ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, June 29, 2017

የተቃወሰ መንግስት ምልክቱ እራሱን ወደ 'አናርኪዝም' ማሸጋገሩ ነው - የኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ ጉዳይ ይመለከታል


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 


ጉዳያችን/ Gudayachn
ሰኔ 23/2009 ዓም (ጁን 30/2017 ዓም)
++++++++++++++++++++
በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ታሪክ የኢትዮጵያ ባንኮች ከሌሎች የአፍሪካ በተለይ ከሣሃራ በታች ካሉት ሀገሮች በተለየ ጥሩ ተአማኒነትን በሌላው ዓለም አትርፈዋል።ለምሳሌ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደርግ ዘመን ማለትም ኢትዮጵያ ከቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ጋር ወዳጅ ሆና ሳለም ሳይቀር የምዕራብ ባንኮች በ"ሌተር ኦፍ ክረዲት" የላኪ እና የአስመጪ ሰነዶች ላይ በሚፈፀሙ ክፍያዎች ታማኝነቱ የተመሰከረለት ነው።ለምሳሌ የአሜሪካው "ሲቲ ባንክ" እና የእንግሊዙ "ስታንዳርድ ቻርተር" የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰነዶች ላይ እምነታቸው ከፍ ያለ ነው።ለእዚህ ደግሞ ምክንያቱ የስርቆት አደጋዎች በብዛት የማይታዩበት፣ለቀረቡለት የክፍያ ሰነዶች በወቅቱ መክፈሉ እና ለእረጅም ጊዜ በባንኩ የዓለም አቀፍ ባንክ አገልግሎት ክፍል (International Banking Division) ላይ የሰሩት ኃላፊዎች የገነቡት ዓለም አቀፍ ስብዕናም ጭምር ነው።ይህ ማለት ታማኝነቱ በአንድ ጀንበር የተገንባ ሳይሆን የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ከቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ጊዜ ጀምሮ የገነባው ብቁ እና ታማኝ የሰው ኃይል ውጤትም ጭምር ነው። በእርግጥ ደርግ የሆነ ወቅት ላይ በሙያው በቂ ስልጠና የሌላቸውን አስገብቶ እንደነበር እና ይህም ለባንኩ የስራ ጥራት ላይ የእራሱን አስተዋፅኦ ማድረጉን የሚናገሩ አሉ። ይህም ሆኖ ግን በታማኝ የሰው ኃይል እና ስራን በማክበር አይታማም።

በእዚህ ፅሁፍ ማንሳት የፈለኩት ግን ይህንን አይደለም።ስለ የባንኮቻችን በቀውስ ላይ ያለው መንግስት አናርክዝም ወይንም ስርዓት አልበኝነት ሰላባ ስለመሆን ነው።በአሁኑ ጊዜ የግል ባንኮችን ጨምሮ 18 ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ።ይህ በራሱ ጥሩ ነገር ነው። ሆኖም ግን የባንክ ቁጥር መደርደሩ ሳይሆን አጠቃላይ የባንክ ኢንዱስትሪው ለኢንዱስትሪው ስነ-ምግባር እና የንግድ ሕግ ተገዢ ነው ወይ? የሚለው ጉዳይ ወሳኝ ነው።አንድ ባንክ ከሁሉም በላይ በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪ ብቻ ሳይሆን በውጭ ሀገር ተመሳሳይ የገንዘብ ድርጅቶች ዘንድም ታማኝ የሚያደርገው ለደንበኞቹ ያለው ዋጋ ነው።ደንበኞቹ ማለት ደግሞ ገንዘብ ያስቀመጡ እና የምበደሩ የሀገር ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ በውጭ ያሉ ባንኮች እራሳቸው ደንበኛ ባንኮች ይባላሉ።ይህ ማለት የውጭ ባንኮችም ደንበኞቻችን ናቸው ማለት ነው።ባንክ ባንክ ለመባል ትንሹ የሚጠበቅበት እና ለምንም ድርድር የማይቀርበው ጉዳይ ደንበኞች ያስቀመጡትን ገንዘብ በፈለጉ ጊዜ መክፈል መቻሉ ነው።ይህ የባንክ ሀ! ሁ! ነው።ይህንን ማድረግ ያልቻለ ባንክ ባንክ አይባልም።ይህ ሃገራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ግዴታ ነው። የብሔራዊ ባንክ ካሉበት ትልልቅ ሃገራዊ ምጣኔ ሃብታዊ ኃላፊነቶች ውስጥ ትንሹ እና ለድርድር የማይቀርበው የቁጥጥር ቀዳሚ ስራው ውስጥ የንግድ ባንኮች ደንበኞቻቸው ገንዘባቸውን ሲፈልጉ መልሰው  የመክፈል አቅም ሳይኖራቸው ተበዳሪ አገኘን ብለው  ያላቸውን ሁሉ አበድረው ደንበኞች ገንዘባቸውን እንዳያጡ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ነው። ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ታሪክ ውስጥ ጥያቄ ሆኖ አያውቅም። በእዚህ በአሁኑ ዘመን ግን አንድ ሰው በፈለገበት ሰዓት ባንክ ሄዶ ገንዘቡን ለማውጣት ሲፈልግ " ሲስተሙ ችግር አለበት ወይንም ዛሬ ሲስተም የለም" እየተባለ መመለስ የተለመደ ነው። ይህ አይነቱ መልስ በባንኮች ታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ በደርግም ሆነ በሃይለስላሴ ዘመን ተደረገ ሲባል አልሰማሁም።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 'ሲስተሙ አይሰራም' በሚል ምክንያት ደሞዝ ወደ ሂሳባቸው የገባ ሰራተኞች ደሞዛቸውን ሳይወስዱ ከሶስት ቀናት በላይ ይመላለሳሉ።የንግድ ውል ተዋውለው ገንዘቡን መክፈል የሚፈልጉ ነጋዴዎች ባንካቸው ገንዘቡን መክፈል ሳይችል ለሳምንት ልዘገዩ ይችላሉ አልያም ደንበኞች ያስቀመጡትን ገንዘብ ለማውጣት ለቀናት በእዚሁ ሲስተም በሚል ሰበብ ይመላለሳሉ። እዚህ ላይ ሲስተም ተብሎ የሚነገረው በኢትዮጵያ ቴሌኮምኒኬሽን ብቸኛ አቅራቢነት የሚሰጠው የኢንተርኔት አገልግሎት ነው።ቴሌን የሚመሩት የኮማንድ ፖስቱም አለቆች ናቸው እና እነርሱ ስለ ንግድ ሕግ፣ ስለ ባንኮች ለደንበኞቻቸው የገቡት ቃልም ሆነ የኢትዮጵያ ባንኮች ለዓለም አቀፍ ባንኮች የገቡት የንግድ ሰነዶች ጉዳይ ሁሉ በወሬ ይሆናል የሚያውቁት። 'ዛሬ ኢንተርነቱን ዝጋው አየሩ ጥሩ አደለም' ካሉ መዝጋት ነው።እዚህ ላይ የባንኮች ለክፍያቸው ታማኝ አለመሆን ያለውን ሌላውን ጣጣ ጉዳያቸው አይደለም። አናርክዝም ወይንም ስርዓት አለበኝነት ማለት ይህ ነው።በሕግ የማይመራ የተቃወሰ መንግስት። በውጪ እና ገቢ ንግዶች ዙርያ ያሉ ክፍያ የሚጠብቁ ዓለም አቀፍ የባንክ የክፍያ መጠየቂያ ሰነዶች ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልጉ እና የክፍያ ሂደቱም ከተባለለት ጊዜ ከፍ ወይም ዝቅ ሳይል መሆን እንዳለበት ይታወቃል። 

አንድ አስመጪ ወይንም ላኪ  እቃው ወደ ሚላክበት ሀገርም ሆነ እቃው ከሚመጣበት ሀገር ያሉ ባንኮች ገንዘባቸው እንዲከፈላቸው የሚፈልጉበት የጊዜ ገደብ በሌተር ኦፍ ክረዲቱ ላይ የተጠቀሰ እና ገዢ እና ሻጭ በገቡበት የውል ሰነድ መሰረት ነው። በሁለቱ ገዢ እና ሻጭ መካከል ከፍተኛ ታማኝ ተብለው የሚያቀባብሉት ደግሞ ኢትዮጵያ ያለው ባንክ እና ውጭ ሀገር ያለው ባንኮች ናቸው። ልብ በሉ። የኢትዮጵያ ቴሌ ሲስተም መዝጋት ስንት የክፍያ ሰነዶች ለቀናት እንዲቀመጡ እና የውጭ ሀገር ባንኮች በእዚህ ሳብያ ስንት ወለድ እንደጠየቁባቸው በእየባንኩ ቤት ያላችሁ መስክሩ።በእዚህ ሳብያ የሚደርሰው ኪሳራ የወለድ ብቻ አይደለም።ወለዱ ቢደመር ኢትዮጵያ በቴሌ እና የኮማንድ ፖስት አለቆቹ ሳብያ ምን ያህል እንደከሰረች መለስተኛ የዳሰሳ ጥናት ቢደረግ አስደንጋጭ እንደሚሆን ለማወቅ ሊቅ መሆን አይጠበቅም። ከእዚህ ሁሉ በላይ ያለው ኪሳራ ግን የኢትዮጵያን መልካም ስም እንዲጠበቅ አድረገው በዓለም አቀፍ ባንኮች ውስጥ ከሁሉም አፍሪካ ሀገሮች በተሻለ ታማኞች የተባሉት የኢትዮጵያ ባንኮችን ስም እንደሚያጎድፍ እና እየቆየም ወደ ጥቁር ዝርዝር መዝገብ እንደሚያስገባን ማወቅ አለብን። 

ለማጠቃለል እነ አባይ ፀሐዬ የቦርድ አባል ሆነው የመሩት የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ የስርዓቱ "አናርክዝም" ወይንም ስርዓት አልበኝነት ሰለባ መሆኑ ሌላው የኢትዮጵያ የወቅቱ ህመም ነው።በየትም ሀገር አልፎ አልፎ የሲስተም መቆራረጥ ሊያጋጥም ይችላል። የኢትዮጵያ ግን ኢንተርኔት የሚዘጋው በተደጋጋሚ ያውም በኮማንድ ፖስቱ አለቆች መሆኑን ሲታሰብ እና እያመጣ ያለው ቀውስ ሲታይ የተቃወሰ መንግስት ምልክት መሆኑ በግልፅ አመላካች ነው።በንግዱ ሕግ እና ስነ-ምግባር መሰረት ቴሌ ለባንኮች አገልግሎቱን ሲሰጥ ውል ገብቷል።ባንኮች ደግሞ ለደንበኞቻቸው አገልግሎታቸውን ሲያቀርቡ ውል ገብተዋል።ቴሌ የገባው ውል አገልግሎቱን ሳያቆም ለማቅረብ ሲሆን ባንኮቹም በበኩላቸው ለሚሰጡት አገልግሎት ምንም አይነት መቆራረጥ ሳይኖር ለማገልገል ነው። ስለሆነም በእዚህ የንግድ ትስስር መሃል አንዱ ውሉን ባያሟላ ሌላው ለሚደርስበት ኪሳራ ተጠያቂ ነው።ኪሳራ የደረሰበትም በፍርድ ቤት ቀርቦ ከሶ ካሳ ማግኘት ይችላል። ይህ የአምባገነን መንግስት መኖር እና አለመኖር ጉዳይ አይደለም።በደርግ ዘመን በትክክል ይቻላል።በደርግ ዘመን የነበረው የመብራት ኃይል እና የውሃ ፍሳሽ አገልግሎቶች በእለተ እሁድ የሚሰጡት አገልግሎት የሚቆም ከሆነ ቀድመው ከሶስት ቀናት በፊት በራድዮ እና ቴሌቭዥን እንዲናገሩ የንግድ ውል ሕጉ ያዛቸዋል። ከደንበኛው ጋር ውል ሲገቡ አገልግሎቱን ላያቆሙ ካቆሙ ግን ቀድመው ሊያሳውቁ ነው። ይህ ቀላል የንግድ ውል ሕግ በተቃወሰው የሕውሓት መንግስት ውስጥ አይሰራም። መብራት እና ውሃ እንደሚቆም ሳይነገር ለቀናት መጥፋት የጅመረው በአናኪዝም ወይንም ስርዓት አለበኛው የሕወሓት መንግስት ነው እንጂ በደርግም ሆነ በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ  ዘመን ማስታወቂያ ሳይነገር ውሃ እና መብራት አይቆምም።ምናልባት ከዋናው ጣቢያ ሳይሆን በመንገድ ላይ በደረሰ አደጋ አገልግሎቱ ካልቆመ ማለት ነው።በዘመነ ሕወሓት ግን ውሃ እና መብራት ለሳምንት ሲጠፋ ማስጠንቀቂያ የሚባል ነገር የለም። ይህንን ነው ስርዓት አልበኝነት ወይንም አናርክዝም የነገሰበት መንግስት የምለው። የዶ/ር ደብረፅዮን መስርያቤት ለባንኮች የሚሰጠውን የኢንተርኔት አገልግሎት በማቆሙ መክፈል ያለበት በሚልዮን ምናልባትም በብልዮን የሚቆጠር ብር አለበት።ባንኮችም ለደንበኞቻቸው መስጠት የሚገባቸውን አገልግሎት በወቅቱ ባለመስጠታቸው ደንበኞቻቸው በንግድ ስራቸው ላይ ለደረሰባቸው ኪሳራ በፍርድ ቤት ከሰው የመጠየቅ መብት አለባቸው።ይህንን ስናገር በዛሬዋ የተቃወሰ መንግስት ውስጥ ስለ ሕልም እንደማወራ እንደምትገምቱ አውቃለሁ።እንደዚህ አይነት ግምት ላይ እንድንደርስ ያደረገን ግን እራሱ አናርክዝም የሰፈነበት ስርዓት ነው። ቢያንስ ግን መሆን ያለበትን እያወቅን እየሆነ ባለው መናደድ ከቻልን ለነገ መስተካከል ያለበትን ከአሁኑ እያወቅን መጣን ማለት ነው።


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።