Tuesday, November 17, 2015

በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በርኀብ የተጎዱትን ወገኖቹን ጉዳይ በቁጭት ሰማ፣ቀጥሎስ (የጉዳያችን ለውይይት የቀረበ ጥያቄ)

በኢትዮጵያ የተከሰተው ርኀብ እንደ ተባበሩት መንግሥታት ዘገባ ከሆነ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ያልታየ ነው።ዓለም አቀፍ የዜና ወኪሎች፣የተባበሩት መንስታት የምግብና እርሻ ድርጅት፣ከርኀቡ ስፍራ በስልክ ቃላቸውን ለኢሣት ራድዮ እና ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛው አገልግሎት የሰጡ የችግሩ ተጠቂዎች ሁሉ ያረጋገጡት የሰው ልጅ መሞት እንደጀመረ ነው።

በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በአንድ በኩል ከገዢው ፓርቲ የሚሰጠው ርኀቡን ተቆጣጥረነዋል የሚለው ዲስኩር እና በሌላ በኩል ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የሚቀርበው የልመና ጥሪ እየሰማ በከፍተኛ ቁጭት ላይ ነው።በአገር ቤት የሚኖረውም በተመሳሳይ ስሜት እና ይብሱን ነገ ይዞ የሚመጣውን ባለማወቅ በስጋት ላይ ይገኛል።ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ስርዓቱ ዛሬም ከፍተኛ ገንዘብ እያወጣ ለቀጣይ የጎጥ ድርጅቶች በመቶ ሚልዮን ብሮች እያወጣ ድግስ እያሳመረ ነው።

በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ችግሩን ከመስማት እና ከመቆጨት ባለፈ ለወገኖቹ የሚደርስበትን አንድ አይነት መንገድ ማመቻቸት አለበት። በተለይ በተበጣጠሰ መልክ በየቦታው የማሰባሰብ ሥራ እንዳይሰራ መጠንቀቅ እና ለአንዳንድ በወገናቸው ስም ለሚነግዱ ስርዓት አልበኞች እንዳይጋለጥ በህብረት አንድ ዓለማቀፋዊ በሆነ መልክ ማስተባበር ተገቢ ነው።ለምሳሌ በሳውዲ፣በየመን፣በሊብያ እና በደቡብ አፍሪካ ወገኖቻችን ላይ ችግር ሲደርስ የአቅሙን ጥረት ያደረገው በአክትቪስት ታማኝ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን የሚስተባበረው ''ግሎባል አልያንስ'' ትልቅ ሥራ መስራት ይችላል።ይህ ተግባር በእራሱ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ለወገኖቹ ከመድረሱ በላይ ህብረቱን የሚያጠነክር አንዱ  አይነተኛ አጋጣሚ ነው።ለወደፊቱም እንደ አገር ለሚገጥሙን  ችግሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ አቅማችንን የምናዳብርበት ሌላው መንገድም ነው። ለኢትዮጵያ ማንም ከየትም አይመጣላትም እኛው ኃላፊነት ያለብን።በአገር ቤት በሕዝብ ንብረት እና ሀብት ላይ የሚቀልደው ስርዓት የተዋጣውን ገንዘብ ወይንም የተገዛውን እህል በትክክል ለወገኖቻችን መድረሱን የማረጋገጥ እና ሂደቱን በዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኩል ማድረግ አሁንም የዓለም አቀፍ እንቅስቃሴው ኃላፊነት ይሆናል።

ምክንያቱም የብዙዎች ስጋት በስልጣን ላይ ያለው ስርዓት በኩል መላክ ያለው አሉታዊ ማለትም ለፖለቲካ ጥቅም ሊጠቀመበት ይቻላል የሚል ነው።ይህ ደግሞ የማይካድ ሀቅ ነው።ሆኖም ግን ኢትዮጵያውያን በአንድነት ግልፅነት ባለው መልክ እርዳታውን ያሰባስቡ እንጂ የሚላክበትን መንገድ በሥርዓት እና በመልኩ እንዲሆን የማድረግ እንዲሁም የማስገደድ አቅም ይኖራል። ገንዘብ ሲያዝ የመደመጥም ሆነ ተፅኖ የመፍጠር አቅሙም በእዛው መጠን ይጨምራል።አሁን ጥያቄው በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በርኀብ የተጎዱትን ወገኖቹን  ከቁጭት ባለፈ እንዴት ይርዳ? የሚለው ነው። ቁጭት፣ሃዘን እና ብስጭት የሰሞኑ ከራሞታችን ሆኗል።ቀጥሎስ? በእዚህን ያህል ደረጃ ኢትዮጵያ ተርባ ዝም እንበል? ይህ ፈፅሞ ሊሆን አይችልም።በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የገንዘብ አቅሙን ማሳየቱ ለወገኖቹ ፈጥኖ ከመድረሱ ባለፈ  አምባገነኑን ስርዓት የመገዳደር አቅሙንም ማሳያ አንዱ መንገድም ነው እና ችላ አይባል።

የኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ''እረኛው'' የተሰኘው ክላሲካል ሙዚቃ 
Ethiopian Music Composer Prof.Ashenafi Kebede classical music



ጉዳያችን Gudayacn

ህዳር 8/2008 ዓም (Nov.18/2015)

Friday, November 13, 2015

ኢህአዴግ/ህወሃት የኢትዮጵያን እርሻ የገደለባቸው ሰባቱ ቀስቶች (የጉዳያችን ልዩ ማስታወሻ)



ኢትዮጵያ ባለፈው ክ/ዘመን ያስተዳደሯት መንግሥታት በኢትዮጵያ እርሻ ላይ መሰረታዊ የመዋቅር ለውጥ ለመምጣት ስራዎችን ሰርተዋል።ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ በዘመናቸው የኢትዮጵያ ገበሬ በፊውዳል ባላባቶች መከራ የማየቱ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ንጉሡ በሰፊው የሰሩት የነበረው የዘመናዊ እርሻ ልማት ሥራ ነበር።በሰቲት ሁመራ፣በአርሲ ዘመናዊ የእርሻ ልማት ሥራ እና የሲዳሞ ዘመናዊ እርሻ ልማት የሚጠቀሱ ናቸው።ከእዚህ በተጨማሪ የአለማያ እርሻ ዩንቨርስቲ በአሜሪካኖች አማካሪነት እንዲከፈት ሲያደርጉ ለኢትዮጵያ እርሻ ትልቅ መዋቅራዊ ለውጥ ያመጣሉ በሚል ሕልም ነበር።

በደርግ ዘመነ መንግስትም ስርዓቱ ገበሬውን በነበረው ርዕዮት ያመረተውን በፈለገበት ገበያ እንዳይሸጥ ቢከለክለውም  የእርሻውን ክፍለ ኢኮኖሚ ግን ለማልማት ጥሯል።ለእዚህም አብነት የሚሆነው ወደመንግስት ንብረትነት የዞሩት ትላልቅ የእርሻ ልማቶች ደካማ አስተዳደራዊ አቅም ቢኖራቸው ምርት ማምረት ግን አላቆሙም።ለምሳሌ የአዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ፣የጣና በለስ ፕሮጀክት እና ከምሥራቅ ጀርመን ጋር በመተባበር የማረሻ ትራክተር እየገጣጠመ ያመርት የነበረው የናዝሬት ትራክተር ማምረቻ ፋብሪካ ተጠቃሽ ናቸው።ከእዚህ በተጨማሪ በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴም ሆነ በደርግ ዘመን የኢትዮጵያ ገበሬ የመሪዎቹ ቅርብ ጉብኝት እና ክትትል አልተለየውም ነበር። ንጉሱም ሆኑ ኮ/ል መንግስቱ በእየገጠሩ የሚደረጉትን ስራዎች እየዞሩ ይጎበኛሉ።ይህ አይነቱ ሥራ በዘመነ ኢህአዴግ/ህወሃት አልታየም።አንድ ወቅት አቶ መለስ ከገበሬዎች ጋር ሲወያዩ የሚያሳይ ፊልም ያውም ከሞቱ በኃላ ደጋግማ ስትታይ መታየቷ ''አንድ ለእናቱ'' የሆነች ብቸኛ ጉብኝት ሆና ቀርታለች።ከእዚህ ይልቅ ኢህአዴግ/ህወሃት በገበሬው እርሻ እያቆራረጠ አዲስ አበባ እንደመግባቱ የኢትዮጵያ እርሻን ችግር በበለጠ የሚረዱ መሪዎች በኖሩት ነበር።እነርሱ ግን አብዝተው ስለ ገበሬው ያወራሉ እንጂ አዲስ አበባን ከረገጡ በኃላ እረስተውታል።ለእዚህም አይነተኛ ምሳሌ የሚሆነን የሰቆጣ እና የዋግ ገበሬ ነው።የአቶ ዋልዋ አገር ዋግ ከአንድ አመት በፊት ያለበትን ችግር እና አቤቱታ አዛውንቱ እያለቀሱ ሲናገሩ ማየት እጅግ የሚያሳዝን ትዕይንት ነበር።

የኢትዮጵያን እርሻ  ኢህአዴግ/ህወሃት የገደለባቸው ሰባቱ ቀስቶች


ቀስት አንድ :- የተፈጥሮ ማዳበርያ የሚጠቀመውን ገበሬ አማልጋሜትድ ካምፓኒን አፍርሰው ጉናን መትከል ሂደት ላይ በነበሩበት ወቅት ከውጭ የመጣ መሬቱ አንዴ ከለመደ የማይለቅ የኬሚካል ማዳበርያ በግድ እንዲለምድ አደረጉት።በእዚህም ሚልዮን ዶላር ዛቁበት።አቶ መለስ  በኖርዌዩ የማዳበርያ ኩባንያ ለመሸለም ሽር ጉድ አሉ።አሁን ኩባንያው ማዳበርያውን ለመሸጥ አላስፈላጊ ሙስና ከአገራት ጋር መግባቱ ይፋ ሆነ።የእራሱ አገር መንግስት ጉዳዩን መመርመር ያዘ።የኢትዮጵያ ገበሬ ግን በግድ ማዳበርያ መሬቱ ላይ እረጭቶ መሬቱ ሌላ እንዳይለምድ ተደርጎ ቀረ።ይህ ብቻ አይደለም የማዳበርያ ዕዳ የኢህአዴግ/ህወሃት ገበሬውን የሚያስፈራራበት ጅራፍ ሆነ።ገበሬው በገዛ አገሩ የመንግስት ጭሰኛ ሆነ።

ቀስት ሁለት :- በአግባቡ ያላጠኑትን እና በቂ የባለሙያ ምክር የሌለበትን የውሃ ማቆር እያሉ ያዙኝ ልቀቁኝ አሉ።አንድ ወቅት ስለ ውሃ ማቆር ማውራት ልማታዊ መሆን ነው ተባለ።ለውሃ ማቆርያ ነው ብለው የፕላስቲክ ፋብሪካዎቻቸውን  ምርት ቸበቸቡ።ከጥቂት አመታት በኃላ የቆረው ውሃ የወባ ማፍሪያ ሆነ።ገበሬው አለቅን አለ።ቀድሞም አልተጠናም እና አሁን ውሃ ማቆር የሚለው ጉዳይ የት እንደደረሰ ሳይነግሩን እና የባከነው ሀብት ምን እንዳስገኘ ሳይታወቅ አረሳሱን።

ቀስት ሶስት  :- ከፍተኛ አምራች የነበሩ በደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ የሚኖሩ በደርግ ዘመን ትግራይን ጨምሮ ከሰሜን ኢትዮጵያ እና ከሐረር ሰፍረው የነበሩ ገበሬዎች ትውልዳችሁ አይደለም እየተባሉ ሲፈናቀሉ አቶ መለስ ፓርላማ ቀርበው ደን መትከል የሚያስተምረውን ገበሬ ደን ጨፈጨፈ ወዘተ እያሉ ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲለያይ ቤንዚን አርከፈከፉ።በከፍተኛ አምራችነታቸው የሚታወቁ ገበሬዎች ከቤንሻንጉል፣ከጉርዳፈርዳ ተፈናቀሉ።በሐረር ደጋማ አካባቢ የሚኖሩ የኦሮምኛ ተናጋሪ ገበሪዎች ከሱማሌ ተናጋሪዎች ጋር በነበሩ ግጭቶች በሱማሌዎች ተገፍተው ስደተኛ ሲሆኑ የሚሰማቸው አልንበረም።ገበሬ በገዛ አገሩ ለማኝ ሆነ።

ቀስት አራት  : - ኢትዮጵያዊ  ኢንቨስተር በእርሻ ሥራ ላይ ገብቶ እንዳይሰራ በየክልሉ አስር አይነት ሕግ አውጥተው የክልሉ ተወላጅ ያልሆነ እንዳይሰራ በውስጥ አሰራራቸው  በተግባር አዋሉት።ከውጭ አገርም ሆነ ከአገር ውስጥ ጥሪታቸውን ሰብስበው ወደ እርሻ የገቡ ኢንቨስተሮች እንዳልሆኑ ሆነው የእርሻ መሳርያቸውን ሳይሰበስቡ ክልሎቹን እየተዉ ወጡ።

ቀስት አምስት  : - ቀድሞ አምራች የነበረው ገበሬ ከእህል ይልቅ በአገሪቱ እንዲስፋፋ ያደረጉት እና የፈቀዱትን ጫት እንዲያመርት ገፋፉት።ጫት በሌሎች አገሮች በአደገኛ እፅነቱ እንደሚመደብ እየታወቀ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ከከተማው አልፎ ገበሬው መሬቱን እየገለበጠ ጫት ሲተክል አበረታቱት።ጫት በቆሎን ተካ፣ጫት ጤፍን ማምረት አስተወ።ቀድሞ የእህል አምራች አካባቢዎች ጫት አምራች ሲሆኑ መንግስት ዝም ብሎ ያያቸው ነበር።አደገኛውን ቅጠል ሻጭ እና አሻሻጭ ከፍተኛ የጦር አዛዦች እና የከፍተኛ ባለስልጣን ሚስቶች ሆኑ።ኢትዮጵያ ጫት የሚቅሙ ገበሬዎች እና ወጣቶች የምንገላወዱባት አገር ሆነች።ቀድሞ የጫት ንግድ ያሳፍር የነበረውን በዘመነ ኢህአዴግ/ህወሃት ጫት ቤቱን ዩንቨርስቲ እና ኮሌጆች ላይ አደረገ።ተማሪዎች በከፍተኛ የጫት ሱስ ወደቁ።

ቀስት ስድስት : - በርካታ የእርሻ ባለሙያ ምሁራን እንዳይሰሩ በካድሬዎች መውጫ መግቢያ አጡ።የእርሻ ምርምር ኢንስቲቱዩት በርካታ በአገር ውስጥ እና በውጭ የሰለጠኑ ምሁራን ቢኖሩበትም የእራሳቸውን የምርምር ፅሁፍ ከመፃፍ እና ትንሽ ሰርተው አገር ጥለው በመሄድ ለሌሎች የአፍሪካ እና አውሮፓ አገራት ሲሳይ ከመሆን ያለፈ ምንም ማድረግ አልቻሉም።የሚገርመው ነገር የእርሻ ምርምር ኢንስቲቱዩት በመጀመርያ በክልል ከተሰነጣጠቁት መስሪያቤቶች ውስጥ አንዱ ነው።መስሪያቤቱ  ከሥራው ባህሪ አንፃር የፌድራል  መስርያቤት ብቻ ነው መሆን ያለበት እንጂ በክልል መደራጀት የለበትም በመላ አገሪቱ ላይ እንደ አየር ንብረት ፀባይ ነው ምርምሮቹ የሚሰሩት በመሆኑም መከፋፈል የለበትም ብለው ኃላፊዎቹ ከአቶ መለስ ጋር ጨምሮ ተከራክረው ነበር።ሆኖም ግን መከፋፈል ስራው የሆነው መንግስት የደቡብ፣አማራ፣ትግራይ፣ወዘተ እያለ ገነጣጠለው።አዲስ አበባ ያለው አስተባባሪ ቢሮ በየክሉሉ ያሉት የእርሻ ምርምር መስርያቤቶችን ማማከር የማይችልበት ደረጃ ደረሰ። ምክንያቱም ክልሎቹ ተጠሪነታቸው ለክልሉ መንግስት ስለሆነ የክልሉ መንግስት ደግሞ በካድሬዎች የተሞላ ስለሆነ በዶክትሬት ደረጃ ያሉት ተመራማሪዎች የጥናት ፅሁፍን በዲፕሎማ ደረጃ ያሉ የክልሉ ተወላጅ በመሆናቸው ብቻ በአለቅነት የተመደቡ ሃሳብ እንዲሰጡበት የተደረገበት ደረጃ ተደርሶ ነበር።የእዚህ ፅሁፍ ፀሐፊ አንድ ወቅት ከአንድ ባለሙያ እንደተረዳው ሐዋሳ ላይ ይሰረ የነበረ ባለሙያው በማስተርስ ደረጃ ቢሆንም የክልሉ ተወላጅ በመሆኑ ብቻ በዲፕሎማ ደረጃ ያለ ምንም አይነት ምርምር አድርጎ የማያውቅ የጥናት ፅሁፎች ላይ ሃሳብ እንዲሰጥ እና ፈርሞ እንዲያሳልፍ ተደርጎ የነበረበትን ሁኔታ ነበር። ይህንን በተመለከተ አዲስ አበባ የሚገኘው የእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ተመሳሳይ ችግር በተለያዩ ክልሎች በማየቱ አቤቱታ አሰምቶ ሰሚ አላገኘም።አንድ ወቅት እንዲያውም የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ  በተደጋጋሚ ያሰሙት ቅሬታን ሰሚ በማጣታቸው ስራቸውን ለቀው ሌላ አፍሪካ አገር ሄደው ተቀጥረዋል።


ቀስት ሰባት : - ገበሬው የነበረውን ማኅበራዊ መስተጋብር አፈረሱት።ገበሬው የእራሱ የሆነ የኖረ ባህል አለው።ከሁሉም በላይ እርስ በርስ መደጋገፍ አንዱ መገለጫው ነው።ኢህአዴግ/ህወሃት ግን አንዱን ታጣቂ፣ሌላውን ፀረ ሕዝብ።አንዱን ሰላም አስከባሪ ሌላውን ፀረ ሰላም እያለ እርስ በርሱ እንዲጠላለፍ አንድ ለአምስት እያደራጀ አንዱ የአንዱ ጆሮ ጠቢ አደረገው።ይህ ማኅበራዊ ሰላምን የሚያናጋ ዘመዳሞች እርስ በርስ እንዲጣሉ አንዱ ባለ ጊዜ ሌላው ጊዜ የጣለው እያደረገ የተገፋው ቀየውን ጥሎ ወደ ሱዳን እና ሌሎች ቦታዎች እንዲሰደድ የቀረውም ተስፋ ቆርጦ እርስ በርሱ የጎሪጥ እየተያየ እንዲኖር ማድረግ ስራው ሆነ።ይህ በከተማ የኢንዱስትሪ ሰላምን እንደሚነሳ ሁሉ በገጠር ትልቅ ቀውስ አስከትሏል።ሌላው ቀርቶ ትርፍ አምራች የተባሉ ገበሬዎችን እሸልማለሁ እያለ ሲመርጥ አንዱ መስፈርቱ ለስርዓቱ ታዛዥ መሆን በውስጥ ታዋቂነት መለያ ሆነ።ለመስኖ አመቺ የሆነ መሬት የሚወስዱት የስርዓቱ ታዛዦች ሆኑ።እውነት መናገር ባህሉ የንበረውን ገበሬ ልቡን አሳዘኑት።የደረሰበትን ዘመን እያማረረ መኖር እጣው ሆነ።

ለማጠቃለል የኢትዮጵያን እርሻ ከነበረበት አሳደግነው ሲሉት የነበረው ሁሉ ሐሰት እንደሆነ ገሃዱ ወጣ።እርሻው አድጎ ቢሆን ኖሮ ከገበሬው አልፎ የከተማው ሰው ምርት እንደልቡ በቀረበለት ነበር።ገበሬውም እንደ ፈለገ በልቶ ባደረ ነበር።የገበሬው ሴት ልጆች ወደ አረብ አገር የሚልኩ ደላሎች እጅ ወድቀው በእየአረብ አገሩ ፍዳቸውን ባላዩ ነበር።እርሻው አድጎ ቢሆን ኖሮ ወጣት የገበሬው ልጆች በእየከተማው ሥራ ፍለጋ ባልተንከራተቱ ነበር።እርሻው አድጎ ቢሆን ኖሮ ኢንዱስትሪው በቂ ግብአት አግኝቶ ባደገ ነበር።እርሻው አድጎ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ዛሬ 15 ሚልዮን ዜጋዋ በአንድ ክረምት ዝናብ ማጣት ብቻ የሚላስ የሚቀመስ ባላጣ ነበር።እርሻው አድጎ ቢሆን ኖሮ አሜሪካ እና ቻይና ለኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ ሰጡ የሚል ዜና እየሰማን አንሳቀቅም ነበር።እርሻውን ገድላችሁታል።የእርሻ ምሁራን እንዳይሰሩ እግር ከወርች አስራችሁ መላወሻ አሳጥታችሁ አሰደዳችሁ።ዛሬ ኢትዮጵያ ተርባም ራበኝ ማለት ፖለቲካ ነው ብላችሁ ለማሳቀቅ በቃችሁ።ለመሆኑ እሩብ ክ/ዘመን (24 አመታት)  የአንድን አገር እርሻ ለማሳደግ ከበቂ በላይ አይደለም? ያውም በእዚህ ቴክኖሎጂ በፍጥነት በሚያድግበት ዘመን።ሃያ አራት ዓመት ውሸት አይሰለችም? አያሳፍርም? ግብርናን መግደል ወጭትን መስበር በወንጀለኝነት አያስቆምም? የኢትዮጵያ እርሻ ላይ 24 ብኩን አመታት በአናቱ ላይ በረው አልፈውበታል።ይልቁን ስለመጪው ዘመን እናውራ።ኢትዮጵያን እንዴት መልሰን እናንሳት? እንነጋገር።በሕይወት እያለን ቤተ መንግስቷንም፣ቤተ እርሻዋን እና ቤተ ኢንዱስትሪውን እንዴት ዘመን ተሻጋሪ ትውልድን አኩሪ አለምን የሚያስደምም እናድርገው? እኛ ከተነሳን እንችላለን።ቁጭት በውስጣችን እና በሌሎች ላይ መፍጠር መቻል አለብን።


ጉዳያችን GUDAYACHN   www.gudayachn.com 

ህዳር 4/2008 ዓም (November 14/2015)

Thursday, November 12, 2015

ኢህአዴግ/ህወሃት የተከሰተውን ድርቅ ጆሮ ተነፍጎታል። የአሜሪካ ኤምባሲ አሜሪካ የላከችው እርዳታ ድሬዳዋ ላይ መራገፉን የሚያሳይ የአንድ ደቂቃ ፊልም ለቀቀ።

የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንም ሆነ ራድዮ  15 ሚልዮን ሕዝብ አደጋ ላይ ስለመሆኑ ምንም ነገር አላወሩም።አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ 97 ሚልዮን ዶላር የሚያወጣ የምግብ ዕርዳታ  አሜሪካ ሰጠች የሚል መግለጫ አውጥቷል።በአዲስ አበባ እና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሊብያ ላይ በአይኤስ ኤስ የታረዱት ኢትዮጵያውያንን ዜና ሊያድበሰብስ የነበረ ኢህአዴግ/ህወሃት በድርቁ ጉዳይ ላይም ተመሳሳይ አካሄድ እያሳየ ስለሆነ በሊብያው ጉዳይ ላይ ሕዝብ ቀድሞ በመውጣት ኢህአዴግ/ህወሃት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ እንዳስገደደ ሁሉ አሁንም ሕዝብ ማስገደድ አለበት የሚሉ በርካታ አስተያየቶች እየተሰሙ ነው።

''ዩኤስ ኤይድ'' ከፊልሙ በታች በለጠፈው ዩቱዩብ ላይ  ''በኢትዮጵያ እራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ለመመገብ በቂ ምግብ ለሌላቸው ...'' የሚሉ ቃላትን ይዟል።

ከእዚህ በታች የሚታየው የአንድ ቂቃ ፊልም አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አሜሪካ 97 ሚልዮን ዶላር የሚያወጣ ምግብ ለኢትዮጵያ መስጠቷን የሚያሳየውን መግለጫ በለጠፈበት ማኅበራዊ ድረ-ገፅ ላይ የተለጠፈ ነው።



Film Source:- USAID Youtube


ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG

Wednesday, November 11, 2015

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! እባክህ ከስልጣን አውርደን? (የጉዳያችን ማስታወሻ)




''መሬት ፖሊሲ መሬት ፖሊሲ እያልን ስንት ዓመት አወራን አንዱም ተግባር ላይ አልዋለም'' አቶ ኃይለማርያም በቅርቡ የተናገሩት። ይህ ማለት እኛ አቅም የለንም ብቃታችን ይህ ነው ስንት ዓመት አልነው አልነው አንዳች ፍሬ የለንም  እናም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ እባክህ በአንድነት ተነስና ከስልጣን አውርደን!!

'' ሙስና ሙስና ትላላችሁ ከእዚህ እንደወጣችሁ ሁላችሁም ወደ ኔት ወርካችሁ ነው የምትሄዱት'' አቶ ሃይለማርያም በቅርቡ የተናገሩት። ይህ ማለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ እባክህ በአንድነት ተነስና ከስልጣን አውርደን!!

''ስምንት ሚልዮን ሕዝብ ተራበ ማለት ምንድነች ይህ ማለት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አንፃር 80 ምናምን ሕዝብ ደህና ነው ማለት ነው'' ዶ/ር ቴዎድሮስ ለቪኦኤ አማርኛው አገልግሎት በቅርቡ የተናገሩት። ይህ ማለት እኛን አይራበን እንጂ ስምንት ሚልዮን ሕዝብ ረሃብ ብዙም ከቁብ አንቆጥረውም ስለሆነም ጥጋባችንን አይተህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! እባክህ በአንድነት ተነስና ከስልጣን አውርደን!! 

''ድርቅ ካሊፎርንያ አሜሪካንም አለ'' ብለው አቶ ሃይለማርያም ሲናገሩ   እበላ ባይ ጭብጨባ ቹአ!! ቹአ!! ቹአ !!! 

''አውስትራሊያም ድርቅ አለ" ሲጨበጨብ ባሰባቸው አቶ ሃይለማርያም ጭብጨባው ቀለጠ።የአሜሪካ ኤምባሲ ሰራተኞች እኛ ድርቅ መታን ስንባል ከንፈር እንደመምጠጥ ያጨበጭባሉ እንዴ? ማለት ጀመሩ። 

አቶ ሃይለማርያም ቀጠሉ '' እኛ ብንራብም አንድም ሕፃን ወደ 'ፊዲንግ ሴንተር' አላስገባንም'' ጭብጨባው ቀለጠ።ተሰብሳቢ ጀግናው መንግስታችን ሕፃናት ተርበው ቢንከላወሱም እናት የልጇን ገላ አቅፋ ብታለቅስም መንግስታችን ግን በፅናቱ እና ከቀደሙት ታጋዮች በወረሰው ውርስ ወደ ''ፊዲንግ ሴንተር'' አላስገባም ሲሉ ተሰብሳቢዎቹ ደጋግመው አጨበጨቡ። አንደምታው ግን እኛ ጥጋባችን ልኩን አጥቷል።ሕፃናት የመመገቢያ ካምፕ ባለማስገባት በመናገር እና ቢቢሲ በቀን 2 ሕፃናት እየሞቱ ያለበት መንደር ወሎ ውስጥ አገኘሁ ብሎ አለምን ማሳዘኑን ጆሮ ዳባ ልበስ በማለታችን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ እባክህ በአንድነት ተነስና ከስልጣን አውርደን!!

''ለስድስት ባለስልጣናት ለእያንዳንዳቸው ከአንድ ሚልዮን ዶላር በሚበልጥ ወጪ ወይንም በ25 ሚልዮን ዶላር ቤቶች ሰርተን እያተናቀቅን ነው። ቤቶቹ ሲያልቁ የባለስልጣናቱ የግል ገንዘብ ነው የሚሆነው።ይህ ለመጀመርያ ነው እንጂ ሌሎች ባለስልጣናትም እደላው ይቀጥላል'' ሸገር የግንባታ ባለስልጣን መሰል የሚል ስም ያላቸውን ባለስልጣን ጠይቆ ያሰራጨው ዜና። ትርጉሙ ኢትዮጵያ ብትራብም፣ለአባይ ቦንድ ከጉልት ቸርቻሪ እና ከድሀ ገበሬ እያስለቀስን ብንሰበስብም፣ እኛ ግን በ25 ሚልዮን ብር ቤት እየሰራን ኦባማ የማይኖሩበት ቤት ውስጥ ለመኖር አቅደናል።ለመሆኑ  25 ሚልዮን ብር ማለት ምን ማለት ነው?

25 ሚልዮን በ6ቱ ባለስልጣናት አባዙት 150 ሚልዮን ማለት ነው። እናም ይህ ብር ማለት ለ100 ሺህ መምህራንበነፍስ ወከፍ  የ1500 ብር የደሞዝ ጭማሪ ለእያንዳንዳቸው ይደርሳቸው ነበር ማለት ነው።
150 ሚልዮን ብር ማለት አዲስ አበባ ከ300 በላይ  ዘመናዊ አውቶብሶችን በአንድ ጊዜ ልታገኝ ትችል ነበር።
150 ሚልዮን ብር ማለት 15ሺህ የጎዳና ተዳዳሪዎች በዓመት 10ሺ ብር ለእያንዳንዳቸው በጀት ተይዞ በአንድ ሙያ ማሰልጠንና ከጎዳና ሕይወት ማውጣት ይቻል ነበር ማለት ነው።

በመሆኑም ጥጋባችን ልክ እንደሌለው አየህ? እናም  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! እባክህ በአንድነት ተነሳ እና ከስልጣን አውርደን!

ለበአዴን በዓል ብለን 300 ሚልዮን ብር ለድግስ እያጠፋን ነው እና  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! እባክህ በአንድነት ተነሳ እና ከስልጣን አውርደን?!

ምን ይሄ ብቻ ለህወሃት በዓል ማክበርያ የሱዳንና የሌሎች አካባቢ አገራት መሪዎች በአይሮፕላን የማንሸራሸር ወጪ ጨምሮ ከእዚች ድሃ አገር ላይ ብዙ መቶ ሚልዮን ብር አውጥተን አክብረናልና  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! እባክህ በአንድነት ተነሳ እና ከስልጣን አውርደን!

እንግዲህ ነገርንህ።ምን አይነት የነቀዘ ሥራ እንደምንሰራ! እኔ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የጠቀመጥኩት ሃይለማርያም ከእራሴ ጀምሮ ለምንም የምንረባ አደለንም ብዬ ነገርኩህ ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! እባክህ በአንድነት ተነሳ እና ከስልጣን አውርደን! የጦር ሠራዊቱም ዝም አትበለን ተነስና አውርደን! እኛ ከተሰቀልንበት ለመውረድ ፈራን! አውርደን! አውርዱን! ጨክናችሁ ዝም አትበሉን። ሳናውቀው እላይ ተሰቅለን ቁልቁል ስናየው የመሬቱ እርቀት አስፈራን።የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ እባክህ በአንድነት ተነስና ቀስ ብለህ አውርደን!?


ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ህዳር 1/2008 ዓም (Nov.11/2015)
www.gudayachn.com 

Monday, November 9, 2015

''7-ኪሎ'' የተሰኘች በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ እና ባህላዊ ጉዳዮች ላይ የምታተኩር አዲስ አለም አቀፍ መፅሄት ተመረቀች

የ7-ኪሎ የመጀመርያ እትም የፍት ሽፋን  (ከ7-ኪሎ ማኅበራዊ ድረ-ገፅ የተወሰደ)

''7-ኪሎ'' የተሰኘች በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ እና ባህላዊ ጉዳዮች ላይ የምታተኩር  አዲስ አለም አቀፍ መፅሄት ትናንት ጥቅምት 28/2008 ዓም በአሜሪካ፣ሲልቨር ስፕሪንግ ተመርቃለች።የመፅሄቱ ይዘት የቀድሞ አዲስ ነገር ጋዜጣ  አዘጋጆች እና ሌሎች ምሁራን የሚሳተፉባቸው ትንተናዊ ፅሁፎች የያዘ ሆኖ ለንባብ እንደሚበቃ ተገልጧል ።አዲስ ነገር ጋዜጣ ሕትመቷ እስከ ቆመበት ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ በተለይ በከተማ ነዋሪው ዘንድ የጋዜጣ አቀራረብ፣አፃፃፍ እና በፖለቲካዊ፣ማህበራዊ ጉዳይዮች ላይ ትልቅ፣ግልፅ እና አሳማኝ ትንተናዎችን በመስጠቷ ትልቅ ዝናን አትርፋ እንደነበር ይታወቃል።

በእዚህም ሳቢያ የማንበብ ባህል እየቆረቆዘባት ለመጣው ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋን የፈነጠቀ የአጭር ጊዜ መልካም ብልጭታ ሆኖ አልፏል።ይህ ሁኔታ በተለይ አዲሱ ትውልድ የአዲስ ነገር ጋዜጣ በእለተ ቅዳሜ መውጣት ዕለቱን በእጅጉ እንዲናፈቅ አድርጎት  ነበር።የኢህአዴግ/ህወሃት ጨካኝ የአፈና ስርዓት የኢትዮጵያን አንድ ሙሉ ትውልድ ለስደት እንደዳረገ የታወቀ ነው።ከፓይለት እስከ ገበሬ፣ከሕክምና ዶክተር እስከ ጋዜጠኛ ለስደት ተዳረገ።የአዲስ ነገር ጋዜጠኞችም ''አዲስ ነገርንም አዲስ ዘመንንም አላነብም'' ብለው በአንድ ወቅት በተመፃደቁት አቶ መለስ ዜናዊ የስልጣን ዘመን አረመኔያዊ ''የሽብርተኝነት'' ወንጀል እየተለጠፈባቸው ተሰደዱ።ሆኖም ግን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሥራ እና በትምህርት የሚገኙት የአዲስ ነገር አዘጋጆች ስራዎቻቸውን እየያዙ ብቅ እያሉ ነው።

በአሁኑ ወቅት የአዲስ ነገር ጋዜጣ መንፈሶችን በሁለት ሚድያዎች ሲንፀባረቁ ማየት ይቻላል።የመጀመርያው ቀደም ብሎ በተመሰረተው ዋዜማ ቦድካስት የራድዮ ዘገባዎች ሲሆን  ሁለተኛው በ7-ኪሎ የድረ-ገፅ እና የሕትመት መፅሄት ይሆናል ማለት ነው። 

በጉዳያችን ድረ-ገፅ ከአመት በፊት ስለ ዋዜማ ቦድካስት ራድዮ መጀመር አጭር ዘገባ ቀርቦ ነበር (http://www.gudayachn.com/2014/06/blog-post.html)። ዛሬ ደግሞ ስለ 7-ኪሎ የድረ-ገፅ እና የሕትመት መፅሄት ከ7-ኪሎ ማኅበራዊ ድረ-ገፅ ላይ የተገኘው ፅሁፍ ይበልጥ ገላጭ በመሆኑ ከእዚህ በታች እንዳለ እንደሚከተለው ቀርቧል።የአዲስ ነገር ቤተሰቦች በርቱልን!
=============/////================////===========///==

ከእዚህ በታች ያለው ፅሁፍ  በመጋቢት ወር ላይ በ7-ኪሎ ማኅበራዊ ድረ-ገፅ (https://www.facebook.com/7kilo/) ላይ ወጥቶ የነበረ ነው።

ሰባት ኪሎ ምንድነው? 

ሰባት ኪሎ ሚዲያ የኢትዮጵያን ፖለቲካ፥ ኢኮኖሚ፥ እና ባህል በጥልቅ የሚዳስስ እና የሚመረምር ተቋም ነው። በተቋሙ የተሰናዱት ሞያዊ ጽሑፎች በመጽሔት፥ በድረገጽ፥ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ኔትወርኮች ይሰራጫሉ። የሞያዊ ጽሑፎቹ ይዘት ሽንጠ-ሰፊ ዘገባን እና የትንተና ጋዜጠኝነት ከሽኖ የሚቀላቅል ይኾናል።

ሽንጠ- ሰፊ ዘገባ ምንድነው?

መጽሔታችን (ኦንላይንም ኾነ የኅትመት) በጥልቅ እና በጥዑም ሽንጠ-ሰፊ ፊቸሮች እና ጽሑፎች የታጨቀ በመኾኑ ለቅዳሜ እና እሁድ ግሩም መዝናኛ እና መማሪያ፥ ለቀሪዎቹ የሥራ ቀናትም የቡና እና የሻይ ሰዓት ማረፊያ የተመቹ ናቸው። በአንባቢዎች ዘንድ በሚገባ የተጠኑ እና የተተነተኑ ፥ ሰፋ ያለ የማሰላሰያ ጊዜ የሚሹ ዘገባዎች እና የቃለምልልስ ፊቸሮች ጽኑ ረሃብ አለ ብለን እናምናለን።

የትንተና ጋዜጠኝነት ምንድነው?

መልካም ጋዜጠኝነት ኹሉ የሰላ እና በሚገባ የተብራራ ነው። ጋዜጠኞች ብዙውን ጊዜ ( ይኾነኝ ብለውም ኾነ በደመነፍስ) ለሚዘግቡት ታሪክ ምክንያተ-ጽሕፈት ያሰፍራሉ፤ ሞዴል ይሾማሉ፤ የትንቢታቸውን አንደምታ እና የትንተናቸውን ውጤት ይዘረዝራሉ። ዓላማችን መልካም ጋዜጠኝነት የመጽሔታችን ብሉይ ገዢ መርኾ ማድረግ ነው። ብሔራዊ ዜናዎቻችንን እና ጉዳዮቻችንን ተረድቶ ለማስረዳት ዳታዎችን እና ማኅበራዊ ሳይንስ ያጎለበታቸው ሜቶዶሎጂዎችን እና ሐለዮቶችን በሚገባ እንጠቀማለን። ሥራዎቻችንንም ለአንባቢዎቻችን በተዋበ ቋንቋ እና በሚያስደስት ዘዬ እናቀርባለን።

ከዚህ በላይ ያላችሁትን እንዴት ታሳኩታላችሁ?

ሥራችንን የምንጀምረው በዐሥር ጸሐፊዎች ( ሁለት ኢኮኖሚስት፥ ሦስት ፖለቲካል ሳይንቲስት፥ አንድ ሶስዮሎጂስት፥ የፍልስፍና የዶክትሬት ተማሪ፥ ሁለት የሕግ ምሁራን፥ አንድ ጋዜጠኛ) ነው። ጸሐፊዎቻችን እና ብሎገሮቻችን አስልቶ ለማሰብ በማኅበራዊ ሳይንስ ሜቶዶሎጂዎች በሚገባ የሠለጠኑ ከመኾናቸው ባሻገር መጽሔታችን ኤክስፐርቶች ጽሑፎቻቸውን እና ምልከታዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ስለሚጋብዝ ከዚህ በላይ ያልነውን እናሳካዋለን።

ሰባት ኪሎ መቼ ወደቡን ይለቃል?

በበራፍ ነን። የሰባት ኪሎ መርከብ በዚህ ሳምንት የፕሮጄክቱን ጉዞ ቀዳሚ ምዕራፍ በይፋ ያበስራል። የሰባት ኪሎ መጽሔት ማኅበራዊ ሚዲያ ክንፍ የሽንጠ-ሰፊ ዘገባዎቹን አጫጭር ጨመቆች ፥ የትዊተር መጣጥፎች፥ እና አጫጭር የፌስ ቡክ ጡመራዎችን በመልቀቅ ይጀመራል። በቀጣይም የሰባት ኪሎ ድረገጽ ይከተላል።የፕሮጀክቱ መደምደሚያ የኾነው የኅትመት መጽሔት በሰኔ ወር ይሰራጫል።

እንዴት ልሳተፍ?

እባካችሁ የሰባት ኪሎን የፌስ ቡክ እና የትዊተር ገጾችን ላይክ አድርጉ፥ተከታተሉ። በፕሮጀክታችን እና በመጣጥፎቻቸን ላይ የሚኖራችሁን ስል እና በሳል አስተያየት በናፍቆት እንጠብቃለን። በየዕለቱ ቀስ በቀስ የምንለቃቸውን አጫጭር ጨመቆች ተከታተሉ።



ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ቅጥምት 29/2008 ዓም (Nov.09/2015)

Thursday, November 5, 2015

መንግስት ''ለውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያቱ እድገቱ ነው'' በሚል አዲስ የማምለጫ ምክንያት እየደረደረ ነው። እውን እድገት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያመጣል?

ዶ/ር አብርሃም ተከስተ 


  • ''ወደ አስር አመት ለሚጠጋ አመታት በውጭ ምንዛሪ እጥረት ስንሰቃይ ነበር'' የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ ዶ/ር  አብርሃም ተከስተ የተናገሩትን ዛሬ የኬንያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እንደዘገበው።

  • ''በዕድገታችን ሳቢያ የውጭ ምንዛሪ ክምችታችን አስተማማኝ ነው'' ቀድሞ አቶ መለስ በመቀጠል አቶ ሃይለማርያም ለምክር ቤት አባላት ባለፉት 10 አመታት ሲነግሩን የነበረው። 
መንግስት ''ለውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያቱ እድገቱ  ነው'' በሚል አዲስ የማምለጫ ምክንያት እየደረደረ ነው።የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ ''የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ምክንያት እድገታችን ነው'' ብለዋል።ቀጥለው ''ችግሩ (የውጭ ምንዛሪ ችግር) በርካታ የመንግስት እና የግል ፕሮጀክቶች ከመኖራቸው ጋር ይያያዛል'' አሉ ይለናል  የኬንያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዛሬ የለቀቀው ዜና።

ጉዳዩ ከእውነታው ጋር ይቃረናል።የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ ለውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያቱ የመንግሥታችን የተሳሳተ ፖሊሲ እና አሳታፊ አለመሆኑ ነው ከማለት ይልቅ በድፍኑ ''እድገቱ''ነው ካሉ በኃላ በማስከተል የፕሮጀክቶች መብዛት ነው ብለዋል።እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን ቀላቅለዋል።እድገትን እንደ አንድ ተጠያቂ ማድረግ እና የፕሮጀክቶች መለጠጥን ምክንያት ማድረግ የተለያየ ነው።ፕሮጀክቶች ስለተደረደሩ እና ሥራ ስለጀመሩ ብቻ እድገት አለ ማለት አይደለም።ፕሮጀክቶቹ አዋጪነት፣ለአገር የሚያመጡት ስልታዊ ጥቅም እና የእርሻውንም ሆነ የኢንዱስትሪውን ክፍል የማንቀሳቀስ አቅማቸው ሁሉ መፈተሽ አለበት።አቶ አብርሃም ግን በድፍኑ እድገቱ ነው በሚል ሊያልፉት ሞከሩ።

ለውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ምክንያት የፕሮጀክቶች መብዛት ብቻ ሊሆን አይችልም።እርግጥ ነው የፕሮጀክቶች መብዛት የውጭ ምንዛሪ ጥያቄን ያንረዋል።ሆኖም ግን  የፕሮጀክት መብዛት ነው ብለን ብንነሳ ይህ በእራሱ የስርዓቱን ስህተት የሚያሳይ ነው።ምክንያቱም የአለም ባንክን ጨምሮ ፕሮጀክቶች በአገሪቱ አቅም እና ቅድምያ የሚሰጣቸው አንገብጋቢ ፕሮጀክቶች ላይ ብቻ መሆን አለበት እንጂ ለምርጫ ፕሮፓጋንዳ ተብሎ ''አስር ወጥ አትጣዱ አንዱንም ሳታማስሉት እንዳያር'' የሚል መሰል ምክር ሲሰጥ ነበር።ይህንኑ የተሳሳተ ተግባር በውጭ የሚኖሩ ምሁራንም በተለያየ ጊዜ ደግመውታል።በመሆኑም የፕሮጀክት መብዛት ነው ቢባልም አሁንም ስህተቱ ወደ እራሱ የስርዓቱ የተሳሳተ ፖሊሲን አመላካች መሆኑ  አይቀርም።

ለውጭ ምንዛሪ እጥረቱ የዓለም አቀፉ ኦርቢት ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ሲሳይ አሁንም ለኬንያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሰጡት መልስ ግን እውነቱም አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል።''የአገሪቱ ወደ ውጭ ሸቀጦችን የመላክ አቅም (ኤክስፖርት ሴክተር) ደካማ መሆን ነው ለውጭ ምንዛሪ እጥረት ዋናው ምክንያት'' ነበር ያሉት አቶ አለማየሁ።

የአቶ አለማየሁ ምክንያት እንዳለ ሆኖ ሌሎች የተረሱ ግን ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያቶች አሉ። ከአገሪቱ በሕገ ወጥ መንገድ በሙስና በተዘፈቁ ባለስልጣናት እና አቀባባይ ነጋዴዎችየሚሸሸው ገንዘብ ጉዳይ ምነው ተረሳ? ከአራት አመታት በፊት ከኢትዮጵያ 'ግሎባል ፋይናንስ ኢንተግሪቲ'' የተሰኘው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም ባወጣው ዘገባ ከኢትዮጵያ በአስር ዓመታት ውስጥ ብቻ በሕገ ወጥ መንገድ 16.5 ቢልዮን ዶላር ከአገር መውጣቱን መገለፁ ይታወቃል።

ከእዚህ በተጨማሪ ስርዓቱ ስልጣኑን ለመጠበቅ የሚያወጣው ወጪ ለምሳሌ የተቃዋሚዎችን የመረጃ መረብ ለመስበር በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር ለአንድ የጣልያን ኩባንያ መከፈሉን ከሰማን ገና ወራት ማስቆጠራችን ይታወሳል።ከእዚህ በተጨማሪ ለጎጥ ድርጅቶች አመታዊ በዓል እየተባለ የሚደገሰው ድግስ በሚልዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ የሚያወጣ ውስኪ እና ሌሎች የቅንጦት እቃዎች ግዥዎች መፈፀማቸውን አንርሳ።ከእዚህ በፊት ለህወሃት፣ለኦሕደድ ሰሞኑን ደግሞ ለብአዴን ተብሎ የወጣው ገንዘብ በእራሱ ስንት ሆስፒታሎችን፣ለስንት ዜጎቻችንን የስራ ዕድል በፈጠረ እና ይልቁንስ በአሁኑ ጊዜ በረሃብ የሚሰቃዩትን ስንት ወገኖቻችንን በታደገ ነበር።

ስለሆነም ለውጭ ምንዛሪው እጥረት ዋነኛ ምክንያቱ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ እንደሚሉት አይደለም።የዶ/ር አብርሀምን ንግግር ነገ አቶ ሃይለማርያም ሲደግሙት ለመስማት ተዘጋጅተናል።እውነታውን ግን ከመናገር እና ለኢትዮጵያ ህዝብም ከመግለፅ ወደኃላ ማለት የለብንም።ምክንያት ያለፈ ስህተትን አይሸፍንምና። 

የአቶ አብርሃም ተከስተን ገለጣ ኬንያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ድረ-ገፅ ላይ ለማንበብ ይህንን በመጫን ይመልከቱ።

ጉዳያችን GUDAYACHN
ጥቅምት 25/2008 ዓም (November 5/2015)
www.gudayachn.com


Monday, November 2, 2015

የአቶ ኃይለማርያም ንግግር ከኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም የመጨረሻ ቀናት ንግግሮች ጋር ይመሳሰላሉ። እግዚአብሔር ወደ ህወሃት የላካቸው ''ነቢያት'' (የጉዳያችን ማስታወሻ)




የአቶ ኃይለማርያም ንግግር ከ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም የመጨረሻ ቀናት ንግግሮች ጋር ይመሳሰላሉ

እንግዲህ ወደ መጨረሻው መጀመርያ ላይ ሲደረስ ንግግሮች እንዲህ ናቸው።አቶ ኃይለ ማርያም ደከማቸው፣ሰለቻቸው እናም በንግግራቸው መንግስታቸው ከእዚህ በላይ ህዝብን የማታለል አቅም እንደሌለው በአደባባይ አመኑ።ማመን ጥሩ ነው። ይህንን ያመኑት ዋልታ ባሰራጨው ስለመልካም አስተዳደር ዝቅጠት በቀረበ የጥናት ፅሁፍ ላይ ነው።በንግግራቸው ወቅት የህወሃት  ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሁሉ ነበሩ።
ከንግግራቸው ውስጥም ''ከእዚህ ስትወጡ'' አሉ እነ በረከት፣ ዶ/ር ደብረፅዮን እና አቶ አባይ ቁጭ ባሉበት ወደ እነርሱ እንዳፈጠጡ ''ለእኔ ሁለተኛ እዚህ አገር ላይ ፈተና የሚሆነው  እዚህ እናወራለን እንጂ ከወጣን በኃላ የተለያየ የእራሳችን ኔት ወርክ እንዳይነካብን እንከላከላለን'' አሉ።

ቀጠሉናም  ''ስንት ጊዜ ስለመልካም አስተዳደር እናውራለን?'' ''ሁላችንስ እስከመቼ ነው የምናወራው?''
የሚል አከሉበት። 
 ንግግራቸውን ዋና ማዕከል ለማግኘት ስትሞክሩ የምታገኙባቸው ነጥብ ግን   የዕለቱን እሳት የማጥፋት አላማ ብቻ ያዘለ መሆኑን ነው።አቶ ኃይለማርያም መንግስታቸው ምን ያህል በሕዝብ እንደተጠላ ስላወቁ ትንሽ እረፍት ብጤ ነስቷቸዋል።በመሆኑም የሆነ ሕዝቡን የምያረግብ እንደ እሳቸው ቀጥታ ቃል አጠቃቀም ''ሕዝቡን ተስፋ የሚሰጥ'' ነገር ቶሎ እንስራ እያሉ ሲማፀኑ ይሰማሉ። ተስፋ ለመስጠት እንጂ ለመፍትሄ አለመሆኑን አስምሩበት።ያሰቡት ቶሎ ተስፋ መስጠት መሆኑን ሲናገሩ ቃል በቃል እንዲህ ነው ያሉት  ''አሁን ቶሎ ሕዝቡን ተስፋ የሚያስጭር ንቅናቄ እና በዘመቻ መልክ መንቀሳቀስ አለብን'' በሚል ነበር።
በመጀመርያ ደረጃ አቶ ኃይለማርያም በእዚህ ንግግራቸው ህወሃት ባለስልጣናት ጋር ይጋጩ ይሆናል እንጂ ለውጥ አያመጡም።በሌላ በኩል ህወሃቶች '' ተወው ይለፍልፍ ምን ያመጣል'' በሚል ንቀው ዝም ካሏቸው ላይጋጩ ይችላሉ።
አቶ ሃይለማርያም እያወቁ እንዳላወቁ ሆነው ያሉበት ጉዳይ  የአገሪቱ ችግር የጥናት እና የእቅድ ጋጋታ እንዲሁም ችግሩ አለ ብሎ የሚደረግ ዲስኩር  ችግር ሳይሆን በመዋቅር የተደረጀ እና በጎጥ የተጠራራ የሙስና ቡድን ነው።አቶ ኃይለማርያም ይህ ቡድን ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ እራሳቸውን ወደ ሲስተም (system) መቀየራቸውን ባይረሱ ጥሩ ነው።ሲስተም ደግሞ የሚስተካከለው ሙሉ በሙሉ ሽባ ሲሆን ነው እንጂ እንደርስዎ አባባል ''እስከ ዓመቱ አጋማሽ ላይ የሆነ ሕዝቡን ተስፋ የሚሰጥ እና ከእኛ ጋር የሚያቆም ሥራ እንስራ'' ብሎ በማወራት አይደለም። ለነገሩ ቢቸግርዎ ነው። ኮሎኔል መንግስቱ መጨረሻ ሰዓት ላይም የእርስዎ አይነት ንግግር አድርገው ነበር።ኮ/ል መንግስቱ እንዲህ ብለው ነበር ''ወደዳችሁም ጠላችሁም ይህ ሕዝብ ያውቀናል።የምትበሉትን የምትጠጡትን ያውቃል'' ብለው ነበር። ሕዝብ ግን ይህንን የሚያውቀው ከአስራ ሰባት ዓመት በፊት ነበር። ዛሬም አቶ ኃይለማርያም ሕዝብ ለ24 ዓመት የተሸከመውን መከራ ደግመው ይነግሩታል።መፍትሄ ያሉት ደግሞ ለጊዜው ህዝብን በተስፋ የሚያቆይ ''ፓናዶል'' እንጂ የዘለቄታውን መፍትሄ ግን አልደፈሩትም።

እግዚአብሔር ወደ ህወሃት የላካቸው ''ነቢያት''

ለኢህአዴግ/ህወሃት  ግን እግዚአብሔር ስንት ''ነቢያት'' እየላከ ነገራት? 
በመጀመርያ ጋዜጠኞችን ልኮ ነገራት አልሰማ አለች። 
ቅንጅትን ልኮ በክርክሩ ችግሩን ነገራት አልሰማ አለችው።
ቀጥሎ ፈረንጅ ብትሰማ ብሎ አናጎሜዝን ከአውሮፓ ድረስ ላከ አልሰማ አለችው።
ቀጥሎ በእየቀኑ ልንገራት ይሆን? ብሎ ኢሳት ራድዮ እና ቴሌቭዥንን በእየቀኑ ጧት እና ማታ ላከ ።ህወሃት አሁንም አልሰማ አለች።
በመቀጠል 9 ሰዎችን መረጠና  ዞን 9 ብለው ''እባክሽ ሌላውን ነገር ሁሉ ተይውና ያወጣሽውን ህገ መንግስት ብቻ አክብሪ'' እያሉ እንዲመክሩ አደረገ። ሕወሓት 9ኙንም ጠራርጋ አሰረች እና 40 ሚልዮን ብር አውጥታ በዓል መደገስ ጀመረች፣ደነሰች፣አርቲስቶችን ይዛ መንሸራሸር ጀመረች።
እግዚአብሔር እስኪ ህወሃት በምድር ላይ የምትፈራውን ሰው ልላከው አለና  ኦባማን  ከዋይት ሃውስ አስነስቶ ላከ እና አፍሪካ ህብረት አዳራሽ ላይ ጮክ ብለው ''አምባገነን መሪዎች ሆይ! ውዮላችሁ!'' እያሉ እንዲናገሩ በንግግራቸውም መካከል ወደ አቶ ኃይለማርያም እንዲመልከቱ፣ንግግራቸውን እንደጨረሱ ግን ወደ አየር ማረፍያ እንዲሄዱ እና የጫማቸውን አቧራ አራግፈው ምድሪቱን ለቀው እንዲሄዱ አዘዘ። ህወሃት ግን አልሰማችም ይልቁንም ኦባማ የመጡት ጥሩ በመስራታችን ነው እያለች ተኩራራች።

በመጨረሻም እግዚአብሔር አለ ይህንን ሁሉ ህወሃት ስላልሰማች አለና   በመሪነት ያስቀመጡት እንዲናገር አንደበቱን እየቆለመምኩ የመጨረሻውን  መጀመርያ ላድርግ ብሎ አቶ ኃይለማርያም በአልጀዚራ እና በኢቲቪ የካዱትን እውነት እንዲናገሩ አደረገ።እናም አቶ ኃይለማርያም ከየት እንዳመጡት ባልታወቀ መንገድ ሙሉ በሙሉ ቀና ብለው የማያዩአቸውን አቶ አባይ እና ሌሎችንም እየገላመጡ ተናገሩ።
ነገሩ አብቅቷል።''ሁልሽም እዚህ ታወርያለሽ እንጂ ስትወጪ ኔት ወርክሽን ልትከላከይ ነው የምትሮጭው በጎሳ ነው የምታስቢው'' አሉ። አቶ ኃይለማርያምን ግን የሰማቸው  አልነበረም።ይልቁንም ህወሃቶች  ሲወጡ ሰብሰብ ብለው ቁሙ እና ''ይሄ ሰውዬ (አቶ ኃይለማርያምን) ጠግቧል ባለፈው ግምገማ ላይ አንድ ነገር ማድረግ ነበረብን ዘፈነብን እኮ''  እያሉ እየዛቱ ወጡ።

በመጨረሻ እግዚአብሔር ይህንን ሁሉ ልኬ ያልሰማች ህወሃት ''ነጋሪት ቢጎሰምባትም አትሰማም'' አለና አጠገቡ ወዳለው መልአክ ዘወር ብሎ እንዲህ አለው ''በል ወደ መሬት ውረድ ወደ የምወዳት ምድር ኢትዮጵያም ምድር ግባ በምድሪቱም ላይ  ተመላለስ።  ዝም ያለውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ልብ ለአገሩ ቆርጦ እንዲነሳ የአገር ፍቅር ፍም በእያንዳንዱ ሰው ላይ አንድድ'' አለው መልአኩም ለእግዚአብሄር  ሰገደ እና ፈጥኖ ወደ ኢትዮጵያ ምድር ወረደ።


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
ጥቅምት 22/2008 ዓም  (November 2/2015)

The Ethiopian Orthodox Tewahedo Church is in turmoil in Athens, Greece.

His Holiness Abune Mathias I, Patriarch of the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church, met with Greece's Ambassador to Ethiopia, Antonios Sg...