ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, July 11, 2016

ኢሳት አገራዊ ኃላፊነት የመወጣት አቅሙን ያስመሰከረባቸው ሁለቱ ዜናዎች


የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን ከተመሰረተ በኃላ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተፅኖ ፈጣሪ ለመሆን ሶስት ዓመታት አልፈጀበትም።አሁን ላይ ኢሳት ከተመሰረተ ገና ስድስተኛ ዓመቱ ቢሆንም በመላው ዓለም ከተበተኑት ኢትዮጵያውያን እና አገር ቤት ከሚገኘው ሕዝብ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የሚገኙ የልዩ ልዩ አገራት ዲፕሎማሲ ማሕበረሰብ እና የኢትዮጵያን ጉዳይ ለበጎም ሆነ በጎ ላልሆነ ስልታዊ ፍላጎት የሚከታተሉ ባዕዳን ኃይሎች ዘንድ ሁሉ ዕለት ከዕለት በሚፈልጉት ቋንቋ እየተረገሙ የሚከታተሉት የዜና ምንጭ ሆኗል። ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮችም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በብቸኛ የዜና ምንጭነት የሚጠቅሱት ኢሳት የሆነበት ጊዜ መኖሩ በእራሱ የድርጅቱን ተአማኒነት እያደገ የመሄዱን እውነታ የሚያመላክት አንዱ ማሳያ ነው። (የዋሽግተኑ ተቃውሞ ኢሳትን በዓለም ዓቀፍ ስመጥር የዜና አውታሮች ዝናው ገንኖ እንዲወጣ አደረገ 

ኢሳት ባለፉት አርባ አመታት ውስጥ  በኢትዮጵያ የማዕከላዊ መንግስት ተቃዋሚነት ተሰልፈው የነበሩ የዜና አውታሮች አንፃር ስንመዝነው በበርካታ መስፈርቶች ገንቢ እና ሚዛናዊ ዘገባዎቹ የተሻለ እና ለወደፊቱ የኢትዮጵያ የሚድያ አገልግሎት የእራሱን በጎ አሻራ ትቶ የሚሄድ  ለመሆኑ የሚያመላክቱ በርካታ ነጥቦች እናገኛለን። ባለፉት አርባ አመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ተፅኖ ለመፍጠር የሞከሩ አንድ ሁለት ተብለው ሊጠቀሱ የሚችሉ ከባህር ማዶ ወይንም ከጎረቤት አገራት መሰረታቸውን ያደረጉ የራድዮ ጣብያዎች ነበሩ።

በ1960ዎቹ መጨረሻ በአጭር ሞገድ ራድዮ ይተላለፉ የነበሩት የኢድዩ፣ህወሓት፣ሻብያ  እና ሱማልያ ራድዮ ጣብያዎች እና በኃላም በ1970ዎቹ መጨረሻ እና 80ዎቹ መጀመርያ እስከ 1981 ዓም በኮ/ል መንግስቱ ሃይለማርያም ላይ በግንቦት 8 እስከተደረገው መፈንቅለ መንግስት ድረስ የቆየው የኢትዮጵያ አንድነት ድምፅ የተሰኘው በአጭር ሞገድ የሚተላልፈው የራድዮ ጣብያ ሁሉ ሙሉ በሙሉ በተቃዋሚ ሚድያነት የሚታወቁት ራድዮ ጣብያዎች ሙሉ በሙሉ በስልጣን ላይ የነበረውን መንግስት ማጥላላት ላይ የተመሰረቱ ቃላት እና ፕሮፓጋንዳ ይዘት ያላቸው ዝግጅቶች ላይ ብቻ ያተኮሩ ነበሩ።

ኢሳት ባለፉት አርባ አመታት ውስጥ ከታዩት በውጭ አገራት መሰረታቸውን ካደረጉ ኢትዮጵያዊ የመገናኛ ብዙሃን የሚለይበት የተለየ ባህሪ ይታይበታል ሲባል የሚከተሉትን ነጥቦች ታሳቢ በማድረግ ነው።ይሄውም - 

  • ኢሳት ከቀደሙት ሚድያዎች በሙሉ በተለየ መልኩ በስልጣን ላይ ያለውን ስርዓት መንግስት ብሎ የሚጠራ እና ለሁሉም አካላት  የመገናኛ ብዙሃንነቱን ያንፀባርቀ ነው፣
  • ኢሳት በስልጣን ላይ ካለው ስርዓት ባለስልጣናት አቦይ ስብሐት እስከ የፅንፍ ፖለቲካ አራማጅ ተቃዋሚዎች ለሁሉም ሃሳባቸውን የመግለፅ ዕድል ለመስጠት ሞክሯል፣
  • ኢሳት በፕሮፓጋንዳ ላይ ከተመሰረተ ዝግጅት ባለፈ የኪነ ጥበብ ዝግጅት፣ የመዝናኛ መርሃ ግብር፣ ሰብአዊ መብት ላይ ያተኮሩ ቃለ መጠይቆች እና ኢትዮጵያውያን በውጭ አገራት የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለምሳሌ በአረብ አገራት የተመለከቱ መርሃ ግብሮችን በማቅረብ ከቀደሙት የተለየ ይዞታ ሁሉ የተለየ ያደርገዋል።

ኢሳት አገራዊ ኃላፊነት የመወጣት አቅሙን ያስመሰከረባቸው ሁለቱ ዜናዎች

ከላይ እንደመነሻ ኢሳት ባለፉት አርባ አመታት ከውጭ አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚተላልፉ መገናኛ ብዙሃኖች ያለውን ልዩነት ከገለጥኩ በመቀጠል የፅሁፉ መነሻ ወደሆነው የኢሳት አገራዊ ኃላፊነት ታይቶባቸዋል ወደምላቸው ሶስቱ ዜናዎች ልግባ። አሁን ባለንበት የ21ኛው ክ/ዘመን ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊነት እጅግ ኃላፊነት ያለበት ትልቅ እና ቁልፍ ሥራ ነው። ለእዚህም ማሳያው የቴክኖሎጂ ብቃት እና ጥራት የዘመኑ መገናኛ ብዙሃን በእያንዳንዱ የገጠርም ሆነ የከተማ ነዋሪ ቤት የመድረስ አቅም መጨመር የመገናኛ ብዙሃን ተፅኖ የመፍጠር አቅም ምን ያህል ከፍ እንዳለ አመላካች ነው።ኢሳት ባለው ግልፅ እና ስውር የመረጃ ምንጮች ከአገር ቤት እና ሌሎች አገራት የሚያገኛቸውን ዜናዎች በኢትዮጵያ ላይ እንደ አገር የሚፈጥሩትን አሉታዊ ተፅኖ ሳያጤን ለአየር እንደማያበቃ እና አንድ ኃላፊነት የሚሰማው መንግስት ከሚወስደው የኃላፊነት ስሜት ባልተናነሰ መልኩ የሚያደርገው ጥንቃቄ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ትልቅ ኩራት ነው። ለአብነት ሁለት ዜናዎችን እንመልከት።

የአቶ መለስ ዜናዊ ሞት 

አቶ መለስ ዜናዊ በብራስልስ ከእዚህ ዓለም መሞታቸውን ቀድሞ ያወቀ ኢሳት ነበር።ኢሳት ዜናውን በሰማበት እና የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ለሕዝብ በገለጠበት ጊዜያት መካከል ከሰላሳ ቀናት ያላነሰ ልዩነት ነበር።ሆኖም ግን ኢሳት የአቶ መለስ ዜናዊን እረፍት እንደሰማ ለአየር አላዋለውም።በየትኛውም አገር ቢሆን በስልጣን ላይ ያለ አገር መሪ ሲሞት በአገሪቱ የዕለት ተዕለት ተግባራትም ሆነ የፀጥታ ጉዳይ ላይ የሚፈጥረው የኃይል ክፍተት እንደሚኖር የታወቀ ነው።ይህ ደግሞ ይዞ የሚመጣው እና የሚያስከትለው ቀውስ ለመገመት በቀላሉ አይቻልም።በተለይ በባዕዳን ዘንድ ሁኔታውን አገሪቱን ለማጥቅያ ምቹ ጊዜ የመጠቀም ሁኔታ የመፈጠር እድሉ ሁሉ ቀላል አይደለም።በመሆኑም ኢሳት በአቶ መለስ ዜናዊ እረፍት ዜና ላይ በቅድምያ ወደ እውነት የቀረቡ ዜናዎች እየወጡ መሆናቸውን በመቀጠል ለተከታታይ ቀናት በስልጣን ላይ ላለው ስርዓት እስከ ቀጣዩ ሰኞ ቀን ድረስ ሁኔታውን እንዲያሳውቅ ይህንን ካላደረገ ደግሞ ኢሳት ባለው ኃላፊነት ጉዳዩን ለሕዝብ ግልጥ እንደሚያደርግ በማሳወቅ እና በመጨረሻም ዜናውን ለሕዝብ ይፋ በማድረግ የአንድ መገናኛ ብዙሃን ኃላፊነትን ተወጥቷል። እዚህ ላይ ኢሳት ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት የማይሰማው ቢሆን ኖሮ ዜናውን እንዳገኘ እና እንዳረጋገጠ  ወዲያውኑ ለፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በተጠቀመበት ነበር።

የ2008 ዓም የሁለተኛ ደረጃ መልቀቅያ ፈተና መሰረቅን በተመለከተ 

በሐምሌ 3፣2008 ዓም የተጀመረው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቅያ ፈተና መሰረቅን በተመለከተ ኢሳት መረጃውን ከማግኘቱም በላይ የተወሰኑ ፈተናዎች ሙሉ ጥያቄ እጁ እንደገባ ገልጧል።ሆኖም ግን ቀደም ባለው ወር ውስጥ ድጋሚ ፈተናው ከመሰረቁ በፊት የፈተና ውጤቱን እንዳሰራጩት ፈተናውን ለሕዝብ አልለቀቀም።ኃላፊነት በተሰማው መንገድ የፈተናው አዘጋጅ የትምህርት ሚኒስቴር ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ እንዲመለከት እና መሰረቅ አለመሰረቁን እንዲያረጋግጥ ከመጠየቅ ባለፈ ፈተናውን ከኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ውጭ ለአየር አለማብቃቱ ኢሳት በእውነትም በመጪው ጊዜያት ኢትዮጵያ እንደ አገር ለሚገጥሟት ችግሮች ሁሉ ኃላፊነት በተሰማው መልኩ የሚሰራ ለመሆኑ ሌላው ማረጋገጫ ሆኖ አልፏል።

ባጠቃላይ የመገናኛ ብዙሃን በአንድ አገር ፖለቲካው፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሕይወት ላይ የሚኖረው ተፅኖ በተለይ አሁን በምንኖርበት ዘመን ከፍተኛ ነው። በአሁኗ ኢትዮጵያ በየትኛውም የዓለም ጫፍ እና በአገር ቤት የሚኖረው ሕዝብ የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያ ነክ ዜናዎችን በማመን የሚሰማው የመረጃ ምንጭ ኢሳት ነው። አሁን በስልጣን ላይ የሚገኙ በለስልጣናት ምሽት ላይ በራቸውን ዘግተው የሚከታተሉት ኢሳት ለመሆኑ በርካታ መረጃዎች ወጥተዋል።በመግብያው ላይ እንደተገለጠውም ከዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ እስከ ገጠር በጀነሬተር መብራት እስከሚያገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢሳት ላይ ከፍተኛ እምነት አላቸው። ኢሳትም ኃላፊነት በተሰማው መልኩ መስራቱ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ኩራት ብቻ ሳይሆን ከነፃነት በኃላ ኢትዮጵያ የሚኖራት የመገናኛ ብዙሃን ብቃት በችግር ጊዜ ተፈትኖ ያለፈ እና ስሜታዊነትን ባራቀ መልኩ የሚሰራ ለመሆኑ ሌላው ማረጋገጫ ነው። እናመሰግናለን ኢሳት!


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።