Thursday, March 5, 2015

የቴሌቭዥን ድራማዎችን በስድስተኛውም የስሜት ህዋሳችንም መቃኘቱን አንርሳ።የትኞቹ ያስተምራሉ? የትኞቹ መታረም ይፈልጋሉ? ''ቤቶች'' እና ''ሞጋቾች'' ድራማ (የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ)


''ሞጋቾች'' የተሰኘው የ  ኢቢኤስ ተከታታይ ድራማ ተዋናዮች (ፎቶ ከኢትዮ ሲኒማ ድረ-ገፅ)

በቴሌቭዥን የሚተላለፉ መርሐ ግብሮች አነሰም በዛም በሕዝብ ላይ የሚፈጥሩት የእረጅም ጊዜ ተፅኖ ቀላል አይደለም።በተለይ በታዳጊ ወጣቶች እና ልጆች ላይ ለነገ እነርሱነታቸው የሚጭረው ስሜትም ሆነ አለማቸውን እና አካባቢያቸውን የሚመለከቱበት ዕይታ የጠበበ አልያም የሰፋ ወይንም የተንሸዋረረ የመሆን እድሉ ትልቅ ነው።እዚህ ላይ ወላጆች ለልጆቻቸው ከቴሌቭዥን መርሃ ግብር በኃላ የሚሰጡት የማስተካከያ ሃሳብ ወይንም ልጆችም ሆኑ ወጣቶች ጉዳዩን የሚያዩበትን እይታ ቀላል አይደለም።

የኢትዮጵያ ተለቭዥንን በሀገር ውስጥ የመረጃ ምንጭነት ተአማኒነቱ የወረደበትን ደረጃ ለመግለፅ ህዝቡ ''የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እውነት የምናገረው ሰዓት ብቻ ነው'' የሚለውን አባባል መግለፁ ብቻ በቂ ነው።ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ በመገናኛ ብዙሃንነት የቆየ የቴሌቭዥን ጣብያ በእዚህ አይነት ደረጃ የወረደ የመረጃ ምንጭ መሆኑ እንደ ኢትዮጵያዊነት በጣም ያሳዝና።ዛሬ ቢልልን ኖሮ ኢቲቪ በመላው ዓለም ባሉ ከተሞች ወኪሎች በኖሩት እና በቀጥታ የሚዘግቡ ዘጋቢዎች በኖሩት ነበር። ይህ ደግሞ ከወጭም አንፃር ብዙ አለነበረም።ምክንያቱም በመላው ዓለም እንደመበተናችን በነፃ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ማግኘት ከባድ አይደለም።ነገር ግን አለመታደል ሆኖ አምባገንነት፣ጎሰኝነት እና ሙስና መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደጠረነፈ ሁሉ የኢትዮጵያ ቴሌቭዝንም አንዱ ሰለባ ነው።ኢትዮጵያውያን ግን በሀገር ቤት የታፈነ ድምፃቸውን በቸልታ አላዩትም።በጥቂቶች አስተባባሪነት የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን በመላው ዓለም እና በሀገር ቤት ላሉ ወገኖቻችን ብቸኛው ነፃ የመገናኛ ብዙሃን ለመሆን በቅቷል።

የእዚህ አጭር ማስታወሻ አላማ ስለ ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ታሪክ ለማውራት አይደለም።ስለሚያቀርባቸው ሳምንታዊ ድራማዎች ግን ትንሽ ማለት ፈለኩ።የቴሌቭዥን ድራማዎቹን ምግብ እየበላሁም ሆነ መንገድ ላይ ባለኝ ክፍት ጊዜ እመለከታቸዋለሁ።ይህንን የማደርገው መዝናኛ ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን አሁን ያለውን የሀገር ቤትን ማኅበራዊ፣ስነ-ልቦናዊ፣ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሁኔታ ስለሚያንፀባርቁልኝ ነው።የድራማዎቹን የመሃል እንቡጥ መልእክት ፈልፍላችሁ ለማግኘት ስትሞክሩ (በስድስተኛው የስሜት ህዋስ ማለቴ ነው) ብዙ ጠቃሚ እና ጎጂ ጎኖቹን ለማየት አያስቸግራችሁም።

በስድስተኛው የስሜት ህዋስ የሶስቱ ድራማዎች እይታ 

እዚህ ላይ በቴሌቭዥን ከሚቀርቡት ድራማዎች ውስጥ የሁለቱ ማለትም ''ቤቶች'' እና ''ሞጋቾች'' ላይ የማነሰው የጠለቀ ሂስ አለመሆኑን እና ያንን ለማድረግ የሙያው ክህሎት እንደሌለኝ ለመግለፅ እፈልጋለሁ።ነገር ግን ድራማዎቹ  በህብረተሰባችን ላይ ያላቸው አሉታዊ እና በጎ ተፅኖ ላይ ሃሳብ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

1/  ''ቤቶች'' ድራማ 

ይህ በየሳምንቱ ቅዳሜ ምሽት የሚቀርበው ድራማ በብዙዎች ዘንድ በአስቂኝነቱ የሚጠቀስ እና በርካታ ተመልካች ያለው መሆኑ ይታወቃል።አመታዊ ዝግጅቱን ሲያዘጋጅም የሚመለከቱት ተመልካቾች በርካታ መሆናቸውን ያሳያል።እንደ እኔ አስተያየት ድራማው ከማዝናናት ባለፈ ሊያስተምር የሚገባው በርካታ ነገሮች ይቀሩታል።በመጀመርያ ደረጃ ታሪኩ አንድ በግንብ በታጠረ ቪላ ቤት ውስጥ የሚኖር ቤተሰብ ዙርያ ያጠነጥናል።ቤተሰቡን መካከለኛ ገቢ ያለው ቤተሰብ ለማለት ይከብደኛል።ምክንያቱም መካከለኛ ገቢ የሚባለው ሕብረተሰብ አሁን  በራሱ  ጠፍቷል።ከሃያ ሶስት አመታት በፊት አንድ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር መሬት ተመርቶ ቤት የመስራት አቅም ነበረው።ዛሬ ቤት ለመስራት ከፍተኛ ገቢ ካላቸው ውስጥ የሚመደብ ካልሆነ አይታሰብም።እናም ድራማው ውስጥ የሚተውኑት ቤተሰብ አባላት ቢያንስ ባለ ሁለት ሰራተኛ እና አንድ የጥበቃ ግለሰብ የሚተዳደሩ ናቸው እና መካከለኛ ከሚለው እናውጣቸው።እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ95% በላይ በእንደዚህ አይነት ኑሮ የሚኖር አይደለም።አዲስ አበባ ብቻ የግል መፀዳጃ የሌለው የሕዝብ ብዛት ከ70% በላይ እንደሆነ ከተገለጠ  እሩቅ አይደለም።በመሆኑም ድራማው ተጨባጩን የሀገራችንን ሕዝብ ኑሮ አይወክልም።ይህ ግን ድራማውን ያስወቅሰዋል እያልኩ አይደለም።ጥቂቶችም ብዙሃኑ ግብር በሚከፍልበት ቴሌቭዥን እርስ በርስ ሲጨዋወቱ መመልከት በራሱ ድራማ ነውና።

በእዚህ ድራማ ላይ ''ይቤ'' ገፀ ባህሪ ይዞ የሚጫወተው ወጣት የዩንቨርስቲ ተማሪ ለወጣቱ ምን ያስተምራል? ብዬ ስጠይቅ በገፀ ባህሩ ላይ ባብዛኛው አሁን በዘመነ ኢህአዲግ/ወያኔ አንድ የዩንቨርስቲ ተማሪ የሚኖረውን መልክ ይዞ ታገኙታላችሁ።ይቤ በድራማው ላይ ይጠጣል፣ይቅማል፣የተለያዩ የሴት ወዳጆች አሉት፣የሚናገረው የተደበላለቀ ማለትም ''ከአራዳ አነጋገር'' እስከ እንግሊዝኛ የተደባለቁ፣ኢትዮጵያዊነት በሙሉ የጠፉበት ሆኖ እናገኘዋለን።በነገራችን ላይ ይቤ መሃንዲስ ነው እና የነገ ኢንጅነሮቻችን የሚቅሙ፣የሚያጨሱ ናቸው በመሆኑም  መስርያቤቶች ከመሃንድሶች ጋር ሲሰበሰቡ የጫት በጀት መያዝ አለባቸው ማለት ነው።

ቤቶች ድራማ ሶስት መስተካከል ነበረባቸው የምላቸው አቀራረብ  አይቼበታለሁ

የመጀመርያው በቅርቡ የታየው ነው ታሪኩ እንዲህ ነው።ሁለቱ የቤት ሰራተኞች ቡና እያፈሉ ሳሉ የቤት ጠባቂው ዘበኛ ያገኘውን ዱቄት መሰል ነገር ፍሙ ላይ ሲጨምሩት እና በቤቱ ውስጥ የነበሩት በሙሉ ሲሰክሩ ያሳያል።እንደ ድራማው አገላለፅ ለካ የጨሰው አደገኛ ዕፅ ነበር።ሙሉ ድራማው በወቅቱ ቀጥሎ ያሳየን ነገር ቢኖር  አንድ እፅ የወሰደ ሰው ምን እንደሚታየው፣ለምሳሌ ድመት ዘንዶ እንደሚመስለው፣ሰዎች ትልቅ ሆነው እንደምታዩት በተግባር እያሳየ ትውልዱን አሰለጠነ።የሚገርመው ድራማው የእፅን አስከፊነት ሳይሆን አዝናኝነት ነው እስኪበቃን የነገረን።እፅ ያጨሱት በፖሊስ ሲያዙ እና ሲቀጡ ሳይሆን የአደገኛ እፅን አዝናኝነት ለታዳጊ ወጣት ሁሉ ተነገረው።ይህንን የተመለከተ ወጣት ''አንድ ቀን ልሞክረው'' እንዲል አድረገው አቀረቡለት።ይህ ክፍል ከታየ ገና ወራት አልተቆተሩም።በአድዋ በዓል ላይ ሸለላችሁ ብሎ ያገደ ፖሊስ ያለው መንግስት በተለቭዝኑ የእፅ አወሳሰድ ስልጠና ሲሰጥ ማየት ያሳምማል።

ሁለተኛው፣  ቤተሰቡ ለሽርሽር ከሄደባቸው ቦታዎች አንዱ ቅዱስ ላሊበላን ያሳየናል።በቅዱስ ላሊበላ ቅፅር ውስጥ በአካል ቤተሰቡ ቆሞ የሚሰጠውን ገለፃ ያዳምጣል።በእምነት ቦታ በመሰረቱ የቀልድ ድራማ መስራት አስቸጋሪ ነው።ድራማው ላይ ግን ሃይማኖታውም ሆነ ታሪካዊ ገለፃ ሲሰጥ በመሃል የፌዝ እና የቀልድ ንግግሮች ይሰሙ ነበር።ይህ እንግዲህ በመሃል ከሚገባው የሳቅ ጋጋታ ጋር አብሮ ነው።የእምነት ቦታዎች የሚሰጣቸው ቦታ እና በአማኙ ዘንድም ሆነ በታዳጊ እና ወጣቶች ዘንድ የሚያሳድረው ተፅኖ ፈፅሞ አልተጤነም።ቅዱስ ላሊበላ ከመጎብኘቱ ባለፈ የከበረ ቀልድ የማይነገርበት ቦታ መሆኑን ማሰብ ተገቢ ነበር።በሌላ በኩል ግን የድራማው አላማ ሀገርህን እወቅ በሁሉም ቤተሰብ መለመድ አለበት የሚለውን ሃሳብ በማንፀባረቁ የሚደገፍ አይደለም እያልኩ አይደለም።ለእምነት ቦታዎች የማይባሉ ቀልዶች ቀላቀለበት እንጂ።

ሶስተኛው የድራማው አቀራረብ የገጠሩን የሀገራችንን ገበሬ ለከተማው ወጣት የሚስልበት የተሳሳተ አቀራረብ ነው።የቤቱ ዘበኛ ሁል  ጊዜ እንቅልፍ በጣም ወዳጅ፣ምግብ የሚወድ፣ሥራ የማይወድ እና ግዴለሽ አድርጎ የሚስልበት ገፀ ባህሪ የኢትዮጵያን ገበሬ ፈፅሞ አይወክልም።የኢትዮጵያ ገበሬ እንቅልፍ የለውም ከማለዳ እስከ ምሽት ሲለፋ ውሎ ማታ የቀረውን ሥራ በመስራት የሚጠመድ፣ንቁ፣በሥራ የሚያምን፣ላመነበት የሚሞት እና ለወዳጁ ሟች ነው።ይህንን የህብረተሰብ ክፍል ነው እንግዲህ ለሕዝቡ ''ሎሽ ማለት ብቻ የሚወድ'' ተብሎ የሚቀርበው።ይህ በእራሱ ከቀልድ ባለፈ ብዙ ማህበራዊ ነገሮችን የሚነካ ነው።በኮሜዲ ፊልሞች ላይ ገፀ ባህርያት የተለያዩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችን እያነሱ ያስተምራሉ እንጂ በኢትዮጵያ ገበሬ ላይ የሚሳለቅ አቀራረብ ይዘው እና ከገበሬው የምንማረው እንቅልፍ ብቻ የመሰለ አቀራረብ ማንንም አይጠቅምም።

እዚህ ላይ የቤቶች ድራማን አንዳንድ ግድፈቶች እና ማስተካከል የሚገባቸውን አቀራረቦች ላይ ሃሳብ ለመስጠት ፍለግሁ እንጂ በደፈናው ድራማውን ለማጣጣል እንዳልተነሳሁ ይታወቅልኝ።ድራማ ከአዝናኝነቱ ባለፈ ወጣቶችን በስነ-ምግባር፣በሀገር ፍቅር ስሜት እና በቅን ለሀገር መስራትን የሚያስተምር ካልሆነ በሳቅ ማንከትከትን ብቻ አላማዬ ብሎ ከተነሳ ስለ እፅ አወሳሰድ የሚያሰለጥነን  ከሆነ አደገኛ ነው።ላሰምርበት የምፈልገው ለሕዝብ የሚቀርቡ ድራማዎች በተለያየ ሙያ ላይ ያሉ አማካሪዎች ያስፈልጋቸዋል።ደራሲው ''ህዝብን ካሳቀ እና መንግስትን እስካላሳቀቀ ድረስ መንገዱ ሰላም ነው'' በሚል አስተሳሰብ ብቻ አየር ላይ ማዋል የለበትም። 

 ''ሞጋቾች'' ድራማ 

ከእዚህ በአንፃሩ በ''ኢቢኤስ''ቴሌቭዥን የሚቀርበው ''ሞጋቾች'' የተሰኘው ድራማ ጥሩ፣አስተማሪ እና ትውልድን የሚያንፅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።ሞጋቾች በአንድ ሆስፒታል ውስጥ የሚሰሩ የህክምና ዶክተሮች እንዴት ህዝባቸውን በታማኝነት እንደሚያገለግሉ እና በማህበራዊ ኑሮአቸው ውስጥ የሚገጥማቸውን ተግዳሮት ያሳያል።የሞጋቾች ድራማ በፊልም አቀራረፅ እና የድምፅ ጥራቱ ብቻ ሳይሆን የመረጡት ሆስፒታል ተራው ሕዝብ የሚገለገልበትን እና እታች ያለው ሕዝብ የሚላቸውን አባባሎች፣ስሜቶችን ሁሉ የሚያንፀባርቅ አቀራረብ ይታይበታል።እዚህ ላይ ማስታወሻዬ አጭር ከመሆኑ አንፃር ባጭሩ ''ሞጋቾች''ድራማ ሶስት ነገሮችን ለአዲሱ ትውልድ እንደሚያስተምር ጠቅሼ ሃሳቤን ልግታ።

1/ ተምሮ በሀገር መስራትን እና ወገንን ማገልገልን
በድራማው ብዙ ክፍሎች ላይ የሚታዩት አቀራረቦች በዶክተር ደረጃ ያሉ የህክምና ባለሙያዎች ምን ያህል እታች ላለው ሕዝብ እንደሚጨነቁ እና ኃላፊነት እንደሚሰማቸው ያሳያል።

2/ የዩንቨርስቲ ሴት ተማሪዎች ጥንቁቅ እንዲሆኑ ይመክራል
የድራማው ዋና ገፀ ባህሪ በአንድ ወቅት የዩንቨርስቲ ተማሪ ሆና ሳላ አንድ ምሽት በተፈጠረ የምሽት ዳንስ ይመሽባትና ከሰው ቤት ታድራለች።ሆኖም በእዚችው ምሽት ተደፍራ ልጅ ትወልዳለች።ድራማው ባብዛኛው  የወለደቻትን ልጅ አባት በመፈለግ ስትደክም ያሳያል።ይህ አሁን ላሉት ወጣቶች እያንዳንዱ ምሽት የምትሰራ ስህተት እና ከዋልጌ ተማሪዎች ጋር መግጠም የሚያስከፍለው ዋጋ ለአመታት የሚተርፍ መሆኑን ያሳያል።ይህም በተለይ ሴት ወጣቶች ጥንቁቅ እንዲሆኑ ይመክራል።

3/ በአንድ ወቅት ችግር ቢያጋጥምም መልሶ መነሳት እንደሚቻል ያስተምራል
የድራማው ዋና ገፀ ባህሪ ባንድ ወቅት ተደፍራ ልጅ ለመውለድ ተገደደች።ሆኖም ተመልሳ ጠንክራ በመማሯ ዛሬ ለህክምና ዶክተርነት በቃች።ይህ በራሱ የሚያስተምረው ትምህርት አለ።ወጣቶች ስህተት ላይ ሊወድቁ ይችላሉ ግን ከስህተታቸው ተመልሰው እንደገና ተነስቶ ለቁም ነገር መብቃት ነው ዋናው ቁም ነገር ይለናል የድራማው መልእክት።

ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን  ድራማዎች የረቀቀ የፕሮፓጋንዳ መስርያ አውድማ  ወይንም የተበላሸ ትውልድ ማፍርያ ማሽን እንዳይሆኑ በስድስተኛውም  የስሜት ህዋሳችንም መቃኘቱን አንርሳ።

ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
የካቲት 26/2007 ዓም (ማርች 5/2015)

Sunday, March 1, 2015

የአድዋን ድል የማያውቁ የአድዋ ልጆች



ኢትዮጵያን  በቅኝ ግዛት ለመያዝ ያለ የሌለ ኃይሉን አሰባስቦ የመጣው ጣልያን በዳግማዊ አፄ ምንሊክ መሪነት፣ በእቴጌ ጣይቱ ሃሳብ አፍላቂነት እና የጦር አዝማችነት ከመላዋ ኢትዮጵያ በዘመቱ ኢትዮጵያውያን አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ ሊባረር እና ኢትዮጵያም  ነፃነቷን ጠብቃ ለመኖር ችላለች።

ይህ ድል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ኩራት እንደሆነ እስከዛሬ ደርሷል።የአድዋ ድል ታላቅነትን በአግባቡ ለመረዳት ጦርነቱ ከተደረገበት ወቅት በፊት የነበረውን የዓለም የፖለቲካ ሂደት በአግባቡ መረዳትን ይፈልጋል።ይህ ወቅት አውሮፓውያን ''የበርሊኑ ጉባኤ'' (በርሊን ኮንፍረንስ) በተሰኘ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪካን እንደ አዲስ በአውሮፓ የወቅቱ ጉልበተኛ መንግሥታት አማካይነት ቅኝ ተገዥ እንድትሆን የተፈረደባት ወቅት ነበር።ይህ ፍርደ ገምድል የሆነውን የአውሮፓውያን  የቅኝ ግዛት ጥማት ግን ኢትዮጵያ ላይ በአድዋ ድል ሙሉ በሙሉ ከሸፈ።

ይህ ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ የሆነ የድል በዓል ላይ የሚዘባበቱ 'የጤፍ እንጀራ ደንበኞች' አልጠፉም።የጤፍ እንጀራ ደንበኞች ማለቴ ከኢትዮጵያ ተፈጥረው በኢትዮጵያ ስም ከበረው እና የእራሷኑ እንጀራ በልተው መልሰው ''እንጀራዬን የበላ ተረከዙን አነሳብኝ''  እርሷኑ የሚሰድቡ ጉዶችን በጉያዋ  ኢትዮጵያ መያዟን ለማመላከት ነው።

የአድዋን ድል የማያውቁ የአድዋ ልጆች የአድዋ ድልን ለማኮሰስ ላይ የሚዘምቱባቸው ሁለት እኩይ ባዕድ-አደር መንገዶች አሏቸው።እነርሱም ዳግማዊ አፄ ምንሊክን እና እራሱ በዓሉ ላይ ጥላ ያጠላል ያሉትን የወሬ ዘመቻ መክፈት እና የአድዋን ድል በራሱ የጎጥ ታፔላ ለመለጠፍ መሯሯጥ ናቸው።በእዚህ እኩይ ባዕድ አደር ተግባራት ላይ የተሰማሩ የታሪክ እና የእውነት ደመኞች ደግሞ በሁለት ክፍል ተከፍለው እናገኛቸዋለን።የመጀመርያዎቹ በኦሮሞ የጎሳ ጥያቄ ዙርያ ጥያቄውን አስቂኝ (እኔ አስቂኝ ነው የምለው) ወደ ሆነው 'የቅኝ ግዛት ጥያቄ' የሚያስፈነጥሩትቱ ሲሆኑ።ሁለተኛዎቹ አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው የህወሓት ጎሳን መሰረት ያደረገው ስርዓት አቀንቃኞች ናቸው።

የመጀመርያዎቹን ክፍሎች ስንመለከት የኦሮሞ ጎሳ የመብት ጥያቄ እንደማንኛውም የኢትዮጵያውያን የመብት ጥያቄ በተጨባጭ ያለ መሆኑን ባምንም ''የቅኝ ግዛት ጥያቄ'' የሚለው በጎሳው ስም እና ፅንፍን በያዘ የእስልማዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚታትሩት ግን ሌላ መዘዝ እንዳያመጡ እና ቆመናል የሚሉትን እንደ ጄነራል ጃጋማ ኬሎ ውብ የሆነ አገላለፅ ''የኢትዮጵያ ግንድ'' የሆነውን የኦሮሞ ብሄረሰብን ከቀሪው ኢትዮጵያዊ ጋር ለማጋጨት የሚሞክሩት ሙከራ ብዙ ዋጋ እንዳያስከፍላቸው  ስጋት አለኝ።

ሁለተኛው እና በእዚህ ፅሁፍ ላይ ላተኩርበት የተነሳሁት ባዕድ-አደር ፖሊሲ የሚገለፀው አሁን በስልጣን ላይ ያለው የህወሓት አቀንቃኞች በአድዋ በዓል ዙርያ የሚያንፀባርቁት ታሪክን የተፃረረ አካሄድ ነው።የስርዓቱ ደጋፊዎች በአድዋ በዓል ላይ የሚያሳዩት የተንሸዋረረ አተያየት ፍፁም የወረደ የጎሳ ዘረኝነት የሚንፀባረቅበት ነው።ይህም  ሁኔታ በሶስት መንገዶች ይገለፃል።

የመጀመርያው በዓሉን የማደብዘዝ ሥራ የሚገልጠው  በህወሓት ቀጥታ ትእዛዝ ስር በሚተዳደረው የሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ነው።የኢትዮጵያ ቴሌቭዝንም ሆነ ራድዮ በዋዜማው ምንም አይነት የአድዋ በዓልን የሚያስታውስ መርሃ ግብር የለውም።ለምሳሌ በዘንድሮው የ2007 ዓም የመገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ቴሌቭዥን ጨምሮ ማለት ነው ምንም አይነት መርሃ ግብር አልተላለፈም።ይህ ሁኔታ በሸገር ኤፍ ኤም ራድዮ አማካይነት የተዘጋጁ መርሃ ግብሮችን አይመለከትም።

ሁለተኛው በዓሉን የማደብዘዝ ሥራ የሚሰራው በማህበራዊ መገናኛ አውታሮች ለምሳሌ በ''ፌስ ቡክ'' አማካይነት ስለ ዳግማዊ አፄ ምንሊክ፣እቴጌ ጣይቱ ወዘተ የፈጠራ ወሬዎችን በመለጠፍ ነው።ለምሳሌ የስርዓቱ የማህበራዊ ሚድያ አፈቀላጤ መሆኑ የሚነገርለት እና ከፍተኛ የህወሓት ባለስልጣናት ጋር ግንኙነት እንዳለው እራሱም ደጋግሞ የሚነግረን  ዳንኤል ብርሃነ የዘንድሮውን የአድዋ በዓል አስመልክቶ ሲሳለቅ ''አፄ ምንሊክ በአድዋ ጦርነት ወቅት የነበሩበትን ትክክለኛ ቦታ ማግኘት አልቻልኩም '' በማለት ነበር።

ሶስተኛው የአድዋን ድል የማያውቁ የአድዋ ልጆች በዓሉን የማደብዘዝ ሥራ የሚሰሩት በዋናው የበዓሉ ቀን የሚደረገውን የበዓል አከባበር 'ተራ' መልክ በመስጠት ነው።ላለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት የእዚህ ፅሁፍ ፀሐፊ እንደሚያስታውሰው የአድዋ በዓል በአዲስ አበባ አከባበሩ (የአበባ ጉንጉን በፓርላማ አፈጉባኤ አባ ዱላ ከማስቀምጥ አላለፈም) በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የምሽቱ የዜና እወጃ ወቅት የተሸፈነው  ሁለት ደቂቃ ባልሞላ እንድያውም አንዱ አንድ ደቂቃ ብቻ በወሰደ የዜና አቀራረብ ሰዓት ነበር።

ልብ በሉ! ያ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ኩራት የሆነ ታላቅ ታሪካዊ ድል በደቂቃ የዜና ዘገባ ሲታለፍ ከባእዳን ጋር ሳይሆን በእርስ በርስ ጦርነት ለሞቱት የህወሓት ሰማዕታት ግን በመቶ ሚልዮን የሚቆጠር ብር ወጥቶ ''አስረሽ ምችው'' ተይዟል።ይህ ፅሁፍ በተፃፈበት የአድዋ በዓል ዋዜማ ዕለትም በአዲስ አበባ ሚሊንየም አዳራሽ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ የተከሰከሰበት የህወሓት 40ኛ ዓመት እየተከበረ ነው።ይህንን ሁሉ ድርጊቶች እያየን አድዋ ላይ የሞቱትን ኢትዮጵያውያን እናስባለን።ከጫፍ ሀገር ኢትዮጵያ እስከ አድዋ ድረስ ተጉዘው የሞቱልንን፣ዛሬ አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ ያበቁንን ሰማዕታት በከፍተኛ ክብር እንዘክራለን፣አርማቸውን እናነሳለን።የአድዋን ድል የማያውቁ የአድዋ ልጆች ልብ ግዙ! እንላለን።ባዕድ-አደር ጫወታቹን እንድታቆሙሉንም ትጠየቃላችሁ።

ጉዳያችን  የካቲት 23/2007 ዓም (ማርች 2/2015)

Saturday, February 28, 2015

«እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም። ሆኖም 
ይህን ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ጥገኛ የሚያድርግ ውል ከመቀበል 
ጦርነትን እመርጣለሁ» እቴጌ ጣይቱ





 ቅድመ የዓድዋ ድል(1885 እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር)

እንደ  አውሮፓውያኑ አቆጣጠር የካቲት 16/1885 ጀርመን በርሊን ከተማ በሚገኘው ውብ በሆነው የ ሀገሪቱ ቻንስለር ቬን ቢስማርክ ባለስልጣን መኖርያ ህንፃ ሳሎን ፌሽታ በ ፌሽታ ሆኗል።ሶስት ወር ሙሉ አሰልቺ ውይይት የተደረገበት ዋና ዋናዎቹ የ አውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ተሰብስበው '' አንተ ይሄን ያዝ አንተ በእዚህ ውረድ''ተባብለው የ አፍሪካ ካርታ  በመካከላቸው ተዘርግቶ ከወታደራዊ ዘመቻ በፊት አፍሪካን የተከፋፈሉባት ቀን ነበረች። በእዚህ ስብሰባ ከ80 በ መቶ በላይ የ አፍሪካ መሬት በ ሃሳብ መስመር እያሰመሩ ተከፋፈሉት። የበርልኑ''General act of Berlin conference''በ ታሪክ ባብዛኛው የሚታወቀው’'The division of Africa ''ወይንም ''scramble of Africa''(አፍሪካንየመቀራመትጉባኤ)ተብሎነው።በእዚህጉባኤላይጀርመን፣ኦስትሮሀንጋሪ፣ቤልጅየም፣ደንማርክ፣ፈረንሳይ፣ታላቅዋብሪታንያ፣ጣልያን ፣ኔዘርላንድ፣ፖርቱጋልን ጨምሮ የተገኙ ሲሆን ቅኝ ግዛትን ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት የተሞከረ ና በዚሁ መሰረት በ 1914 በ ፈረንጆቹ አቆጣጠር አብዛኛው የ አፍሪካ ግዛት በ ቅኝ ገዢዎች የወደቀበት ሁኔታ ነበር።

 ''ቀን እባብ ያየ   ምሽት ልጥ ይፈራል''

ጣልያን ከዚህ ስብሰባ ብዙ የተጠቀመች መሰላት።ቢያንስ ሀገራችንን ስትወር በ አፋርና ኢሳ (የአሁኑ ጅቡቲ) ከሰፈረው የ ፈረንሳይ ሰራዊትና ከ ግብፅ አስከ ሱዳን ከተዘረጋው ከ ብሪታንያ ቅኝ ግዛቶች ጋር አያተናኩልም ብላ አሰበች። የመስፋፋት ሕልሟንም ቀጠለች ።ዋናው  የጣሊያን የመስፋፋት ዘመቻ የመሰረት ድንጋይ የተጣለው አሰብ ላይ ነበር። ሩባቲኖ የተባለ የጣሊያን የመርከብ ድርጅት በወቅቱ የአሰብ ግዛት አስተዳደሪ ከነበሩት ሱልጣን ስፋት ያለው መሬት  በ9 ሺ ዶላር ገዛ። በሁዋላ ግን የጣሊያን መንግስት ወደ ተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ለመረማመጃነት እንደሚጠቀምበት በማመኑ፣ ከዚሁ ኩባንያ  መሬቱን በ43 ሺ ዶላር ገዛው(ይህ ግዢ ኢጣልያ በአድዋም ሆነ በ 1928 ዓም ኢትዮጵያን ለመውረር በርከፋች ከመሆኑም በላይ ለአካባቢው ችግር መዘዝ ደውል ተደርጎ ይጠቀሳል)።                                                                                                                        

ጣሊያንም አሰብን መያዝዋ እንደታወቀላት በቀጥታ አፍሪካን ለመቀራመት አላማ ካደረገው የበርሊን ጉባኤ እንድትሳተፍ ተደረገ።ይህ ብቻ አደለም ቅደም ብላ ጣልያን ምፅዋን ይዛ ስለነበር ከ ራስ አሉላ ጦር ጋር ተደጋጋሚ ውግያ ገጠማት።ለምሳሌ አንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ጥር 26 /1887 ራስ አሉላ ''የ ኢትዮጵያ ድንበር ቀይ ባህር ነው ያለው'' በሚለው የፀና አምነታቸው ዶጋል ላይ ጣልያንን ሙሉ በሙሉ ድል አርገው መልሰውታል። የበርሊን ጉባኤ ተሳታፊ አገሮችም ጣሊያን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት እንድትይዝ ፈቃድ የሰጡት ከዚህ ሁሉ ትንኮሳ በሁዋላ ነበር ።ዛሬ ብዙ ወገኖች በ ኢንቨስትመንት ስም ለ ባአዳን በሀገራችን ደቡባዊ ና ምራባዊ ክፍል የሚደረገውን ቅጥ ያጣ የ መሬት ሊዝ'' ኪራይ'' ይባል ''ውል'' በ ስጋት ቢያዩት አይፈረድባቸውም።በ ትክክልም ''በ ቀን እባብ ያየ በ ምሽት ልጥ ይፈራል'' እንዲሉ የ አሰብን ታሪክ ና ቀጥሎ የተከተለውን ያየ ተመሳሳይ ችግር ነገ አይመጣም ለማለት ዋስትና የለውም።                                         

''እግዚአብሄር ድንበር ይሁናችሁ ብሎ የሰጠንን ባህር እየተሻገረ እንደፍልፈል መሬት እየቆፈረ በመስፈር ላይ ነው''

የ ኢትዮጵያ ና ጣልያን ጦርነት ዋነኛ መነሻ የ ጣልያን የ ቅኝ ግዛት ጥማት ሲሆን እንደ ፈጣን ምክንያት  የሚጠቀሰው ግን የ ውጫሌ ውል አንቀፅ 17 ትርጉም ነው።የትርጉም ልዩነቱ ጉዳይ ሊታወቅ የቻለው እቴጌ ጣይቱ የውጫሌው ውል አንቀፅ 17 ላይ ዓለቃ ዓፅመ ጊዮርጊስ የተባሉት የጣልያንኛ ቋንቋ አዋቂ ዓፄ ምኒልክ በሰጧቸው ትዕዛዝ መሠረት የውሉን ሰነድ በመመርመር የውሉ አስራ ሰባተኛው አንቀፅ የያዘውን የትርጉም መዛባት በመግለፅ ጉዳዮ ኢትዮጵያ የምትጐዳበት ስለመለሆኑ ጭምር በማስረዳት በሰጡት ቃል ሲሆን እቴጌ በዚህ ወቅት ነገሮችን በጥንቃቄ የሚከታተሉ ስለነበር ዓፄ ምኒልክ በመጀመሪያ ሳይረዱ ዓለቃ ዓፅመ ጊዮርጊስ እንዲታሰሩ ቢያደርጉም እቴጌ ጣይቱ ግን እኒህ ሰው  ትክክለኛ የኢትዮጵያ ወዳጅ መሆናቸውን ለዓፄ ምኒልክ በማስረዳት ከሦስት ዓመታት እስራት በኋላ ማስፈታቸው ይታወቃል።

በዚህ በኩል ሲታይ እቴጌ ጣይቱ የምኒልክ የቅርብ አማካሪ በመሆን በፖለቲካ ተግባሮች ምን ያህል አስተዋፅኦ እንዳበረከቱ መገንዘብ ይቻላል። እቴጌ እንደተናገሩትም «ዓፅመ ጊዮርጊስ ቢታሰር ቢፈታም ለሀገሩ የሚገባውን ሠርቶ ነው። ኧረ ለመሆኑ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለውዮሴፍ፣ ጣሊያኖች በተንኮል ገብተው በማታለል ይህን የመሰለ ሥራ ሲሠሩ አነጋጋሪ ሆኖ ሳለ እንዴት ሳይስጠነቅቅዎ ቀረ?»በማለት የእቴጌ ጣይቱ የቁጣ መዓት ወደ ዮሴፍ ዞረ።ከዚያም ጨምረው «ከእንግዲህ ወዲህ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ፣ ሥር የሚነቅል፣ መሠረት የሚያፈርስ ጉዳዮን ሁሉ እኔ ሳላየው እንዳያልፍ ይፍቀዱልኝ» ብለው ለንጉሡ ባመለከቱት መሠረት ይኸው አንቺ ሳታይው ሳትመረምሪው አያልፍም በማለት ፈቀዱላቸው፣ይህ እንደሚያመለክተው እቴጌ ጣይቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበራቸውን ተገቢ ቦታ የሚያመለክት ነው። ውሉንም ለማስተካከል ዓፄ ምኒልክ ያደረጉት የዲፕሎማቲክ ጥረትው ጤታማ ሊሆን ባለመቻሉ ሚኒስትሮች የጦር አለቆችና መኳንንት የሚገኙበት ጉባዔ እንዲጠራ አደረጉ።

በአንቀጽ 17 ላይ የሰፈረው ስምምነት ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ውስጥ የሚያስገባ ነበር። ይህ አንቀጽ በአማርኛው ቅጅ ላይ የሚከተለውን አሰፍሯል “ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት በምታደርግበት ጊዜ የጣሊያንን መንግስት እገዛ ከፈለገች ጣሊያን የኢትዮጵያን ፈቃድ ለመፈጸም ፈቃደኛ ነች።” ይሁን እንጅ በጣሊያንኛ ቁዋንቁዋ በተፈረመው ቅጅ ላይ ያለው ስሜት ከዚህ በተለየ ቀርቦአል “ኢትዮጵያ ማንኛውንም አይነት የውጭ ግንኙነት በጣሊያን መንግስት በኩል ታደርጋለች'' የሚል ትርጉም ይዞ ነበር።ይህም ቆይቶ ዓፄምኒልክ ከ አንግሊዝ መንግስት ጋር ሊያደርጉ ላሰቡት ግንኙነት በ ጣልያን በኩል ይምጡ መባላቸው ሲሰማ የ ውሉ ትርጉም ምንነት ለየለት።ይህ ብቻ አደለም የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው ክርስፒ ግን ጉራና ንቀት በተሞላበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ከዛሬ ጀምሮ በጣሊያን ስር ነች እያለ ከማወጅ በስተቀር ውሉን ለማስተካካል የሚያስችል እርምጃ አልወሰደም ነበር። ይባስ ብሎም ኤርትራን በመውረር የመጀመሪያዋ የጣሊያን ቅኝ ግዛት አገር ተመሰረተች ብሎ 1890ዓም አዋጅ አስነገረ። እንግሊዝም ሳትውል ሳታድር ጣሊያን ላቀረበችው ሀሳብ ድገፉዋን ሰጠች

የጣሊያንና የሌሎች መንግስታት ተንኮል ያበሳጫቸው አጼ ሚኒሊክ፣ ወዲያውኑ ከጀርመን፣ ከሩስያና ከቱርክ መንግስታት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠንከር፣ ጣሊያንን ለመፋለም ወስነው ዝግጅት ጀመሩ። እንዲህም ሲሉ ለህዝባቸው ተናገሩ “ እግዚአብሄር በቸርነቱ ጠላቶቼን ድባቅ መትቶልኝ፣ ግዛቴንም አስፍቶልኝ፤ እስከዛሬ ድረስ አቆየኝ። በእግዚአብሄር ጸጋም ነግሻለሁ። ጠላት አገራችንን ለመውረር ሀይማኖታችንንም ለማስለወጥ ደጃፋችን ድረስ መጥቷል። እግዚአብሄር ድንበር ይሁናችሁ ብሎ የሰጠንን ባህር እየተሻገረ እንደፍልፈል መሬት እየቆፈረ በመስፈር ላይ ነው። ጉልበት ያለህ በ ጉልበትህ ጉልበት የለለህ በ ፀሎትህ አግዘኝ። ከዚህ ሌላ ወስልተህ የማገኝህ ግን ማርያምን አልምርህም''

  «እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም። ሆኖም ይህን ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ጥገኛ የሚያድርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ» እቴጌ ጣይቱ

ዳግማዊ ምኒሊክ እና ንግስት ጣይቱ እውነተኛ ፎቶ (ፎቶ አዲስ ጆርናል) 

ጣሊያን ከባዱን የአድዋ ጦርነት ከማካሄዷ በፊት በርካታ መለስተኛ የሆኑ ጦርነቶችን ከኢትዮጵያውያን ጋር ስታደርግ ቆይታለች። እነዚህ ጦርነቶች ግን ሁሌም በጀግኖቹ የኢትዮጵያ መሪዎች አሸናፊነት ይጠናቀቁ ነበር። በተለይ የራስ አሉላ ብልህ የጦር አመራር ና ብቃት ያለው ሰራዊታቸው ለ ጣልያኖች የ ውስጥ አግር  ፍም ሆኖባቸው ቆየ።

የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በአፍሪካ ምድር ያልታየ አዲስ ታሪክ በኢትዮጵያ ምድር ተሰራ። እለቱ በኦሮቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ የቅዱስ ጊዮርጊስ ወርሀዊ በአል የሚከበርበት ቀን ነበር ። ሰማይ ከ መሬት ሳይለቅ ከ ለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ንጉሡ ና የ ጦር ሹማምቶቻቸው ከ አዲስ አበባ ድረስ አብሮ በመጣው የ አራዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦተ-ሕግ ዙርያ ከበው ቆመው የ ኪዳን ፀሎት በማረግ ላይ   ነብሩ።  በ መካከል የሚኒሊክ የመረጃ ክፍል የሆነ አንድ ወጣት እየተንደረደረ መጥቶ ለንጉስ ሚኒልክ ''ጌታየ “ባራቴሪ” ተኩስ ከፍታብናለችና ቶሎ ብለው አንድ ነገር ያድርጉ'' በማለት ሹክ ያላቸው ፣ በመቀጠል ከ መቅደሱ ውስጥ ለ አፄ ሚኒሊክ ና ሹማምንቱ '' የቀረውን ፀሎት እኛ እንፈፅመዋለን ሂዱ አይዟችሁ የ ኢትዮጵያ አምላክ ይከተላችሁ'' የሚል ቃል ተቀብለው ፣ መስቀል ተሳልመው ዘመናዊ መሳሪያ እስካፍንጫው የታጠቀውን የጠቅላይ ሚኒስትር ክርስፒን ጦር ለመግጠም ቤተክርስቲያኑዋን ለቀው ወጡ።

ማታ ነው ድሌ


ጣሊያን ጂኔራል ባራቴሪ ለተባለው የጦር መሪዋ የቀይ ንስር የተባለውን ከፍተኛ ወታደራዊ ማእረግ ሸልማ ላከች። ጄኔራሉ ከ20 ሺ በላይ የሚሆነውን ጦሩን ይዞ፣ የኢትዮጵያን ጦር ለመግጠም ጦሩን በሶስት ማእዘን አንቀሳቀሰ። በጄኔራል ዳቦር ሜዳ የሚመራው ጦር የበለሀ ተራሮችን በቀኝ በኩል አጥሮ እንዲይዝ፣ የጄኔራል አርሞንዲ ጦር ደግሞ በመሀል ሰንጥቆ እንዲገባ ታዘዘ። ጄኔራል አልቤርቶኒ በበኩሉ የኪዳነምህረት ታራራን እንዲቆጣጠር ትእዛዝ ቢሰጠውም፣ እንዳ ኪዳነምህርትና ኪዳነምህረት የሚባሉት ሁለቱ ቦታዎች ስለተምታቱበት፣ ከኪዳንምህረት ተራራ ሳይደርስ በሌላ ቦታ ላይ ሰፈረ በጄኔራል ኢሊና የሚመራው ጦር ደግሞ ከጀኔራል ባራቴሪ ጦር ጋር በመሆን በተጠባባቂነት እንደቀመጥ ተደለደለ:: 

ከ አንድመቶ ሺ የሚበልጡት የ ኢትዮጵያ ሰራዊት   በየጦር አበጋዞቻቸው ና ''ፋኖ ተሰማራ '' ብሎ ልጁን ቤተሰቡን ተሰናብቶ ተነቃነቀ።ጦርነቱን የተቀላቀለው ከ ሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የተውጣጣው ጦር ውግያውን በየመጣበት ጠመደው።ድሉ ግን የማታ ማታ የ ኢትዮጵያ ሆነ። ጣልያኖች መሸሽ ጀመሩ። የንግሥት ጣይቱ በተመረጡ ወታደሮች ሥልታዊውን የ ጣልያኖች የ ውሃ ቦታ አስያዙ።ጣልያን ጀነራሏን በቁሙ አስማርካ በወቅቱ በ ምስራቅ አፍሪካ ከነበራት ከ ግማሽ በላይ የሚሆን ሰራዊቷን አጥታ ጦርነቱ ተጠናቀቀ።                                                                                                
ዶክተር ታደሰ ስለ ድሉ ሲገልፁ-
''በኢትዮጵያዊያን የጦር ሃይል ጥቅም ላይ የዋሉት ስትራቴጂዎች እና ታክቲኮች በንጉሰነገስቱ ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ ክህሎት ላይ ብቻ የተመሰረቱ ሳይሆኑ በበርካታ ሺዎች በሚቆጠሩ አመታት በኢትዮጵያ የጎለበቱ ልዩ አስተሳሰቦች ላይም ጭምር የተመሰረቱ ነበሩ፡፡ እነዚህ አስተሳሰቦች በሌሎች የአለም ክፍሎች ትምህርት ከተወሰደባቸው ወታደራዊ ትምህርቶች ለየት ባሉ ሁኔታዎች የተፈጠሩ ነበሩ፡፡ ከዚህም ባሻገር እነዚህ የጦር ታክቲኮች እና ስትራቴጂዎች በሃገሪቱ ታሪክ እና መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ተንፀባርቀው ነበር፡፡ በዚህ አካሄድ የኢትዮጵያ ሃይሎች ጣሊያኖች ይጠብቁት ከነበረው አኳኃን በተለየ ደረጃ ላይ ይገኙ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የአድዋ ጦርነት በቀጣይ ምእተ አመት በተለያዩ ወታደራዊ /ቤቶች የጥናት ርእስ ሆኗል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የአድዋ ጦርነት ከተካሄደበት ጊዜ ጀምሮ ለረጅም ጊዜ የትኩረት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል፡፡'' ብለዋል።
የ ድሉ ዜና በመላ ዓለም ተናኘ ። ጥቁር አፍርካውያን አውሮፓውያንን አሸነፉ የሚለው ዜና ጣልያንን ብቻ ሳይሆን በተዋበው ህንፃ ውስጥ አፍሪካን ለመቀራመት ተሰብስበው የነበሩ   
መንግስታትን ሁሉ 'ክው !' ያደረገ መራር ዜና ነበር።በወቅቱ የ ኒውዮርክ ታይምስ  ጋዜጣ በ  ሽፋኑ ላይ በ ያወጣው ዜና ርአስ''ITALY's TERRIBLE DEFEAT'' የጣልያን አስፈሪው ሽንፈት''ማለቱ አስፈሪነቱ ለ በርሊኑ ጉባኤተኞች ሁሉ ማለቱ ሳይሆን ይቀራል?

አድዋ ጦርነት ድል ተከትለው የመጡ ክስተቶች


የ አድዋ ድል በ ኢትዮጵያ ድል አድራጊነት መጠናቀቅ የሚከተሉትን ሁኔታዎች በ ሀገርውስጥም ሆነ በ ዓለም አቀፍ የ ዲፕሎማሲ መድረክ ላይ ተከስቷል;-

    በ ጥቅምት ወር ላይ ጣልያን ከ ኢትዮጵያ ጋር ''አዲስ አበባ ውል '' የተባለ አዲስ ውል ለመፈረም ተገዳለች፣

    በ አሜሪካ፣አፍሪካ ና በመላው ዓለም ያሉ ጥቁሮች ለመብታቸው ተነሳስተዋል፣

    እ.ኤ.አ. በ1903 ዊሊያም ሄንሪ የተባሉት አፍሪካ አሜሪካዊ የንግድ ስራ ዋነኛ አንቀሳቃሽ የሄይቲ ዜግነት ካላቸው ገጣሚ እና ተጓዥ ከሆኑት ቤኒቶ ሲልቪያን ጋር በመሆን ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡አላማቸውም ንጉሰ ነገስት ሚኒሊክን ለመጎብኘት እና ከእርሳቸውም ጋር ለመተዋወቅ ነበር፣

    የኢትዮጵያን ነፃነት በአሜሪካ ለሚኖሩ ጥቁሮች እንደ ነፃነት ነፀብራቅ እና መሰረት በማየት ጋርቬይ በቂ ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚያስችል የባህር ላይ የንግድ ስራ ለመመስረት አሰቡ፡፡ ከዚህም ሌላ ወደ አፍሪካ የሚመለሱ በርካታ አባላትን ለመመዝገብ አቀዱ፡፡ በጥቂት አመታት ውስጥ የጋርቬይ ማህበር ከሞላ ጎደል 10 ሚሊዮን ዶላር በማሰባሰብ እስከ ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱ አባላትን ለማቀፍ ችሏል፣

    ታዋቂ የሆነው የሲቪል መብቶች መሪ ማልኮም ኤክስ አባቱን ቄስ ኢያርል ሊትልን በመጥቀስ የሕይወት ታሪኩን መፃፍ ጀመረ፡፡ ለዚህም ምክንያት የሆነው አባቱ ከላይ የተጠቀሰው 'የዩናይትድ ኒግሮ ኢምፕሩቭመንት አሶሲየሽን' ከፍተኛ ደጋፊ ነበሩ፡፡ ማልኮም በዚህ ረገድ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል፡- ‘አባቴ ወደ ጋርቬይ ማህበር ስብሰባዎች የሚወስደው እኔን ብቻ ነበር፡፡ እነዚህ ስብሰባዎች በተለያዩ ሰዎች ቤቶችበሚስጥር ይካሄዱ ነበር፡፡ አባቴም እኔን አንዳንድ ጊዜ ወደ እነዚህ ስብሰባዎች ይወስደኝ ነበር፡፡ “አፍሪካ ለአፍሪካውያን የሚለውን አባባል አስታውሳለሁ፣ ኢትዮጵያዊያን ተነሱ’ ማልኮን ከጋርቤይ የፓን አፍሪካ መልእክት ጋር የነበረው ቁርኝት እና ይህም መልእክት በንባብ፣ በፅሑፍ እና በታሪክ ራሱን ሲያስተምር እንደ መነሻ ምክንያት የሚጠቀምበት ነበር፡፡ ‘በከፍተኛ ደረጃ ያስደሰቱኝን የመጀመሪያዎቹን መፅሐፍት በሚገባ ማስታወስ እችላለሁ፡፡ ጄኤ ፕሮዘርስ በፃፋቸው ሶስት መፅሐፍት ጥቁር የነበረው ኤዞፕ ስለ ታላቋ የ ክርስቲያን ግዛት ማለትም ስለ ኢትዮጵያ ገልጸል፡፡ ይህችም ሃገር የጥቁርን ቀጣይ እድገት ያስመሰከረች የምድርን ረጅም እድሜ ያስቆጠረች ሃገር ናት'' ብሎላታል።

    የናይጄሪያው ናሜንዲ አዚኪዊ፣ የጋናው ኩዋሜ ንክሩማ እና የኬንያው ጆሞ ኬኒያታ በመጀመሪዎቹ የአፍሪካ ነፃነት እንቅስቃሴዎች እንዲሁም በምእራብ ኢንዲንስ ያሉ መሪዎች ማለትም ጆርጅ ፓድሞሬ እና ማርከስ ጋርቬ (ጀማይካ) በድሉ ከፍተኛ የተነሳሽነት ስሜት እንዲያድርባቸው ሆኗል፡፡


ዳግማዊ ምኒልክ በ ኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የፈጠሩት በጎ ሁኔታዎች

ዳግማዊ ምኒልክ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የፈጠሩት በጎ ሁኔታዎች ሁሉ ሲወሱ የሚኖሩ ናቸው።ሀገራችን ለመጀመርያ ጊዜ የ ሚንስትሮች ካቢኔ፣ስልክ፣ባቡር፣ሆቴል፣መኪና፣ ያየችው በ ዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ነበር። ከሁሉ የሚገርሙኝ ግን ሁለት ነገሮች ናቸው።የመጀመርያው ዛሬ ተማሩ በሚባሉ ሰዎች ዘንድ ስለ አካባቢ ጥበቃ ለማስረዳት ብዙ ጊዜ የመፍጀቱን ያህል የ ዛሬ መቶ ዓመት በፊት የነበሩት ዳግማዊ ምኒልክ ለ ወደፊቱ ትውልድ የ አካባቢ ጥበቅ ልማት አስበው በሃርዛፍ ከ አውስትራልያ ድረስ ማስመጣታቸው ና አጀንዳ ብለው መነጋገራቸው ሲሆን ሁለተኛው በ 1988 አዲስ ዓለም ማርያም ሙዜም ስጎበኝ የ ሙዝየሙ አስጎብኚ የነገሩን ነገር ነው። ጉዳዩ አንዲህ ነው-

ዳግማዊ ምኒልክ አንድ ቀን ጠባቂዎቼ በደንብ ይጠብቁኝ አንደሆነ ና አንዳልሆነ ላረጋግጥ ብለው ሌሊት ጋቢ  ለብሰው ይወጣሉ። ግቢውን ሲዞሩ  ጠባቅያቸው ከሩቅ ያየውን ሰው ስላላወቀ ''ቁም!ቁም!'' ብሎ መሣርያውን ያቀባብላል። ምኒልክ ቀልድ ያሉት ነገር ስህተት መሆኑን አውቀው ባለማወቅ አንዳይተኮስባቸው '' አይዞህ ምኒልክ ነኝ....ጌታህ ነኝ አይዞህ....''ይሉታል። ጠባቂውም ከሩቅ ሆኖ ''በምን አውቃለሁ ምኒልክ ተኝቷል'' ይላቸዋል። ወደአርሱ ቀርበው ''ምኒልክ ነኝ አይዞህ ስራህን በደንብ መስራትህን ላይ ነው'' ይሉታል። ተባቅያቸው ይደነግጣል። ''አሁን ተኩሼ ቢሆን ጌታዬን ገድዬ ነበር'' ብሎ ላብ አጠመቀው። ቀጥሎ ግን ተናደደ አሳስተውኝ ቢሆንስ ብሎ ዱላውን አውጥቶ ሁለት ጊዜ መታቸው። ምኒልክ አየፎከሩ አንዴት አንተ ሲሉ ግቢውን ለቆ ወጣ። ጧት ግብር ተበልቶ። ዳግማዊ ምኒልክ ያን ጠባቂ አስጠሩት። በሰራው ሥራ ግዞት አንደማይቀርለት ገምቶ ከፊታቸው ቆመ። ሌሊት የሆነውን ሁሉ አስረድተው ለ ሹማምንቱ ፍረዱ አሉ። ሁሉም ተነስቶ '' ግማሹ አርባ ይገረፍ....ሌላው ይገደል....'' ብሎ ፈረደ። ዳግማዊ ምኒልክ ግን '' ምን አረገ ካለበት የሄድኩበት ሳለሁ ስራውን በሚገባ በሰራ ሰው ላይ ለምን ትፈርዳላችሁ?'' ብለው መሬት ሸልመው ሾሙት።'' አሉን የ ሙዝየሙ አስተዋዋቂ። ቀጥለውም ''የናንተ ዲሞክራሲ  ዱላ አደለም ተናገራችሁኝ ብሎ ፍዳ የሚያሳይ ነው። ያኔ ይህም ተደርግዋል።ይህ ሲፈፀም የነበሩ የ 96 ዓመት የአድሜ  ባለፀጋመኖራቸውን ነገሩን ።የዚህ አይነት ዲሞክራሲ ነበረ!

ጉዳያችን

Saturday, February 21, 2015

ሰበር - እምነትን ከእምነት ጋር ማጋጨቱ ቀጥሏል፣በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ውስጥ 'የእሬቻ' በዓል እንደሚከበር ኢቢሲ መግለጡ ቁጣ ቀስቅሷል።



የአቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ አመታዊ ንግሥገዳሙ የሚገኝበት ተራራ ላይ ያለው ሀይቅ ዙርያ ታቦተ ሕጉ ሲዞር 

ባለፈው መስከረም 15/2007 ዓም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (በቀድሞ ስሙ ኢቲቪ) በአማርኛ እና በኦሮምኛ እንደተለቀቀው ዜና ከሆነ ''በመጪው መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ የእሬቻ በዓል በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ውስጥ ይከበራል ''ይላል።ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከተከበሩት እና ከታፈሩት ገዳማት ውስጥ አንዱ ነው።ገዳሙ ፃድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለኢትዮጵያ እና ለመላው የሰው ዘር የፀለዩበት ቅዱስ ስፍራ ነው።

ይህንን ከ800 ዓመታት በላይ ፀንቶ የኖረ ገዳም ''እሬቻ'' እንዲከበርበት የተደረገበት ዋና ምክንያት እምነትን ከእምነት ለማጋጨት በስርዓቱ የተሸረበ ተንኮል ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው።ከእዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መሰረተ እምነትን የጣሱ ተግባራት ሲፈፀሙ እና ሙስና የሚፈፅሙ የስርዓቱ አጎብዳጆች (በቤተ ክህነቱ ዙርያ 'የጨለማው ቡድን አባላት' በመባል የሚታወቁቱ)  የቤተ ክርስቲያኒቱን ንብረት  እና ገንዘብ መተዳደርያቸው ሲያደርጉት አንዳች እርምጃ ሳይወሰድባቸው አመታት መቆጠራቸው ይታወሳል።

በቅርቡም በርዕሰ አድባራት እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሙዚየም የወርቅ መስቀልን ጨምሮ ሌሎች በቅርስነት የተመዘገቡ ንብረቶች መጥፋታቸው ይታወሳል።ከእዚሁ ጋር ተያይዞ የደብሩ አስተዳዳሪ ቀደም ብለው ሰራተኞችን ሰብስበው ''በሙዚየሙ የሚገኙ ቅርሶች ተሸጠው ለአባይ ቦንድ መግዣ ይዋሉ'' የሚል ሃሳብ አቅርበው በደብሩ አገልጋዮች እና ሰራተኞች ''ታሪክ አጥፍተን ታሪክ አንሰራም'' የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው የገለፀው የሪፖርተር ጋዜጣ ባለፈው ሮብ የካቲት11/2007 ዓም በዘገባው  ''የቤተ ክርስቲያኗ ካህናት፣ ሠራተኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች የደብሩን አስተዳዳሪና ሌሎች ኃላፊዎች ተባብረው ወርቆቹን ማጥፋታቸውን፣ በቤተ ክርስቲያኗ ሠራተኞች ላይ በደልና ብልሹ አሠራር እንዲደርስ ማድረጋቸውን በመግለጽ ተቃውሟቸውን በፊርማ በተደገፈ አቤቱታ ለሚመለከታቸው ሁሉ መላካቸውን'' ይገልጣል። 

ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ላይ የእሬቻ በዓል እንዲከበርበት መገለፁን የዘገበው የማኅበረ ቅዱሳንድረ-ገፅ  በበኩሉ ጉዳዩን አስመልክተው አቡነ ማትያስ ለኦሮምያ ፕሬዝዳንት አቶ ሙክታር ከድር ደብዳቤ መፃፋቸውን ይገልጣል።

ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ታሪክ እና አመሰራረት 

የዝቋላ አቡ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም በ1168 ዓ.ም.ታላቁ ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ በነበሩበት ጊዜ ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ቅዱሳት በሆኑ እግሮቻቸው በመርገጥና በመባረክ በተራራው አናት ላይ በሚገኘው ውብና ማራኪ በሆነው ባሕር ውስጥ ለ1ዐዐ ዓመታት በመጸለይ ከዘለዓለማዊው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማይታበል ሕያው ቃል ኪዳን የተቀበሉበት በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ጽላታቸው የተቀረጸበት ቤተክርስቲያናቸው የታነጸበት በክቡር ስማቸው ገዳም የተመሠረተበት አምላከ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ብርሃነ ረድኤቱን በየጊዜው የሚገልጥበት በሀገራችን ኢትዮጵያ አሉ ከሚባሉት ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማት አንዱ ነው፡፡

የደብረ ዝቋላ ገዳም ከተመሠረተ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርነው የ835 ዓመት እድሜን ያስቆጠረ ታላቅ ገዳም ነው፡፡ የመጀመሪያው መሥራች በውስጡ ልዩ ልዩ ጸዋትወ መከራዎችን በመቀበል ገድላቸውን የፈጸሙበት ታላቁ ጻድቅ አቡ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሲሆኑ እርሣቸው በ14ዐዐ ዓመት ውስጥ በነበረውና በኢትዮጵያው ንጉሥ በአጼ ዳዊት ልጅ በሕዝበናኝ (እንድርያስ) ዘመነ መንግሥት ካረፉ በኋላ ንጉሡ ሕዝበናኝ (ሁለተኛ ስሙ እንድርያስ) በዚህ አምሳለ ደብረ ታቦር በተሰኘ፣ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የማይታበል ሕያው ቃል ኪዳን ከልዑል እግዚአብሔር በተቀበሉበት ተራራ ላይ በስማቸው ጽላት በማስቀረፅ ቤተክርስቲያን በማነጽ ገዳም እንዲመሠረት ካደረጉ በኋላ በሺህ የሚቆጠሩ መናንያን መነኮሳት በውስጡ ለዓለም ሰላም ለሕዝበ ክርስቲያን ይቅርታና ምሕረትን ከእግዚአብሔር እየለመኑ ትሩፋን እየሠሩ መንፈሳዊ አገልግሎትን እያገለገሉ እስከ ግራኝ ወረራ ድረስ ገዳሙን በማስፋፋት ቆይተዋል፡፡

ኋላም ግራኝ መሐመድ የኢትዮጵያን ገዳማትና አድባራት ባቃጠለና ባጠፋ ጊዜ ይህም ገዳም በግራኝ ወረራ መነኮሳቱ ተጨፍጭፈው አልቀዋል፣ ቤተክርስቲያኑም ተቃጥሏል፣ ገዳሙም ፈርሷል፡፡ ይሁን እንጂ ገዳሙ ዘወትር መንፈስ ቅዱስ የማይለየው እውነተኛ የቅዱሳን ቦታ በመሆኑ ሥራውን ባህታውያን ሳይለዩት እስከ ንጉሥ ማህለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ ለብዙ ዓመታት ያህል ጠፍ (ባዶ መሬት) ሆኖ ቆይቷል፡፡
የደብረ ዝቋላ ገዳምን መልክአ ምድር አቀማመጥ ከአየር ላይ ሲታይ  
በኋላም የንጉሥ ወሰን ሰገድ ልጅ የሆኑት ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ የታላቁ ጻድቅ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ መካነ ገድል የሆነውን የዝቋላን ገዳም እንደገና አሳድሰው እንደ ቀድሞው የመንፈሳውያንና የመናንያን መነኮሳት መሰብሰቢያ አድርገው አቋቁመውታል፡፡ ከዚያም በኋላ አጼ ምኒልክ ለገዳሙ መናንያን መነኮሳት መተዳደሪያ ሰፊ ርስት ጉልት ከመስጠታቸውም በላይ የመንፈሳዊ መተዳደሪያ ሕግና ሥርዓቱንም በወቅቱ ከነበሩት መንፈሳውያን አባቶች ጋር ሆነው በመወሰን ያወጡት ሕግ የሚሻሻለው በቅዱስ ሲኖዶስ ተሻሽሎ እነሆ እስከ አሁን ያለው የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያንም አጼ ምኒልክ ያሠሩት ነው፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን አጼ ምኒልክ ለደብረ ዝቋላ ገዳም ብዙ መጻሕፍትና ንዋየ ቅድሳትን የሰጡ ሲሆን አስከ አሁንም በቅርስነት ተጠብቀው ይገኛሉ፡፡

የዝቋላ አቡ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም በታላቅ ተራራ ላይ የተመሠረተ ውብና ማራኪ የሆነ ምን ጊዜም ጸጋ እግዚአብሔር የማይለየውና ንጹህ ጤናማ አየር ያለው በአጠቃላይ ተፈጥሮ ያደለው እውነተኛ መካነ ቅዱሳን ነው፡፡ ወደዚህ ታላቅ ገዳም ለመድረስ ከአዲስ አበባ እስከ ዝቋላ ተራራ 82 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለው ሲሆን የተራራው ርዝመት በመኪና መንገድ 9 ኪ.ሜ. ነው፡፡ በእግር ተራራው ብቻ ከ2 ሰዓት ተኩል እስከ 3 ሰዓት ያስኬዳል፡፡ ይሁን እንጂ የዝቋላ ተራራ ዙሪያውን በደን የተሸፈነ በመሆኑ ተራራውን ለመውጣት ጉዞ ሲጀምሩ ውብና ማራኪ የሆነው የደን መዓዛ፣ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ፣ የቅዱሳን ረድኤት ልብን እየመሰጠ ያለምንም ድካም ከተራራው አናት ላይ ያደርሳል፡፡

ከዚያም ታላቁ ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቀዱስ ለዓለም ሰላም ለኢተዮጵያ ምሕረትን በመለመን )/1ዐዐ ዓመት ሙሉ በውስጡ የጸለዩበትን ባህር ዙሪያውን ጥቅጥቅ ባለ የተፈጥሮ ደንና የባሕር ዛፍ አጣና በሚያካክል ቀጤማ ተከቦ ሲታይ ሰማያዊ ገነትን የሚያስታውስ ምድራዊ ገነት እውነተኛ የጽድቅ ቦታ ለመንፈሳውያን መኖሪያ የተፈጠረ መሆኑንና ታላቅነቱን ያስመሰክራል፡፡ በዚህም የሐይቅ ጸበል ብዙ ሕሙማን ከልዩ ልዩ ደዌያቸው ይፈወሱበታል፡፡
የዚህ ሐይቅ አቀማመጥ ከተራራው አናት ላይ እንደ ገበታ ወይም ሣህን በጎድጓዳ ቦታ ላይ ያለ ሆኖ ዙሪያው በደንና በቀጤማ የተከበበ ነው፡፡ እጅግ በጣም የሚያስደንቀው ይህ ባህር ባልታሰበ ጊዜ እንደ አምፖል ያለ ብርሃን በግምት ርዝመቱ ከ2 እስከ 3 ሜትር የሚደርስ በባህሩ መካከል ሲበራ ማየት በዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ለሚኖሩ መነኮሳት የተለመደ ነው፡፡ 

የብርሃኑም ዓይነት ነጭ ሲሆን ይህ ከላይ የጠቀስነው ዓይነት ብርሃን በመካከሉ የሚቆም ሲሆን በቀጤማው ዙሪያ ደግሞ እንደ አምፖል ዓይነት ብርሃን ባህሩን ከቦት ለብዙ ሰዓት ይቆያል አንዳንድ ቀንም ሙሉ ሌሊቱን ሲያበራ የሚያድርበት ጊዜ አለ፤ ይህን ስንል ለአንባብያን ማመን ያስቸግር ይሆናል፡፡ ነገር ግን የሚጠራጠር ሁሉ በዝቋላ ገዳም ለጥቂት ቀን ከተቀመጠና እግዚአብሔር ከፈቀደለት አይቶ ማመን ይችላል፡፡


ከዚህ በላይ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን አስደናቂ ተአምርና የገዳሙን ይዘት በመጠኑ አቅርበናል፡፡ በዝቋላ አቡ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገደም በየዋሻውና በየጫካው ወድቀው ለዓለም ሰላምን ለሕዝበ ክርስቲያን ይቅርታና ምሕረትን ከልዑል እግዚአብሔር እየለመኑ የሚኖሩ ባህታውያን ያሉበት በብዙ የሚቆጠሩ አረጋውያን አባቶችና እናቶች እንዲሁም አቅመ ደካሞች የሚጦሩበት አምላከ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ብርሃነ ረድኤቱን ሁል ጊዜ የሚገልጥበት ታላቅ ገዳም ስለሆነ ምዕመናን በዚህ ቅዱስ ቦታ በመገኘት የቅዱሳንን በረከት በመቀበል የታላቁ ጻድቅ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የቃል ኪዳናቸው ተካፋይ ትሆኑ ዘንድ እያመላከትን ጽሁፋችንን በዚሁ እናጠቃልላለን፡፡


ጉዳያችን GUDAYACHN

የካቲት 14/2007 ዓም (ፈብሯሪ 21/2015)

የገዳሙ ታሪክ ምንጭ - የአዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ድረ-ገፅ 

Wednesday, February 18, 2015

የየካቲት 12 አርበኞቻችን እና ሰማዕታቱ


ገነተ ልዑል ቤተ መንግስት 

በእዚህ ፅሁፍ ስር የሚከተሉትን ርዕሶች ያገኛሉ 
  • አብርሃም ደቦጭ፣ሞገስ አስገዶም እና ስምዖን አደፍርስ እነማን ናቸው?
  • 'እልል! በሉ' ልዕልት ተወለደች፣
  • የካቲት 12፣1929 ዓም ደም እንደ ጎርፍ፣
  • ሞግስ አስገዶም፣አብርሃም ደቦጭ እና ስምዖን አደፍርስ ፍቅር እስከ መቃብር፣
ጉዳያችን / Gudayachn
የካቲት 12/2008 ዓም (ፈብሯሪ 18/2015 ዓም)

ታሪክ ምን ያስተምረናል?


የካቲት 12 /1929 ዓም አዲስ አበባ ሰላሳ ሺህ በላይ ነዋሪዎችዋ አንዲት ጀንበር ሰማአትነት የተቀበሉባት ቀን ነበረች። ይህ ታሪክ አስተማሪነቱ ዘርፈ ብዙ ነው።የሀገራችን ፖለቲካ የየካቲት 12 አይነት ታሪኮችን ትውልዱ በማስተማር በተለይ ከታሪክ አንፃር ብዙ ቁም ነገር ሊሰራበት ይገባል ለመሆኑ ዛሬ ስማንያ አራት ዓመት አዲስ አበባ ምን ሆነች? ብዙዎቻች ታሪኩን የምናውቀው የሚመስለን ግን አውቀነውም ቁምነገሩን እና አንደምታውን ችላ ያልነው ጥቂቶች አይደለንም። 
የዛሬ ሰማንያ አራት ዓመት አብርሃም፣ሞገስ እ ስምዖን በግራዝያን ላይ ባቀናበሩት ቦንብ አደጋ (ጣልያን አሸባሪ ብሏቸው የነበረ መሆኑን ሳንረሳ) የጣሉበት እና አዲስ አበባ ደም ጎርፍ የታጠበችበት መከራ ቀን፣የካቲት 12/1929

አብርሃም ደቦጭ፣ሞገስ አስገዶም እና ስምዖን አደፍርስ እነማን ናቸው?


 አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1936 (1929 ዓም )  ዓለም ፖለቲካ ብዙ አዳዲስ ክስተቶች የታዩበት ነበር።

- የጣልያኑ ፋሺሽት መሪ ሞሶሎኒ  ሮማ 'ኤምፓየር' አዲስ መሬት   አዲስ አበባን መያዙን  ያሳወቀበት፣ ቀደም    ብለው ተግባሩን  በስውር ሲደግፉ የነበሩ ሀገሮች ማንነታቸው የለየበት፣
 - ብሪታንያ ዜና አገልግሎት' ቢቢሲ' የመጀመርያ ቴሌቪዥን ፕሮግራሙን  የጀመረበት፣ 
 - አሜሪካው ፕሬዝዳንት  ሩዝቬልት ሁለተኛ ጊዜ የተመረጡበት
 - ጃፓን ባህር ኃይል ቻይናን ሻንጋይ ክፍለ ሀገር የወረረበት  እ ባጠቃላይ ጊዜው ዓለም ወደ ሁለተኛው ታላቁ ጦርነት ለመግባት አራት አመታት ብቻ ቀርቷት የምትታትርበት ጊዜ ነበር።

አብርሃም ደቦጭ እ ሞገስ አስገዶም ሐማሴን አና አካለጉዛይ (አሁኗ ኤርትራ)ተነስተው በፋሺሽት እጅ የወደቀችው የሀገራቸውን ኢትዮጵያ አርበኞች ሊቀላቀሉ መጡ።
ከለበሱት ልብስ ውስጥ ኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ አጥፈው ይዘዋል።ህልማቸው፣ሳጋቸውን እየተናነቀ የሚይዛቸው ሀገራቸው መከራ እረፍት ነሳቸው።


በወቅቱ ከነበሩት ትምህርት ቤቶች ጣልያንኛ ተምረው ስለነበር ቅኝ ግዛት ችግርን ሀገራቸው ኢትዮጵያ ላይ የሚያመጣውን አንደምታ ጊዜው ፖለቲካ ጋር አዛምደው መረዳታቸው ሌላው የእግር ውስጥ እሳት ነበርእዚህ ጊዜ ነበር እንደነሱ በሀገሩ ጉዳይ ውስጡ ይንተከተክ የነበረውን ስምዖን አደፍርስን  ያገኙት።

ስምዖን አደፍርስ ''በመናደድ ብቻ መቆም የለብንም  ወሳኝ የሆነ ሥራ መስራት አለብን ፋሽሽትን ደሞ ትጥቅ ትግል በቀር ምንም ሌላ መንገድ የሚዋጋው  የለም'' ይላቸው ነበር። ስምዖን አደፍርስ ገና የከተማ መልክ አየያዘች በነበረችው አዲስ አበባ ውስጥ ጅቡቲ ይኖር ከነበረው ወንድሙ በተላከለት ታክሲ  ሥራ ላይ ነበር። ስራው ላይ አያሌ ፋሺሽት ጣልያኖች ግፍ በደል እ  ሃገሩ የወደፊት እጣ ሲያስበው ንዴት ፣ውርደት አልገዛም ባይነት አንድ ላይ ተደባልቀው ውስጡን አናውጠውታል። ይህን ስሜት ይዞ ነበር ሌሎቹ ሀገራቸው  ኢትዮጵያ ፍቅር ያንገበገባቸውን ሁለቱን ወጣቶች አብርሃም ደቦጭ  ሞገስ አስገዶምን ያገኛቸው።

እልል! በሉ ልዕልት ተወለደች

አብርሃም፣ሞገስና ስምዖን አዚህ ሃሳብ ላይ ሳሉ ነበር ሞሶሎን ኢትዮጵያ ሹመኛ ግራዝያን'' ልእልት ተወለደች ተሰብሰቡቸርነቴን ተመልከቱ ላብላችሁ፣ላጠጣችሁ''ብሎ አሁኑ ስድስት ኪሎ ዩንቨርስቲ የያኔው አፄ ኃይለስላሴ ገነተ ልዑል ቤተመንግስት አዲስ አበባን ሕዝብ የጠራው። ይህ አጋጣሚ እነ አብርሃም ታላቅ አጋጣሚ ሆነ። ድግሱ ላይ ንግግር እንደሚያደርግ  የሚጠበቀው ግራዝያን ላይ የእጅ ቦንብ ወርውረው መግደል የሚል አቅድ አዘጋጁ።እዚህ ሃሳብ ደግሞ እጅ ቦንብ አጠቃቀም መማር ያስፈልጋል።ስምዖን ደጃዝማች አፈወርቅ ወታደሮች በድብቅ አንዲያስተምሯቸው ሁኔታውን አመቻቸ። በየቀኑ ወደ ስፍራው አዲስ አበባ ውጭ ከሁለት ሰዓት በላይ በታክሲው  እየወሰደ አስተማራቸው  ቀኑ ደረሰ።በአቅዳቸው መሰረት ሞገስ እ አብርሃም ግራዝያንን ቦንብ ገደሉ በሁዋላ አሁኑ ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስትያን አጥር በኩል ይዘሉና ቆሞ  የሚጠብቃቸው ስምዖን ታክሲ ውስጥ ገብተው አዲስ አበባ መውጣት ቀጥለውም ሰሜን ሸዋ ላይ በውጊያ ላይ ካለው ራስ አበበ አረጋይ አርበኛ  ጦር ጋር መቀላቀል እ መዋጋት የሚል  ታላቁ አቅድ ብለው መከወን ተግባራቸው ሊሆን' ቃል ለምድር ለሰማይ 'መሀላቸው  ነበር።

የካቲት 12፣1929 ዓም ደም እንደ ጎርፍ

የካቲት ከገባ ገና አስራ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።የ አዲስ አበባ አየር ደመናማ ነበር። የተለመደው በልግ ዝናብ ሊመጣ ዳር ዳር የሚል ይመስላል። አዲስ አበባ መንገዶች ጣልያን ወታደሮች ይታመሳል። ሰሜን ሸዋ ላይ የሚዋጋው አንዳንዴም አዲስ አበባ መግብያ በር ደረሰ እየተባለ የሚወራለት  አርበኛው ራስ አበበ አረጋይ ሰራዊት ጠጅ ቤቱ በ ቅኔ አዘል ግጥም ይሞገሳል። ቅኔው የገባቸው ባንዳዎችም አዝማሪውን እየጠቆሙ ፍዳውን ያሳዩታል። አዝማሪው ገና አለ ገና በሚል መልክ ውግያው ይቀጥላል የሚል ቃና ያለው ግጥም  ያንቆረቁራል-

 '' የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ፣
  ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ''

እየተባለ ሴት ወንዱ ውጊያ የተዘጋጀበት አርበኛ ሆኖ መሞት የተናፈቀበት  ጊዜ ነበር። ስድስት ኪሎ የያኔው ቤተመንግስት አሁኑ ዩንቨርስቲ አዲስ አበባ በግድም በውድም በተሰበሰቡ ባብዛኛው ሴቶች ሕፃናት ተሞላ። እብሪት የተሞላበት ግራዝያኒ ንግግር ተጀመረ። በንቀት ያየው ሕዝብ ላይ ስለ ''ታላቂቱ ጣልያን'' መደስኮር ጀመረ። ግን ብዙ አልቆየም አብርሃም እ ሞገስ ሕዝቡን ጥሰው ከፊቱ ደረሱ ሰባት ቦንቦችን አከታትለው ወረወሩበት፣ግራዝያን ቆሰለ፣ አየር ኃይሉ ኃላፊ ተገደለ። አብርሃም እ ሞገስ ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስትያን በኩል ባለው ቤተመንግስቱ ጋራ  አጥር ዘለው ወጡ እ ታክሲ ይዞ ወደሚጠብቃቸው ስምዖን ገሰገሱ፣ ስምዖን በታክሲ ወጣቶቹን ይዞ ነጎደ፣ እንጦጦ ተራራ ላይ ውጥተው አዲስ አበባን ቁልቁል አይዋት፣ ግራዝያን በቆሰለበት ሆኖ አዋጅ አውጆ ለካ አዲስ አበባ ወንድ ሴት ሕፃን አዋቂ ሳይባል ጥይት፣በ አካፋ እ ዶማ በተገኘው ሁሉ መፈጀት ተጀምሯል።

ሶስቱ ወጣቶች ተቃቅፈው ተላቀሱ።ጊዜው እስኪመሽ ጠበቁ እ ስምዖን ወደ ደብረሊባኖስ ይዟቸው ነጎደ።ለ ሰሜን ሸዋ ራስ አበበ አረጋይ ቅርብ የሆነችው -ደብረሊባኖስ አመቺ መስመር እንደሆነች ሁሉም አምነውበታል። ስምዖን ተልኮውን ፈፅሞ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ። አብርሃም ሞገስ ራስ አበበ አረጋይ ጦር ጋር ተቀላቀሉ።

የካቲት አስራ ሁለት ቀን አዲስ አበባ ብቻ ሰላሳ ሺህ በላይ ነዋሪዎችዋ ሰማአትነት ተቀብለዋል። ብዙ የሚቆጠሩ ቤቶች ተቃጥለዋል። ግድያው በመንገድ ላይ የተገኘ ማንኛውም ሰው ላይ ሲሆን ለመግደል  የሚፈለገው መስፈርት ኢትዮጵያው መሆኑ ብቻ ነበር።



አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ የሚገኘው የካቲት 12 የሰማዕታት ሃውልት

ሞግስ አስገዶም፣አብርሃም ደቦጭ እና ስምዖን አደፍርስ ፍቅር እስከ መቃብር 

ስምዖን አብርሃም እ ሞገስን ደብረሊባኖስ ወደ ሰሜን ሸዋ መንገድ ከሚያውቃቸው አርበኞች ጋር አገናኝቶ ተመለሰ።ብዙም አልቆየ ፋሽስቱ ጥቁር ለባሾች ተይዞ ብዙ መከራ እና ስቃይ ተገደለ። የታሪክ ምሁራን እንዳስቀመጡት ስምዖን እጁም ሆነ እግሩ ጥፍር በጉጠት እየተነቀለ ጣቶቹን እየሰባበሩ አሰቃይተው ገደሉት።

አብርሃም ደቦጭ እ ሞገስ አስገዶም 

አብርሃም ደቦጭ ሞገስ አስገዶም ራስ አበበ አረጋይ አርበኞች ጦር ጋር ከተቀላቀሉ በኃላ ራስ አበበ አረጋይ ልዩ እንክብካቤ እንዲያገኙ አደረጉ።ቆይተው ግን የነበራቸውን ትምርት ደረጃ በመረዳት ሀገር ውጭ ወጥተው ሀገራቸው ቢሰሩ ይጠቅማሉ ብለው በማሰብ ስንቅ እ ገንዘብ ጋር ወደ ሱዳን እንዲሄዱ መከሯቸው። ሆኖም  ግን ጉዞአቸው ላይ ሱዳን ሊገቡ ትንሽ ሲቀራቸው  ፎቶዋቸው ገጠር ባሉ ፋሺሽት ወታደሮች ሁሉ ተናኝቶ ነበርና ፋሺሽቶች  ተይዘው በስቅላት ሰማዕት ሆኑ።በኃላ ግን አፄ ኃይለሰላሴ ሱዳን በኩል ጣልያንን እንግሊዝ ሰራዊት ጋር ሆነው ድል ሲያደርጉ አብርሃም እ  የሞገስ አስከሬን ተቆፍሮ ወጥቶ አሁን አዲስ አበባ በሚገኘው ቅድስት ስላሴ አርበኞች ሃውልት ስር እንዲያርፍ አድርገዋል።

ዘመኑን ዋጁት
'
ዛሬ ላይ ሆነን ዛሬ ሰማንያ አራት  ዓመታት የነበሩትን ወጣቶች ስናስብ እ ሐማሴን እ አካለጉዛይ እኛ ኢትዮጵያውያን የተለዩ አስመስለው ሊያወሩን ለሚፈልጉ መረብ ማዶም ሆነ ከመረብ ወዲህ ላሉት ባለ ጊዜዎች ትንሽ ጊዜ ወስደው እንዲያስቡ ማረግ ተገቢ ነው።መረብ ማዶውን መረብ ወዲሁ የተለያየው ታሪክ፣በዘር፣ ሃይማኖት አይደለም።ከእዚህ ይልቅ '' ውሸት ሲደጋገም እውነት የመሆን እድል ይኖረዋል'' የሚለውን ብሂል ሁል ጊዜ የሚሰራ የሚመስላቸው ወገኖች በሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ብቻ ነው።

ፅሁፌን ከመጠቅለሌ በፊት አንዲት ሃሳቤን የምታሳርግልኝ ታዋቂው አሜሪካዊውን  ሀገራችን ታሪክ አዋቂ እ ስለ ኢትዮጵያ በመፃፍ የሚታወቁት አማርኛም አቀላጥፈው የሚናገሩት ፕሮፌሰር ዶናልድ ለቪን ከስምንት ዓመታት በፊት ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ በተናገሩት ንግግር ልደምድም።እንዲህ ነበር ያሉት :-''ኢትዮጵያን በአሁኑ ሰዓት የሚያስተዳድሯት የሀገሪቱን  ታሪክ በሚገባ የማያውቁ ናቸው።ስለዚህ የምመክረው ታሪክን በደንብ ይረዱ .......እናንት ኢትዮጵያውያን የችግሮቻችሁ ሁሉ መፍቻ ታሪካችሁ ላይ አለ በደንብ ተረዱት'' ፕሮፌሰር ዶናልድ ለቪን ።



ጉዳያችን Gudayachn

www.gudayachn.com  



ማሳሰብያ - ይህ ፅሁፍ ከአራት ዓመታት በፊት ለመጀመርያ ጊዜ በእዚሁ ገፅ  ላይ ወጥቶ ነበር።በሌሎች ድረ-ገፆችም ከእዚህ ገፅ ተወስዶ ተለጥፎ ነበር።


የፅሁፉ መርጃዎች

፩/ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ  http://www.ethioobserver.net/forgoten_heroes.ሕትም

፪/ኢሳት ራድዮ የካቲት 11/2004 ዓም ዝግጅት

፫/ ግሎባል አልያንስ ኢትዮጵያ  http://www.globalallianceforethiopia.org























በጠ/ሚ/ዐቢይና ሙ/ጥ/ዲ/ዳንኤል ላይ በውሸት ወሬ የዘመቱት ''አፈ-ጊንጦች'' በቴዲ አፍሮ ዘፈን ሊሸሸጉ ሲሞክሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ እየሳቀባቸው ነው።

ጠ/ሚ/ዐቢይ አሕመድ እና ሙ/ጥ/ዲ/ዳንኤል ክብረት በታላቁ የዓባይ ግድብ ምርቃት ቀን። ======== ጉዳያችን ምጥን ======== አፈ ጊንጥነቱ እና የውርደት ካባው ''አፈ ጊንጥነት'' የሚለውን ...