Friday, February 22, 2013

ሃሳቤን እንዳልገልፅ የታገድኩት የ እኔ አውነተኛ ታሪክ

ይህን ፅሁፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ በ እዚህ ሳምንት በማህበራዊ መገናኛ መድረኮች የተጀመረው ''ሃሳብን የመግለፅ መብት ይከበር'' የሚለው ነው። ስለራስ ማውራት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። ነገር ግን ይህ ታሪክ ብዙ በእኔ ትውልድ ያሉ የገጠማቸው እና አሁንም ሃሳብም ከማፈን ጋር የሚመጣው ችግር ዘርፈ ብዙ መሆኑን ለማሳየት ዛሬ ስለ እራሴ ትንሽ ላውራ።

ጉዳያችን ጡመራን መጻፍ ስጀምር ብዙ ቅን የሆኑ ሃሳቦችን ለመጻፍ በማሰብ ነበር።በተፈጥሮዬ ዜጋ መንግስትን ሲቃወም ስርዓት ባለበት መንገድ ከሆነ ነገሮች ይስተካከላሉ እያልኩ የማስብ ሰው ነበርኩ።ዩጋንዳ ሳለሁ  ወደ ሌላ ሃገር የመሔድ እድል (እድል ከተባለ) እና እዛው ሃገር ያገኘሁትን ስራ አቁሜ ወደ ሃገሬ ስመለስ በውስጤ የነበረው ህልም በሃገሬ የልማት ጥናት በመጀመርያ ዲግሪ ደረጃም ሆነ በዲፕሎማ ደረጃ አለመሰጠቱ በጣም ይቆጨኝ ነበር እና ስራ ለማግኘት ትንሽ ጊዜ ብወስድም ትምህርቱ ቢያንስ በሃገር ውስጥ ባሉ ተቋማት ቢስፋፋ ትልቅ ለውጥ ይመጣል በሚል  ተስፋ ነበር ሃገሬ የገባሁት።

ከዩጋንዳ እንደተመለስኩ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የልማት ጥናት ዲፓርትመንት ሃላፊን አንድ ቀን ከቢሮአቸው አነጋገርኳቸው። በተለይ የ ኢኮኖሚክስ ትምህርት በባለ ብዙ ዘርፍ ትምህርቱ የ ልማት ጥናት እየታገዘ  በ አስተዳደር ስራ ከ ክፍለ ከተማ እስከ ቀበሌ ያሉ የልማት ባለሙያዎች በ ዲፕሎማ ደረጃ እንዲማሩ ብታደርጉ ብዬ የዩጋንዳን፣የሩዋንዳን እና የታንዛንያን ተሞክሮ አስረዳሁ።የሚገርመው ነገር በወቅቱ (በ1997ዓም) የ ዲፓርትመንቱ ሃላፊ ወደ ክፍሉ የሚመጡት ግማሽ ቀን ሲሆን ግማሹ ቀን ከዩንቨርሲቲ ውጭ በሚያገለግሉበት የ ኢህአዲግ አጋር ድርጅት ውስጥ ይሰሩ ነበር። ይህ ክፍል የሙሉ ጊዜ ስራ የሚሰራ እና በሙያው በ ፒኤችዲ ዲግሪ የጨረሱ ባለሙያዎች ቢኖሩም ለመስራት ያልቻሉበት ጉዳይ ተከሰተልኝ። 
በእዚህ አላቆምኩም ከ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር ተነጋግሬ  ''የልማት ጥናት (Development Studies) ትምህርት በኢትዮጵያ አስፈላጊነት'' በሚል ርዕስ በ ሳይንስ እና  ቴክኖሎጂ አዳራሽ (በወቅቱ ከብሄራዊ ቲያትር ጀርባ ከ ብሔራዊ ባንክ ፊትለፊት ይገኝ ነበር) ውስጥ የግል ጋዜጦች የ ሪፖርተር ጋዜጣንም ጨምሮ በተገኘበት የ ጥናት ፅሁፍ እና የ ፓናል ውይይት አዘጋጀሁ ።በ ፕሮግራሙ ላይ ከ ግል ኮሌጆች እና ከ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የተገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክፍሎች ስለ ትምህርቱ አስፈላጊነት በተለይ በታችኛው ሕብረተሰብ ደረጃ ላሉ ሁሉ በሰርተፍኬት እና በ ዲፕሎማ ደረጃ ማስተማር ወሳኝ ነው። የልማት ፕሮጀክቶች ከላይ ጥሩ ሆነው ቢሰሩ እንኳን ከታች ያለው አስፈፃሚው አካል ዘርፈ ብዙ የሆነ (multi dimentional) ክህሎት እንዲኖረው ስለ ወጪ እና ገቢ ብቻ ሳይሆን ማወቅ የሚገባው ስለ ማህበራዊውም፣ፖለቲካውም፣በስራው ላይ ስለሚፈጠሩት  ውጭያዊ እና ውስጣዊ ተፅኖዎች ሁሉ መረዳት ይገባዋል የሚለው የትምህርቱ  አስፈላጊነት ዋና ነጥብ ነበር።
ይህንኑ ተከትሎ በወቅቱ ከነበሩት ጋዜጦች  የ ሪፖርተር ጋዜጣ በ ግንቦት 1/1996ዓ ም  በወጣው ዕትም ላይም ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስለቀረበው ወረቀት እና እና ስለ ውይይቱ  ያቀረበልኝ ቃለ መጠይቅ  በፎቶግራፍ ተደግፎ ይገኛል።

አሁንም ይህንን ሃሳብ በሚገባ በፖሊስ አውጭዎች ዘንድ ከግንዛቤ እንዲገባ በነበረኝ ጉጉት የተነሳ ቀድሞ እሰራበት የነበረው የ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ሆነ ሌሎች ባንኮች ላለመስራት ነገር ግን ከልማት ሥራ ጋር የተያያዘ ሥራ መስራት አለብኝ ብዬ በ 1996 መጨረሻ ላይ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በወጣው ማስታወቂያ መሰረት የስራ መደቡ ''የ ሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ኤክስፐርት'' ሥራ በ አዲስ አበባ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ስር በነበረው የአነስተኛና ጥቃቅን ንግድስራ ማስፋፍያ ክፍል ውስጥ ተቀጠርኩ።ከነበሩት ፕሮጀክት ስራዎችን በተለይ በአነስተኛ እና ጥቅቅን ንግድ ዘርፍ ላይ የ ኢህአዲግ ትልቅ የአስራር ግድፈት የታየኝ ያኔ ነው።

አነስተኛ እና ጥቃቅን ንግድ ዘርፍ ለማንኛውም ሀገር ልማት ወሳኝ ነው።በምጣኔ ሀብት ጥናትም ይህ ዘርፍ ብዙ የሰው ኃይል ስለሚይዝ  እና የስራ ዕድል የመፍጠር ችሎታ ብቻ ሳይሆን ወደከፍታኛ ንግድም የማደግ እድሉ ብዙ ስለሆነ በእጅጉ ይበረታታል።ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የወጣለትን ገንዘብ ያህል ውጤት እያመጣ ነው ለማለት ይከብዳል። አዎን ብዙዎች ከእለት ጉርስ አልፈው ለጥሩ ነጋዴነት በቅተውበታል።ጥያቄው ግን በሚልዮን የሚቆጠር ብር በትክክል ሥራ ላይ አለመዋሉ እሙን ነበር።ይህ ብቻ ሳይሆን የሚደራጁት የንግድ ማህበራት የኢህአዲግ ደጋፊ እንዲሆኑ ተፅኖው ከባድ ነው።አንድፍሬ የሚያህሉ ልጆች ለመስራት ብድር ሲጠይቁ ወደፊት ምን እንደሚጠበቅባቸው ያውቃሉ። ቢያንስ በክፉ ኢህአዲግን አለማማት ለበረቱ ደግሞ አባል መሆን መጥቀሙን ለአራዳ ልጆች ግልፅ ነበር። የ 1997 ዓም ምርጫ ዋዜማ ሚያዝያ ሰላሳ ቀን  አንድ ወደ ስድስት ኪሎ አካባቢ ያለ ማህበር (ከ ጉለሌ ክፍለ ከተማ በወሰደው ብድር የሚሰራ) አባላት ሰልፉ ላይ ነበሩ ተብለው በቀጣዩ አመት ብድር ከመከልከል አልፈው የተቀበሉትን ፈተና በወቅቱ የነበረ ሰው ያውቀዋል።ብድሩ ግን የሚያገኙት በኢትዮጵያዊነታቸው እንጂ በኢህአዲግ ደጋፊነት ፈፅሞ ሊሆን አይገባውም ነበር።
የአመለካከት ችግር አለባችሁ  የምንባለው ባለሙያዎችማ እንደጠላት መመልከት ልማድ ነበር።እኛ በአይምሮ የማሰብ መብታችንን  ማንም እንዳይነጥቀን እንሞክር ነበር። የግል ጋዜጣ መያዛችን ያውም በምሳ ሰዓታችን ላይ ብዙ ቅር ያሰኛቸው የነበሩ የስርዓቱ ደጋፊዎች ነበሩ። ለሁለት አመት  በ እዚህ ክፍል  ውስጥ ስሠራ ብዙ ፈተናዎችን አሳለፍኩ። የኢህአዲግን ግድፈት እና ችግር በትክክል እንድረዳም  አደረገኝ።
ቀድሞ እሰራ የነበረበት ሀብታሞች ብቻ የሚመጡበት ባንክ ትቼ  እታች ያለው የሸማነውን ችግር፣የ አነስተኛ ነጋዴውን ብሶት፣ሥራ ያጣው ወጣት ወገኔን እንግልት አየሁት። አንድ ቀን ''የ አመለካከት ችግር አለበት'' ተብዬው  እኔው ላይ የቡድን መሪው አንዲት ወረቀት እንዲፅፍብኝ     እንደተነገረው ነገረኝ። ለምን?አልኩት ''እኔም አላምንበትም ግን የአመለካከት ችግር አለብህ ደግሞ የግል ጋዜጣ ታበዛለህ'' አለኝ። እያፅናና ፃፈብኝ።ግን አላመንኩበትም አለኝ።ይህን የሚለኝ በጣም ስለሚያዝንልኝ እና  ህሊናው ስለከበደው ነበር። በሚቀጥለው ቀን ግቢው ውስጥ ያለ ሰው ሁሉ እንዴት እንዲህ ይደረጋል? አለ። የአለቃዬ አለቃም ሁኔታው አሳዘናቸው።ጠሩኝ እና ''ያ ደብዳቤ እንዳለ ይሁን አኔ ግን የምስጋና ደብዳቤ እፅፋለሁ አሉኝ።'' እሳቸው ደግሞ የምስጋና ደብዳቤ ፃፉልኝ ለእኔ የምስጋና ደብዳቤ ሲፅፉ ግን ለአንተ ብቻ ማለት ስለከበዳቸው ባንተ ሰበብ ለጠቅላላ ለክፍሉ ልጆች በሙሉ አደርገዋለሁ አሉኝ። አደረጉት።የወቀሳ ደብዳቤ ባመለካከት የምስጋና ደብዳቤ በስራዬ ተሰጠኝ።የሚገርመው ነገር የቅርብ አለቃዬ በምስጋናው ደብዳቤ ስላመነበት ማህተም ያደረገው እርሱው ሆነ።አልፈረድኩበትም የኢትዮጵያን ኑሮ የሚያውቅ ያውቀዋል።

በ እዛው ሰሞን የፍትህ ማጣት ስሜት ውስጤን ናጠው።እኔ ለሀገሬ  የማስበው እና እየሆነብኝ ያለው ተለያየ።ፒያሳ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አፀዱ ጋር ቆሜ  አለቀስኩ።በሕይወቴ እንደዛች ቀን አልቅሼ አላውቅም።ከ ቤተክርስቲያኑ ወጣሁ እና ቭኦልስ መኪናዬን  አስነስቼ ወደ ሰፈሬ ነጎድኩ  ሰፈሬ ከመድረሴ በፊት ከነበረው ካፌ ገብቼ ሻይ መጠጣት አማረኝ ገባሁ።ቀድሞ ንግድ ባንክ አውቀው የነበረ ወዳጄ ሲያገኘኝ በደስታ አቀፈኝ።ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀዘኔን እንደሰማኝ ታወቀኝ።'ፍጡነ ረድኤት' የሚለው መዝሙር ትዝ አለኝ።የድሮ ወዳጀ አሁን በወጋገን ባንክ  የክፍል (dipartment) ኃላፊ መሆኑን አጫወተኝ።ባንኩ ያወጣውን የስራ ማስታወቂያም ከያዘው ጋዜጣ ላይ አሳየኝ እና ለምን አታመለክትምም? አለኝ።ከዩጋንዳ እንደተመለስኩ የልማት ጥናት እያልኩ የምጮህለት ጉዳይ በሀገሬ ላይ አንደማይሆን  ከተረዳሁ ሰነበትኩ።እኔ ደግሞ የማላምንበትን የኢህአዲግ አባል ለመሆን አልችልም።(ላመኑበት አባል የመሆን መብታቸውን ባከብርም)።ስለሆነም ወደቀደመው የባንክ ሙያዬ መመለስ የግድ ሆነ።አስቤበት እደውልልሃለሁ አልኩት።በሚቀጥለው ቀን ተመልሶ ቢሮ መሄድ አስጠላኝ።ደወልኩለት እና አመለከትኩ።ለቃለመጠይቅ ተጠራሁ።አለፍኩ። ሌላ ሁለት አመት በደንበል ስድስተኛ ፎቅ ሥራ ተጀመረ።ከሙያው ስነምግባር አንፃር የባንክ ሥራ ዝርዝር አይወራም።ቢያንስ ለጊዜው እዚህ ላይ መግታት ይገባኛል። 

ሆኖም ግን አንዳንድ ሰዎች የምሰጣቸው አስተያየቶች ከባዶ ጥላቻ የሚመስላቸው ካሉ በሥራ አለም የነበረኝን ያህል የኢህአዲግን አሰራር በቅርብ የማወቅ ዕድል እንደነበረኝ እና  ችግሩን የምረዳው ባላየሁት ነገር ከሩቅ የሚመስላቸው ካሉ እንደተሳሳቱ  ይወቁልኝ።

እዚህ ኖርዌይ በጋብቻ እንደመምጣቴ ክፉ ደግ ሳይናገሩ ሀገርቤት እየገባሁ የመውጣት ችግር የሚኖርብኝ ሰው አይደለሁም።አንዳንድ ብሎጎች የስደተኛ መኖርያ ወረቀት ለማግኘት ተብለው የሚከፈቱ እንዳሉ አውቃለሁ።ስደተኘነትን የሚናፍቅ ሰው ማንም የለም።እኔም አልናፍቅም።ነገር ግን በውጭ ሀገር ሲኖር ለሀገር አንዳንድ ሃሳቦችን ማበርከት ይገባል ብዬ 'ጉዳያችን' ጡመራን ጀመርኩ። 
ምስጋና ለምዕራቡ አለም ሰው ሃሳቡን እንዲገልፅ ዕድል በመስጠቱ።ሆኖም ግን ማንም ምንም እንዳይተነፍስ አንቆ እረግጦ መያዝ የሚፈልገው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን 'የጡመራ'  መድረኩን ሲያውከው እና ከ አንድ አመት ወዲህ ደግሞ በመዘጋቱ ኢትዮጵያ ውስጥ በተዘጉ ድህረገፆች መክፈቻ በኩል ከሚያነቡት በቀር ለተቀረው ሰው እንደማይነበብ ብዙ ወዳጆቼ ይነግሩኛል። ሆኖም ግን ብዙ ጊዜ ያዝ ለቀቅ ይደረግ ስለነበረ እና ደግሞስ 'ጡመራዬ  ታገደች' ብሎ ማውራት ምን ጥቅም አለው?የሚለው ሃሳብ ያይልብኝ ነበር እና ብዙ ማለቱ አላስፈላጊ ሆነ።ደግሞስ የስንቱ ሊቃውንት ጡመራ ታግዶ የእኔ ማን ሆና ይጮህላታል?ብዬ ማሰበም አልቀረም።ሰሞኑን ''የመናገር ነፃነት ይለቀቅ'' የሚለው ዘመቻ ሲጀመር ግን ''እኔን ያየህ አትቀጣ'' ለማለት ወሰንኩ።''ተቀጣ'' አደለም አትቀጣ ተስፋ አትቁረጥ ነው የምለው።የታደለ መንግስት መንገድ ላይ ከምለፈልፍ እብድ ይማራል።ያልታደለ ደግሞ ሃሳብ የመግለፅ ነፃነት አግዶ እንደጨለመበት ያሸልባል።

ባጠቃላይ የእኔ አይነት በ ሺህ የምትቆጠሩ የሀገሬ ዜጎች እንደኔ ይህን ለሀገሬ ብሰራ ብላችሁ ብትነሱ፣ህልማቸሁ ሁሉ የ ኢህአዲግ አባል ባለመሆናችሁ ብቻ የሚሰማችሁ ብታጡ፣አባል ለመሆን ደግሞ ያላመናችሁበትን ለመምሰል ቢያቅታችሁ፣ በአንድም በሌላም ከሀገር ወጥታችሁ ሃሳቤን በ ጡመራ መድረክ ልግለፅ ስትሉ ሀሳባችሁ ወደ ወገናችሁ እንዳይደርስ ብትታገዱ ተስፋ አትቁረጡ።

ይብቃኝ

ጌታቸው

ኦስሎ   

Thursday, February 21, 2013

የ ፓትርያሪክ ስየማ -''ሰኞ ተወለድኩ ማክሰኞ እንጨት ለቀማ ሄድኩ''

የ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተከርስቲያን በማዕበል በተሞላው አለም ውስጥ ከወድያ ወዲህ እየንተንገላታች እነሆ የ ሁለትሺ አምስት ዓመተምህረትን ፆመ ነነዌ ልትቀበል ቀናትን እየቆጠረች ትገኛለች። ወደ ግማሽ መቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ምዕመናኗ  እንደ ሌላ እምነት ተከታዮች ሁሉ በሀገሪቱ የሚከሰቱት ፖለቲካዊው፣ማህበራዊው እና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮች  በ እጅጉ እየጎነትሏቸው አንዳንዴም  የመኖር ትርጉሙ ግራ እስኪያጋባቸው ድረስ  በፈተና ላይ ፈተና እየተጫናቸው ወርሃ የካቲትን ማጋመስ ይዘዋል። ብዙሃኑ ሕዝብ (ትኩረቴ የ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምዕመን ላይ መሆኑ ልብ ይባልልኝ) እንዲህ በመምሸት እና በመንጋት መካከል ልዩነቱ እስኪጠፋው ድረስ ይባክን እንጂ በሌላው ጎን ግን የሚታየው መምነሽነሽ ግርምትን ይፈጥራል።ይህ የመኖር ጥያቄ ገዝፎ እና አድጎ በ ቤተክርስቲያኒቱ የአንድነት እርቅ ሂደት ላይም ሆነ መንግስት ''ይደልዎ'' በሉ እያለ በሚያስፈራራበት የ አዲስ ፓትርያሪክ ስያሜ ላይ ብዙ አድርባዮችን አፍርቷል።አቦይ ስብሐት የቤተክርስቲያንቱን ችግር ለመፍታት ከመድከም ይልቅ እንደፈለጉ እንዲናገሩ የአድርባይ አባቶች መብዛት ተመችቷቸዋል።


የ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያሪክ ፅህፈት ቤት 

የአቦይ ስብሐት ለእርቅ የተነሱ  አባቶች ''ይሰቀሉ'' አንደምታ 


በመንፈሳዊ አለም ውስጥ ብዙ የዋሃንን ማግኘት ይቻል ይሆናል።በፖለቲካው አለም ግን በተቃራኒው ብዙ ብልጣብልጦች ተትረፍርፈዋል።በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የአባቶች እርቅ ሂደትም ሆነ የመንግስት ፓትርያሪክ ስየማ ሂደት ላይ የታዩት አመለካከቶች የእነኚህ ሁሉ ድምር ሆኖ ነው የተሰማኝ።አንድ ጊዜ አንድ ቀድሞ በኢህአዴግ አቀንቃኝነት የሚታወቅ እና የድርጅቱን ባህሪ በደንብ የተረዳ ሰው የተናገረውን እዚህ ላይ መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል።ለግለሰቡ የቀረበለት ጥያቄ ''ለምንድነው ኢህአዲግን ተቃዋሚዎች በሚገባ ሊቃወሙት ያልቻሉት? ለምንስ አላሸነፉትም?'' የሚል ሲሆን የመለሰው መልስ '' ኢህአዲግ በውጊያ እየገደለ ነው አዲስ አበባ የገባው የኢህአዲግ ተቃዋሚዎች አመራሮችን ፐርሰናሊቲ ብንመለከት በጎ በማድረግ፣በማስተማር፣ወዘተ ህይወታቸውን ፈጅተው ፍትህ ሲጎድል የተነሱ ናቸው።ለምሳሌ ፕሮፌሰር አስራትን ውሰዱ እኚህ ሰው እድሜ ልካቸውን ሁሉ በህክምና ሰው ሲያድኑ ነው የኖሩት እኚህ ሰው እንዴት ነው የኢህአዲግ ተቃዋሚ ሆነው ኢህአዲግን የሚገዳደሩት ኢህአዲግ የሚመጥነው ተቃዋሚ አላገኘም።የሰብአዊ መብት ለ ኢህአዲግ ምኑ ነው?----'' ማብራርያው ይቀጥላል።ቤተክህነቱ ውስጥ ሰርገው የገቡት የመንግስት አፈቀላጤዎች እና በአገልጋይ ካህናቱ መካከል ያለው ልዩነት ይሄው ነው።


በቤተክህነቱ ጉዳይ ውስጥ እንደፈለጉ የሚናገሩት  አቦይስብሐት ''ለእርቅ ያሰቡም ሆነ የደከሙ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች መሰቀል ይገባቸዋል'' ብለው ሀገርቤት ለሚታተም መፅሄት ሲናገሩ የቤተክህነቱ ሰዎች አራትኪሎ ሻይ እየጠጡ በየዋህነት ይስቁ ነበር። የሃይማኖት ሰዎች እምነት ስላላቸው ሰዎች ሁሉ እነሱ በሚያስቡት መጠን ደጎች ይመስሏቸዋል።አቦይ ስብሐት ሰዎችን ያውም ለእርቅ የተነሱ የቤተክርስቲያን አባቶችን ''መሰቀል''ይገባቸዋል ሲሉ ከልባቸው እንደሆነ የሚረዳላቸው ምናልባት የተሰቀለ እና ነፍሱ በአፀደ ነፍስ ያለ ብቻ ነው።እሳቸውም አሰቃቀሉ በእንጨት ይሁን በገመድ በኃላ በኮሚቴ የሚወሰን ስለሆነ ወደ ዝርዝር የ አሰቃቀል ሂደት አልገቡም።በእዚህ በኩል አንድ ''ደግነት'' ታይቶባቸዋል። 

አቦይ ስብሐት የሚያህል ከሱዳን እስከ ትግራይ ቀጥሎም 'አዲስ አበባ በደርግ ዘመን እየገቡ ይወጡ ነበር' የሚባሉ ሰው ስለ ቤተክህነቱ መናገር የሚገባቸውን መርጠው መናገር አቅቷቸው የሚመስለው ካለ እርሱ እንደተታለለ ይወቅ። አቦይ ስብሐት ይህን ያሉት የመንግስት የፓትርያርክ ስየማ ከመገለፁ በፊት በቤተክርስቲያኒቱ ዙርያ ያሉትን ከአባቶች እስከ ማህበራት ዝም ለማሰኘት ነው። የሚገርመው ነገር ይህን የተባሉ አባቶች በግልፅ ምላሽ መስጠት የሚገባቸው የነበረ መሆኑ እና  አሁንም ቢሆን አለመርፈዱ ይሰማኛል። አንድወቅት አቶ ተፈራ ዋልዋ ''የ ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የነፍጠኞች አስተሳሰብ ያላት ነች'' አዘል ልንግግር ተናግረው በውቅቱ የነበሩት የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች እስከ ቢሯቸው ድረስ በጥያቄ አጣድፈዋቸው የነበረ መሆኑን እና ይህም ለሌሎች ባለስልጣናት ''ሃይማኖት የህዝብ ሥስ  ብልት ነው'' የሚለው አባባልን በሚገባ የተረዱበት የነበረ መሆኑን አስታውሳለሁ። አይሁድ  ክርስቶስን  ይሰቀል ብለው  ለመፍረድ የጵላጦስን  ምስክርነት እና የህዝብ ዳኝነት ለማግኘት ሲጥሩ ሕጉን ጣሱ እንዳይባሉ ስለተጨነቁ ነበር።አቦይ ግን እርቅ ባሰቡ አባቶች ላይ ''ይሰቀሉ'' ሲሉ ዳኛም ወቃሽም የለባቸውም።የ አይሁድን ያህል ሕግን ለመጠበቅ አለመሞከራቸው አሰቃቂ ነው።



ከፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እረፍት በኃላ የ ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቀድሞ በውጭ ከሚኖሩ  አባቶች ጋር የተጀመረው የእርቅ ሂደት ብዙ ተስፋን አጭሮ የነበረ ለመሆኑ የ ዳላስ ምእመናን ከሀገርቤትም ሆነ እዚያው አሜሪካ ለሚገኙት አባቶች ያደረጉት በእንባ የተቀላቀለ  ልዩ አቀባበል እና መስተንግዶ አመላካች ነው። በእዚህ የእርቅ ሂደት ላይ በተለይ ከአዲስ አበባ ብዙ መደናገጦች እና እርቁን ያለመፈለግ ሂደት ብዙዎቻችን ከጠበቅነው በላይ ታይቷል።ሁኔታው በተለይ የእርቅ ሂደቱ ለሌላ ቀጠሮ ሎስአንጀለስ ላይ ተቀጥሮ ሲለያይ መንግስት ቀደም ብሎ በ ቤተክርስያኒቱ ላይ ያቀዳቸው የቆዮ ድብቅ እቅዶች መበላሸታቸውን ስላወቀ በ ፕሬዝዳንት ግርማ ''ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ ይመለሱ'' የሚለው ደብዳቤ ላይ ድምፁን አጥፍቶ የነበረ የመሰለው መንግስት ከሎሳንጀለሱ ቀጠሮ በኃላ በግልፅ የ አስታራቂው  ኮሚቴ አባላትን ማዋከብ ያዘ።ለእዚህም ማስረጃ የሚሆነው የ አስታራቂ ኮሚቴው የካቲት 13/2005ዓም የእርቅ ሂደቱን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዲህ የሚል መገኘቱ ነው።
  ''የሰላምና አንድነት ጉባኤው አባላት ፍጹም ሰላማውያን መሆናቸው እየታወቀ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት አብዝቶ መድከም እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ብዙ እንግልት ደርሶባቸዋል።እንደሚታወቀው የዕርቀ ሰላሙን ሒደት ለማሰናከል የፈለጉ ጥቂት አባቶችና “የቤተ ክርስቲያን” ባለሥልጣናት የሆኑ ግለሰቦች ለመንግሥት አካላት የተዘባ መረጃ በመስጠት የሰላም ልዑካኑ ከሀገር በግዳጅ እንዲወጡና እንዲጉላሉ ተደርጓል። ከዚህም ጋር በሰላም ልዑካኑ ስም ከሰላሙ በቀር አንዳችም አጀንዳ የሌለውን ጉባኤያችንን የማይወክል የሐሰት ወረቀት በመበተን ያለስማቸው ስም ለመስጠት ተሞክሯል። ለዚህ ሁሉ ግን የቤተ ክርስቲያን አምላክ ራሱ በጊዜው እንደሚመልስና እንደሚፈርድ ወደፊትም ታሪክ እንደሚያስታውሰው ስለምናምን ሁሉንም በአኰቴት እንቀበለዋለን።''http://www.dejeselam.org/2013/02/blog-post_20.html 


 የ መንግስት የ ፓትርያሪክ ስየማ ''ሰኞ ተወለድኩ ማክሰኞ እንጨት ለቀማ ሄድኩ''


 ከደደቢት ጀምሮ በድብቅ  ተወያቶ በአደባባይ ሌላ በማውራት የተካነው ኢህአዲግ የህወሓት 38ኛ አመት ከመከበሩ በፊት  ''የፓትርያሪክ ምርጫ'' ቀን በቤተክህነት ውስጥ ባሉ ወኪሎቹ አማክይነት አስነገረ። በ እዚሁም መሰረት ''በ ጥቂት ቀናት  ውስጥ ፓትርያሪክ  ይመረጣል።'' መሰል ማስታወቂያ ሲነገር ያላዘነ የቤተክርስቲያኒቱ ልጅ የለም።''ሰፈራችን የዕድር  ሰብሳብያችንን ስንመርጥ  እንዲህ አልተዋከብንም'' ያሉት የአንዲት ምዕመን አገላለፅ የሚያሳየው የሂደቱን እፍትሃዊነት  ብቻ ሳይሆን  ምርጫው ከምርጫነት ወደ የመንግስት ስያሜነት መቀየሩን ነው።በትክክል ሂደቱን የሚገልፀው ካለ ደግሞ 'ሰኞ ተወለድኩ ማክሰኞ እንጨት ለቀማ ሄድኩ' የሚለው  አባባል ብቻ ነው።


 እርግጥ ነው በፓትርያርክ ምርጫ ዙርያ የሚነሱ ብዙ ተቃራኒ ሃሳቦች አሉ።ከ እነዚህ ውስጥ 
- ገና ለገና አባቶች አይታረቁም እና ቤተክርስቲያን ካለ መሪ ስንት አመት ልትጠብቅ ነው?
- ቤተክርስቲያን በብዙ መከራ ውስጥ እያለች ስንት የሚሰራ ሥራ እየጠበቃት በፓትርያርክ ጉዳይ ላይ መነታረክ ይገባልን?
- አቡነ ጳውሎስ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ ይህን ያህል ያልተናገሩ ሰዎች ለምን ዛሬ ከሀያአንድ አመት በኃላ ጉዳዩን ያነሳሉ?
- ቤተክርስቲያን ወትሮም በንጉሱም ሆነ በ ደርግ ዘመን የመንግስትን ይሁንታ ያገኙ ናቸው ፓትርያርክ የሆኑት ምነው ዛሬ ተጋነነ?
- አሁን የሚፈለገው የቤተክርስቲያንቱን ችግሮች በተለይ የገንዘብ አስተዳደር እና የሙስናን ችግር የሚፈታ ፓትርያርክ ከተገኘ ቅድምያ እርሱን መፍታት እና ሌላውን በሂደት መመልከት ተገቢ ነው የሚሉ እና ሌሎች አስተያየቶችን መጥቀስ ይቻላል።


በተለይ በአንዳንድ ድህረገፆች ላይ የምዕመኑ ዝምታ ምንድነው? የሚሉ ብዙ ጥያቄዎች ከመነሳታቸውን አንፃር በመንግስት የፓትርያርክ ስየማ ጉዳይ ላይ  የ ምእመናንም ሆነ የአባቶች አመለካከት ከሚከተሉት አስተሳሰቦች አንፃር እንደሚሆን እገምታለሁ።እነርሱም-

ሀ/ ለመንግስት ካላቸው ታማኝነት አንፃር

መንግስት ያለው ሁሉ ልክ ነው ብሎ ከማሰብ። እነኚህ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ቢሆኑም የመንግስትን መኖር ከእነርሱ መኖር ጋር አስተሳስረው የሚኖሩ ናቸው፣

ለ/ ከወንዛዊ ስሜት በመነጨ

ሰውን በሰውነቱ እና በሚያደርገው በጎ ሥራ መለካት ያቃታቸው መንፈሳዊ የሆኑ ሲመስላቸው፣ ግን በወንዛዊ ስሜት የተዋጡ፣ በቤተክርስቲያኒቱ የተለያየ የስልጣን ተዋረድም ሆነ ምዕመናን ብሎም ማህበራት ውስጥ ሁሉ ሳይቀር መኖራቸው እሙን ነው።ያፈጠጠ እውነትን ለመናገር እንቅ ስቃሴ  ለማድደርግ ደካማ ''የወንዜ'' ስሜት ታስቸግራቸዋለች።

ሐ/ እግዚያብሔር የፈቀደውን ያድርግ የሚሉ

 እነኝህ መንፈሳዊ ናቸው ግን በብዙ የኑሮ ውጣውረድ ውስጥ የቤተክርስትያኒቱ ጉዳይን አጀንዳ አድርገው ከመወያየት ወይንም መፍትሄ ከመሻት ይልቅ ''እግዚአብሔር የፈቀደውን ያድርግ'' የሚሉ ናቸው። ''ንስሐ አለ ተብሎ ኃጢያት አይሰራም፣ወጌሻ አለ ተብሎ ገደል አይገባም'' እንዲሉ የሚሉትን ያህል የ እምነት ደረጃ ሳይደርሱ የቸልተኝነት መሸፈኛ እግዚያብሄር መሆኑ ቅር ያሰኛል።

መ/ ምጣዱ ከሚሰበር አይጧ ትለፍ  የሚሉ

እነኚህ ስለ በተክርስቲያኒቱ ችግር ከስር የተረዱ፣ሌላው የማያውቃቸው ችግሮች ባላቸው ቦታ እና የመረጃ ምንጭነት የሚጨነቁ፣ለእራሳቸው ብዙ የማይጨነቁ ግን ጉዳዩን እየተከታተሉ ቤተክርስቲያኒቱ  እንደምንም ብላ መፍታት ያለባትን ችግሮች ትፍታ ሌላው የትም አያመልጥም ይሚሉ ናቸው። በተለይ  የሚያስጨንቃቸው መንግስት መድቦትም ሆነ ተመርጦ የሚመጣው አባት ሕዝቡን ካስደሰተ፣ሙስና ካጠፋ፣ቤተክርስቲያኒቱ ከመንግስትም ጋር ሆነ ከተለያዩ  አካላት ጋር ይሚገጥሟት ተግዳሮቶችን በጥበብ እና በመንፈሳዊ አፈታት ዘዴ የሚፈታ ከሆነ እዳውገብስ ነው ባዮች ናቸው። 

 የእዚህ ሁሉ መፍትሄ ምን ይሁን?

ከላይ የተወሱት ሁኔታዎች ሁሉ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ነው።የአባቶች የዕርቅ ሂደት ለጊዜውም ቢሆን ቆሟል።መንግስትን ተገን ያደረጉ አባቶች አዲስ ፓትርያሪክ ለመሰየም ቀናት እየቆጠሩ ይገኛሉ።በውጭ የሚገኙ አባቶች ከሀገርቤት የፓትርያርክ ስየማ  በኃላ ምን እንደሚያደርጉ ለጊዜው አልታወቀም። ምናልባት የበለጠ የሀገረስብከት ማጠናከር እና ይበልጥ የሲኖዶሱን ማዕከልነት  የመሳብ ሁኔታ ሊኖር ይችላል።በ እዚህ ሁሉ ፈተና መሃከል የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ሚና ምን መሆን ይገባዋል? ፈታኙ ጥያቄ ነው።እንደ እኔ አስተሳሰብ መፍትሄውን መደረግ  የሚገባቸው እና የማይገባቸው ጉዳዮች ብዬ በመክፈል ለማቅረብ እፈልጋለሁ።

መደረግ የሚገባው ጉዳይ 

- ቤተክርስቲያንን ከመንግስት ጋር ለማጋጨትም ሆነ ከመንግስት እግር ስር እንድትሆን አሳልፈው የሰጡ አካላትን በሙሉ ማጋለጥ እና ከተግባራቸው እንዲታቀቡ ማድረግ፣
- መንግስት እጁ አንዳለበት ፀሐይ የሞቀውን የ ፓትርያሪክ ስየማ ቢያንስ ህዝበ ክርስትያኑ ሳይስማማ፣የዕርቅ ሂደቱ ወግ ባለው ሁኔታ ሳይፈፀም፣ የምርጫ ሂደቱ ግልፅነት፣እርጋታ፣ከሰዎች ሃሳብ ይልቅ የመንፈስቅዱስ ሥራ የሚታይበት እንዲሆን ዕድል ሳይሰጥ እና ቢያንስ ሂደቱ የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንትን አስተያየት ከ ቅዱስ ሲኖዶስ ምእላተ  ጉባኤ ጋር ሳይጣጣም በአንድወር ጥሪ መደረጉን  አበክሮ መቃወም ለወደፊቱም ቤተክርስቲያን ተመሳሳይ ችግር እንዳይገጥማት ዘለቄታዊ ሥራ መስራት፣
- ''ቀድሞም ቤተክርስቲያን የመንግሥታት ተፅኖ ነበረባት አይገርምም'' ለሚሉ የምንኖረው በ ሃያንደኛው ክፍለዘመን መሆኑን አበክሮ መንገር። የቀደመው አሰራር በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ ጋር አብሮ የሚወቀስ እና የሚሞገስ መሆኑን እና የአሁኑን የከፋ የሚያደርገው መንግስት በመንፈስቅዱስ ሥራ ላይ መግባቱ መሆኑ እና የቀደሙት ቤተክርስቲያንን ቢቀርቡ አምነውባት፣ተቆርቁረውላት እና ሊፅድቁባት አስበው እንጂ አልመው እና  አቅደው ህዝብን ለማታለያ እንደ አንድ ስልት የያዙበት ሁኔታ  አለመኖሩን ማሰብ ተገቢ መሆኑን የማሳወቅ ሥራ መስራት እና 
- ቤተክርስቲያኒቱ እና ሀገሪቱ የገጠሟት ችግሮች ተመሳሳይ ባህሪ ስላላቸው እና በ እያንዳንዱ ንዑስ ችግሮች ላይ ከማተኮር በአጠቃላይ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች ላይ አተኩሮ ተግቶ መስራትእና ትውልዱም ለእዚሁ ሥራ እንዲነሳ ማብቃት የሚሉት ሲሆኑ።

መደረግ የማይገባው ጉዳይ


የቤተክርስቲያንቱን እምነት የተከተለ ሁሉ ከቅን በሚሰጣቸው ሃሳቦች ላይ ቀድሞ አለመፍረድ።በተለይ በእዚህ ወቅት በቤተክርስቲያኒቱ ምእመናን መሃከል  የሚኖረው የሃሳብ ልዩነት ወደሰፋ ጉዳይ እንዳያመራ  ወቀሳዎችን ግለሰባዊ አለማድረግ።ለምሳሌ በፓትርያርክ ምርጫ ሂደት ላይ ሂደቱን እና የበተርክስትያንቱን የእርቅ ሂደት ላይ ቅድሚያ የመስጠት አስፈላጊነትን እንጂ ግለሰቦችን አለመውቀስ።ይህ ማለት ጎልተው የሚታዩ ለቤተክርስቲያኒቱ ፈተና የሆኑትን ግለሰቦች  ከማስረጃ ጋር በማቅረብ ጥንቃቄ እንዲደረግ መንገር አስፈላጊ ቢሆንም ለሀገርም ሆነ ለቤተክርስቲያን ብዙ የሚሰሩ ሃብቷየሆኑትን ልጆቿን በሆነ ባልሆነ ለመውቀስ አለመቸኮል።ይህ ልዩነትን የመፍጠር እና የማስፋት ሂደት በተለይ መንግስትን ጨምሮ እጃቸውን በቤተክርስቲያን ላይ ለመጫን የሚያስቡ  ሁሉ  የተካኑበት አካሂያድ ስለሆነ ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባ ይመስለኛል። 


ይቆየን 

ጌታቸው 

ኦስሎ