነው።

ይህ በእንዲህ እያለ በአማራ ክልል ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 19 ዓመት የሆናቸው ታዳጊዎችን በተለያዩ ሰዋራ ቦታዎች ወታደራዊ ስልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን መረጃዎች ወጥተዋል።ስልጠና እንዲሰጡ የሚያደርጉት ደግሞ የጽንፈኝነት እንቅስቃሴ ለማራመድ ዕቅድ በያዙ አካላት መሆኑን መረጃው ያሳያል። እነዚህ በታዳጊዎች ህይወት ቁማር ለመጫወት የቆረጡ ሰዎች በተጠቀሰው የእድሜ ክልል ብቻ የሚገኙ  የአማራ ተተኪ ትውልዶች እንዲመለምሉና ጫካ ገብተው የትጥቅ ትግል እንዲጀምሩ በወሰኑት መሰረት በርካቶች እንደ እሳት እራት በከንቱ መስዋዕት ለመሆን እየተዘጋጁ ይገኛሉ፡፡ ይህ የአማራ ክልል ወደ እርስ በርስ ግጭት እንዲገባ ብቻ ሳይሆን ክልሉ ለኢትዮጵያ ካለው ጉልህ ሚና አንጻር የእዚህ ዓይነት የጽንፍ እንቅስቃሴዎች ለኢትዮጵያ ትልቅ አደጋ አለው።

የኢትዮጵያ የቅርብም ሆኑ የሩቅ ጠላቶቿ በአሁኑ ጊዜ ትልቁ ፍላጎታቸው በኢትዮጵያ የእርስበርስ ጦርነት እንዲነሳ በቻሉት መንገድ በተለያየ መንገድ ያኮረፉ ግለሰቦች በገንዘብ በመደገፍ ወደ ጽንፍ እንቅስቃሴ እንዲገቡ ማድረግ ነው። የሚገርመው ታዳጊዎችን የመመልመሉ ተግባር ከአልሸባብ ጭምር መማር አለብን የሚል አቋም ማንጸባረቁ አስገራሚው ጉዳይ ነው።በእዚህ እኩይ ተግባር የተሰማሩ ነገ ክልሉን ማባርያ ወደ የሌለው እልቂት ከትተው ሕዝቡን ወደ የማይወጣው ማጥ ውስጥ ብቻ የሚከቱ ሳይሆኑ እርስ በርሱ ተከባሮ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ወደ የባሰ ግጭት ከትተው መጪውን የኢትዮጵያውያንን ሕይወት የሚያጨልም አደገኛ አካሄድ በመሆኑ ከወዲሁ ህዝብ አውቆ ነቅቶ እና ተግቶ መቀመጥ አለበት።

ይህ በእንዲህ እያለ የትግራይ ወጣቶችን ያስጨረሰው ሽብርተኛው ህወሃት የትግራይ እናቶች ልጆቻችን የት አሉ? ብለው ሲጠይቁ ''የትግራይ ወጣቶችን ቆጥሮ ያስረከበኝ የለም '' የሚል የትዕቢት መልስ ከሰጠ በኋላ የትግራይ እናቶች በቤታቸው በድብቅ ከማልቀስ ሌላ አማራጭ አላገኙም።በኢትዮጵያ ያለውን የትግራይ ወጣት ያስጨረሰው ሽብርተኛው ሕወሃት ወደ ሱዳን ዘልቆ ታዳጊዎችን መመልመል ሥራ ላይ ተጠምዶ ሰንብቷል።ይህ በእንዲህ እያለ ግን በህወሓት ውስጥ የሁለቱ ቡድን ማለትም ድርድር እናድርግ የሚለው እና ጦርነቱን እያረዘምን እንዋጋ በሚሉት ቡድኖች መሃከል ውጥረቱ ከሯል።ጦርነቱን እንቀጥል የሚሉት የቡድኑ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች የሱዳኑን እንቅስቃሴ በዋናነት እንደሚመሩት  የሚነገር ሲሆን፤ ድርደር ይሻለናል የሚለው ጎራ የእነዚህን እንቅስቃሴ በጥርጣሬ ከማየት ባሻገር ውስጣዊ  ሽኩቻውን ከፍ እንዳደረገው በስፋት እየተሰራጨ ነው፡፡

በእነዚህ ሃይሎች የሚዘወረው ሱዳንን ማዕከል በማድረግ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የህወሓት ሽብር ቡድን በተደጋጋሚ በአልፋሽጋ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ለመግባት ሙከራ አድርጓል፡፡ በድንበር አካባቢ ሰርጎ ለመግባት በሚደረገው ሙከራ በርካታ የትግራይ ወጣቶችን ህይወት እንደዋዛ እየቀጨ የአካል ጉዳተኛ እያደረገ ከንቱ ምኞት ሆኖ ቢቀርም፤ ቡድኑ ለትውሉዱ ደንታ ቢስ መሆኑን በሚያሳይ መልኩ ትንኮሳውን ቀጥሏል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም መጨረሻ በአልፋሽጋ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ የቡድኑ ታጣቂዎች ውስጥ በርካቶች በኢትዮጵያ የፀጥታ አካላት በወተሰደ እርምጃ ተገድለዋል፡፡ ብዛታቸው ያልታወቀ የቡድኑ ታጣቂዎች ቆስለው በሱዳን ጦር ወታደራዊ ካምፕ ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል። 

ቡድኑ በሱዳን የሚገኘውን የህወሃት ክንፍ ለማጠናከር የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ መሆኑንም ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ በዚህ መሰረት የሰው ሃይል ከመመልመል አንፃር ዶክተር መኮነን፣ ብ/ጄኔራል ግደይ ሃይሉ (ወዲ ፊውዳል)፣ ኮሎኔል ዕኮት፣ ኮሎኔል ሃይለ፣ ኮሎኔል ወዲ አማረ የተባሉ እና በየደረጃው የሚገኙ የቡድኑ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች በተለያዩ የስደተኛ መጠለያ ካምፖች በመዘዋወር የትግራይ ተወላጆችና ታጣቂዎችን ለመቀስቀስ ኮሚቴ በማዋቀር እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። 

በዚህ መሰረት የሰው ሃይል ከመመልመል አንፃር ዶክተር መኮነን፣ ብ/ጄኔራል ግደይ ሃይሉ (ወዲ ፊውዳል)፣ ኮሎኔል ዕኮት፣ ኮሎኔል ሃይለ፣ ኮሎኔል ወዲ አማረ የተባሉ እና በየደረጃው የሚገኙ የቡድኑ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች በተለያዩ የስደተኛ መጠለያ ካምፖች በመዘዋወር የትግራይ ተወላጆችና ታጣቂዎችን ለመቀስቀስ ኮሚቴ በማዋቀር እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። የምልመላ ስራውን ለማሳካትም በጄኔራል ወዲ ፊውዳል የሚመራ ኮሚቴ ገዳሪፍ በሚገኘው የስደተኛ መጠለያ ካምፕ የሚገኙ ወጣቶችን ለመመልመል እንደተሰማራ ተጠቁሟል። በተመሳሳይ ኮሎኔል አጽረጋ እና ዶክተር መኮነን በተባሉ ግሰለቦች የሚመራ ኮሚቴ በካርቱምና አካባቢው የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ቡድኑን በመቀላቀል ወደ ስልጠና እንዲገቡ የመመልመል ስራዎችን እየሰሩ ነው። ሱዳንን ማዕከል በማድረግ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የህወሓት ሽብር ቡድን የሰው ሃይል አቅሙን ለማጠናከር የሚያደርገውን የቅስቀሳና ታጣቂዎችን የመመልመል ስራ አጠናክሮ ከመቀጠሉ ባሻገር ወታደራዊ ስልጠና እየሰጠ መሆኑ ታውቋል።አሸባሪው ቡድን በዚህ መልኩ የትግራይ ወጣቶችን ከመቀሌ እስከ ሱዳን እግር በግር እየተከታተለ መከራቸውን ለማራዘም እየሰራ ሲሆን፤ ይህ የማያባራ ሰቆቃ የሚጋብዝ እኩይ ሴራ አንድ ቦታ ሊቆም ይገባል፡፡ ቡድኑ በቃህ ሊባል ይገባል፡፡


በሌላ በኩል የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከሸኔ የጸዳ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ በህዝቡ መሃከል እየተወራ ነው። ለእዚህ መነሻነት በርካታ ጉዳዮች እየቀረቡ ነው።ከእዚህ ውስጥ አንዱ ድርጅቱ በቅርቡ ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ የአቋም መግለጫ ላይም ሆነ በኋላ ያወጣው መግለጫ ላይ አንድም ቦታ ሸኔ ያላወገዘ ብቻ ሳይሆን ከፓርቲው ጋር ቁርኝት ያላቸው አባላቱ በማኅበራዊ ሚድያ ሳይቀር ሽኔን ሲያሞካሹ ታይተዋል። ኦፌኮ ሸኔን በተመለከተ አለማውገዙ ብቻ ሳይሆን መንግስት እንዲደራደር የሚያግባባ መግለጫ ከማውጣቱ በላይ አመራሮቹ የሚሰጧቸው የተለያዩ መግለጫዎች የሚያሳዩት ይህንኑ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

ባጠቃላይ የጽንፍ እንቅስቃሴዎች በአዲስ መልክ በአማራ ክልል፣በመሃል ሃገር በኦሮምያ ብልጽግና ውስጥ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሸኔ አሁን በኦፌኮ ውስጥ አለ ተብሏል።በሌላ በኩል ሽብርተኛው ህወሓት ውስጡ እንደገና ከመከፋፈሉ በላይ ወደ ሱዳን ተሻግሮ ለአቅመ አዳም እና ሔዋን ያልደረሱ ልጆች እየመለመለ ነው። ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ለመክተት የሚደረግ የሃገር ውስጥም ሆነ የባዕዳን ሴራ ሁሉ ውጤት እንደሆነ ለማወቅ ሊቅነት አይጠይቅም። ኢትዮጵያውያን ጸንተው በመቆም ኢትዮጵያን ወደ የትኛውም የጽንፍ እንቅስቃሴ የሚገፉ ኃይሎች ከየትኛውም ክልል ቢነሱ ህዝብ እንደ ህዝብ ሊቃወመው ይገባል።ይህ የአሁኑ ትውልድን ማዳን ብቻ ሳይሆን መጪውን ትውልድም የማዳን ስራ ነው።
===============////============

Sunday, April 17, 2022

በኖርዌይ ኡስታዝ አቡበክር አሕመድ በተገኙበት ከኢድ እስከ ኢድ ጉዞ ወደ ሃገርቤት መርሃግብር ዙርያ ውይይት ተደረገ።አስተባባሪ ኮሚቴ ተዋቅሯል።ኢትዮጵያውያን የተጎዱትን ወገኖቻችንን ለመደገፍ በጉዞው እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።

====================

ጉዳያችን ዜና/Gudayachn News

====================

የአገር ቤት ጉዞ ሁለተኛ ክፍል የሆነው ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሃገር ቤት ጥሪ ከተደረገ በኋላ ዝግጅቱ መጠናቀቁ ከሰሞኑ ተሰምቷል።ይህንን ተከትሎም መርሃግብሩ ወጥቷል። በእዚህ መሰረት ዛሬ ሚያዝያ 9/2014 ዓም የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ (ኮሚኒቲ) በኖርዌይ ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሃገር ቤት ጉዞ ላይ ማብራርያ እንዲሰጡ ኡስታዝ አቡበክር አሕመድን በዙም ጋብዞ ከኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት አድርጎ ነበር።

ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ

በእዚህ መሰረት ኡስታዝ አቡበክር አሕመድ በማብራርያቸው ላይ ዝግጅቱ ትኩረት የተሰጠው እና ዝግጅቶችም እየተደረጉ መሆናቸውን አብራርተው፣ጥሪው ግን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያጠቃልል መሆኑን ገልጸዋል።በተጨማሪም እስልምና ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ ጀምሮ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በሰላም የኖረበት ሁኔታ ላይ አጽንዖት በመስጠት ከሌሎች አጎራባች ሃገሮች ጋር አነጻጽረው ገለጻ አድርገዋል።በተጨማሪም ኢትዮጵያ በእስልማን ውስጥ ያላት ከፍተኛ ቦታ እና ስደተኞችንም በመቀበል ደረጃ ቀዳሚ ሃገር መሆንዋን አብራርተው በአሁኑ ጊዜ በሳውዲ የሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ስላለው ፈተናም ድምጻችንን ማሰማት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በመጨረሻም ከኖርዌይ ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሃገር ቤት ጥሪ የሚሄዱም ሆኑ በሃሳብ እና በተለያዩ መንገዶች የራሳቸውን ድርሻ ለመወጣት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንን ለማስተባበር የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በኖርዌይ የስራ አስፈፃሚ አባላትን ያካተተ ጊዜያዊ ኮሚቴ ያቋቋመ ሲሆን በኖርዌይ የሚገኙ የሙስሊምን አደረጃጀቶችን እንዲያካትት ሃሳብ ተሰጥቶ ስብሰባው ተፈጽሟል።በጉዞ የማስተባበር ሥራ የተመረጡ ከኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በኖርዌይ ስራ አስፈፃሚ አባላት ውስጥ ወ/ሮ አስማ እና ወ/ሮ ለይላ ሲመረጡ፣ ከእነርሱ ጋር በተጨማሪ አብረው የሚሰሩ ወ/ሮ ኢትዮጵያ እና ወ/ሮ ሮዛ ተመርጠዋል።

ከእዚህ በታች ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሃገር ቤት ጥሪ መርሃግብር ያገኛሉ።

የሰንጠረዥ ምንጭ  = አዲስ ማለዳ ሚያዝያ 12/2014 ዓም

=============///================

Friday, April 15, 2022

የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግሮች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የፈጠሯቸው ችግሮች አይደሉም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰሜን ሸዋ ጉብኝት ላይ 
ሚያዝያ 7/2014 ዓም

===============
ጉዳያችን / Gudayachn
===============

ከችግር የፀዳ አገር የለም።የችግር ዓይነቱ መለያየቱ እርግጥ ነው። የኢትዮጵያ ወቅታዊውም ሆነ የከረሙት ፖለቲካዊ፣ምጣኔሃብታዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች ስረ መሰረታቸው ከኋላ የሚጀምር እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የፈጠሩት በሚመስል መልክ አንዳንድ ዩቱበሮችም ሆኑ ግለሰቦች ለህዝብ እንደሚያስተላልፉት የተሳሳተ መረጃ አይደለም። ችግሮቻችንን መረዳት እና የሚፈቱበት መንገድ ላይ ከመምከር ይልቅ በመንጋ አስተሳሰብ በመዋጥ ብቻ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ በተልዕኮ የማጥላላት ዘመቻ ከከፈቱ የአገር ውስጥ እና የባዕዳን የኢትዮጵያ ጠላቶች የሚወረወርላቸውን መርዘኛ ቃላት በማወቅም ካለማወቅ ወደ ውስጣቸው እያስገቡ መልሰው የወሬያቸው ማሟሻ ሲያደርጉ መመልከት አሳዛኝ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ሲመጡ የጠበቀቻቸው ኢትዮጵያ በጎሳ ላይ የተመሰረተ ህገመንግስት ብቻ ሳይሆን ታች ወረዳ ድረስ በጥላቻ የጎሳ ፖለቲካ የተወታተበ አሰራር እና አመራር ብቻ ሳይሆን የጸጥታ አስጠባቂም ጭምር ነው። አንዳንዶች ይህንን አሰራር እና አመራር ለምን አልቀየሩትም? የሚል ጥያቄ ይጠይቃሉ። ይህ ጥያቄ ተገቢ ጥያቄ ነው።ነገር ግን ጥያቄው የለውጡን አካሄድ ካለመረዳት የሚመነጭ ችግር ነው።ይህ ለውጥ በኢትዮጵያ በ1966 ዓም እና የ1983 ዓም ለውጥ የሚለይበት በተለይ የጸጥታ አጠባበቅ ታች በወረዳ ደረጃ የተለየ ባህሪ አለው። 

በ1966 ዓም የንጉሱ ሥርዓት በወታደራዊ መንግስት ከተቀየረ በኋላ ከመደበኛ ወታደሩ ውጭ ያለው ታች ያለውን የቀበሌ እና የወረዳ የጸጥታ አጠባበቅ በአብዮት ጠባቂ እና የገበሬ ማኅበር ታጣቂዎች የጸጥታ የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ወሰዱ። ወቅቱ በፖለቲካ የስልጣን ግጭት ከፍተኛ የደም መፋሰስ ቢያስከትልም የቀበሌና ገበሬ ማኅበር ታጣቂ ከስር ያለውን የጸጥታ አጠባበቅ እስከ የግለሰብ ቤት ድረስ እንዲወርድ አድርጓል።

በሌላ በኩል በ1983 ዓም የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ ብሔራዊ ጦር ሰራዊቱን ከማፍረስ ባለፈ አሁንም በከተሞች በቀበሌ እና በገጠር ደግሞ በገበሬው ደረጃ ልክ ወታደራዊ መንግስት በአብዮት ጠባቂ እና የገበሬ ማኅበር ታጣቂ እንዳደረገው ሁሉ ህወሃት/ኢህአዴግ በከተሞች 'ሰላምና መረጋጋት' የተሰኙ ታጣቂዎች በገበሬው ዘንድም በወታደራዊው መንግስት ዘመን የታጠቁ ታጣቂዎች በአዲስ ታጣቂዎች በመቀየር ከታች ያለውን የጸጥታ አጠባበቅ በማገዝ በቶሎ ጸጥታውን ማረጋጋት ተሞክሯል። የጸጥታው አካል ግን በራሱ የቆመ ሳይሆን የፖለቲካ አካሉ በታች ወረዳ ደረጃ ስለተቀየረ በ1966 ዓም ሆነ በ1983 ዓም የተፈጠሩት የጸጥታ አካላት ከፖለቲካ አመራሩ ጋር አብረው የተፈጠሩ ስለሆኑ እንደ እጅ እና ጓንት ለመያያዝ እና ለመናበብ ችለዋል።

አሁን ያለው ለውጥ ግን በትልልቅ የኢትዮጵያ የጸጥታ አካሎችን ለምሳሌ የመከላከያ እና የደህንነት መዋቅር ለማስተካከል የደከመውን ያህል ታች ወረዳ ላይ ያለው የጸጥታ መዋቅር እና የፖለቲካ አስተዳደሩን ግን እንደ 1966 ዓም እና እንደ 1983 ዓም አልቀየረም።በመሆኑም በክልል ደረጃ እና ከዋና ከተማዋ በራቁ ቦታዎች ላይ ያለው የጸጥታ መረጃዎች በስርዓት እንዳይፈሱ ቀድሞም የነበሩ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች በከተሞችም ሆነ በገጠር የመንግስት የአስተዳደር መዋቅር ላይ ብቻ ሳይሆን በህወሃት/ኢሃዴግ ዘመን የነበሩ ለውጡ የደከመ ሲመስላቸው ከህወሃት ጋር የሚጻጻፉ ሌላ ጊዜ ደግሞ የለውጥ ሃዋርያ እየሆኑ በዘረፋ ሲጠመዱ ከርመዋል።በመሆኑም ይህ ለውጥ በጸጥታ አደረጃጀትም ሆነ ከታች ያለውን የፖለቲካ አመራር ሳይቀየር የተገባበት ስለሆነ ብዙ ነገሮች ተደባልቀው መሄዳቸው ያስከተሉት ችግር አንዱ እና ዋናው የለውጡ ችግር ነው።ይህ ሁኔታ ወደ ኦሮምያ ክልል ሲመጣ ቀድሞ ከነበረው የኦህዴድ አክራሪ ቡድን ላይ ከውጭ የመጣው የኦነግ የተለያዩ አደረጃጀቶች በክልሉ አስተዳደራዊም ሆነ የክልል ኃይል ውስጥ በቀጥታ ገቡ።ከእዚህ ሁሉ በላይ ግን ህወሃት በኢትዮጵያ ላይ አጥምዶት የሄደው ከፋፋይ የጎሳ ፖለቲካ አራማጅ ሕገ መንግስት የችግሮቹ ዋና አንቀሳቃሽ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለአክራሪ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች እንደ ጋሻ ሆኖ ለወንጀል መፈጸምያ መጠቀምያ መሆኑ የታወቀ ነው። 

ይህ ለውጥ የጎሳ ፖለቲካን ተንጠላጥለው የስልጣን ጥማቸውን ለማርካት በሚራወጡ ኃይሎች እና ኢትዮጵያን የሁሉም እኩል ጠቃሚ ትሁን በሚሉ ኃይሎች መሃከል የሚደረግ ፍትግያ ውስጥ ለመሆኑ የሚጠራጠር የለም።ይህም ሆኖ ግን በብሔራዊ ውይይት ኮሚሽን ሃሳቦችን በሰላማዊ መንገድ ቀርበው ውይይት ሲደረግባቸው ብዙዎቹ ሃሳቦች መፍትሄ ያገኛሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።መፍትሄ የማያገኙ ሃሳቦች ቢኖሩ ቢያንስ ሕዝብ የበታኝ ኃይሎች ሃሳብ ምን ያህል ትውልድ እና አገር በታኝ እንደሆነ በውይይቱ ሂደት ለህዝብ መጋለጡ አይቀርም።

ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ወቅታዊ ችግርን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የፈጠሩት አይደለም። የችግሩ ስሮች ወደ ኋላ የሚወስደን ነው።ይህ ማለት ግን አሁን ላሉት ችግሮች የመፍትሔ አካል አይደሉም ማለት አይደለም።የህወሃት ደጋፊዎችም ሆኑ የጽንፍ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች አሁን ዋና ዒላማቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው። ከዩቱብ እስከ ትዊተር፣ከመንደር ጠጅ ቤቶች እስከ የገጠር ጠላ ቤት ድረስ ሁለቱም ኃይሎች ያሰማሯቸው እና ተከፋዮችን አሰማርተው የኢትዮጵያ ችግር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የሆኑ አስመስሎ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ላይ ተጠምደዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ይልቅ ኃይለስላሴ የበለጡ ኦሮሞ ናቸው የሚል ትርክት ይዘው ብቅ ካሉት ከዶ/ር መራራ ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማራ ጠል ናቸው እስከሚለው ውሸት ድረስ የምዕራባውያን ሚድያዎች ሁሉ ዋና የጥላቻ ዘመቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ የዘመቱ ናቸው። አንዳንዶች ከወሬው ብዛት ሳያውቁት እንዲጠራጠሩ የራሳቸውን የማገናዘብ እና ምክንያታዊ አስተሳሰብ ሲቃረኑ፣ ሌሎች ዐቢይ አማራ ጠል ሆነ ማለት ልጆቹ እና ባለቤቱን ጠላ ማለት እንደሆነ አዙረው ለማሰብ አለመቻላቸውን ለመገንዘብ ሲያቅታቸው መመልከት ያሳዝናል። ኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግል አገር አይደለችም።ሁላችንም እንደሚያገባን እና እንደምንወዳት እርሱም ይወዳታል።ምናልባት የእርሱ የመምራት ዕድሉን አግኝቷል። ኢትዮጵያውያን በወሬ ማዕበል ከመወሰድ ኢትዮጵያን ብሎ የቆመን መሪን በማገዝ ኢትዮጵያን ወደየተሻለ ደረጃ እናድርስ። የዩቱብ አሻሻጮች እየተከትልን የወሬ አዳማቂ መሆን አገር አይጠቅምም።
===============///============

The Ethiopian Orthodox Tewahedo Church is in turmoil in Athens, Greece.

His Holiness Abune Mathias I, Patriarch of the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church, met with Greece's Ambassador to Ethiopia, Antonios Sg...