ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, November 2, 2015

የአቶ ኃይለማርያም ንግግር ከኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም የመጨረሻ ቀናት ንግግሮች ጋር ይመሳሰላሉ። እግዚአብሔር ወደ ህወሃት የላካቸው ''ነቢያት'' (የጉዳያችን ማስታወሻ)




የአቶ ኃይለማርያም ንግግር ከ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም የመጨረሻ ቀናት ንግግሮች ጋር ይመሳሰላሉ

እንግዲህ ወደ መጨረሻው መጀመርያ ላይ ሲደረስ ንግግሮች እንዲህ ናቸው።አቶ ኃይለ ማርያም ደከማቸው፣ሰለቻቸው እናም በንግግራቸው መንግስታቸው ከእዚህ በላይ ህዝብን የማታለል አቅም እንደሌለው በአደባባይ አመኑ።ማመን ጥሩ ነው። ይህንን ያመኑት ዋልታ ባሰራጨው ስለመልካም አስተዳደር ዝቅጠት በቀረበ የጥናት ፅሁፍ ላይ ነው።በንግግራቸው ወቅት የህወሃት  ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሁሉ ነበሩ።
ከንግግራቸው ውስጥም ''ከእዚህ ስትወጡ'' አሉ እነ በረከት፣ ዶ/ር ደብረፅዮን እና አቶ አባይ ቁጭ ባሉበት ወደ እነርሱ እንዳፈጠጡ ''ለእኔ ሁለተኛ እዚህ አገር ላይ ፈተና የሚሆነው  እዚህ እናወራለን እንጂ ከወጣን በኃላ የተለያየ የእራሳችን ኔት ወርክ እንዳይነካብን እንከላከላለን'' አሉ።

ቀጠሉናም  ''ስንት ጊዜ ስለመልካም አስተዳደር እናውራለን?'' ''ሁላችንስ እስከመቼ ነው የምናወራው?''
የሚል አከሉበት። 
 ንግግራቸውን ዋና ማዕከል ለማግኘት ስትሞክሩ የምታገኙባቸው ነጥብ ግን   የዕለቱን እሳት የማጥፋት አላማ ብቻ ያዘለ መሆኑን ነው።አቶ ኃይለማርያም መንግስታቸው ምን ያህል በሕዝብ እንደተጠላ ስላወቁ ትንሽ እረፍት ብጤ ነስቷቸዋል።በመሆኑም የሆነ ሕዝቡን የምያረግብ እንደ እሳቸው ቀጥታ ቃል አጠቃቀም ''ሕዝቡን ተስፋ የሚሰጥ'' ነገር ቶሎ እንስራ እያሉ ሲማፀኑ ይሰማሉ። ተስፋ ለመስጠት እንጂ ለመፍትሄ አለመሆኑን አስምሩበት።ያሰቡት ቶሎ ተስፋ መስጠት መሆኑን ሲናገሩ ቃል በቃል እንዲህ ነው ያሉት  ''አሁን ቶሎ ሕዝቡን ተስፋ የሚያስጭር ንቅናቄ እና በዘመቻ መልክ መንቀሳቀስ አለብን'' በሚል ነበር።
በመጀመርያ ደረጃ አቶ ኃይለማርያም በእዚህ ንግግራቸው ህወሃት ባለስልጣናት ጋር ይጋጩ ይሆናል እንጂ ለውጥ አያመጡም።በሌላ በኩል ህወሃቶች '' ተወው ይለፍልፍ ምን ያመጣል'' በሚል ንቀው ዝም ካሏቸው ላይጋጩ ይችላሉ።
አቶ ሃይለማርያም እያወቁ እንዳላወቁ ሆነው ያሉበት ጉዳይ  የአገሪቱ ችግር የጥናት እና የእቅድ ጋጋታ እንዲሁም ችግሩ አለ ብሎ የሚደረግ ዲስኩር  ችግር ሳይሆን በመዋቅር የተደረጀ እና በጎጥ የተጠራራ የሙስና ቡድን ነው።አቶ ኃይለማርያም ይህ ቡድን ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ እራሳቸውን ወደ ሲስተም (system) መቀየራቸውን ባይረሱ ጥሩ ነው።ሲስተም ደግሞ የሚስተካከለው ሙሉ በሙሉ ሽባ ሲሆን ነው እንጂ እንደርስዎ አባባል ''እስከ ዓመቱ አጋማሽ ላይ የሆነ ሕዝቡን ተስፋ የሚሰጥ እና ከእኛ ጋር የሚያቆም ሥራ እንስራ'' ብሎ በማወራት አይደለም። ለነገሩ ቢቸግርዎ ነው። ኮሎኔል መንግስቱ መጨረሻ ሰዓት ላይም የእርስዎ አይነት ንግግር አድርገው ነበር።ኮ/ል መንግስቱ እንዲህ ብለው ነበር ''ወደዳችሁም ጠላችሁም ይህ ሕዝብ ያውቀናል።የምትበሉትን የምትጠጡትን ያውቃል'' ብለው ነበር። ሕዝብ ግን ይህንን የሚያውቀው ከአስራ ሰባት ዓመት በፊት ነበር። ዛሬም አቶ ኃይለማርያም ሕዝብ ለ24 ዓመት የተሸከመውን መከራ ደግመው ይነግሩታል።መፍትሄ ያሉት ደግሞ ለጊዜው ህዝብን በተስፋ የሚያቆይ ''ፓናዶል'' እንጂ የዘለቄታውን መፍትሄ ግን አልደፈሩትም።

እግዚአብሔር ወደ ህወሃት የላካቸው ''ነቢያት''

ለኢህአዴግ/ህወሃት  ግን እግዚአብሔር ስንት ''ነቢያት'' እየላከ ነገራት? 
በመጀመርያ ጋዜጠኞችን ልኮ ነገራት አልሰማ አለች። 
ቅንጅትን ልኮ በክርክሩ ችግሩን ነገራት አልሰማ አለችው።
ቀጥሎ ፈረንጅ ብትሰማ ብሎ አናጎሜዝን ከአውሮፓ ድረስ ላከ አልሰማ አለችው።
ቀጥሎ በእየቀኑ ልንገራት ይሆን? ብሎ ኢሳት ራድዮ እና ቴሌቭዥንን በእየቀኑ ጧት እና ማታ ላከ ።ህወሃት አሁንም አልሰማ አለች።
በመቀጠል 9 ሰዎችን መረጠና  ዞን 9 ብለው ''እባክሽ ሌላውን ነገር ሁሉ ተይውና ያወጣሽውን ህገ መንግስት ብቻ አክብሪ'' እያሉ እንዲመክሩ አደረገ። ሕወሓት 9ኙንም ጠራርጋ አሰረች እና 40 ሚልዮን ብር አውጥታ በዓል መደገስ ጀመረች፣ደነሰች፣አርቲስቶችን ይዛ መንሸራሸር ጀመረች።
እግዚአብሔር እስኪ ህወሃት በምድር ላይ የምትፈራውን ሰው ልላከው አለና  ኦባማን  ከዋይት ሃውስ አስነስቶ ላከ እና አፍሪካ ህብረት አዳራሽ ላይ ጮክ ብለው ''አምባገነን መሪዎች ሆይ! ውዮላችሁ!'' እያሉ እንዲናገሩ በንግግራቸውም መካከል ወደ አቶ ኃይለማርያም እንዲመልከቱ፣ንግግራቸውን እንደጨረሱ ግን ወደ አየር ማረፍያ እንዲሄዱ እና የጫማቸውን አቧራ አራግፈው ምድሪቱን ለቀው እንዲሄዱ አዘዘ። ህወሃት ግን አልሰማችም ይልቁንም ኦባማ የመጡት ጥሩ በመስራታችን ነው እያለች ተኩራራች።

በመጨረሻም እግዚአብሔር አለ ይህንን ሁሉ ህወሃት ስላልሰማች አለና   በመሪነት ያስቀመጡት እንዲናገር አንደበቱን እየቆለመምኩ የመጨረሻውን  መጀመርያ ላድርግ ብሎ አቶ ኃይለማርያም በአልጀዚራ እና በኢቲቪ የካዱትን እውነት እንዲናገሩ አደረገ።እናም አቶ ኃይለማርያም ከየት እንዳመጡት ባልታወቀ መንገድ ሙሉ በሙሉ ቀና ብለው የማያዩአቸውን አቶ አባይ እና ሌሎችንም እየገላመጡ ተናገሩ።
ነገሩ አብቅቷል።''ሁልሽም እዚህ ታወርያለሽ እንጂ ስትወጪ ኔት ወርክሽን ልትከላከይ ነው የምትሮጭው በጎሳ ነው የምታስቢው'' አሉ። አቶ ኃይለማርያምን ግን የሰማቸው  አልነበረም።ይልቁንም ህወሃቶች  ሲወጡ ሰብሰብ ብለው ቁሙ እና ''ይሄ ሰውዬ (አቶ ኃይለማርያምን) ጠግቧል ባለፈው ግምገማ ላይ አንድ ነገር ማድረግ ነበረብን ዘፈነብን እኮ''  እያሉ እየዛቱ ወጡ።

በመጨረሻ እግዚአብሔር ይህንን ሁሉ ልኬ ያልሰማች ህወሃት ''ነጋሪት ቢጎሰምባትም አትሰማም'' አለና አጠገቡ ወዳለው መልአክ ዘወር ብሎ እንዲህ አለው ''በል ወደ መሬት ውረድ ወደ የምወዳት ምድር ኢትዮጵያም ምድር ግባ በምድሪቱም ላይ  ተመላለስ።  ዝም ያለውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ልብ ለአገሩ ቆርጦ እንዲነሳ የአገር ፍቅር ፍም በእያንዳንዱ ሰው ላይ አንድድ'' አለው መልአኩም ለእግዚአብሄር  ሰገደ እና ፈጥኖ ወደ ኢትዮጵያ ምድር ወረደ።


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
ጥቅምት 22/2008 ዓም  (November 2/2015)

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...