Saturday, November 30, 2013

በእዚህ ዘመን ካሉት ከአዋቂዎቹ ይልቅታዳጊ ህፃናቱ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የተሻለ የሀገር ፍቅር ያንፀባርቃሉ(ቪድዮ)

በእዚህ ዘመን አርቲስቶቻችን በእራሳቸው ምህዋር ውስጥ እየዞሩ ሀገራቸውን ባብዛኛው የዘነጉበት፣ለሙያ፣ለእውነት እና ለሕዝብ ፍቅር ከሚሰሩ ስራዎች ይልቅ ብዙ ብር የሚያስገኙ ስራዎች የተወደዱበት እና በሕዝብ ከመወደድ ይልቅ ከሚሊንየሮች ጋር ሸራተን መታየት የበለጠባቸው ዘመን እየሆነ ነው።እርግጥ ነው እንደ እነ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) አይነቶች በባትሪ ተፈልገው የተገኙ አልጠፉም።ኢትዮጵያ ግን የጥበብ ስራዋ በእዚህ አይነት ደረጃ ህዝብን እና ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ስራዎች የወደቁበት ወቅት አሁን ነው።

እዚህ ላይ የኢትዮጵያ የኪ-ነጥበብ   እድገት እና ውድቀት ትንተና ላይ አይደለሁም።ሕዝብን፣ሃገርን የተመለከቱ ያለፈውን እና መጪውን የሚያማትሩ ስራዎች ግን በፈጣን ገንዘብ አስገኚ ስራዎች ተተክተዋል።ፊልሞች ወጣቶችን በፍቅር ታሪክ በማማለል ተሳክቶላቸው ይሆናል።ወጣቶቹ ወዴት እንደሚሄዱ፣ከየት እንደመጡ፣የጋራ ሃገራዊ እሴታቸው ምን እንደሆነ ግን አይነግሩም።ይህ በጣም ጥቅል እና በወፍ በረር የታየ ሃሳብ ይሆናል።በእዚህ ዘመን ካሉት አዋቂዎቹ ታዳጊ ህፃናቱ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የተሻለ የሀገር ፍቅር ያንፀባርቃሉ።

ለናሙን ከእዚህ በታች ያሉትን የሸገር ራድዮ ለወጣት ሴቶች በራስ መተማመን ዙርያ የሚያስተምርበት ''የኛ'' የተሰኘ ተከታታይ ተውኔት ላይ የሚሰሙ ዜማዎች ናቸው። ቀደም ብሎ የወጣው ''አቤት'' የተሰኘው ዜማ የ2005 ዓም የዓመቱ ምርጥ ዜማ ተብሎ በሕዝብ ተመርጧል።በቅርቡ በተቀረፀው ''እቴጌ'' በተሰኘው ዜማ  ላይ ደግሞ ታዳጊ ህፃናቱ አስቴር አወቀ እንድትሳተፍበት አድርገዋል።ይመልከቷቸው።





Wednesday, November 27, 2013

ሰበር ዜና በሰሜናዊ ኢትዮጵያ በሁመራ ቃፍታ ወረዳ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር የሰነዘረውን ጥቃት ከመንግስት አካል በኩል ተረጋገጠ


በሰሜናዊ ኢትዮጵያ በሁመራ ቃፍታ ወረዳ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ከጋምቤላ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ ጋር በመሆን  የሰነዘረውን ጥቃት የወረዳው የፀጥታ ኃላፊ ገዛይ ዳኘው ለአካባቢው ራድዮ ማመናቸውን ቪኦኤ የአማርኛው አገልግሎት ዛሬ ህዳር 18/2006 ዓም አስታወቀ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሽምቅ ውግያ ሂደቶች ከሰሜናዊ ኢትዮጵያ በኩል እየተሰማ ነው።''የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል'' እና ''የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር'' ያሰለጠኗቸውን ሰራዊቶች ማስመረቃቸውን በእዚሁ በያዝነው ህዳር ወር ላይ ማስታወቃቸው ይታወቃል።

በእዚሁ ወር ኢሳት ለወራት በኢህአዲግ-ወያኔ ሲቀናበር የነበረ ኤርትራ በሚገኙ  በግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል አመራሮች ላይ ግድያ ለመፈፀም የተሸረበ ሴራ መጋለጡ መዘገቡ ይታወቃል።የሴራው ሂደትም ኢህአዲግ-ወያኔ በቁጥር አንድ ያስጨነቀው ጉዳይ ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ ኃይሎች መሆናቸውን ያመላከተ አይነተኛ ማስረጃ መሆኑን ብቻ ሳይሆን የአሁኑ ሂደት ከእዚህ በፊት ከነበሩት ሁኔታዎች የተለየ ነባራዊ ሁኔታ መኖሩን ብዙዎች ይስማማሉ።

ዛሬ ቪኦኤ የመንግስት መዋቅር የትግራይ ምዕራባዊ ዞን ቃፍታ ወረዳ የፀጥታ ኃላፊ ውግያውን ማመናቸውን ለአካባቢው ራድዮ መናገራቸውን ከመግለፁም በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አርበኛ ኑር ጀባን ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸዋል።አርበኛ ኑር ጀባ ስለውግያው ሲናገር  በ24ኛ ክፍለ ጦር ላይ ጉዳት ማድረሱን እና በርካታ ቀላል እና ከባድ የጦር መሳርያዎችን መማርኩን ገልጧል።በነገራችን ላይ ኢሳት በትናንትናው እለት ቀደም ብሎ ዜናውን ማወጁ ይታወቃል።በውቅቱም ጦርነቱ የተደረገው ህዳር 13/2006 ዓም መሆኑ ተዘግቦ ነበር።

ከእዚሁ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን ኢትዮጵያ ውስጥ በሌለበት ፍርድ ቤት ተከሶ የነበረው በአሁኑ ወቅት የግንቦት ሰባት ሕዝባዊ ኃይል አመራር ካሴ ዘመነ ''ከወያኔ ጋር ከአሁን በኃላ የምንገናኘው ቃሊቲ ወይም እስር ቤት ሳይሆን ጦር ሜዳ ነው እዝያው እንገኛኛለን'' ያለውም በእዚሁ በያዝነው ሳምንት ነው።

ዛሬ ግንቦት 19/2006 ዓም ዘግይቶ በወጣ ዘገባ ራድዮ ፋና በድህረገፁ ጥቃቱን አምኗል።

ጉዳያችን
ህዳር 19/2006 ዓም

Monday, November 25, 2013

ኢትዮጵያዊ ቆስሎም እንዲህ ይከበር ነበር።በኮርያ ዘመቻ ላይ ተሳትፈው ለቆሰሉ ሰላሳ የኢትዮጵያ ወታደሮች ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ በተኙበት የጀግና ሜዳልያ ሲሸልሟቸው (ታሪካዊ ፎቶ)

ኢትዮጵያዊ ቆስሎም እንዲህ ይከበር ነበር።በኮርያ ዘመቻ ላይ ተሳትፈው ለቆሰሉ ሰላሳ የኢትዮጵያ ወታደሮች ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ በተኙበት የጀግና ሜዳልያ ሲሸልሟቸው (ታሪካዊ ፎቶ)

በኮርያ ዘመቻ የዘመቱት የኢትዮጵያ ወታደሮች አስከሬንም ሆነ ቁስለኛ 9,252 ኪሎ ሜትሮች ተጉዞ ለሀገሩ አፈር ይበቃ ነበር። ዛሬ ዓለም በሰለጠነበት እና መገናኛ በተስፋፋበት ዘመን ሳውዲ ውስጥ ወገኖቻችን አሳራቸውን የሚያዩት በ 1,900 ኪሎሜትር ማለትም የሁለት ሰዓት ተኩል የአይሮፕላን በረራ እርቀት ላይ ሆነው ነው።


Saturday, November 23, 2013

በዓለም ላይ በሳውዳረብያ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ሰቆቃ ለመቃወም ሰልፍ የከለከለች ብቸኛ ሀገር-ኢትዮጵያ ነች። ይህ እንቅልፍ ያስወስዳል?

አዲስ አበባ ፌድራል ፖሊስ የሳውዲን መንግስት ለመቃወም ሰልፍ የወጡትን ሲደበድብ 

በዓለም ላይ በሳውዳረብያ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ሰቆቃ ለመቃወም ሰልፍ የከለከለች ብቸኛ ሀገር-ኢትዮጵያ ነች።
ኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረብያ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ሰቆቃ አስመልክተው

ሰሜን አሜሪካ 

 - የተለያዩ ግዛቶች

 በአውሮፓ-

በጀርመን፣

እንግሊዝ፣

ጣልያን፣

ስዊድን፣

ኖርዌይ፣

 ካናዳ-

የተለያዩ ግዛቶች 

 አውስትራሊያ


መካከለኛው ምስራቅ 

- እስራኤል፣
- ቤሩት 

አፍሪካ 

 ደቡብ አፍሪካ፣

 ዑጋንዳ ፣

እስያ 

 ደቡብ ኮርያ፣

 በሚገኙ የሳውዳረብያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ሰልፍ አድርገዋል።በለቅሶ በቁጭት እንባ ተራጭተዋል።ኤርትራውያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን አብረው ተሰልፈው ተላቅሰዋል ቁጣቸውን ገልፀዋል።

ቀሪ ሰልፎች ለምሳሌ በቤልጅየም ብራስልስ እና ሌሎችም ሀገሮች ይቀጥላሉ።
በዓለም ላይ የሳውዲን መንግስት ተቃውመው ዜጎች ሰልፍ እንዳይወጡ የከለከለች ብቸኛ ሀገር የጉዳዩ ባለቤት ኢትዮጵያ ብቻ ነች።ሌላ ማንም ሀገር አልከለከለም።

ኢትዮጵያ የሳውዲን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ተቃውመው ሰልፍ የወጡ እንቡጥ እና ለጋ ወጣቶችን፣አረጋውያንን፣አዛውንቶችን በፖሊስ እየደበደበች ብዙዎችን አካለ ስንኩል አደረገች።የቀሩትን  ሰልፉ የተደረገበት ቀን ሳትውል ሳታድር ወደ እስር ቤት ወረወረች።ይህንን የሚቀበል እንዴት አይነት ህሊና ነው?
ኢህአዲግ-ወያኔዎች ሆይ! ይህ ጠረንጴዛችሁ ላይ ያለ ያልተመለሰ ምን ጊዜም ልንረሳው የማንችለው ግን መልስ የሚሻ አጀንዳ ነው።

ጉዳያችን 

ህዳር/ 2006 ዓም 

Friday, November 22, 2013

አስር ጊዜ ከንፈር ከመምጠጥ ኢሳትን መርዳት!


የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን -ኢሳት ከተመሰረተ ገና ሶስት አመታትን ቢያስቆጥርም በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳይ ላይ ቁጥር አንድ ተፅኖ ፈጣሪ ሆኖ ወጥቷል።ዛሬ ዛሬ ኢሳት ባይኖር ኖሮ ስንት ሕዝብ ሊሰማቸው የሚገቡ ጉዳዮች ሳይሰሙ ሊቀሩ የመቻላቸውን ሁኔታ ስንመለክት ኢሳት ወሳኝ መሆኑን እንረዳለን።

በቅርቡ ከተከሰቱት የሙስሊሞች ጥያቄ፣በቤንሻጉል የጉርዳፈርዳ ነዋሪዎች መፈናቀል፣ሰሞኑን በሳውዲ አረብያ በወገኖቻችን ላይ የተፈፀመውን ግፍ ለሕዝብ በማድረስ በኩል ሁሉ የኢሳትን ታላቅ የስራ ክንውኖች የሚገልፁ ናቸው።ኢሳትን  ኢትዮጵያን የሚወድ ሁሉ ሊደግፈው የሚገባ ነው።የመረጃ  መታፈን ቁጥር አንድ ሉዓላዊነታችንን የሚያሳጣን መሆኑን የተገነዘበው ስንት ሰው እንደሆነ አላውቅም።ይህንን ስንረዳ የመገናኛ ብዙሃንን አስፈላጊነት እንረዳዋለን።ይህንን በደንብ የተረዳ የስርዓቱ ደጋፊ ቢሆንም ኢሳትን ለመርዳት ግዴታው ነው ብዬ አስባለሁ።ዛሬ ኢሳት እና ኢቲቪ ለሕዝብ በሚያቀርቡት ይዘት ተለያዩ እንጂ ሁለቱም የህዝብ ንብረት ናቸው።

ነገን አማትረን ስናይ ግን ኢትዮጵያ መንገዷ ሲሰምርላት ትልቅ አለማቀፍ የዜና አውታር እንደሚሆኑ አንጠራጠርም።ለእዚህ ሁሉ ግን ዛሬ ላይ ሆኖ ኢሳትን ማገዝ ከኢትዮጵያውያን የሚጠበቅ ትልቅ ቁምነገር ነው።ኢሳት በውጭ ከሚኖረው ሕብረተሰብ ማግኘት የሚገባውን ያህል እያገኘ አለመሆኑ በተደጋጋሚ የተገለፀ ጉዳይ ነው።አሁንም ጥያቄው ስንቶች በወር ሻይ ሲጠጡ ጉርሻ የሚሰጡትን ሃያ ዶላር በአግባቡ ይሰጣሉ? ነው።በቀን 2 ዶላር ብንሰጥ በወር 60 ዶላር መሆኑን ሳንረሳ ማለት ነው።አሁን የተጠየቀው በትንሹ 20 ዶላር ነው።ኢሳት በመጪው እሁድ ህዳር 15/2006 ዓም (ኖቬምበር 24/2013) ''እሳት የእኔ ነው'' የተሰኘ በቀጥታ ስርጭት ልዩ መርሃግብር አዘጋጅቷል።በዝግጅቱ ላይ በቀጣይነት የሚከፍሉ አባላትን ለማፍራት አስቧል።ቢያንስ ከቤት ሆኖ ይህንን መርሃግብር መሳተፍ ትንሿ ማንም ሰው ሊያደርገው የሚችለው ሥራ ነው።አስር ጊዜ ከንፈር ከመምጠጥ ኢሳትን መርዳት።ደግሞ መርዳት አይደለም ግዴታን መወጣት ነው።

ጉዳያችን
ሕዳር/2006 ዓም







Thursday, November 21, 2013

በሳውዲ አረብያ ያሉ ወገኖቻችን ጉዳይ ብዙ እርቀት መሄድ ይፈልጋል። ገጠራማው የሳውዳረብያ ግዛት የኢትዮጵያውያንን ሰቆቃ እያስተናገደ ነው።



ሳውዲ አረብያ ያሉ ወገኖቻችን ችግር ገና አልተቀረፈም።እስካሁን ባብዛኛው የታየው በከተሞች አካባቢ ያሉት ነው።ቢጮሁ የማይሰማበት ማንም የማይሰማቸው በገጠራማ የሳውዲ ግዛቶች ያሉ ብዙ ሺህ ወገኖቻችን ድረሱልን እያሉ ነው።ከከተማ እየጠለፉ የሚወስዷቸውን እህቶቻችንን የሚደብቁባቸው ቦታዎች እነኚሁ ከከተማ ራቅ ያሉ ቦታዎች ናቸው።

በኢሳት አስተባባሪነት የተመሰረተው ዓለም አቀፍ ግብረሃይል ለሳውዲ ንጉስ፣የደህንነት እና የፖሊስ መስርያቤት ግልፅ ደብዳቤ ፅፏል።ይህ የስራው መጀመርያ ነው።ግብረ ኃይሉ ከዲፕሎማሲ ሙያ ጀምሮ የተለያየ ሙያ ያላቸው ኢትዮጵያውያንን የያዘ ለእራሳችን ችግር መፍትሄዎቹ እኛው ነን የሚለውን ብሂል በተግባር ያመላከተ ድንቅ ጅምር ነው።በቀጣይ ጊዜ ለሚኖሩ የስራ ዝርዝሮች እንደሚኖሩት ይጠበቃል። የእዚህ አይነቱ ግብረ ኃይል በተጠናከረ መልክ በቀጣይነት ሊኖር የሚገባው እና ለሌሎች ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ለሚገዳደሩ ተግዳሮቶች ሁሉ ምላሽ የሚሰጥ እና አቅም የሚያጎለብት እንዲሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ነው።

በሌላ በኩል ወደሀገር ቤት በመንግስት እየተመለሱ መሆናቸውን ኢቲቪ እያሳየ ነው።ስደተኞቹ በሲቪል ሰርቪስ ግቢ በግዝያዊነት ያረፉ እንዳሉ ተነግሯል። ሆኖም ግን በሺህ የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ  ስደተኛ ሃሳሩን ከሚያይባት ሳውዲ አረቢያ መንግስት እስካሁን ሀገርቤት አድርሻለሁ ያለው ቁጥር ግራ እያጋባ ነው።ለምሳሌ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ትዊተር ገፅ እና ኢቲቪ የተናገሩት የተምታታ ቁጥር ነው።ለምሳሌ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ዲና  4,961 ወደ ሀገርቤት አስገብተናል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶ/ር ቴዎድሮስ በትዊተር ገፃቸው ላይ የተመለሱትን ቁጥር 10,707 ናቸው ብለዋል።ዛሬ ኢቲቪ ደግሞ 13,000 ሰው ተመልሷል ብሏል።በዚህን ያህል ቁጥር የአንድ መንግስት ድርጅቶች እንዴት ይለያያሉ? በቁጥር ነገር መቸም መንግስትን ማመን እንደማይቻል ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል።

የችግሩ ግዝፈት ግን ወደ ሀገር የማስገባት ሥራ ብቻ አይደለም። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በገጠራማ የሳውዲ ግዛቶች ውስጥ ይኖራሉ።በአንድ የዓለም ባንክ በአለማችን ላይ በገጠራማ ቦታዎች የሚኖሩ ህዝቦች ቁጥር በሚያሳይ ዘገባው ላይ ሳውዳረብያ በ 2012 ዓም እ ኤ አ ወደ 5ሚልዮን የሚጠጋ ህዝቧ ከከተማ እርቆ ነው የሚኖረው።(http://data.worldbank.org/indicator/SP.RUR.TOTL) እንግዲህ ስንት እህቶቻችን እና ወንድሞቻችን የሚሰማቸው አጥተው በየገጠሩ ሃሳራቸውን እያዩ ነው? ምን ያህል ኢትዮጵያውያን በሳውዳረብያ እንደሚኖሩ የኢትዮጵያ ኢምባሲ የጠራ መረጃ የለውም። አሁን ብዙዎቻችን ትኩረት የሰጠነው እና ስለችግሩ እየሰማን ያለነው በሪያድ እና ጅዳ አካባቢ ነው።በሌሎቹ አካባቢ ያሉት ወገኖች ጋር ለመድረስ ግን ምናልባት ጥቂት ሳምንታት ብሎም ወራት ልፈልግ ይቻላል።

 በሳውዲ መንግስት ላይ አስፈላጊው ዓለም አቀፍ ተፅኖ ለማድረግ ከተቻለ እና ተከታታይ እረፍት የለሽ ወቀሳዎች ከተሰነዘሩ ሳውዳረብያ ወደመሰላቸቱ ብቻ ሳይሆን በሃገሯ ካለባት ውስጣዊ ችግሮች አንፃር ለችግሩ መፍትሄ የማትሰጥበት ምክንያት የለም።ዓለም አቀፉ የኢትዮጵያውያን ግብረ ኃይል ግን ተከታታይ የስራ ሪፖርቶቹን ለሕዝብ እየገለፀ የራሱ የሆነ በጎ ተፅኖ መፍጠሩ አይቀርም። ከእዚህ በዘለለ በሌሎች የአረብ ሃገራት ላሉት ወገኖችም አንድ አይነት ማዕከልን የጠበቀ እርዳታ ለማድረግም ሆነ መብታቸውን እዲያስከብሩ ገንቢ ሃሳቦችን የማቅረብ ብሎም በየሀገራቱ የሚከራከርላቸው አካል ለመመስረት ይችላል።

ከእዚህ በታች የተለጠፈው የሩስያ ቲቪ (RT) ሳውዲን የተመለከተ ልዩ ዘገባ ሀገሪቱ ያለባትን የውስጥ ችግር ያመላክታል።የሀገሪቱን ኢ-ሰብአዊ አያያዝ ብቻ ሳይሆን የመንግስት መዋቅር ጭምር  ወጣቱ ንጉሳዊው ቤተሰብ የነቀፉበት አግባብን ዘገባው ይጠቁማል።



ጉዳያችን GUDAYACHNgetachewb221@gmail.com

The Ethiopian Orthodox Tewahedo Church is in turmoil in Athens, Greece.

His Holiness Abune Mathias I, Patriarch of the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church, met with Greece's Ambassador to Ethiopia, Antonios Sg...