ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, October 6, 2016

የትግራይ ሕዝብ ሕወሓት በግብፅ ሊያስመታህ መሆኑን ዕወቅ! እንዴት? (የጉዳያችን ማስታወሻ)






ጉዳያችን / Gudayachn
www. gudayachn.com 
መስከረም 27/ 2009 ዓም 
==============================

ሰሞኑን ኢቲቪ ግብፅ ተቃዋሚዎችን እየረዳች ነው የሚል ዜና የግብፅ ቴሌቭዥን ያቀረበውን ዘገባ በመጥቀስ አሳይቷል።
በመጀመርያ ደረጃ ግብፅ ይህንን የማታደርግ ቢሆን ነው የሚገርመው።ግብፅ ምን እንደምታደርግ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ በትርጉም መፅሃፎቻቸው ሲነግሩን ነው ያደግነው።´´የካይሮ ጆሮ ጠቢ´´ ላይ በጀርመን ዜግነት ግብፅ ገብተው ከላይ እስከ ታች የበረበሯት እነ ዎልፍጋንግ ሎትዝ ታሪክ ትዝ ይለናል።አሁን ቁም ነገሩ ግብፅ ግድብ አትፈልግም፣ተቃዋሚ እረዳች አይደለም።ይህንን ባታደርግ በገረመን።

ዋናው ነጥብ የችግሩ መነሻ እና የችግሩ ውጤት መለየት ላይ ነው።ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የህዝብ መነሳሳት መነሻ ግብፅ ሳትሆን ሕወሓት ነው።ስልጣን አልለቅም ያለው እና ለሕዝብ ታማኝ ያልሆነው ሕወሓት ነው።የሕወሓት መነሻ ችግር ሲመነዘር ውጤቱ ግብፅ ተቃዋሚ እንድትረዳ አደረጋት። እኛ ቤታችን እንድናስተካክል ሕወሓት እንቅፋት ባይሆን ኖሮ ግብፅ ባልረዳች።በሌለ እሳት ላይ እሳት መጫር አትችልም ነበር።

ሕወሓት እያደረገ ያለው ሁሉ ግብፅን ወዴት ይመራል? የሚለው ላይ ጥቂት ላንሳ።ግብፅ ግድብም እንበለው ሌላ አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት እንዲወርድ ትፈልጋለች እንበል።በእዚህም ሳብያ ጦርነት ብትከፍት ማን የበለጠ ዕድል አለው? ግብፅ የጋራ ድንበር አትጋራንም።ይህ ማለት በጦርነት ከኢትዮጵያ ይልቅ የተሻለ ዕድል የሚሰጣት ለግብፅ ነው ማለት ነው።

ለምን? 

ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር በጋራ ድንበር እስካልተጋራች ድረስ ጦርነቱ ሲጀመር (መሸጋገርያ መሬት ካልተገኘ በቀር) በአየር እና በሚሳኤል መደብደብ አማራጭ እና በአጭር ጊዜ ጦርነቱን ለመፈፀም ይረዳታል። በአየር ኃይል አቅምም ሆነ በአጭር ርቀት ሚሳኤል ውግያ ግብፅ ከኢትዮጵያ የተሻለ አቅም እንዳላት እገምታለሁ። ግብፅ የተቃዋሚ ኃይል በሚገባ ካልገፋ ግብፅ በአየር ወይንም በሚሳኤል ጥቃት ልትፈፅም ትችላለች።ጥያቄው የት ላይ ጥቃት ልትፈፅም ትችላለች? የሚለው ነው። እንደሚመስለኝ ሁለት የተመረጡ ኢላማዎች ትመርጣለች።

1/ የታወቀው ግድቡ የሚገኝበት ቦታ 

ግድቡ የሚገኝበትን ቦታ  በመምታት የምታገኘው ጥቅም እና ጉዳትስ ምንድነው?  

 1/  ግድቡን ከመታች  የምትጎዳው 

    ሀ/  የግድብ ስራው ላይ በድርድር የተያዘ ጉዳይ ካልሆነ  በመጪ መንግስትም ቢሆን የተራዘመ እና አጨቃጫቂ የካሳ ጥያቄ ማስነሳቱ  አይቀርም እና ለዘለቄታ የውሃ መፍትሄ አይሆንም።ይልቁንም ለትውልድ የሚቆይ ሌላ ውስብስብ ጉዳይ ታቆያለች።ውሃ የአንድ ትውልድ ጥያቄ ሳይሆን የመጪውም ትውልድ ነው።የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትርን የሚያማክር ሰው ይህንን አማራጭ ብሎ ላይወስደው ይችላል።ሆኖም ለጊዜው ለራስ ምታት የሚሆን መፍትሄ ሰጪ (እንደ ፓናዶል) ከሆነ ግን መፍትሄ ሊለው ይችላል።

   ለ/ ከአፍሪካ ሀገሮች እና ከአፍሪካ ህብረት በኩል በአረብ ሀገሮች የመጠቃት ትልቅ ስሜት ይፈጥራል።የግብፅ መዋለ ንዋይ በጥቁር አፍሪካ ሀገሮች  ውስጥ ግንኙነቱ ይበላሻል።የዩጋንዳው መሪ ለእዚህ ምሳሌ ናቸው።በግንባር ቀደምትነት ግብፅ ትዕቢት እንዳይዛት በአደባባይ ተናግረዋል።ብዙ አፍሪካ ሀገሮችም ከመካከለኛ ምስራቅ በኩል የሚመጣ የወታደራዊ ጡንቻ ማፈርጠምያ ልምምድ አድርገው ስለሚያዩት ከኢትዮጵያ ጋር መቆማቸው አያጠራጥርም (ጥሩ መንግስት ስናገኝ በተለይ በቀላሉ ማስተባበር ይቻላል)። ይህም ግብፅ በተቻለ መጠን ከአፍሪካ ጋር ያላት ግንኙነትን ማቆም አትፈልግም።

2/ ግድቡን ከመታች የምትጠቀመው 

ግብፅ ግድቡን ከመታች የምትጠቀመው አንድ ነገር ነው።ይሄውም አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት በሀገሩ የግብፅን ሕዝብ ጉራ ያተርፋል፣ህዝቡ ያፏጭለታል፣ግብፅን ከውሃ ስጋት ያዳነ አንበሳው መንግስት ይባላል።እግረ መንገዱን በአካባቢው ተፅኖ ፈጣሪ ግልገል ኃያል መሆኑን ያሳይበታል።ይህ ግን ጊዜያዊ ጥቅም ነው።

ስለዚህ ግብፆች ሊያደርጉ የሚችሉት አስጊው ጉዳይ ምንድነው?

ግብፅ የኢትዮጵያን የውስጥ ፖለቲካ መከታተሏ የማይጠረጠር ነው።ስለሆነም አሁን ያለውን ሕወሓት በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል የፈጠረው ልዩነት ያውቁታል።ይህንን ኢቲቪም አምኗል።ስለሆነም ወደ ኢትዮጵያ የሚወረውሩት እያንዳንዱ በአየር ኃይል የተጫነ ጥይትም ሆነ ሚሳኤል ሁለት ነገሮችን ማሟላት አለበት።

አንድ፣የኢትዮጵያ ህዝብን ሆ! ብሎ ሉዓላውነቴ ተደፈረ ብሎ እንዲነሳ የማያደርግ እና ውስጣዊ ህብረት የማይፈጥር። 

ሁለት፣ ለዘለቄታ ማለትም ከመጪው መንግስት ጋር የማያቃቅር መሆን አለበት።ለእዚህ ደግሞ ቢያንስ የሁለቱን ትልልቅ ብሔሮች ማለትም የዐማራ እና ኦሮሞ ብሔሮችን የማይነካ ያሉትን (ነው አላልኩም ግብፆች የሚገምቱትን)  የሕውሓት መንግስት ላይ ብቻ ያነጣጠረ ጥቃት  ማለትም በትግራይ የሚገኙ ፋብሪካዎችን፣የአየር ኃይል ጣብያ፣መቀሌ እና ሌሎች ቦታዎች ያሉ ግንባታዎችን ላይ ሁሉ ጥቃት ሊፈፅሙ ይቻላሉ። በእዚህ ደግሞ ሁለት ጥቅሞች የሚያገኙ ይመስላቸዋል። እነርሱም : - 

  1/ በሕወሓት የተበደለው ሕዝብ ኢትዮጵያ ተጠቃች የሚል ስሜት ሳይሆን ይልቁንም ሕወሓት ተጠቃ በሚል ስሜት በግብፅ ይደሰታል ብለው ያስባሉ።ለባድማ ደሙን የገበረውን ሕዝብ ሕወሓት ስላስከፋው እና ስለገደለው አሁን እንደ እዚህ በፊቱ አይነሳም የሚል እሳቤ ይይዛሉ። 

2/ ለመጪው መንግስት መቀጣጫ ይሆናል።የውሃ ጉዳይ መንግስት እንደሚያስቀይር ትምህርት ይሆናል ብለው ያስባሉ። 

ስለሆነም ሕወሓት የግብፅ ጉዳይ ሲያነሳ ግብፅ ተቃዋሚን መርዳት የመጀመርያ ሥራ እንጂ በቀጣይ ጥቃት ሊኖር ቢችል  ጥቃቱ አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት የተሰበሰበ ኃይል አለ ብላ ግብፅ በምታስበው ላይ ነው የምታደርገው።ለእዚህም ኤርትራ ከምታደርገው ግብፅ ብታደርገው የተመረጠ እንደሆነ የሚመክሩ የጎረቤት ሀገሮች አይጠፉም።

ስለሆነም የትግራይ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ጋር ትግሉን አስተባብሮ ሕወሓትን ማስወገድ እና ኢትዮጵያን አብሮ መገንባት ብቸኛ አማራጩ ነው።ይህ ካልሆነ ግን ትግራይ እራሷን እንድትነጥል እያደረገ በግብፅ የሚያስመታት የትግራይ ወዳጅ መስሎ የሚያስጠፋት እራሱ ሕወሓት እንደሆነ ማወቅ ተገቢ ነው።


ጉዳያችን GUDAYACHN

 www.gudayachn.com

No comments: