ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, October 16, 2016

ሕወሓት በአሰቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊያሳካ ያሰበው ግልፅ እና ድብቅ ግቦች


ጉዳያችን / Gudayachn  
ጥቅምት 7፣2009 ዓም
www.gudayachn.com
=====================

የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኢትዮጵያ ላይ ከታወጀ ጥቂት ቀናት ውስጥም በሕወሓት ላይ የሚደረገው ተቃውሞ የመቀነስ አዝማምያ አላሳየም።በባህር ዳር የስራ ማቆም አድማ የተደረገው ከአዋጁ በኃላ ነው፣ አሁንም ከአዋጁ በኃላ በሰሜን ጎንደር የትጥቅ ትግሉ ቀጥሏል፣ ባለፈው ዓርብ በጎንደርም የስራ ማቆም አድማ እንዲደረግ ጥሪ ቀርቧል።ይህ ሁሉ የሚያሳየው የአዋጅ ጋጋታው ያመጣው ለውጥ አለመኖሩን ነው።እርግጥ የኢትዮጵያን ሕዝብ መስዋዕትነትን ሊጨምረው ይችላል።ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን አዋጁ በወጣ በሳምንቱ አዋጁ ምን ምን እንደሚከለክል የመከላከያ ሚኒስትር በሚል ስም ስር በሚገኙ ግለሰብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተገልጦለታል።እዚህ ላይ የተከለከሉ እና ያልተከለከሉ የተባሉትን የገዢው ስርዓት  መገናኛ ብዙሃን ያሉትን መድገም አያስፈልግም።ባጭሩ አዋጁ በአዲስ አበባ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቦች ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር በላይ እንዳይርቁ ተነግሯል።በተጨማሪም መሰረታቸውን ውጭ ያደረጉ የቴሌቭዥን እና የራድዮ ጣብያዎችን ኢሳት እና ኦኤምኤን ጨምሮ መስማት የተከለከለ መሆኑም ተነግሯል።አሁን ጥያቄው ሕወሓት ይህንን አዋጅ ያወጣበት እና እግረ መንገዱን ሊያሳካው ያሰበው ግልፅ እና ድብቅ ግብ ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ መመለሱ ነው።

ሕወሓት በአዋጁ ሊያሳካ ያሰበው ግልፅ እና ድብቅ ግቦች 

1ኛ/ ግልፅ ግብ  

አዋጁ በዋናነት ለሁሉም ግልፅ እንደሆነው የሚታየው ዓላማ የሕወሐትን የስልጣን ዘመን ማራዘም ነው።ይህም የሚቃወሙትን በሙሉ አንገት አስደፍቶ እና አሸማቆ በስልጣን ዘመኑ መቆየት ነው። ማሸማቀቅ እና አንገት ማስደፋት ብቻ አይደለም ጎን ለጎን በፈረሰው የኦህዴድ እና የብአዴን ድርጅቶች ምትክ አዲስ አሽርጋጆች እና መስሎ አዳሪዎችን ወደ መድረኩ እያመጣ የተቀባቡ ግለሰቦች እና ድርጅቶችንም ይፈጥርበታል።ለእዚህም ነው እንደ ልደቱ አይነቶቹን መድረክ መስጠት የፈለገው።በእዚህ ሂደት ውስጥ ግን መንገዱ አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ በእርግጠኝነት አብዛኛው የሕውሓት አቀንቃኝ ያውቀዋል።ሆኖም ግን ተስፋ መቁረጥ እና ከወንጀል ነፃ ሆኖ ለመኖር እንደ ብቸኛ መፍትሄ የተወሰደው ዛሬ እየገደሉ እና እያሰሩ ነገን በተስፋ መጠበቅ ነው። ይህ ሁኔታ ግን ተቃውሞው እየጠነከረ ሲመጣ እና የበላይነት መያዝ ሲጀምር ለሕወሓት የበለጠ ወደ አዘቅት ብቻ ሳይሆን እርስ በርሱም የመከፋፈል ዕጣ እንደሚገጥመው የሚያጠራጥር አይደለም። 

2ኛ/ ድብቅ ግብ 

ሕወሓት በአዋጁ ዋናውን እና ግልፅ ግቡን ለማሳካት ከሚሄድበት መንገድ በተጨማሪ ሁለት ድብቅ ግቦችን ማሳካት ያስባል። 

አሰቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደ አካባቢ ስጋት እንዳልሆነ የሚነገረው በትግራይ አካባቢ ነው።በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ከስጋት አልፎ ለበለጠ ትግል መነሳት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ብቸኛ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል።የአዋጁ አፈፃፀም ለምሳሌ የአደጋ ቀጠና ተብለው ከተጠቀሱት መንገዶች ውስጥ አንድም የትግራይ ክልል መንገድ የለም።ይህ ማለት ሕወሓት በአንደኛ ደረጃ ስጋት አለብኝ የሚለው ያውም ተቃዋሚዎች መሽገውባታል የምትባለው ኤርትራ ጋር የሚያዋስን መንገድ ለምን አንዱም ቀይ መስመር አልተባለም? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።ይህ ብቻ አይደለም አዲስ አበባ ዙርያን ለዲፕሎማቶች የስጋት ከተማ አድርጎ  ያስቀመጠበት አግባብ እንደተባለው ሕዝባዊ ተቃውሞው የውጭ ሀገር ዜጎችን ኢላማ አድርጎ ነው? ባለፈው በሰበታ መስመር መገደሏ የተገለፀው አሜሪካዊት በእውነት በተቃዋሚ ሕዝብ ነው የተገደለችው? ከእዛ በፊት የሚኒባስ ጥቃት ያውም ተሳፋሪ ባለበት ተደብድቧል? እነኝህ ሁሉ ጥይቄዎች በአግባቡ መመለስ አለባቸው። በሌላ በኩልም መጠየቅ ያለብን ጉዳይ አለ በኦሮምያ እና በአማራ የተቃጠሉት ፋብሪካዎች እና እርሻ ቦታዎች በእውነት ሁሉም በተቃዋሚ ነው የተቃጠሉት? በጎንደር ገበያ ላይ የተፈፀመው እና በኃላም ሌላ የጎንደር ቦታዎችን ልታቃጥል ስትል የተደረስባት ከትግራይ የመጣች ነች የተባለችው ሴት ሰሞኑን ከሚቃጠሉት ቃጠሎዎች አንፃር ምን ይነግረናል? ይህችው ወንጀል ለመስራት ሙከራ ላይ እንደሆነች የተነገረው ሴት በወታደር ታጅባ እጇ ላይ ሰንሰለት ሳይገባ እንድትሄድ የሆነበት ጉዳይስ ምን ያሳየናል?

ከላይ ከተነሱት ጥያቄዎች አንፃር አዋጁ ሊያሳካ የሚያስባቸው ድብቅ አላማዎች እንዳሉት እና እነኝህ ድብቅ አላማዎች ደግሞ ከሕወሐት የረጅም ጊዜ ስልቶች ጋር ሁሉ የተቆራኙ እንደሆኑ መረዳት ይቻላል።በእዚህ አዋጅ ሕወሓት ግልፅ ከሆነው ስልጣኑን ማስጠበቅ በተጨማሪ ሁለት ድብቅ አላማዎች (ግቦች) አሉት። እነርሱም ; - 

ሀ/ የመሃል ሃገሩን እና የደቡብ አካባቢን በአዋጁ አማካይነት ሙሉ በሙሉ በመምታት ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መሰረቱን ማናጋት እና የበለጠ ማደህየት።

በእዚህ አዋጅ መሰረት በሕወሓት መዘውር ውስጥ በሚገባ ያልገቡ የንግድ ድርጅቶች በሰበብ አስባቡ እና የሽብርተኛ ታቤላ እይተለጠፈባቸው ይዘጋሉ፣ይወረሳሉ ወይንም ከገበያ እንዲወጡ ይደረጋሉ።
በእዚህም የሕወሓት ሰዎች እንዲቆጣጠሩ ይደረጋሉ።የበለጠ ድሃ እንዲሆን  የተደረገው ሕዝብ የበለጠ የእነርሱ ተገዢ እንዲሆን እና አመፁን ዝም ማሰኘት ይቻላል ብለው ያስባሉ።ለእዚህ ነው የሚቃጠሉት ድርጅቶች ሁሉ የሕወሓት ሳይሆኑ እንደ ጎንደር ገበያ ሕወሓት እራሱ የሚያቃጥላቸው ድርጅቶች እንዳሉ ማወቅ ያለብን።

ሌላው የማደህየት ሥራው የሚገልጠው የአዋጁ አስፈፃሚ ኮማንድ ፖስት ስር ያሉ  ወታደሮቹ እንዲዘርፉ የውስጥ በጎ ፈቃድ አሳይቷል። ለእዚህም ማስረጃው በአዲስ አበባ በተደረጉ አሰሳዎች የውጭ ምንዛሪ እና ሞባይል ስልኮች መዘረፋቸው እና ወታደሮቹ በግላቸው መውሰዳቸው ነው።ይህ በትንሹ የተጀመረ ሂደት ነገ ኮማንድ ፖስቱ የእገሌ ድርጅት በሽብር ተግባር ሊሰማራ ሲል ተይዞ ድርጅቱ ተወረሰ ሲል እንደምንሰማ መጠራጠር የለብንም።

ለ/ የትግራይን ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ልዕልና በቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በሚገባ መስፈኑን ዋስትና ለመስጠት 

ሕወሓት ከመነሻው ዋና ግቡ መሃል እና ደቡብ ኢትዮጵያን ከቻለ ለሚገነባው የትግራይ ኢምፓየር በግብዓትነት እንዲያገለግሉ ማድረግ እና  የተወሰነ ልማት እያሳዩ የቀረውን ግን ማጋበስ ነው።ይህ የሚሆነው ግን ሕዝብ በተቃውሞ እስካልተነሳበት ድረስ ነው።ሕዝብ በተቃውሞ ከተነሳበት ግን ሊያደርግ የሚያስበው መሃል ሃገሩን እና ደቡብን በብሄር ግጭት  እና በምጣኔ ሀብት ቀውስ አተራምሶ ቀጥሎም ማውደም እና የትግራይ ምጣኔ ሀብት የመሳብ (puling role) ወይንም የማዕከላዊ ሚናውን(central role) እንድትጫወት ማድረግ ነው። ይህም የአዲስ አበባን የዋና ከተማነት እና የኢንዱስትሪ ማዕከልነት በተለያየ መንገድ አውድሞ ልማቱ ወደ ትግራይ ማዕከልነት እንዲቀየር ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ የእረጅም ጊዜ ሂደት ነው።ሆኖም ግን የእዚህ አይነቱ ግርግሮች እንደ አንድ አጋጣሚ ሕወሓት ይመለከተዋል እና የእረጅም ጊዜ ሂደቱን ያፋጥናል ብሎ ያስባል። 

ባጠቃላይ ሕወሓት በአዋጁ ግልጥ እና ድብቅ ዓላማዎች እንዳሉት መረዳት ይገባል።ብዙ ሕዝብ የሚያወራው ስለ ግልጡ እና የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ነው የሚለውን እንጂ እግረ መንገዱ እየሰራ ያለው የእረጅም ጊዜ ግቡ የተከሰተለት አይመስለኝም።የፖለቲካ መፍትሄዎችን የማይሰጥበት ዋናው ምክንያት ድብቅ አላማውን እንደሚያሳኩለት ስለሚያምን ነው።የጎንደርም ሆነ የኦሮምያ ተቃውሞዎች ከመጀመርያው ፍፁም ሰላማዊ ነበሩ።በጎንደር በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ታሪካዊውን ሰልፍ ሲያደርግ አንዳች ኮሽታ አላሰማም።ነገር ግን ሕወሓት ቀላል መነሻ የነበራቸውን ጉዳዮች እያከረረ እና የህዝቡን ሰላም እየነሳ እዚህ አድርሶታል።በእዚህም የአማራ እና የኦርሞ አካባቢዎች የስጋት ቀጠና አድርጎ ትግራይ ግን ሰላማዊ ቀጠና አድርጎ አቅርቧል።ይህ ማለት አንድ ቱሪስት ጎንደር ከምትጎበኝ መቀሌ ብትሄድ የተሻለ ነው እያለ የሕዝብ ምጣኔ ሀብት እድገትን በማቀጨጭ የእረጅም ጊዜ የእድገት ማዕከልን የመቀየር ሂደቱን ያጧጡፍበታል።በተመሳሳይ መንገድም መሃል ሀገር ያለውን ባለ ሀብት ለ25 አመታት ያህል ከከተማ ይዞታው ከማፈናቀል ጀምሮ ከገበያ እንዲወጣ እያደረገ እና የንግድ መስመሮቹን በሙሉ በእራሱ ሰዎች በማስያዝ የምጣኔ ሀብቱንም ሆነ የማኅበረሰባዊ የበላይነትን ለመቆጣጠር ይጠቀምበታል።

ስለሆነም እንደ ኢትዮጵያዊነት መኖር ካለብን እኩልነት በቅድምያ መምጣት አለበት።ይህ እኩልነት ደግሞ የጥቂቶች (minority ) መንግስት የሆነው የሕወሓት መንግስት ስልጣኑን ለሕዝብ ማስረከብ እና የሁሉንም ሕዝብ ውክልና ያገኘ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ መመስረት የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ ነው።ከእዚህ ውጭ አዋጁ በእራሱ ከፋሺዝም አዋጅ ያልተለየ እና ከፍተኛ ጦርነት የሚቀሰቅስ አደጋውም በበለጠ ለሕወሓት ህልውና ቆምያለሁ በሚለው ላይ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።ይልቁንም እነኝህ አደጋዎች ከመድረሳቸው በፊት የሕወሓት ደጋፊዎች በመጨረሻው መጨረሻ ሰዓት ላይም ሆነው ሊያስቡበት ይገባል።የማይስኬድ መንገድ ለጊዜው የሚያራምድ ይመስላል እንጂ በማንኛውም ሰዓት ይርዳል።ይህ ደግሞ ያለፉት ጥቂት ወራቶችም በሚገባ አስተማሪ ናቸው።


ጉዳያችን GUDAYACHN


 www.gudayachn.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...