ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, August 9, 2017

የኢትዮጵያ አምላክ እንዲነሳ እንባ አዋጡ! (የጉዳያችን መልዕክት)

ኢትዮጵያ አምላክ አላት።የሁሉም አምላክ እንደሆነ ሁሉ በተለይ የኢትዮጵያ አምላክም መሆኑን የነገረን ደግሞ ከ40 ጊዜ በላይ በቅዱስ መፅሐፍ ስሟ እንዲጠራ ያደረጋት ሀገር ኢትዮያ ነች።ይህ ያለንበት ወቅት (ከነሐሴ 1 እስከ 16፣2009 ዓም) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ስርዓት መሰረት ከሰባቱ ዋና የፆም ወቅቶች ውስጥ አንዱ ነው።ፆሙ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የትንሣኤ እና የእርገት ምስጢርን ለሐዋርያት በሁለት ዙር ሱባኤ  ከእግዚአብሔር ምስጢሩን የተገለጠላቸው ወቅት ነው።ኢትዮጵያ እና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፊት ለፊት የሚነጋገሩ ምስጢረኞች ናቸው።ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴን ጨምሮ ከእሳቸው በፊት የነበሩ የኢትዮጵያ  መሪዎች በእግዚአብሔር የሚያምኑ በድንግል ማርያም አማላጅነት የተጠቀሙ ነበሩ።አንዳንዶች እግዚአብሔርን በሚገባ ስለማያውቁት ወይንም ከስንፍና የተነሳ ስለድካማቸው መሸፈኛ እግዚአብሔርን ማመን የመሸነፍ እና የተስፋ መቁረጥ ምልክት ይመስላቸዋል።ጉዳዩ ግን በተቃራኒው ነው።አባቶቻችን እና እናቶቻችን ኢትዮጵያን ለትውልድ ሲያስተላልፉ መንገዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር አድርገው እንጂ በትዕቢት መንገድ ተጉዘው አልነበረም።

ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ይህ የፍልሰታ ፆምን የዓመት እረፍት ወስደው  ድሬዳዋ ኪዳነ ምሕረት አልያም መስቀል አደባባይ የሚገኘው ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን 15ቱንም ቀኖች እያስቀደሱ ያሳልፉ ነበር።በተለይ ድሬዳዋ በወረዱበት የፍልሰታ ፆም ወቅት እርሳቸውን በፍጥነት ለማግኘት የመጣ የውጭ ሀገር ልዑክ ድሬዳዋ መውረድ ነበረበት።ኢትዮጵያ የተሰጣት ፀጋ ይህ ነው።ከእግዚአብሔር ጋር መንገዱን ያላስተካከለ ቤተ መንግስቷ ውስጥ ቢገባ እንደታወከ ይኖራል።በደርግ ዘመንም ሆነ አሁን አራት ኪሎ የሆነውን እያየን ነው።

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ጊዜ አንድ ሱባኤ አይደለም በርካታ ሱባኤዎች ይፈልጋል።ሕዝብ በጎሳ በተከፋፈለ ችግር ነው።ከወዲህ በጎሳ የሚከፋፍል በመንግሥትነት ተሰይሞበት ያሰቃየዋል፣ ከማዶ በእየጎሳው የተደራጁ ድርጅቶች የነገ አንደነቱን ሊያጨልሙበት ሲሯሯጡ ይታያሉ።በእግዚአብሔር ዕርዳታ ሰው በጥረቱ የሚፈታው ጉዳይ አለ። ሰው ምንም ያህል ቢሮጥ በእግዚአብሔር ብቻ እና ብቻ የሚሰራ ሥራ አለ።ስለ ኢትዮጵያ ማንባት ጥቂት እንባ ማዋጣት ከእግዚአብሔር ጋር መንገዷን ያስተካክላል።ለዘመናት መላ ያጣችበትን የቤተ መንግስቷን ጉዳይ መልክ ያስይዘዋል።መልክ የምያስይስዘው ከሰማይ ወርዶ አይደለም።የሕዝብን ልብ ያፀናል፣ፍቅር ይሰጣል፣አሸናፊ ያደርገዋል።ይህ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያን ሕዝብ ልብ አፅንቶ፣በአንድ አቁሞ፣የሚወደው መሪ አውጥቶ ኢትዮጵያን ለመጪው ክፍለ ዘመን ነፃነቷን፣አንድነቷን፣እምነቷን እና ብልፅግናዋን አምጥቶ ያሻግራታል።እግዚአብሔር በቸርነቱ፣ ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ የኢትዮጵያን ምስጢር እንድትፈታ ትንሽ ትንሽ እንባ እናዋጣ። እንደ እውነቱ ለመናገር ማናችንም ስለ እራሳችን እና ቤተሰባችን እንፀልይ ይሆናል።ጥያቄው  ከልብ ጊዜ ሰጥተን የኢትዮጵያ ጉዳይ ብለን እየፀለይን ነው ወይ? የሚለው ነው።ከሆነ መልካም።እርግጥ ነው ቀን ከሌሊት የሚፀልዩ በግልጥም በስውርም የሚኖሩ የእግዚአብሔር ወዳጅ ቅዱሳን የሚኖሩባት ነች ኢትዮጵያ። የእዚህ ማስታወሻ ዋና አላማ ግን ስለ ካህናቱ፣መነኮሳቱ ለማውራት አይደለም።ከእዛ በታች ስላለነው ምእመናን ሁሉ ነው።እስኪ የኢትዮያን ጉዳይ ፍታው ብለን ትንሽ ትንሽ እንባ እናውጣ። እግዚአብሔር በኢትዮጵያ እና በሕዝቧ ላይ የተነሱባትን ባያንበረክክ በእዚህ እንፈትነው።

ከስር ቪድዮ "ቅያሜው ይቅርና አምላክ ሆይ ታረቀን" በዘማሪ ይልማ ኃይሉ (ያድምጡት)



ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...