ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, January 13, 2016

በኢቲቪ መድረክ ላይ በውሃ አስተዳደር የዲግሪ ተመራቂዋ ወጣት ለቅሶ፣ነፃነት! ወይንም ሞት! ይላል (የጉዳያችን ማስታወሻ)


ከክብር ወርደናል።ሕዝብ እንደ ሕዝብ ተገፍቷል።ጥቂት በጎጥ የተጠራሩ ምንደኞች ኢትዮጵያን ለእሩብ ክ/ዘመን አምሰዋታል።በፍቅር ይኖር የነበረ ብሄረሰብ በቢላዋ እንዲተራረድ አደረጉት።አንዱ ላንዱ ይፀልዩ የነበሩ እምነቶች በጥርጥር እንዲተያዩ እና በአንድነት ኢትዮጵያ ስለምትባል አገር እንዳይናገሩ ታፈኑ።ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ አገር ጉዳይ በአዋጅ ወደ አምላክ መቼ መፀለይ እንዳለባት ለመንገር የሚቃጡ ቅምጥሎች በቤተ መንግስት ሆነው ሊመሯት ፈለጉ።

መኖር ያስጠላው ሕዝብ፣የመኖር ትርጉሙ የጠፋበት ሕዝብ፣ግፍን ከምሽት እስከ ንጋት መመልከት የመረረው ሕዝብ፣ጥቂት በጎጥ እና በጥቅም የተጠራሩ የትውልድ ነቀርሳዎች ከህዝብ በዘረፉት ገንዘብ ሲቀማጠሉ መመልከት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በባሰ ሰልችቶታል።
የተራቡ ልጆቹን በአግባቡ መመገብ ያልቻለ አባወራ፣የልጆቿን መራብ እና መጠማት እየተመለከተች መግቢያ ያጣች እናት ዛሬ ከምን ጊዜውም በላይ ለለውጥ ብትነሳ ሲያንስባት እንጂ አይበዛባትም።

የወጣቷ መከራ የጎጠኛው ስርዓት የአድልዎ ውጤት 

መማር በእራሱ በጎጥ ካባ ካልተሸፈነ ለውጤት የማያበቃ መሆኑን ለማየት ባሳለፍነው ገና ለእይታ የበቃውን የአንዲት የአዲስ አበባ ወጣትን ታሪክ ማንሳቱ በእራሱ ይበቃል።የወጣቷ ታሪክ መጀመርያ በሸገር ላይ ከተላለፈ በኃላ የአፍቃሪ ሕወሃቱ እና የኢትዮ-ቻናል ጋዜጣ አዘጋጅ ሳምሶን በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ያለፈው የገና ዝግጅት ላይ ወጣቷን በአካል ይዞ ብቅ አለ።እንደ ሳምሶን አገላለጥ ልጅቱ ጠንካራ ሰራተኛ በመሆኗ ነው ያቀረባት። በእርግጥ ወጣቷ ጠንካራ ሰራተኛ ነች። ሆኖም ከጠንካራ ሰራተኛነቷ ባለፈ ግን የኢትዮጵያ የተማረ ወጣት እንዴት በዘረኛ እና አፋኝ ስርዓት ውስጥ ትምህርቱን ቢማርም ለምንም አይነት ውጤት እንደማይበቃ የሚያመላክት ነው።

ወጣቷ ከመቀሌ ዩንቨርሲቲ በውሃ አስተዳደር ተመርቃለች።ሆኖም ግን ጊዜው ወጣቱ በሙያው እና በተማረው ትምህርት ሥራ የሚያገኝበት አይደለም እና ሥራ አጥታ ለአመታት ተቀመጠች።ይታያችሁ ስንት ወንዞች እና የከርሰ ምድር ውሃ ባለባት አገር አንዲት በውሃ አስተዳደር የተመረቀች ያውም ወጣት ሴት ሥራ አጥታ ተቀመጠች።የጎጥ እና የጥቅም  ተጋሪዎች ግን ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ በሀብት ይንበሸበሻሉ።ይህች ወጣት ግን በውሃ ምህንድስና ትመረቅ እንጂ የውሃ ማማ በተባለችው የኢትዮጵያ ምድር በሺህ እንደሚቆጠሩት የእድሜ አቻዎቿ ሥራ ማግኘት አልቻለችም።ይልቁንም በልጆች ምሳ መያዣ ላስቲክ ውስጥ አድርጋ መርካቶ በቀን ሥራ ለሚተዳደሩ ሰራተኞች መሸጥ ጀመረች።''ምሳ ሰዓት ላይ አንድ የምሳ ስህን ከአንድ የላስቲክ ውሃ ጋር አድርጋ እያደለች ትሄድ እና ከቀትር በኃላ ተመልሳ ትሰበስበዋለች'' ይላል አንድ ለሸገር ራድዮ ቃሉን የሰጠ ወጣት።

የውሃ መሃንዲሷ ወጣት የስርዓቱ አቀንቃኝ እንደሆነ የሚነገርለት የኢትዮ ቻናል ሳምሶን በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ፊት በተሰበሰበው ሕዝብ መሃል ሲያቆማት ወጣቷ እንባዋ ይወርድ ነበር።ወደ መሬት አቀርቅራ ታለቅሳለች።ሳምሶን ስለስራዋ ታታሪነት ይናገራል።እርሷ ግን ማልቀሷን አላቆመችም።በእርግጥ ለወጣቷ የተለያዩ ድርጅቶች እና ግለሰቦች የገንዘብ አስተዋፅኦ አድርገዋል።የህ በእራሱ በጎ ተግባር ቢባልም የወጣቷ ውክልና ግን የኢትዮጵያን ወጣቶች በሙሉ ነው።ተምረው እንዳልተማሩ የተገፉት፣በጎጥ ማጥለያ እንዲገፉ ሆነው ከስራ ዓለም የተባረሩ እና የሚሰሩት ሥራ የባርነት ቀንበር ሆኖባቸው ለሚገኙት ሁሉ ወጣቷ በመድረኩ ላይ እንባዋን አፈሰሰች።

የእዚች ወጣት ሁኔታ ሥራ በማጣቷ አማራጭ ሥራ ሰራች እፁብ እፁብ በማለት የሚታለፍ አይደለም። ይልቁንም በእርሷ ማሳያነት ኢትዮጵያን ጠርንፎ የያዘው የህወሓት የጎጥ መርዝ ነቅሎ መጣል ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ የሚያሳይ አንዱ እና አይነተኛው ማሳያ ነው።ሃያ ዓመት ያልዘለላቸው የጎጡ አባል በመሆናቸው ብቻ እና የሙሰኛ ባለስልጣናት ወገን ሰልሆኑ ቪላ ቤት እና መኪና በሚሰጥበት አገር በብዙ መከራ እና ጥረት የውሃ አስተዳደር በዲግሪ ደረጃ ያጠናችው ወጣት የሥራ ዕድል አጥታ ኢቲቪ በተቆራረጠ ጆንያ በተሰራ ማዕድ ቤት ውስጥ የምትሸጠውን እንጀራ እና ወጥ ስትሰራ ያሳየናል።የወጣቷ ጥረትም ሆነ የንግድ ፈጠራዋ የሚደነቅ ነው።በጎጥ የምትተዳደር አገር ውስጥ ሆና ተምራ እንዳልተማረች አገሯን ለማገልገል ሳትችል መቅረቷ ግን የምንም ውጤት ሳይሆን አገራችን በጎጥ ባርነት ውስጥ በመተብተቧ ሳብያ የመጣ ነው።ይህ ችግር ደግሞ ካለ ነፃነት አይጠራም።የወጣቷ የመድረክ ላይ ለቅሶም ሌላ አይደለም።እነ ሳምሶም እና መሰሎቹ ''የእኔ'' የሚሉት ጎጠኛው ስርዓት አፈና ነው።እንዳትናገር እነ ሳምሶን ቆመዋል።እንዳትተወው ብሶቱ ይገፋል።

ጉዳያችን Gudayachn
www.gudayachn.com 
ጥር 4/2008 ዓም (ጃንዋሪ 14/2016)

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።