Friday, August 11, 2017

በኢትዮጵያውያን ደም የተጨማለቀ የአሸንዳ በዓል ከፋሺስት ብሔራዊ መዝሙር እኩል ነው።ፋሺሽት ሕወሓት በቃን!የኢትዮጵያ ሕዝብ እያሰማ ያለው መፈክር።

ኢትዮጵያ ከሰሜን ተራሮች እስከ ደቡብ ምስራቅ ጅጅጋ፣ ከጋምቤላ አኮቦ እስከ አፋር አሳይታ የ26 ዓመታት የወያኔ አገዛዝ ያንገሸገሸው ሕዝብ ለነፃነቱ እየወደቀ እና እየተነሳ ነው።በያዝነው ሳምንት ብቻ በሐዋሳ የባጃጅ ትራንስፖርት ሥራ ማቆም አድማ ተጀምሮ እስከዛረዋ እለት ድረስ እንደቀጠለ ነው። ሰሜን ጎንደር ያሉ የንግድ ቦታዎች በሙሉ ተዘግተው አድማ ላይ ናቸው፣ ባህር ዳር 50 በላይ ነዋሪዎቿን በህወሓት ወታደሮች የተፈጁባት አንደኛ ዓመት ለማክበር በያዝነው ሳምንት የስራ ማቆም አድማ መትጣለች። እስካሁን ድረስ በርካታ የከተማዋ ነጋዴዎች እና ነዋሪዎች እየታሰሩ ነው።ፋሺሽት ወያኔ በቃኝ! ያሉ እና በንግድ እና ሥራ ማቆም አድማ ላይ ያሉ ሌሎች ከተሞች ወልዲያ ፣ አምቦ፣ጎንደር፣በለሳ እና ሌሎች በርካታ ከተሞች ሲኖሩ ምስራቅ ሐረርጌ ባቢሌ ሱማሌ እና ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በመሬት ጉዳይ ስርዓቱ አጋጭቷቸው እርስ በርስ ውጊያ ላይ ናቸው።

አንዳንዶች ፋሺስት ሕወሓት ሲባል የተጋነነ ስድብ አድርገው የሚያስቡ አሉ። ሆኖም አሁን ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ካለው አንፃር ፋሺስት የሚለው አጠራር ለህወሓት ሲያንሰው እንጂ ከልኩ በላይ የተሰጠው ስም አይደለም።በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያውያን ላይ ሰራዊት አዝምቶ፣መሳርያ ወድሮ እና በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ታጅቦ ኢትዮጵያውያንን መጀመርያ ሀብታቸውን ቀጥሎ ሕይወታቸውን እየቀጠፈ የሚገኘው የህወሓት ቡድን ፋሽሽት የሚለው ቃል ቢያንሰው እንጂ አይበዛበትም።

ኢትዮጵያውያን በሲቃ መከራ ላይ በሚገኙበት በእዚህ ወቅት ስለ ሕወሓት እና ጀሌው ትንታኔ መስጠት ወይንም ፀሐይ የሞቀውን የሕወሓትን ግፉን መዘርዘር አንዳች ፋይዳ የለውም።ባጭሩ የህወሓት ፈድራሊዝም ተንኮታኩቷል።የወደቀ ነገር ትንታኔ አይፈልግም። ሕዝብ ለወያኔ አለመገዛቱ ያሳየበት አንዱ መንገድ ለወያኔ ግብር አልከፍልም በማለትም ነበር።ኢትዮጵያውያን እዚህ የመጨረሻ የትዕግስት እንጥፍጣፊ ደረጃ ለመድረስ በርካታ የመከራ ፅዋዎችን ተጎንጭተዋል።አሁን ግን ከእዚህ በላይ የመኖር እና አለመኖር ወሳኝ ጥያቄ ላይ የደረሰበት ሕዝብ ሕወሀትን  ከትከሻው ላይ ለማሽቀንጠር ወስኗል።ይህንን የኢትዮጵያ ሕዝብ ውሳኔ ለጊዜው በአፈሙዝ ተገድቦ የተያዘ ይምስለ እንጂ በከባድ አሻጥር እና ኢትዮጵያዊ ስሜት አመፁ እንደሚቀጥል እና በሌላ መልክ እንደሚከሰት በእርገጠኘንት መናገር  ይቻላል። ይህ ወቅት ኢትዮጵያን ከእነሙሉ ክብሯ ለማስጠበቅ የመነሳት ኃላፊነት የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ነው።"ከሚቃወሙት ይልቅ ዝምተኞቹን እና ቸልተኞቹን እፈራለሁ" እንዲል በቸልታ ውስጥ ያለው በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ አሁን ላይ ቆሞ መመልከት ያለበት በርካታ ጉዳዮች አሉ። አሁን ሕዝብ ሁሉንም ጉዳዮች ተመልክቶ  በአንድነት የመቆም ግዴታ እንዳለበት እየተረዳ ነው።

መላዋን ኢትዮጵያ በደም እየነከረ ያለው የፋሽሽት ስርዓት በኢትዮጵያውያን ደም ከመነከሩ በላይ የተቀረውን ኢትዮጵያዊ የምጣኔ ሀብት አቅም በበለጠ ለማቆርቆዝ እና የበለጠ ባርያ ለማድረግ በግብር ሰበብ ነጋዴውን ከንግድ ቦታው እየነቀለ የእኔ ለሚላቸው የጎሳ መሰሎቹ እና አድር ባይ ካድሬዎች ለመስጠት አዲስ ዘመቻ ላይ ነው።አንዳንዶች እንዴት ወያኔ በእዚህ በተወጠረበት ወቅት የንግድ ግብር ጉዳይ አንስቶ ሕዝብ እንዲነሳ ምክንያት ሆነ? ብለው ይጠይቃሉ። ለእዚህ ምክንያቶቹ ግን ሁለት ናቸው።አንደኛው ከውጭ የሚገባ እርዳታ እና ብድር ከመመናመኑ የተነሳ እና የውጭ ንግድ ገቢው ስለወረደ ቀሪ የበጀት ማሟያ ብቸኛ ምንጩ ቀረጥ ህዝቡ ላይ መጣል ሲሆን ሁለተኛው እና እግረመንገዱ ለማሳካት ያሰበው ከውጭ በተለይ ከአረብ ሀገሮች ወደ ኢትዮጵያ የምገቡቱ የጎሳው ሰዎች አነስተኛ እና መካከለኛ ንግድ እንዲሰሩ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ማፈናቀል የሚለው እንደ ቀዳሚ ተግባር ተደርጎ ተወስዷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ማለትም ኢትዮጵያውያን ከገጠር እስከ ከተማ በሚታሰሩበት፣በሚገረፉበት  እና በሚገደሉባት ኢትዮጵያ አሸንዳ ሊዘፈንበት ሽር ጉድ ተይዟል።አስከሬን ላይ ቆሞ አሸንዳ የለም።በኢትዮጵያውያን ደም የተጨማለቀ የአሸንዳ በዓል ዘፈን ከፋሽሽቶች ብሔራዊ መዝሙር እኩል ይቆጠራል።ህዝብን አስለቅሶ ባሕሌን ተጋቱልኝ ማለት አይቻልም።ለሃያ ስድስት ዓመታት ሕዝብን ንቆ የቆመ ፋሽሽታዊ ስርዓት ጋር አብሮ ለመቀጠል የሚፈልግ እና እራሱን ከእውነት ጋር በተ ንጠፈጠፈች ሰዓትም ላይ ቢሆን  የሚለይ ካለ ሕዝብ አሁንም እጁን ዘርግቶ እየጠበቀ ነው።ሁኔታው ግን "ካፈርኩ አይመልሰኝ" ሆኗል።አይን አውጥቶ መግደል፣የንግድ መደብሮችን ማሸግ እና ቤተሰብ ተርቦ እንዲያድር ገፋ ስል ደግሞ ለጎዳና ሕይወት ተዳርገዋል።ባዕዳን ወራሪዎች ኢትዮጵያን ቢወሩ ሊያደርጉ የሚችሉት አሁን ወያኔ እያደርገ ያለውን ነው።ወያኔ ፋሽሽት እንጂ ኢትዮጵያዊ መንግስት አይደለም።ኢትዮጵያዊ መንግስት ወገኖቹ ወደ ባህር ሲጣሉ ጉዳዩን የሚያጣራ ልዑክ ቢያንስ ሰይሞ ይንቀሳቀሳል።አረመኔው ወያኔ ግን ትናንት በመላው ዓለም የተሰማው የ160 ኢትዮጵያውያን ወደ የመን ሲሄዱ ሆን ተብሎ ከመርከብ ወደ ውሃ እንደወረወሩ መደረጋቸውን እንዳልሰማ አንዲት ዜናም ሳይሰራለት ይሄው አሁን 24ኛ ሰዓቱ አልቆ ወደ ሁለተኛ ቀን አልፈናል።ጉዳዩን ግን በመላው ዓለም ተናኝቷል። 

ፋሽሽት ወያኔ የኢትዮጵያ ወኪል ሆኖ መቀመጥ እንደማይችል ከአንድ መቶ ስልሳ በላይ ኢትዮጵያውያን እጅ እና እግራቸው እየታሰረ ወደ ባሕር ውስጥ መወርወራቸው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ከተነገረ 24 ሰዓት ቢያልፈውም የኢትዮጵያ ራድዮ እና ቴሌቭዥንም ሆነ ሕወሓት የሚመራው መንግስት አንዳች ነገር አልተናገረም።የትኛው መንግስት ነው ዜጎቹ ባህር ውስጥ ገብተው አንዳች የማይተነፍስ? በአሸንዳ ከሚውረገረገው ወያኔ በቀር።ሕዝብ አሁን መድረሻ ግቡን እያስቀመጠ ነው።ይሄውም በቅደም ተከተል ከወያኔ በኃላ ስለሚኖረው መንግስት ሕዝብ ይወያያል።ፋሺሽት ሕወሓት በቃን!የኢትዮጵያ ሕዝብ እያሰማ ያለው መፈክር ነው። ከእዚህ በኃላ የወያኔ የባርነት ቀንበር ውስጥ የሚገባ ኢትዮጵያዊ የለም።

ቪድዮ - ጎንደር ላይ የተደረገው ሕዝባዊ ሰልፍ በከፊል።ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com
Post a Comment

GUDAYACHN BLOG started on August 28/2011 ኢሜይል አድራሻዎን በመሙላት ጽሁፎቹን መከታተል ይችላሉ/Follow by Email

በብዛት የተነበቡ/Popular Posts

ጉዳያችን በፌስ ቡክ ገፅ / GUDAYACHN ON FACE BOOK

https://www.facebook.com/gudayachn/?pnref=story