ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, October 5, 2016

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ በተመለተ: እየሆነ ያለው፣የፖለቲካ ኃይሎች አሰላለፍ፣የውጭ ኃይሎች አጀንዳ እና ለነገዋ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ያድርጉ? (የጉዳያችን ማስታወሻ)


ኢትዮጵያ ውስጥ የለውጥ እንቅስቃሴው እያየለ ነው።ይህ ለቀባሪው ማርዳት ነው። 
ስለሆነም ከእዚህ በታች ያሉት ወቅታዊ የሀገራችን ጥያቄዎች ላይ ያለኝን ምልከታ ለማስፈር እሞክራለሁ።የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ አስመልክቶ በብዙዎቻችን ውስጥ የሚንገዋለሉ ጥያቄዎች ብዬ ከምገምታቸው ውስጥ:- ምን እየሆነ ነው? የወቅቱ የፖለቲካ ኃይሎች አሰላለፍ ምን ይመስላል? የውጭ ኃይሎች አጀንዳ ምን መልክ አለው? የነገዋ ኢትዮጵያን ለመገንባት የፖለቲካ ፓርቲዎች  ምን ያድርጉ?  የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

  ምን እየሆነ ነው?


ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው ግልፅ ነው።ለ25 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን በመጀመርያ በሽግግር መንግስት ስም ፣ ቀጥሎ በአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ስም፣በማስከተል በልማታዊ መንግስት ለወደፊቱ ደግሞ ´´በስር ነቀል ታዳሽነት´´ ስም ኢትዮጵያን የገዛው እና ለመግዛት የሚመኘው የሕወሓት መንግስት በሁሉም መስፈርት በሕዝብ ሞራላዊም ሆነ ሕጋዊ መሰረቱን በማጣቱ ከስልጣን እንዲወርድ በሚፈልግ በብዙሃኑ ህዝብ በአንድ በኩል በሌላ በኩል ደግሞ  በሕወሓት እና የጥቅም ተጋሪዎቹ በአንድነት ሆነው የተሰለፉበት የነፃነት ትግል ነው።አሁን እየሆነ ያለው ባጭሩ ይህ ትግል ከሰላማዊ ወደ ትጥቅ እና የመረረ ትግል መሸጋገሩ  ነው አዲሱ ክስተት።

የወቅቱ የፖለቲካ ኃይሎች አሰላለፍ ምን ይመስላል?


በዓላማ እና ግብ አንፃር ስንመለከተው የፖለቲካ ኃይሎቹ እራሱ ሕወሓትን ትተን ተቃዋሚዎች በግልፅ በፖለቲካ ኃይልነትም ሆነ እራሳቸውን በተለያየ አደረጃጀት ያደራጁ፣ ግን ምን ያህል የሀገር ቤት መሰረታቸው የጠለቀ መሆኑ ያልለዩ ኃይሎች አሉ።ይህ ማለት ስርዓቱ አፋኝ እንደመሆኑ መጠን የፖለቲካ ኃይሎችም በተቻለ መጠን ሚስጥራዊ ባህሪ እንዲይዙ ማድረጉ ይታመናል።ሁሉም ተቃዋሚ ኃይሎች ግን  በአንድ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ ዓላማ አላቸው።ይሄውም ሕወሓትን ከስልጣን  በማውረድ ላይ ነው።

ቀደም ብሎ የነበረው የፖለቲካ ኃይሎች አሰላለፍ በሁለት የሚከፈል ነበር።ይሄውም የአንድነት ኃይል እና የብሔር ፖለቲካ ኃይሎች የሚሉ ነበሩ።የአንድነት ኃይሉ ፍፁም አሃዳዊ የመንግስት ስርዓት ሳይሆን የፌድራል መንግስትነትን የሚቀበል ነገር ግን የብሔር አደረጃጀትን አደገኛ ብሎ የሚጠራ ነው።የብሔር ፖለቲካ አራማጆች የእራስን ሀገር እስከመመሥረት የሚሄድ አጀንዳ አስቀምጠው የሚሄዱ ናቸው። ከእዚህ አይነቱ አሰላለፍ ለየት ያለ ብሔርን መነሻ ያደረገ ነገር ግን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ሳይቀይር ´´ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!´´ በሚል መፈክር ብቅ ያለው የቅርቡ እንቅስቃሴ ደግሞ ´´የዐማራ ተጋድሎ´´ የተሰኘው ነው።ይህ እንቅስቃሴ ትኩረቱ አንድ ብሔር ላይ ሆኖ ግን የነፃነት ጥያቄን ያላነሳ ኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያለ የፖለቲካ፣ምጣኔ ሀብት እና ማኅበራዊ መሰረቱ ያልታሰረ የዐማራ ብሔረሰብ ተሳትፎ እንደሚታገል እንቅስቃሴው በተለያዩ መግለጫዎች ገልጧል። 

እዚህ ላይ የአንድነት እና ኢትዮጵያዊነት መነሻ ያደርጉ የፖለቲካ ኃይሎች ለምሳሌ ´´የአርበኞች ግንቦት ሰባት´´ የመሳሰሉ ግልፅ ግብ እና የፖለቲካ ፕሮግራም ሲኖራቸው ብሔርን መሰረት አድርገው የሚንቀሳቀሱት እንቅስቃሴዎች ለምሳሌ የኦሮሞ ተቃውሞ (Oromo protest) እና የአማራ ተጋድሎ በፖለቲካ ፓርቲነት ያልወጡ ግን ተፅኖ የመፍጠር ኃይላቸውን እያጎለበቱ የመጡ ናቸው።

በተለይ የኦሮሞ ተቃውሞ እስከ እዚህ ሳምንት መጀመርያ ድረስ እንቅስቃሴው ወዴት እንደሚሄድ እና ግቡ ምን እንደሆነ አልታወቀም ነበር። በእዚህ ሳምንት መስከረም 23፣2009 ዓም ላይ አቶ ጀዋር  መሐመድ ከኦሮሞ አክትቪስቶች አንዱ ሚኒሶታ ላይ በተደረገ አንድ ስብሰባ ላይ እንደገለፀው  የኦሮሞ ተቃዋሚዎች ´´የኦሮምያ ነፃነት  ሽግግር ቻርተር´´ ለማዘጋጀት እየሰሩ መሆኑን እና የወታደራዊ ክንፍ እንደሚኖረው ገልጧል።እዚህ ላይ ´´የኦሮምያ ነፃነት  ሽግግር ቻርተር´ የሚለው አገላለፅ በበርካታ በኢትዮጵያውያን የኦሮሞ ተወላጆች እና ቀሪው ኢትዮጵያውያን ዘንድ አነጋጋሪ ሁኔታ ፈጥሯል። የፀረ ሕወሓት ትግሉ በሁሉም ኢትዮጵያውያን እየተደረገ እና ለጋራ ሽግግር  የሁሉንም ኃይሎች መሰባሰብ ሕዝብ እየጠበቀ ባለበት በእዚህ ወቅት ´´ኦሮምያ ለብቻዋ የምትሸጋገርበትን ቻርተር ታፀድቃለች´´  የሚለው የጀዋር ንግግር  በርካታ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ላይ እንዲፈጥር  ሆኗል። 

ጉዳዩ በተለይ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ዝምታ ለበለጠ ጉዳት እንዳይዳርግ የብዙዎች ስጋት ነው።በተለይ  ከእዚህ በፊት በኦሮሞ የመብት ትግል ውስጥ ከወያኔ ውድቀት በኃላ በኢትዮጵያ ውስጥ ችግሮችን  መፍታት ይቻላል የሚል ፅኑ እምነት ያላቸው የኦሮሞ ተወላጆች በርካታ ጥያቄዎች እንዲያነሱ ሆኗል።ከእነኝህ ጥያቄዎች ውስጥ በእኛ ላይ የነፃነት  ወይንም ከኢትዮጵያ የመለየት ቻርተር ማን ነው የሚያፀድቀው? እንቅስቃሴው ባብዛኛው በሙስሊም  ፅንፍ በያዙ አካሎች ነው የሚመራው የሚባለው ሐሰት አይደለም ማለት ነው?  ኦሮምያ ብቻዋን ከሌላው ኢትዮጵያ ተነጥላ  ትሸጋገራለች ማለት ምን ማለት ነው? በእዚህ ሂደት ውስጥ ከኦሮምያ ተወላጆች በተለየ የእምነት ልዩነት ሁለንተናዊ የአቅም ድጋፍ የሚደረግላቸው እና ኦሮምያን ከሌላው ኢትዮጵያ የመነጠል ዋና ግብ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አሉ ወይ? የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች አስነስቷል። የኦሮምያ የሽግግር ቻርተር በተመለከተ ጃዋር የተናገረውን ለማንበብ ይህንን ይጫኑ።(የኦሮሞ ተቃውሞ መሪዎች የኦሮሚያ ነፃነት ቻርተርና የሽግግር መንግስት ዝግጅት እያደረጉ ነው)።


ባጠቃላይ የፖለቲካ ኃይሎችን አሰላለፍ በእዚህ አጭር ፅሁፍ ብዙ ማለት ባይቻልም የኃይል ሚዛን ለማስተካከል እና አንዱ ከአንዱ ልቆ በመታየት ነገ ሌላ የአምባገነን ስርዓት እንዳናስተናግድ ካሁኑ መታረም የሚገባቸው ጉዳዮች በወቅቱ መታረም አለባቸው።ይህንን ለማድረግም የፖለቲካ ኃይሎች ከአሁኑ መጠናከር እና ሕዝባዊ መሰረታቸውን ማጠንከር ይጠበቅባቸዋል።የኢትዮጵያ ህዝብም ትግሉን ሲያከሂድ መገንዘብ ያለበት ነገ እንደ ሕዝብ የማያኖሩ ፅንፍ አካሄዶች የያዙ በተለይ የኢትዮጵያን መሰረት ከባዕዳን ጋር  በመሻረከ ለማጥፋት የሚፈልጉትን ሕዝባዊ መሰረት እንዳይኖራቸው ከአሁኑ ነቅቶ መጠበቅ አለበት። በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥም ከዳር የተቀመጡ ምሁራን እና ዜጎች የኦሮሞ ፖለቲካ የጥቂቶች ፖለቲካ እንዳይሆን በስፋት ገብቶ ወይንም የመሰላቸውን የፖለቲካ አስተሳሰብ ማራመድ እና የኢትዮጵያ አንዱ እና ትልቁ መሰረት የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ባልሆነ የመለያየት ፖለቲካ ትግሉ እንዳይታገት ሊታደጉት የግድ ይላል።

የውጭ ኃይሎች  አጀንዳ ምን ሊሆን ይችላል? 


የውጭ ኃይሎች አጀንዳ ብዙም አሻሚ አይደለም።የውጭ ኃይሎችን አካባቢያዊ ጥቅም (Regional Strategic Interest) ያላቸው እና የእሩቅ ፍላጎት ( Geo-political interest) ያላቸው ብለን በሁለት መክፈል እንችላለን። የአካባቢ ውስጥ ሳውዲ አረብያ እና ግብፅ ሲሆኑ በሩቁ ውስጥ ልዕለ ኃያሏ አሜሪካንን መጥቀስ ይቻላል። የሁለቱም ኃይሎች ፍላጎት የተለያየ ቢሆንም በአንድ ነገር ላይ ግን ይስማማሉ።እርሱም  በመጪው መንግስት ላይ ተፅኖ ፈጣሪ መሆን እና የእየራሳቸውን አጀንዳ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንዲያስፈፅምላቸው መጣር  የሚሉት ናቸው። ይህ አሁን ሕወሓትን ከማስወገድ ትልቁ አጀንዳ ጋር መጋጨት የለበትም።ምክንያቱም በሕወሓት ዘመን የምትኖር የተከፋፈለች ኢትዮጵያ  የበለጠ ለውጭ ኃይሎች የተጋለጠች ነች እንጂ የፖለቲካ ችግሯን የፈታች አገር  አደጋ ላይ ትሆናለች ብሎ ማሰብ አይቻልም። ስለሆነም ሕወሓትን ከስልጣኑ አንስቶ በህዝባዊ መንግስት መተካት ቅድምያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።

ባጭሩ የውጭ ኃይሎች አጀንዳ የተበታተነች ኢትዮጵያን ከመናፈቅ አንስቶ እስከ አንድነቷ የተጠበቀ እና አካባቢ ተፅኖ የመፍጠር ያላት ግን ከባእዳኑ ጥቅም ጋር ያልተጋጨች ኢትዮጵያን ለማየት እንስከመፈለግ ድረስ ያለመ ሂደት መኖሩን ማወቅ አለብን።

የነገዋ ኢትዮጵያን ለመገንባት ዛሬ ምን መደረግ አለበት?

 

አሁን በተጨባጭ የሚታየው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሂደት እየመራ ያለው ሀገር ቤት የሚገኘው ወጣቱ ትውልድ ነው።በፀረ ሕወሓት ትግሉም በግንባር ቀደምትነት እየተሳተፈ ያለው አሁንም ወጣቱ ነው።ይህ ወጣት እራሱን ከሕወሓት ታንክ ጋር በባዶ እጁ ሲፋለም አንድ የሚያልመው እና የሚናፍቃት ኢትዮጵያ እንዳለች ለማወቅ ነቢይ መሆን አይጠይቅም።አንድ ነገር ግን እርግጠኛ መሆን ይቻላል የወያኔ አይነት ግልባጭ የጎሳ ፖለቲካን አይናፍቅም።ይህ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ደሙን የወያኔን ዘረኛ ስርዓት ለማውረድ ባልተፋለመ ነበር። ስለሆነም መጪዎቹ የፖለቲካ ኃይሎች አዲስ ነገር ይዘው የማይመጡ ከሆነ እንደ ወያኔ በሕዝብ ታንቅረው እንደሚጠሉ ማወቅ ቀላል ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች አሁን ላይ መስራት የሚገባቸው የቤት ስራዎች ውስጥ: -

1/ ከአክትቪስት ሥራ ወጥተው የመሪነት ተግባራቸውን መስራት፣

2/ የፖለቲካ መድረኩን ብቃት ያላቸው እና የሚያጋጥሙ ችግሮችን ወደ መልካም ዕድል የመቀየር አቅም ያላቸውን መሪዎችን ወደፊት ማምጣት፣

3/ የፖለቲካ ለውጥ ዋዜማ ላይ እንደመሆናችን መጠን ለእያንዳንዱ የፖለቲካ ክስተት በቶሎ በቂ ምክንያቱን እና ግልፅ ዕይታን ለሕዝብ መግለፅ።በተለይ የእዚህ አይነቱ ተግባር ሕዝብ በአንድ የፖለቲካ ጉዳይ ክስተት ላይ የተለያየ አስተሳሰብ እንዳይይዝ ክስተቱን የሚመለከትበትን ዕይታ ቅርፅ እንዲይዝ ያደርጋል።ስለሆነም ህዝብን በህብረት እና የዓላማ ግብ ዙርያ የበለጠ  ያስተሳስራል፣

4/ ለኢትዮጵያ አንድነትም ሆነ ለሕዝቡ ሰላም አስጊ የሆኑ ኃይሎች ሕዝብ እንዳያታልሉ ትግሉን በማይጎዳ መልኩ  ለሕዝብ መረጃ እንዲደርስ ማድረግ እና ሕዝብ የእራሱን ግንዛቤ እንዲወስድ ማብቃት፣

5/ የመገናኛ ብዙሃንን አቅም በበለጠ ማሳደግ፣ማግነን እና ተአማኒነቱን ማፅናት፣ 

6/ ሕዝብ ለአገሩ የመረጃ ምንጭ እንዲሆን እና ወደ ዲሞክራሲያዊ፣ፍትህ እና እውነተኛ የተባበረች ፌድራላዊት  ኢትዮጵያን እንዲያልም እና ወደዛ የሚወስዱ መንገዶች እና ስልቶችን ከወዲሁ እንዲያውቅ ማድረግ እና  ለአፈፃፀሙም ብቃት ያለው እንዲሆን ማዘጋጀት እና 

7/ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲቆም ለማድረግ አማራጭ ኃይል ሆኖ መገኘት የሚሉት ናቸው። 

በእርግጥ ከላይ የተጠቀሱት በእራሳቸው ሰፊ ማብራርያ ይፈልጋሉ።ሆኖም ግን በእራሳቸውም ደግሞ ሃሳቡን ይገልፃሉ።በእዚህ ፅሁፍ ላይ የሕዝብ ሚና ላይ ያልተጠኮረው ሕዝብ የእራሱን ድርሻ እየተወጣ ስለሚገኝ መሆኑ ከግንዛቤ ውስጥ ይግባ።

ባጠቃላይ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ወሳኝ ወቅት ነው።የፖለቲካ መፍትሄውም ከሕወሓት በኩል ፈፅሞ ስለጨለመ ስርዓቱ ይህን ቢያደርግ ይህንን ባያደርግ የሚል ሃሳብ እዚህ ላይ ማካተት አስፈላጊ ሆኖ አልታየኝም። ምክንያቱም ቢያንስ ላለፉት አምስት ዓመታት ይህ ቢደረግ ይህ ባይደረግ ሲባል ተከርሟል። አሁን ወሳኙ ሕዝብ ሆኖ ወጥቷል።የኢትዮጵያ የዛሬውም ሆነ የወደፊቱ  ተስፋዋ እግዚአብሔር እና ሕዝብ ናቸው።ሁለቱም ግን በጥንቃቄ መያዝ ይፈልጋሉ። እግዚአብሔርም ተገቢውን አምልኮ፣ሕዝብም ብቃት ያለው የፖለቲካ አመራር።



ጉዳያችን GUDAYACHN 
  www.gudayachn.com

No comments: