ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, March 20, 2018

አሁንም ትኩረት የመኖርያ ፍቃድ ላላገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች

ጉዳያችን/Gudayachn
መጋቢት 12/2010 ዓም (ማርች 21/2018)

በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም ተበትነው ይኖራሉ።ከእነኝህ ውስጥ የሚኖሩበት ሀገር ሕግ ተከትለው የስደተኛነት ከለላ ጠይቀው ያላገኙ ነገር ግን በከፍተኝ ችግር ውስጥ የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን በአውሮፓ እና አሜሪካ ይገኛሉ።ችግሩ በተለይ በአውሮፓ የከፋ ነው።በአውሮፓ ውስጥ የስደተኛ ከሌላ ያላገኙ ኢትዮጵያውያን የስራ ፈቃድም ስለማያገኙ ለእለት መኖርያ እጅግ ይቸገራሉ።

በአውሮፓ ውስጥ ስደተኞች ከሚቸገሩባቸው ሀገሮች አንዷ ኖርዌይ ነች።በኖርዌይ ውስጥ የመኖርያ ፍቃድ ሳያገኙ ሥራ መስራት ክልክል ነው።እንደ አሜሪካ በጥቁር (በድብቅ) ሰርቶ መኖር አይቻላም።ምክንያቱም የግል ዘርፉ በኖርዌይ እንደ አሜሪካ የተስፋፋ አይደለም።ከእዚህ በከፋ ሁኔታ ደግሞ የኖርዌይ መንግስት ፍቃድ የሌላቸው ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ሲገፋፋ እና አንዳንዴ በግዳጅ ለመውሰድ ሲሞክር ይታያል።ይህ ተግባር ኖርዌይ ከገባችው የዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር ፈፅሞ የሚቃረን ነው።እንደ ኖርዌይ ያሉ ከበርቴ የአውሮፓ ሀገሮች ይህንን የዓለም አቀፍ ሕግ በተለይ ስደተኞችን አስመልክቶ የሚጠቀሱ ሕጎችን የተለያዩ የሕግ ትርጉም እየሰጡ ሲጥሱት ይስተዋላል።ሕጉ የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን የመሳሰሉ ድርጅቶች ሁኔታውን እንዳላዩ ሆነው ሲያልፉት ይታያል።ለእዚህም ዋናው ምክንያት ሀብታሞቹ ሀገሮች ለዓለም አቀፍ ድርጅቶቹ መንቀሳቀሻ ዳጎስ ያለ በጀት ስለሚለቁ ነው።

በኖርዌይ የሚኖሩ መኖርያ ፍቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ችግሮች 

በኖርዌይ የሚኖሩ መኖርያ ፍቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ችግሮች ዘርፈ ብዙ ናቸው።በመጀመርያ ደረጃ በእድሜ ስንመለከት አብዛኞቹ ወጣቶች ከመሆናቸውም በላይ የመስራት፣የመማር እና ጊዜያቸውን በሚገባ ለመጠቀም ጉጉት ያላቸው ናቸው።ከእዚህም በላይ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ጉልህ እና ግንባር ቀደም ተሳትፎ ያላቸው ናቸው።ሆኖም ግን በመስራት እራሳቸውን እና ሀገራቸውን እንዳይረዱ አስፈላጊውን የመኖርያ ፍቃድ ስላላገኙ ብቻ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብተዋል።ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ ደግሞ የኖርዌይ መንግስት አብዛኞቹን የስደተኛ ካምፖች እየዘጋ ስደተኞቹን ኢራቅ ወዳሉ ቦታዎች ስለወሰዳቸው ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሆኑ እየተሰማ ነው።የስደተኛ ካምፖቹን መዘጋት ተከትሎ በርካቶች ከተማ የሚያውቁት ወዳጅ ጋር ተጠግተው ለመኖር ተገደዋል።ከእዚህ በባሰ ደግሞ የኖርዌይ ፖሊስ አንዳንዶቹን እየያዘ በግዳጅ ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑ ተሰምቷል።በእዚህም ሳብያ ብዙዎች ተስፋ መቁረጥ፣የአዕምሮ ጭንቀት እና ስጋት ተዳርገዋል።

የመኖርያ ፍቃድ የሌላቸው ስደተኞች ለመርዳት ምን አይነት የመፍትሄ እርምጃዎች ይወሰዱ?

በርካታ የመኖርያ ፍቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን እነኝህን ስደተኞች ለመርዳት ይፈልጋሉ። ሆኖም ግን እንዴት የሚለው ጥያቄ ያሳስባቸዋል።ሆኖም ግን እነኝህ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን እንዲደግፉ የሚያስተባብርላቸው አካል ይፈልጋሉ።እዚህ ላይ አንዳንዶች የፖለቲካ ድርጅቶች የስደተኞችን ጉዳይ እንዲሰሩ ሃሳብ ያቀርባሉ። ሆኖም ግን ይህ ስህተት ነው።ምክንያቱም የፖለቲካ ድርጅቶች ስራቸው ሰብዓዊ ተግባር ላይ ያተኮረ አይደለም።የስደተኞች ጉዳይ ፖለቲካዊ ቃና ብቻ ሳይሆን ያለው ሰብአዊነት ተግባርም ጭምር ነው።
የመኖርያ ፍቃድ የሌላቸው ስደተኞች ለመርዳት የሚከተሉት የመፍትሄ እርምጃዎች ቢወሰዱ ብዙ ችግሮችን ለመቅረፍ ይቻላል። እነርሱም :-

1/የስደተኞች ማኅበርን በአዲስ መልክ ማጠናከር፣ አመራሩ ላይ ፍቃድ የሌላቸው ብቻ ሳይሆን በስደተኛ መስመር አልፈው ፍቃድ ያገኙትን ወደ አመራር ማምጣት እና የስደተኛውን ማኅበረሰብ ችግር በጋራ እንዲቀርፉ ማድረግ፣

2/በሰው ኃይል እና በገንዘብ የተጠናከረው የስደተኛው ማህበር ከማህበረሰቡ ጋር እንዲገናኝ ልዩ ልዩ መድረኮች ማዘጋጀት።

3/  የሃይማኖት ድርጅቶች፣የማኅበረሰብ ማኅበራት ማስተባበር እና ፍቃድ የሌላቸው ስደተኞች እንዴት፣በምን እና መቼ ሊደገፉ እንደሚችል የአንድ ዓመት እቅድ ማዘጋጀት እና እቅዱን ለሁሉም በግልጥ ማስተዋወቅ።

4/ፍቃድ የሌላቸው ስደተኞች አቅም፣ችግር እና መፍትሄዎች መለየት እና ከተጨባጭ ስራዎች ጋር ማኅበረሰቡ እንዲያግዝ ከበቂ ሥራ ጋር ማውረድ የሚሉት ዋና ዋናዎች ናቸው።

ባጠቃላይ ግን ትልቁ እና ዋናው ቁምነገር የስደተኛ ማኅበሩን ማጠናከር እና ሕጋዊ ሰውነቱን አስከብሮ በየትኛውም የኖርዌይ ቢሮ ውስጥ ገብቶ ችግሩን ለመግለጥ በቂ ቁመና ያለው ድርጅት ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህ ካልሆነ ግን አሁንም እሳት የማጥፋት ሥራ ላይ ብቻ መጠመድ ይሆናል።የስደተኛ ማኅበር አቅሙን አጠናክሮ በእዚህ ዓመት ሊሰራ ካቀደው እቅድ ጋር በመሃል የሚያጋጥሙ ስደተኞችን በኃይል ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶችን ለግብር ከፋዩ የኖርዌይ ሕዝብ በቀላሉ የሚያደርስበት መረብ ዘርግቶ መጠባበቅ አለበት።ከእዚህ ውስጥ አንዱ በግድ ሊመለሱ ተፅኖ የተፈተረባቸው ግለሰቦችን ታሪክ እና የደረሰባቸውን በደል በማኅበራዊ ሚድያ እና የኖርዌይ የዜና አውታሮች እንዲዘግቡ የመጠየቅ ተግባር አስፈላጊ ነው።በአሁኑ ወቅት የምዕራብ መንግሥታት ከቀረጥ ከፋይ ሕዝብ የሚመጣ ጥያቄ መስማት ግዴታቸው እንደሆነ ያምናሉ።ቀረጥ ከፋይ ሕዝብ የሚገኝበት አንዱ መንገድ ደግሞ ማኅበራዊ ሚድያ ነው። በመሆኑም የስደተኛ ማኅበር እራሱን በሰው ኃይል፣በገንዘብ እና በመገናኛ መረብ ማጠናከሩ በድንገተኛ መልክ በስደተኛው ኢትዮጵያዊ ላይ ለሚደርሰው ችግር በቶሎ መፍትሄ ለመስጠት ያስችለዋል።

ስደት የተሰኘው በተለይ ለዘመን ድራማ የተዘጋጀ ዜማ 


ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...