ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, February 15, 2018

የጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ስልጣን መልቀቅ ለውጭው ዓለም፣ተራው የጦር ሰራዊት አባል እና ለገጠሩ ነዋሪ ያለው መልዕክት። የዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ምን አሉ? (ጉዳያችን)


ጉዳያችን/Gudayachn 
የካቲት 10/2010 ዓም (ፈብሯሪ 16/2018)

በእዚህ ፅሁፍ ውስጥ የሚከተሉት ንዑስ ርዕሶች ይነበባሉ። እነርሱም : -

- የዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች በዛሬዋ እለት ስለአቶ ኃይለማርያም ስልጣን መልቀቅ አስታከው ምን  
  አሉ? (ሊንኮቹን በመጫን ማንበብ ይችላሉ)፣
- የአቶ ሃይለማርያም ስልጣን መልቀቅ በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል፣በተራው የጦር ሰራዊቱ አባል 
  እና  ለውጭው ዓለም ያለው መልዕክት፣
- ህወሓት እራሱ በውስጡ በሁለት  "ከይሲ" ኃይሎች ተወጥሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ የካቲት 8/2010 ዓም ከስልጣን መልቀቃቸውን በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሰበር ዜና አስታውቀዋል።አቶ ሃይለማርያም በንግግራቸው ውስጥ የተጋጩ በርካታ ቃላት አሉበት።ከእዚህ ውስጥ ስልጣን የሚለቁት "የለውጡ ሂደት አካል ለመሆን ነው" የሚለው አባባል ነው። የለውጡ ሂደት አካል ለመሆን ከጠቅላይ ሚኒስትርነት እና ከደቡብ ህዝቦች ግንባር መውጣት አስፈላጊ መሆኑን እየገለጡ ነው እንዴ? ማለት ያስፈልጋል። ይህ የብዙ ነገሮች አመላካች ነው። በመጀመርያ በኢህአዴግ ውስጥ ሆኖ በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ሆነህም ለውጥ ልታመጣ አትችልም የሚል መልዕክት ሲኖረው በሌላ በኩል ደግሞ ህወሓትን መታገል እና የለውጥ አካል መሆን የሚቻለው በውስጡ ሳይሆን ወጥቶ በተቃራኒ በመቆም ነው የሚል መልዕክት ያለውም ይመስላል።

የአቶ ኃይለማርያም ሌላው በንግግራቸው ውስጥ የጠቀሱት ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያ በአስከፊ ሁኔታ ላይ መሆኗን ይገልጣሉ።አስቸጋሪ ማለት ሲያብራሩ በመገናኛ ብዙሃን የተነገሩትን የህዝብ መፈናቀል እና ሞት ጠቀሱ እንጂ የውጭ ምንዛሪው ማለቁን፣ምጣኔ ሃብቱ ከእዚህ በላይ አለማስኬዱን አላብራሩም።

የአቶ ሃይለማርያም ስልጣን መልቀቅ በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል፣በተራው የጦር ሰራዊቱ አባል እና  ለውጭው ዓለም ያለው መልዕክት

ለገጠሩ ክፍል

በማኅበራዊ መገናኛዎች የአቶ ኃይለማርያም ስልጣን መልቀቅ በበርካታ ቀልዶች ታጅቦ ሃሳብ እየተሰጠበት ነው።ሆኖም ግን ኢትዮጵያን በደንብ ከተረዳናት እያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍል መንግስት የሚለውን ፅንሰ ሃሳብ ከሚሰጠው ትርጉም አንፃር የእራሱ የሆነ ትርጉም የለውም ማለት አይላችልም።ኢትዮጵያ ከ85% በላይ ሕዝብ የሚኖረው በገጠር ነው።በተለይ በገጠር እና ጠረፋማ አካባቢዎች አቶ ኃይለማርያም በቂ ስልጣን እንደሌላቸው የማያውቅ የለም ብለን ባንገምት ከፍተኛ ቦታ ላይ ቢያንስ በስም መሆናቸውን ይረዳል።ይህ ማለት ለአንዳንድ የገጠር አካባቢዎች እና ጠረፋማ ቦታዎች ትርጉሙ መንግስት ፈረሰ ነው።

በሌላ አገላለጥ ለአካባቢው አስተዳደር አለመታዘዝ እና ግብር በወቅቱ ላለመክፈል መዘግየት አስፈላጊ መሆኑ ላይ ባለሀገሩ ያስብበታል።ይህ ማለት የአካባቢ አስተዳደሮች ቀድሞም የነበረው ደካማ የአስተዳደር አቅም በፍጥነት የማስፈፀም አቅም መውረድ ላይ ይወድቃል።ይህ እንግዲህ በስነ ልቦና ሂደት ብቻ የሚመጣ ነው።ከእዚህ ሁሉ በላይ ግን በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል መንግስት እየፈረሰ መሆኑን ከመረዳት በላይ ከተቃዋሚዎች ጋር መሰለፍ አስፈላጊ መሆኑን የገጠሩ ሕብረተሰብ ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚያምንበት ወቅት ነው።ይህ  ማለት በከተማው የእዚህ አይነት ስሜት አይፈጠርም ማለት አይደለም።ሆኖም ግን በገጠር ያለው ሁኔታ እና ትኩሳት ቀላል አይሆንም።

ለውጭው ዓለም

የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ መልቀቅ ለውጭው ዓለም ከምንጊዜውም በላይ ትልቅ ደውል አስተላልፏል።ይሄውም የህወሓት መንግስት እያበቃለት መሆኑን ከምንጊዜውም በላይ የተረዱበት ወቅት ነው ለእዚህም ነው የአቶ ኃይለማርያምን መልቀቅ ቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ጨምሮ አመፁን ተከትሎ መልቀቃቸውን እየገለጡ ያለው።ይህ ማለት አቶ ኃይለማርያም ስልጣን የለቀቁት በአመፁ ግፊት እንደሆነ ደምድመዋል።በአጭሩ የአቶ ኃይለምርያም መልቀቅ የበርካታ ሀገሮችን የውጭ ፖሊሲ ከምር እንዲመለከቱ የሚያደርግ ነው።ይህ ማለት የህወሓት መንግስት በፍጥነት ሊወድቅ እንደሚችል እና መጪው ግንኙነት ምን፣እንዴት እና ከማን ጋር መሆን እንዳለበት አሁንም ከምር እንዲያስቡ ያስገድዳል።

በተራው የጦር ሰራዊት አባል ውስጥ

በአሁኑ ሰዓት ያለው የኢትዮጵያ ሰራዊት መካከለኛ እና ከፍተኛ መኮንኖች በህወሓት አባላት እና አፍቃሪዎች የተሞላ ቢሆንም ተራው ሰራዊት ግን አሁንም ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።ይህ ማለት በኢትዮጵያ የሚደረጉት የግፍ ስራዎች ሁሉ ይመለከታል፣ይሰማል፣ስሜቱ ከሁኔታዎች ጋር ይቀያየራል።የአቶ ኃይለማርያም ከስልጣን መልቀቅ ለተራው ሰራዊት አንድ ነገር ግልጥ ያደርግለታል። እዚህ ላይ ሰራዊቱ ሌላው ሕዝብ ከማኅበራዊ ሚድያም በተባራሪ የሚደርሰው መረጃ ለእርሱ ብርቅ ነው።የእርሱ መረጃ ከመንግስት ሚድያ እና ከካምፕ ሲወጣ ከሚገናኘው ቤተሰብ እና ወዳጅ ነው።ዛሬ አቶ ኃይለማርይም ስልጣን በፈቃዳቸው ለቀቁ ማለት ለምን? የሚል ጥያቄ ይጭራል። ለሰራዊቱ ቢያንስ አንድ ነገር እርግጠኛ ይሆናል።ቤተ መንግስት ውስጥ ችግር አለ የሚለው እና በህወሓት እና በሌሎች ተጣማሪ በነበሩት መሃል ያለው ችግር ከሚገባው በላይ ተካርሯል ማለት ነው ይላል።ይህ መረጃ የሚያሳየው ጉዳይ መጪው ጊዜ የለውጥ መሆኑን ያሳየዋል።ውጤቱ ምን ይሆናል የሚለውን ወደፊት የሚታይ ነው።

ህወሓት እራሱ በውስጡ በሁለት  "ከይሲ" ኃይሎች ተወጥሯል


ብዙ ቅን ፖለቲከኞች ወይንም አስተያየት ሰጪዎች ከአሁን በኃላ ህወሓት ወደ ሽግግር መንግስት እንዲሄድ  ይገድዳል፣ነገሮች ሳይበላሹ ስልጣን ህወሓት ይለቃል ወይንም ነፃ ምርጫ ይሳተፋል ብለው ያስባሉ። ይህ ግን የህወሓትን ባሕሪ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው።ህወሓት እራሱ በውስጡ በሁለት "ከይሲ" ኃይሎች ሃሳብ ተወጥሯል።ከይሲ የሚለውን ቃል የክፉ ክፉ በሚል ትርጉም ውሰዱልኝ።የመጀመርያው የህወሓት ከይሲ ቡድን መሃል ሃገሩን ለጊዜው ለቀቅ እናድርግ እና ትግራይ ላይ እናተኩር።ትግራይ ላይ ስናተኩር ግን የዐማራ አዋሳኝ ቦታዎች ይዞታዎቻችንን ማጠናከር እና የመሃል ሀገር ጥቅማችንን ፖለቲካውን በተወሰነ ደረጃ በመልቀቅ ምጣኔ ሃብታዊ የበላይነት ላይ እናተኩር የሚል ሲሆን ይህ ቡድን አቶ ኃይለ ማርያም በህወሓት ሰው ካልተተኩ የመሃል ሀገር አስተዳደር እንዲዳከም ዘረፋ እንዲስፋፋ እና ሕዝብ ህወሓት ተመልሶ እንዲመጣ እንዲለምነው ተስፋ ያደርጋል።ይህም ማዕከላዊ መንግስትን ለተወሰነ ጊዜ  በማላላት ለተደራጀው ህወሓት የዘረፋ ጊዜ መግዛት የሚል ሃሳብ ነው። በመሆኑም በብሄር መካካል ጠብ መባባስ ላይ እና የዘረፋ ዜናዎች በብዛት እንዲሰሩ ያስባል።

ሁለተኛው ከይሲ ቡድን ተደፈርን ባይ ነው።ትናንት የተፈቱት እስረኞች የህወሓት ሞት ነው ባይ ነው። የእዚህ ቡድን አባሎች በከፍተኛ ዘረፋ የናጠጡ በሀገር ውስጥ እና ውጭ ሀገር እየኖሩ የሚፎክሩ ሲሆን በከተሞች አካባቢ ህወሓት ያስታጠቃቸውን መሳርያ ቁምሳጥን ውስጥ አስቀምጠው ዘራፍ የሚሉ ናቸው።ይህ ቡድን በህወሓት ውስጥ ነገሩ አለማስከዱን አምነው ለውጥ ለማምጣት ዳር ዳር የሚሉትን ቁም ስቅል የሚያሳዩ ቡድኖች እነኝህ ናቸው። አቶ መለስ በ1997 ዓም የቅንጅት መሪዎች ባይታሰሩ ኖሮ እልቂት ነበር እያሉ የተሳለቁት እነኝህን ቡድኖች ጋር ከተመካከሩ በኃላ ነው።በአፍሪካ የእዚህ አይነት ቡድኖች የተለመዱ ናቸው።በብሔራዊው ጦር መተማመን ያልቻሉ አምባገነኖች እና የጎሳ ቡድኖች ሁል ጊዜ የእዚህ አይነት ከይሲ ቡድን የስልጣናቸው መጠበቂያ ያደርጉታል።ሆኖም ግን የእዚህ አይነት ቡድኖች የሰሩት ወንጀል ስቆለል እና ህሊናቸው በእራሱ ጥፋት ሲበሳሳ የሞራል ልዕልናቸው ተንኮታኩቶ ሕዝብ እጅ የወደቁ ቀን ዝናብ የመታት ዶሮ መሆናቸው ከግብፅ እስከ ኢራቅ የታየ ነው።

የሁለቱ ብድኖች እነኝህን የከይሲ ስራዎች ለመስራት በማገቻነት የሚጠቀሙት የትግራይን ሕዝብ ነው።ለእዚህም ሕዝቡን በማናቸውም መንገድ ከቀረው ሕዝብ ጋር ማጋጨት ብቸኛ አማራጭ መንገዳቸው ነው።ጭር ካለ እንደ አደጋ ያዩታል።ለምሳሌ ሰሞኑን በሰሜን አሜሪካ የትግራይ ልማት ማኅበር የአሜሪካ ድምፅ ራድዮ እና ኢሳትን ለመክሰስ መወሰኑ አንዱ ምክንያት በሰሜን አሜሪካ የሚኖረው የትግራይ ተወላጅ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንዳይተባበር አንድ አይነት ማኅበራዊ ግጭት ማስነሻ ጉዳይ ለመፍጠር ሁለተኛው የከይሲ ቡድን የመክሰስ የሚል ሃሳብ ይዞ ብቅ አለ።በነገራችን ላይ የትግራይ ልማት ማኅበር በእዚህ ሳብያ ገንዘብ ለማሰባሰብ እና በሙስና የተጨማለቀው አመራር ኪስ ለማድለብ የታለመ ነው።አሁንም ግን የትግራይ ማኅበረሰብ ከእዚህ በላይ በጥቂት ከይሲ አስተሳሰብ አራማጆች ባይታለል በጣም ጥሩ ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁለቱ ከይሲ ቡድኖች እንደሚያስወሩት ሳይሆን በነገዋ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው ከትግራይ ሆነ ከጅጅጋ  በመሆኑ ብቻ አንዳች በደል እንደማይደርስበት ዋስትና የማትሰጥ ሆና እንደማትሰራ ከአሁኑ ማመን ተገቢ ነው።

ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢም ተስፋ ሰጪም ደረጃ ላይ ነው ያለው።አሳሳቢነቱ የህወሓት ከይሲ ቡድኖች ከጀርባ እንደ ባዕድ የሚሸርቡት ተንኮል ኢትዮጵያን ወደ አደገኛ መስመር የመውሰድ አደጋ አለው።ለምሳሌ ዛሬ የሚናፈሰው ከአቶ ኃይለማርያም የመልቀቅያ ጥያቄ ተከትሎ አዋጅ ለማወጅ እያሰበ ነው የሚል በእራሱ የማኅበራዊ ሚድያ መስመር በኩል እየተሰማ ነው።ይህ ኢትዮጵያን ሆን  ብሎ ወደ እርስ በርስ ትርምስ ለመክተት በህወሓት የተወሰነ ውሳኔ ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል።ምክንያቱም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በእራሷ የፀጥታ ችግር የለባትም።የፀጥታ ችግሯ የህወሓት ስልጣን ጠቅልሎ መያዝ የጎሳ እና አድሏዊ ስርዓት ያደረሰው ጥፋት ነው።ይህንን ለመፍታት የችግሩ መፍትሄ በውድም ሆነ በውድ ህወሓት ስልጣን ለሕዝብ  እንዲያስረክብ ማድረግ ነው።ይህ የአዋጅ ጋጋት እና  የአስከሬን ክምር አያስፈልገውም። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ተስፋ ሰጪም ነው። ይህ ማለት ሕዝብ በኅብረት ተነስቷል።በቃኝ ያለ ሕዝብ በእራሱ መድረሻው ምን ይሁን ምን አልገዛም ብሏል።ይህ የኢትዮጵያ ተስፋ ነው።ሌላው ተስፋ ኢትዮጵያ ይህንን የሁለት ከይሲ ቡድኖች ተንኮል ከተሻገረች ብሩህ የሆነ ሕብረት የመፍጠር ዕድል አላት።ይህ ዕድል የበለጠ የሚሳካው ደግሞ የቀና ሃሳብ ያላቸው የህወሓት  አባላት ሁለቱን የከይሲ ቡድኖች አስተሳሰብን ማምከን ችሎ መራመድ ከቻለም ጭምር ነው።

የዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች በዛሬዋ እለት ስለአቶ ኃይለማርያም ስልጣን መልቀቅ አስታከው ምን አሉ? (ሊንኮቹን በመጫን ማንበብ ይችላሉ)

ጉዳያችን GUDAYACHN 

 www.gudayachn.com

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።