ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, July 18, 2016

¨በሰላም ባስ¨ የቃጠሎ ነበልባል ውስጥ ዋልድባን አየሁት (ጉዳያችን ማስታወሻ)


የዋልድባ መነኮሳት 

ኢትዮጵያችን የተጎዳችው በጭፍን የጎጥ ፖለቲካ ብቻ አይደለም።ሚዛናዊ አስተሳሰብ ደብዛው መጥፋቱም ብቻ አይደለም። እንደ ሰው የማሰብ ተፈጥሯዊ ክህሎት ነው። እንደ ሰው ማሰብ የአምሳያው ሰው ሞት፣ስደት፣ነፃነት ማጣት እና ድህነት ሁሉ የእኔ ችግር ነው ብሎ ከማሰብ ይጀምራል። የማኅበራዊ ሚድያው ፈጣን መረጃ ከመስጠት አልፎ ሰዎች ስለ ክስተቶች ምን እንደሚያስቡ ሃሳባቸውን በቀላሉ ለማካፈል ዕድል ፈጥሯል።በእዚህም ሳብያ የብዙዎች የአስተሳሰብ ጥግ ከየት ተነስቶ የት ላይ እየደረሰ መሆኑን ለማወቅ ሙሉ በሙሉ በቂ ባይባልም ጥሩ መረጃ ግን ይሰጣል።

ከአራት አመታት በፊት በሰሜን ጎንደር ከነበረው ትልቅ የአገራችን አነጋጋሪ ጉዳይ ውስጥ አንዱ የህወሓት የዋልድባ ገዳምን ይዞታ የሆነ መሬት አብያተ ክርስቲያናትን እና የቅዱሳንን መቃብር እየፈነቀለ ስኳር ሸንኮራ አገዳ ለመትከል መወሰነኑን የመናገሩ ጉዳይ ነበር።በወቅቱ የገዳሙ መነኮሳት በማያውቁት የከተማ ሕይወት የገዳሙ አባቶችን የተማፅኖ ደብዳቤ ይዘው አቶ መለስ ቢሮ አዲስ አበባ ድረስ መጥተው ሲጠይቁ ሃይማኖታዊ ከበሬታው ቢቀር ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በማይገልፀው መልኩ በስልክ እንደተሰደቡ በሃዘን በወቅቱ ለአሜሪካ ራድዮ አማርኛው ክፍል መግለፃቸው ይታወቃል።በወቅቱ ገዳማውያኑ ስለ ዋልድባ የገለፁበት ቃላት ''ቦታው የቃል ኪዳን ቦታ ነው ገዳሙ ሀጥያት የማይሻገርበት ፣ዘር የማይዘራባት፣እህል የማይበላባት ቦታ ነው''  ( ጉዳያችን፣2014የሚል ነበር። በጎንደር ከተማ እና በውጭ አገራት የተለያዩ የተቃውሞ ሰልፍ ቢደረግም በአቶ አባይ የሚመራው ፕሮጀክት እንዲህ ከ70 ቢልዮን ብር በላይ ውጦ ዝም ሊል በወቅቱ በእየመድረኩ ላይ በትዕቢት የተወጠረ ንግግር ማድረግ ልማዱ አድርጎት ነበር። ሌላው አስገራሚው ጉዳይ ዋልድባ ለምን ይታረሳል? በርካታ የአገራችን መሬቶች መች ተነኩና ነው ዋልድባ ይታረስ የተባለው? ሲባል የህወሓት እና እራሳቸውን የትግራይ ጎሳ ጠበቃ አድርገው የሾሙ ወገኖች ¨የዋልድባን ጉዳይ የምትቃወሙት ትግራይ እንዳትለማ ነው¨ የሚል ትግራይ የእነርሱ ብቻ ትመስል ባጠለቁት የጎጥ ፖለቲካ ጥብቆ ልክ ሲናገሩ ታዝበናቸዋል። ይህ አባባል ደግሞ ሃይማኖተኛ ነን እያሉ እራሳቸውን በሚጠሩት ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት አባቶች ሁሉ ጉዳዩን ለማድበስበስ ቢያንስ እንደ ሰው መቃወም የሚገባቸውን ግልፅ ጉዳይ ለስርዓቱ በማደር እንዳላዩ አልፈውታል።ይህ ሁሉ ሆኖ ግን አቶ መለስም በሞት ወደ ማይቀረው ሳጥን ገቡ፣ የስኳር ፕሮጀክትም ጥቂት የህወሓት ሰዎችን ኪስ አደልቦ አንድም ሳይራመድ ባለበት እየረገጠ ይሄው አለ።የሰላም ባስ ባለቤቶች በወቅቱ በዋልድባ ጉዳይ የተናገሩት ለጆሮ የሚጠልዝ እና ሃይማኖት የእዚህን ያህል በጎጠኝነት ተቀይራለች እንዴ? የሚያስብሉ ንግግሮች ከብዙ ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል።ችግሩ ዛሬም ድረስ እውነትን ከመጋፈጥ ይልቅ ከአርባ ዓመት በፊት በቆሙበት የጎጥ ጭቃ ውስጥ እየዳከሩ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ሊለውሱ የመዳከራቸው ድፍረት ነው።


የዋልድባ ጉዳይ የህወሓትን የጎጥ ፖለቲካ የሚጋሩ ሁሉ ማንነት በሚገባ የተፈተሸበት ነው።እንደ ሰው የሚያስቡ ሳይሆን የጎጥ ስብስባቸው ለክቶ እና ሰፍሮ በሚሰጣቸው የጎጥ መለክያ ብቻ ለማሰብ እራሳቸውን እና ስብእናቸውን ለመሸጣቸው ማሳያ ነው። ማንም ሰው የፈለገውን ስብስብ የመደገፍ መልኩ የተጠበቀ ነው።ነገር ግን የተሰበሰበበት ስብስብ ስህተት ሲሰራ ስህተት ነው።ትክክል ሲሆን በእዚህ በዚህ ምክንያት ትክክል ነው ብሎ መናገር ጤነኛ አስተሳሰብ ነበር። የህወሓት የጎጥ ስብስቦች ግን ድርጅታቸው ገዳማትን ሲወር ትክክል ነው። ገዳማውያኑን በጎጥ እየከፈለ አንዱን የእንጀራ ልጅ ሌላውን  የአገር አባት ሲያደርግ ልክ ነው።በዋልድባ ዙርያ ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን እየነቀለ፣የቅዱሳንን አፅም እየፈነቀለ ሲጥል ሁሉ በእነርሱ አባባል ለትግራይ ነው እና ተዉ! ሲሉን ከረሙ።በአሶሳ፣ጉርዳፈርዳ፣ቡራዩ፣ እና ሌሎች በርካታ ቦታዎች ሰዎች በትውልድ ቦታቸው እየተጠራ ሲባረሩ እና ንብረታቸው ሲዘረፍ በህወሓት በጎ ፍቃድ ነው ነው እና  አንዳች ሳይተነፍሱ ይልቁንም የሚናገሩትን ሲያስሩ እና ሲገድሉ ሰነበቱ። ይልቁንም አቶ መለስ ሰዎች ለምን ይፈናቀላሉ? ተብለው ሲጠየቁ ¨ጉርዳፈርዳ ምስራቅ ጎጃም መስሏል¨ በሚል የጎጥ ንግግራቸውን በጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ ተቀምጠው የኢትዮጵያ ምክር ቤት  በሚሉት ፊት በቴሌቭዥን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጥታ በሚተላለፍ ንግግራቸው ላይ ተናገሩ። ከእዚህ በላይ መታወር ከየት ይመጣል?

ከ20 አመታት ባላነሰ በጎንደር ላይ ሲሽከረከር የነበረው የሰላም አውቶቡስ ጎንደር ከተማ ላይ በእሳት ጋይቷል።ግን ጥያቄው ለምን ለዓመታት ያልሆነው አሁን ሆነ? ነው።ጉዳዩን በአንክሮ ስንመለከተው የነገው የህወሓት ዕጣ አመላካች ነው።በአውቶብሱ ነበልባል ውስጥ በሚገባ መመልከት የቻለ ሰው ዋልድባን ይመለከትበታል።ከአራት ዓመታት በፊት የዋልድባ መነኮሳት እንባ በጉንጫቸው እየወረደ ከሰሜን ጎንደር ተነስተው አዲስ አበባ የአቶ መለስን ቢሮ እና የአቡነ ጳውሎስን ልዩ ፅህፈት ቤት ደጅ ሲጠኑ እና የሚያናግራቸው አጥተው መንግስት የሚባለው አካል እና ቤተ ክህነት ይህንን ያህል የስምንተኛው ሺህ ትንቢት መፈፀምያ መሆናቸውን ተመልክተው ሞታቸውን የተመኙባትን ደቂቃ ያጤንበታል። በእሳቱ ነበልባል ውስጥ  በጎንደር ዋልድባን አስመልክተው የተደረጉ የህዝብ ስብሰባዎች ላይ እንባቸውን እየዘሩ የተናገሩ አዛውንት እና እናቶች ድምፅ ይሰማል።በእሳቱ ነበልባል ውስጥ በእግራቸው ከጎንደር ተነስተው  እስከ ዋልድባ እያለቀሱ የሄዱ የጎንደር  ወጣት ወንዶች እና ሴቶች ሰቆቃ ይታያል።በእሳቱ ውስጥ የህወሓት ¨ነፍሰ በላ¨ ገራፊዎች የዋልድባ አባቶችን ልብስ አስወልቀው እያዋረዱ እና እየሰደቡ የገረፉበት እና የመነኮሳቱ ገላ ከሰንበር አልፎ ደም ያፈሰሱበት መሬት እና ጨለማ ቤት ይታያል።በእሳቱ ነበልባል ውስጥ የህወሓት ገዳዮች ዋልድባን ደም ባፈሰሰና  በረከሰ እግራቸው ገብተው ያመሱበት እና ለዓመታት ከገዳማቸው ወጥተው የማያውቁ መነኮሳት ወደ ሱዳን እና ኤርትራ ሌት በቁር ቀን በሐሩር እየተንከራተቱ መሰደዳቸው ይታየናል።በሰላም ባስ እሳት ነበልባል ውስጥ እነኛ ሮጠው ያልጠገቡ ኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ታዳጊ ሕፃናት በአጋዚ የጥይት አረር የመፈጀታቸው ግፍ እና የወላጆቻቸው እሪታ ይታየናል።

ባጠቃላይ ከአራት ዓመታት በፊት የህወሓት እብሪተኛ መሪዎቹ ደረታቸውን ነፍተው፣አንገታቸውን አቅንተው ዋልድባን እንደሚያርሱ ሲነግሩን አልቅሰናል። የእነርሱን ንግግር ተከትሎ የህወሓት መንደርተኛ አስተሳሰብ አራማጆች ጎጠኛ ድርጅታቸው ወደ ፋሽሽትነት እየተቀየረ መሆኑን ስንነግራቸው፣ እናምነዋለን የሚሉት ሃይማኖትም ሳይገዛቸው ቀላብቸውን አጥተው ፎክረዋል።ይህ ብቻ አይደለም የእዚህ አይነት እብሪት ዞሮ ዞሮ ለወገናችን የትግራይ ሕዝብ እንደሚተርፍ እና ችግሩን መቀልበስ አስቸጋሪ እንደሆነ እያለሳለስንም እያከረርንም ስንመክራቸው ስቀውብናል። ዛሬ ላይ የሰላም ባስ ሲቃጠል ከድንጋጤ ባለፈ መጪው ጊዜ በትንሹ እንደ እነርሱ አገላለጥ ¨በወጋገን¨ እየታያቸው ነው። የሚያሳዝነው ግን አሁንም ለሌላ እልቂት በኦሮምያ እንደፈፀሙት በጎንደርም ለመፈፀም ሳንጃቸውን ስለው ጎንደር ላይ እየከተሙ ነው።

ባጠቃላይ የህወሓት ወደ ፋሽሽት ድርጅትነት መቀየር ለትግራይ ሕዝብ ግልፅ ሊሆንለት ይገባል።የሰሞኑ በጎንደር ሕዝብ ላይ የሚፎከረው ¨አማራ ገዳይ¨ ፉከራ  የመጨረሻው መጀመርያ እንደሚሆን ማንም አይጠራጠርም።መታወቅ ያለበት ገበሬ ካልቆረጠ በሰኔ እና ሐምሌ መሣርያውን ይዞ ከቤቱ አይወጣም።ይህ ወቅት የእርሻ ወቅት ነው።ከቆረጠ ግን እንዲህ እንዳሁኑ ይነሳል።የተከበረውን የትግራይ ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ ጋር  በማጋጨት የሚጠቀም የሚመስለው ህወሓት በመጨርሻ ችግሩ ሲጠና ቀድሞ የሚነሳበት የትግራይ ሕዝብ ለመሆኑ ባይተራጠር ጥሩ ነበር። የአሁኑ የጎንደር እንቅስቃሴ ከመነሻው ጀምሮ ፍትሃዊ እና እውነት እንደሆነ  ህሊናውን ለመሸፈን ያልፈለገ እና እራሱን ከእብሪት ለማራቅ የሚፈልግ የህወሓት አቀንቃኝ ሁሉ ያውቀዋል።የወልቃይት ኮሚቴ አባላትን ኮ/ል ደመቀን ጨምሮ አቶ ሃይለማርያም አሁኑኑ ላናግርህ እፈልጋለሁ ወደ አዲስ አበባ ና! ቢሏቸው በቀጥታ የሚመጡ ህዝቡ ውስጥ የሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች ናቸው። ለአማራ ካልል የፀጥታ ኃይል ሳይናገሩ እንደ ጅብ በሌሊት የመጡት የአባይ ወልዱ ቅልቦች ናቸው። ጧት እንዲመጡ ስነግራቸው በሩን የሰበሩት አሁንም እነኝሁ ቅልቦች ናቸው።የነገሩ መነሻ ከሰው አይመስልም።ህወሓት መውጫ እንዲያጥረው ነገሩን የሰራውም የሰው ሥራ አይመስልም።የዋልድባን ሰቆቃ በሰላም ባስ የቃጠሎ ነበልባል ውስጥ የሚታይ ብዙ ነገር አለ። ለህወሓት የጎጥ ፖለቲካ ኢትዮጵያን በዘር ሊለበልቡ የተነሱ ሁሉ የሰላም ባስ ከሃያ አመታት በላይ እንደፈለገ ሲሄድ የነበረው አውቶብስ ለምን ዛሬ አቃተው? ብለው መጠየቅ እና የዋልድባን ሰቆቃ በእሳቱ ነበልባል ውስጥ ማየት ካልቻሉ የዕይታ ችግር ያለው ከእነርሱ እንጂ ከእሳቱ ነበልባል አይደለም። 

ጉዳያች Gudayachn
www gudayachn com 

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...