ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, March 27, 2018

ዶ/ር አብይ አህመድ የኢትዮጵያን መጪ ነባራዊ የፖለቲካ ሂደት ለመቀየር ሊያስቀድሟቸው የሚገቡ አስር ተግባሮች


ዶ/ር አብይ አህመድ 

ጉዳያችን/ Gudayachn
 መጋቢት 19/2010 ዓም (ማርች 28/ 2019)

ዶ/ር አብይ አህመድ ከቀናት የኢህአዴግ ስብሰባ በኃላ የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸውን የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በሁለት ሰዓቱ የዜና እወጃ ላይ ይናገራል ተብሎ ሲጠበቅ ምንም ሳይናገር ማለፉ የመጋቢት 18/2010 ዓም ግርምታ በሕዝቡ ዘንድ ፈጥሮ አመሸ።በእርግጥ ቀደም ብሎ ከቀኑ አስር ሰዓት ጀምሮ የተመረጡ ጋዜጠኞች ተጠርተው መግለጫ እየተጠባበቁ መሆናቸውን እና ኢህአዴግ በስብሰባው ላይ የአቶ ኃይለማርያምን መልቀቅያ መቀበሉን ሸገር በአስራ ሁለት ሰዓት ዜና ላይ በቀዳሚነት አሰምቶ ነበር።ከእዚህ ሁሉ በኃላ ግን ከሁለት ሰዓቱ ዜና በኃላ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በሰበር ዜናነት ዶ/ር አብይ የድርጅቱ ሊቀመንበር መሆናቸውን አስደመጠ። ዶ/ር አብይ በ108 ድምፅ፣ አቶ ሽፈራው በ59 ድምፅ እና ዶ/ር ደብረ ፅዮን በሁለት ድምፅ ብቻ መመረጣቸው ተከትሎ በማኅበራዊ ሚድያ ጭምር ተገለጠ።

ዶ/ር አብይ አህመድ የኢትዮጵያን ነባራዊ ፖለቲካ ሁኔታ መቀየር ይችላሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ጥያቄ ነው።ከእዚህ በፊት ግን መሬት ላይ ያለውን እውነታ ዶ/ር አብይ ወደ ሊቀመንበርነቱ የመጡት በህወሓት በጎ ፈቃድ አለመሆኑ ነው።ህወሓት ለደጋፊዎቹ አቶ ሃይለማርያም የመጨረሻ ከህወሓት ውጭ የሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ እየማለ እና እየዛተ ደጋግሞ ተናግሮ ነበር።ለእዚህም ነበር ዶ/ር ደብረ ፅዮን የህወሓት ሊቀመንበር እንዲሆኑ የፈለገው እና ወደፊት ያመጣበት አንዱ ዓላማም ይሄው ነበር።ሆኖም ግን ይህ ሁሉ ጥረት በህዝባዊ አመፁ ከጥቅም ውጭ ሆኗል።ዶ/ር አብይ አህመድ የድርጅቱ ሊቀመንበር መሆናቸውን ዘግይቶም ቢሆን ለመግለጥ ተገዷል።

ዶ/ር አብይ ነባራዊውን የፖለቲካ ሁኔታ ለመቀየር ይችላሉ? ለሚለው ጥያቄ ዶ/ር አብይ የመቀየር እና ያለመቀየር እድላቸው የሚወሰነው በሚመርጡት የትኩረት አቅጣጫ የሚወሰን ይሆናል።ኢትዮጵያ በህወሓት ለለውጥ አለመዘጋጀት ምክንያት አሁን ያለችበት ሁኔታ ወደ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ልትገባ ጫፍ ላይ ያለችበት ወቅት ነው። በኃይል የሚመጣ የለውጥ ሂደት ይዞት የሚመጣው የስልጣን መመንጨቅ ተከትሎ የሚመጣው የደም መፍሰስ እና የሚፈጥረው መቃቃር፣ምጣኔ ሃብታዊ ድቀት እና ቀውስ ሁሉ በአደጋ ያልተከበበ ነው ማለት አይቻልም።በእዚህ ላይ የጎሳ ፖለቲካው እንደ ነዳጅ ሀገር  እንዲያቀጣጥል  እየተርከፈከፈ ነው።የጎሳ ፖለቲካ በምጣኔ ሀብት በተቃወሰ እና የሀብት ክፍፍል አድሏዊ በሆነበት ማህበረሰብ ውስጥ ደግሞ ትልቅ ቀውስ እንደሚከተለው ማወቅ ተገቢ ነው። ስለሆነም ዶ/ር አብይ የህዝብ ድጋፍን ተንተርሰው ሊያተኩሩበት የሚገባው በሚከተሉት ስልታዊ  ነጥቦች ላይ ነው።እነኝህ ስልታዊ ነጥቦች በእራሳቸው የጎሳ ፖለቲካውን ሕዝባዊ መሰረት የማሳጣት ተልኮ የያዘ ይሆናል። እነርሱም : -

1ኛ) በጎሳ ፖለቲካ የተጎሳቆለውን ማኅበራዊ፣ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ግንኙነት ወደ ሃገራዊ የጋራ ደረጃ ማድረስ። ይህንንም የፖለቲካ ድርጅቶች ከጎሳ ፖለቲካ ወደ ሃገራዊ አጀንዳ እና አደረጃጀት እንዲቀየሩ ሁኔታውችን ማመቻቸት።ሀገር አቀፍ የሙያ ማኅበራት፣የሰራተኛ ማህበራት እና የዩንቨርስቲ እና ኮሌጅ ተማሪዎች ህብረቶች ሁሉ ከጎሳዊ አደረጃጀት ይልቅ  በሃገራዊ አደረጃጀት እንዲጠናከሩ ማድረግ፣

2ኛ) ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት የመገለል ስሜት የተሰማቸው ክልሎችን ሃገራዊ ሚናቸውን ከፍ ማድረግ እና የታወጀውን አዋጅ መሻር፣

3ኛ) የፍትህ ስርዓቱ፣የመገናኛ ብዙሃን፣ጋዜጦች እና ጋዜጠኝነት ደረጃቸውን የጠበቁ እና ነፃነት ያላቸው ሙያዎች እንዲሆኑ በብቁ የሰው ኃይል ማጠናከር እና በቂ ጥበቃ እና ዋስትና መስጠት፣

4ኛ) ሙስና የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብታዊ፣ማህበራዊ እና መንግስታዊ ድርጅቶች ሁሉ የጎዳ በመሆኑ በሙስና የተተበተቡ ሁሉ ለፍርድ የማቅረብ ሥራ መስራት ለእዚህም ሕዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር እና እርምጃው በሕዝብ የጀርባ ድጋፍ እና ደጀንነት እንዲታገዝ  በማድረግ ወደ ማይቀለበስ ደረጃ ማድረስ፣

5ኛ) የትግራይ ሕዝብ ከህወሓት ይልቅ ኢትዮጵያ እንደምታዋጣ በማሳየት ህወሓት የትግራይ ሕዝብ ዋስትና አለመሆኑን ማሳየት፣

6ኛ) የጦር ሰራዊቱ ከመስመር መኮንኖች ጀምሮ እስከጠራው ድረስ ከላይ በምተገበሩት ተግባሮች ሁሉ በሃሳብ እንዲሳተፍ በሕዝብ መገናኛ ሚድያ አማካይነት ድጋፍ እንዲሰጥ ድምፁን ለሕዝብ እንዲያሰማ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች ማዘጋጀት እና የተናበበ እንዲሆን ማድረግ፣

7ኛ) የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ቃል አቀባይ ከፍተኛ ባለሙያ እና የሚሰሩትን ስራዎች በእየሳምንቱ ለሕዝብ የምገልጡበት መድረክ ማዘጋጀት፣ እርሳቸው በማይመቻቸው ጊዜ በሕዝብ አእምሮ ሊቀር በሚችል መልክ በተክለ ሰውነት፣በአገላለጥ ጥራት እና የሚለውን ወይንም የምትለውን በመግለጥ ሕዝብ የሚያስደምም ወይንም የምታስደምም ቃል አቀባይ መመደብ፣

8ኛ) የሀብት ክፍፍሉ አድሏዊ የሆነበትን መንገድ ለማስተካከል ከአሁኑ መሰረት መጣል።ይህም ስልታዊ በሆነ የቀረጥ ፖሊሲ በሂደት ለውጥ በሚያመጣ መልኩ መሄድ እና 

9ኛ) ኢትዮጵያ በሶስት ወይንም ሁለት ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክር የሚደረግባት ለማድረግ የፖለቲካ ድርጅቶች አደረጃጀት ላይ አቅጣጫ መስጠት፣

10ኛ) ጠንካራ እና ታማኝ የምርጫ ቦርድ መመስረት እና ከላይ የተጠቀሱት ስራዎች ወደ ኃላ እንዳይመለሱ ዋስትና የሆነ ስልታዊ አደረጃጀት ላይ መስራት እና የህዝቡን አቅም ማጎልበት የሚሉት አስፈላጊ ስራዎች ናቸው።

ባጠቃላይ ዶ/ር አብይ ሁሉን ሥራ እንዲሰሩ አንጠብቅም።ያለባቸውን ተግዳሮት ይታወቃል።ሆኖም ግን ኢትዮጵያ በኃይል በሚፈጠረው ቅራኔ ወደ አልታወቀ መንገድ እንዳትሄድ የሚያስፈልጋትን የሽግግር ወቅት ላለፉት 27 አመታት የተጎሳቆሉት ዋና ዋና እሴቶቻችንን ማስመለስ እና ማጠናከር በእራሱ የህወሓትን የጎሳ ፖለቲካ የሚያደክም ብቻ ሳይሆን ነገ ለሚመጣው ዘገምተኛ ወይንም ፈጣን ለውጥ ዋስትና መስጠት ነው። ዶ/ር አብይን ብዙ ከባድ ነገሮች አንጠብቅም ከላይ የጠቀሱትን በፅኑ መሰረት ላይ ካስቀመጡ ትልቅ ሥራ ሰሩ በማለት ታሪክ ያስታውስዎታል።

ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments: