ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, January 3, 2017

ዛሬ ኢትዮጵያ የምትሄድበትን መንገድ እያየን የነገ መውጫውን ካሁኑ መተለም የግድ ይላል (ክፍል 2 እና የመጨረሻው)



የአርባ ሶስት አመታቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት 

ከእዚህ ፅሁፍ በፊት በተመሳሳይ ርእስ በክፍል አንድ ላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የኢትዮጵያ መጪ የፖለቲካ ሂደት ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ እና ለእዚህም ሃሳብ ማምጣት እንደሚገባ ለመግለፅ ተሞክሯል።እንደ ኢትዮጵያ ባለ ከአርባ አመታት በላይ ባልተረጋጋ፣በአምባገነን እና የጎጥ ፖለቲካ ሲታመስ ለኖረ ሀገር እና ሕዝብ መጪ ጉዳይ ላይ የመስራት አስፈላጊነት ላይ መነጋገር እና ኃላፊነቱ የማን እንደሆነ ማውሳት ከጊዜው የቸኮለ ሃሳብ ሊመስል ይችላል።ለእዚህም ዋነኛ ምክንያቱ ስልጣንን በተደጋጋሚ ከህዝብ ነጥቀው በሕዝብ ደም የታጠቡ መንግሥታት ከአንዴም ሁለቴ ኢትዮጵያን የመምራታቸው እውነታ ነው።በ1966 ዓም የተነሳው የኢትዮጵያ ግብታዊ አብዮት በኃይል የነጠቀው ወታደራዊ ደርግ  መስከረም 2፣1967 ዓም የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴን መንግስት ከስልጣን ማውረዱን ሲያውጅ ¨ኢትዮጵያ ትቅደም ካለምንም ደም¨ የሚል መፈክር በታንኮቹ ላይ ሁሉ እየሰቀለ ነበር።ሆኖም ግን ደርግ ስልጣን ለሕዝብ እመልሳለሁ ያለውን ቃል አጥፎ በ1972 ዓም ኢሰፓአኮ (ኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን)፣ በ1977 ዓም ደግሞ ኢሰፓ (ኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ) መሰረትኩ ብሎ ከኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያም ሊቀመንበርነት ጀምሮ እስከ ቀበሌ መዋቅር ድረስ እራሱ ወታደሩ ስልጣኑን ተቆጣጠረ።

ከደርግ በከፋ መልኩ ሕወሓት በ1983 ዓም አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ¨ዲሞክራሲ የህልውናችን መሰረት ነው¨ የሚል ማባበያ ንግግር እየተጠቀመ የህዝብን ስልጣን ብቻ ሳይሆን የንግድ እና ምጣኔ ሀብት መዋቅር  በሙሉ በአንድ መንደር እና ስብስብ ስር እንዲውል አደረገ።ኢትዮጵያ የጥቂቶች የግል ንብረት እስክትመስል ድረስ ከመሬት እስከ ጉልት ንግድ ድረስ ለሕወሓት ታዛዥ የሆኑ ብቻ እንደፈለጉ የሚሆኑበት ሆነ።የሕወሓት እኩይ ተግባራት ከደርግ የከፋ የሆኑበት አያሌ ነጥቦችን መጥቀስ ይቻላል።ደርግ በሙስና ተግባር እና የኢትዮጵያን ሕዝብ የዜግነት መብት በመግፈፍ አይታወቅም።ሕወሓት ግን በሙስና እና ኢትዮጵያውያን የዜግነት መብታቸውን በጎሳ ስም በመግፈፍ ወደር አልተገኘለትም።በደርግ ዘመን አንድ ሰው በሀገሩ የትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሶ ለመስራት ጎሳው አይጠየቅም።በሕወሓት ዘመን አንድ ሰው ከአንዱ ወደ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ተንቀሳቅሶ ለመስራት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ከኖሩበት መሬት በጎሳ ስም የተፈናቀሉበት ዘመን ነው።ደርግ ከ17 አመታት አገዛዝ በኃላ ስልጣኑን ሲለቅ፣ሕወሓት ደግሞ ከ26 አመታት አገዛዝ በኃላ ላለመውደቅ እየተንገዳገደ ነው።መንግሥታት ይመጣሉ ይሄዳሉ። ትልቁ ቁምነገር ግን ኢትዮጵያን እንዴት በኢትዮጵያዊነቷ እንድትቀጥል እናድርግ? የነገዋ ኢትዮጵያ ባለፉት 43 አመታት ከነበረችበት የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዴት መውጣት ትችላለች? ከፖለቲካው በተጨማሪ ሌላው ቁልፍ ተግባር ምን መሆን አለበት? የሚሉት ጥያቄዎች  መመለስ መቻሉ ነው።

ከአርባ ሶስት አመታት በኃላም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙርያ የሚታዩት ሶስቱ ክፍሎች 

ኢትዮጵያ ላለፉት አርባ ሶስት አመታት ያህል በጦርነት፣በርሃብ፣በፍትህ እጦት እና በስደት ከተጎሳቆልን በኃላም  ¨የኢትዮጵያ ፖለቲካ¨ ተብሎ በሚጠራው አስተሳሰብ ዙርያ ያሉት የአስተሳሰብ ጥጎች በሶስት የግለሰብ እና ማኅበረሰብ አስተሳሰቦች ማጠቃለል ይቻላል።እነኝህ ሶስቱ አስተሳሰቦች:

1/ በወደፊቷ ኢትዮጵያ  ሁኔታ  ላይ ተስፋ ብቻ የተሞሉ 
በእዚህ ክፍል ውስጥ ይካተታሉ የምላቸው በመጪው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ በጎ ተስፋ ያላቸው ናቸው።ለተስፋቸው መነሻ ነጥባቸው ግን ድፍን ተስፋነት ይታይበታል።በድፍኑ ሕወሓት ይወድቃል፣መጪው የኢትዮጵያ ፖለቲካም ላለፉት አመታት ያየነውን አይነት ሊሆን አይችልም የሚል እሳቤ ይይዛል። ይህ ግን እንዴት ሊሆን ይችላል? ለሚለው ጥያቄ ግልፅ የሆነ መልስ አልያዙም።ብዙ የኢትዮጵያ ሕዝብ በእዚህ ተስፋ ውስጥ እንዳለ መገመት ይቻላል።ተስፋው በእራሱ በጎ ነገር ቢሆንም በእዚህ ተስፋ ውስጥ ያሉ ሁሉ ግን የእራሳቸው ድርሻ ካልተጨመረበት የነገዋ ኢትዮጵያን በብሩህ ተስፋ ማየት እንደማይቻል አለመታሰቡ ነው ክፋቱ።በእዚህ ሃሳብ ስር በውጭ ሀገር የሚኖሩ ምሁራን፣የንግድ ሰዎች፣በሀገር ቤት በልዩ ልዩ ሙያ የተሰማሩ ሁሉ ይካተቱበታል።በአቅም ደረጃም የደረጁ እና ለሀገራቸው የበለጠ አስተዋፅኦ ለማድረግ የአሁኑ ስርዓት መውረድን በጉጉት የሚጠብቁ እና ሀገራቸውን የሚወዱም ናቸው።

2/ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ከተስፋ ባሻገር ድርሻ እንዳላቸው የሚያምኑ

ይህ አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ላለፉት አርባ ሶስት አመታት ከገባችበት አጣብቂኝ የማውጣት አጀንዳ መቅደም እንዳለበት ያራምዳል።አጣብቂኙ የአምባገነን ስርዓት፣የፍትሕ እጦት፣የአንድ ጎሳ የበላይነት ሁሉ ይጨምራል።በእዚህ ሃሳብ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያውያን ኢትዮጵያን ከእዚህ አጣብቂኝ ለማውጣት ድርሻዬን መወጣት አለብኝ የሚል ቁርጠኝነት የያዙ ግለሰቦች እና የማኅበረሰብ ክፍሎች ናቸው።በእዚህ ዙርያ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞች፣የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አባሎች፣ አክትቪስቶች፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ እና ሃሳብ የሚያፈልቁ ምሁራን ሁሉ ይጠቀሳሉ።

3/ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳይ አያገባኝም የሚሉ አስተሳሰቦች  

የእዚህ አይነቱ አስተሳሰብ ሰለባዎች ስደት የሚሄደውን ኢትዮጵያዊ ለምን ተሰደደ? ብለው የማይጠይቁ፣ የኢትዮጵያ የውጭ ብድር እየጨመረ እና የውጭ ምንዛሪ በባለስልጣናት እየተዘረፈ መሆኑን እየሰሙ ቃላት የማይተነፍሱ እና ኢትዮጵያ በሕወሓት የጎሳ ፖለቲካ ስትታወክ አይመለከተኝም በሚል ስሜት በቸልተኝነት የሚኖሩ ናቸው። እነኝህ የሀገራችን ዜጎች ስለሃገራቸው የማይጨነቁ ሆነው አይደለም።ሆኖም ግን ግማሾቹ ፖለቲካ ደክሟቸዋል።የተቀሩት በእለት ከእለት ኑሮ ውስጥ ተውጠዋል።ከፖለቲካ ውጭ የሚሰሯቸው በርካታ ተግባራት መኖራቸውን እና እነኝህ ተግባራት ደግሞ ለነገዋ ኢትዮጵያ ወሳኝ መሆኑን ያልተረዱ ናቸው።

ሶስቱም ክፍሎች ለኢትዮጵያ ያስፈልጋሉ 

ከላይ የተጠቀሱት በሙሉ ተስፋ ውስጥ ያሉትም ሆኑ፣ ድርሻቸውን አውቀው እየሰሩ ነገን  በተስፋ የሚያዩት እና የፖለቲካ ጉዳይ አያገባኝም ያሉት ሁሉ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ እና ጠቃሚ ናቸው።አንዳንዶች ስለፖለቲካ አያገባኝም የሚሉትን የኢትዮጵያ ጠላት አድርገው የሚፈርጁ አሉ።አንዳንድ ጊዜ ፖለቲካ አያገባኝም ያሉ ሰዎች ለሕብረተሰባቸው፣ለሀገራቸው እና ለዓለም ምን እየሰሩ ነው ብለን ጠጋ ብለን ስንመለክት በማኅበራዊ  ወይንም በምጣኔ ሀብት ዘርፍ ትልቅ ሥራ ላይ እንደሆኑ ትመለከታላችሁ።ይህ ማለት በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት ፖለቲካ ባያንፀባርቁ ለኢትዮጵያ ግን ዛሬም ነገም ጠቃሚ እሴቶች ናቸው። በእርግጥ እኔም ለመመለስ የምቸገርበት በከፍተኛ አቅም ያሉት እነኝህ ኢትዮጵያውያን   ፖለቲካ ያሉትን ባይነኩት የሰብአዊ መብት ሲጣስ እና ፍትህ ስትረገጥ ዝምታው ለነገ ትውልድም ጭምር ዋጋ እንደሚያስከፍል ምን ያህል ከግንዛቤ አስገብተውታል? የሚለው ጥያቄ አሁንም የሚነሳ እና ምላሽ የሚሻ ነው። ቁም ነገሩ ግን አሁንም ሶስቱም ክፍሎች ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ናቸው የሚለው ሃሳብ ነው።ችግሩ ሶስቱንም እንዴት ለሀገር ጥቅም እንጠቀምባቸው? ሶስቱ አስተሳሰብ ውስጥ ያሉት አንዳቸው ከአንዳቸው ሳይጋጩ እንዴት ያላቸውን አቅም ለነገዋ ኢትዮጵያ ህልውና እንደየዝንባሌያቸው እንጠቀምባቸው? የሚለው ነው። 
 

የኢትዮጵያ የነገን  ፖለቲካ ለማስተካከል ማን ምን የስራ?

ኢትዮጵያ አጠገባችሁ ነች።

ብዙዎች ለኢትዮጵያ ምን ለስራ? የእኔ ሚና እና ድርሻ ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሲቸገሩ ይታያሉ።አሁን ባለንበት ጊዜ ለኢትዮጵያ መስራት ማለት ከሕወሓት ጋር ግብ ግብ መፍጠር ብቻ የሚመስላቸውም አሉ።በርግጥ ኢትዮጵያን ወደ ሚቀጥለው የተሻለ ደረጃ ለማሻገር አሁን በጎጥ ሕዝብ እና ሀገር ከፋፍሎ የሚገዛው ስርዓት መወገድ ጥያቄ ውስጥ አይገባም።ሁሉም ሰው ግን እኩል ተሰጥኦ እና ችሎታ አለው ማለት አይቻልም።ኢትዮጵያን ስናስባት ከሕወሓት ውድቀት በኃላ ስለምትኖረውም ማሰብ ስንጀምር ዛሬ መሰራት ያለባቸው ስራዎች ፍንትው ብለው ይታዩናል።ስለሆነም ከላይ ተራ ቁጥር 1 እስከ 3 በተጠቀሰው ስር የሚገኙ ሁሉ በየትኛውም ጥግ ላይ ቢቆሙ ለነገዋ ኢትዮጵያ መስራት የሚገባቸው በርካታ ስራዎች አሉ።ከእነዚህ ውስጥ በዋናነት ለእዚህ ፅሁፍ ላተኩርበት የምፈልገው የተዳከመውን ማኅበራዊ አንድነት ለመጠገን እና ያለውን ለማጠንከር ድርሻን መወጣት በሚለው ነጥብ ላይ ነው።

የተዳከመውን ማኅበራዊ አንድነት ለመጠገን እና ያለውን ለማጠንከር ድርሻን መወጣት 

ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን አደጋ ላይ ከሚጥሉት አደጋዎች ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያውያንን ማኅበራዊ አንድነት መናጋት ነው።ብዙውን ጊዜ ሀገር የሚፈርሰው ድንበር ሲጣስ እና የውጭ ወራሪ ሲመጣ ብቻ የሚመስለን ጥቂቶች አይደለንም።አሁን ባለንበት ዓለም ግን በርካታ ስልታዊ ስራዎች በማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ዘርፍ ላይ በመስራት በአንድ ሀገር ላይ ከባድ ጥፋት ማስከተል ይቻላል። ስለሆነም ኢትዮጵያ ነገን እንድትሻገር በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ጎሳን መሰርት ያላደረገ ማኅበራዊ አንድነትን ማጠንከሩ አንዱ አስፈላጊ ጉዳይ ነው ማለት ነው። በየትኛውም እድሜ ክልል ቢሆኑ ኢትዮጵያ ወደተሻለ ደረጃ እንድትደርስ ሊነሱ የሚገባቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉ። እነርሱም: በሰፈርዎ የሚሰሩ ምን ስራዎች አሉ? የሰፈርዎ ዕድር ፈርሷል? የሚኖሩበት የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ (ኮሚኒቲ) ተዳክሟል? ምን አይነት ኢትዮያጵያዊ ስብስቦች አሉ? የእርስዎስ ድርሻ በስብስቦቹ መጠናከር ዙርያ ምንድን ነው? የኢትዮጵያውያንን ህብረት፣መተሳሰብ እና አንድነት የሚይጥላላ ወይንም የሚያዳክም ተግባር አለ? ይህ የማዳከም ተግባር ካለስ እርስዎ ምን የመከላከል ሥራ ሰሩ? እና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ፖለቲካዊ ያልሆኑ ነገር ግን ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ማሻገር የሚችሉ ተግባራት አሉ።ብዙዎች እነኝህ የሚንቁት ምናልባትም ብዙ አንገብጋቢ ስራዎች የማይመስሏቸው ተግባራት ናቸው።በኢትዮጵያ ውስጥ ግን የጎሳ ፖለቲካ 26 ዓመታት ሙሉ ታውጆብን እንደ ሕዝብ በህብረት ያቆመን የማኅበራዊ አንድነታችን  ሙሉ በሙሉ ያለመፍረሱ እና መኖር ነው። 

የማኅበራዊ አንድነት አሁን ባለንበት ዘመን እራሱን የቻለ አንዲት ሀገር ከሚኖራት ሀብት መካከል የሚቆጠር ነው። ማኅበራዊ አንድነት በሀብት መልክ ሲገልጥ ደግሞ ማኅበራዊ ካፒታል ይባላል። ማኅበራዊ ካፒታል የአንድ ሕዝብ የማይዳሰስ ሀብት ውስጥ የሚመደብ እና የህዝብ የእርስ በርስ የመተማመን ደረጃ ሁሉ የሚገለጥበት አይነተኛ መንገድ ነው።

ማኅበራዊ ካፒታል መንከባከብ፣መጠበቅ እና መጎልበት ይፈልጋል።ይህ ካልሆነ በተቃራኒው እየቀጨጨ እና እየደከመ የመምጣት ዕድል ይገጥመዋል።ይህ ማለት ሀገር እና ሕዝብ በጋራ የሚቆሙለት የጋራ እሴት ሁሉ እየመነመነ ይመጣል ማለት ነው።ማህበራዊ ካፒታሉ የላላ ሕዝብ ደግሞ አምባገነኖችን ሊዋጋ ቀርቶ ወደ እርስ በርስ ግጭት የመግባት መጥፎ ዕድል ይገጥመዋል።

ባጠቃላይ ዛሬ ኢትዮጵያ የምትሄድበትን መንገድ እያየን የነገ መውጫውን ካሁኑ መተለም ማለት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከሀገር ቤት እስከ ባህር ማዶ ያለው ሁሉ አካባቢውን በአግባቡ እንዲቃኝ ማስቻል ነው።ዛሬ በአካባቢያችን ባሉ ኢትዮጵያውያን ዙርያ ያልሰራናት ኢትዮጵያ ነገ ከየትም አናገኛትም። ምናልባት ለመልካም ሥራ ስንነሳ በእራሳችን ላይ የሚደርሱብን አያሌ በደሎች በጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች እና በሕወሓት ስውር ተንኮል ጉዳት ሊደርስብን ይችላል። ሆኖም ግን መመልከት ያለብን ጥቂት ደካማ አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች ኢትዮጵያውያንን ሁሉ የማይወክሉ መሆናቸውን ነው።በመሆኑም ከሕወሓት በኃላ የምትኖር ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማሻገር የግለሰቦችን በደል ወደ ጎን ትቶ ስለ ትልቅ ኢትዮጵያ ለመስራት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በአካባቢው የፈረሰውን ወይንም የተዳከመውን የኢትዮጵያውያን የጋራ ማኅበራዊ እሴት በሙሉ ለማጠናከር ቆርጠው መነሳት እና ወደ ሥራ መሰማራት አለባቸው። ያን ጊዜ የዛሬዋን ብቻ ሳይሆን የነገዋ ኢትዮጵያ የማይጎረብጣት ለም መሬት አዘጋጀን ማለት ነው።በእዚህም የኢትዮጵያን የቅርብም ሆነ የሩቅ ጠላቶችን ሕልም የማምከን ስልታዊ ሥራ መስራት ይቻላል።ማኅበራዊ አንድነታችንን እና እሴቶቻችንን እናጠናክር፣እንንከባከብ፣ አስፈላጊ ሲሆንም እንመስርታቸው።


ጉዳያችን GUDAYACHN

 www.gudayachn.com

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...